#ይርባል። የተሳትፎ ዕድል ክብርም፤ የስኬት ድልም #ይ---- ርባል።
የዓለም እግር ኳስ እና የኢትዮጵያ ተስፋ እክል።
"አቤቱ የቤትህ ቅናት በላኝ።"
#elfmeterschießen ምዕራፍ ፲፰።
ኢትዮጵያን የሚገልጹ፤ የሚያብራሩ፤ የሚያነቡ፤ የሚጽፋ፤ የሚተረጉሙ ወይንም የሚያመሳጥሩ ክስተቶች ሁሉ #ባለፈተና ናቸው። የሚፈትኖቸው ደግም የኢትዮጵያ ፖለቲካ ነው።
ስሜን ---- ጠል፤ ኢትዮጵያኒዝም -----ጠል፤ የአማርኛ ቋንቋ ---- ጠል፤ የግዕዝ ቋንቋ ---- ጠል፤ ብሄራዊ ሰንደቅ---- ጠል፤ የኢትዮጵያ የአመጋገብ ሥርዓትን፤ የአኗኋር ዘይቤ ---- አቃላይ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶን ሁለመና #አግላይ እና ጭቆና ነው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዘሃ ግራው የተሸመነበት።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ አየር ላይ ተንሳፎ አይደለም የሚሠራው። በባዕቱ፤ በምድሩ፤ በባድማው፤ በመሬቱ ላይ ነው። ኢትዮጵያ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ዕውቅና ባለው ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ያሉ ማህበረ - ህዝብ ወይንም ማህበረሰብ+ የተፈጥሮ ጸጋ እና በረከት በውህደት የሚገኙባት #ሉዓላዊት አገር ናት።
ይህ ሉዓላዊነቷ በቅኝ ገዢወች ተከፍሎ፤ ተሰምሮ የተሰጣት አይደለም። ይህ የሆነበት መሰረታዊ ጉዳይ ኢትዮጵያ የገዛት፤ የነዳት፤ የራሱን ወግ እና ባህል የጫነበት አገር ስለለ ነው። ኢትዮጵያ እንደ ሌሎች አገራት ቅኝ የተገዛች አገር አይደለችም።
ፈላስፊት ኢትዮጵያ #አለኝ የምትለው ያልተቀየጥ ወይንም ያልተኮረጄ፤ ወይንም #የውራጅ ያልሆነ ባህል፤ ወግ፤ ልማድ፤ ታሪክ፤ ዕውቀት፤ ሥልጣኔ ያላት ሁሉም ያላት አገር ናት።
ሳይንቲስቷ ኢትዮጵያ የአየር ባህሬዋም ለጤና የሚታዘዝ ቅዱስ ፈውስ ነው። ወቅታቷ በጋ፤ ክረምት፤ በልግ፤ ጸደይ ተስማምተው፤ ተዋህደው ዘመን ከዘመን በሰናይ የሚንሸራሸሩባት አገር ናት።
ኢትዮጵያ ከአበባ እንኳን አድዮ የሚባል ብሄራዊ የዓዲስ ዓመት የምሥራችን አብሳሪ ያላት፤ በራሷ ቀመር፤ በራሷ አንድ አይሉ ሁለት የፊደል ገበታ #ዘምነን የምትል ዘመናይ አገር ናት።
ኢትዮጵያ #የዜማ ሥርዓቷ በቤተ እግዚአብሄር ግዕዝ፤ ዕዝል አራራት፤ በገኃዱ ዓለም የሙዚቃ ኖቱ ትዝታ፤ ባቲ፤ አንቺ ሆዬ አንባሰል ንድፋ፤ ቀመሩ፤ ዘየው ዕውቀታዊ የሆነ። - ለዛው - ወዙ - ጠዓሙ እና ሳቢነቱ ልዩ ፍፁም ልዩ ነው።
ቅኔው ቃናው፤ ንባቡ ትርጓሜው፤ ዕድምታው ድጓው፤ ምሰጣው ጥሞናው፤ ፆመ ድጓው ዜማው፤ ማህሌቱ ዝማሬው፤ ሽብሸባው የአቋቋም ሥርዓቱ፤ ቅዳሴው ጸሎቱ፤ ስግደቱ ምህላው፤ መንዙማው ዱዋው ተዘርዝሮ የማያልቅ ጥልቅ የሆነ ጸጋ ነው።
የዩንቨርስ ቀደምት ቤተኝነቱ ጥልቅ ዕውቀቱ፤ ገዳማቱ እና ሥርዓቱ፤ ፍትኃቱ እና ተክሊሉ፤ እርቅና ተጠየቁ፤ የሞራል አደረጃጀቱ እና የህግ አከባበር ይትብኃሉ፤ የዓውድ ዓመታት አከባበር እና ህብረ ቀለማቱ ለዓለም ጉልላት ሊሆን የሚችል ነው።
የኢትዮጵያ ፖለቲካው ግን በማንነት #ቀውስ የሚዳክር በመሆኑ ኢትዮጵያ እንደ ቀደምት አገርነቷ እንደ እሷ ከቀደሙት ጋር ቀርቶ በኋላ ከተፈጠሩትም ተርታ ለመሰለፍ ጋዳ ነው።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ በኢትዮጵያዊነት የሚቀና፤ ኢትዮጵያ ባላት የተፈሪነት አቅም #የሚርድ፤ የእሷ መገለጫ የሆኑ ቋሚ ውርስ እና ቅርሷን በመሰረዝ፤ ወይንም በመለጣጠፍ፤ ወይንም በመሾክሾክ "ሥራ ያጣ መነኩሴ ቆቡን ቀዶ ይሰፋል" የሚለውን የሚተረጉም ዓይነት ጉዞ እንሆ ኢትዮጵያ ከዘመን ዘመን ለለት ጉርስ፤ መጠለያ ለከፈን እንኳን ጋዳ የሆነባት አገር ናት --- እንኳንስ የወል አህትዮሽ ጥረትን የሚጠይቀው የእግር ኳስ ስልጣኔ።
ከሁሉ በላይ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ትጋት ያለውን የማስቀጠል አቅም ሳይሆን የነበረውን በማጥፋት፤ በመደርመስ፤ #በማጣጣል ያዬለ መከራ በየዘመኑ ታስተናግዳለች እናት አገር ኢትዮጵያ። አሁን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ጋር ያለው መከራም ተቋምነቱን ሽባ አድርጎ ኢትዮጵያዊነትን የመፈተን ትልም ነው።
ትግሉ ከኢትዮጵያ ጋር ነው። ያልተበረዘ፤ ያልተኮረጄ የጠራ ዊዝደም ያለው ከምንጩ ስለሆነ ነው።
ሌላው ለየትኛው የሥልጣኔ ጉዞ የመንፈስ አለመታወክን ይጠይቃል። ሰላም በኢትዮጵያ የሚንፈቅ ግን የማይገኝ #ሩቅ የሆነ ክስተት ነው። ሰላም ከሌለ ደግሞ ከግሎባል ስልጣኔ ጋር መራመድ ቀርቶ ያለውን #ድህነት ለማስቀጠልም አይቻልም።
ከሁሉ በላይ በኢትዮጵያ #የዛለ ፖለቲካ የኢትዮጵያኒዝም ማለምለሚያ የሆኑ ቅን እና ቅዱስ መንፈሶች በእጅጉ ይፈራሉ፤ ይሳደዳሉ፤ ይዘመትባቸዋልም። በዚህ ውስጥ የብሄራዊ ስሜት ማሰልጠኛ፤ #ማሳለጫ የሆነው የእግር ኳስ እንዴት ይፈቀድለታል?
እግር ኳስ የጠራ የማንነት፤ የብሄራዊ ሰንደቅ መድመቂያ፤ መፍለቂያ ግሎባል ክስተት ነው። ሥልጣኔውን መከብከብ ኢትዮጵያዊነትን መከብከብ በመሆኑ "ሙቱልን! ደግሞ ቅበሩን አትበሉን" የሚል አረም ሃሳብ ተሸክሞ ቅዱሱን እግር ኳስ እንዴት ማሰብ ይቻላል?
የቀደምት ባህል፤ የሥነ ጹሁፍ አቅም፤ የጥበብ ብራና በእጅጉ ይፈራል። አንድ ቀላል ምሳሌ ላንሳ "ፍቅር እስከ መቃብር" ለእኔ አብሮ አደግ ጓደኛዬ ነው። መጽሐፋን ፲፭ ጊዜ አንብቤዋለሁኝ።
በስንት ወጪ ድንቅ ትዕይንቱ ተዘጋጄ። በዘመነ ህወሃት ጧፍ ማዕቀብ ተጣለበት። በዘመነ አብይዝም ያ ሁሉ ድንቅ ድካም፤ ከተማ የመሥራት ልዩ ክህሎት ሁሉ እንዲመክን ተደረገ። ከሁለት ዕይታ በኋላ #ቆመ። ተከለከለ። እኔ ለአዘጋጁ ለአቶ ሰው መሆን ይስማው ሶሚክስ ህይወትም እፈራለሁኝ። የአሞራ እና የንሥር ታሪክ እኮ የጀግናው የአሞራው ውብነህ ቀደመት ታሪክ ስለፈለቀ ነው።
በየፌርማታው መሰናክል አለ። ለምን? ትናንትን ስለሚገልጽ። የቋንቋ ጥራት፤ የቤተ - እግዚአብሄር ሥርዓት፤ የመታመን አቅም፤ የጥልቁ ዊዝደም የተዋህዶ ልቅና በልዕልና ይሄ ትውልድ አይቶ እንዲደመምበት አልተፈለገም። በፍቅር እስከ መቃብር ውስጥ ያለው ጭብጥ እኮ ፍልስፍና እኮ ነው። #የሐዋርያት ተግባርም ነው። ከዚህ አዲሱ ትውልድ እንዲማር አይፈለግም። ከእስያ የመጣ የፒኮክ ክብረ በዓል የበለጠ አደብ ይለገሳል። #ቅናት!
ጠቅላይ ሚር አብይ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት ፋሲል ከነማ የዓጤወቹ ዓርማ ያበበ ተሳትፎ ነበር። እሳቸው ከመጡ በኋላ ተስፋው #ሟሟ።
በህወሃት ዘመን የኢትዮጵያ የፊልም ኢንደስትሪ ማቆጥቆጥ ጀመረ። ብዙ የጥበብ ቤተሰቦች ተገኙ። ዛሬ የለም። ይጀመራል። እንዲቆም ይገደዳል። ተቆራረጠ። ጥበብ፤ ቋንቋ፤ ሥነ - ጹሁፍ፤ ተጨማሪ ተጽዕኖ ፈጣሪ ለማዬት በምን አቅል??? ሥነ - ግጥም፤ የፈጠራ አቅም ተዳፈነ። አርቲስቶች ሁሉ ዛሬ #አወያይ ናቸው። ምን ያድርጉ? የትስ ይሂዱ?
የህወሃት ህገ - መንግሥት #ዜግነትን አያውቀውም። ስለዚህም ብሄራዊ ስሜት የሚፈጥሩ አቅሞች ሁሉ #ተዳፈኑ። ችግሩ በአብይዝም ብቻ ሳይሆን በህወሃቲዝም ዘመንም ነበር።
ኢትዮጵያዊነት እንደ አንድ መጓጓዣ ነው ፖለቲከኞች የሚጠቀሙበት። ስለዚህም ነው ዜጎች ሲያዝኑ #ማጽናናት፤ #አይዟችሁ ማለትን የማይደፍሩት። የተከፋ ዜጎችን አቅርቦ እቅፍን መመገብ ሰማይ ቤት ያለ፤ የማይገኝ ነው።
ስለሆነም ነው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኢሊቶች የሰውን ልጅ ህይወት የማትረፍ ፍልስፍናም የራቃቸው ለዚህ ነው። ይህ ድውይ መንፈስ እንደምን ኢትዮጵያን የሚያጎላትን፤ የሚያስተዋውቃትን፤ የሚያስከብራትን የኳስ ዓለም ብርታት፤ ጥንካሬ ላይ የእሷ አለመገኜት እንዴት ሊጨንቀው ይችላል? ንጹሁ ብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ በዓለም መድረክ ማየት ሆስፒታል የሚያስገባ፤ ድንገታኛ ክፍል የሚውል የሚያሳድር መከራ ነው ለእነሱ።
በማንነት ቀውስ ውስጥ የመጣ ወይንም የሚመጣ የፖለቲካ ፍልስፍና በምንም ታምር ለብሄራዊነት #ጉልበታምነት ፈቃድ አይሰጥም። ከአገር ይልቅ የግለሰብ ሰብዕና ግንባታ ተኮር ብቻ ይሆናል። ኢትዮጵያ የሚለውን የማንነት መጠሪያ ሲሰሙ ጸጉራቸው የሚቆም የካቢኔ አባላት አሉ። አህጉር ላይም ይሠራሉ።
የአፍሪካ ህብረት መሠረቱ #ኢትዮጵያዊነት ነው። ቃናው የአፍሪካ ህብረት የተሰራው በኢትዮጵያዊነት ነው። ብዙወች የአፍሪካ አገሮች ሰንደቅ ዓላማ የኢትዮጵያን መንፈስ የዋጠ ነው። የእኞች ደግሞ ያንገሸግሻቸዋል። ግን አፍሪካ ህብረት በተቋሙ ውስጥ በኢትዮጵያ ሪኮመንዴሽን ቀብረር ብለው ተመድበው ይሠራሉ።
ለአፍሪካውያን ሆነ በዓለም ያሉ ተፈርያውያንን ጨምሮ የጠይም ማህበርተኞች ሁሉ ኢትዮጵያ #ሃይማኖታቸው ናት። በመሬቷ ግን ስደተኛ።
ይህ ሃቅ መታረቅ ካልቻለ በቀጣዩ ጊዜም በግሎባሉ የእግር ኳስ ክስተታዊ ተሳትፎ ሩቅ ይሆናል። በተሠራች አገር ተቀምጠው የተሠራችበትን ንጥረ ነገር ሲንዱ ውለው የሚያድሩ ፖለቲከኞች እስከ አሉ ድረስ። ለዓለም የሰናይ ቋት ኢትዮጵያ ባይተዋርነቷ ይቀጥላል። ምክንያቱም ፖለቲካው ላዕላይ እና ታህታይ መንፈሱ ውስጡ ለኢትዮጵያዊነት ምስጥ ነውና።
ኢትዮጵያ ከወገብ በላይ እና በታች፤ ሰሜን ደቡብ ምስራቅ ምዕራብ ብለህ እንደ ሥጋ ቅርጫ የምትሸነሽነው ማንነት አይደለም። እየጠላት፤ እየተንገፈገፈ ከዛው ከአማርኛ ቋንቋዋ፤ ወይ ከእንጀራው ወይ ከቋንጣው ሲንደፋደፍ ታገኜዋለህ። ዕውነቱ ይህ ነው።
የሆነ ሆኖ ግማሽ ሚሊዮን ህዝብ ያላቸው፤ ከዚህም ያነሰ 150 -158 ሺህ ህዝብ ያላቸው የታደሉ ትናንሽ አገሮች ዕድሉን አግኝተው ስለ አገራቸው ሙሉ የዲፕሎማሲ ተግባር የመከወን ዕድል አገኙ። የተሳትፎ ዕድልም፤ የስኬት ድልም ይ---------ርባል።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
29/06/026.
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
See less
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ