#የ106 ደቂቃወች የምጥ ግልግል #በኒወርክ።
"የሰው ልብ መንገድን ያዘጋጃል፤
እግዚአብሄር ግን አካሄዱን ያቃናለታል።"
(ምሳሌ ፲፮ ቁጥር ፱።)
#ምዕራፍ ፲፱።
#ጠብታ።
ክብረቶቼ የእኔ አዱኛወቼ፤ የአገሬ ልጆች የእቴጌ ድንቡልቡል የልብ ህሊናወች፤ የእግር ኳስ አፍቃሪወች፤ አትኩራታውያን ሁሉ ምሽቱ፤ አዳሩ፤ ረፋዳው እንዴት ይዟችኋል?
ስለ - ተፈጥሯዊነት፤ ስለ - ጥበብ፤ ስለ - ሰው ልጅ ሐሤት የአሰጣጥ ሥርዓትየሚመስጣችሁ ወገኖቼ፤ በማስተዋል የአርቱ ቤተኛ ለመሆን የመስጠት አቅም ያላችሁ ውዶቼ እግር ኳስ ለእኔ 13ኛው #ፕላኔት ነው። ተክለ - ሁነቱን እዩት ማዕድ ነው። ክብ ነው። እቅፍቅፍ ጥግትግት - ውህድህድ - ያለ የዓለም ማህበረሰብን የሚናፍቅ ሐዋርያ፤ ትንቢተኛም።
እግር ኳስ በፍቅር ተፈጥሮ የጰጰሰ፤ በተፈጥሯዊነት ነብይነትን የተጎናጸፈ ልዩ ስጦታ ነው። ግሎባላይዜሽን - ሲታሰብ፤ ደንበር አልቦሽ እኛዊነት ሲታሰብ፤ አብሮነት - ሲታጭ፤ ህብራዊነት - ሲታለም፤ ዕንባ - ሳቅ - ሲቃ - የጋብቻ አጋጣሚ፤ ቤተሰባዊነት፤ ማህበራዊነት፤ ታዳሚነት - አድማጭነት ሲታለሙ ፌክ ያልሆነ የውስጥ ለውስጥ አገናኝ ነው። ድልድይ ነው የላቀው የእግር ኳስ ቅኔዊ - ጥበቡ፤ ዘለግ ሲል ዊዝደሙ።
በኳስ ውስጥ መሰጠትን፤ ማተኮርን፤ ማስተዋልን፤ የጋራ እና የግል ኃላፊነትን፤ ፖስተኝነትን፤ ቅብዓን፤ ህግን፤ ጥሪን፤ የድንጋጌ አፈፃጸም ሂደትን፤ የትውልድ አገነባብ ሜቶሎጂን፤ ትውልዳዊ ድርሻን፤ ታሪክን - ትውፊትን - አደራን - ስልጣኔን - መኖርን - መታመንን - ሞራልን - ዲስፕሊንን - ድንበር አልቦሽነትን - እድገትን - ስኬትን - መደመጥን - ቅንነትን - ማግስትን አጭቶ ያጋባል። ለተሰጣቸው ሙያ ነው። ሙያው ደግሞ ከፍ ያለ የመኖር ደረጃንም ሰጪ ነው።
ስለ እግር ኳስ ሲታሰብ ድሎት፤ ምቾት፤ ቅንጦት የሚመስላቸው ሊኖሩ ይችላሉ። እግር ኳስ #ህይወት ነው። በህይወት ውስጥ መሰናክሉ፤ እክሉ፤ ግድፈቱ፤ ቃና ውበቱ ሁሉም አሉ።
በየዘመኑ ተጨንቃ ውላ በምታድረው ዓለማችን ውስጥ ዋሻ፤ ዋርኳ ለመንፈሳችን መጠጊያ ከለላ የተሰጠን ሽልማትም ነው እግር ኳስ። በስሱም ቢሆን እፎይ የምንልበት። ከገጠር እስከ ከተማ፤ ከባዶ እግር እስከ ስልጡኑ የአዲዳስ መጫሚያ፤ ከጨርቅ ኳስ እስከ የሰለጠነ የኳስ ቁመና፤ ያለ ደንበር ለሁሉም - ስለሁሉም ነፍስ ሆኖ፤ ነፍስ ሰጥቶ እግር ኳስ ያስፈነድቃል፤ ያሟጋታል፤ ያወጋግናል፤ ሚዲያን ሚዲያ ይሰራው ዘንድ ይፈቅዳልም።
#ዘመን እና እግር ኳስ።
ዘመንን አደብ፤ አቅል፤ ስክነት፤ እርጋታ ያደርግ ዘንድ እግር ኳስ ይመክራል፤ ይዘክራል። የእግር ኳስ ፍልስፍና ሳይንሱ በተሰጠው ልክ አቃፊ፤ ተንከባካቢ፤ አሰልጣኝ፤ ሰልጣኝ፤ አትራፊ ነው። አትራፊነቱ የቁስ አይደለም። ይልቁንም የመንፈስ ልቅና በልዕልና ጽፎ የሚያስኮን፤ በትልም ውስጥ ሰክኖ የሚያሰክን፤ በሚሊዮኖች ልብ ደልደል ብሎ ቤተኛ የመሆን አቅም ያለው የዕውነተኛ ሰውኛ ሐዋርያም ነው። በየቤቱ የነገሰ አባ ወራም።
ስለሆነም ዓለም የሚመራበት የየዘመኑ የፖለቲካ መስመር በተጽዕኖው ስር ለማድረግ ቢሞክርም፤ አሻፈረኝ ባይነቱን በዬዘመኑ አይተናል። የኢራኖች በዚህ የ2026ቱ የኳስ ጨዋታ ቤተኝነት ሚስጢሩም ትንግርቱም የፍልስፍናው የአቅም ልቅና ቁልፍነት ያሳያል። ሲሰናበቱ ጹፈው የተውት የምስጋና ደብዳቤ ዝክረ መሰጠትም ነው።
እርግጥ ነው በካታሩም ይሁን በዘመኑ በካናዳ፤ በሜክሲኮ እና በአሜሪካ በሦስት አገሮች በተካሄደው ውድድር ማዕቀብ ያለበት ትውልድ ቢኖርም፤ ማዕቀብ የተደረገበት አገር ያለው ህዝብ ግን ማዕቀብ ቢጣልበትም፤ በእግር ኳስ #ትርታ ውስጥ ይኖራል። ይህ ሃቅ ነው።
ይህ ተመስጥሮ ያለው የእግር ኳስ የአቅም ሞገድ ዘመንን እየታገለ ቤተሰቦቹን ማበራከቱ የዘመኑ የፖለቲካ ባህሬ የሚጭንበትን ጫና ለመመከት ያስቻለው አስገዳጅ ሁኔታም ነው። ጦር ግንባር ሳይቀር ፋታ ሲያገኙ ተዋጊወች፤ #ስርቅ አድርገው የማየት ጉዳይ አይቀሬ ነው። እግር ኳስ ስብከቱም፤ አስተምኽሮውም #ሰላም ነው። የውስጥ ሰላም አመንጭት መስጠት ነው የእግር ኳስ ጥሪው።
#የ2026ቱ የእግር ኳስ ትዕይንት ደራሽ ክስተት።
በካታር ቅድመ የላቀ መሰናዶ፤ የካታር ብሄራዊ የህግ ፈቃድ እና የግሎባሉ ፍላጎት የተገራበት ሁነት እጅግ የሚደንቅ ነበር። የዚህ ዓመቱ ትዕይንት ደግሞ ግማሽ ሚሊዮን ያልሞላ ህዝብ ያለው የካፕ ቤርዴ፤ የኩራሳኡ፤ የኖርወይ፤ ብዙም የማይጠቀስለት የሲዊዝ እግር ኳስ ቲም ያሳየው ሥር - ነቀል የመነቃቃት የብቃት ደረጃ፤ የጀርመን እና የብራዚል ጉዳይ ከተስፋቸው ጋር ሳይገናኙ ቤተኝነታቸው በአጭሩ መቀጨቱ፤ የፈረንሳይ የላቀ ተገማችነት እና የገጠመው ሁነት እራሱን የቻለ ዝክረ ፊፋ የሚያስፈልገው መጸሐፍ ነው። በታሪክ ውስጥ የአርጀንቲና እና የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን በአንድ ሜዳ መታደም ዘመኑን አጉልቶ ጉልላት አድርጎታል።
ሌላው በህፃንነቱ የታቀፈው የያማል እና የአጤው ሜሲ ጉዳይ፤ የያማል የአምስ ዓመት ወንድሙ ፍቅር እና የስሜት ውህደታዊ ትዕይንት፤ የአጤ ክርስትያን ሮናልዶ ስንብት እና መራራ ገጠመኝ፤ የካፕ ቤርዴ ጎል ጠባቂ የ15 ሺህ ዶላር አስይዞ እናቱን የማሳደም ምኞት የተሳካበት ሁኔታ፤ የትንሹ ያማል ክርስትያን ሮናልዶን - ማፔን፤ ሜሲን ለማጽናናት ያደረገው ጥረት ልዩ ፍጹም// ልዩ የሆነ የዘንድሮውን የዓለም ዋንጫ ልብ አንጠልጥሎ ያሟገተ፤ ያስጨበጨበ፤ ቤተሰባዊ ህብረትን የፈጠረ ትዕይንት ነው።
እራሱ የያማል ሥም አወጣጥ እርዝማኔን #ላሚን #ያማል ተከትሎ ውለታን፤ ታማኝነትን፤ ቃልን ያከበረ ሚስጢራዊ ሂደት የሰማንበት አጋጣሚ ዓለማችን ቀንጣውን ታምኝነት ብቻ ሳይሆን #ፍጹም ታማኝ ዜጎች እንዳሏትም ያደመጥንበት #ደግ አጋጣሚ ነበር። የጊዜ ማንነት ርህርህናን አጭቶ እስከ ዓለም ዓቀፍ ተጫዋች የመጠሪያ ሥም እስከ መሆን ያደረሰ ያታላቅነት ስጦታ ነው። እርህርህናን እባካችሁ ቅኖቹ አንሸሸው።
በተለይ አጤ ሜሲ እና ልዑል ላሚን ያማል የተገናኙበት የሜዳ ትዕይንት አባት እና ልጅ በአንድ ሜዳ ይገናኙ ዘንድ ፈጣሪ አምላካችን፤ አላኃችን ያስተማረን፤ የመረመረን፤ የፈተሸበት ታላቅ እዮራዊ የሚስጢር ትንግርት ነው። እኛ በየጨዋታወች እንዲህም እንዲያ ስንል በረቂቅ ሥልጣነ አምላክነቱ የመሰጠት ቅብዓ ሽግግር እንዲህም አለ ብሎ ሲያስተምር ነው።
#ልዩነታችን፤ ክፍፍላችን፤ ማግለል መገለላችን ብኩን እንደ ሆነ፤ ረብ የለሽ እንደሆነ አየን። የፈጣሪ ጥበብ የማይለካ፤ የማይመዘን የማይደረስበትም ስለመሆኑ ህሊናቸውን ከፍተው በማስተዋል ለሚጓዙ የዓለም ዜጎች ሁሉ የመማሪያ ሌሰን ነው። የቅባ ውርስ በማናቸውም ጊዜ፤ በየትኛውም ሁኔታ፤ በየትኛውም ሁኔታ ሊከሰት እንደሚችልም አጤ ዘመን አስተምሮናል።
እግዚአብሄር የፈቀደው፤ አላህ የወደደው ለካንስ የቅብዓ ውርርስ በተቀደሰ ውሃ የፒንጉይ መፈጠርን እንድናስበው አደረገልን። የቆዳ ቀለም የኦርጋናችን መሸፈኛ ብቻ ስለመሆኑ #የፊደል ገበታ እንደሆነ ይሰማኛል። አጤ ሜሲ በስስት እያዬ ትንሹን ላሚን ያማልን የደባበሰበት ማዕዶተ ዩኔስፍ ስንት ዓመት ንጽህናው ተጠብቆ ገኃድ ሆነ።
በሌላ በኩል ከአፍሪካ የሞሮኮ፤ የኢጅብት፤ የሴኔጋል፤ የጊኒ የጋና ወዘተ ድንቅ የብቃት የእድገት እምርታም ሌላው የዘመኑ ተፈጥሯዊ የውበት መግለጫ ሲሆን፤ የብሄራዊ አሰልጣኞች፤ የየአገሩ ክሩወች፤ የሚዲያወች፤ የደህንነት ሁነት፤ የሙዚቃ ዝግጅት፤ የተሳታፊ አገሮች ብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማ፤ ብሄራዊ መዝሙር ክብር እና ሂደቱ በየራሱ ልዩ ጣዕም እና ለዛ ነበረው። የተወዳዳሪ አገሮች ብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማ ከፍታ ለትውልድ ብሄራዊነት፤ የዜግነት ማንነት ባለአሻራ ሂደት ነበር።
ቀደም ብለው የገጠሙ የቢዛ ፈተናወች፤ የዳኝነት ወጣ ገባነት - ጉዳይ፤ የቢጫ እና የቀይ ካርድ የቅጣት ደረጃወች፤ የማለያ ህብረ - ቀለማት፤ በተመልካችነት ከቤተሰቦቻቸው ጋር የተገኙ የልጆች ፍካት፤ ፈንጠዝያ እና ዕንባ ሁሉም ለሁሉም በየራሳቸው መቆም የሚችሉ ትዕይንቶች ነበሩ።
በዚህ ዓመት የውሃ እረፍት መኖሩ በራሱ ቀለል ያሉ ክፍተቶችን እያንዳንዱ ቲም ያርም ዘንድ ዕድል የሰጠ ገጠመኝ ነበር። ሌላው ባለቁ ደቂቃወች የሚመጣ ጥንካሬ እና አቅጣጫ ቀያሪ ግን ተገማች ያልሆኑ የጎል ቁጥር ውድድሮች ልባችን እንደ ቅል አንጠልጥሎ መንፈሳችን የገዛ ገጠመኝ ነበር።
በዓለም የእግር ኳስ ኮከብነት ሳይቀር #የቅጣት ምት መሳት እና የደጋፊ ታዳሚው መከፋት፤ የቅጣት መሳካት እና የአሰልጣኞች ቡረቃ፤ የመደበኛ ጨዋታ ጎል እና በባከነ ጊዜ የሚገቡ ጎሎች ፍጥጫ እና #ርጋነታቸው ዋ! 2026 መልሰን ብናገኝህ ያሰኛል።
#ቅየራ እና ዕድል መጣጣም።
ሌላው ድንቅ ትዕይንት አንዳንድ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኞች ተጫዋቾችን እንደ ቀየሩ በሚገኙ የጎል ዕድሎች የሚገኜው የማስተዋል አቅም ደረጃን ከፍ ያደረገ ሌላው ገጠመኝ ነው።
#የቀይ ካርድ ድንጋጌ።
በዚህ ዘመን ከተከሰተው ሁነት ቀደም ባለው ጊዜ የነበረው የቀይ ካርድ ዕቀባ እና ትራንፒዝም የተገናኙበት መስመር ብዙ ፕሮፌሽናል ኤክስፐርቶችን የአስቆጣ ገጠመኝ ነበር።
#ጥም ቆራጭ ጨዋታ።
የስፔን እና የአርጀንቲና፤ የአርጀንቲና እና የስፔን የዋንጫ ፋክክር ገጠመኙ ይገርማል። በእናሸንፋለን የውስጥ ቀጠሮ አቅዶ ለመጣው የአርጀንቲና ቲም እና የሜሲዝም ትውልድ ሜዳ ላይ የተገናኙበት ሁነት ይገርም ነበር።
በበዛ የማጥቃት ዘመቻ ላይ የተጠመደው የስፔን ቡድን መጨረሻው ሲባረክለት፤ የዕንባ ውስጥነት በአጤ ሊዌኒ ሜሲ የታየበት የመጨረሻው መራራ ስንብት እንደ ሰው በተለይ ለሴቶች "ወንድ ልጅ ብቻውን ነው የሚያለቅሰው" ያለውን አፍሪካዊው የቅኔ ንጉሥ የብላቴ ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን ሚስጢርን የፈተነ ነበር። ሁለቱ አጤወች ለእግር ኳስ አጤ ሜሲ እና አጤ ክርስትያኖ ዕንባማ ስንብት ሆድ ያባባል። አብሮ ማልቀስ የእኛ ፈቃድ ሳይሆን ስሜቱ ፍሉን ማፍሰስ ግድ አድርጎታል።
"…… የብቻ ብቸኝነቱ፥ የጭለማ ልብሱ እስኪደርስ
በዓይን ሃሞት አዋጅ ሃሞቱ እንዳይረክስ
ቅስሙ በገብያ እንዳይፈስ
ተገልሎ በእኩለ-ሌት፥ ወንድ ብቻውን ነው የሚያለቅስ።"
የግጥሙ ሥጦታ ለዘውዴ ሽዋሞልቶት - (፲፱፻፶፭ አምቦ - ኮልፌ
እሳት አበባ መድብል ገጽ 204 የመጨረሻውን ብቻ ነው ያቀረብኩት። ይህን ብያኔ፤ ይህን የተፈጥሮ ሂደት፤ ይህን ጠጣር ቅኔ የፈተነ ገጠመኝ አየን በሜሲም፤ በክርስትያኖም እንደ ማለት። ተብዓት ጥቃትን ዋጥ አድርገው እንዳይዙ የሚፈትናቸው ክስተቶችን ለማጠየቅ የተፃፈ ይመስለኛል።
በአሜሪካ ፕሬዚዳንት ትራንፕ፤ በፊፋ ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ፤ የስፔን ንጉሥ ፊሊፒ 6ኛ፤ እና በርካታ ዓለም ዓቀፍ ዕውቅናን፤ ተጽዕኖ ፈጣሪወች በተገኙበት ትናንት 19/07/026 በሙዚቃ የተጀመረው የ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ሂደት ከጅምሩ እስከ ፍፃሜው በተጠበቀው ልክ በያንዳንዱ ሰከንድ ጥረት፤ ተከታታይነት ያለው ትጋት፤ አሸንፋለሁ፤ አታሸንፍም ፋክክር ሙሉ ሜዳውን ያካለለ ተውኔት ለእኔ በልኩ ለልኩ ሆኖ ቀልብ ገዝቶ በብቃት ተልዕኮውን የተወጣ ፕሮግራም ነበር ማለት እችላለሁኝ።
አርጀንቲናውያን እንደ ማህበረሰብ የድጋፋቸው ልክ መጠነ ሰፊ እና የገዘፈ መሆኑን ተመልክቻለሁኝ። ቡድናቸውን በመደገፍ የማይደክሙ መሆናቸው፤ የነገ ተስፋቸው ስንቅ መሆኑን በሚገባ የተረዱ ስለመሆኑ አይቻለሁኝ። ትውልድ በዚህም መስክ መቅረጽ ስለሚያስችል።
አጤ ሜሲ እንደ አንበል፤ የእራስ ዘብነትም በጥንቃቄ፤ እንደ አሰልጣኝ፤ እንደ ሁለተኛ ጎል ጠባቂ ሆኖ ነው ተግባሩን በጣምራ የሚጀምረው። አራቱንም የኃላፊነት ሁነቶች አስማምቶ፤ ሆኖበትም ይጫወታል። የማይገኝ ጸጋ ነው።
በሌላ በኩል የእግር ኳስ የምርምር ተግባር በቢሮ ብቻ ላይ ሳይሆን፤ ሜዳ ላይም የሚጠበቡት ስፔኖች በግልም በጋራም የተደራጄ አቅም ያለውን የፈረንሳይ ቡድንን ልክ እንደ ቤልጀም የቡድን ጉዞ ስስነት #መበታተን ገጠሞት ነበር የፈረንሳይ ቡድን ከስፔን ጋር በነበረው ግጥሚያ። ስፔኖች የፈረንሳይን የማጥቃት አቅም የደም መተላለፊያ ቧንቧውን እያጠኑ፤ እዛው ላይ ሪሰርች እየሠሩ የፈረንሳይን ቡድን የመከቱበት ሁኔታ ለየት ያለ ጸጋቸውን አይቸበታለሁኝ።
ከደቡብ አፍሪካው የዋንጫ ባለቤትነታቸው ጀምሮ የስፔን ክሩ በመጨረሻ ደቂቃወች የተጫዋች ቅየራ እና ድል ቋሚ ባህላቸው ማድረጋቸው፤ ስልታቸው ለምልሞ መቀጠሉ ለ2026ቱ ህልማቸው ስኬት ብር አንባር ሁኖላቸዋል። በካታሩ ይህን የመሰለ ዕድል ባያገኙም ክፍተታቸውን አስተካክለው የአውሮፓ ሻንፕዮን መሆን መቻላቸው ለዘንድሮው የዓለም ዋንጫ የኮንፊደንስ ስንቅ እና ትጥቅ የሆነላቸው ይመስለኛል።
መጀመሪያው ጨዋታው ሲጀመር ዕይታን #ኒውትራል የማድረግ አቅም ነበረው ለእኔ። ይህም ሆኖ ስፔኖች ሙሉ የጨዋታ ጊዜ በአርጀንቲና መረብ ላይ የፈጠሩት ጫና፤ የአርጀንቲናን ጎል ጠባቂ ሥራ - በሥራ አድርገው፤ ለእነሱ የጎል ጠባቂ ደግሞ የአውሮፓ የበጋ ጊዜ እረፍትህን ዘና ፈታ በል ብለው ፈቀዱለት።
የስፔን ቡድን ገና ጨዋታው በተጀመረ በአራት ደቂቃ ውስጥ ነበር የአርጀንቲናን መረብ በጥዋቱ ያስደነገጡት። ከዛ በኋላም የአርጀንቲናን ቡድን መረብ ቁጥር ስፍር በሌለው የመረብ አስገድዶ የመድፈር ሙከራቸውን አጠናክረው ቀጠሉ። ይህ መረጃ ይሰጥ ነበር ለተመልካች። ማን ሊያሸንፍ እንደሚችል።
አርጀንቲና በባከኑ ጊዚያት ከሞከሩት በስተቀር ፈታኝ የሆነ የግብ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። መጋፋታቸውን አጠንክረው መጀመሪያ በቢጫ በኋላ በቀይ ካርድ ልክ ሲዊዝ እና አርጀንቲና በገጠሙበት ወቅት እንደ ሆነው በጎደሎ ፍልሚውን ቀጠሉት። ያ ድንጋጤ ከባድ ነበር #ለሜሲዝም ትውልድ።
የሁለቱም ቡድኖች ጥንካሬ ጨዋታው እንዲራዘም አደረገው። ተራዘመ። ከዛ ስፔን አሳካ። ስፔን በኒወርክ 106ኛው ደቂቃ ላይ ምጡ መገላገልን ፈጥሮ አዲስ ፏ ፍንትው ያለ የምስራች ዜና አበሰረ። ከስፔን አንድ ጎል በኋላ አርጀንቲና የጥቃት ጎሉ ግሉኮስ ይመስል፤ ሙከራውን አጠንክረው ሲቀጥሉ አቻ በሆነ ውጤት ለፔናሊቲ ይበቁ ይሆን የሚል አዲስ አጀንዳ ህሊናችን ጠበቀ።
ይሄዳል፤
ይሄዳል ይሄዳል
ይሄዳል ይሄዳል ይሄዳል
ይሄዳል ይሄዳል ይሄዳል ይሄዳል
አያ ሆይ ይነጉዳል፤ ምኑንም ሳልከውን አያ ሆይ መጭ ይላል፤ ተፈጸመ።
የትኛው የአዋቂወች መድብለ ግጥም መጸሐፌ ላይ የፃፍኩት እንደ ሆነ ባላስታውሰውም ጊዜው አርጀንቲናዊውን ቲም ጥሏቸው ከነፈ፤ ያን መራራ ስንብት ትውልደ ሜሲ ይቀበል ዘንድ ተገደደ። ያደነቅኩት አጤ መሲን የሁለተኛ ደረጃ የብር ሜዳሊያውን ሲረከብ ያሳዬው ትህትና ልቤ ውስጥ ገብቷል። ይህ ሥልጣኔ፤ ይህ የተሰጠውን፤ የተፈቀደውን አክብሮ የመቀበል ሁነት በየትኛውም ገጠመኝ ያላየሁት የላቀ ዲስፕሊን ነው። ይህ ትውልድን ያስተምራል። በመሸነፍ ውስጥ ትንፋሽን የሚገዛ የሞራል አቅም የማሸነፍም ጸጋ ነውና።
#ሰላማዊ ቀን መመኜት።
ዛሬን ጠብቅልን ብየ በጀርመንኛ ትንሽዬ ሐረግ ጽፌ ነበር። ድባቡ በሰላም ተጀምሮ፤ በሰላም ይፈጸም ዘንድ አስኳላዊ ጉዳይ ነበር። የጨዋታው ፍፃሜ በአገረ አሜሪካ ፕሬዚዳንቱ በተገኙበት ሲሆን አሳሳቢ ነበር።
ሌላው የሰው ልጅ ሊቆጣጠረው የማይችል የተፈጥሮ ድንገቴ፤ የተጨዋቾች ደህንነት፤ የተመልካቾች ደህንነት፤ የተበሳጬ መንፈስ ቢከሰት ወዘተ ያሳሰበኝ ሁኔታ ነበር። በሰላም ተጀምሮ በሰላም መጠናቀቁ ከድል በላይ ለዘመኑ የፖለቲካ ባህሬ ትልቅ ስኬት ነው።
#ነገረ እማፔ።
እማፔ በዓለም የእግር ኳስ ታሪክ ውስጥ በአንድ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 10 ጎል አስቆጥሯል። መሰጠት ነው። ምንምም እንኳን እማፔ የቡድኑ እንጂ የእሱ የወርቅ ጫማ ሊበልጥ እንደማይችል ቢያስተምርም።
በእማፔ ላይ ከፍተኛ የሆነ የተለዬ ጫና አለ። ይህን ተቋቁሞ ለዚህ መብቃት፤ በጎል አስቆጣሪነት መሪነት መታደል ነው። ይህ የብቃት ክህሎት የእሱን የአይበገሬነት ብቃት ያብራራል። መጪው ጊዜ እጅግ የማከብረው ሲዳን አሰልጣኝነቱን ከተረከበ የፈረንሳይ ቡድን ተስፋ ይፋፋል።
ፖርቹጋል፤ እንግሊዝ፤ ጀርመን ወዘተ አገሮች የአሰልጣኝ ዝውውር የፈጸሙም ንግግር ላይ ያሉም እንዳሉ እያዳመጥ ነው። አፍሪካ ላይም እንዲሁ።
የእኔ ዕይታ ለኮከብ ጎል አዳኝ ተጫዋቾች አንበልነት ባይሰጣቸው መልካም በሆነ ነበር። ምክንያቱም የኃላፊነት መደራረብ ጋር ጫና የሚፈጥር ይመስለኛል።
ውስጥ ሆኖ ማኔጅመት የሚጠይቅ ጉዳይ ብቃትን ቢጠይቅም እነሱን ከኃላፊነት አግልሎ በውስጥ ረዳት አንበልነት ፈቅደው፤ እንዲሳተፋ ቢደረግ ጥሩ ይመስለኛል። ይህን በክርስቲያኖ፤ በእማፔ፤ በሜሲ አይቻለሁኝ። የጎል አዳኝነት ጸጋ አንበልነት ሲጨመርበት ጫና የሚያሳድር ይመስለኛል።
#ቅየራ።
የቅየራ ጊዜ ከእረፍት መልስ ቢሆን ይሻላል ባይ ነኝ። ድንገተኛ ነገር ካልተፈጠረ። ለምን? ቀደም ባሉ ጹሁፎቼ አስተያዬቴን ጽፌያለሁኝ።
ከሁሉ ከባዱ ግን የቡድኑን አከርካሪ መቀየር ብዙ ዋጋ ያስከፍላል። ይናዳል ጥበቃው። ይህን መሰል ሁነት በተወሰነ ቡድን አሰልጣኞች አይቻለሁኝ።
ከቤታችን ቁጭ ብለን የእግር ኳስ አፍቃሪወች የጨዋታውን ሂደት እናይ ዘንድ፤ የሐሴቱ፤ የሲቃው፤ የዕንባው ተጋሪ እንሆን ዘንድ ለፈቀደልን አምላካችን፤ አላሃችን ክብር ይገባዋል። ተመስገን።
በሌላ በኩል ለአዘጋጁ ለፊፋ፤ ለአዘጋጅ አገሮች ለአሜሪካ፤ ለካናዳ፤ ለሜክሲኮ፤ ለየአገሩ ስፖርት ፌድሬሽኖች፤ ማጣሪያውን አልፈው ለታደሙ ተጫዋቾች - ለቲሞች፤ ለአስልጣኞች፤ ፍቅር ሆነው ፍቅር ለሰጡ ተመልካቾች፤ ለደህንነት እና ለጸጥታ ሠራተኞች፤ ለቅዱሳን ልጆች ሜዳ ላይ ተገኝተው ሐሤትን ለመገቡን፤ ለሙዚቃ ባለሙያወች፤ ለዳኞች ለሁሉም ምስጋናዬ የላቀ ነው።
እፎይ ብዬ፤ እርፍ ብዬ፤ መንፈሴ ተረጋግቶ እንዳይ ሰውነቴ ፈታ ዘና እንዲል፤ ሐሤትን ለሰጣችሁኝ ሁሉ እጅግ አመሰግናለሁኝ። የሚናፈቅ የሚያጓጓ ጊዜ ነበር ያሳለፍኩት። ተመስገን።
"አድርገህልኛል እና አመሰግንኃለሁኝ።" አሜን።
ኳስን - አትዩ፤ ኳስን አታድንቁ፤ ግሎባላይዜሽንን አግልሉ ለሚሉ ጎድጓዳ ጥሪወች፤ ትውልዱ ዘመን ሰጥ በሆኑ ንጹህ የስልጣኔ ስጦታወች፤ የሰላም መድረኮች፤ የመሳተፍ ሙሉ መብቱን ለማንም፤ ለምንም አሳልፎ ሊሰጥ አይገባም። ሙሉ ተሳትፎ ለማድረግ የየትኛውም አካል ፈቃድ አያስፈልግም። ትውልድ ሆይ! መኖርህን ነፃነት ስጠው። የራስህ እንደራሴ እራስህ ነህና።
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
20/07/026.
ኳሲዝም ይለምልም።
See less
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ