ክብርት ሆይ! እጩ ጠቅላይ ሚኒስተርነት ከወደ ጋንቤላ #ሃሳቡን እና ሰብአዊነትን እንደምን ሊያስታርቁት አሰቡ?
ክብርት ሆይ! እጩ ጠቅላይ ሚኒስተርነት ከወደ ጋንቤላ #ሃሳቡን እና ሰብአዊነትን እንደምን ሊያስታርቁት አሰቡ?
"እግዚአብሄር በአንድም በሌላም መንገድ
ይናገራል፤ ሰው ግን አያስተውለውም።"


#ምዕራፍ ፲፰።
#ክብርት ሆይ!
እንዴት ሰነበቱልን? የፎቶ ቅደም ተከተል ግር እንዳይለወት። እኔ በጋሜዬ ጊዜ ነበር ህይወቱን የፖለቲካውን የጀመርኩት። ስለሆነም እያንዳንዱን ቅንጣት ሁነት ከውስጤ በአትኩሮት ነው እምከታተለው። ስለሆነም በፖለቲካ ህይወት ውስጥ #ሲነሪቲ የሚባል የፕሮቶኮል ጥያቄ አለ።
ስለሆነም እጅግ የማከብረው አቶ ኦባንግ ሜቶ ከእርሰወ የቀደመ የፖለቲካ ተሳትፎ ስላለው፤ በሲነሪቲ እንደሚበልጠወት ስለማውቅ ነው እሱን ያስቀደምኩት። በዚህ አጋጣሚ ሁለት ጠይም #ዕንቁ የአገሬን ልጆች ላፈራችው ጋንቤላ ምስጋናዬ ከልብ ነው።
#መቅድመ የፖለቲካ ውሳኔ።
የህወሃት ሥርዕወ - መንግሥት ፍፃሜ ሲጠናቀቅ የቀደመ ውሳኔ ያሳለፈ አቶ ኦባንግ ሜቶ ነበር። ምን ብሎ ይመስለወታል ክብርት ሆይ! ያ ውሳኔ ከእርስወም ተሳትፎ የሚቀድም ይመስለኛል። ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድን "#የእኔ ጠቅላይ ሚኒስተር" ያለ የመጀመሪያው ሰው ነበር። እኔ እንዲያውም በዘርፋ ትጉህ ስለነበርኩ ጽፌበታለሁኝ።
ከዛ ልዑል አስፋው ወሰን አስራተ ካሳ፤ የመኢሶኑ ዶር ነገደ ጎበዜ በተጨማሪም ታላላቅ ቀደምት የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ሁሉ ጠቅላይ ሚኒስተራችን አብይ አህመድ ሲሉ ተደመጡ። ታላላቆቼ በአደባባይ ወጥተው ድምፃቸውን ሲሰጡ እዬተከታተልኩ እኔ እጽፍ ነበር። በሩን #ቧ #ፏ አድርጎ የከፈተው ግን አቶ ኦባንግ ሜቶ ነበር።
እኔ ከኢንጂነር ስመኜው ህልፈት በኋላ እማልወደውን ስልክ ደውዬ፤ ሁኔታውን በእርጋታ እንዲከታተለው ነግሬው ነበር። እሱ ግን ሰፊ የሆነ መታመን ለጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ስለነበረው በፍጥነት ወደ ኢትዮጵያ አቀና። አቀባበሉ #የንጉሥ ነበር።
እነኝህን ግብረ መልሶች ያዬ የዓለም ፖለቲካ የፊደል ገበታው "አብይ - አብይ - አብይ" ሆነ። ለጠቅላይ ሚኒስተር አብይ #የይሁንታ #ቅበላ ቀድሞ የተከወነ ብልህ ተግባር ቢኖርም፤ ለዛ ተጨማሪ የማጠናከሪያ ፖለቲካዊ ጉዝጓዝ ግን የኦባንግሻ አስተውሎት አስተዋፆው ከፍ ያለ ነበር። የሌሎችም ቀናወችም እንዲሁ።
#ጥበቃዬ ውሃ በላው።
እኔ እጠብቅ የነበረው አቶ ኦባንግ ሜቶን ለተመደ የኢትዮጵያ #ባለሙሉ አንባሳደርነት ነበር። አገር የገቡትን አቶ ነዓምን ዘለቀ፤ ጋዜጠኛ እና ፖለቲከኛ አቶ ክንፋ አሰፋን፤ የሰብአዊ መብት ተሟጋቹን አቶ ያሬድ ኃይለማርያምን፤ ጋዜጠኛ አበበ ገላውን፤ ፖለቲከኛ እና ጋዜጠኛ አቶ መስፍን አማንን፤ ሌሎችንም ወጣት የፖለቲካ ሳይንስ ሊቃውንታት በአንባሳደርነት ኢትዮጵያ ትሾማቸዋለች የሚል ተስፋ ነበረኝ።
ጥበቃዬ ግን ውሃ በልቶት፤ የውሃ ሽታ ሆኖ ቀረ። አሁን ጋዜጠኛ እና ፖለቲከኛ አቶ ክንፋ አሰፋ የት እንዳለም አላውቅም። የክንፋሻ የአደባባይ ተሳትፎው በውነቱ ናፍቆኛል። ግን ክንፋሻ እና ብዕረኛው እና ጋዜጠኛው ተመስገን ደስአለኝ የት ናቸው???
#ስለ ዓለም ዓቀፋ የሰብአዊ መብት ታጋይነት።
ኦባንግሻ ለክፋ ጊዜ ደራሽ እናት ሆዱ ነበር። ኦባንግሻ በስደት ያለውን መከራ የተጋራ ወገኖቹ ሲከፋ ፈጥኖ ደራሽ፤ ሩህሩህ፤ ሞጋች እና ቅን ልቦና ያለው #መልካዕ ኢትዮጵያ፤ መልዕካ ፓን አፍሪካኒስት ነው።
ኦባንግሻ በዓለም መድረክ ስለ ሰው ልጅ ነፃነት፤ ፍትህና እኩልነት የሞገተ ብቻ ሳይሆን ያስተማረ ጠይም ዕንቁዬ ነው - ለእኔ። እኔ ኦባንግሻን በየለቱ እማገኜው ሰው አይደለሁም። ፍላጎቱም በውነቱ የለኝም። ለምን????
1) ስልክ መደወል፤ ስልክ ማንሳትም ፈጽሞ አልወድም።
2) ከየትኛውም ሰው ጋር ጥብቅ ያለ ግንኙነት በፍጹም አልፈልግም።
3) ከተጽዕኖ ፈጣሪ ጋር መገናኜት በጭራሽ የማልፈልገው አመክንዮ ነው።
ግን የኢትዮጵያን ልጆች ከሊቅ እስከ ደቂቅ እመ - አምላክ እንድትጠብቅልኝ እለምናታለሁኝ። ክፋቸውን እንዳያሰማኝ እማጸናታለሁኝ። ፖለቲካ እጅግ አድካሚ፤ እራስን የሚያስረሳ፤ ቅራኔ ውስጥ የሚማግድ የቀራንዮ ወላፈን ነው። ያን ህይወት የፈቀዱ ሁሉ መኖራቸው ሁልጊዜ ሱባኤ ነው። ኑሬበታለሁኝ። አውቀዋለሁኝ።
ይህንን ፈቅዶ ማገዶ ለሚሁኑ፤ በተግባር ለሚገኙ የኢትዮጵያ አርበኞች ልዩ ክብር አለኝ። ኢትዮጵያ የምትመራው በፖለቲካ ኢሊት ነው። ሃሳቡ ተደገፈ፤ ተመሳሰለ፤ ተዋህደ ሳይሆን ኢትዮጵያኒዝም የጸነሱ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ግን ለኢትዮጵያ #ትርታ በእጅጉ ያስፈልጋታል።
ከዚህ አንፃር ነው ስለ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ኢሊቶች ክትትልም፤ ሙግትም ሲኖረኝ እምሳተፈው። የፖለቲካ ኢሊት ጥበቃ፤ በህይወት መቀጠል፤ ነፃነት ኢትዮጵያን የማክበር #እርካብ ነው ብዬም አምናለሁኝ።
የወል አቅም፤ የጋራ ክህሎት፤ የተባበረ የልምድ ዓውደ ምህረት ኢትዮጵያ ጠቀም ስለሆነ ሊገለል አይገባም ብዬ አምናለሁኝ። ፈላስፊት ኢትዮጵያ ስለምትጠቀምም። ትውልድም ያፈራል በመቻቻል ማሳ።
ለዚህም ነው ባልተራራቀ ጊዜ ኤክስ አካውንቱን፤ ፌስቡኩን ሳይቀር በመጎብኜት "#እንፈላለግ" በሚል መሪ ቃል ኦባንግሻ የት ነው ያለው እያልኩ የምጽፈው። እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ ኦባንግሻን አየሁ፤ ተዚህ ነው ያለው የሚል መልስ የለም።
በጤና፤ በህይወት፤ በመሰወር፤ በአካል መጎዳት፤ በዕምሮ መዛል ይሁን ስለ ኦባንግሻ #ዜናው እየራቀ፤ እየተረሳ እየሄደ ነው። እኔ እማስበው እንደ እናት ነው። በሌላ በኩል ኢትዮጵያን በውስጡ በጸነሰ አንድ ቅን፤ ገራገር ኢትዮጵያዊ ማሰብ፤ ማፈላለግ ጥሪዬ ነው ብዬ አስባለሁኝ።
በአቶ ኦባንግ ሜቶ አገር ቤት ገብቶ ክብር ማግኜት በአደባባይ ቅናታቸውን የዘረጋገፋ፤ በጥርጣሬ ዓይን እንዲታይ ያደረጉ፤ መሰወሩ ፍጹም ሰላም የሰጣቸው ሰወች እንዳሉ ይገባኛል። በወቅቱም ጽፌበታለሁኝ። አቶ ኦባንግ ኢትዮጵያ ነው ያለው። ለጥቃት ይጋለጣል ብዬ ሞግቻለሁ። መተዛዘን፤ መሸፋፈን፤ ክድን ማድረግ ያስፈልግ ነበር።
ጥቆማውን ለተቀበለው አሉታዊ፤ ቅናታዊ መስመር እሽታን ማተም፤ አብይዝም ይህ ጉዞው አይጠቅምም። ፈጽሞ። ነግ ለእኔ ብሎ ማሰብም ያስፈልጋል።
ሁሉም የአቅሙን አዋጥቶ ለተገኜ በረከት ከመጠን ያለፈ #ለእኔ ብቻን ማጽናት ለትውልድ አይሆንም። የብልጽግና ቲም ሰርክ በየመድረኩ "ብልጽግና የነገ፤ የመደመር፤ የትውልድ" እያሉ የሚገልጹት ከዚህ አንፃር ነው ሊፈተሽ የሚገባው። ዛሬ በትናት ውስጥ፤ ነገም በዛሬ ውስጥ ነው የሚበቅሉት። ለዛሬ የብልጽግና ትንሳኤ ብዙ እጅግ ብዙ ግብርነት፤ ማገዶነት ፈሶበታል።
አንድ መንግሥት ምህረት፤ ይቅርታ፤ እርቅ መርሁ ሊሆን ይገባል። በምንም ታምር ትውልድ በማይተካቸው ብቁወች ሊቀ - ሊቃውንታት ጉዳይ ለውሳኔ #ዳ ሊል ይገባል። መንግሥት የሚወስዳቸው ማናቸውም እርምጃወችን ዘለግ ባለ ጊዜ ሊያጤናቸው፤ ሊመረምራቸው ይገባል።
አቶ ኦባንግ ሜቶን ጋንቤላ #በ100 ዓመት ደግማ አታገኜውም። ፈጽሞ። አፍሪካዊነታችን የሚነበበው፤ የሚተረጎመው፤ የሚመሳጠረው አምጡ ድገሙ ቢባል በአቶ ኦባንግ ልክ ማግኜት ፈጽሞ ለቀጣይ 200 ዓመታት አይቻልም።
ኦባንግሻ ቅን ሰው ነው የነበረው። ለጉባኤ ሲጠራ እንን ብቻውን አይሄድም። ወገኖቹ እንዲታወቁለት ጨምሮ ይዞ እንደሚሄድ አጫውቶኛል። የዕውነት ሰው ነው የነበረው። #ፍንካች የሥልጣን ጥም አልነበረውም። መነሻውም መድረሻውም ሰዋዊነት፤ ተፈጥሯዊነት ይከበር ነው መርሁ።
እንግሊዘኛው ለዛው ይናፍቃል። አማርኛ ቋንቋ ቃናው ልዩ ስጦታ ነው። ቤተ-ሰባዊ አቀራረቡ ይመስጣል። ኦባንግሻ እዚህ ዙሪክ መጥቶ ነበር። ምሳውን ይዞ እኔ ከተቀመጥኩበት ቦታ መጥቶ ተቀመጠ። በአካልም፤ በፎቶም አያውቀኝም።
ግን "#ደወል" የሚል የድርጅታቸው ርዕሰ አንቀጽ ነበረቻቸው። እሷን በወር ሁለት ጊዜ በጸጋዬ ራዲዮ አቅርብ ነበር። ከቲሙ ጋርም አገናኝቶኝ ነበር። ቲሙ ለሴቶች ያላቸው አቀባበል የጸሐይ ብርሃን ያህል ጉልበት ነበረው።
እምንተዋወቀው በስልክ ነበር። ጄኔባ ይመላለስ ነበር። ሂጄ አግኝቼው አላውቅም። ዙሪክም ፍሪቡርግ ያለችው እህቴ እኔ ካለሁበት ከተማ ዙሪክ መጥታ፤ እጅግ በጣም ስለምትሳሳለት እሷ ነበረች የወሰደችኝ።
የምሳ ሰዓት ምን እንደ አመላከተው አላውቅም መጥቶ ከአጠገቤ ከልዑኩ ጋር ተቀመጠ። ከዛ ሥርጉተ ሥላሴ ማለት እኔ ነኝ አልኩት። በቃ። ከዛ በኋላ ወደ መድረክ ሄዱ ደግሜ አላገኜሁትም። አልተሰናበትኩትም። ቤቴም አልጋበዝኩትም። የእኔ ነገር እንደዚህ ነው። ኢትዮጵያ በምትፈልገኝ ቦታ እገኛለሁ። #ቀጣይ ኮንታክት ከማንም ጋር አያስፈልገኝም። ወደፊትም።
የብልጽግናዋ ክብርት እጩ ጠቅላይ ሚኒስተር እና አቶ ኦባንግ ሜቶ በሰብአዊነት ጉዳይ በመንግሥት ሚዲያ ያለምንም ተጽዕኖ ተከባብረው የሚሞግቱበት መድረክ ነው።
#አቤቱታ ለክብርት እጩ ጠቅላይ ሚኒስተር።
1) አቶ ኦባንግ ሜቶ የት ነው ያለው?
2) ፓርቲወት ብልጽግናን ፈቅዶ የተደመረው ዓለም ዓቀፋ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አቶ ኦባንግ ሜቶ በህይወት አለን?
3) ወይንስ ታሟል፤
4) ወይንስ በዕምሮው ላይ የደረሰ ጉዳት አለን?
5) ዕውን አቶ ኦባንግ ሜቶን ዓለም በዛ በሚያጓጓው አቅሙ፤ ብቃቱ፤ ሰዋዊነቱ እና ተፈጥሯዊነቱ ልክ ደግሞ የማዬት፤ እንደገና የማግኜት ዕድል ይኖር ይሆን?
6) ይህ ባለፈው የክርክር መድረክ ጊዜ ሺህ ሚሊዮን ጊዜ የቀደሱት ብልጽግና ፓርቲወት መልስ ይሰጥበት ዘንድ ሊጠይቁት ይገባል። በስተቀር ክልላችሁ እኩል እንደ ማዕከላዊ መንግሥት ተጠያቂ ይሆናል።
አቶ ኦባንግ ሜቶ ለፓን አፍሪካኒስትነትም #ክስተት ነው። በእሱ ልክ ከጋንቤላ ሰው እናምጣ ብትሉ በስንት ዓመት ልትችሉ እንደምትችሉት ፈጣሪ ይወቀው። ደግሞ አይገኝም።
አቶ ኦባንግ ሜቶ ቅንጣት የሥልጣን ፍላጎት የለውም። በፊት በአደባባይ የሚነግረን ህወሃት ሥልጣኑን ሲለቅ ሚስት አግብቼ እንደ አንድ ገበሬ እኖራለሁ ገጠር ገብቼ እኖራለሁ ነበር ምኞቱ።
ክብርት ሆይ! አቶ ኦባንግ ሜቶ የት ነው ያለው? አቶ ኦባንግ አልባሌ ሰው አይደለም። ሉላዊ፤ ታዋቂ እና የሰብአዊ መብት ሞጋች ጽኑ፤ ብቁ፤ ብልህ ወንድማችን ነው። የት ነው ያለው ኦባንግሻ????
የጋንቤላ እጩ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስተር ፍላጎትን በሂደት እናዬዋለን። እኩል ተፎካካሪው ከስልጤም አንባሳደር ሬድዋን ሁሴንን ሪኮመንድ ሲያደርጉም አነባለሁኝ። ይህንንም ቢሆን በሂደት የምናዬው ይሆናል።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን፤ አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
25/03/026
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ዕውነት ወጌሻ ወይንም ጋራጅ አያስፈልገውም።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ