"አለባብሰው ቢያርሱ ባ'ረም ይመለሱ።"


"አለባብሰው ቢያርሱ ባ'ረም ይመለሱ።"
 
"ምህረትህ ከሰማያት
በላይ ታላቅ ናትና።"
(መዝሙር ፻፰፡፬)
 
#ተፈጥሯዊነት ምዕራፍ ፲፱።
 
ማህበረ ቅንነት እንዴት ናችሁ? እኔ አምላኬ ክብሩ ይስፋ ደህና ነኝ።
"አለባብሰው ቢያርሱ ባ`ረም ይመለሱ።" በስሱ ስለ አገራዊ ምክክሩ ዕይታዬ። 
 
ይህ የቀደምቶቹ ቅኒያዊ የትጋት ካፒቴን ሊሆን የሚገባው የአነጋገር ፈሊጥ ነው። አስተውሎታዊ ዘዬው ከግል ኑሮ ጀምሮ ዘለግ ላሉ የኃላፊነት እና የተጠያቂነት እርከን ሐዋርያ ነው።
 
አባባሉ ከእኔ ጀምሮ እኔኑ - ይፈታትሻል። እኛን በጋራ በወልዮሽም --- ይጠይቃል። በአነጋገሩ ዘዬ ለዛና እና ካፒቴንነት ነገን ለማግኜት ከአጀማመራችን ጀምሮ የተቀጣ ትልም ይኖረን ዘንድ አበክሮ ይመክራል። ምክንያቱም ትትርና ስኬትን ካልሰነቀ "ታጥቦ ጭቃ" መሆኑ አይቀሬ ይሆናል። 
 
የአንድ ተቋም የሂሳብ ሥራ ጥራት የዛን ተቋም ስኬት ያውጃል። ውጥኑ ተጣኖ ተጣብቆ ተንጋሎ አንክሶ የተፈጠረ ተቋም ከሆነ የቀመር ስኬቱም በጥዋቱ ጨንጋፊ ይሆናል። አንድ ችግኝ ለመትከል ይቀላል። የሚተከልበት ቦታ ለቡቃያው ምቹ መሆኑ ሳይረጋገጥ፤ ሳይመረመር ከሆነ ግን ችግኙ የተተከለበትን የ30 ቀን ልጅነቱን ሳያሳካ ይጠነዝላል። 
 
" አለባብሰው ቢያርሱ ……… " ከሁሉም በኃላፊነት የሚገኙ አካላት ቤተሰብ ከማስተዳደር አገር እስከ መምራት ላሉ ዜጎች ሁሉ መሠረትህን አሳምረህ ተነሳ፤ ፍፃሜይ እንዲያሰብል በማለት #የሰላ አቅጣጫ ይነድፋል።
 
የአነጋገር ዘዬው የነገ ስኬት ዛሬ በሚቋጠሩ ብቃት እና ጥራት ባላቸው ሁነቶች ሊወሰኑ እንደሚችሉ ይነግራል። የፈላስፊት ኢትዮጵያ ዘዬ፤ የአነጋገር ፈሊጥ፤ የአስተምህሮ ቅየሳ አንቱ ነው --- ና።
 
የአማርኛ ቋንቋን የለማ፤ የተባ፤ ድርጁ እና ብቁ የሚያደርገውም ይህን መሰል አጋዥ እና መሪ የአሰትውሎት ቀያሽ ንድፎችን #የተጠበበ #ሥልጡን እና ክህሎት ዘለቅ ስለሚያደርገው ነው።
 
ኢትዮጵያ ኮሚሽን በማቋቋም መቼም በዚህ ፰ ዓመታት ባለሪከርድ ናት። ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ መድብለ የኃሳብ ክህሎት ሊያስገኝ ይችላል ተብሎ ይታይ ዘንድ በርካታ ኮሚሽኖቹን ሾሙ። ግን " አለባብሰው ቢያርሱ ባ`ረም ይመለሱ ሆነ እና ሳያዘሩ፤ ሳይበቅሉ ከእሳት እንደ ገባ ፕላስቲክ ኩምሽሽ ብለው ቀሩ።
 
እሳቸው ጠቅላዩ ያሳኩት ፖለቲካዊ ዕድምታ ይኖራል።
1) ከሊቅ እስከ ደቂቅ ፖለቲከኞችን የማማከል ሁነት ---የማስተኛት ፖሊሲ፤
2) የቀደመ የፖለቲከኞችን ስንቅ እና ትጥቅ የመቦረሽ ወይንም የመበወዝ ትጥቅ የማስፈታት ስልት፤
3) የማዘናጋት ስልት፤
4) ወይንም አዳዲስ የሃሳብ አሉታዊም ይሁን አወንታዊ ጭብጦችን የማግኜት ዕቅድም ሊሆን ይችላል።
4.1) አሉታዊ ያልኩት ብዙም የማያውቋቸውን የፖለቲካ ኢሊቶች ምልከታቸውን ከውስጥ በማግኜት፤ አቅርበው የሚያዘልቁትን ወይንም አቅርበው #የሚያርቁትን መለያ ማንዘርዘሪያቸው አድርገው ተጠቅመውበት ሊሆን ይችላል።
4.2 ) ለወቅቱ የሚዲያ ፎርማትም ጥሬ ዕቃ ማቅረቢያ አድርገው ለመጠቀም የሃሳብ ማሟሟቂያ ነበር። ለወቅቱ። እኔ በደመነፍስ ታቅዶ፤ ተበተነ የሚል ግምት ስለለኝ።
4.3 ) አወንታዊ ያልኩት ግን የሃሳብ እጥረት እንዳይገጥማቸው የሃሳብ ማሰባሰቢያ ጎተራ አድርገው ለመጠቀም አስበው ይሆናል። ብቻ የአብይዝም ኮሚሽን በበላዩ ሌላ ሲዳርበት --- ሲኳልበት - ሲለጣጠፍበት ቆይቷል። የካርቶን ፊልም መሰል ነገርም ነበር።
 
ለምሳሌ ……
 
( ከማንነት ጋር የተያያዘ ብሄራዊ ኮሚሽን እያለ የሰላም ሚኒስትሯ ይመሩት የነበረ ፰ አካላት ያሉት ነገረ አዲስ አበባን ብቻ የሚመለከትም ስብስብ ነበር። የሚገርመው በስብሰባ ሥርዓት እና ህግ መሠረት ጎደሎ ቁጥር የግድ ሲሆን ፰ ግን ግራ የሆነ ገጠመኝ ነበር። ፕሮሲጀራሊ አደናጋሪ ነበር። የሰብሳቢን ሚና የሳተ) ብቻ የኮሚሽኖቹ ሂደት ባለበት ጸጥ እረጭ አሉ። ወደ ላይ ይረጉ ወይንም ወደ ምድር ይስመጡ ውሾን ያወሳ ውሾ …… በዚህ ውስጥ፤ አቅም፤ ጊዜ፤ መዋለ ንዋይ እና ተስፋም #ገውለል ሳይሉ አይቀሩም።
 
ከኮሚሽኖች ክስመት በኋላ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን መውሊድ ሆነ። ለእኔ ምርጫ ሳይሆን ፖለቲካዊ #ምደባ ነው ብዬ ነው የማስበው። ይህ የሆነበት ምክንያትም የመሥራቹን የፈቃጁን የብልጽግና #ኮፒራይት {© }ለማስጠበቅ ነው ብዬ አምናለሁኝ።
 
በአመሠራረቱ ላይ የነበሩ ጥያቄወች ትክክለኛ መልስ ሳያገኙ ነበር ኮሚሽኑ ሥራውን የቀጠለው። ይህ ከመግቢያ በሩ ጀምሮ የኢትዮጵያ ታላላቅ የተከበሩ ሊቃውንታት + ተመክሮ + ክህሎትን ፈታኝ የሆነ ታዕማኝነቱን ያሳሳዋል። ተቀባይነቱንም --- ይታገለዋል። 
 
ተስፋ እንዳይሰነቅበት የሆነውም በዚህ ይመስለኛል። #አጓጊነቱም የዛኑ ያህል ብልጭ ድርግም የሚል ነው። ኮሚሽኑ የመደበውን፤ ሹመት የሰጠውን፤ በጀት የመደበለትን ፍላጎት ከማስፈጸም ውጪ ዕድል ሊኖረው እንዴት ይችላል? እራስን በራስ መታገል ወይንም መቅጣት።
የኮሚሽኑ የሥራ ዘመን ሲያልቅም በጀት ጨማምሮ የሚያራዝምለት አቤቱ ብልጽግና ነው። ስለሆነም ኮሚሽኑ በራሱ ትንፋሽ ውስጥ ሆኖ የአብዛኛውን ኢትዮጵያዊ የልብ አድርስ ተልዕኮ ሊያሳካ ይችላል ወይ? 
 
#ሰሞንኛው ጥድፊያ። "ሱሪ ባንገት" ይሉታል ጎንደሬወች። 
 
ሲያስፈልግ ፌዝ፤ ሲያሰኝ ቦዝ፤ ሲልም ጥድፊያ ……… ብቻ፤ አወን ብቻኮሚሽኑ የ፯ኛውን አገራዊ ምርጫውን የምሥራች አብሳሪ ዓይነት የሆነ ይመስላል። የምርጫው መጠናቀቅ ተከትሎ የተሰናደለትን የጊዜ ሰሌዳ ተከትሎ ወደ መቋጫ አድራሽ ሁነቶች ላይ እንዳለ እየተደመጠ ነው።
 
የምክክር ኮሚሽን መፈጠሩ፤ መወጠኑ በእኔ ዘንድ #አወንታዊ ነው። የሃሳቡ ጥንስስ የማንን ፍላጎት ያሳካል የሚለው ይመስለኛል አመክንዮዊ ጉዳይ። ኮሚሽኑ የአገር ውስጥ በቻለባቸው ቦታወች፤ ከግልም የፈቀዳቸውን ጥያቄወች ተቀብሎ ሊሆን ይችላል፤ ግን ባልደረሰባቸው ቦታወች እያሉ ሙሉዑነት ሊያገኝ ይችላል ወይ? 
 
ለምሳሌ ዲያስፖራ ላይ የተወሰኑ አካባቢወች ላይ ተገኝቶ ውይይት አካሂዷል። ግን በጣም ጎደሎ ነው። እኔን አሜሪካ የተካሄደ፤ ሲዊዲን የተከወነ የሃሳብ መንሸራሸር አይወክለኝም። እኔ ባልገኝ እንኳን ሲዊዝ ያሉ የጨመቱ ወገኖቼ ቢሳተፋበት ስፕሪቱ በአንፃራዊነት ወጥ ባይሆን ተቀራራቢ ስለሚሆን ይወክለኛል ልል እችላለሁኝ።
 
ሌላው ሲዊዘርላንድ፤ ኦስትራሽ፤ ኒወርክ ያለው የየአገሩ በዲፕሎማሲ ጠረን ብቃት፤ ልቅና ተመክሮ ይለያያል። ያን ዕውነተኛ ጠረን ለማግኜት ከቦታው ተገኝቶ ዕድሉን ከፍቶ ከዛ የሚኖሩ ኢትዮጵውያንን ማነጋገር፤ ማወያዬት እንደ ዜጋም የማየት ሁነት ቢፈጠር ይበጅ ነበር። የዜግነት እኩሌታ፤ የዜግነት የክት እና የዜግነት እርቦ እና ሲሶ ወይንም የዘወትር ስለለው። 
 
እርግጥ ነው ኦስትራሽ ያለ ኢትዮጵያዊ ሚዲያ አዘጋጁ ልጅ ሞገስ ዘውዱ ሃሳቤን ልኬያለሁ ሲል አዳምጫለሁኝ። ምን አልባት ለእሱ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይችል ይሆናል፤ በምሥረታው ላይ እኔ የግሌን መልዕክት ልኬ መልስ አላገኜሁም። ስለበዛባቸው ይሆናል ብዬ ተውኩት። በዚህ ውስጥ ለእኛ ኢትዮጵውያን ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ሊቃናትም ይሁን ተጽዕኖ ፈጣሪወች ይልቅ የውጭ አገሮች ምቹ እና ደልዳላ ምላሽ ይሰጡናል። 
 
የሆነ ሆኖ እያንዳንዱ አገር በአኗኗር ዘይቤው፤ በሜንታሊቲው፤ በሥነ - ምግባሩ፤ በሞራላዊው ኤቲክስ ይለያያል። ከሌላ አህጉር እና አገር የሚመጡ የራሴ ቤተ - ዘመዶቼ ጋር ያለንን ልዩነት እኔው ዳስሼዋለሁኝ። ለዚህ ነው የሌላ አገር ወገኔ ያገኜው ዕድል እኔን ሊወክል አይችልም የምለው። ስለሆነም ሙሉዑ የሚለው #ወላዊ አመክንዮ የምክክር ኮሚሽኑን ሚና ፈታኝ ያደርገዋል። 
 
በሌላ በኩል የንጹሁ የገራገሩ #ገበሬ ውስጥነት ሰፊ እጅ ያያዘው ማህበረሰብ ጣዕም፤ ቃና፤ ዕውነት፤ ቅንነት እና ገራገርነትም በተፈለገው ልክ አለመካተቱም ሙሉዑነቱን በእጅጉ ዳጥ ያደርገዋል።
 
ከዚህ ጋር አያይዤ የማነሳው ጉልላታዊ አመክንዮ እስር ቤት የሚገኙ ሊቃውንታት ያለመካተት ጉዳይም ጠንካራው ፈታኝ አመክኗዊው ጉዳይ ይመስለኝ። ጥረቱን #ግንጥል ጌጥ ያደርገዋል። የተፈናቀሉ ኢትዮጵያዊ ወገኖቻችን ጉዳይስ??? 
 
ይህ ለነገ መፍትሄ ከማፍለቅ ይልቅ ወጣ ገባ ቀጣይ ፈተና ጠንሳሽ ይሆናል። ቀድሞ ነገር የኮሚሽኑ አፈጣጠር #ተፈጥሯዊ ቢሆን እኮ ከፋኝ ብለው ኢትዮጵያዊ ዜጎች ጫካ- ለጫካ የሚያባትላቸው ምንም የዕውነት ጓል አይኖርም። ተስፋ ሲኖር ከተስፋ አይሸሽም። ይልቁንም ወደ ተስፋ ይገሰገሳል እንጂ።
 
ለተስፋ ጥግ፤ ለምኞት መጠለያ፤ ለራዕይ ታአማኒ አካል ካለ ሰላማዊ ህይወት ተመራጭ መሆኑ እሙን ነው። ከዚህ አንፃር የሰላም ሚር በስንት መዋለ ንዋይ ፍሰት ተደራጅቶ ስኬቱን መመዘን ነው። ሰማዕትነቱ፤ ውድመቱ፤ ድቀቱ ሲታሰብ ተቋሙ #ባይፈጠር ይሻል ነበር ያሰኛል። ሙቶ እንደ ተፈጠረ ነው እኔን የሚሰማኝ። ኪሳራ ስለሆነ።
 
መቼም የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንዲህ ነህ፤ እንዲያ ለማለት አይቻልም። ወዘተረፈ ጥልቅ እና ውስብስብ ችግር ነው። እራሱ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ፤ ኢትዮጵያዊ ማንነት፤ ኢትዮጵያዊ ተቋማት ሁሉ የሚሸሹበት፤ የሚፈሩበት አመክንዮ እራሱን የቻለ የእኛው ገመና ነው። ሁሉ ነገር በጥላቻ እና በግለት፤ በአሉታዊ እና በሽፍንፍን የተለጎመ ነው።
 
አሁን ከሰሞኑ የአቶ ሌንጮ ለታ የልጃቸው የአማርኛ ቋንቋ ማወቅን ለማስቀረት ቀድመው የወሰዱት እርምጃ እና ያ የሚጸየፋት ቋንቋ ዕውቅና አግኝቶ በአማርኛ ቋንቋ መጸሐፍ የተፃፈበት የማንነት ቀውሱ በአንድ ሰብ ውስጥ ሲታሰብ ውሃ ያዘለ ተራራ ነው። 
 
ኮሚሽኑ የተሰጠው ኃላፊነት እና ያለበት የተጠያቂነት ደረጃ መጠነ ሰፊ ነው። ለእያንዳንዱ፤ በየጓዳው #የህሊና አብዮት የሚጠይቅ ነው። ይህን መሰል ቅይጥ፤ ድብልቅልቅ ችግር ለመፍታት ከአመሠራረቱ ይሁንታው ቢያንስ 90% ሊሆን ይገባ ነበር።
 
የችግር የአፈታቱ ዘዴ ደግሞ እንደ ገና #ጎድጓዳ ከሆነ ተመልሶ የእኛ ነገር ገደልማ መሆኑ ያሰጋል። ተስፋ ስንቁ ዕውነት ነው። ተስፋ ስንቁ የሃቅ ማሳ በርግጥም የማግኜት ዕድሉ ነው።
 
ኮሚሽኑ የተቋቋመበት ዓላማ እና ህወሃት ያጸደቀው ህገ መንግሥት የዘመን፤ የአካሄድ ልዩነት ሊኖረው ቢችልም ግን የህሊና ጥያቄን ፈቶ ወህ የሚያሰኝ፤ አንፃራዊ ሰላም ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ያውጃል ብሎ ማሰብ ይከብዳል።
 
አንድ ዘንበል ያለ እንሥራ ውሃው ዘንበል ባለበት አቀጣጫ ይፈሳል። አወቃቀር፤ አደረጃጀት፤ አፈፃጸም መሠረቱን ይከተላል። መድከም ካልቀረ ታሪካዊም፤ ክስተታዊም ሊሆን የሚችል ንድፍና ክንውን ቢሆን ነገ ተስፋ ሰንቆ የመምጣት ተስፋ ይኖረው ነበር። ግን ገንግኖ ግንን አምጦ ከወለደ ግን እራሱን እያራባ ይቀጥላል።
 
፲ ዓመት የሥልጣን ዘመን ቀመሩ ከ፰ኛው ምርጫ ጀምሮ ይሆናል፤ 2013 ዓ.ም (5) + 2018 ዓ.ም (5) ከ2010 ዓ.ም- 2013ዓ.ም በድምሩ 13 ዓመታት አይቆጠሩም። ሌላ ሁለት 10 ተጨማሪ የሥልጣን ዘመን ችሮታ በህግ በደንብ ተገንዞ ይከወናል። 
 
በዚህ ውስጥ ሌላ አቅም ያለው ትንታግ ወጣት ለ23 ዓመታት ከአገር መሪነት #ውጭ ይሆናል። ኢትዮጵያም ከአንዱ ልጇ ያገኜችው ብቻ ሳይሆን ከሌላ ልጇም አዲስ ክህሎት ራዕይና ትጋት ትፈልጋለች። ዕድሜ ያልፋል፤ ሞትም ይከተላል። ከዚህ በኋላም ሁሉ በእጁ ያለ አካል አዲስ ኮሚሽን ፈጥሮ ደግሞ ህጉን ቢያሻሽል ማን ጌታ ይኖርበታል። ነገ የሚነገረን የሥልጣን ዘመንም እርግጠኛ የሚያደርግ አይደለምና። ………
ሌላው ተጠባቂው ጉዳይ #ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ወዘተ ……… ታቅዶ ይከወናሉ። መንፈሱ ገዢ ፍላጎቱ የማን ሊነግሥ እንደሚችል ተንታኝ አያስፈልግም። በኮሚሽኑ አፈጣጠር ላይ ጥራት ያለው፤ አሳታፊ፤ ነፃ እና ማዕከላዊ ሁነቶች ተፈጥረው ቢሆን ኖሮ የአብዛኛውን ጥያቄ መላሽ ስለሚሆን፤ ጥቂቶች ለብዙኃን ፍላጎት መገዛት የማያቅት ፋክት ይሆን ነበር። 
 
እኛም በአገራችን ጉዳይ በነፃ የምንተጋ ወገኖች ዘላለማዊ እረፍት ሰንቀን ወህ እንል ነበር። አሁን ግን ያልተቋጨ የተጠቀለለ ቻሌንጅ ኢትዮጵያን እያፈናት ስለመሆኑ እያሰብን ወህታ አይታሰብም።
 
አንድን ዕውነት በዲኮሬሽን፤ በፌስታ ይሁን በፈንጠዝያ ብዛት ፋክቱን አይፈቀፍቀውም። ወይንም አያሳጣውም። አንድን ዕውነት በተፈጥሯዊ ውበቱ የተነሳ ፋክቱን አያጣፋውም። ዕውነት ጊዜ ሰጥቶት ራሱን ሲገልጥ ዕውነት ሆኖ ነው። አይቀያዬጥም። ዕውነት ምንም ክንብንብ ስለማያስፈልገው። በሌላ በኩል ዕውነት ፕሮፖጋንዲስትም ይሁን ካድሬ አያስፈልገውም። ዕውነት ወጌሻ አያስፈልገውምና።
 
የኮሚሽኑ አካላት ወግ ደርሶት ዲያስፖራው፤ ዜጋ ነህ ተብሎ፤ ሃሳብህን እናዳምጥ ሲባል፤ የሚችል በዕድሉ መጠቀም እና በኦርጋኒኳ ኢትዮጵያ የሞራል ልዕልና ልክ ብስጭትን ገርቶ በፋክት፤ በዕውነት መሞገት ሲቻል፤ ያዬሁት ነገር አልወደድኩትም። 
 
የኢትዮጵያ ሊቀ ሊቃውንታት ያመኑበትን የመከተል፤ የማገዝ፤ ወይንም የመቃወም ነፃነታቸውን መጠበቅ ስለ ነፃነት የምኔታገልለትን ዕውነት ያበራዋል። ተቀናቃኝ ከሆን ግን ዓላማችን እኛው እራሳችን እየታገልነው መሆኑን ያመለክታል። ከሁሉም አክሰሱ ላላቸው ታዳጊ ወጣቶች ሥነ ልቦና ጥንቃቄ ልናደርግ በእጅጉ ያስፈልገናል። 
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
27/06/026.
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ዕውነት ጊዜ ሰጥቶት እራሱን ሲገልጥም #ዕውነት ይሆናል። #አይቀያዬጥም
See less

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።