“ህዝቡን በምን #ልካሰው?" (ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ) ከልበወት ነውን? ከእግሩ ሥር ወድቀው #ተጸጽተው ይቅርታ መጠየቅ። ትልልፋን ማቆም። ማጽናናትን መድፈር። ማድመጥ። ማክበር።
“ህዝቡን በምን #ልካሰው?" (ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ) ከልበወት ነውን?
ከእግሩ ሥር ወድቀው #ተጸጽተው ይቅርታ መጠየቅ። ትልልፋን ማቆም። ማጽናናትን መድፈር። ማድመጥ። ማክበር።
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።
#ምዕራፍ ፲፱።
“ይሄንን ሕዝብ ማገልገል መታደል ነው” ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)
«የኢትዮጵያ ህዝብ #አስደናቂም #ታምረኛም ህዝብ ነው። ከፈጣሪ በስተቀር ህዝባችነን አሟልቶ ሊገመግም የሚችል ማን ነው? የዳበረ ባህል አገር #ወዳድና የወል መሻቱን መጠበቅ የሚችል ህዝብ መሆኑን በዘንድሮው ምርጫ ዳግም ለአለም አሳይቷል።» (ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ። )
“ህዝቡን በምን #ልካሰው?፤ ያሳስበኛል” ዐቢይ አህመድ |“የተጠመዱትና የተለቀሙት ቦምቦች” ምርጫ 2018 | PM Abiy Ahmed, Election 2018,
"የኢትዮጵያ ህዝብ አሰደናቂ ታምረኛ ህዝብ አሉት።" ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ። የኢትዮጵያን ህዝብ #ተክለ ሰብዕና #ዛሬ ነው ያወቁትን እስቲ በአክብሮት እና በትህትና ልጠይቀወት? እስኪ መጋቢት 24/2010 ዓ.ም ያደረጉት የረሱትን ንግግር ደግመው ያዳምጡት። ንግግሩ እና እርስወ ምን ላይ እንደምትገኙ ያረዳወታል።
ወር እኮ አልሞላውም " ጯሂ፤ ቁራ፤ ቁራ ቆሻሻ ይወዳል፤ ለማኝ ነን፤ ለማኝ ጥገኛ ነው። ጥገኛ ሉዓላዊነት የለውም" ያሉት። ኢትዮጵያኒዝምን ህዝበወት አልቆ ሲዘምር፤ በዛ ውስጥም ሲመሰጥ ነበር ይህን ህግ መተላለፍ ደፍረው የተናገሩት። በጣም እኮ ነው የኢትዮጵያን ህዝብ የሚዳፈሩት። ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚ/ር ሳሉ ምነው ይህን አገላለጽ ተጠቅመውት በነበር። መስፈርታችን ሌላ ይሆን ነበር።
እርስወን ተከትለው ደግሞ የቅርበወትም በድፍረት የተናገሩት ጸያፍ ቃል፤ ነውረኛ ንግግር አድርገዋል። "ባለቤቱ የናቀውን አሞሌ ባለ ዕዳ አይቀበለውም እንዲሉ። " እርስወ ያላከበሩትን ህዝብ የበታችወት እንደምን ክብር ይስጡ? የኢትዮጵያ ህዝብ ያልቻለው እኮ የለም። ተቃዋሚው ይቀጠቅጠዋል፤ እርሰውም እንዳሻወት ይናገሩታል። ለዚህ ነው እኔ እባከወን ንግግርወት ይፃፍ ያልኩት።
የህዝብ ቁጣ ሲኖር እርስወን ህዝበወት እንደቻለወ ሁሉ እርስወም መሸከም መቻል ያስፈልገወታል። የህዝብን ብሶት፤ ቁጣ የውስጥ ስሜቴን መሸከም መቻል የመሪነት ግዴታ ነው። እንደመሪ ምርጫ ካርድ ይዞ ለመምረጥ የተሰለፈውን ህዝብ አለባበስ፤ አኗኗር፤ የመኖር ተስፋው ገጹን ይዩት እስኪ። #የከፋው የጠነዘለ ህዝብ ነው ያለው። "ሆድ ለባሰው ማጭድ አታውሰው የሚባለውም" ለዚህ ነው። በስንቱ ይንገላታ ይህ ቅን፤ ገራገር፤ ደግ፤ ህግ አክባሪ ቻይ ህዝብ። ስንቱ ይውገረው???
በአገሩ፤ በባዕቱ በገፍ መፈናቀሉ፤ በሃይማኖቱ መሳደዱ፤ በኑሮው መጎሳቆሉ፤ በምድርም በሰማይም መዓትን ማስተናገዱ አልበቃ ብሎ ደግሞ መወረፍ፤ ማቃለል፤ ማጣጣል ለማንም አይበጅም። ለማንም አይጠቅምም።
የኢትዮጵያ ህዝብ #ብልህ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ጎርፍ፤ ወጀብ፤ አውሎ ሁሉንም አይቶታል። ኑሮበታል። ከከተሞች ወጣ ሲባል ያው የጥንቱ የጥዋቱ የጭቃ ምርጊቱ ቤት ውስጥ ነው የሚኖረው። ይህንንም እኮ ነው የተነጠቀው።
የኢትዮጵያ ህዝብ ሞቱ፤ ስቃዩ፤ መራቡ፤ መጠማቱ፤ መታሰሩ፤ መንገላታቱ፤ መፈናቀሉ፤ አካሉን ማጣቱ ሁሉንም ቻለ። ሞገድ ላይ ያለውን እርስወም ያዳምጣሉ እኔም አዳምጣለሁኝ። "የኬኒያ ህዝብ ናፈቀን" የሚል ጉልህ ድምጽ አለ። ለምን የኬኒያ ህዝብ የሳንቲም ጭማሪ ከመጣ፤ በግፍ ግድያ ከተከሰተ የሚቀበል ህዝብ አይደለም።
የኢትዮጵያ ህዝብ በመንግሥት አደረጃጀት ውስጥ የዳበረ ልምዱ፤ ቅኝ አለመገዛቱ የህሊናውን አቅም፤ የገዘፋ ፈተናወችን ሆነ፤ በደራሽ ስሜታዊ ጉዳዮች ላይ ሰክኖ በማስተዋል እንዲጓዝ አድርጎታል። ይህ ህዝብ #ከአልማዝም፤ ከዕንቁም የከበረ ሰብዕና ያለው ህዝብ ነው። በቃላችሁ የማትገኙት እናንተ ብቻ ናችሁ ሊቃናቱ። ይህ አደብ ግን ሁልጊዜ አይቀጥልም። ሲከር ይበጠሳል፤ ሲሞላም ይፈሳል። የኢትዮጵያን ህዝብ የመቻልን አቅሙን በቅጡ ማስተዳደር ይጠይቃል።
"#በምን ልካሰው" ጥሩ ጥያቄ ነው።
ሰላሙን በመስጠት። በችግሮቹ ላይ ፈጥኖ በመድረስ መፍትሄ መስጠት። ከላይ ተሁኖ ሳይሆን በትህትና ዝቅ ብሎም ቁንጥጫውን በመፍቀድ። ጥቁር ሲለብስ አብሮ ጥቁር በመልበስ። በችግሩ ጊዜ በቅርቡ ተገኝቶ - በማጽናናት። #አይዞህ በማለት። ከኮንስትራክሽን በላይ #ሰውነቱን በማክበር።
ተጸጽቶ ምህረት በመጠየቅ። በፖለቲካ የታሠሩትን ልጆቹን ከካቴና በማላቀቅ። የተፈናቀሉትን እቦታው ተገኝቶ በማገዝ። ዘመናዊ መንደር ሰርቶ በመካስ። የፈረሱ ትምህርት ቤቶቹን በመስራት። #መስቀልን ባለማሳደድ፤ ጦርነቱን በቅንነት ተነሳስቶ በመስማማት - በማስቆም፤ የመኖር ዋስትናውን በማረጋገጥ፤ ዝንጥ ካለው ቄንጠኛ ፍላጎት ወጣ ብሎ የሚቀድመውን የዕለት ጉርስ በማደራጀት።
የመናገር፤ የመፃፍ፤ የመደራጀት፤ የመሰብሰብ ነፃነቱን #ባለማገት፤ ኢትዮጵያ የፖለቲከኛ እስረኛ እንዳይኖርባት በማድረግ። ወንጀለኛን፤ በደለኛን በህግ አግባብ በመቅጣት፤ የዞግ ፖለቲካን በማስቆም፤ ለኢትዮጵያዊነት #ንጹህ ልብን በመመገብ።
ጥላቻን በመቅበር። አብነት ሆኖ በማሳየት …… ያ ሥልጣን የተረከቡ ጊዜ ያደረጉት ንግግረወት እኮ በቂ ነበር። ፖሊሲም ማኒፌስቶም ለመሆን ይችል ነበር። ሦስት መጸሐፍ ከሚጽፋ። የገቡትን ቃል ዞር ብለው አላዩትም። ለነገሩ የአለም የሰላም አባትነት፤ ሎሬት፤ የኖቤል ተሸላሚነተወት እኮ ትዝ ብሎወት አያውቅም።
ፓርላማ ላይ የሚጠሉት ሰብዕና ሲኖር ፊትወት እንዴት እንደሚከፋወት። ቢፈልጉ እኔ እለጥፍለወታለሁኝ። ግን የውነት አማራን እንዴት ያዩታል - ከቀን አንድ ጀምሮ በምን ደረጃ ይገኝ ይሆን? ። ውስጠወት ይህን ህዝብ ይቀበለዋልን? እባክወት ውስጠወትን ያሸንፋት።
እስቲ ጥሞና ይውሰዱ። ትዕዛዝ አሻቅቤ አይሆንም ዕይታዬን ነው እማጋራው። እስቲ ለጥቂት ጊዜ የሚያምኑትን ዩንቨርስ ይሁን ኢነርጂ፤ አላህ ይሁን አማኑኤል፤ ፒኮክ ይሁን ንስር ብቻ በዕምነትወት በሚያምኑት ሁነት ይነጋገሩ። የጠፋው፤ የወደመው፤ ያለቀው፤ የደቀቀው፤ ከሠሩት ከተጉበት ጋር ይመጣጠናልን ወይንስ? ይመዝኑት። በእርስወ የኃላፊነት ደረጃ ተጠያቂ የሚያድርገወትን ጉዳይ ይመርምሩት። ያለወት እና ያጡትን ነገር ይለኩት። #መንሹ ከእጀወት ነው።
በዚህ ምርጫ አማራ ክልል፤ አዲስ አበባ እና ኦሮምያ ነፍሱን አስይዞ ከኢትዮጵያ ህገ - መንግሥት ሥር እንጂ በላይ አይደለሁም ብሎ ነው ለምርጫ የተመዘገበው። ወጥቶም የመረጠው። ቤቱ ቁጭ ማለት ይችል ነበር። ኮረጆ ሲያንቀላፋ ሊውል ይችል ነበር። ለዛውም በራሱ በእናንተው ድርጅት ወከባውንም፤ ግልምጫውንም ችሎ ነው የተሳተፈው።
#መካሻው። እንደ መከወኛ።
የህዝብ በደል መካሻው #ሰው ሆኖ መገኜትን ይጠይቃል። ትህትናን በቅንነት ይጠይቃል። ትዕግሥትን በፍቅር ተፈጥሮ ማስከን ይጠይቃል። አክብሮትን በማጽናናት መግቦትን ይጠይቃል። አይዟችሁ የተራበ ህዝብ ነው የሚመሩት ህዝብ። አለሁልህን ይህን እንኳን የተነፈገ ህዝብ ነው ህዝበወት።
ፈተናን የተጋፈጡ ዜጎች በግል ዩቱብ ሲቀርቡ ህዝቡ እንዴት እንደሚሳሳላቸው አያዳምጡም? በ24 ሰዓት 5000 ሺህ የስልክ ጥሪ ለአንዲት ብላቴና? በየትኛው ዓለም ይህ አለ? የእኛ ተፈጥሮ #ርህርህርህና እንጂ ጭካኔ አይደለም። ፍቅር እንጂ ጥላቻ እና በቀል አይደለም። የሰው ልጅ ለጭካኔ አልተፈጠረም። እኛ ለክፋ ሃሳብ አምራችነትም አልተፈጠርነም።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ቤተ - ቅንነት ኑሩልኝ። አሜን።
ዛሬ ረዘም ላለ ጊዜ አብረን ቆየን። የምርጫ ሂደቱን በጥሞና ነበር ከወትሮው በተለየ አትኩሮት የተከታተልኩት። ምርጫው እስኪያልፍ ስሜትን ገዝቶ በአደብ መጠበቅ ይገባ ነበር። ያን ነበር እኔ ያደረኩት።
ኑሩልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ.
SerguteSelassie.
06/06/026.
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ