#ትዕግሥት ሲያልቅ ፍቅር ይሰደዳል። #ፍቅር ሲያልቅም ትዕግሥት ይሰደዳል።
"ዳዊትም ሰው ከንቱን ይመስላል፤
ዘመኑም እን ጥላ ያልፋል፤ እያለ
ስለእሱ ተናገረ።"
(መጽሐፈ መቃብያን ምዕራፍ ፱ ቁጥር ፳፫)

#ምዕራፍ ፲፱።
ትዕግሥት ሲያልቅ ፍቅር ይሰደዳል፤ ፍቅር ሲያልቅም ትዕግሥት ይሰደዳል። በህወሃት መሸኛ ዘመን እጠቀምበት የነበረ አገላለጽ ነው። የሆነ ሆኖ አብን የሚሊዮኖች ድምጽ ሆኖ ወጥቶ፤ ያን ኃላፊነት እና ግዴታውን የተወጣበት መንገድ ግን ተስፋ ሰጪ አልነበረም።
ሥልጣንን በሚመለከት አንድ የፖለቲካ ድርጅት የሚታገልበት በኽረ ጉዳይ ስለሆነ ለጋሱ ብልፄ ያቀረበለትን ገጸበረከት ይሁንታ ሰጥቶ መቀበሉ ለእኔ የሚጎረብጥ አልነበረም።
ግን መነሻውን ከመድረሻው ለማዋህድ የተከተለው መስመር ግን ለአማራ ይሁን ለኢትዮጵያኒዝም የተስፋ ሂደት #እክል ነበር። ለብልፄ ብሎ አላስፈላጊ ቅራኔ ሁሉ ይገባ ነበር። ሁልጊዜ ከህውሃት ("ትህነግ") ጋር የነበረው አቲካራ አላስፈላጊ ነበር።
አንድም የአማራ ጥያቄን የማስመለስ አቅምም አልነበረውም። በሌላ በኩል እሱ ያመነበትን መንገድ የሚከተሉ አማራወችን የማግኜት ዕድሉም ስስ ነበር። ስለሆነም ብልፄው የአማራ ህዝብን አራጦ ለመግዛት ዕድሉን አብን የማመቻቸት ዕድል ለብልፄ ማጉረስ አልቻለም። የተወሰኑ የአብን አመራሮች ህይወትን የማሻሻል ነገር እንደ ትርፍ ካየው ይሁንለት።
የሆነ ሆኖ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ለጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ #የበኽር ልጃቸው ነው። ለትውልድ እንዲሆን አድርገው በሚገባ አደራጅተውታል። እኔም እከታተላቸው የነበረው ከዛ አንፃር ነበር። ልዩ ጊዜ ያሳለፋበት በኢትዮጵያኒዝም መንፈስም ያ የማይገኝ ጊዜ ይመስለኛላ ለሳቸው። ተወዳጅ እና ተከባሪ ተደማጭ አለቃም ነበሩ። ያን ጸጋቸውን ጠቅላይ ሚር ሲሆኑ #ስደት ላኩት።
ብቻ አወን ብቻ ወደ ጠቅላይ ሚኒስተርነት ሲመጡ #የልቤ ለሚሏቸው ሁሉ በአደራ የሚሰጡት የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ነው። ሥሙን ቀይረውታል። ግን መንፈሱ እሳቸው በነበሩበት እና በተጉበት መንፈስ እንዲቀጥል ለልብ ወዳጃቸው በአደራ ይሰጡታል።
አብን የተሰጠው ቦታ ይህ ነበር። ምርጣቸው ስለሆነ። እና #ንስርን ዓርማው ያደረገው፤ ሰዓትን የምርጫ መወዳደሪያው ያደረገው አብን ከአማራ ህዝብ ጥያቄ እና ፍላጎት ጋር በምን ያህል እንደተቀራረበ፤ ወይንም እንደራቀ እራሱ ይገምግመው። በውነቱ እኔ አብን እና ባልደራስን ረስቻቸዋለሁኝ።
"አገራዊ" የምክክር ኮሚሽኑ ጉዳይ በሚመለከት ብልፄው ፈቅዶለት ይሁን፤ በአማራ ህዝብ የተራቆተውን ተቀባይነቱን ለማደስ፤ ወይንም በአዲሱ የካቢኔ አደረጃጀት ቦታውን የማጣት #ሹክታ ገጥሞት ይሁን ሙግቱን ቀጥሏል። የዛሬው ለስለስ ያለ መንፈስ ያለው ይመስላል።
በጣም አሳዛኙ ገጠመኝ አንድ አፍታ ከፋኖ ጋር ለማገናኜት የሄደበት መንገድ ነው። ከኢትዮጵያኒዝም ወደ ኦነግ ፍላጎት ሲያማትር ዝም የተባለው ልጅ አማን አብን ከፋኖ ጋር ለማለካለክ ፈልጓል። ቢፈልጉ ጫካው እኮ ቅርባቸው ነበር።
ማን አገዳቸው? ሽንጣቸውን ገትረው ብልፄው ሆነው ነበር ሲሟገቱ የቆዩት። ለዚህም ነው በአማራ ህዝብ ዘንድ የተረሱት። ብዙ ክብር እና ማዕረጋቸውን ያጡት ስለ ብልፄው ነው። ያልተመቸን ሃሳብ በሥርዓት ማቅረብ ተደፍነህ፤ ተቆልፈህ ኑር ፋሺዝም ነው።
ቀድሞ ነገር የማስተር ፕላን ጥያቄ እንጂ የቄሮ ንቅናቄ #የአዲስ አበባ ጥያቄ አልነበረም። ሁላችንም የነበርንበት፤ የሞገትንበት፤ በጥረት በሙሉ አቅም #ለስኬት ያበቃንበት ሂደት ነው የነበረው። ልጅ አማን እሱም የዱር ቤቴ ቤተኛ ነበር። ይህን አውቃለሁኝ። እሱ አልነበረም የሬቻ ጭፍጨፋ ዓለምዓቀፍ ዕውቅና እንዲያገኝ ያስደረገው። የአማራ ልጆች ነን።
በእኛ ስለቀረበም ጭፍጨፋው ምስክርነት ነው ግሎባሊ ዕውቅና ያገኜው። ዝመታችን ይከበር። ውዳሴ ከንቱ ስለማንሻ ነው። የእኛ ከብረት ቁርጥራጭ የተሰራ ጥንካሬ፤ ትጋት፤ ተከታታይ ትጋት ብልህነት የህወሃት ሊቃናትም ሳይጎዱ፤ የኢህአዴግ አመራሮችም ሳይጎዱ ሰላማዊ ሽግግር ይከወን ዘንድ ብልህነት በዊዝደም ተጠልፎ እግዚአብሄር መርቶ ነው ለዚህ ተበቅቷል። ብዙ መንጠራራቶች ባይኖሩ፤ ብዙ መለጠጦችም ባይኖሩ ምርጫዬ ነው። የሰው ምንም አይደል የእግዜሩ ይፈራ። ማተቡ ካለ ወይ ከኖረ።
ጠቅላይ ሚር አብይ የቄሮ የማስተር ፕላን ትግልን ወደ ስኬት ያበቃው "የኦሮሞ ደም ደሜ ነው" የሚለው ንቅናቄ ለድል እንዳበቃቸው አምነውበታል። ይህን እኛ ጎንደር ያለው ኦሮሞ ነው የሠራው ነው ሲሉ አድምጫቸዋለሁኝ። ይህን የኮፒ ራይት #ሽሚያ ዝም ብዬ ነበር ያለፍኩት። በዓለም ዓቀፍ የታሪክ መዘከር ያለ የተመዘገበ ጉዳይ ስለሆነ። ታላላቅ በ100 ዓመት የማይገኙ የዓለም ሊቀ ሊቃውንታት በትጋት፤ በልዩ አትኩሮት፤ በምክክር በፈጣሪ ጥበብም የተገኜ ስኬት ነበር።
ጠቅላዩ ላነሱት ሃሳብ እግረ መንገዴን መግለጽ እሻለሁኝ። ኦሮሞ አዋሳ፤ ኦሮሞ አፋር፤ ኦሮሞ ቤንሻንጉል ጉምዝ፤ ኦሮሞ ጋንቤላ፤ ኦሮሞ ጂጂጋ፤ ኦሮሞ አዲስ አበባ አልበረምን? የጎንደርን ብልህ #ልቅና፤ የመሰጠት ዊዝደም ዕውቅና ላለመስጠት ሲሉ ያመጡት ጠማዳ አፍላሽ #ቡግንጅ ሃሳብ ነው። "ወልቃይት ብረሳሽ ቀኜ ትርሳሽ$ የፈጠረውን ሞገድ የደህንነት ሰው ናቸው ያውቁታል። ያ ግሎባል ንቅናቄ የተደራጀውን አዛውንቱን ህወሃትን በልዩ የፈጣሪ ጥበብ ቀስ አድርጎ ካለምንም ደም መፋሰስ ነበር ሽግግሩ እንዲፈጸም የሆነው።
ይህንን ሂደት የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚር አቶ ኃይለማርያም ደስአለኝ ከእንግሊዘኛው ዶቼቤሌ ጋር በነበራቸው ቆይታ እሳቸው በፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን እንዲለቁ ያደረገው የአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ መሆኑን ገልጸዋል። እኛ ስንሰራ አንዱ ብስል አንዱ ጥሬ አይደለም።
ከግል የሃሳብ መደራጀት ጀምሮ ያለ ጥድፊያ ተከታታይ እና ትጋት ያለው፤ ለስኬትም የሚያበቃ ተግባር ነው የምንከውነው። ምስጋናው ቢቀር የኮፒራይት ሽሚውን ማስታገስ፤ ህዝባችን በተገኜበት ቦታ ሁሉ የማዋከፍ ተግባር እንዳይኖር ማድረግ ይገባል። እነ አንድ አፍታ አዲስ የካቴና፤ ወይንም የቀብር ሥርዓት የናፈቃቸው ይመስላል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሙሉ አቅሙን ለብልፄው እየመገበ ያለው፤ ዘመኑን ለድሬ እና ለአዲስ አበቤ ፈቅዶ የሰጠው አቶ ኤርምያስ ለገሰም ምርር ብሎት ሲናገር ሰምቻለሁኝ። ይህን ምሬት አድምጦ ለራስ ላፒስ ገዝቶ፤ እራስን ወቅሶ የህዝብን ውስጥ ማረጋጋት በእጅጉ ያስፈልጋል።
https://www.youtube.com/watch?v=XM6NXHOH9QI
«ጥብቅ ማሳሰቢያ፣ የአዲስ አበባ ጉዳይ፣ የRSF ግስጋሴ»
አንድ የፖለቲካ ድርጅት የሚወደድበትን እንጂ በሚጠላበት ተግባር ላይ ተግቶ ሊሠራ አይገባም። የ130 ሚሊዮን ህዝብ ቤት ጣሪያ መንቀል የሚያመጣው ጣጣ ብዙ ይሆናል። የአንድ አገር ሉዓላዊነት እንደምን ለአንድ ዞግ ይሰጣል??? እንዴት????
በሌላ በኩል የታሪክ ዝበትን #የማንፈቅድ ሰወች አለን። ፕሮፌሰር ህዝቃኤልም ሰሞኑን በዚህ ጉዳይ ግልጽ አቋማቸውን ሰጥተዋል። የቄሮ ትግል #የማስተር ፕላን ጉዳይ ነበር ብለዋል። በዚህ አጋጣሚ መድህን ለሆነው ወቅታዊ፤ ፋክታዊ ምስክርነታቸው ምስጋናዬን አቀርብላቸዋለሁኝ።
#ህም። እምም።
"አገራዊ" የሚለውን ትምህርተ ጥቅስ ውስጥ ያስገባሁት ኢትዮጵያ በሚፈትን #የህሊናዋ የአዲስ አበባ ጉዳይ ሁለቱን አማራጮች እራስ ገዝ፤ ክልል ትሁን የሚለውን ኮሚሽኑ የተወበት መንገድ #ጎድጓዳ ሆኖ ነው ያገኜሁት።
በተጨማሪም ከሽሮ ወጥ ላይ መጀመሪያ ተመጥኖ ውሃው ካልሆነ ሲወፍር ውሃ ከተዶለበት ውሃው ላይ ይጠላል፤ የተልባ ጄልም ሲሰራ ቀድሞ ካልተመጠነ ተመሳሳይ ፈተና ይገጥመዋል። ኮሚሽኑ ሁለት አማራጮች ብቻ እንዲኖሩ አድርጎ ልክ ኤርትራ እንደተሸኜችበት (ነፃነት ወይ ባርነት) በሚል ፤ ከዛ "#የበላይ" አካል የሚል ቅብጥ ያለ አናርኪዝም ታከለበት። ፕሮሲጀሩ ነው አናርኪ የሚያደርገው እኔ አይደለሁኝም። አናርኪዝም ስኬቱ ፍ ር --- ሰ ---ርሰ ነው።
በሌላ በኩል ከአማራ ክልል የተወከሉ ወገኖቻችን በፈተና ውስጥ መሆናቸውን እየተደመጠ ነው። የአማራ ህዝብ በዚህን ያህል ውክቢያ፤ ዘለፋ፤ መገለል፤ መንጓጠጥ፤ ማስፈራራት ሲካሄድበት እቴጌ ትግራይ ሰብሰብ ብላ መቀመጧ ልባምነት ያሰኛታል። የአማራ ህዝብ ሊከበር ሲገባ ይህን ያህል መገፋት ብልፄው እርግማኑን ከቻለ ይቀጥልበት።
ይህን በምርጫ ውድድሩ የዶር ሊሊሴን #መቀናጣት ሚዲያ ላይ ዘለፋቸውን አስተውያለሁኝ። ሁሉን ነገር ዕድል ሰጥ - ዘመንን ሰጥ ቢሆን፤ ሥልጣንም ቢሆን የሞራል ከፍታንም ቢሆን በልኩ መያዝ ቢጠቅም እንጂ አይጎዳም።
ሌላዋ የብልፄው ቋሚ ሠራተኛ ምክትል ሚኒስተር ይመስሉኛል፤ "ማን አምጥቶ ደፋብን" ብለው የስላቅ፤ የመመፃደቅ ጹሁፋቸውን አንብቤያለሁኝ። የሰው ልጅ እንደ አፈር፤ እንደ አሽዋ በጭነት መኪና መጥቶ "የሚደፋ " አይደለም። በጣም ነውረኛ የሆነ ቃል ነበር የተጠቀሙት። እሳቸውን እኛ አናውቃቸውም። ለዚህ ለምክትል ሚ/ር ማዕረግ ያደረሳቸው የእኛ ትግል እንጂ የሳቸው አልነበረም። እሳቸው ደራሽ ታጋይ ናቸው።
በየክስተቱ እየወጡ ሲዘልፋ በአዲስ አበባ ለፓርላማ እጩነት ተወዳዳሪነት ታጩ፤ እንደገናም ለሚዲያ የቦርድ አባልነት ተሾሙ። መሳደብ፤ መዝለፍ፤ ማግለል፤ ማጣጣል የሰውን ልጅ እንደ አሽዋ "መደፋት" ያሉ ጸረ ሰብዕ ተሿሚ። ሰብዕን መጫን፤ በነውረኛ ቃል ማዋከብ ለብፄ የልብ አድርሱ መንገድ መሆኑን ማጣቀሻ እንዲሆን ነው ይህን ያቀረብኩት።
ስለሆነም የአማራ ክልል ተወካዮች የደረሰባቸው ጫና፤ ጭቆና ኮሚሽኑ ከምንም ያልቆጠረው መገፋት በትክክል ለእኔ ከውስጤ የሚገባኝ ዕውነት ነው። ለአማራ ህዝብ ብትን አፈር አሁን ባለው አሳቻ ዘመን እንደ ሌለ እሙን ነው። የፈጣሪ ጥበብ ነው ትንፋሽን ያስቀጠለው እንጂ ዙሪያ ገባው መከራ ነው።
ደስታ፤ ማግኜት፤ ስኬት፤ ብሥራት ያልፋሉ። ከማለፋቸው በፊት ግን በልክ መያዝ ብልህነት ነው። የሆነ ሆኖ ዛሬም አቤቶ አብን አክብሮ ያቀረበው አቤቱታ አንድ ቀን ለቀረው ማጠቃለያ ጥቅሙ ይሁን ተፈፃሚነቱ ምን ያህል የልብ ያደርሳል ባይባልም BBC ዕውቅና ሰጥቶ መዝግቦለታል። ይህ ማለት ታሪክ ላይ ባለ አሻራ የሆነ አቤቱታው #ግሎባል ይሆናል ማለት ነው።
#ፍራቻ።
ነገ ይጠናቀቃል ተብሏል። ሮቡ ለምን እንደተመረጠ ባላውቅም። ሁሉም ምክንያት ስላለው። "የእነ ቶሎ ተሎ ቤት" እንዳይሆን ያሰጋል። ቅሬታን ሳይፈቱ፤ ቅሬታን መልክ ሳያስይዙ፤ ቅሬታን እንክህ እንክህ የሚል፤ ቅሬታን #ያረገዘ ነገ ጊዜ ጠብቆ የሚፈነዳ ፈንጂ ይሆናል። ጠብቁት።
በሌላ በኩል ጠንካራ ሃሳብ ያቀረቡ ተሳታፊወች ሰበብ እየተፈለገ ሰማዕትነትን ሊቀበሉ፤ ሊሰወሩ፤ ወይንም ሊታሰሩ ይችላሉ። ይህ ነው እኔን በእጅጉ የሚያስፈራኝ።
በሂደቱ የብልፄው የደህንነት አካላት፤ ባለስልጣናት ነበሩ። እንደ ገናም በውይይቱ ሂደት በስተጀርባ ውይይቱን የሚከታተሉ አካላት በስክሪን ይከታተላሉ ይኖራሉ።
ጠቅላይ ሚር አብይ የደህንነት ሰው ስለሆኑ፤ በIT ም ባለሙያ ስለሆኑ ከቅንጣት እስከ ገዘፈው ጉዳይ ከክትትል ውጪ የሆነ ምንም ሂደት፤ አመክንዮ አይኖርም። በዚህ ውስጥ ኮሚሽኑ ሰጠሁት የሚለው ነፃነት እራፊ መጠጊያ ያጣል። ለነገሩ ኮሚሽኑ ሞትም የተፈረደበት ነው። "እርምጃ ውሰዱ ብለን" ወስነናል ሲሉ የአውስትርልያው ዶር ጸጋዬ አራርሳ አዳምጫለሁኝ።
ይህ ሥልጣን የሚባል አይጠረቄ አዬን እኮ ሥልጣን እንዴት እንዴት እንደሚያደርግ #በደፂዝም። ሥልጣን ደዌ ነው። ሥልጣን ሃሺሺ ነው። ሱስ። ስለዚህ ለሥልጣኑ የትኛውም አካል ስስም፤ ጥንቁቅም ቢሆን አይደንቅም። በዚህ ሂደት ግን ሰብዓዊ መብት ሊቀጠቀጥ፤ ሊረገጥ፤ ሊጨፈለቅ አይገባም ነው የእኔ ሙግት። ነፃነትም ይህን ያህል አሳሯን ልታይ አይገባትም ባይ ነኝ።
እሜቴ ነፃነት እንደምን ከርመሻል?
ከአምናው ሸክማሸክምሽ ዘንድሮ ከብዶሻል……… (ለህትም የበቃ።)
#ክወና።
ምን አገባን የፈለገው ይወሰን፤ ብልፄ ዕድሜ የለውም፤ አቅም አናዋጣም የሚሉ የውስጥ ሞጋቾች ገጥመውኛል። #የህውሃትወኦነግ ህገ - መንግሥት ለስንት ዓመት እንደ ቀጠቀጠ ይታወቃል። ይህም ሂደት ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ አይታወቅም። የሕይወት ጉዳይ ነው። የመተንፈስ ጉዳይ ነው። የመኖር ጉዳይ ነው። ስለዚህ ተግቶ መከታተል የግድ ነው።
እንደ ተለመደው በወጀቡ ውስጥ አንድ አዲስ ድምጽ ይሰማል። በቅዱስ ሲኖዶስ እንዳየነው። አስታራቂ ሆኖ የመቅረብ ሁነት። ሁሉንም እናያለን። የተሳተፋችሁ ሁሉ ግን ጸጸት #ሊኖርባችሁ አይገባም። በዕድሜያችሁ፤ በዘመናችሁ ለተሰጣችሁ፤ ለተፈቀደላችሁ ሁሉ ዕድል አድምጦ መሳተፍ ነውር አይደለም። ማየት - መማር፤ መገኜት - ክህሎት ነውና።
ውዶቼ ውቦቼ እንዴት አረፈዳችሁልኝ?
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
18/08/026.
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
"አማራነት ይከበር!"
************************************************
"ከኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መግለጫ ለቀረቡት ድምዳሜዎች ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተሰጠ ምላሽና አቋም፤
*****
ዛሬ ነሐሴ 11 ቀን 2018 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ፓርቲያችን አብን ቀደም ሲል በ 09/12/2018 ዓ.ም ያወጣውን መግለጫ አስመልክቶ የሰጠውን ማብራሪያ ተመልክተናል።
አብን ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በሀገራችን የተደራረቡና ውስብስብ ፖለቲካዊ ችግሮች ሰላማዊና ዘላቂ መፍትሔ ሊገኝላቸው የሚችለው ተአማኒነት ባለው እውነተኛ የምክክር መድረክ ብቻ መሆኑን በጽኑ ሲያራምድ ቆይቷል።
በመሆኑም ፓርቲያችን ከተለያዩ ጎራዎች የሚሰነዘሩበትን ጠንካራ ነቀፌታዎችና ትችቶች በጽናት በመቋቋም፣ የምክክር ኮሚሽኑ በህግ ከተቋቋመ ብሎም የምክክር ሂደቱ ከተጀመረበት ዕለት አንስቶ የክቡራን ኮሚሽነሮቹን ጥረትና ታሪካዊ ሚና በከፍተኛ ደረጃ ሲደግፍ ቆይቷል።
እንዲሁም ሀገራችንን ከገጠማት የፖለቲካ ቀውስ ሊታደግ የሚችል ብቸኛና አወንታዊ አማራጭ ሀገራዊ ምክክሩ በመሆኑ፤ መላው የአማራ ሕዝብና የኢትዮጵያ ሕዝቦች በሂደቱ ሙሉ የባለቤትነት ስሜትና ተስፋ እንዲሳተፉ ጥሪ ስናቀርብና ስናስተባብር የቆየነው በዚሁ ጽኑ እምነታችን ምክንያት ነው።
አሁንም ቢሆን ለክቡራን ኮሚሽነሮቹ ቅን ሀገራዊ ፍላጎት፣ ለሚያደርጉት ያላሰለሰ ጥረትና ታሪካዊ አደራ ከፍተኛ ዋጋ እንሰጣለን፤ እናከብራለንም። ሆኖም ኮሚሽኑ ዛሬ ነሐሴ 11 ቀን ባወጣው መግለጫ የፓርቲያችንን መሠረታዊ ሥጋቶችና ቅሬታዎች አቅጣጫ የሚያስቱና ያቀረብናቸውን ተጨባጭና ተደጋጋሚ አቤቱታዎች ከግንዛቤ ውስጥ ያላስገባ ሆኖ አግኝተነዋል።
በመሆኑም የሚከተሉትን መሠረታዊ ነጥቦች ለሕዝባችንና ለባለድርሻ አካላት ማሳወቅ አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል፡
1. የገዥው ፓርቲና የደጋፊዎች ያልተገደበ ጣልቃ ገብነትን በተመለከተ፤
አብን ሙሉ የኮሚሽን አባላትም ሆነ ኮሚሽኑን እንደ ተቋም "በጅምላ ጥፋተኛ ናቸው" ወይም "ገለልተኛ አይደሉም" የሚል ቅሬታ ወይም ድምዳሜ አላቀረበም። የፓርቲያችን ዋነኛና መሠረታዊ ቅሬታ ከገዥው ፓርቲና አንዳንድ ደጋፊወቹ በኩል የተፈጸሙት ያልተጠበቁና ያልተለመዱ የአሠራር ጥሰቶች ናቸው። አንዳንድ የገዥው ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች የምክክሩን ሂደት በማዛባት፣ አጀንዳዎችን በበላይነት ለመጫን እና በተሳታፊዎች ላይ ያልተገባ ተጽዕኖ ለመፍጠር ባደረጉት ጣልቃ ገብነት ሂደቱን የሚያስተጓጉሉ ተግባራትን ፈጽመዋል። ይህንንም ሪፖርት አድርገናል።
2. የተወሰኑ የኮሚሽኑ አመራር አባላት ጣልቃ ገብነት፣ የባለሙያዎች ቡድን አሳሳች አቀራረቦች እና የአንዳንድ አስተባባሪዎች ወገንተኛ እንቅስቃሴ፤
ኮሚሽኑ ቅሬታችንን "አጠቃላይ የሂደት ክፍተት" አስመስሎ ለማቅረብ ቢሞክርም፣ ተለይተው የታወቁ ሁለት ኮሚሽነሮች በቀጥታ በምክክሩ ሂደት ውስጥ በተለይም በከተሞች አጀንዳ ውስጥ እጃቸውን በማስገባት የተሳታፊዎችን ፍላጎት ለማስቀየር እና ተጽዕኖ ለማሳደር ሙከራ ማድረጋቸውን በተደጋጋሚ ታዝበናል።
በተጨማሪም በኮሚሽኑ የተመደቡ አንዳንድ "ባለሙያዎች" በምሁርነት ስም አድሏዊና ተገቢ ያልሆኑ ሀሳቦችን ሲያራምዱ እንደነበር፣ የተወሰኑ አስተባባሪዎች ደግሞ የፓርቲያችን ተወካዮችና ሌሎች ተሳታፊዎች ያሏቸውን መሠረታዊ አቋሞችና ሀሳቦች እንዳያቀርቡ ደጋግመው ዕድል በመንሳት በስልታዊ መንገድ አፈና ሲፈጽሙ ቆይተዋል፣ ይህንንም ሪፖርት አድርገናል።
3. አዎንታዊ እርምጃዎችና ያልተፈቱ ችግሮች፤
አብን ያቀረባቸውን አቤቱታዎች ተከትሎ ኮሚሽኑ ጥሰት የፈጸሙ የተወሰኑ አካላትን በመለየትና ከኃላፊነት በማንሳት የወሰዳቸውን አዎንታዊ እርምጃዎች (በሚዲያ መግለጫ ይፋ የተደረገ) እናደንቃለን። ሆኖም እርምጃዎቹ ሙሉ ባለመሆናቸው፣ በተለይም የሁለቱ ኮሚሽነሮችና የጥቂት አስተባባሪዎች አሉታዊ ጣልቃ ገብነት መቀጠሉ እንዲሁም የመንግሥት አካላት አሠራር ሙሉ በሙሉ አለመታረሙ ቅሬታ ፈጥሮብናል።
4. የቀጠለው የመንግሥት ሚዲያዎች የተሳሳተ ፕሮፓጋንዳ፤
የዛሬው የኮሚሽኑ መግለጫ በወጣበት ቅጽበት ገዥው አካል ዋና ዋና የመንግሥት መገናኛ ብዙኃንን እና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን የኮሙኒኬሽን ክፍሎች በመጠቀም መግለጫው በስፋት እንዲሰራጭ ማድረጉ ፓርቲአችን ያቀረበውን አቤቱታ ዋጋ የማሳጣት አጋጣሚ አድርጎ ለማቅረብ በማሰብ ነው።
ይህ ድርጊት መንግሥት ቀደም ሲል የፈጸማቸውን ስህተቶች ለማሸፋፈንና የራሱን አቋም በኮሚሽኑ ስም ተጠልሎ ለማስፈጸም የሄደበት መንገድ ሆኖ አግኝተነዋል። ይባስ ብሎም መንግሥት አካሄዱን ለማረም፣ ስህተቶቹን ለማስተካከል እና ሂደቱን ጤናማ ለማድረግ ምንም ዓይነት ፍላጎትና ቁርጠኝነት እንደሌለው የሚያረጋግጥ ሆኖ አግኝተነዋል።
ፓርቲያችን አብን አሁንም ቢሆን ሀገራዊ ምክክሩ ከግለሰቦችና ከገዥው አካል ወገንተኝነትና ጣልቃ ገብነት ነፃ ሆኖ እንዲቀጥልና በውጤት እንዲጠናቀቅ የበኩሉን ጥረት ያደርጋል።
ያቀረብናቸው መሠረታዊ ቅሬታዎች ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኙ በአጽንኦት ስንጠይቅ የምክክር ሂደቱ ውጤታማ እንዲሆን፣ በሂደትም እውነተኛ እና ዘላቂ ሀገራዊ መግባባት እንዲፈጠር ከልብ በመሻት ነው።
ፓርቲያችን ለሀገራችን ሰላም፣ ፍትሕና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መረጋገጥ የሚያደርገውን መሠረታዊና መርህ ተኮር ትግል አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን እያረጋገጥን የኢትዮጵያ ህዝብም እየተካሄደ ያለውን ምክክር በልዩ ትኩረት እንዲከታተለው በድጋሜ ጥሪ እናደርጋለን።"
ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!
አማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)
ነሐሴ 11/ 2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ
"አብን የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሁለት ኮሚሽነሮች በጉባዔው አጀንዳዎች ላይ እጃቸውን ለማስገባት ሞክረዋል ሲል ከሰሰ
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሁለት ኮሚሽነሮች በምክክር ጉባዔው አጀንዳዎች ላይ በቀጥታ እጃቸውን በማስገባት ተጽዕኖ ለማድረግ ሞክረዋል ሲል ከሰሰ።
ፓርቲው ይህንን ያለው ነሐሴ 11፣ 2018 ዓ.ም. ኮሚሽኑ አብን አቅርቧቸው ለነበሩ ቅሬታዎች የሰጠውን ምላሽ ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ላይ ነው።
አብን በመግለጫው ሁለት ኮሚሽነሮች በቀጥታ በምክክሩ ሂደት ውስጥ "በተለይም በከተሞች አጀንዳ ውስጥ" እጃቸውን ማስገባታቸውን ጠቅሶ፣ "የተሳታፊዎችን ፍላጎት ለማስቀየር እና ተጽዕኖ ለማሳደር" ሙከራ ማድረጋቸውን በተደጋጋሚ መታዘቡን አመልክቷል።
አብን ሰኞ ምሽት ባወጣው በዚህ መግለጫ ላይ ያቀረባቸውን አቤቱታዎች ተከትሎ ኮሚሽኑ ጥሰት ፈጸሙ የተባሉ የተወሰኑ አካላትን ለይቶ ከኃላፊነት ማንሳቱን ጠቅሷል።
ይህ እርምጃ የተሟላ አይደለም ያለው ፓርቲው "በተለይም የሁለቱ ኮሚሽነሮችና የጥቂት አስተባባሪዎች አሉታዊ ጣልቃ ገብነት" መቀጠሉን አስታውሷል።
ፓርቲው አክሎም "የመንግሥት አካላት አሠራር ሙሉ በሙሉ አለመታረሙ" ቅሬታ ፈጥሮብናል ሲል በመግለጫው ላይ ዳግም አቅርቧል።
አብን ቅዳሜ ዕለት በአገራዊ ምክክር ሂደት ከተራ የአሠራር ግድፈት የዘለሉ ተደጋጋሚ እና የተደራጁ ጥፋቶች ተፈጽመዋል ሲል ቅሬታውን ባወጣው መግለጫ ላይ አስታውቆ ነበር።
አክሎም ገዢው አካል መዋቅራዊ ጥሰቶችን ፈጽሟል ሲል የከሰሰው አብን፣ በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ "የከተማዋ ነዋሪዎች ድምፅ እና ፍላጎት በአግባቡ ሳይወከል" ታልፏል ብሏል።"
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ