የቀጣይ የጠቅላይ ሚር #እጩነት ከወደ ጋንቤላ።

 

የቀጣይ የጠቅላይ ሚር #እጩነት ከወደ ጋንቤላ። 
 
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።
 
#ምዕራፍ ፲፰።
 
 
በቅድሚያ ማህበረ ቅንነት እንዴት ናችሁ? እንዴት ነን??? ዘለግ ያለ ሃሳብ ነው ያለኝ። በተለይ በአውራው መሪ ፓርቲ በብልጽግና ላይ። ከምርጫ በኋላም ብልጽግና ኢትዮጵያን የመምራት ዕድሉ 50+ ነው። ኃላፊነት እና ተጠያቂነቱም በእሱ ላይ ጠንከር ይላል። ትዝብቴ ሁለገብ ነው። ዕይታይም ከአንድ የፖለቲካ ድርጅት የአመራር እና የፋክክር ሁነት ጋር የተገናዘበ ነው። ሁለተኛ ሴት እጩ ጠቅላይ ሚኒስተር የመሻት አዝማሚያውም ትኩረቴን ሳብ አድርጎታል።
ብዙ ጊዜ ዩቱብ ቻናል ላይ አንባሳደር #ሬድዋን ሁሴን ብቅ ሲሉ ሚዲያ ላይ፤ ወይንም ከጠቅላዩ ጋር ጉዞን ሲጋሩ፤ ከሥር የተሰጠውን አስተያዬት ሳነብ ቀጣዩ #ጠቅላይ ሚኒስተራችን የሚል አነባለሁኝ። በተደጋጋሚ ይህን ገጠመኝ አያለሁኝ። ከዚህ አንፃር ከወደ ጋንቤላ መሻቱን ለዛውም ከአንስት ፖለቲከኛ በቅርቡ አስተዋልኩኝ። በፊት ጊዜ የኢህፓዋ ጸሐፊ ወይዘሮ ደስታን ነበር ያዳመጥኩት። ከሰምኑ ጠይም ዕንቁዋ ከወደ ጋንቤላ ከደቡብ መሻቱ ከች ብለዋል።
#መሻት - መፈለግ - መመኜት መብት ነው።
የ2018 የምርጫ ክርክር በEBC ተከታተልኩት። አራት የፖለቲካ ድርጅቶች የተሳተፋበት ነበር። ብልጽግና፤ አብን፤ ነፃነት እና እኩልነት እና ትብብር ለኢትዮጵያ። ጭብጡ ወጣት ተኮር ነበር። አራት አንስት የፖለቲካ ሊቃናት ተሳትፈዋል። ሁለቱ #ከብልፄው፤ አንድ ከትብብር፤ አንድ ከነፃነት እኩልነት።
አብን በልሙጥነት። አንዲት ሴት የፖለቲካ ሊሂቅ ለማብቀል ያላጣረ፤ ያላሰበለም፤ ብዙ ተጠብቆ በብዙ አመክንዮወች የልብ ሳያደርስ የቀረ ነው። ለምስረታው ጉዝጓዙ ግን ትንታግ ሴት የአማራ የፖለቲካ፤ የብዕር፤ የኮርድኔተር አንስታት ስኬት ነበር። ይህን በድፍረት የምናገረው አመክንዮ ነው። ግን አቤቶ አብን ሲወጥነውም በከረባት እና በገበርዲን ምልዓት ጀመረው እስተዛሬ የታዬም ቅንጣት የአንስት ፖለቲከኞችን የማሳተፍ ብቅታ የለም። የወንዶች የፖለቲካ ድርጅት ልክ እንደ ኦፌኮ።
ሴት የፖለቲካ ሊቃናት ተኮር አቅጣጫን ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ካመጣበት በኽረ ግሎባል አመክንዮ የመነጨ ነበረ። አዳመጡ ዕድሉ ስለነበራቸው። ፈጸሙት።
ስለሆነም የመጀመሪያው የጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ እርምጃ የአውሮፓ ቁንጮ ፖለቲከኞች ምኞት ምን ተኮር ነው ከሚል የተነሱ ስለነበረ፤ ገና ሲወጥኑት ካቢኔውን 50% በሴት የፖለቲካ ሊቃናት ተንበሸበሼ። በወቅቱ የዓለም መነጋገሪያም ነበር።
ይህን በኽረ ጉዳይ #በአፍላነት እንደ ሳሙና ተኩረፍርፎ ረብ ይላል ሲባል አስቀጥለውታል። ተመችቷቸዋል። እንዲያውም በዚህ የሃሳብ ፍትጊያ ከክብርቷ የሰማሁት ጋንቤላ ለእጩ ጠቅላይ ሚኒስተርነት ሃሳብ እንዳለ ነው። ማለፊያ ነው። በመጪው የብልጽግና ጉባኤ ሴትነት ታክሎበት እጩ የጠቅላይ ሚር ውድድር ክብርቷ ሊሆኑ ይችሉ ይሆናል።
ያለፈው ጊዜ የብልጽግና ፕሬዚዳንት የመምረጥ ሂደት ጠቋሚም፤ መራጭም አስመራጭም እሳቸው እራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ እጣ ነፍሳቸውን ተወዳድረው፤ ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ሆኑ።
ይህ ታርሞ በቀጣዩ የብልጽግና ጉባኤ ተጨማሪ እጩ #ለአጃቢነት ካስፈለገ ፆታዋዊ ስብጥር ያደምቃል፤ ለማሟያነት ይህን መሰል ሂደት ሊሆን ቢችል እኔ አይደንቀኝም። የኢህአፓዋ የቀድሞ ጸሐፊ ወ/ ደስታም ጠቅላይ ሚ/ ር የመሆን ህልማቸውን ለማሳካት እንደሚተጉ ነግረውን ነበር። የት እንደደረሰ ያ ምኞት ዛሬ ላይ ባላውቅም። ቀን ይጠብቅ፤ ይትነን አይታወቅም።
#ብስጭት እና እላፊ።
የብልጽግና ተሟጋቾች በአካላቸው ንቅናቄ፤ በገፃቸውም እልህ፤ በውስጥ በሚነሳሱ ቅንጣት ጉዳዮች ቁጭት፤ የበላይነት ለምን ተነካን ባይነት ካዛም ባለፈ እላፊ አዳምጫለሁኝ። ይህ ሊታረም የሚገባ በኽረ ጉዳይ ነው። በዛ መደረክ ለዛች ሰዓት ሁሉም የክርክር ባልደረባ አንድ ቲም፤ እኩል መብት እና ግዴታ እንዳለበት ብልጽግና ለውክሎቹ የውስጥ መመሪያ ሊሰጥበት ይገባል። አገሪቱ እኮ ኢትዮጵያ ናት። በምናውቀውም፤ በማናውቀውም ፈጣሪ ሰጥ ጸጋዋ ኢትዮጵያ ልዩ አገር ናትና። ተምሳሌትም ናት። መንፈሷም ገናና ነው።
ተሟጋቾች ብልጽግና ገዢ መሆኑን ምክንያት አድርገው ሊሞግቱት መቻላቸው የተገባ እና ሊሆን የሚገባው ሆኖ ሳለ፤ የብልጽግና ቲም ግን የተላኩበት ዕድምታ ጋር ቅርርባቸው እንብዛም ሆኖ ነው ያዬሁት።
መሪ፤ አውራ ፓርቲ ሲኮን በዲስፕሊን ውስጥ ሆን እራስን አጨምቶ አብነትነት በድርጊት ማስጌጥ ይገባል። በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ወጣት ወደ ፖለቲካ ከገባ በኋላ ወጣትነት ሆይ! ደህና ሁን፤ አንተን አቆላምጬ የማስተናግድበት ዘመን ከእንግዲህ የለም ሊል ይገባዋል። ይህ ማለት ምን ማለት ነው። በወጣትነት ዘመን መብት ሊሆኑ የሚችሉ ዕድሎች ጋር ሁሉ ፈቅዶ መፊታት የግድ ይሆናል።
ሌላው "ከተወሰኑ ክልሎች ብቻ ቁልፍ ኃላፊነት መውሰድ" የሚል #ጥላቻ ያንዣበበት ንግግርም አዳምጫለሁኝ። ይህም የተገባ አይመስለኝም። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስተር አቶ ኃይለማርያም ደስአለኝ ከደቡብ፤ እሳቸውን የተኩት ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድም ከኦሮምያ ናቸው።
"የተወሰኑ ክልሎች" ሊባልም አይቻለም። #አሽሙሩ አማራ ክልል እና ትግራይን ለማለት ነው። በዚህ ክርክርክር የገጽ ለገጽ ስለሆነ ግልጽ ንግግር፤ ቅኔ አልቦሽ የሆነ እንቅጩን አቅርቦ መሞገት ይቻል ነበር። በ60 ዓመታት ውስት ትግራይ፤ ኦሮምያ፤ እና ደቡብ ነው ኢትዮጵያን በቁልፍ መሪነት የገዙት። አማራ ክልል ዕድለ ቢስም ነው። ዕድሉን ፈቅዶ ሲያፈስ የኖረ።
ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጨዋነት ድንቅ ነው። ይህን ተቀብሎ ጸጥ ለጥ ብሎ የሚገዛውም የኢትዮጵያ ህዝብ ነው። (በትግራይ ያለውን አሁናዊ ሁኔታ ዘንግቼ አይደለም) አቀራረቡ በግርዶሽ ጥላቻ ቀመስ ነው።
ይህ እራስን ይሁን #ክልልን ለጠቅላይ ሚኒስተርነት ላጬ የትኛውም ሰብዕና ሊሆን ፈጽሞ የማይገባው ዳጎስ ያለ ግድፈት ነው። የንግግር ጥበብ አስተምህሮ ስስነት ይህን መሰል ነጥሎ የመምታት ግድፈትን ሊያመጣ ይችላል። ከህዝብ ፊት ኢትዮጵያን ያህል አገር ተወክሎ ሲቀረብ፤ በመንፈስ የገዘፈች እናት ምድርን መምራት የተለይ መሰጠትን እንደሚጠይቅ በየደራጃው ያሉ የፖለቲካ መሪወች ሊገነዘቡት ይገባል። መሪነት የአቦሰጥ ገጠመኝ ሊሆንም አይገባም።
በዚህ አጋጣሚ እላፊው ቢቀጥል ፍርሻ ሊመጣ ይችል ነበር። አወያዩ ጋዜጠኛ ማህል ላይ ገብቶ የሥርዓት ጥሰቱን አስቁሞታል። ግን ይህን መሰል ሰብዕናን ጨምተን የኢትዮጵያን ፖለቲካ ለምንከታተለው፤ ተሚመሩት ድርጅት፤ ወይንም ክልል ውስጥ ምን ዓይነት የአግላይነት ሁነት ሊኖር እንደሚችል ግብረ መልሱ አሳይቶናል። ሊታረምም ይገባል።
የጎንደር እና የጎጃም የአማራ ንቅናቄ የተፈጠረው የአቶ አባይ ዘውዱ ኢትዮጵያን የምንመራው እኛ ነን ብለው ባሳዩት ያበጠ ድፍረት ምክንያት ነበር። የአማራ ክልልን ጥሰው ገብተው ወንጀል ፈጸሙ፤ መጨረሻቸውም #የላመ ዕድል ሆነ።
በክርስትና ዕምነት ተከታዮች ዘንድ " ሁሉ ተፈቅዶልኛል፤ ሁሉ ግን አይጠቅምም።" የሐዋርያው፤ የመምህሩ፤ የወንጌላዊው ቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት ነው። ቀስ አድርጎ መያዝ ያስፈልጋል። ጎንደሮች ባለ ቅኔ ናቸው። ይህን ሲገልጹት "ልክን ማወቅ ከልክ ያደርሳል።" ይላሉ።
ሌላ አዙሮ ማዬት ያስፈልጋል። አንገት የተሰራው አዙሮ ለማዬትም ነውና። የውጭ ጫናም ቢኖርም ህወሃት ቱባ ባለሥልጣናቱ ባሉበት ፈቅዶ #ስልጣኑን ማስረከቡ ለእኔ የታምር ያህል የምመለከተው ክስተታዊ ጉዳይ ነው።
በሌላ በኩል ብአዴን እንጂ ደህዴን አልነበረም ለኦህዴድ ሙሉ ዕድሉን አስረክቦ አጨብጭቦ ባዶ እጁን የቀረው። መሬት ላይም ይሁን የሎቢ ተግባሩን ያረጋጉት የአማራ ልጆች ናቸው። ሦስት ጣምራ ክስተት ነው ከዚህ ላይ ተዋህደው ዛሬ ለምናያቸው አዲስ ገብ ፖለቲከኞች የዕድል በር ተከፍቶ፤ ምስጋናው ቢቀር #ዘለፋው በፍጹም የተገባ አይደለም።
ይኑረው አይኑረው አላውቅም ብልጼው የፖለቲካ ድርጅት የሥነ ምግባር መመሪያ፤ ልጆቹን፤ አካሎቹን አደባባይ ከመላኩ በፊት ኢትዮጵያዊው ይሉኝታው ቢቀር፤ ሰዋዊ አክብሮት በብልጽግና ዲስፕሊን ውስጥ አንገት ሊደፋ አይገባም።
የሥርዓት፤ የአካሄድ ስብሰባዊ ሂደትን ያስቀደምኩትም ለዚህ ነው። እስከ አሁን በብልጽግና በኩል ከፍተኛ ቁንጮ የመንግሥት አካላት ናቸው በክርክር ላይ የማያቸው። አንድ ጥያቄ ተዚህ ላይም ላንሳ? ብልጽግና ፓርቲው ውስጥ ቋሚ ተግባራትን የሚከውኑ ፋንክሽነሪወች የሉትም ማለት ይሆን? የመንግሥት አካላትን ፊት - ለፊት እያቀረበ ያለውን? ምክንያቱም የፖለቲካ ድርጅት ውስጣዊ መንፈስ አላይም።
ይህ አካሄድ የኢትዮጵያ መንግሥት ከሚባል ይልቅ፤ የብልጽግና መንግሥት ቢያስብለው ምንም ግድፈት የሌለበት ሆኖ ነው ያገኜሁት። ይህ ከሆነ በየሚኒስተር ጽህፈት ቤቶች ዕድገት፤ ዕድል በር የሚከፈትላቸው #ለብልጽግና ፓርቲ አባላት ብቻ ይሆናል ማለት ነው።
እጅግ ያሳሰበኝ በኽረ ጉዳይ ደግሞ ይህ ኩነት እንደ አንድ ብሄራዊ መንግሥት የሁሉም #አባትነት ቋሚ መርህን የሚፃረር ይሆናል ባይም ነኝ። እርግጥ ነው አውራው የብልጽግና ፓርቲ መሆኑን ባውቅም፤ በግላጭ እንዲህ መቅረቡ በየተቋሙ ያሉ፤ የሚኖሩ የሚሰሩ ባለ መሃያወች፤ ዝምተኛው ይሁን የሌላ የፖለቲካ ድርጅት አባላት ስውር ጭቆና ሊደርስባቸው፤ ስውር መገለል ሊደርስባቸው ይችላል።
#ፌድራሊዝም እና ኢትዮጵያ።
ፌድራሊዝም ለኢትዮጵያ ህልም ነው። ህወሃት ሥሙን ስለለጠፈ ፌድራሊዝም በኢትዮጵያ የለም። ልሙጥ ነው። አለ ከተባለ አማራ ክልል ብቻ ነው። አማራ ክልል ላይ የዞግም፤ የዜግነት የፖለቲካ ድርጅቶች የመወዳደር አንፃራዊ ነፃነት አላቸው።
በሌላ በኩል አማራ ክልል ብቻ ተለይቶ የኦሮሞ፤ የአገው፤ የአርጎባ፤ የቅማንት ነዋሪወች የወረዳ፤ የዞን ዕድል ተሰጥቷቸዋል። የሚገርመው በኬሚሴ ያለው የአማራ ህዝብ በራሱ ቋንቋ የመማር፤ የመዳኜት መብት የለውም። ልክ በኦሮምያ ክልል እንዳለው ሚሊዮን የአማራ ህዝብ አንገቱን ደፍቶ፤ ማንነቱን አስጨቁኖ ነው የሚኖረው። ይህ በፍጹም የፌድራሊዝምን መርህ የተከተለ አካሄድ አልነበረም። አይደለምም። ይህን የአማራ ክልል ብልጽግናም፤ አቤቶ አብንም ሞግቶ አሳምኖም ለማስተካከል የተደረገ ሙከራ የለም።
ይህም ብቻ አይደለም። ለሙ መተከል በቤንሻንጉል ጉምዝ እንዲከለል፤ ወልቃይት፤ ጠገዴ፤ ጠለምት፤ አዳርቃይ፤ ማይጠምሪ ራያም በትግራዬ ክልል እንዲሆኑ ተደረገ። የአማራ ህዝብ የተፈጸመበት ግፍ ብዕርም ብራናም አይችለውም።
ሁላችሁም እንደምታውቁት አባይን ከነምንጩ የመቆጣጠር ህልም ያላት ግብጽ ናት። ይህን ህልም "የወተት አንጀት" ይለዋል ዓለም ዓቀፋ ጋዜጠኛ አቶ ዓለምነህ ዋሴ እስከ ጋንቤላ የመውሰድ ህልም በህወሃት የታቀደ ነበር። የአባይ ግድብ አሰራርም ከዚህ ሃሳብ ጋር #የተኮራረፈ ሳይሆን የተዋህደ ኩነትም ነው። ወደፊትም ህወሃት ዕድሉን ካገኜ ይህ አይቀሬ ፕሮጀክቱ ይሆናል። ህወሃት ገብ የአማራ ልጆችም ይህን ግንዛቤ ሊያስቡበት ይገባል። ነገም የዳመነ ስለመሆኑ ከህወሃት ጋር ተዳብሎ ተስፋን አሳካላሁ የሚለው ዕሳቤ።
በሌላ በኩል ሽዋ ላይ በደራ፤ በደብረዘይት፤ በናዝሬት፤ በሐረር፤ በድሬ፤ በአዲስ አበባብም የህወሃት ትልም የአማራ ህዝብን ስሜት የማጫጫት ተግባር በሥልጣን ዘመኑ በስፋት ሰርቶበታል። አሁንም የቀውስ መሪ ሆኖ የአማራ ህዝብ ከአገልግሎት ዘርፍ ውጭ ይሆን ዘንድ፤ የአማራ ክልል የጦርነት ምድጃ እንዲሆን ተግቶ እየሠራበት ነው። በሌላው የፖለቲካ ሊቃናት ሲታደም ግን በአህትዮሽ ነው። "#ስሜነኞች" በሚል።
በሌላ በኩል የእጩ ጠቅላይ ሚኒስተር የፌድራሊዝም ዕውቀትም ደረጃውን ለማየት የቻልኩበት አጋጣሚ እንደሆነ የሚያሳጡ አመክንዮች አሉበት።
#የአማራ ህዝብ የአኗኗር ዘይቤ ግሎባል ነው። ህብራዊነቱም የጸደቀ ነው። ሥልጡንም።
"ከሥያሜው ጀምሮ ከክልል ያልተሻገረ ፓርቲ እንደምን ብሄራዊ ተባለ፤ እንደምንስ የኢትዮጵያ ወጣቶችን አድሬስ ሊያደርግ አይገባም።" ይህ የክብርት እጩ ጠቅላይ ሚኒስተሯ ሙግት ነው ለአቤቶ አብን።
አብን በሚመለከት የማከብረውን ጋዜጠኛ ተቦርን ለኢዜማ የሰጠውን ሥያሜ ለአብን ቢሰጠው፤ "ሙሽራ ሁን ስንለው ሚዜ ሆኖ ተገኜ።" አብን ትንፋሻቸው የሆነ የአማራ ልጆች እልፍ ነበሩ። ይህን ጸጋ እና በረከት #እልፍ ማድረግ የተሳነው አብን እንኳንስ አማራን ሊያድን እራሱንም ማዳን ያልቻለ፤ በህዝቡ ፊት - ለፊት በሙሉ እራስ መተማመን ሊቀርብ የማይችል ሆኖ ነው ያለው።
ወደ ዲያስፖራም ቢወጣ ወጀቡን ሊቋቋመው አይችልም - አቤቶ አብን። አገር ቤት ትናንሽ የገጠር ከተሞች እንኳን የተጠለለበትን የፖለቲካ ድርጅት የሚያስጠጋ ሆኖ አይታይም። 5 ሚሊዮን የአማራ ወጣት ከትምህርት ገበታ ሲገለል ይህን የዕውቀት ድርቀት ዛሬ ሳይሆን በዛሬ 10/15/20 ዓመታት ነው ጉዳቱ የሚታዬው። የአማራ ህዝብ ተስፋ ከአብ መዳፍ ውጭ ነው። ስለዚህ ክብርቷ ከዚህም ባለፈ ቢገስጹት የፈለገውን፤ የፈቀደውን መደፈር ማፈስ የግድ ይሆናል።
ይህም ቢሆንም ግን በመርኽ ደረጃ አዲስ አበባን ህወሃት ሥልጣኑን ሲያስረክብ 50+ የአማራ ህዝብ ነበር። በመላው ኢትዮጵያም ሚሊዮን አማራወች ዬኖራሉ። ሚሊወኖቹ አማራወች ከክልል ውጭ የሚኖሩት ክልል እንሁን ማለት የሚያስችል ፖለቲካል አቅም አላቸው። ዞን እንሁንም ማለት ይችላሉ። ወረዳም እንሁን ማለት ይችላሉ። ግን ልሙጥ ነው። ፌድራሊዝም በኢትዮጵያ ይህን ሲመልስ ነው ኢትዮጵያ ፌድራሊዝም ተርጉማለች የሚባለው።
ነገረ አማራ "ጽድቁስ ቀርቶ በወጉ በኮነነኝ።" የፖለቲካው ውክልና ቀርቶ፤ በራስ ቋንቋ የመዳኜት፤ በራስ ቋንቋ የመማር፤ የመምረጥ ግዴታ ብቻ ሳይሆን የመመረጥ #መብት ቀርቶ በአቀናው በዓት መፈናቀል ዕጣው፤ መኖሩ ስቃይ ሆኗል። ይህ የፌድራሊዝምን ጠቅላላ መርህ የሚጠቀጥቅ ብቻ ሳይሆን የሚድጥም ነው። ክብርቷ ስለፌድራሊዝም ዕውቀታቸው የሚታዬው ከዚህ አንፃር ነው።
ፖለቲካ ለሰው ነው። ለሰው ከሆነ ሰውኛ የሆኑ ዕውነቶችን ለማስገኜት ነው የአንድ አገር የፌድራሊዝም የአወቃቃር ዘይቤ የሚያመሳጥረው። ይህ የለም። አለመኖሩ ብቻ ሳይሆን አትመኙም ነው ክርክሩ። አብን በተደራጀበት ዓላማና ግብ ቢሆንማ ስንት የአብሮነት ህብርን አስከብሮ ተከብሮም እራሱ በቀጠለ። ግን ………?
በዚህ አጋጣሚ ክብርቷ ሞጋቾቻውን እኛን ምሰሉ ብለዋል። ብልጽግናን ተቀላቀሉ ሲሉ ተደምጠዋል። እኔ ደግሞ መሪነት ገጠመኝ ስላልሆነ ፌድራሊዝምን ጽንሰ ሃሳቡን፤ የፌድራሊዝምን መብት እና ግዴታ ብስጭት ሳያጎርስቱ እንደ እናትነት በስክነት ያነቡት ዘንድ እጋብዛቸዋለሁኝ።
በሌላ በኩል ግሎባል ደረጃም በውጭ የምንገኝ በኢትዮጵያኒዝም ማዕቀፍ ውስጥ ያለንም እንሁን በአማራነታችንም እማናፍርበት የአማራ ልጆች ትጋት ነው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ትንፋሹ ሊዘልቅ የሚችለው።
ይህን በብዙ አመክንዮ ላቀርበው ብችልም አንድ ምሳሌ ብቻ ላቅርብ፤ ለመሆኑ በአንድ ቀን 600 የሬቻ ባዕልን አክባሪ በጭፍጨፋ ያሳጣንን ያን አሰቃቂ ገጠመኝ ማን ይሆን ለዓለም ዓቀፍ ዕውቅና ያበቃው? እሳቸው ነበሩበትን? እእ።
ስኬቱ የአማራ ልጆች ብርታት እና ጥንካሬ ነው። ኢትዮጵያ ለእኛ ትንፋሻችን ናት። አብን እኮ ያልተሳካለት ዞጋዊ ነኝ አለ፤ ግን ተጠቅልሎ ከዜግነት የፖለቲካ ድርጅቶችም በላይ ሆንኩ ብሎ ከአንዱም ሳይሆን ቀኑ #ድብ አለበት።
በዚህ ዙሪያ ለክብርቷ አንድ ጥያቄ በአክብሮት ላቅርብ፤ ኦነግ የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር ምርጫ እሳተፋለሁ እያለን ነው። በአማራ ክልል፤ አዲስ አበባ ላይም ብሏል፤ ኦፌኮም አዲስ አበባ ላይ ብሏል እነሱንም ለአብን ባለው የቡጢ አቅም ልክ መሞገት ይችሉ ይሆን???? ኦነግም ይሁን ኦፌኮ ከክልል ያላለፈ ስያሜ ስላላቸው።
"#የነ ቶሎ ተሎ ቤት ግድግዳው ሰንበሌጥ።"
ክብርት እጩ ጠቅላይ ሚኒስተር ሆይ! ቅኔኛ መሆነወት ድንቅ ነው። ብዙ ከመድከም ያዳነ አገላለጽ ነው። ይህ ለዚህ ምርጫ ጊዜ ብቻ ሳይሆን የሆነ ነገር ሲከሰት እሱን ተከትሎ ለሚፈጠሩ ቀንጣ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ ህብረቶች፤ መድረኮች፤ ቅንጅቶች፤ መተባበሮች ሁሉ በዘለቄታ ሊጠቅም የሚችል አስተምህሮ ስለሆነ፤ የፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉ በአወንታዊ ያዩት ዘንድ በትህትና ላሳስብ እፈልጋለሁኝ።
በቅርቡ በነበረ አንድ ክርክር ኢህአፓን ተቀላቅለው፤ ትብብር ለኢትዮጵያን ወክለው ለክርክር የቀረቡት የፓርላማ ሞጋች ያን ማንነታቸውን ይዘው ነበር ሙግት ላይ የቀረቡት። የፋናው አወያይ ጥያቄው ኢህአፓ ተኮር ሆኖ ይህን ሥርዓት ማስያዝ ሲገባ መልሱ ላይ አተኮሩ። ለምን? ገና ሳይዋህዱ ነውና የተቀላቀሉትን ትብብር ወክለው አደባባይ ላይም የወጡት።
ክቡርነታቸው አቅም ያላቸው፤ የሰከኑ ወጣት በፓራላማ ሲሞገቱ የምናውቃቸው ነበሩ፤ በተዋህዱት አዲስ ፓርቲ ውክልና ግን ዳገቱን መውጣት አቃታቸው። ለምን? የጥሞና፤ የማጥኛ፤ የመዋህጄ ጊዜ አልነበራቸው። ጥድፊያ ነው። የተጽዕኖ ፈጣሪም ሽሚያ። የፖለቲካ ድርጅት አባልነት ከእጩነት ተጀምሮ ነው ወደ ሙሉ አባልነት ሽግግር የሚደረገው። ዲስፕሊኑ እየተለካ። የአኗኗር ዘይቤው በፖለቲካ ህይወት ላይ እየተመዘነ። የማዬው ግን ይህ አይደለም። ስኬቱም ሩቅ የሆነው በአመሠራረት ችግር ነው።
ለምን? በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የሰከነ ሂደት ልምድ የለም። ብልጽግና ላይ ያለው ችግር እኮ እንደ አለ የኢህዳግ አካል፤ መርህ፤ ያቀፋቸውን ሦስቱን ድርጅቶች አባላት እንደ አለ ነው የተቀበለው። በትውስት ማንነት ስኬቱ፤ ፈተናን የማለፍ አቅሙ ዳጥ ነው። ስለዚህ የክብርቷ "የእነ ቶሎ ተሎ ቤት" ከኦህዴድ ወደ ኦዴፓ፤ ከኦዴፓ ወደ ብልጽግና የተሸጋገረው የራሳቸውን ፓርቲያቸውን ብልጽግናንም የዚህ ወጀብ ተጠቂ ስለመሆኑ ላጠይቅላቸው እሻለሁኝ። ችግሩ የትብብር ለኢትዮጵያ ብቻ ስላልሆነ።
ህወሃት ሦስቱን አባል ድርጅቶች ብአዴን፤ ህወሃት፤ ደህዴን በግንባር አደራጅቶ ሲመራ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የሚባል መረብ ነበረው። መረቡን አጥብቆ የሚይዝ የአደረጃጀት መርህ ነበር። ብልጽግና በትውስት ሲወስድ አባላቱን አካላቱን ማንነታቸውን እንደያዙ ግን በተረተረ ኔት ነበር።
ለዚህም ነው የበታች አካሉ መፍረክረክ የሚታዬው። የቀኜ አፈጣጠርም፤ በኦሮሞ ብልጽግና፤ ምን አልባት ቤንሻንጉል ላይ ይህ ፈተና አይቀሬ ነው። በሱማሌ ክልል ያን መሰል ፈተና መቋቋም የተቻለው የክልሉ አመራር ጥንካሬ ነው። እንጂ የብልጽግና ፖለቲካል ፓርቲ ብርታት አይደለም።
ያ ቢሆን እንዲህ አማራ ክልልን መንፈሱን አያጣም ነበር። የሰሞኑ የህወሃት አንደበቶች ጎርፍም በሱማሌ ክልል እንደ አማራ ክልል ያሰቡትን ቀውስ ሊያሳኩ ስላልቻሉ ነው። ምክንያት ሱማሌ ክልል የህወሃት መዳረሻ መሆን ቀርቶበት መሰናበቻ ስለሆነ።
የሆነ ሆኖ ምርጫ ብቻ ታስቦ፤ ለውጥ የሚመስል ነገር ሲመጣም ያን ታኮ ተደርጎ የሚደራጁ የፖለቲካ ተቋማት ተልዕኳቸው መርኽ ሳይሆን የገጠመኝ ጥገኛ ስለሚሆኑ ዝልቀታቸው ፍርክርክ ይሆናል።
ለሰከነ ፖለቲካ የተረጋጋ፤ የሰከነ፤ ቀድሞ ያሰበ ትልም ለግብ ለትውልድ ለአደራም የመሆን አቅም አለው። ስለሆነም ይህ ድግግሞሽ እና ውድቀትን በማሰብ ስክነትን ደራሽ እልህና ስሜታዊነት እንዳይመራው የሚያስገነዝብ አገላለጽ ለሁሉም ጠቃሚ መልዕክት ነው። "የእነ ቶሎ ተሎ ቤት ግድግዳው ሰንበሌጥ።"
በሌላ በኩል ስለ ፖለቲካ እስረኞች ክብርቷ ገረፍ አድርገው ያለፋትም ሁነት አሳዛኝ ነው። ክብርት ወይዘሮ መስከረም አበራ ትንታግ ብዕረኛ፤ መምህርት፤ የፖለቲካ ተንታኝ፤ ደፋር ለእነሱ ዛሬ ለዚህ መብቃት የተጋች አርበኛ ናት። እሷ ካቴና ላይ ናት።
እሷን ለምሳሌ አነሳሁኝ እንጂ በርካታወች በዘመነ ህወሃትም ለነፃነት ሲታገሉ፤ ታስረው የነበሩ በእነሱ ግብር የመጣ ብልጽግና አሁን ደግሞ ያሰራቸው ናቸው። ይሉኝታ የሚባል ታላቅ አስተምኽሮ ኢትዮጵያ አላት። ክብርት ወይዘሮ መስከረም አበራ ብቁ ፖለቲከኛ፤ አንደበተ ርትዑ ወጣት ናት። ግን ካቴና ላይ ናት። ይህ የእኔን ውስጥ ያቆስለዋል።
አንዲት ቅንጣት አስተዋፆ ያላደረጉ አዘኔታ ሲርቃቸው አዝናለሁኝ። ሴት ፖለቲከኞች ወደ ፖለቲካ ስልጣን ይመጡ ዘንድ በትጋት የሞገተ እንደ እኔ ብዕር አልነበረም። ያ ሁሉ ተደክሞ የልቤ ደርሶ ዛሬ ወህ ብል ምንኛ በታደልኩ ነበር። ግን አልሆንም። ሃሳብ ሊፈራ አይገባም። መሞገት ይቻላል።
#የውይይቱ ዓውድ።
ለቲም ብልጽግና ወፍ ያወጣቸው ምክንያታዊ ጉዳይ የኢህአፓ ጸሐፊ ጋዜጠኛ ሚስጢረሥላሴ ታምራት አለመገኘታቸው ነበር። ሁሎችም ተሟጋቾች በተመጣጣኝ የአቅም ሁኔታ ላይ ነበሩ። የነፃነት እኩልነት ፓርቲ የመግቢያ ንግግር የፖለቲካ ድርጅቶች የህዝብን ህይወት የመኖር መርኽ የተከተለ፤ ተጨባጩን በፋክት ያቀረበ መሳጭ መሰናዶ ነበር።
#ብልጽግና አውራ ፓርቲ ነው። አገር እየመራ ያለም።
ይህን ሃሳብ ኢትዮጵያን እንደ አፍሪካ አንከርነቷ ስታዩት ከብልጽግና ተሟጋቾች መድረኩ የፕሮፖጋንዳ ሊሆን አይገባም። ዕድሉን አስክኖ በዲስፕሊን በፓርቲያቸውን ፕሮግራም፤ በእያንዳንዱ ዘርፍ ላይ ያለውን የፖሊሲ ትልም፤ ፖሊሲውን የሚተዳደርበትን የፖለቲካ ፕሮግራም፤ ፕሮግራሙን የሚመራው አይዲወሎጂ፤ አይዲወሎጂው የሚመራበት መሪ ዕቅድ ፋክት ገብ ሆኖ ሊቀርብ ይገባ ነበር።
"ብልጽግና የትውልድ፤ ብልጽግና የዕሴት፤ ብልጽግና የተስፋ፤ ብልጽግና የነገ፤ ብልጽግና የመደመር፤ ብልጽግና አሻጋሪ ወዘተ ……" ከብልጽግና ጋር ፍቅር ለሚይዛቸው ካድሬወች ህሊና ማረፊያ ሊሆን ይችላል። ለምርጫ ውድድር ነገ ምን ከጃችሁ ከደጃችሁስ ነው ጥያቄው የዳቦ፤ የመኖር ዋስትና፤ እኩል የመታዬት ጥማት፤ የዜግነት አብሮነት፤ የተስፋ ጭብጥነት ወዘተ …
ኢትዮጵያ ለሚቀጥለው አምስት ዓመት ብልጽግና 50+ አምጥቶ እንደሚያሸንፍ እኔ አምናለሁኝ። ስለሆነም የፖለቲካ ፓርቲ መርህ፤ አካሄድ፤ የአራር ዘይቤ ከበቀል እና ከቂም፤ ከማስጨነቅ እና ከቀውስ የዳነ ክህሎት፤ ጥርት ያለ የማያወላዳ ርዕዮት፤ ሥርአት አልበኝነት የሚመክት ዲስፕሊን፤ የሰላም ጸኃይን የሚያፈልቅ ሁነት ወዘተ …… ካለፋት ስምንት ዓመታት ድክመቶች፤ ዘመን ሰጥ - ስልጣኔወች እና ፈተናወችን ለመሻገር ያለው የህሊና፤ የመንፈስ፤ የመዋለ ንዋይ ፍሰት ምንድን ነው? እስከ አሁን ምላሽ የለም።
ሁሉ ነገር በአንድ ጠቅላይ ሚኒሰር ህሊና ቀመር ብቻ ተስፋን መሰነቅ አደጋው ብዙ ነው። ቲም ወርክ ላይ ምን መሰናዶ አለ? ግንዛቤው ቢያንስ ተመጣጣኝ ለማድረግ የማብቃት ብቃት ይጠበቅ ነበር።
ያዬሁት፤ ያዳመጥኩት በተመሳሳይ ፍሬም ወርክ ድግግሞሹ ተስፋን #ሲያችከው ነው። ብልጽግናን ተስፋ ለሚያደርጉ ማለቴ ነው። ከሁሉ ሰላምን አስፍኖ ኢትዮጵያን ከስሜን እስከ ገቡብ፤ ከደቡብ እስከ ምስራቅ፤ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ለመምራት ምን ታስቧል? ይህ የማይነካ ጥያቄ ነው???
ሌላው ሁሉም የፖለቲካ ድርጅት የፓርቲውን የውስጥ መሻት ማስተርድ ሊያደርገው ይገባል። ምክንያቱም አገር እና ትውልድ በጥበብ እንጂ በዘልማድ ሊመሩ ስለማይችሉ። ኢትዮጵያ ደግሞ ብዙ በጣም ብዙ አመክንዮዊ ስኬቶች የሚጠበቅባት አገር ናት። በአህጉርም፤ በዓለም ዓቀፍም ደረጃ።
#እርገት ይሁን።
በመጨረሻ የነገ እጩ ጠቅላይ ሚኒሰተር ጋንቤላ ክልል ቢሆን ደስታውን አልችለውም። ይቅናው! አሜን! ለምን? ኢትዮጵያዊነት ተለጥፎ ሳይሆን እኔነቴን የሚመራ ጠቅላይ ሚኒስተሬ ስለሆነ።
"ጠንካራ ሀሳቦች የታዩበት ክርክር - ፓርቲዎቹ ለወጣቶች ምን አዘጋጅተዋል? | EBC | Political Debate | Ethiopia | Election 2018 |"
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
ኑሩልኝ አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie.
24/03/926
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ዕውነት ጋራጅ ወይንም ወጌሻ አያስፈልገውም።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።