#ገዳይ ሃሳብ በአካልም ይሁን በመንፈስ #በታኝ ነው።

 

#ገዳይ ሃሳብ በአካልም ይሁን በመንፈስ #በታኝ ነው።
 
"እግዚአብሄር ቃየልን ወንድምህ አቤል
ወዴት አለ አለው፤ ቃየልም በልቡ ትዕቢት
የወንድሜ የአቤል ጠባቂ ነኝ አለ።
አቤል ንጹሕ ሰውን ሆነ ቃየል ግን ደግ
ሰው ወንድሙን አቤልን በመግደል
ኃጢያተኛ ሆነ።"
(መጸሐፈ መቃብያን ቀዳማዊ ም ፳፰ ቁ ፬ - ፭)
 
#ምዕራፍ ፲፱።
 
እንዴት አደራችሁ ማህበረ - ቅንነት። 
 
እኔ አቶ ሽመልስ አብዲሳን ኢትዮጵያዊ #ጎልጉል እላቸዋለሁኝ። ግልጽ እና ቀጥተኛ ሃሳባቸውን ማጋራታቸው መልካም ነገር ነው። አይደለም በአገር ደረጃ በቤተሰብ እንኳን ይህን መሰል ግልጽ እና ቀጥተኝነት ጠቃሚ ጉዳይ ነው። ትዕቢታዊ ሁነታቸው ግን ይጎፈንነኛል። መታበይ ወንዝ አያሻግርም፤ ሥልጣንንም አያጸናም። 
 
4ሺ ኢትዮጵውያንን በጋራ አሰባስቦ ያለው አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ረጅም ጊዜ የወሰደበትን ተልዕኮ ለመቋጨት ስምንት በኽረ አጀንዳወችን የያዘ የመወያያ አቅጣጫ አመልካች ሰነዱን ሰሞኑን አስተዋውቋል። የተሳታፊ ቁጥር እየጨመረ ስለመሆኑም እያደየጥኩ ነው። " ኑ በራችን ክፍት ሆኖ ይጠብቃችኋል" የሚል ዕድምታ እንዳለም አንብቤያለሁኝ።
 
የሆነ ሆኖ ከዚህ ጋር በተያያዘ ብልፄው እንደ ፓርቲ ለምክክር ኮሚሽኑ አቀረበ የተባለው ሰነድ ደግሞ በአቻነት ወጥቷል። ከውስጥ የተገኜ መረጃ ይሉታል ዘመነኛ ተጽዕኖ ፈጣሪወች ወይንም የዩቱብ ባለቤቶች። 
 
እንደምን የሚስጢር በር ለእነሱ ቧ ብሎ እንደሚከፈት፤ ለሌሎቻችን ደግሞ ክርችምችም እንደሚል በይገባኝም። የክት እና የዘወትር፤ የቤት እና የእዳሪ ልጅነት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ልሙድ ነው።
 
የኦሮምያ ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ አገራዊ ምክክሩን ተከትሎ፤ ከውስጥ ምንጭ ተገኜ የተባለውን ጭብጥ የሚያቃልል ብቻ ሳይሆን ያለ እርህራሄ የሚደመስስ ንግግር በኦሮምኛ ቋንቋ እንደተናገሩም ተርጉሞ ተደምጧል። ይህን በሚመለከት ሁለት ሚዲያወች ኢትዮ ሰላም ሚዲያ እና የሃሳብ ገበታ የየግላቸውን አስተያዬት ሰጥተውበታል። የሃሳብ ገበታ እንዲያውም ጠንከር ያሉ ስንኞች ተቆርጦ እንደወጣም ተጨማሪ መረጃ ሰጥቷለኝ። 
 
#መታበይ ምኑ ያስቀናል?
 
የእኔ ጉዳይ ህወሃት መራሽ ሥውጣን ላይ ኢህአዴግ በነበረበት ጊዜ የትግራይ የክልሉ ፕሬዚዳንት የአገር መሪነት ስልጣን እንዳለው ያስብ ነበር። ለዛም ነው አማራ ክልልን ጥሶ የአቶ አባይ ዘውዱ ሠራዊት ጎንደር ከተማ ላይ በኮነሬል ደመቀ መኮነን ቤተሰብ ላይ ተኩስ የከፈተው። ያን ችግር በወቅቱ አቃለው ያዩ ነበሩ። ጦሱ ግን ረመጥ ስለመሆኑ ጽፌበት ነበር። ጎንደር ከተማን ለማንደድም በወቅቱ አንድ አጥፊ ቡድን አሰማርተው ነበር።
 
ግን ትዕቢቱ ከመጠን ያለፈ #የድፍረት ኮንፊደንስ በመፍጠሩ የህወሃትን አቅም የፈተነ፤ ሉላዊ ንቅናቄ ፈጥሮ ህወሃት ለ100 ዓመት የነበረውን ኢትዮጵያን አራጦ የመግዛት ህልም በድንገት እንኩቶ አደረገው። መታበይ ሲጥል እንዲህ ነው።
 
የአማራ የማንነት እና የህልውኒ ተጊድሎ ንቅናቄው እንደ ተነሳ፤ የህውሃት አመራር አካላት በአቶ በረከት ስምኦን መሪነት ጉዳዩን ለማርገብ ጎንደር ከተማ ድረስ ሄደው የሚችሉትን ያህል ሞክረው ነበር። በሌላ በኩል በአቶ ልደቱ አያሌው፤ በአቶ በረከት ስምዖን ሌላም አንድ ጨመት ያሉ ሙሁር በተገኙበት አዲስ አበባ ላይም ጉባኤ ነበር። ግን አልተሳካም። መጨረሻ ህወሃት ፈቅዶ እና ወዶ የኢትዮጵያን መንበረ ሥልጣን እንዲለቅ ተገደደ።
 
ዛሬ ህውሃት ያለበትን ሁነት የሚታወቅ ነው። ለህወሃት "የቆጡን አወርድ ብላ #የብብቷን ጣለች" ብሂል በሁሉም ዘርፍ ዕውን ሆኗል። ያ የሚናፍቃቸው አቶ ሽመልስ አብዲሳም በየጊዜው ታሳቢ እጩ አቅጣጫወችን እንደ አንድ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚር በድፍረት ይናገራሉ።
መሰረታዊው የሚናገሩበት አቅም እሳቸው የሚያስቡት የኦሮሞ ብልጽግና መራሽ መንግሥት ኢትዮጵያን ሙሉ እየመራ ነው የሚል ግንዛቤ ነው ያላቸው። ድንበር ዘለል የሃሳብ ሠረጋላቸው ካለ ልጓም የሚሻው ጉዳይ መስመር ይስታል። 
 
አቶ ሽመልስ አብዲሳ፤ የኦሮሞ ብልጽግና ኦርጅናሉን በዕት ኦሮምያን እየመራሁ ነው። ኢትዮጵያን የሚመራት የኦሮሞ ብልጽግና ነው። ይህ ማለት ቀመሩ እኔ ኢትዮጵያን እየመራሁ ስለመሆኑ ያመሳጥራል ባይ ናቸው። ድፍረታቸው፤ ግልጽነታቸው፤ ቀጥተኛ ሃሳብ ገላጭነታቸው #የተንጠራራው ኮንፊደንሳቸው ይህ ነው። ምን አልባት እኔ እና አንተ እኮ እኩል ሥልጣን ነው ያለን የሚል ፍንጭ፤ ወይ ዝንባሌ ይኖር ይሆን ያሰኛል።
 
ይህ አይጠቅም ----- ም። አበክሬ ነው እምናገረው። የሚጠቅም እና የማይጠቅመውን መለየት የመሪ ቀዳሚ መርሆ ሊሆን ይገባል። በዛ ላይ ትዕቢት ፈፅሞ አይጠቅምም። ሥርዓት #አልበኛ ሃሳብ አይጠቅምም። ከተሰጠን በራስ የመተማመን መብት በላይ መወጠረም #ፍንዳት ያመጣል። 
 
አቶ ሽመልስ አብዲሳ ከሱማሌ፤ ከአፋር፤ ከሲዳማ ወዘተ የየክልል መሪወች በላይ በፕሮስጄር ደረጃ ሥልጣን የላቸውም። አፈነግጣለሁ ካሉ አናርኪዝም ነው። አናርኪዚም የሚራራለት ነገር የለውም። ሁሉም የዶግ አመድ ይሆናል። ዘመን ሰጥ ሥልጣንን ቀስ አድርጎ፤ አረጋግቶ፤ መጥኖ በበዛ ቁጥብነት መያዙ ብቻ ጠቃሚ ጎዳና ይመስለኛል። 
 
"ከውሻ ሆድ ቅቤ አያድርም" የሚባል ብሂል አለ። ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ፈቀዱም // አልፈቀዱም፤ ሃሳቡ ተመቻቸው // ጎረበጣቸው፤ ሥርዓትን የጠበቀ አካሄድ የመደቧቸው አካላት እንዲኖራቸው ማድረግ ይጠበቅባቸው ነበር። ግን #ስምምነት ያለ ይመስላል ቸልታውም ይሁን ዝምታው ያስፈራል። ቀን ሲሰበር የቅጽበት ጉዳይ ነው።
 
" ገና እንሰፋለን፤ ኦሮምያ ክልል ይጨመራል። ወዘተ ወዘተ " ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ" ነው። የማህበረ ኦነግ ፍላጎት እና ትልም ይታወቃል። የኢትዮጵውያን ቅንነት ለማህበረ - ኦነግ ልቡን #ቧ አድርጎ ያልተገደበ ፍቅሩን፤ አትኩሮቱን፤ ደግነቱን ሆነ ድጋፋን ሰጠ።
ግን ትዕቢትን ፈጠረ፤ ከመጠን በላይ አገነነ፤ ከመጠን ያለፈ #መስቃም ተደመጠ። ከመጠን ያለፈ በራስ መተማመን ፈጠረ፤ ሁሉም ተችሎ፤ ሁሉም ተፈጽሞ ደግሞ ይቀረናል፤ ገና ምን ዓይታችሁ፤ ምክክሩ ፌክ ነው፤ በአለቀ በተወሰነለት ተግባር ላይ ለፎርማሊቲ ነው ወዘተ አሳዛኝ ትራጀዲ ነው - ለእኔ።
 
የኢትዮጵያ ሊቃናት በብዙ ድካም ውስጥ፤ በብዙ መገለል ውስጥ፤ በብዙ ሙግት ውስጥ ሆነው የብልጽግና ፓርቲ በሰጣቸው የኃላፊነት መስመር ልክ እየተጉ ለሚገኙት የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኖች ይህ እጅግ ፈታኝ ጉዳይ፤ #መሰናክል ሩጫ የሚያስጀምር መለከት ነው፤ በአቶ ሽመልስ አብዲሳ የተነገረው። የእስከዛሬውም የኮሚሽኑ ድካም፤ አሁን ያሉበትም የተግባር ሂደትን ሁሉ የሚያውክ ጭብጥ ነው የተናገሩት የኦሮምያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ። 
 
ሃሳቡ የምክክ ኮሚሽኑ አቅጣጫየ ያለውን ሃሳብ በትኖ የሚገድል ነው። የምክክር ኮሚሽኑ አነሰም በዛ ጥረት #ቃሬዛ ላይ ዋል ብሎ የፈረደ ይመስለኛል። በትዕቢት ውስጥ የመታገስ ለዛ የለም። በማንኽሎኝነት ውስጥ ለህግ ተገዢነት ልሙጥ ነው። ኢትዮጵውያን ይሉኝታ የሚባል ሥርዓት የሚያስዝ ያልተፃፈ ህግችን አካልም አለ። በማህበረ ኦነግ ቀደምት ትውፊት "ጥዩፍ ቢሆንም። 
 
ይህን መሰል ያልተገራ ሃሳብ ብዙ ነገር እንደ ዳንቴል #ይተረትራል። ግን አሁን ላይ የኢትዮጵያ መሪ ዛሬ ማን ነው? መስከረም ላይስ ምን እንጠብቅ ያሰኛል። ጭብጡ የሃሳብ ንደትን ስለሚጣራ። ኢትዮጵያስ ለማይሠራ ተስፋ ስለምን በሌለ ጎኗ ይህን ያህል ወጪ የምታወጣው? አድሮ ጥጃ ለሚሆን የተስፋ ጉዞ ………
 
አቶ ሽመልስ አብዲሳ "አባይ ማዶን ተሻግረን፤ …… አዲስ አበባን ሪለባንት እናደርጋታለን፤ የአሜሪካ የነቀዘ ስንዴ አያስፈልገንም፤ የአማራ ክልል ያለውን የጸጥታ ችግር በሚመለከትም አልቀረባቸውም የጦር መሪ ጄኒራል ማርሻል ለመሆን ሲቃጣቸው፤ እሳቸው እንደ አንድ አገር መሪ ብዙ ጉዳዮችን ደፍረው ተናግረዋል። ምን አልባት በውስጠ ታዋቂ ሁለት መሪ ኢትዮጵያ ይኖራት ይሆን? ለነገሩ ወንበሩ እኮ የቢሮክራሲው ዘርፍ ባዶ ነው። መስክ ተጫኝ መሪነት ነው ያዬነው ሙሉ ስምንት ዓመታት።
 
#ማረም ስለምን አቃተ?
 
የኦሮምያ መስተዳድር ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በየትኛውም አፈንጋጭ ንግግራቸው #ሃግ አልተባሉም፤ እሳቸው ደፍረው በሚንዱት ተስፋ ላይ ማስተባበያ አልተሰጠም፤ መግለጫም አልወጣም።
 
ይህ ማለት የእሳቸው የአገር መሪነት ድፍረት ይለፍ ተሰጥቶታል ማለት ነው። በዝምታ ውስጥ የሚገኘው የኢትዮጵያ ወሳኝ ድምጽ ሳይለንት ማጆሪቲው ምን እንደሚያስብ ማንም አያውቅም። ሲከር መበጠሱ ሲሞላ መፍሰሱ ደግሞ አይቀሬ ነው። አጤ ሂደት በራሱ ጊዜ ያሻውን የመከወን ሥልጣን ስላለው።
 
ከእንግዲህ "የት ሊሰፋ ይችላል ኦሮምያ" የሚለ አዳምጫለሁኝ። ሥልጣን ካለ፤ በዝምታ ውስጥ መቻሌ ሆይ! ምራኝ የሚል ህዝብ ካለ ምን ችግር አለው? ችግሩ ትዕቢት ስኬትን የማያዋልድ ከመሆኑ ላይ ነው።
 
#አዲሷ እና ማንነቷ።
 
አዲስ አበባ ሲነሳ እና የማህበረ ኦነግ ቤተኞች በሚያነሱት #ንደት ናፋቂ ሃሳብ ብዙ ሰው ይደነግጣል። እኔ አልደነግጥም። እንዲያውም ኦነግ ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ ከተደራደረበት፤ ከጸደቀለትም አንዱ ነገረ አዲስ አበባ ሊሆን ይችላል የሚል ዝንባሌ አለኝ።
 
የዛን ጊዜ ለድርድር አስመራ የገቡት ዶር ወርቅነህ ገበየሁ፤ አቶ ለማ መገርሳ ነበሩ። ሲሄዱ ዜና ነበር። ሲመለሱ ዜናው #የውሃ ሽታ ሆነ። ምን ሰጥተው ምን እንደተቀበሉ፤ የድርድሩ መንፈስ ብጣቂ መረጃ እስከ አሁን አልተገኜም። 
 
ያን ጊዜ በሙሉ ጊዜ እከታተል ስለነበር። ብአዴን ለአዲስ አገር ገቢ ካባ እና ክብር በጀምላ ሲያከፋፍል፤ ኦህዴድ ግን ለዘላቂ ዓላማው ስኬት የኦነግ መንፈስን ለማሰባሰብ ጠንካራ ጥረት ያደርግ ነበር።
 
ምክንያቱም ለኦሮማራ ጥምረት ቻሌንጅ ማህበረ - ኦነግ ፈታኝ እንዲሆን፤ ለኦህዴድ የአቅም ምንጭ ይሆን ዘንድ ታስቦ በትጋት ተሰርቶበታል። #ኦሮማራ አፈጣጠሩ አቻዊ ስሜት ነበረው። በውስጥ ታዋቂነት ግን የበላይነት መሻት በኦህዴድ ዘንድ ነበር። ኦሮማራ ያሳካውም የማህበረ ኦነግን የበላይነት ፍላጎት ቁንጮ አድርጎ ብን ትን ብትን ብሎ ቀረ። አሟሟቱ የከፋ ነው የኦሮማራ። 
 
ያን ጊዜ በኢህዲግ ስብሰባ የአዲስ አበባ ጉዳይ በዘመነ ኦሮማራ አጀንዳ እንዲሆን ተፈልጎ ነበር። ኦህዴድ ግን አልፈቀደውም ነበር። ሃሳቡ ውይይት ቢደረግበት በቀጥታ አሰባሳቢውን "ኢትዮጵያዊነት ሱሴ" ያለምንም ቅድመ ሁኔታ #ይበትነው ነበር።
 
ስለሆነም ኦህዴድ እስኪደላደል ድረስ ጥያቄው ተሰውሮ እንዲቆይ አደረገው። ይህ ትልቁ ስትራቴጅም ነበር። የቅደም ተከተል ጉዳይም የውስጥ አጀንዳ ነበር። መጀመሪያ የኢትዮጵያን መንበረ - መንግሥት በብአዴን ድምጽ መረከብ ሊቀድም ይገባል የሚል የጋራ ውል ነበር፤ በኦህዲዶች መንፈስ ውስጥ የጸደቀው። 
 
ዲያስፖራውን ውስጡን ለመያዝም የአዲስ አበባ ጉዳይን ተግ ማድረግ ጠቃሚ ጎዳና ነበር። የአማራ ልጅም ይሁን ብአዴን "ኢትዮጵያዊነት ሱሴ ነው፤ ጣና ኬኛ ላይ" #ፎርሾው ስለነበር፤ የኦህዴድ የስትራቴጂ ትልም በነፃነት ዕድሉ ተሰጠው። አሳካም። ያን ጊዜ የአዲስ አበባ ጉዳይ ጉልላታዊ ጉዳይ ነበር። የሚጠየቁት ግን ብአዲኖች ብቻ ነበሩ። የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችም አንድም ሚዲያ ጠይቋቸው አያውቅም ነበር። አቶ ምግባሩ ከበደ እንደተጠየቁት ሌሎች ሊጠየቁ ይገባ ነበር። 
 
እኔ አዲስ አበባ ከኦነግ አቀባበል ጋር ተያይዞ የቡራዩ ጭካኔ፤ የለገዳዲ ለጋጣፎ ወከባ፤ የሰበታ መፈናቀል እና የኗሪው እንግልት፤ አዲስ አበባ ላይ በአደባባይ በ5 ነዋሪወች ላይ የተወሰደው ነፃ እርምጃ፤ ወደ 1300 የአዲስ አበባ ነዋሪወች ጦላይ መታሰር፤ የግማሽ ሚሊዮን የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪወች ከሱማሌ ክልል ወደ አዲስ አበባ እና ዙሪያ የሚኖሩበት ሁኔታ መደራጀት፤ ባልደራስ ሲመሰረት የጠቅላይ ሚር አብይ ብስጭት፤ አዲስ አበባ ላይ ከብልፄው ፈቃድ ውጪ ሰላማዊ ሰልፍ ባልተፃፈ ህግ መታገዱ ወዘተ ……
 
………አዲስ አበባ ከመስከረም 5/2011 ዓም ጀምሮ አመራሯ በኦሮምያ ሥር እንደሆነ ስጽፈው ኖሪያለሁኝ። የማልደነግጠውም ለዚህ ነው። ሰሞኑን አቶ ጃዋር መሃመድ ያወጣው ሰነድ እኔ ከማስበው ውጪ መሆኑን አዳምጫለሁኝ። ያድርገውም ብዬ ነበር። 
 
በውስጤ ለአዲሷ የመልካም ምኞት ተስፋ ሰጪ ስለሆነ። አቶ ሽመልስ አብዲሳ ግን ያ ፋንታዚ ነው፤ የማይታሰብ ነው ሲሉ የቀደመው የእኔ ዕይታ #ትርታ እንደቀጠለ መሆኑን አዳምጫለሁኝ። 
 
ኦህዴድ የባሰ ቢመጣ በሚል ነው ሸገርን አደራጅቷል። መብለጥ፤ መቅደም። ቀድሞ ተደራጅቶ መጠበቅ በዚህ ሂደት ውስጥ አይቻለሁ። ሊሞግት የሚችለው የኦሮማራ ቤተኛ ደግሞ በአንድም በሌላም አይሆኑ ሆኗል። 
 
ይህን ይህን እያሰቡ እኮ ነው አቶ ሽመልስ አብዲሳ ልክ እንደ #ጠቅላይ ሚኒስተር ሆነው ጠንካራ ሃሳቦችን በልበ ሙሉነት የሚያቀርቡት። የሚናገሩት ደግሞ ሲስተጓጎል አይቼ አላውቅም። 
 
ግን የመንግሥት አወቃቀር ሥርዓት አለው። ማዕከላዊ መንግሥት በአንድ አገር ውስጥ ይኖራል። ይህ ማዕከላዊ መንግሥት አመራሩ #በጥምዝ ከሆነ ግን አጤ ዛሬ አደጋ ላይ ነው ያለው ማለት ነው። ማነው ጠቅላይ ሚኒስተሩ? 
 
በብልፄው ላይ ሙሉ ዕምነት፤ ሙሉ ተስፋ ያላቸው በዚህ ሃሳብ ብቻ ንደት ሊፈጥር ይችላል ሃሳቡ በታኝ ስለሆነ። ሃሳቡ ጤነኛ ሃሳብን ገዳይም ስለሆነ። በታኝም። በሌላ በኩል እስኪ የተያዘ የተረዘዘውን ከመቃወም ይልቅ፤ እራሳችን አጠሙነን በመቻል አቅም የአገራዊ ምክክሩን የመጨረሻ ሃሳብ ጤናማ ከሆነ፤ ከጸጸት ለመዳን በዝምታ ሁኔታውን ሁሉንም እንይ የሚሉም አሉ። ለእነሱ ሁሉ ተነሱብኝ ብሎ የሚቀሰቅስ ሃሳብ ነው። 
 
#የራስ - እንደራሴ።
 
አዲስ አበባን በሚመለከት የኢትዮጵያ፤ የአፍሪካ፤ የዓለም የዲፕሎማቲክ ከተማ ሁለገብ ግሎባል ስለሆነች እራሷን ለማዳን ፖለቲካዊ አቅም ያላት ርዕሰ መዲና ናት። ባልጠራ ውሳኔ ብትንገላታም። ነገ የተሻለ ቀን ይሆንላታል ብዬ አስባለሁኝ።
 
ያገባናል የሚሉ አህጉራዊ፤ ሉላዊ አካላት ስላሉ። ዒላማ ናትና። ትንሽ የኮኦርድኔሽን፤ ተከታታይነት ያለው ትጋት ቢጠይቅም ፓን አፍሪካኒዝም እራሱን ለማዳን መንቀሳቀስ ይችላል። ልባም - ከተገኜ። ለራሱ ለአፍሪካኒዝም እራሱን እንዳያጣ የሚያደርግ ሚስጢር ርዕሰ መዲናው አዲስ አበባ ናትና አትኩረተ አዲስ አበባ ሰብሰብ ያለ ቅናዊ የሃሳብ አቅም ይጠይቃል እንጂ የራሷ እንደራሴ የመሆን ክህሎቷ በመዳፏ እንዳለ ይሰማኛል። 
 
ሌላው በነጋ በጠባ የኢትዮጵያ ህዝብ በብዙ ነገር መወጠሩ ቢታገስለት ጥሩ ነው። መኖሩ እራሱ ፈተና ውስጥ ነው። በአንድ ወር የቤት ኪራይ ከ10 - 15 ሺህ ብር ጭማሬ በማዕከላዊው ነዋሪ ያለው ይሉኝታ ቢስ ገፈፋ፤ በታችኛው ክፍል ይህ ሲሰላ ዳገት እና ዳጡ በራሱ ጊዜ የሚያመጣው አይታወቅም። 
 
ስለሆነም የብልፄው መሪወች በወዘተረፈ ገዳይ እና በታኝ ሃሳብ ከጨማሪነት ቢታቀቡ ጥሩ ይመስለኛል። ዶር ዮናስ ብሩ በተገጋጋሚ የሚያነሱት ሃሳብ አለ። ብልጽግና የሚወድቀው በኢኮኖሚ ድቀቱ ነው የሚል ዕድምታዊ ሃሳብ አላቸው። የሩስያ እና የዩክሬን፤ የሃማስ እና እስራኤል፤ የሆርሙዝ እና የቀይ ባህር መጠነ ሰፊ ችግር ባልታቀደ ሁኔታ መታከል እንደ ኢትዮጵያ ላለ የኢኮኖሚ እድገት አለመመጣጠን + ጦርነትም ያለበት አገር ቀርቶ፤ ላደጉት አገሮችም ፈታኝ ሁኗል - እና።
 
በዛ ላይ ይህን መሰል መፈናፈኛ የሚያሳጣ፤ የመተንፈሻ ቧንቧን ክርችምችም የሚያደርግ የሃሳብ አዟሪት ማቅረብ አቶ አባይ ወልዱን መናፈቅም ነው። ከዚህ ቀደም በአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ህልፈት ተሞካክሯል። በፈጣሪ ጥበብ ወጀቡ ተግ አለ። ………እንጂ የዛን ጊዜ የታገሉ እስር ቤት ናቸው። ከጦላይም የተረፋት ያልተፈቱ የአዲሷ ልጆች እስከ አሁን በካቴና ነው ያሉት።
 
ለማህበረ ኦነግ አቀባበል የዶሮ፤ የፍየል፤ የበግ ደም ሳይሆን የአዲስ አበባ ነዋሪ "እኔ ልሙትለት ከአብይ በፊት ያለ፤" አንድ ያልተደረገለት ለጋሱ፤ ጨዋው የአዲስ አበባ ህዝብ ለሰማዕትነቱ ሰማዕትነቱን ዋጋ ማሳጣት ነበር የሆነው። 
 
በተጨማሪም በተለያዬ ጊዜም ቅኑ ህዝብ ይወቀሳል ይነቀሳል። "ከፍተኛ የኦሮሞ ጥላቻ አለ ይባላል፤ የኦሮምያ ክልልነትን የማይፈልጉም" አሉ ይባላል። ኢትዮጵያኒዝም ውስጡ ለጸደቀ መንፈስ በማህበረ ኦነግ የሚቀነቀነው ሃሳብ አድራሻ የለውም። የኢትዮጵያዊነትን ቁመና ማንበብ፤ መተርጎም እና ማመሳጠር ለአቃተው መንፈስ ሊመስል ይችላል። ኢትዮጵያዊነት አፍሪካኒዝምን የፈጠረ ያደራጄ አንቱ ማንነት ነው። ሲፈቀድለት ብቻ ሚስጢሩ ፏ ፍንትው ብሎ ይገለፃል። 
 
አዲስ አበባ + ጎንደር ሜትሮፖል ከተሞች ናቸው። የሠፈርተኝነት ኩድኩድ ያለ ጥብቆ ማንነት የላቸውም። አፈጣጠራቸው ሰውኛ፤ ተፈጥሮኛ እና ግሎባል ስለሆነ። ባልሆኑበት ማንነት ግን ይከሰሳሉ፤ በየዘመኑ በበቀል ይገረፋሉ።
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
21/07/026.
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
See less

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።