#ሙሉዑነትን መናፈቅ ጤነኝነት ነው። የእቴጌ ትግራይ ንጥረ - ነገር #ሲጎድልስ? ኢትዮጵያም፤ ኢትዮጵያዊነትም #የወል ሥም ነው። ባለቤቱም አንድ የፖለቲካ ድርጅት ሳይሆን #ህዝብ ነው።

 

#ሙሉዑነትን መናፈቅ ጤነኝነት ነው። የእቴጌ ትግራይ ንጥረ - ነገር #ሲጎድልስ?
 
ኢትዮጵያም፤ ኢትዮጵያዊነትም #የወል ሥም ነው። ባለቤቱም አንድ የፖለቲካ ድርጅት ሳይሆን #ህዝብ ነው።
 
"አቤቱ የቤትህ ቅናት በላኝ።"
 
#ምዕራፍ ፲፱።
 
«ኢትዮጵያ መርጣለች!»
«ኢትዮጵያ እየመረጠች ነው !»
«ኢትዮጵያ መርጣለች፣ ጸንታለች፣ አሸንፋለችVETV | EBC | EBCDOTSTREAM»
 
#ነገረ ዕርዕስ እንደ በር። 
 
ዕርስ ጥምን ያረካል። ግን ዕውነት ከሆነ ----- ብቻ።
ዕርዕስ ይክሳል። ግን ዕውነትን የማያቆስል ወይንም ዕዳ የማያስከፈል -------ከሆነ።
ዕርዕስ ተስፋ ይሰጣል። ግን ዕውነትን የማይፋለም -------ከሆነ።
ዕርዕስ ማግስትን ያበስራል። ግን ዕውነትን ባለአንጣ ------ካላደረገ።
 
* ኢትዮጵያ መረጠች።"
*** ኢትዮጵያ እየመረጠች ነው።"
****ኢትዮጵያ መርጣለች፤ ጸንታለች፤ አሸንፋለች።" እነኝህ ዕርዕሶች በተደጋጋሚ አየኋቸው። ሙሉነትን መናፈቅ ጤነኝነት ነው። ደስ ይላልም። ግን የመሻት ላዕላይ እና ታህታይ መዋቅሩ ማረግረግ እንዳይኖርበት ጥንቃቄን ይጠይቃል።
 
ተችሎ ምርጫ በተካሄደባቸው ቦታወች ሁሉ ዘመኑ ጥሩ ነው ተከታትየዋለሁኝ። ምርጫው ተካሂዷል። በተጨማሪነት ዘመናይ የሆኑ መሻቶችን ተመልክቻለሁኝ። "ፍትኃዊ፤ ነፃ፤ አሳታፊ፤ በጣም ቄንጤኛው ዴሞክራሲያዊ" ይላል። ዴሞክራሲ ወጫችሁን ችዬ ያለእናንተ ድካም በእኔው ጊዜ አንቱ ላሰኛችሁ ብሎ የኢትዮጵያን ፖለቲከኞች ቢጠይቅ ኧረ አበድክ አጤ ዴሞክራሲ ልክህን ወደ አውሮፓ አፈላልግ ይሉታ። እርግጥ ነው የተጠቀሱት ሰውኛ ምግባሮች ለሳይንቲስቷ ኢትዮጵያ የማይገባ ሆኖ አይደለም።
 
ኢትዮጵያ አፈጣጠሯ #ኦርጋኒክ ስለሆነ ተፈጥሯዊ ዲስፕሊኖች ይገባታል። ግን ቅንነትን መድፈር የሚያቅተው የኢትዮጵያ ፖለቲካ አልቻለውም። ልኩም አይደለም። እኔም አልጠብቅም። በሁለቱም በተፋላሚወችም በብልፄውም "ብትመሩጡ ወዮላችሁ፤ ባትመርጡም ወዮላችሁ" ስለነበር በሰላም መጠናቀቁ ነበር ጉዳዬ። ህዝቡ ደፍሮ መውጣቱ ድንቅነት ነው። ማት ሲወረድበት ሰምቻለሁኝ። አለመታደልም ነው። መብት እኮ ነው።
 
የሆነ ሆኖ ምርጫውን አልታዘብም ያለው የአውሮፓ ህብረት አባል ያልሆኑ ሦስት አገራትን አክሎ፤ ጃፓን ድጎማዬ ይቆጠርልኝ ሲል፤ የአፍሪካ ህብረት ሽርሽር በሚመስል መልኩ በአዲስ አበባ ያደረጉት የተመጠነ ክትትል፤ ኢጋድም የሰጠው መግለጫ በትግራይ፤ በአማራ ክልል፤ በኦሮምያ ባለው የፖለቲካ ውጥረት አንፃር በዚህ መልኩ መከወኑ መልካም ነው በኽረ ጉዳይ ሆኖ የታዬው።
 
ይህም ሆኖ ጎንደር ዩንቨርስቲ የቦንብ ፍንዳታ፤ የአርሲ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እልቂትም የከፋ ገጠመኞች ናቸው። ግን አገሮች ከዚህም በላይ ስጋት ነበረባቸው ማለት ይሆን? የመንግሥት ሚዲያወች ፌስታም እንዲሁ ከዚህ አንፃር ይመስለኛል ግንን ያለ ዕርዕስ የሰጡት። 
 
በደረግ ጊዜም አንድ ለእናቱ ኢሠፓ ምርጫ ነበረው፤ በዘመነ የህወሃት ዓውራነትም ምርጫ ነበር፤ ለዛውም በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ውዳሴ የተሰጠው ፭ኛው ምርጫ ነበር። ግን በተባለው፤ በሚባለው ልክ ነውን? ያ ቢሆን በየዘመኑ ይህን ያህል ዋጋ አያስከፍልም ነበር። አገር ያልሆነው #የሱማሌ ላንድን ያህል ብቃት ተምጦም አይመጣም። 
 
"ነፃ አካታች አሳታፊ ፍትኃዊ ዴሞግራሲያዊ" ለአንደበት ያማምራሉ። ለረጅም ጊዜም ይሳካል የሚል ተስፋም የለኝም። በአሁኑ ምርጫም ሁሉም በነበረው መልክ ይቀጥላል። ያሸነፈው ብልጽግና ነው። ትንሽ ቀለም ቀቢ ተፈልጎ #ቦረሽ ቦረሽ ይኖራል። ይህን መሰሉ ሂደት ለ15 ዓመት ይቀጥላል። የምክክር ኮሚሽኑ ተጨማሪ 10 ዓመት ያክልበታል። የሚቆጠረው ከዚህኛው ምርጫ ባሻገር ይሆናል። ያን ጊዜ ሌላ ትውልድ ነው የአብይዝም። እኛም የለንም። 
 
#እቴጌ ትግራይ።
 
የሆነ ሆኖ እቴጌ ትግራይ እንደ አንድ ክልል ማንነት አላት። ጸጋ አላት። ተስጥዖ አላት። የትግራይ ህዝቡም ይሁን ሊቃናቱ መክሊት አላቸው፤ ጸጋ አላቸው፤ ጥሪ አላቸው። በ፮ኛው አገራዊ ብሄራዊ ምርጫ ይሁን በ፯ኛው አገራዊ ብሄራዊ ምርጫ እቴጌ ትግራይ እንደ ክልል፤ የትግራይ ህዝብ እንደ ህዝብ፤ የትግራይ ሊቃናት እና ሊሂቃን የሉበትም። ይህ ያጎድላል። ህብራዊ ቀለምን ድብ ያደርጋል።
 
ስለሆነም "ኢትዮጵያ መርጣለች። ኢትዮጵያ እየመረጠች ነው። ኢትዮጵያ መርጣለች፤ "ጸንታለች"፤ አሸንፋለች፤" ይህ አገላለጽ #ከባድ ነው። የየሚዲያወቹ ኤድትርያል ቦርዱም ሊያስብበት ይገባል ባይ ነኝ። ከስሜታዊነት መውጣትንም አጥብቆ ይሻል። ፓርላማ ውስጥ፤ ካቢኔ ውስጥ፤ ፌድሬሽን ምክር ቤት ውስጥ የእቴጌ ትግራይ ጠረን አይኖርም። ንጥረ ነገር ይጎድላል። የውስጥ አካላችን እንሰበው። የሆነ ነገር አይኑር፤ ጨጓራችን ቢጎድል፤ ኩላሊታችን መሥራት ቢያቆም፤ ሙሉ ጤና ይኖራልን? #ሙሉዑነት ይኖራልን?
 
ኢትዮጵያ ትግራይን ብታጣ "ምንም አትሆንም" "መንገዱን ጨርቅ ያድርግላቸው" ወዘተ የሚል ሃሳብ አደምጣለሁኝ። የእቴጌ ትግራይ መንፈስ ተቃሎ ሊታይ አይገባውም ባይ ነኝ። የሆነው ሁሉ በፈቃደ እግዚአብሄር ቢሆንም። "የሰይጣን ጆሮ ይደፈን" እና ትግራይም ከእናት አገሯ "ከህቅታዋ" ኢትዮጵያ #ተነጥላ ይቀናታል ብዬ አላስብም። እራሱ ሃሳቡ ጉዟዋን ኮረኮንችማ ያደርገዋል። እናት ስታዝን ከጡቷ፤ ከማህጸኗ ነው። ስለዚህ ጉዳቱ ከፍ ያለ ፈውስም የማይገኝለት ይሆናል ባይ ነኝ። 
 
አንድ አይሉ ሁለት ወደብ የባህር በር ብቻ ሳይሆን ወሳኝ ጆግራፊያዊ አቀማመጥ ያላት ኤርትራ ምን ተጠቀመች???? መገንጠሉ ምርቃት ረበበትን? ምኞትን አሳካን? ተፎካካሪ ተደማጭ አገር አደረጋትን? መዝኑት። በማስተዋል መርምሩት። 
 
የህወሃትን #ሞገደኝነት በጋሜ ቁንጮ ዘመን ጀምሮ አውቀዋለሁኝ። የህዝቡን፤ የሙሁራኑን አንድ ቤት በማደግ፤ በጋብቻም፤ አብሮ በመኖር፤ አብሮ በመማር፤ ኮርሰኛ በመሆን፤ በመሥራት ደግሞ አውቀዋለሁኝ። ስለዚህ እኔ የትግራይ መነጠል ለውስጤ ሙሉነት አይመግበውም። ለዚህ ነው "የኢትዮጵያ መረጠች አሸነፈች" ኃይለ ቃል ባይጎረብጠኝም እጅግ #ከብዶኛል። 
 
እኛ ኤርትራ ፲፬ኛ ክ/ አገር ሆና ነው የምናውቃት። ለዚህ ነው ጨከን ያለ ሃሳብ ለማቅረብ #ዳ እምለው። የህወሃት ትውልድ ደግሞ ኤርትራን ሌላ አገር አድርጎ ያውቃታል። ነገ የአብይዝም ትውልድም ትግራይ የሌላ አካል አድርጎ ቢያያት የሚል ትልቅ ሥጋት አለኝ።
እቴጌ ትግራይ የህወሃት ብቻ በፍጹም አይደለችም። የሥምረትም፤ የአረናም፤ የባይቶናም ወዘተ ዘለግ ሲል የኢትዮጵያም ናት። ተነጥላ፤ ተለይታ ስትቀር ሙሉዑነቱ ላይ ይጫነዋል። በነገራችን ላይ ሥምረት የሚለውን ሥያሜ እወደዋለሁኝ። ሥምረት #ለኢትዮጵያ ቢባልም ምኞቴ ነው።
 
ስለሆነም አገላለጽ ላይ ውስጣችን በልኩ ማዬት፤ ዕርዕስ ስንሰጥ ደጋግመን በአትኩሮት ቁመናውን መመርመር ያስፈልጋል። አገራዊነት በገጠመኝ ስሜት አይተመንም። ጥልቅ ፍልስፍና ነው። ማንም ያጉድለው፤ እኛ ግን የጎደለብንን #የእኔ ብለን መቀበል ያለብን ይመስለኛል። በየትኛውም ብሄራዊ ጉዳይ ላይ የፖለቲካ ሊቃናቱን ጉዳይ ቆየኝ ብለን ውስጣችን በውስጥነቱ ልክ መቀበል ያለብን ይመስለኛል።
ኢትዮጵያ ከሌላ አገር ጋር አልተወዳደረችም። ስለዚህ "አሸንፋለች" ሊባል አይገባም። አሸናፊው #ብልጽግና ነው። ይህ ሳይታለም የተፈታ ነው። አስቀድሜ ጽፌበታለሁም። ኢትዮጵያ ደግሞ #የብልጽግና ብቻ አይደለችም። 
 
ጠንካራም ሞጋች ተፎካካሪ ብልጼው አልገጠመውም። ህወሃት ከጦርነት በመለስ መስመር ይዞ ቀጥሎ ቢሆን ኖሮ ጠና ያለ ዕድሜ ጠገብ ሞጋች ይወጣው ነበር። ከሌላ የፖለቲካ ፓርቲ ጋር ቢቀናጅ ዕድሉ ነበረው። አቅል #አይሸመት ነገር። አደብ አይገዛ ነገር። የጨመቱ የህወሃት ሊቃናት እኮ አሉ። እንደ ዶር አርከበ ዕቁባ ዓይነት። የሚመስጡም።
 
ግን ህወሃት ማዘዝ እንጂ መታዘዝን፤ መምራት እንጂ መመራትን የማይፈቅድ ድርጅት ሆነ እና አገረ ኢትዮጵያ ታመሰች፤ አፋር፤ አማራ እና ትግራይም ደቀቁ። መከራውም አላለቀም። ገና ያልተቋጬ ፈተና ፊት ለፊትም ይጠብቃል።
 
#ኦሮምያ እና አማራ ክልልስ?
 
ሌላው እንደ እቴጌ ትግራይ ባይሆንም በአማራ እና በኦሮምያ ክልል ምርጫው ቢካሄድም ሙሉዑነት ይጎድለዋል። የፖለቲካ ውክልና የሌላቸው ህዝቦች አሉ። እነሱም የራሳቸው ጥሪ፤ መክሊት እና መልዕክት ስላላቸው ይህም ንጥረ ነገር ይጎድላል። በሙሉዑነት ላይ ተጽዕኖ አለው። ስለዚህ "ኢትዮጵያ መረጠች" ይጎድልበታል።
 
"#ኢትዮጵያ ጸናች።"
 
1) በምኑ----- ????
2) ኢትዮጵያ --------አረግርጋ ነበርን?
3) ኢትዮጵያ --------ተነቃንቃ ነበርን?
4) ከምርጫ ፯ በፊት ኢትዮጵያ ጽናቷን የሚፈታተን እኛ እማናውቀው ምን ክስተት ነበር?
5) የመንግሥት ሚዲያወች ሞገድ ላይ ባለው ሁነት ሆዳቸው ባብቶ፤ ተረባብሸው ነበር ማለት ይሆን?
ለዚህም ነው እኔ ኢትዮጵያ #የከበደችን ለሁላችን ነው የምለው። እንዴት ነው ፈላስፋዋን ኢትዮጵያን የምናስባት ይሆን? #በጭቃ ምርጊት እንደተሰራ ድሆኖ ወይንስ ጎታ?
EBC ይህን ቢመልስልኝ ደስ ይለኛል።
 
"#ኢትዮጵያ አሸነፈች"
 
1) የእግር ኳስ ግጥሚያ ነበረባትን --------- ኢትዮጵያ? ቲሟ ማንስ ተሰኜ????
2) ከየትኛው አገርጋር ተወዳድራ? በምን ዓይነት የውድድር መስፈርት ይሆን ያሸነፈችው እናቱ? ይህም ለEBC ነው ጥያቄዬ። 
 
#እርገት ይሁን።
 
ኢትዮጵያ የወል ሥም ነው። ኢትዮጵያዊነትም የወል ሥም ነው። በወል ሥም ላይ፤ በወል ማንነት ላይ አዛዥም ናዛዥም የለም። ሊኖርም አይገባም። በሌላ በኩል ኢትዮጵያን ሆነ ኢትዮጵያዊነትን የመንሳትም ይሁን የመስጠት መብት ማንም የለውም። ሁላችንም እኩል መብት፤ እኩል ግዴታ በዜግነት ማንነት፤ በአገር ባለቤትነት አለን።
 
ስለሆነም ብሄራዊ፤ አገራዊ በሆኑ ፖለቲካዊ ዕሳቢወች ላይ ለአውራ ፖለቲካል ፓርቲ መብቱን ጠቅልሎ መስጠት፤ ግዴታውን ደግሞ ለህዝብ ጠቅልሎ ማሸከም አይገባም። ልንስማማበት የሚገባ ጉዳይ ኢትዮጵያ የብልጽግና ፖለቲካል ፓርቲ ብቻ #አለመሆኗን ነው። በፖለቲካ ድርጅት ያልተደራጁ ሚሊዮን ልጆች ኢትዮጵያ አላት። ይህ መሠረታዊ ጉዳይ ነው።
 
ብልጽግና ስላሸነፈ ኢትዮጵያ ተጠቅልላ "ኢትዮጵያ አሸነፈች" ሊባል ፈጽሞ አይገባም። ብልጽግና ፯ኛውን አገራዊ ምርጫ አሸነፈ ማለት ትችላላችሁ። እኔ ግን አስቀድሜ ጽፌያለሁኝ። ወደ ፵ የሚጠጉ ፓርቲወች አሉ፤ ብልጽግና ከ40ወቹ አንዱ ነው። ሁሎቹም አባል ደጋፊ አድናቂ መራጭ ህዝብ አላቸው። ምንም የፖለቲካ ፓርቲ የማያስፈልገን ኢትዮጵያዊ ዜጎች ደግሞ አለን። ኢትዮጵያም #የእኛም ናት። እኛ ደግሞ ከፋክክሩም፤ ከእጩነትም፤ ከመራጭነትም የለንበትም። ግን አገራችን ኢትዮጵያ የወል ማዕድ ማዕረግ ክብር ጉልላት ናፍቆትም ናት - ለእኔ። 
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
06/06/026.
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ኢትዮጵያም #የሁላችን!
See less

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።