"እንዳያማም ጥራው፤ እንዳይበላም ግፋው።" ለሰብ ትርታ #መደንገጣችሁን እስከ ምን ይጠበቅ?
"እንዳያማም ጥራው፤ እንዳይበላም ግፋው።" ለሰብ ትርታ #መደንገጣችሁን እስከ ምን ይጠበቅ?
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።
• ቅኒትን፤ የልቅና ባለቤቷን፤ የዊዝደም ጉልላቷን ቅድስት ኦርቶዶክስ
ተዋህዶ ደረጃዋ ይህ ነውን?
በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተሰጠ መግለጫ
#ምዕራፍ ፲፱።
ከኢትዮጵያ መንግሥት የተሰጠውን መግለጫ አዳመጥኩት። አገርን - በቅንነቷ፤ በዊዝደሟ - ልዕልና፤ በመንፈስ #ንጽህናዋ ልክ መሠረት ያስያዘች ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ #ዕንባ በምን መልኩ እንደሚታይ ሙሉ ፰ ዓመት አይቻለሁ። አድምጫለሁኝ። ለእኔ ምንም አዲስ ነገር የለውም። ምን አልባት "እንዳያማም ጥራው …"የመግለጫው ዓይነት ይሆናል አዲሱ።
በሌላ በኩል ብሄራዊት፤ ዓለም ዓቀፋዊት የሆነችው ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶም ሊቃናት፤ ሊሂቃን፤ የተደራጄ መዋቅር፤ ቀኖና እና ዶግማ ያላት ተቋማዊ ሃይማኖት ናት።
የቅድስቷ #ነቁጧ ብቻ የሚስጢር ዲካዋ ሊሠፈርም ሊለካም አይችልም። ፈተናዋም የዚያኑ ያህል ዲካ የለሽ ነው። እራሷን የቻለች፤ ሁሉ ያላት፤ የምትችል ሆና ግን የዝምታዋ #መንገሥ ልጆቿ የየለት ሰማዕትነት፤ የተቋማቷ ስደት፤ የሁለመናዋ ተከላካይ አልባ መደፈር በበዛ ትዕግሥት መያዟ ፈተናዋ መቋጫ አጣ። የእኛ የታናናሾቿ ዝምታም ልኳ፤ ልዕልናዋ፤ አቅሟ፤ ልቅናዋ የማይደረስበት በመሆኑ በደል ሲጠናባት ዕንባችን አፍስሰን ተማጥኗችን ለላይኛው እንልካለን።
አጽናኟ፤ አይዞሽ ባዮዋ ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ፤ እንዲህ ለራሷ መሆን ሲሳናት ማዬት እጅግ ያሳዝናል። በማናቸውም ብሄራዊ ጉዳይ ልጆቿ ትጉኃን ናቸው። ልጆቿ ግን ብሄራዊ ግዴታ ብቻ እንጂ መብታቸው #በየለም ደረጃ ነው ያለው።
ለዚህም ነው ማህበረ ምዕመኑ እና አገልጋዮቿ በአገራቸው፤ በባዕታቸው አንገታቸውን ደፍተው በባይታዋርነት እንዲኖሩ የተገደዱት። ወደፊት በዚህ አያያዝ መስቀል ከአንገት አስሮ መንቀሳቀስ ሊታገድ ይችል ይሆናል። ማህበረ ምዕመኑ #ያልፋን በፆም፤ በጸሎት፤ በሰጊድ፤ በአርምሞ፤ በጥሞና፤ በምህላ፤ በሱባኤ ቢማጸኑትም #ርትህ ራቃቸው። ነገረ አርሲ እኔ ኑሬበታለሁኝ። እንዲህ ዓይነት መገፋት አይቼ አርሲ ምድር ላይ አላውቅም። አላዬሁምም
#ጭካኔው ምንጩ ፖለቲካዊ ነው። ስለሆነም ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት እና ጥንካሬን በእጅጉ ይፈልጋል። ለዚህ ደግሞ እናታችን ቅድስት ተዋህዶ በአቅሟ ልክ ስለመብቷ ከገዢው መንግሥት ጋር ውል የተደነገገ ያላት አይመስለኝም። " ውል ያዋውላል ታንኳ ያሻግራል" የሻሸመኔው ሰቆቃ እኮ ብዙ ሊያስተምር የሚገባ ክስተት ነበር። ስለዚህም ነው ዕንባው መቆሚያ ያጣው። ሰማዕትነቱ የቀጠለው። በአገር ውስጥ ፍልሰቱም #አና ያለው።
የኢትዮጵያ መንግስት በተከታታይ በአርሲ ዞን አደጋ እንዳለ ያውቃል። የሰሞናቱ ፈቃዱ የአማኑኤል ሆነ እና #ጎላ ጎልበት ሆኖ ወጣ እንጂማ የሰው ቄራው እኮ በየለቱ ነው። ህዝቡ መድረሻ አጥቷል። የኢትዮጵያ መንግሥት የዜጎቹ ሞት፤ መፈናቀል፤ ማንባት፤ ከባዕታቸው መነቀል፤ እንደ የሚታረድ በግ ሰርክ መሰዋት #አያስደነግጠውም። መደንገጥ - አልፈጠረለትም።
ስለማይደነግጥ ዜጎቹን እንደ ሌላ አገር ስለሚይ ይመስለኛል የሰውን ልጅ መራራ ስንብትን ያህል መከራ አትኩሮት አይሰጥም። ኢትዮጵያ ከቅድስት ኦርቶዶክስ ትውፊት እየራቀች እንድትሄድ፤ እርቃኗን እንድትቆም፤ ከዊዝደም እንድትራቆት የተፈለገበት መስመር መርግ የሆነ ጉድ ነው።
"ጠቅላይ ሚሩ ዝምታቸውን ሰበሩ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት መግለጫ ሰጠ" ሲባል ታምር እንደ ሠራ ይቆጠርለታል። ይገርማል። እሳቸው ደፍረውም አይናገሩት። የእግረ መንገድ ጉዳይ ነው። የፓርክ ምርቃት ይበልጣል ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ተቋምነት። "ኦርቶዶክስ አገር ናት ካለ አንደበት" እንዲህም፤ እንዲያም ……
የመንግሥት ኃላፊነት እኮ የመጀመሪያው የዜጎቹን #ሰላም ማስጠበቅ ነው። ለዜጎቹ የመኖር መጉላላትም ፈጥኖ ደርሶ #ማጽናናት ነው። ይህቺ ትንሹ ኃላፊነቱ ነበር። በብልጽግና ፓርቲ የሚመራው መንግሥት ግን ማጽናናት የማያስበው ብቻ ሳይሆን፤ ጨርሶ ቃሉ እራሱ እንዲደርስበት የማይፈቅደው፤ የሚፈራውም ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥት በጣም ዘግይቶ ባወጣው መግለጫ ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እንዴት እንደሚያት አስተውሉት ብሎና። አስተውሉት ያለው ለእኛው ነው። በዛ ሐተታ ውስጥ #ሙጣጭ እንጥፍጣፊ የብዕር ጠብታ እና እራፊ ቦታ ተስጥቷል። ይህ የገዘፈ እጅግ ሰቅጣጭ የክፋ ሃሳብ ድርጊት።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ጉዳይ ኢትዮጵያን እንደ አገር አጽንቶ የማቆየት ጉዳይ #ህሊናዊ ነው። ተማላ ጉዳይ አይደለም። የኢትዮጵያ "ህቅታ" ያለው ከዚህች ቅድስት ሃይማኖት ላይ ነው።
ቅድስቷ ከአብይዝም መንግሥታዊ ካቢኔው ላይ ሙሉ ፰ ዓመት #ልሙጥ ነው። በቀጣዩም ያው ነው። የየክልሉን እጩወች አየሁት፤ መረመርኩት። የጎረቤት አገር ያህል እንኳን ቦታ ለአናቷ ሃይማኖት አልተሰጠም። የዚህ ሂደት መጨረሻው አያምርም። #እርግማንም ያመጣል። እርግማኑ ደግሞ የማይቻል ይሆናል።
ግብግቡ ከቀደምት፤ ሁሉ ካላት ባለ ቅዱስ መንፈስ #ስጦተኛ ከሆነችው ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ጋር ነው።
ጠቃሚ አይደለም። ኢትዮጵያ እንድትቀጥል ከተፈለገ የሴራ ፖለቲካውን አቁሞ በክብሯ ልክ ልጆቿን መጠበቅ፤ ተቋማቷን አለመዳፈር ይጠይቃል። በስተቀር ሁሉም ነገር የእንቧይ ካብ ይሆናል።
በሌላ በኩል አንድ መግለጫ ሪፖርት አይደለም። የመግለጫ ባህሪው አንድን ክስተት ጭብጡን አብራርቶ የተደረሰበትን የውሳኔ ሃሳብ በቀላል እና ግልጽ ቋንቋ መግለጽ ነው።
ያዳመጥኩት መግለጫ ነው ቢባልም ሪፖርት ነው። ጭብጡም በተከሰተው የሃዘን ድባብ እግዚአብሄር #ያጽናን የፈራ፤ ለተጎዱት ካሳ እና የመልሶ ማቋቋም ጉዳይ ያላነሳ፤ የሃዘን ዳርቻ ለማድረግ የመንግሥት ወጣ ገብ፤ ነቀል ተከል ያልሆነ ወዝዋዛ ውሳኔ ሳይሆን በጠራ አቋም የነጠረ ውሳኔ ይጠይቅ ነበር። ፈጣን የሆነ፤ ቋሚ እና ተከታታይ እርምጃም ያስፈልጋል። ዛሬ በአገርም፤ በአፍሪካ ቀንድም፤ በዓለም ፖለቲካዊ ሁነት ዳጥ እንዳይገጥም በሁሉም ዘርፍ ብልህነትን የሰነቀ ትሁታዊ የህዝብ አያያዝን ይጠይቃል።
"እንዳያማም ጥራው፤ እንዳይበላም ግፋው" ፈጽሞ አይጠቅምም። ከውስጥ የሆነ፤ ፌክ ያልሆነ ጥርት ያለ ተግባር የሚጠይቅ ክስተት ነው። እግዚአብሄርን ታግሎ ያሸነፈ እንደሌለው ሁሉ ቅድስት ተዋህዶን ማሸነፍ ቀርቶ #መነቅነቅ አለመቻሉን ዘመቻ ታውጆ ስኬቱ ተለክቷል።
ከሁሉ አምላክ አለ የሚባል ከሆነ እሱን ፍሩ። ቁጣው የመጣ ዕለት የቅጣቱ ቡፌ በያይነቱ ይሆናል እና። አገር #እንዳታሳጡን በአትኩሮት እና በጥሞና እሰቡበት። ቅድስት ኦርቶዶክስን ጥንታዊነት፤ ብቃት እና ልቅናዋን #ማሳደዳችሁም ይብቃ! #ልሙጥ ኢትዮጵያን አትሰቧት።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ማህበረ ቅንነት ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
06/06/026.
"እግዚአብሄር በአንድም በሌላም
ይናገራል፤ ሰው ግን አያስተውለውም።"
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ