#ግነትም ይሁን #ኩሰት የአንድን ክስተት ተአማኝነት #ያስበረግጋል። ፋክትንም #ይጫናል።
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።
#ምዕራፍ ፲፱።
ኃላፊነት ያለበት መንግሥታዊ ተቋም ላይ ስለሆነ አትኩሮቴ በመንግሥት ተቋማት ላይ ነው። ቴሌቢዥን፤ ራዲዮ ለሚያዳምጡ ታዳጊወችም ብርቱ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ብዬም አምናለሁኝ።
«የዓለምን ትኩረት የሳበው የኢትዮጵያ ምርጫ» |EthiopianElection2018| UK| EU| Australia| Japan| US| Dasesa|ዳሰሳ|
«የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬት፤ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና ለአፍሪካ ያጎናጸፈው አዲስ የዲሞክራሲ ክብር» | Election Ethiopia | EBCDOTSTREAM
«7ኛው ሀገራዊ ጠቅላላ ምርጫ የመድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲ ማሳያ @ethiopiannewsagency»
የግነት ተፈጥሮም ያለ ይመስለኛል። በአንፃሩም የማንኳሰስ የማጣጣል ተፈጥሮም እንዲሁ። ሁለቱም ለፋክትም ይሁን ለጭብጥ ተፈጥሮ አዘናጊ፤ ትጥቅ #አስፈቺ ክስተቶች ናቸው።
በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ህይወት የተዘነጋ ማህበረሰብ አለ። ሙሉ አቅም፤ ሙሉ ትህትና፤ ሙሉ ሥነ - ምግባር፤ ሙሉ ታጋሽነት ያለው ማህበረሰብ። ጭምቱ ማህበረሰብ (ሳይለንት ማጆሪቲው።) እሱ እንኳን ይታዘበኛል፤ ይዳኜኛል ብሎ አለማሰብ የሚገርም ገጠመኝ ነው። ይህ ልዩ አቅም የልቡን አድራሽ ሁነት ሲገጥመው ደንበር የለሽ እርምጃ ይወስዳል። ቁጣው የዘገዬ፤ ድጋፋም የጨመተ የማይክለፈለፍ በኢትዮጵ ኦርጋኒክ ተፈጥሮ ልክም የሆነ ይመስለኛል። ሰበር ችሎትም።
አንድ ክስተትን፤ ወይንም ሁነትን ሲበየንበት ከጥላቻ ይሁን ከቅናት፤ ከኢሞሽን ይሁን ከቅሬታ እራስን አርሞ ቢሆን ይመረጣል። ምክንያት ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት አክሰሱ ላላቸው ታዳጊ ወጣቶች የአቀራረጽ ፎርማቱ ጥሩ ስለማይሆን።
1) ቅድመ ምርጫ እና ብልፄ።
1.1 ክርክራዊ ገጠመኝ።
የቻልኩትን ያህል አዳምጫለሁኝ። የሚዲያ ተሳትፎ ጥሩ ነበር። ዕድሉም እኩላዊ የሚዲያ አክሰስ ነበር። ጠና ያሉ ሙግቶችም አዳምጫለሁኝ። ለመጀመሪያ ጊዜ ከዘመነ ቅንጅት ወዲህ በአትኩሮት የተከታተልኩትም ነበር። ትዝብቴንም ጽፌያለሁኝ በፔጄም። ዩቱብ ኮሜንት መስጫ ላይም አልፎ አልፎ ተሳትፌያለሁኝ።
ምርጫ 2018 ዓም ስለመኖሩ ያወጀውም ይህ የሚዲያ ፋክክር #ጤናማ ንቅናቄ ነበር ብዬ አስባለሁኝ። ምርጫ 2018 ከመረሳት ያዳነውም ይመስለኛል። የብልፄውን ሞጋቾችንም ጥሩ አድርጌ ያዬሁበት ገጠመኝም ነበር።
1.2 ለተፎካካሪ፤ ተግባቢ፤ ተጠማኝ፤ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ህዝባዊ ስብሰባ የተከለከለ ነበር። ለብልፄው ደግሞ በኢትዮጵያ ባጀት 100% የተፈቀደ ነበር። ይህ ሂደት "የዓለምን ትኩረት የሳበው ምርጫ፤ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬት፤ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና ለአፍሪካ ያጎናጸፈው አዲስ የዴሞክራሲ ክብር፤ የ7ኛው አገራዊ ምርጫ የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ ማሳያ" የሚለው አገላለጽ ዕርዕሱ በራሱ ፍጹም #የተጋነነ እና ከዕውነት ጋር ፊት ለፊት ቆሞ ሊሞግት የማይችል የፎቶ ሾፕ ትርኪ ዓይነት ነው - ለእኔ።
1.1.1 " የዓለምን ትኩረት የሳበው የኢትዮጵያ ምርጫ።" ለምን ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል። ግንቦት ምርጫ ሊካሄድ አገሮች ወርኃ ሚዚያ ላይ ኢትዮጵያ #አትሂዱ፤ ከሄዳችሁ አዲስ አበባ ብቻ የሚል ለዜጎቻቸው አሜሪካን ጨምሮ መመሪያ ሰጥተው ሰጥተው ነበር። የስጋቱ ደረጃም ከፍ ባለ ሁኔታ ነበር። ይህ የደህንነት ስጋቱ #የታመቀ ጭንቀት ነበር።
በሌላ በኩል "ተጨማሪ ዕድል ለብልፄው አንሰጥም" ያሉ ጽኑ ተቃዋሚወች ዱር ቤቴ ያሉት የፈጠሩት ሰፊ ጫና ነበር። በተጨማሪም የቀንዱ የጎረቤት አገሮች ትርምስ፤ ግብጽ የምትፈጥረው የካርቶን ፊልም ግርግር ታክሎ፤ እንዲሁም የመላ ዓለም ሁነትም አስጨናቂ ጊዜ ላይ ነገረ ሆርሙዝን ተሸክሞ፤ በኢትዮጵያ ምርጫው ስለሚካሄድ አትኩሮት በአውንታዊም፤ በአሉታዊም መከሰቱ አይቀሬ ነበር።
በሌላ በኩል እኛ የማናውቃት ፈላስፊት ኢትዮጵያ ግርማ ሞገሷ፤ ነገረ ኢትዮጵ፤ ሚስጢረ ኢትዮጵያ ለገኃዱም ለመንፈሳዊው ዓለምም #ጉልህ ናት። እኛ ብናቃልላትም፤ ባንረዳትም፤ በልኳ ለመገኜት አቅሙም ቁመናውም ቢፈትነንም። ዓለም ግን የማይክደው ረቂቅ ጸጋ የተሰጣት አገር ስለሆነች ነው። ለእኔ ኢትዮጵያ መንፈሷ አህጉርም፤ አገር ናት ብዬ አስባለሁኝ።
የሱማሌ ላንድን የአገርነት ጥያቄ ቅድመ ስምምነት መፈረሟ ያስነሳው የሚዲያ ወጀብ ውሰዱና በብዙ ሁነት ልቃ የምትገኜው እስራኤል ዕውቅናውን በአደባባይ ሰጥታ፤ ተጨማሪ እርምጃወችም እየወሰደች ግን የኢትዮጵያ ያህል አውሎ አልተነሳባትም። አውሎ አለ ግን የኢትዮጵያው ቱርክን አነሳስቶ የአንካራው ዲክላሬሽንን ወለደ። ኢትዮጵያ ቀለሟ ጉልህ ነው።
1.1.2. የ7ኛው አገራዊ ብህራዊ ምርጫ ስኬት፤ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት፤ እና ለአፍሪካ ያጎናጸፈው፤ አዲስ የዴሞክራሲ ክብር" ይህ እግዚኦ ያሰኛል። "ዴሞክራሲ" ኧረ በፈጠራችሁ። አጤ ዴሞክራሲ ወጩን እኔ ችዬ ላጓጓዛችሁ ቢል ለኢትዮጵያ ፖለቲከኞች አይፈቅዱለትም። ምክንያቱም ዴሞክራሲ እኮ ከራስ የሚጀምር ፈታኝ ክስተት ነው። እራስህን ሊቀመንበር፤ ሰብሳቢ ለዘመናት ሁሉ አድሮጎ በሚመሠረት የፓርቲ ባህል አይታሰብም።
አንጋፋውን ህወሃት ለምሳሌ ላንሳ፤ ከሥልጣኑ መሰናበቻ መባቻ ጀምሮ ስብሰባ ምግቡም መጠጡም መተንፈሻ ቧንቧው ነው። በራሱ መድረክ በድምጽ ተሸንፎ ነበር። #ተናነቀው። ይኽው አሁንም ያምሳል። ሌላውም የፖለቲካ ድርጅት አንጃው፤ ልዩነቱ፤ ተስፋው ሰሌዳ ላይ መቅረቱ እኮ ዴሞክራሲ እና የኢትዮጵያ ፖለቲካ #እእ ስለሆኑ ነው። ይህ ፈጽሞ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ የማይታሰብ፤ የማይታለም ጉልበታም አመክንዮ ነው። ይህ ጉዳይ በብልጼ ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ፖለቲካዊ ተቋም የተከለከለ መንገድ ነው።
ጋና፤ ደቡብ አፍሪካ፤ ኬኒያ፤ ሱማሌ ላንድም ም ምን ሊባሉ ይሆን። የአፍሪካ የዴሞክራሲ ተምሳሌት የክብር ማማ እነኝህ አገሮች ናቸው። በሌላ በኩል ድህነትን ያሸነፋ፤ አፍሪካዊ የስካንዳንቢያ አገሮች ዓይነት ዜጎቻቸውን ከድህነት አውጥተው፤ ጽድት ያለ የመኖር ዋስትናን ለህዝባቸው በፍቅር ያረጋገጡ ሞሪሽዬስ እና ቦትስዋናስ ምን ይባሉ ይሆን።
እንደ ሚዲያ በምልሰት የ6ኛው አገራዊ ምርጫ የብልጽግና ጉባኤ እና አመራር እጩነት፤ እንዴት ነበር የተከወነው? የምርጫ አስፈፃሚ ሰብሳቢ ጠቅላይ ሚር አብይ እራሳቸው ነበሩ። በየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት የስብሰባ ደንብ እና ህግ ይህ ሆኖ አያውቅም። የዛን ቀን የነበረው ገጽታቸውም እራሱ ስጋታቸውን ያሳይ ነበር።
ኢትዮጵያ ቀደምት፤ ቅኝ ያልተገዛች፤ የእኔ የምትለው የመኖር ሥልጣኔ ባለቤት፤ የእኔ የምትለው የፊደል ገበታ፤ የሃይማኖት ሥርዓት፤ ተዝቆ የማያልቅ የባህል ህብራዊነት፤ የቋንቋ በረከት፤ የህግ አካባሪነት ህዝብ ያለባት፤ አድማጭና ጭምት ህዝብ የሚኖርባት፤ የተመድ፤ የአፍሪካ ህብረት፤ የፓን አፍሪካኒዝም ተምሳሌት ናት።
ፈላስፊት ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ፤ ለግሎባሉም የዲፕሎማሲ አራተኛ አገር (ከኒወርክ፤ ከጄኔባ፤ ከቤይና ) ቀጥላ ያለች አገር መሆኗ ትኩረት ቢስብ፤ ማግኔታዊ ጸጋዋ እራሱን ቢያብራራ፤ ያለችበት መልዕካ ምድራዊ አቀማመጥ ቁልፍነት፤ ተፈጥሯዋ ማንነቷ ጽድት ያለች አገር መሆኗ እንጂ የፖለቲካ ሥርዓት በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ፤ የቅንነት ፖለቲካ፤ የሰብአዊነት እና የተፈጥሯዊነት ፖለቲካ፤ የመኖር ዋስትና የተረጋገጠባት አገር ሆና አይደለም።
ትዮጵያ ሳይንቲስት፤ ፈላስፋ፤ ህግ ዩንቨርስ ብትሆንም የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ቀመር ከዞግ ዕሳቤ ያልወጣ፤ በጥላቻ እና በበቀል የታመለ፤ ዜጋ በአገሩ እንዳይኖር ህገ መንግሥታዊ ሽፋን ያለው፤ ኢትዮጵያዊነትን የሚፈትን ህገ መንግሥት በበቀል የተቀመረ ርዕዮት አቅሟን አዶክኮ የሚገኝባት አገር ናት።
ጥሩ ነገሩ ታላቅነቷ ሰው ሰራሹን መሰናክል ጥሶ ጎልታ የመታዬት አቅሟን ጉልበታም አድርጓታል። ብንታደል ሌላው የማያገኜው ረቂቅ ምርቃት ጸጋ እና በረከት አለን።
ስለሆነም ኢትዮጵያ ባላት ቀደምትነት ጥሪታዊ፤ ትውፊታዊ አቅም የህዝቧ የተመጣጠነ የሥነ - ልቦና ቁመና፤ በራስ የመተማመን አቅም ተቀንቶበት እሱን የሚበርዙ ያልተገቡ ንግግሮች ሁሉ ይደመጣሉ።
ሌሎች አገሮች በልነበሩበት የዓለም ታሪካዊ ሂደት አለን፤ ነበርን እያሉ ብዙ ጥልቅ ተግባር ሲከውኑ "ድሃ ሉዓላዊነት የለውም" የሚል የተፋለሰ ትርክት ልፍስፍስ መንፈስ በቀጣይ ትውልድ ለመፍጠር ፈተና ተደቅኖባታል። ሚዲያወች እንደ እኔ ደፍረው ይህን ባይሞግቱም ሚዛኑን የጠበቀ ዕርዕስ መስጠት ግን የተገባ ነበር። "ሙያ በልብ" እንደሚባለው።
የመንግሥት ይሁኑ የግል አገር ቤት ያሉ የሚዲያ ባለሙያወች እነሱ እንጀራቸው ነው። ቤተሰብ አላቸው። በጥንቃቄ መስራት ይገባቸዋል። ግን በሌለ ታላቅ የፖለቲካ ምኽዋር በሆነው ዴሞክራሲ መቀለድ አይገባም። ማግነኑም፤ ማኩሰሱም አይገባም ባይ ነኝ። ለምን? ፋክት አፈላላጊ ትውልድ መፍጠር የሁላችንም ግዴታ ስለሆነ።
ኃላፊነት ወላዊ ነው። ስለሆነም ኃላፊነት የሁሉም ኃላፊነት ስለሆነ በተፈቀደው ሩም ውስጥ ፋክትን አጥርቶ ማስኬድ ያስፈልጋል። ኢትዮጵያንዚምን የሚፈራ ትውልድ እኮ ታቅዶ ተሠርቶበታል። ግን ነገር ግን ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሽንፎ የተፈጠረ ሚስጢር ስለሆነ ፈተናወችን ተቋቁሞ ኢትዮጵያን እንደ አገር አስቀጥሏታል። ኢትዮጵያዊነት ለኢትዮጵያ የትርታዋ ማስቀጠያ #ኦክስጅኗ ነው። ለኢትዮጵያዊነት የጨመተ፤ እዩኝ እዩኝ የማይል ሠራዊት አለው፤ ሳይለንት ማጆሪቲው።
የዚህን ልዩ የአቅም መሰጠት፤ በዝምታው ውስጥ ያለ የማድመጥ መክሊቱን በዘመነ ቅንጅት፤ በዘመነ አብይዝም አቀባበል፤ በእዮሪካ እና በኢትዮጵያ የላቀ የጥበብ ቃና ተደራሽነት በተጨባጭ ታይቷል። ይህን አድምጦ እራስን ገርቶ እና አሂሶ ከዕውነት ጋር መታረቅ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ዕውነት ሊሆን ይገባል። መዳኛቸውም፤ መሻታቸውን የሚያስፈጽመው በኽረ ጎዳና ይህ ስለሆነ። አገራዊ ፕሮጀክቶችን ሎጎ እዩት። ከኢትዮጵያዊነት መንፈስ በጣም በሩቁ ሆኖ ነው የሚነደፈው። ይታገሉታል። ይቀኑበታል። ግን #ይሸነፋበታል።
1.1.2 "7ኛው አገራዊ ምርጫ የመድብለ ፓርቲ ማሳያ" ኦኦ። ይህ ደግሞ የባሰበት ያለ አቅሙ የተንጠራራ ጉድ ነው። ጎንደሮች ባለ ቅኔ ናቸው። "ልክን ማወቅ ከልክ ያደርሳል" ይላሉ። የ7ኛው አገራዊ ምርጫን ካለልኩ ያንጠራራ፤ ከግነትም በላይ በኩሸት የኮፈሰ ዕርዕስ ነው። ይህን ስልጡኖቹ ትንታጎቹ የጀርመን የፖለቲካ ድርጅቶች፤ ወይንም ጭምትነት በሥልጣኔ ያዋህዱት የሲዊዝ የፖለቲካ ድርጅቶች "መድብለ ፓርቲ ሥርዓትን" ይናገሩት። ሠርተውታልና። ዕጹብ ድንቅ በሆነ ግለኝነትን አሸንፈው ሥልጣን በመርኽ በመከፋፋል የህዝባቸውን ፍላጎት በትክክልም በዕውነተኛ፤ በሃቀኛ ዲሞክራሲ የሚመሩበት ዊዝደማዊ ብልህነታቸው።
ሚዲያ ላይ መቅረብ የሥልጣን ሽግሽግ፤ ውህደት እና የዲሞክራሲ መለኪያ አይደለም። ከእነኝህ ውስጥ የጠቅላይ ሚኒስተሩን ቦታ እንተው እና ምክትል ጠቅላይ ሚር፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር፤ የደህንነት ሚኒስተር፤ የመከላከያ ሚኒሲተር፤ የኮምኒኬሽን ሚኒስተር፤ የጠቅላይ ሚኒስተር ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሚሆኑ፤ የሚሆን አይደለም ያልኩት #የሚሆኑ ብዙ ቁጥር ነው የተጠቀምኩት አሉን??? ይኖራሉ ብላችሁ ታስባላችሁን????
ቀመሩ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደት አልገባችሁም። የነበሩት ይቀጥላሉ። ትንሽ ሽግግር ይኖራል ከሚኒስተርነት ወደ አዲስዬ ጉዞ፤ ወይንም ወደ ክልል ወዘተ። እንዳለ ይቀጥላል።
ጀርመኖች ከሶሪያ የስደተኛ ፍልሰት ጋር ከፍ ያለ ችግር ገጠማቸው። አዲስ ሞጋች ፓርቲ ተቋቋመ። ከዛ በፊትም ፋክክር ላይ የድምጹን ፍሰት አስተውለው ውህደት ፈጥረው ነበር፤ አዲሱ ፓርቲ ሲመጣ ደግሞ የመድብለ ፓርቲን ሚና አጎልብተው በፍቅር፤ በመተማመን፤ በመነጋጋር አገራቸውን አክብረውና አስከብረው፤ የህዝባቸውን የመኖር አቅም ሳያውኩ ቀጥለዋል። አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ችግሮች ተጽዕኖ እንዳላቸው ታሳቢ ማድረግ እንደተጠበቀ ሆኖ።
ጭምቶቹ ሲዊዞች አንድ ጠቅላይ ሚኒስተር የሚባል የለም። ሰባት ሆነው ድንቅነት ለዓለም ህዝብ የመሪነት #ካሪክለም ነድፈዋል። ዓለም ቢማርበት እምዬ ሲዊዝ ለመድብለ ፓርቲም፤ ለዲሞክራሲም፤ ለሰብአዊነትም ይሁን ለተፈጥሯዊነት ምቹ አገር ያደረጋት የፖለቲካ ዕሳቤዋ ልቅና እና ልዕልና ነው። አከራካሪ ጉዳዮች ለህዝብ ቀርበው ይወሰናሉ።
ዕውነት በሆኑ ጉዳዮች ግነቱ ይቁም። ዴሞክራሲው፤ መድብለ ፓርቲው ቀርቶ የመፃፍ፤ የመናገር፤ የመሞገት፤ የመደራጀት ነፃነት እስኪ ይከበር። ወጣቶች አዲስ ቡቃያ ፈልገው ፖለቲካል ፓርቲ ጠነሰሱ። አሁን የት እንዳሉ አይታወቅም። ለዴሞክራሲም ሆነ ለመድብለ ፓርቲ #ታቱ አልተጀመረም #ገና ነን፤ እግረ ተከል ለመሆን ቀርቶ ባጉምባጉም፤ ወፌ ቆመች ላይም አይደለም የኢትዮጵያ ፖለቲካ። የአገራችን የአፈጣጠር አቅም እና መንፈስ ግን ገናና ነው። ለዚህም ነው ኢትዮጵያ በዚህ ሁሉ ውስብስብ ችግርም ሆና ትኩረት የማታጣው።
2. ምርጫውን አስመልክቶ የፖለቲካ ድርጅቶች የነበረው ጫና ትዝብቴ።
2.1. በሚዲያ፤ በማህበራዊ ሚዲያ ምርጫ እንዳይታሰብ አጋች ማስጠንቀቂያወች ማነቆወች ነበሩ።
2.2. በመንግስት በኩልም በሞጋች ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅት መሪወች ላይ ጫና ነበር። የተለመደም ነው።
2.3. ከፋኖ እና ከኦላም የተሰጠ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ፤ እርምጃም ነበር።
የፍርሃት፤ የስጋት፤ የጭንቀት ድባብ ነበር 7ኛው አገራዊ ምርጫ። ለብ ባለው የምርጫ አየር ውስጥ ዕለታቱ እጅግ አስጨናቂ ነበሩ። ሰማዕትነትን የተቀበሉ ወገኖቻችንም አሉ።
የኢትዮጵያ ህዝብ እንደ ህዝብ ግራቀኙን አድምጦ፤ ጫናውን ተቋቁሞ፤ "ወዮልህን" ችሎ፤ በራሱ ህሊና ተመርቶ መኖሩን ለማስቀጠል ለምርጫ ተመዝግቧል። በዕለቱም ምርጫው ማን ያሸንፋል ሳይሆን ጉዳዩ ለህዝቡ የራሱን የግል ውሳኔ መኖሩን ለማስቀጠል የውሳኔውን ረቂቅ ሃሳብ በፊርማው መፈጸም ላይ አተኩሯል። ከጨዋነት በላይ ነው፤ ምራቁን የዋጠ ህዝብ ነው ያለን።
ስሜቱን የገራ፤ ችግሩን አምቆ ግን ለህግ እና ለሥርዓት ትውፊቱን በህግ አምላክን ነፍስ ዘርቶበታል። ውሳኔው ግን ጨቁነኝ፤ ግደለኝ፤ አፈናቅለኝ፤ እሰረኝ፤ ናቀኝ፤ ዘልፈኝ፤ አጣጥለኝ፤ ጥላኝ ብሎ አይደለም። መኖርን ለማስቀጠል ብልሁ መንገድ ጊዜን ማድመጥ የሥልጡኑ ህዝብ ትውፊት ነውና።
በዚህ የምርጫ ሂደት የፖለቲካ ድርጅቶች ተሳትፎ እና የታዛቢ፤ የካድሬ፤ የጸጥታ ኃይሎች ሁነት በሚመለከት ከቦታው ካልሆነ በስማ በለው #መሰለኝ ተስፋ መስጠት አልፈለኩም።
3. ኦላ ሙቀቱ ለብ ያለ ነበር። አሁን ከሆነ መኖሩ የሚታወቀው ብዙውን ከፋኖ በሚወጡ ዕይታወች ተከታይ ሆኗል። ፋኖ ለኦላን መንፈስ #መሃንዲሱ ወይንም ካፒቴኑ የመሆን ዝንባሌ አይበታለሁኝ። መደማመጡ ባይከፋም ግን ቀድሞ የማሰብ፤ ቀድሞ የመወሰን አቅም በፋኖ አያለሁኝ።
ሁለቱም በምርጫው ሂደት ላይ የሰጡት ዕይታ እንደ ሞጋችነታቸው አድንቀው መውጣት ባይጠበቅባቸውም፤ በእነሱ ማስጠንቀቂያ፤ በእነሱ ጠብሰቅ ባለ ትዕዛዝ፤ በእነሱ እርምጃ፤ በእነሱ ውሳኔ ልክ #የታቀበ ሂደት አላየሁም። ይህን ዕውነት፤ ይህን ፋክት መቀበል ይገባል።
ሌላም ፋክት አለ። ብልጽግና ምርጫ ቢያካሂድ ሥልጣኑን አያዘልቅበትም፤ ወይንም ምርጫውን ቢሰርዝ ህልውናውን አያሳጥርም። ህወሃት 5ኛውን ብሄራዊ ምርጫ በአሸናፊነት ደመደመ። ዘመኑ ሳይጠናቀቅ በአቋራጭ ፍፃሜውም ሆነ። ለህወሃት የምርጫ ሂደት ተቀባይነት እነ አንባሳደር ሱዛን ራይዝ የሰጡት አስተያዬት ለስልጣኑ ቀጣይነት ጥበቃ አላደረገለትም።
በሌላ በኩል ህዝብ ወጥቶ መመዝገብ፤ መምረጥ ሙሉ መብቱ ነው። ይህን መንፈግ የተገባ አይደለም። ለወደፊትም። የህዝብን ቀልብ ለመያዝ፤ የህዝብን አደብ ለማጣጣም፤ የህዝብን አትኩሮታዊ ሥጦታ ለማግኜት በህዝብ ፍላጎት ውስጥ እራስን ማስገዛት ይጠይቃል።
ከሁሉም የህዝብን ክብር፤ የመኖር ነፃነት፤ ተፈጥሯዊ ጸጋውን አለመዳፈር በእጅጉ ይጠይቃል ተደማጭነትን ለማስቀጠል። ትህትና በታዛዥነት፤ ቅንነት በርህርህና፤ ተፈጥሯዊነት በፍቅራዊነት፤ ቃልን በኪዳኑ ልክ መፈጸም ይገባል። ነገም፤ ተነገ ወዲያም ምርጫ ይመጣል፤ ይሄዳል። ምርጫ ግን የሥልጣን ማቆያ፤ ማዝለቂያ አለመሆኑ ሊታወቅ ይገባል።
ዕድልን ሳያፈሱ፤ ከዕድል ጋርም ሳይተላለፋ ዕድልን በትክክል ማኔጅ ማድረግ፤ ከአቅም ጋር ማጋባትም ይገባል። "አመላቸው ነው፤ ብለው ነበር" ከመባል የሚያወጣ ትክክለኛ አቅምን የመጠነ ውሳኔ መርኽ ማድረግ ይገባል። ክሽፈት እንዳይገጥም። ተደራሽነት #ቆባ እንዳይሆን። ለውሳኔ ሳይቸኩሉ ግብረ ምላሽን አስቀድሞ መተንበይ ይገባል።
የድጋፍ ሰልፎች እኮ የተናገሩት፤ ያብራሩት ሐተታ ነበር ……… ያ ሁሉ ህዝብ ግልብጥ ብሎ ሲወጣ ግንቦት 24/2018 ዓም እንገናኝም ነው። አንቀርም ከምርጫው ነበር። ያን አድምጦ በዛ ልክ ዕውን ሊሆን ከሚችል ውሳኔ መድረስ ተደማጭነት ያስቀጥላል።
4. በሌላ በኩል የኦሮሞ የፖለቲካ ሊቃናት ዘመንን የመጠቀም ብልህነት አላቸው። በአጤው ዘመን፤ በደርግ ዘመን በነበሩ 5 (ማለሊት፤ ሰደድ፤ ኢጭአታ ወዘተ) ድርጅቶች ሰብሳቢ ነበሩ፤ በኢህአፓም፤ በመኢሶንም፤ በመድህንም፤ በቅንጅትም፤ በኢህአዴግም፤ በአንድነትም፤ በሰማያዊም፤ በግንቦት 7ትም፤ በኢዜማም፤ በባልደራስም፤ በኦህዴድም፤ በኦፌኮም፤ በኦነግም፤ በብልጽግናም በተገኜው አጋጣሚ ሁሉ እነሱ አሉ - የኦሮሞ የፖለቲካ ሊቃናት። ስለዚህ ተመጣጣኝ የፖለቲካ ውክልና፤ ተመጣጣኝ ተመክሮ የማግኜት ዕድሉን አግኝተዋል። ፍላጎታቸውንም ኮተት እያደረጉ ሲያጠጋጉ ቆዩ አሁን የልብ አድራሽ ዘመን ተሰጣቸው። ከጠየቁት፤ ከተመኙት፤ ካለሙት በላይ ብዙም ገጭ ገው ሳይገጥመው ተሳካላቸው።
ይህ ብልህነት በትግራይ ሊቃናትም በስሱ ይገኛል። የአማራ ፖለቲካ ከመኢህድ በፊት የነበረ አይመስለኝም። እሱም በዜግነት ፖለቲካ ላይ ዝንባሌው ያደላል። የአማራ ፖለቲካ ሙሉ አትኩሮቱ ዜግነታዊ ፖለቲካ ላይ ነው። ልሁን ቢልም ከዚህ ውጭ አይችለውም። አልቻለበትም። የአብን ትልቁ ፈተና ይህ ነበር። የፋኖ ትግልም የገዘፈ ፈተናው ይህ እንደሆን አስተውላለሁኝ።
አንድ ምሳሌ ላንሳ፤ የአማራ ፖለቲከኛ ሚዲያ ላይ ለመቅረብ የግድ መምረጥ አለበት። ሌት እና ቀን የሚሰሩ የአማራ ፋኖ ደጋፊወች አሉ። #ፋና ልብ ገዝቶ እስኪ ቃለ ምልልስ ላድርግላችሁ ብሎ ቢጠይቅ አይፈቅዱም። ውስጣቸው ሊፈቅድ ይችላል። ከዛ በኋላስ ደጋፊዬ ምን ይሰማዋል ብለው ይሰጋሉ። በኦሮሞ ፖለቲካ እንዲህ የለም። የተገኜችውን ጥቃቅን ዕድል በአግባቡ ይጠቀማሉ። ሞጋችም፤ ወቃሽ ነቃሽም የለባቸውም። ስለዚህ ትግሉ ተጠቃሚነቱ በየዘመኑ ጎልብቶ የአቶ አባ ዱላ ኦህዴድ ከዚህ ደረሰ - ለኖቤል ሽልማት፤ ለዩኒስኮም ለሄሰኑም። ያለፈበትን ጉዞ እሰቡት።
በዚህ ውስጥ ቅንጅትን እሰቡት። ዛሬ አዲስ አበባ የገነት በር መግቢያ ሆናለች። ቅንጅት ምራኝ ብሎ በፍቅር የመረጠውን፤ የተገበረለትን ህዝብ መልሶ አሸንፌያለሁ ግን ልግባ አልግባ ፓርላማ፤ አዲስ አበባን ልረከብ አልረከብ ብሎ ጠየቀ፤ ከስንት ዓመት በኋላ የቅንጅት መንፈስ በዛው ህገ - መንግሥት ትምህርት ሚኒስተርን መርቶ አንቱ ሊባል የሚችል ድርጊቱን አቅሙን አሳዬ።
ቅንጅት በትዕግሥት፤ በሆደ ሰፊነት ዕድሉን ተጠቅሞ ቢሆን በትክክልም የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት በኢትዮጵያ፤ የዴሞክራሲ ፍንጭ እና የዕድገት ጅማሪ በኢትዮጵያ ማየት ይቻል ነበር። ብዙ መዋለ ጊዜ፤ መዋለ መንፈስ፤ መዋለ ንዋይ ማትረፍም ይቻል ነበር።
ዛሬ ኢትዮጵያ ህልም ሊመስል የሚችል የምኞታችን መተግበሪያ የመሆን አቅም ይኖራት ነበር። ከሁሉም የእናቶች ዕንባ ጥግ ያገኝ ነበር። የዞግ ፖለቲካ ሥርዓተ ቀብሩ ይፈጸም ነበር። በምትኩ የዞግ የሲቢክስ #የተራድዖ ተቋማት ሊያብቡ ይችሉ ነበር። ዕድሉን ኢትዮጵያ ከተሰጣት ጸጋ መክሊት ጋር የተስተካከለ የፖለቲካ ህይወት እሰቡት። ያመለጠ ዕድል።
#ክውና።
በምርጫ ዙሪያ ይህ ማብቂያ ነው። ከምርጫ ጋር በተያያዘ ሌላ እስር፤ ሌላ ወከባ ካልኖረ በስተቀር።
1) ጠቃሚው ከሂደቱ መማር።
2) ዕድልን አለማፍሰስ።
3) ዕድልን በልኩ ማኔጅ ማድረግ።
4) አርቆ ነገን ማስተዋል ይበጃል።
5) ፍላጎትን በአቅም መመጠን።
6) ምኞትን በልክ ማቀድ። ማዶ ሳይሆን ከራስ አቅም፤ ችሎታ፤ ክህሎት እና ፍላጎት ከዘመኑ ግሎባል የፖለቲካ ባህሪ ጋር ማስተጋበር ያስፈልጋል።
7) የዘመን የፖለቲካ ባህሪ የሚባል አስተምኽሮም አለ። ያን አለመሳት።
ስምንተኛ) ዕድሜን ማሰብም ይገባል።
ወላዋይ፤ አደናጋሪ፤ ወይንም ህልም ዕልም በሆነ ተስፋ ነገን ማጓጓት መጓጎልን እንዳያጋጥም ራስን መግዛት ይጠይቃል። ጥርት ባለ ፍላጎት፤ ጥርት ያለ አቋም በማስፈጸም አቅም ልክ መወጠን መቋጫውን ያሳምረዋል።
ስኬት የጀንበር ዳንቴል አይደለም። የጥረት ሂደት የልፋት፤ የትጋት፤ የቀንም ቀናነት ውህደት ነው። ከሁሉም አወንታዊነት እና ቅንነት፤ ሰብአዊነት እና ተፈጥሯዊነት ፈጣሪን አላህን አስቀድሞ የመነሳት ጥበብን ከቀደምት አቨው፤ እና እመው ልንማር ይገባል።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
06/06/026.
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ስኬት የጀንበር ዳንቴል አይደለም፤ የልፋት ሂደት ትጋት እንጂ።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ