"ጽድቁስ ቀርቶ በወጉ በኮነነኝ።" ተናፋቂው ባህርዳር በብልጽግና ምን አገኜ???

 

"ጽድቁስ ቀርቶ በወጉ በኮነነኝ።" ተናፋቂው ባህርዳር በብልጽግና ምን አገኜ???
 
"ባሕር ዳር ከተማ ዐይን ገላጭ ፕሮጀክቶች የተሠሩላት በብልጽግና ፓርቲ ነው" ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ" መሃከነ፤ እግዚዖ ተሳህለነ። አሜን።
 
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።
 
ምዕራፍ ፲፱።
 
 
 
"ባሕር ዳር ከተማ ዐይን ገላጭ ፕሮጀክቶች የተሠሩላት በብልጽግና ፓርቲ ነው" ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ"
 
እንዴት ነን? ጭምት ናቸው ሲባል እሰማለሁኝ። የዛሬን አያድርገውና መስኪ ይህን ጽፋው ነበር የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት ሳሉ። ዛሬ ዘለግ ያለ ሙግት "ብልጽግናን መምረጥ ነገን መምረጥ ነው" ሲሉም ሙግት ቢጤ ነበረኝ ከምክትል ጠቅላይ ሚሩ አቶ ተመስገን ጥሩነህ ጋራ። ተጥፏልም። 
 
የዘገየሁት ለምርጫው ሳንክ መሆን ባለመፈለጌ ነው። አስክኖ እና አስተውሎ ማየት የብትን አፈር ለማኝነትን ይታደጋል። የዘመኑ የዓለም ዓቀፍ የፖለቲካ ባህሪንም በቅጡ ማድመጥ ይገባል። አገር ሊኖር ይገባል ለማሄስ፤ ለመሞገት። 
 
ለእኔ ቁጥር ፩ የኢትዮጵያ መኖር እንደ አንድ አፍሪካዊት አገር ወሳኝ ጉዳይ ነው። ለዚህም ነው ሰላማዊ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶችን በምርጫ ተሳትፎ ያደርጉ ዘንድ በትህትና ያሳሰብኩት። ኢትዮጵያ እንደ አገር አናርኪያዊ ሁነት ገጥሟት ስለማያውቅ ላታውቀው ትችል ይሆናል። 
 
#አናርኪዝም ከፋመ ጦርነት የባሳ አሰቃቂ ክስተት ነው። ለአገሬ ለኢትዮጵያ ከዚህ ፈጣሪዬ እንዲሰውራት ምኞቴ ነው። የመጸለይ አቅሜ አናሳ ቢሆንም - ሁልጊዜ አገሬን ኢትዮጵያን አስባታለሁኝ። 
 
እርግጥ ነው በዚህ በአብይዝም ዘመን አናርኪያዊ ድርጊት የለም፤ አልገጠመም ልል አልችልም። ቡዙ አሰቃቂ የተናጠል የአናርኪዝም ትዕይንቶች ታይተዋል። መንግሥት አልባ ሲኮን ግን ከዚህ የገዘፈ #ኮምዳዳ ኮምጣጤ ዕጣ ፈንታ ህዝባችን ሊያስተናግድ ይገደዳል። በጣም የምፈራው ገጠመኝም ይህ ነው።
 
#አጤ ባህርዳር ይሁን የአማራ ክልል በብልፄ ዘመን ምን አሳካ?
 
ምክትል ጠቅላይ ሚር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በባህርዳር ከተማ ቅልጥ ያለ የህዝብ ድጋፍ ሰልፍ ላይ ንግግር አድርገዋል። ባህርዳር በዘመነ ብልጽግና የተሻለ ዕድል እንዳገኜም ተናግረዋል። ከእንግዲህ "ታዛዣችሁ እንሆናለን" ባሉት በቀድሞው ም/ጠቅላይ ሚር ደመቀ መድረክ ላይ ተሰይመው ነበር ይህን ኃይለ ቃል የተናገሩት። ቃል ሲፈስም፤ ፍዳ እና መከራ አጭቶ ሞት ማጫ ሲያማታም ያዬንበት ዘመን ነበር ያለፈው የምርጫ ፮ ዘመን። ስለነገም የብልፄው ተሟጋቾች ወጥ በሆነ ሲናሪወ ሪፖርት ከማቅረብ ውጪ ነገን እንዲህ እና እንዲያ እናዘናክተዋለን ሲሉ አላዳመጥኩም።
 
ምክንያቱም ፕላኑ፤ ማኒፌስቶው ያለው በአብይዝም የህሊና ሰሌዳ ብቻ ነው። ጉባኤው የብልፄው ማኒፌስቶ አጸደቅኩ ያለው እኮ የ፮ አገራዊ ምርጫ እና ስኬቱ ሪፖርት ነበር የያዘው። ነገስ ለሚለው በአንድዬ ህሊና ብቻ የተከተበ ነው። በወቅቱ ጽፌበታለሁኝ። 
 
ወሮ አዳነች አበቤ "ጎዳናችን መደመር፤ ግባችን ብልጽግና፤" ሲሉ አድምጬ ኦኦ ብልጥግናው አልተጀመረንም፤ ገና ግቡ ላይ ይሆን አቤቶ ብልጥግና የሚገኜውን? ማኒፌስቶው መሐንዲስ አይደለምን። ሁሉ ብያለሁኝ። ጥንስሱን፤ ትልሙን አያውቁትም። ፍሬ ነገሩ ያለው በአብይዝም ህሊና ብቻ ነው። ምን አልባት እንዳይነፍስበት ታስቦ ይሆናል። መንገዱ ለቲም ወርክ ጋዳ ነው። እንደ ገናም አንድ ነገር ቢፈጠር ይናዳል። አደጋው ሰፊ ነው። ቢያንስ የቅርቦቹ ፍላጎታቸውን፤ ራዕያቸውን ማስተርድ ሊያደርጉት ይገባል። 
 
ጨዋታን ጨዋታ እያነሳው ……… ወደ ቀደመው አቶ ተመስጌን ጥሩነህ ፕሬዚዳንት በነበሩበት ጊዜ ባህርዳር የሥራ ቦታ #መኝታ ክፍል አዲስ አበባ እንደ ነበር ዘገባወች ይጠቁሙ ነበር። የአማራ ክልል በዘመነ ህወሃት ሁለት ጊዜ በአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ሥር ነበር። አሁንም በዘመነ አብይዝም ከፋኖ ንቅናቄ ጀምሮ በአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ሥር ተሁኖ የተሻለ ዕድል አጤ ባህርዳር እንዳገኜ አማርኛውም፥ ቋንቋው አልገባኝ አለ።
 
1) የህዝብን ህይወት የቀየረ ምን????
2) የህዝብን ሰላም ያዘለቀ ምን?
3) የነበረን ጥንካሬ ያስቀጠለ ምን?
4) አዲስ አቅም ምን ተገኜ የኃይል ማመንጫ፤ ኢንደስትሪ?
5) የነፍስወከፍ ገቢ መመጣጠን? ወዘተ ………
6) የትኛው ሜጋ ፕሮጀክት አማራ ክልል ተጀምሮ ተጠናቀቀ ይሆን? እንዲያውም የአማር ክልል ውክል አካላት ከሱማሌ፤ ከኦሮምያ፤ ከደቡብ ክልል ውክል አካላት ጋር እኩል ደፍረው ሲቀመጡ በእጅጉ እገረማለሁኝ።
 
ራስ ጋይንት የነበሩ የብልጽግና ሊቃናት ምጥጥ ብለው አልቀዋል። ከዛ በፊትም ቲም ዶር አንባቸው ሰማዕትነት ተቀበለዋል። እንኳንስ አዲስ ዓራት ዓይናማ ተደማጭ ሊቅ ሊፈጠር ቀርቶ?
 
በሌላ በኩል የራስ ጋይንት የብልጽግና ሊቃናት መሰዋት ያበሳጨው ሠራዊቱ ደግሞ አጸፋውን መልሷል። በሁለቱም ዘርፍ የአማራ ሊቃናትም ህዝቡም ማቅ ለብሷል። ከ፭ ሚሊዮን በላይ ታዳጊ ወጣቶች ከትምህርት ገበታ የተስተጓጓለበት ክልል በብልጽገናል? 
 
ከአማራ ክልል ወደ ፌድራሉ ሄደው ቁልፍ ቦታ በተሰጣቸውም ይሁን በክልሉ ያሉ የአማራ ሊቃናት "ትርፋችን ተስፋችን" ብልጽግና የሚሉት ድፍረቱ ይገርመኛል። ጥበቃ በሠራዊት ኃይል ነው። ላንቁሶነት ነው ያለው። ለተወሰነች ደቂቃ ሠራዊቱ ሲለቅ ጭንቅ ነው። ሞት ነው። እራስን ችሎ እንደ ሱማሌ ክልል መቆም አልተቻልም። ሁልጊዜ ስጋት ነው።
 
እንኳንስ አቅም ያለው ተተኪ ለመፍጠር በዘመነ ህወሃት የተፈጠሩ ሊቃናትን ህይወት የመጠበቅ አቅም እንኳን የለም። የህፃናት መታገት፤ መደፈር፤ ቀጥሎም መገደል በየትኛውም ዘመን ያልታዬ #ገመና ነው። የአማራ ባህልም አይደለም። ይህ አንገት ሊያስደፋ እንጂ ነጭ አስለብሶ በድፍረት የሚያናግር አልነበረም። የባጄ መከራ እኮ በቃል መግለጽ አይቻልም። ማርቆስ፤ ዳንግላ፤ ፍኖተ ሰላም እኮ የሰላም ገነት ነው የነበሩት። ኮሽታ አልነበረም። 
 
የሆነ ሆኖ ጥቁርም ባይሆን ድብ ያለ ግራጫማ ነገር መልበስ የአባት አደሩ ይትብኃል ነበር። ሐዘን ላይ የተቀመጠ ህዝብ ነው ያላችሁ። አብሮ ማዘኑ፤ አይዟችሁ ማለቱ፤ ማጽናናቱ ቢቀር #የተቀናጣ ቄንጠኛ ንግግር ግን አስፈላጊ አልነበረም።
 
#እኛ ሞጋቾች ግድፈት አለብን። 
 
መከራ ከሆነ ለህወሃት፤ መልካም ነገር ከሆነ ለኢህዴግ እንሰጣለን። ይህ የተገባ አይመስለኝም። በደርግ ጊዜም ባህርዳርን አውቀዋለሁኝ። በዘመነ ህወሃት ሄጄ ባላየውም ዝንጥ ያለ ሙሽራ ከተማ ነበር።
 
ሆቴል ባህርዳር ችግር አልነበረበትም። የገዘፋ ሆቴሎች ነበሩ። በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የሚመረጡም። እንዲያውም ባህርዳር የጨርቅጨርቅ ፋፍሪካ ነበረው። ህዝቡ ሥልጡን ነው፤ በሳይክል የመጠቀም ባህሉ አንቱ ነው። በኮርስ አገኛቸው የነበሩ የባህርዳር ልጆችም ልቅናቸው፤ ዲስፕሊናቸው ይመስጣሉ - ትናንት።
 
በሠራዊት ኃይል ያለ ክልል ይህን ያክል የሚያስፎክር ተግባር ፈጸምኩ ሊል ፈጽሞ አይችልም። ጦርነቱ ምን ያህል ጥንታዊነትን፤ ትውፊታዊነት ፈትኖ ክልሉን እንደ ጎዳው ይታወቃል። የተቀነሰ እንጂ ማካካሻ የሚሆን የተጨመረ ነገር አላየሁም። የታደሱ ነገሮች አሉ ፋሲል ግንብ፤ አባይ ድልድይ፤ የከተማ ኮሪደር ወዘተ ……።
 
 የተጀመሩ፤ የተጠናቀቁ ትውልዳዊ #ፕሮጆክቶች ምን??? እኮ ምን?
 
ስማዳ በራስ ጋይንት አውራጃ ካሉ ሦስት ወረዳወች ውስጥ አንዱ ነው። ስይቴ ጤፍ አምራች ነው። በደርግ ዘመን ይሁን፤ በህወሃት ዘመን የኢትዮጵያ ሠራዊት ትውር ብሎ አያውቅበትም። አሁን የኢትዮጵያ ሠራዊት ከዛ እንዳለ ሰማሁኝ። አንድ ማዘን እንዳይመስላችሁ የተሰማኝ ንብርብር ሃዘን እንጂ። እዛ ለሥራ ስሄድ ሆቴሌን ቆልፌው አላውቅም። ዛሬ ይቻላልን? እእ።
 
ከቆላድባ ማክሰኝት፤ ከማክሰኝት ጎርጎራ፤ ከጎርጎራ ደልጊ አይታሰብም። ተሰብሳቢወች ሲናገሩ ነው የሰማሁት። ጯሂት እኮ ሚጢጢ የገጠር መንገድ ላይ ያለች የቅቤ ከተማ ናት። የጎንደር ሰው የዓመት የቅቤ ስንቁን ሄዶ የሚገዛው ከዛ ነበር። ያቺ ሚጢጢ ከተማ ሰላም የላትም? ኃላፊነት እኮ የሚጀምረው ከትንሹ ዝቅ ካለው ነው።
 
አቶ ተመስገን ጥሩነህ የደህንነትም ሰው ስለሆኑ ይህ ተመክሯቸው ሊረዳ የቻለበት ስኬት ፈለግሁኝ። ግን አላገኜሁም። ደህንነት ሙያው መቅደምን እንጂ መቀደምን አያመሳጥርምና። ከቤታቸው፤ ከባዕታቸው ያለው የሰላም እጦት የገዘፈ ነው። በጣም ብዙ ጊዜ ማንኩሳ ተመላልሻለሁኝ። የማንኩሳ ፍራፍሬም የትም ምድር የማያብቅለው ነው። ጣዕሙም ጠረኑም ልዩ ነው።
 
ግን፤ አሁን ብድግ ብሎ ወደ ውዱ #ማንኩሳ መሄድ ይቻላልን? በነገራችን ላይ ያን የመሰለ የፍቅር እስከ መቃብር ነፍስ ያለው ተውኔት እሱን የእኔ ብሎ ለማስቀጠል እንኳን አልተቻለም። ፍቅር እስከ መቃብርን እኔ ፲፭ ጊዜ አንብቤዋለሁኝ። 
 
ያ ደረጃውን የጠበቀ፤ ብዙ የተለፋበት የዘመናችን ክስተትን የገጠመውን እንቅፋት አሸንፎ የዕውቀቱ ልክ ለአደባባይ ይበቃ ዘንድ አለማስቻል ከምን ይመደባል? እራሱን የሚታገል - ክልል? ከተሰጠው የዕውቀት ጸጋ ጋር ፍልሚያ ላይ ያለ - ክልል። የሌለው አዲስ ትርክት ፈጣራ ላይ ይጣደፋል፤ ያለው ደግሞ እራሱን ፈቅዶ ያፈሳል???? 
 
#ትርፍ የሚባል ነገር ምን ይሆን??? 
 
አማራ ክልል የአማራ ልጆችን ጥያቄ ዕውቅና ሰጥቶ፤ ፌድራሉ እንዲመልሰው ማድረግ ሲገባው ጥያቄወችን እያፈራረሰ፤ እያስፈራራ አልፈስፍሶት ቀረ። ክልሉ ጥቃትን በእሽታ እዬተቀበለ በአጤውም፤ በደርግም፤ በህወሃት ዘመንም የተፈጠሩ ፕሮጀክቶች ሁሉ አመድ ነው የሆኑት። ህዝቡ ጥቁር ለባሽ ነው የሆነው።
 
ይህም ሆኖ የአማራ ህዝብ እንደ ህዝብ የመንግሥት ሥርዓትን አደረጃጀት፤ አመራር የሚያውቅ፤ የሚቀበል ክህሎታዊ ብቃት ስላለው ስ ሁሉን ታግሶ፤ ያውም እየተሰዋ መቅደም የሚገባውን በኽረ ጉዳይ እየሞተም፤ #በመስቃ ውሃ በቀጠነ እዬተቀጠቀጠም ፈላስፊት ኢትዮጵያ ትቀጥል ዘንድ በመቻል ቅኔዊ አቅሙ አተመበት። ኢትዮጵያን ቁምነገር የማድረግ ዓላማ ያለው ህዝብ ስለሆነም በማለት ሳይሆን በመሆን አረጋገጠ። 
 
የአማራ ህዝብ መገለሉን፤ መጨቆኑን፤ መጠላቱን፤ ተቀርቦ አለመያዙን ጠንቅቆ ያውቃል። ለከፈለው ሚዛን ለማይወጣለት መስዋዕትነት ምላሹን አይቶታል። የመሪወቹንም አቅም እና አቅል በሚገባ ያውቃል። መሪወቹን በመደዳ መነጠቁም ይገባዋል። ግን ቅኔው ከባለ ቅኔው ስላለ ልምዱም፤ ተመክሮውም "በህግ አምላክን" አክብሮ ያስከበረ መምህር ህዝብ ነው- የአማራ ህዝብ። 
 
አንድ ጊዜ አውድዮ ሠርቻለሁኝ። የአማራ ህዝብ ፈጣሪ ከፈጠረው ቅንነት በላይ ቅንነት አለው ብዬ። ዕውነቴንም ነው። በሬውን ገበሬው "አያ ሆይ! በሬ ሆይ!"ብሎ በዜማ እያቆላመጠ ነው ጠምዶ የሚያርሰው። የአማራ ህዝብ ተፈጥሯዊነቱም ጥልቅ ነው።
 
በጥቅሎ በኦሮማራ የአማራ ህዝብ ያተረፈው፤ ያገኜው የለም። የሲዳማ ራስገዝ #ካለማገዶ የወልቃይት ጠገዴ ራያ ጠለምት አዲረመጥ ራዕያን ተማግዶለት፤ ተደክሞለት፤ ተግተንለት እንኳን የቆረጠ ውሳኔ ማስደረስ ያልቻለ፤ ደረጃውን የጠበቀ ውይይት ከፋኝ ካሉ ወጣቶች ጋር ለማድረግ ያልደፈረ፤ በማለት ብቻ ዕድሜውን የቀጠለ ክልል ቢኖር አማራ ክልል ነው። 
 
ከምርጫው በፊት ክብርት ወ/ሮ ሎሚ በዶ ምክትል አፈጉባኤዋ ላይ አርማጭሆ ነበሩ። ለምን ፕሮግራሙ እንደተዘጋጄ አላውቅም። ጉብኝት ይሁን እረፍት አልገባኝም። የዛሬ ፶ ዓመት የተሠራን የጭቃ ምርጊት እና የፍራፍሬ ተክል ጎበኙ። " የተሠራው ጥሩ ነው ይቀራል" ሲሉ አዳመጥኩኝ። መቼ ተጀምሮ ይሆን ይቀራል የሚባለው? 
 
#ቢያንስ ዝምታችን ብታከብሩት ምን አለ? 
 
1) ዛሬም እኮ የታሠሩ የአማራ ልጆች ይፈቱ እያል ነው እንደ ትናንቱ? #ደከመኝ። ልታግዙን አልቻላችሁም።
2) በሚሊወን ለሚቆጠሩ የአማራ ልጆች ተፈናቃዮች እናንተ አላችሁን? ቀን በሐሩር፤ ሌሊት በውርጭ እና በብርድ ስለሚቀጡት ደብረብርሃን እና ሌሎች አካባቢወች ስላሉ አካሎቻችን ምን ታስባላችሁ? አንድ ቀን ሄዳችሁ አይታችኋቸው አታውቁም።
3) ግን አማራ ክልል ያለው የብልጽግና ሙሉ መዋቅራችሁ ይሠራልን? ከእናንተ ጋር ነውን አመራሩ? ተወያይታችሁ ታውቃላችሁን?
4) መከላከያ ክልሉን #ለቆ ቢወጣ እራሳችሁን ችላችሁ ማስተዳደር ትችላላችሁን?
 
#ቀጠሮው ለመቼ?
 
1) መቼ ነው ይፋዊ የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጁ የሚነሳው?
2) መቼ ነው ለተፈናቃዮች አብነታዊ ሞዴል የቤት ሥራ በአማራ ክልል የሚጀመረው?
3) መቼ ይሆን ያለምንም ስጋት ህዝቡ መኖሩን ማኖር የሚችለው?
4) መቼ ይሆን የአማራ ልጆች ትምህርታቸውን በተሟላ ሁኔታ መማር የሚችሉት?
5) መቼ ነው እስር ቤቱን የሞሉት የአማራ ሊቃናት ከካቴና የሚላቀቁት?
6) መቼ ይሆን በተፈናቃዮች ሰፈራ ተገኝታችሁ ችግራቸውን የምታደምጡት? ለመሆኑ ስታስቲኩስ አላችሁን?
7) መቼ ይሆን ለትውልድ ቀጣይነት የሚሆኑ ዘላቂ ፕሮጀክቶች፤ ዓለም ዓቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ፤ አውራ ጎዳና፤ የኃይል ማመንጫ አማራ ክልል ላይ የሚኖረው?
 
ስምንተኛ) መቼ ይሆን የአማራ ህዝብ በየከተማ ያለው ከውሃ ጥም ጋር የሚቆራረጠው? የገጠሩ ችግሩ ሰፊ ቢሆንም የታለመ ነገር አለን?
9) መቼ ይሆን የአማራ ህዝብ ከኤሌትሪክ መጥፋት ጋር የሚፋታው?
 
10) ለመሆኑ አማራ ክልል ስለ ኢትዮአፍሪካ ርዕሰ መዲና አዲስ አበባ አጀንዳችሁ ሆኖ ያውቃልን?
11) መቼ ይሁን በቃላችሁ የምትገኙት?
12) መቼ ይሆን እንደ ሱማሌ ክልል ዳይናሚክ የሆኑ ወጣት ሊቃናትን ወደፊት የምታመጡት?
13) መቼ ይሆን ህፃናት ሳይሰጉ፤ ሳይደፈሩ ከሞት የሚያመልጡበትን የዋስትና ተግባር የምትፈጽሙት?
14) መቼ ይሆን የእናቶችን፤ የባለሙያወችን፤ የሹፌሮችን እገታ የምታስቆሙት?
15) መቼ ነው የወልቃይት፤ ጠገዴ፤ ጠለምት፤ ራያ፤ አዲረመጥ፤ አዲአርቃይ ጥያቄን ለስኬት እምታበቁት? ሁልጊዜ በእንጥልጥል?
16) መቼ ይሆን የአማራ ክልል ህብራዊነት አክብሮ የፖለቲካ ውክልና ለኦሮሞ፤ ለአገው፤ ለአርጎባ እና ለቅማንት እንዳሰጠው አማራ በብዛት በሚኖርባቸው ክልሎች የአማራ ብቁ ሊቅ ግዴታውን ይወጣል፤ የፖለቲካ ውክልና ግን የለውም። ከክልሉ ውጭ ስለሚኖረው የአማራ ህዝብ የፖለቲካ ውክልና ደፍራችሁ መብቱን የምታስከብሩለት?
 
17) መቼ ይሆን ካለ አጃቢ፤ ካለ ጥበቃ እናንተ በህዝባችሁ #መሃል እየተንቀሳቀሳችሁ ችግሩን፤ ሐዘኑን፤ ደስታም ከኖረው መጋራት የምትችሉት?
 
18) መቼ ይሁን እንደ ባህርዳር እና ጎንደር ዩንቨርስቲ የአማራ ልጆች በሌሎች ዩንቨርስቲወች #የቦርድ አባል የሚሆኑት? ባዶ ወንበር ነው እኔ የሚታዬኝ። ፍላጎቱን ዘርዝሮ፤ አቅዶ መከወን እና ማስከወን ሾልኳል ወይንም ፈሷል። ፌድራሉ ላይ ሳይሆን ችግሩ ያለው አማራ ህዝብን ወክላችሁ ባላችሁት ላይ ነው። መጀመሪያ ትንሽ ተንቀሳቀሱ እስቲ። 
 
19) መቼ ነው ጦርነቱ ቆሞ የአማራ ህዝብ እፎይ የሚለው? ቅብ ያልሆነ፤ ለብለብ ያላለ የአማራ ህዝብ የሰላም ተስፋ መቼ ይመጣል? የመኖር ዋስትናውስ እንደምን ይረጋገጣል? ጫን ተደል ኃላፊነት አለባችሁ። ሠርግ ላይ መገኜት ሳይሆን በተከፋ ህዝባችሁ መሃል ሆናችሁ ለማድመጥ ጀምሩት። የእናንተ ጥንካሬ አለመኖር ነው ሆድ ብሶት ዱር ቤቴን የመረጠው። 
 
"ከጎዳና ፓርላማ" ስትሉ ህሊናዊው የአማራ ህዝብ ይሁን ብሎ እኮ ተቀብሎ ነበር። ገፊ ኃይሎች እንዳሉ ጠንቅቄ አውቃለሁኝ። ማህበራዊ መሠረቱን ያጣው ሁሉ ወደ አማራ ፖለቲካ እንደሚተም ይገባኛል። በር የለውማ? በአቅሙ የሚጓጉ ብዙ ናቸው። ያው ለማገዶነት እንጂ የአማራ ህዝብ ታማኝ አጋር ይኖረዋል ብዬ አላስብም። ይካዳል። አማድ አፋሽም ነው። 
 
ቢያንስ ቦታውን ከያዛችሁ ግን #ከማስከፋት ተቆጥባችሁ መቅደም ትችሉ ነበር። አቅም ከሌለ ደግሞ አቅም ላለው ፈቅዶ ማስረከብ ይገባል። የህዝብ ተስፋ ለመሆን ገና አልጀመራችሁትም። 
 
#ጥያቄው አላችሁ ወይ? ወይንስ {}? እንደ መከወኛ።
 
የተሻለ ብዬ የማስበው ሚዲያችሁ አለ አሚኮ ይሠራል በተፈቀደለት ፎርማት ሲናርዮ ልክ። ሌላው የኢንተርኔት አገልግሎቱ ጥሩ ነው ብዬ ነው እማስበው። አቅሙ ግን የፌድራሉ ነው። ፌድራሉ በዘርፋ ተግቶ ይሰራል። አማራ ክልልም ጠበለ ጣዲቁ ደርሶታል። እንደ ሌላው ዘላቂ ፕሮጀክት ቁጭብለህ ጠብቀን አልተባለም።
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ ቤተ ቅንነት። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie።
06/06/926.
 
ዕውነት #ወጌሻ አያስፈልገውም ወይንም #ጋራጅ አያሰኜውም።
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
See less

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።