#ራስጌ፤ #እግርጌ፤ #ቁርጭምጭሚትን ያላገኜም ተገኜ --- በዘመነ #ብልፄው።
"አቤቱ ንፁህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።

#ምዕራፍ ፲፰።
ዘለግ ያለ ዕይታ ነው ምርጫ ሂደቱን በዚህ ብከውነው ፈቃዴ ነው ግን ብዕሬ ከፈቀደች ብራናዬ ይሁን ካለ።
#እፍታ።
የአፍሪካ ግርማ ሞገስ፤ የዓለም ዲፕሎማሲ ፬ኛ ከተማ፤ የኢትዮጵውያን እኩል የተስፋ አንባ በሆነችው ውብ፤ ድንቅ፤ ለጋስ፤ ሩህሩህ፤ ህብራዊት፤ ተደሟዊት #ማንጠግቦሽ በሆነችው የእኛይቱ እቴጌ አዲስ አበባ ላይ ብልፄው ግልጽ የሆነ አቋሙን ሰሌዳው ላይ ለጥፎ አነበቡኩት፤ ተርጉሙት፤ አመሳጥሩት እያለን ነው።
እኔ እንኳን የብልጼው ለቀቀቅ ያለው መጠሐፋ ከመቅደሙ በፊት በዚህ ዙሪያ በጣም የቀደመ ዕይታዬን ማጋራቴን ድፍን የቤታችን ቋሚ እና ጽኑ ታዳሚወች ያውቃሉ። አዲስዬ ከመስከረም 5/2011 ዓም ጀምሮ በኦሮምያ ክልል ህግ ነው የምትተዳደረው የሚል አቋም ነው ያለኝ። የሂደቱ ሁሉ ግብረ መልስ ያን ስለሚያመለክት።
በኢትዮጵያ ፖለቲካ አንዱ አቅላይነት የተለመደ ነው። ገዢው ብልፄውም ይሁን ተደማሪ፤ #ተቀላች፤ ተመጋጋቢ፤ ተፎካካሪ፤ ተቃዋሚ፤ የፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉም አንዱ ሌላኛውን ሲያቀል፤ ሲያጣጥል ውሎ ያድራል።
ግርም ይለኛል። በማጣጣል፤ በማቅለል አቅምን መገንባት አይቻልም። አቅም አቅም ፈጣሪን፤ አቅም አክባሪን፤ ለአቅም ዕውቅና ሰጪን፤ አቅም አድራጊነትን ይጠይቃል።
ምንም ሳይኖር የደከምክበት፤ እራስህ - የምታዝበት፤ አንተው የምትመራው ወይንም የምታስተዳድረው የተደራጄ አቅም በሌለበት ቀን ቆርጠህ፤ ጊዜ ወስነህ በዚህ ጊዜ፤ በዛኛው ጊዜ ብትል፤ የሰሞናት የሚዲያ አትኩሮት በገፍ አንተም አግኝተህ፤ ፎቶህን ለጥፈው ከይቱብ ድጎማ ሊያስገኝ ይችል ይሆናል እንጂ የመፍትሄ ጎዳና በዚህ መስመር ትናንትም አልመጣም፤ ዛሬም አልተገኜም ነገም አይመጣም።
የከፋን ቤተሰቦች ስደቱም፤ ምቾቱም ሃራም ብለው ድላችን በጠበንጃችን ያሉት እንኳን ቢሆኑ አቅማቸውን በቅጡ የማስተዳደር፤ ዕድሎችን ሰዓት ሳያሳልፋ መጠቀም ካልቻሉ እጅግ አሰልቺው፤ አታካቹ፤ የከፋ መስዋዕትነት አስከፋዩ የትጥቅ ትግል በተራዘመ ቁጥር መከራውን፤ ፈተናውን፤ ውጣ ውረዱን የመቋቋም አቅሙን በቀጣይ ለመተንበይ ያዳግታል። ጦርነት እና ሁነቱ ተገማች አይደለምና። ከሁሉ ዓለም አቀፍ ሁነቶች የትኩረታቸው አቅጣጫ ተለዋዋጭ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል።
የሆነ ሆኖ እነሱም ቢሆኑ የትጥቅ ትግልን የመረጡት የሚታገሉትን አካል አቅልለው መመልከት አይገባቸውም። #ብልጼውም የከፋኝ ግራ ቀኝ ቤተኝችን አቅልሎ፦ አንኳሶ ሊመለከት አይገባም። ቀን የሚሰጠውን "የእናት ልጅ አትሰጥም" ይላሉ ልባሞቹ ጎንደሬወች ሲቃኙ። መፍትሄ ሰጪወች ጊዜያት ናቸው እንደማለት።
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ተቃዋሚ፤ ተፎካካሪ የሚሉ ይዘወተራሉ። ተደማሪም አብይዝም ሰጥ ሥያሜ ነው። እኔ ደግሞ ተመጋጋቢ፤ ተጠማኝ፤ ተቀላች እያልኩ አክላለሁኝ። ከሰሞኑ ቢቢሲ ኢዜማ እና አብን ተቃዋሚ የሚል ጥፎ አነበብኩኝ። ውሽክም አልኩኝ።
1) ተቃዋሚ ለሚለው እኔ #ታጣቂወች ልኩ ናቸው ባይ ነኝ።
2) ተፎካካሪ ለሚለው ደግሞ እናት ፓርቲ እና ኢህአፓ ይመጥኑታል ብዬ አስባለሁኝ።
3) ተመጋጋቢ የፖለቲካ ድርጅት ከብልጼው ጋር ኢዜማ ይመስለኛል። ኢዜማ ነው አላልኩም። ይመስለኛል ነው ያልኩት። ጥናት ስላልሰራሁበት።
4) አንዱ የኦነግ ቅርንጫፍ ደግሞ ተደማሪ ነው።
5) እራሱን አስረክቦ የብልጼው ችሮታ አብን ደግሞ ተቀላች ነው። ሙሉ አቅሙን፤ ሙሉ ማህበራዊ መሠረቱን ያጣ፤ በብልጼው ላይ ብቻ ተጠምኖ የሚገኝ። ዕውነት ለመናገር አብን በአፍላው ከብአዴንም በላይ ተቀባይነት ብቻ ሳይሆን ተወዳጅነትን ያገኜ የወጣት አማራ ተስፋ ነበር። ገኑ ወጥቶ ግን ፈቅዶ ክብሩን፤ ልዕልናው ለብልፄው የገበረ።
ያን የመሰለ፤ አቻ የማይገኝለት፤ ሙሉ መንፈስን የገዛ የክብር ጸጋ አቅም አስከብሮ ማስቀጠል ሙሉለሙሉ ተስኖት ባለፋት ዓመታት ከፍቅር - ተፍቆ፤ ተፈግፍጎም ብቻውን የቆመ ሆኗል። ይህ ለአማራ ፖለቲካ ከባድ ራስምታት ነው። በፍጹም መጠገን አይቻልም።
ተመልሶም ያ ዕድል አይገኝም። የባከነ ጊዜ፤ በከንቱ የቀረ ድካም።
የቀሩት የአብን ሥ/አ/አ ቁጭ ብለው መገምገም እንኳን የቻሉ አይመስለኝም። ስንት ነገር አጡ? ከእጃቸው ምን ያህል ፍቅር አመለጠ? በምንያህ መከበራቸው አደጋ ውስጥ ተገኜ? ከስንት ጊዜ በኋላ አሁን ለፓርላም እጩነት ፎቷቸው ተለጥፎ አየሁት። አዬ አማራዬ አመድ አፋሹ።
ወርቅ ከቀለጠ ይፈሳል። አብን እንደዛው ነው። በነገራችን ላይ አብን ይሁን ኢዜማ፤ ከብልጽግና የተቸራቸውን የሥልጣን ስጦታ መቀበላቸው እኔ ጥሩ ገጠመኝ ነው ብዬ ነው እማምነው። ብልፄው ለጋስ ነው። የስልጣን ቻሪቲ ቢያቋቁምም ያዋጠዋል።
ቸርነቱ የበረከተለት ብልፄው በመጪው ምርጫም 80 እየቻለኩኝ ለቅርቦቼ ለቅቄያለሁ ብሏል ለውሃ አጣጮቹ። ዋው። ብልፄው ትችላለህ ተብሎ ይጨብጨብልህ ይሆን? ከዚያስ አጤ በራስ መተማመን አድራሻው የት ይሆን? ሙሉ ፭ ዓመት እንዴት እና እንደምንስ ትኳኳኑ ይሆን? ለዛውም ነገ ተፈቀደ? ነገ የራሱ ማኒፌስቶ አለውና።
#የምርጫ ቦታ ድልድል እና የዕውነት ማሾ የነገረኝ።
ሰፊ ሚና፤ ልባም ዕውቅና በሚያስገኜው ነገረ አዲስ አበባ ላይ አብን #ትውር እንዳይል ብልፄው በይኖበታል። የኢዜማ ሊቀመንበር፤ ምክትል ሊቀመንበር አዲስ አበባ ላይ እንዲወዳደሩ ቦታውን ፈቅዶ ሲለቅ፤ አብንሻ ግን ወደ ጦርነት ቀጠናው ሥራ ያውጣህ ተብሎ ተሸኝቷል።
በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሙሉ የጥበቃ ጊዜ ነፍሳቸው ትርትር እያለች አብኖች በአማራ ክልል ይወዳደራሉ። ብልፄውም በተለይ ለአማራ ክልል እና የተወሰኑትን ቦታ ለቅቄያለሁ። አሸንፋኝ ብዬ። እንጂ ብፈልግ ያነንም እኔ ብወዳደርበት አሸንፍ ነበር።
ልግስናዬ እንጂ የእናንተ አቅም ለዚህም አይበቃም ብሏል። ጉርሻዋ ለአብን ትጣፍጥ ትምረር ሂደት ይነግረናል። ነፍሳቸው ተርፋ ፓርላማ ላይ ገበርዲን እና ከረባታቸውን ገጭ አድርገው ጉብ ……… ካሉ አብኖች። አብን ሲፈጠርም የተባዕት ንቅናቄ ነው። የገበርዲን እና የከረባት።
በፋኖ በኩል የተሰጠው መግለጫ ጠንከር ያለ ነው። ከዚህ በላይ ፋኖ ሊጨክን ይገባል ባዩ የ2013 ዓም ህብርን ወክለው እጩ የፓርላማ ተወዳዳሪ የነበሩት፤ የፋኖ የቅርብ ነኝ የሚሉት ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት አሜሪካን አገር በጥገኝነት ተቀምጠው፤ ከአሜሪካ ጥገኝነት ጋርም የተጠየፈ ሃሳብ ሲያቀርቡም አዳምጫለሁኝ።
መሳሪያ የያዘ፤ የተበሳጬ፤ እልህ ውስጥ የሚገኝ፤ ለዛውም አብዛኞቹ በወጣትነት ዕድሜ የሚገኙ፤ ቋሚ የሎጅስቲክስ በጀት አልባ ለሆነ የከፋኝ ሠራዊት ያወጣኽው "የጥብቅ እርምጃ ውሳኔ ልል ነው፤ አጠንክረው" የሰው ልጅ ሲባል ጭካኔ ብቻ ነውን? ዕድል ሲገኝ እንዲህ በቃ።
የአማራ ህዝብ ሙሉ 60 ዓመታት የመከራ ማሳ ነው። የኢንጂነሩ የጭካኔ ሃሳብ በማን ላይ ይሆን? የብልጽግና አካል፤ ይሁን የብልጽግና አባሉ፤ ሚሊሻው ይሁን አድማ በታኙ፤ ፖሊሱ ይሁን ፋኖ ያው አማራ እኮ ነው። የአማራ እልቂት የዓለም የህዝብ ቅነሳ ፕሮጀክትን ለማሳካት ካልሆነ በስተቀር የአማራን ትውልድ፤ ተስፋ የሚያበቅል አይደለም።
አንዲት እስክርቢቶ ገዝቶ፤ ቀለብ ሰፍሮ ያላሳደገ ፖለቲከኛ በመከረኛ የአማራ ወላጅ ላይ የሙት በቃ ፍርድ ቀራኒወነት ነው። የአማራ ህዝብ እንደ እህል ዘር ማለቁን አላስተዋሉትም። የአማራን ህዝብ የህሊና ነፃነቱን በዚህን ያህል ሁነት ማሰርም ፤ ማስደንገጥም፤ ስጋት እንዲያድርበት ማድረግ በፍፁም አይገባም።
ሌላው የአማራ ሊቃናት በተገደሉ ቁጥር ማን መሪ እያጣ እንደሚሄድ ፈላስፋ አያስፈልገውም። ከሁሉም የአማራ #እናት ስቃይ ሰው ሆኖ ተፈጥሮ ለአንድ የምርጫ ጊዜ ይቀጥል፤ አይቀጥል ለማይታወቅ ክስተት ይህን ያህል በረደን የአማራ ህዝብ የይሸከም ውሳኔ ከፋኖ መሪወች ይልቅ ህይወታቸውን ለማትረፍ የተሰደዱት የጭካኔ ሃሳብ ይሰቀጥጣል።
የዚህ ሁሉ መከራ ምንጩ አብን የተነሳበትን ዓላማ እና ግብ ለማስፈጸም የልምድ፤ የተመክሮ፤ የትጋት እጥረት ያመጣው ዶፍ ነው ለአማራ እናት። አብን አንዱንም የአማራ ህዝብ ጥያቄ ሳያስመልስ፤ ለብልጽግና የሥልጣን ዘመን ምቹ አልጋ ከመሆን የዘለለ ትሩፋት ለአማራ ህዝብ ያስገኜው ነገር የለም።
አብን ከብልጽግና ጋር ሰርቶም የአማራ ህዝብን የሁለት ትውልድ መከራ ቢያስቀር፤ ማስቀረቱ ቀርቶ ቢያስቀንስ፤ ይህም ቀርቶ በአማራ ህዝብ ላይ ያለው ንቀት መስመር እንዲይዝ ቢያስደርግ በምን ዕድል። አንድ ሰው ለሌላው መገበርን ሲፈቅ ቢያንስ የተነሳበትን ዓላማ እና ግብ አስፈጽሞ ሊሆን በተገባ።
ይህም ሆኖ ብልፄው በእጩ ጠቅላይ ሚኒስትሯ ክብርት ከወደ ጋንቤላ በአደባባይ የተሰጠው የአብን ዘለፋ፤ ማቃለል፤ በኢትዮጵያዊነቱ የመሳለቅ ሁነት ድልደላ ላይ መነሻው ከምን ለሚለው ማስተዋል ይመልሰዋል።
1) ብልጽግና ሙሽራ ነው።
2) ከኦነግ የተገነጠለው ሌላው ወገን ራስጌ ነው።
3) ኢዜማ እግርጌ ነው።
4) የአብን ደረጃ ዳሹን ሙሉለት ------?
#ውቢቱ ልዕልት አዲስ አበባ።
አዲስ አበባን በሚመለከት በቋሚነት የእኔ ፔጅ የሆናችሁት ታውቃላችሁ ስጽፍ የነበረውን። ለእኔ አዲስ አበባ በመንፈስ የኦሮምያ ክልል ከሆነች ቆየች። የቡራዩ መከራ፤ የለገዳዲ ለጋጠፎ አሳር፤ የአምስት የአዲስ አበባ ልጆች በመሃል አዲስ አበባ መገደል ሰማዕትነት። (ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ) እንደ ለውጡ ሰማዕትነት እዩት ብለውን ነበር።
ግን በመንግሥታቸው እነዛ ሰማዕታት ሲዘከሩ ሰምቼ አላውቅም። ሥማቸውንም አናውቀውም። ቤተሰቦቻቸው በምን ሁኔታ እንደሚገኙ አናውቅም። ምንም ያላደረጉ ንጹኃን ነው የተሰውት። አዲስ አበባ ለድላችን ግብር የሰው ታቅርብ ተብሎ፤ ለማህበረ ኦነግ ፈንታዚ።
በዛን ጊዜ 1300 የአዲስ አበባ ልጆች ጦላይ ታስረው ነበር። እንደ ዘመነ ህወሃት "አይደገምም" ብለው አብዛኞቹ ከእስር ተለቀዋል። በሃይማኖታቸው ይሁን በማንነታቸው አይታወቅም እስካሁንም እስር ቤት የሚገኙ ባለቤት አልባወች አሉ።
በሌላ በኩል 500000 የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪወች ፈቃዳቸው ሳይጠየቅ፤ ካደጉበት ቀዬ ከሱማሌ ክልል በአዲስ አበባ እና በዙሪያው እንዲኖሩ ሲደረግ የአዲስ አበባን እና የዙሪያ ከተሞች የአሉታዊ ዴሞግራፊ ለውጥ ስለመሆኑ ጭምቱ ፖለቲከኛ ዶር ለማ መገርሳ በአደባባይ ነግረውናል።
እሳቸውን የተኩት አቶ ሽመልስ አብዲሳም እጅግ የሚገርም ንግግር ልክ እንደ ህወሃቱ መሪ እንደ አቶ አባይ ወልዱ ያደርጋቸው ነበር። ቅጁን ነበር የወሰዱት። በሳቸው ልክ በጣም ከፍ ያለ የሥልጣን ልክን የማሳየት ሁነት በሌሎች የኦህዴድ ልጆች አላዬሁም። እኛ ነን እየገዛን ያለነው የሚለውን ለማስገንዘብ በየንግግራቸው ላይ ኃይለ ቃላትን ይመናገራሉ።
በሌላ በኩል አዲስ አበባን ከሁለት ከፍሎ አዲስ ከተማ ሸገር ብሎ የመሰየም ሁነትም፤ 50+ ለነበረው የአማራ ህዝብን ፖለቲካ ቅጥመጠን የማሳጣት የተደራጄ ተግባር ነበር።
በሌላ በኩል አዲስ ልጆቿ የኢትዮጵያዊነት ሁነት የውስጣቸው ማህተም ስለሆነ በዚህ ላይም አሉታዊ ዴሞግራፊ የህሊና ነቀላ እና ተከላ ተከውኗል። መንፈሱ ተበውዟል። የኮሪደር ልማት የፕሮጀክቱ ዓይን ህብራዊ ትስስሩን የመፈተን፤ የማሳካት ሁነት ተከውኗል። ከተማን ማሰልጠን መልካም ቢሆንም፤ ፕሮጀክቱ በውስጡ ያለው ረቀቅ ያለ መንፈስ ግን ለሳይለንት ማጆሪቱ ይመቻል ብዬ አላስብም።
ጉዳዩን በግርግር፤ በሁካታ ሳይሆን አደብ ገዝቶ ማጥናት፤ መጪው ጊዜ እኩል ፍትህን የኢትዮጵያ አዲስ ትውልድ እንዲያገኝ በማድረግ ዙሪያ ትጋት ይጠይቃል።
ወደ ቀደመው ጉዳዬ ወደ #ሽመልዚም ስመለስ አሁን ሁሉ ነገር ተደላደለ መሰል ተቆጥበዋል #መስቃን ከመዝራት። የሚገርመኝ አብዛህኞቹ በጸረ ህወሃት የትግል ስኬት አንዳቸውም አልነበሩም። እንዲያውም ተጠቃሚ ነበሩ።
ነገረ ኢትዮጵያ መሬት ላይ ባለ ተጨባጭ ንቅናቄ ብቻ ድል አይታፈስባትም። ወደፊትም። የዓለምን ይሁንታ ይጠይቃል። ለዛውም በስክነት፤ በብልህነት፤ በማስተዋል፤ ግብታዊ ባልሆነ የተረጋጋ ተግባር። በዚህ ዘርፍ ሬሳችሁ እንኳን ብትን አፈር አያገኝም #መስቃ ሌላ ማት እንዳያመጣ እሰጋለሁኝ።
የሆነ ሆኖ የማህበረ ኦነግ + የማህበረ ኦህዴድን ሁነት ተመልክቼ የኦነግ ድርድር ፍሬ ሃሳብ በኤርትራ ዝግ መሆንን በማስተዋል መርምሬም #ከመስከረም 5/2011 ዓም ጀምሮ #አዲስዬ #በኦሮምያ ክልል ሥር በመንፈስ እንደተከለለች ጽፌያለሁ።
አስገንዝቤያለሁኝ። በተከታታይ እንዲያውም ሰላማዊ ሰልፍ ሲጠራ የኦሮምያ ክልልን ፈቃድ ጠይቁ እል ነበር ለአዘጋጆች። ይህን ለምፃት አይደለም። ከልቤ ከዕውነቴ ነው። ግልጹ እና ዕውነቱ ነገር አዲስ አበባ ከእነ ህዝቧ፤ ከእነ ተቋሞቿ ፤ ከእነ ሥልጣኔዋ በኦሮምያ ህግ ሥር ናት። ይህን ሃሳብ 100% አምንበታለሁኝ። ይህን አንድም የኦሮሞ የፖለቲካ ሊቅ አያሳካውም ነበር። ፍርሻ ነበር የሚሆነው።
ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ግን እያለሳለሱ፤ እያዋዙ፤ ሳያስጠጡ አዲስ አበባን መንፈሷን ሁሉ አባ ጠቅልዬ በዝምታ ውስጥ ለኦሮምያ ጠቅልለዋታል። ጥምር ተግባር ነው የሚከውኑት። ኢትዮጵያን የመግዛት ዕድሉን ማስቀጠል አንዱ ሲሆን፤ በአቻም ዕድሉ ቢሾልክ ኦሮምያ ክልልን በተሟላ ሥልጣኔ እና ክህሎት የማደራጀት ጥንቁቅ ተግባር ይከውናሉ። ለዚህም የትውልድ የሚሆኑ ሜጋ ፕሮጀክቶች ታቅደው ኦሮምያ ላይ እየተከወነው ያለው።
አማራ ክልል አንድም ይህ ነው የሚባል ብቁ ፕሮጀክት አልተወጠነም። ሃሳቡም የለም። ቁሞ ቀር ፕሮጀክቶችን ምርጫ ሲመጣ እንደ እንሶስላ የመዳፍ ማሞቂያ ይሆናል። በአጤውም፤ በደርግም፤ በህወሃት ጊዜ ትርትር የሚሉ ተቋማት እንኳን ሞት ተፈርዶባቸው የጭስ ሲሳይ ሆነዋል። በህወሃትም በራሱ የአማራ ልጅም። እንኳንስ ነፍስ ያለው ሜጋ ፕሮጀክት ታቅዶ ሊከወን።
#የብልጽግና የማኒፌስቶ ሰሌዳ የዶክተር አብይ አህመድ የህሊና ሰሌዳ ነው።
ብዙ ሰው ስለብልጽግና ማኒፌስቶ፤ መሪ ዕቅድ ግልጽ አለመሆን ይነጋገራል። የኢትዮጵያ ንድፍ ሰሌዳ ያለው በጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ህሊና ብቻ ነው። የሚገለጠው ደግሞ በድንገቴ ሁነት ነው።
ጠቅላ ሚኒስተሩን የሚያቃልሏቸው፤ የሚያጣጥሏቸው ሰብዕናወች ይገርሙኛል። በብዙ ሁኔታ ከተቀናቃኞቻቸው ጋር #እርቀት አለ። የቅርቦቻቸውም ቢሆኑ የሚያውቁት የተመጠነች፤ በጠስጣሳ መረጃ ነው ያላቸው። ሁሉ ነገር ተጠቃሎ ያለው በዶር አብይ አህመድ የህሊና ሰሌዳ ነው። እርግጥ ነው ጊዜ የሚገልጠው ዕውነት ይኖራል።
በምርጫ ክርክር ከፍተኛ መሪ አካላትን አሰማርተዋል። ሚኒስትሮቻቸውን። ፍሬም ወርኩ የተሰራው ወጥ በሆነ ሁነት ስለሆነ ከፋክት ይልቅ የአክቲቢስትነት፤ የካድሬያዊነት ሁነት ነው ያስተዋልኩት። ለምን? ነገ ምን የሚለውን የሚያውቀው የጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ህሊና ብቻ ነው።
እሳቸውን ለመመከት የሚመጥን ብቻ ሳይሆን የበሰለ፤ የተጠሞነ፤ ምራቁን የዋጠ በላጭ ዕሳቤ፤ መሰናዶ እና የማስተዋል አቅም ይጠይቃል። በችኮላ ይሁን በማቃለል የሚታፈስ ድልም የለም። ህልማቸውን ለማሳካት አንዲት ቅንጣት ቀን አትባክንም። ይጣደፋሉ።
#የሰሞኑን ሦስት ፍንጭት ላንሳ ……
1) አንባሳደር ዲና ሙፍቲ የማከብራቸው ብልህ ሰው ናቸው። አዳምጣቸዋለሁም። ሰሞኑን ቃለ ምልልስ አድርገዋል። ስለ ግብጽ እና ኢትዮጵያ ያቀረቡት ሃሳብ ለስላሳ ነበር። ይህ የሚጠቁመው ቀጣዩ ጊዜ የሁለቱ አገሮችን ውጥረት የሚያረግብ ትልም በጠቅላዩ የህሊና ሰሌዳ እንዳለ ለእኔ አመላክቶኛል። አቅጣጫውን የሚሰጡ ዶር አብይ አህመድ ናቸው።
2) ሚኒስተር የዲያቆን ዳንኤል ክብረት የስደተኛ እሬሴ አገር አልባነት አዋጅ ሲያውጁ፤ ለእኛ ብቻ አልነበረም። ኢትዮጵያ ተወልዶ ላደገው የሃዘን ስርዓት እና ወግ ሙሉ በሙሉ የሚቀይር የሰሞኑ የጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ቃለ ምልልስ ይገልጣል።
3) የጋንቤላዋ እጩ ጠቅላይ ሚር አብን የተዳፈሩበት ልክ፤ ዛሬ አብን በአዲስ አበባ ድምጹ በሳይለንት እንዲለሰን የተደረገበት ሁነትን ያመሳጥራል። ከአብን በስተጀርባ አማራ የሚባል ቅን ህዝብ አለ። ይህ ህዝብ በአዲስ አበባ ላይ የሚኖረው የባለቤትነት መብት ልኬታ አመላካች ሁነቶች እንሆ ከምርጫ ድልድል ጋር እያዬን ነው።
አብን እና ኢዜማ በብልጽግና እኩል አይታዩም። አብን ለብልጽግና ቅብር ነኝ የሚለው ዕድምታው እና ግብርነቱ ደረጃውን እያዬን ነው። አብን አለሁ ቢልም በአማራ ህዝብ ይሁን በብልጽግና እንደ አለ የሚቆጠር አይደለም። የሚኒስተርነት ቦታውን የማስቀጠል አቅሙ በችሮታ ብቻ ሳይሆን በግል ጓደኝነት ከቻለም ወፍ ያወጣዋል እንጂ በብልፄው ከአገልግሎት ውጪ እንደተደረገ ነው እኔ የማስተውለው።
ኢዜማ ሊቀመንበሩም፤ ምክትሉም አዲስ አበባ የመወዳደር ዕድል አግኝተዋል። የአብን ሊቀመንበር እና ምክትሉስ??? {}። አብን ተልዕኮውን ያሾለከው በ2018 ዓ.ም አይደለም። ለመሆኑ አብን ምን አለው፤ ማንስ አለውና?
በ2013 ዓም ተኖ ከቀረው ባልደራስ ጋር ተሁኖ የአማራ ህዝብ ብሄራዊ ንቅናቄ የሚለው በምልዓት የሚደገፍ ንቅናቄ ሥሙ አዲስ አበባ ከተማ ላይ #አብሰንት ነበር። ትራጀዲ ነበር።
ያን የተወነው ተዋናይ ዛሬ ደግሞ የብልጽግና ሞጋች ሆኗል። ነገ ሌላ ሁነት ቢሳካ ደግሞ ሌላ ይኮናል። የአዲስ አበባ ህዝብ ለባልደራስ፤ ለዓድዋ መታሰቢያ በዕላት፤ ለካራማራ በዓላት በብዙ ተገብሯል። በምናውቀውም /// በማናውቀውም ሁነት።
ያ አልበቃ ብሎ ሙሉ ፰ ዓመታትም ያ መንፈስ የአማራን ህዝብን በገፍ ፍዳ አስከፍሏል። እያስከፈለም ነው። ፖለቲካ ተጽዕኖ ፈጣሪነት፤ ዕድል፤ ቀን ስለሰጠ ብቻ ሳይሆን አቅምን፤ ክህሎትን መጥኖ እና አጽንቶ መነሳት አለበት። ያንን ለማስተዳደረም የሰከነ መንፈስ፤ ድልድል ያለ አዕምሮ ይጠይቃል። በስተቀር ማትረፋ ቀርቶ የተስፋ ዕዳ ይሆናል።
የሆነ ሆኖ ለኦፌኮ፤ ለኦነግ የተፈቀደው የአዲስ አበባ የምርጫ ዕጩነት የአብን ተሳትፎ ትናንትም ይሁን ዛሬ በዳሽ ሙላ እንደምን ሊወራረድ ቻለ?
1) የዘመኑን የፖለቲካ ባህሬ አለመረዳት።
2) የልምድ ማነስ።
3) የክህሎት እጥረት።
4) ነገን የማሰብ ስስነት።
5) የተደራጁበትን ዓላማ እና ግብ መሳት።
6) የህዝብን ህይወት አብሮ የመኖር ብልህነት ድርቀት።
7) የህዝብ ድጋፍ የወንዝ ዳር አሽዋ አድርግ መወሰድ።
ስምንተኛ) የአማራ እናት ዕንባ በውስጥ ለማስቀመጥ መሳን።
9) የአማራ ትውልድ የነገ ተስፋ ላይ ቅንነት መንጠፍ።
10) የሰላማዊ ትግል ዲስፕሊን ጋር አለመተዋወቅ።
11) ያለውን የመንፈስ ጥሪት ሙሉውን ሳይቆጥብ ለሌላ አካል ፈቅዶ የማስረከብ ግድፈት።
12) በማይመለከት ጉዳይ አላስፈላጊ ቅራኔ ውስጥ መዶል ወይንም መግባት።
13) የግል እና የጋራ ዘመን ሰጥ ዕድልን በአግባቡ ማኔጅ የማድረግ አቅም የፆም ውሃነት።
14) ከዜግነት ፖለቲካ ወደ ዞግ ፖለቲካ ዝውውር ሲደረግ፤ የማንነት ግጭቶች በሚፈጥሩት ቀውስ።
15) እራስን አስከብሮ ለመዝለቅ በቂ መሰናዶ እና ተግባር አለመኖር።
16) ትኩረት ለሚያስፈልገው አመክንዮ ያለው መጠነ ሰፊ ቸልተኝነት።
17) ትኩረት በማያስፈልገው አትኩሮት መስጠትና ጊዜን፤ መዋለ መንፈስን፤ መዋለ ንዋይን ማፍሰስ።
18) ትልቅ ኃላፊነትን ለመወጣት የጥሞና ጊዜ ከፈጣሪ /// ከአላህ ጋር የመምከር አቅም ውስኑነት።
19) ህዝብ በቃል ውስጥ ሲገኙለት የሚሰጠውን ክብር ዕሴቱን አለማገናዘብ።
20) የህዝብ መከፋትን ለማድመጥ ፈቃደኛ አለመሆን። ወዘተ………
ምኞቴ እስከ ግንቦት 24/2018 በምርጫ ዙሪያ በዚህ ሃሳቤ ቢጠቃለል፤ በምርጫ ጉዳይ ባልመለስበት ምርጫዬ ነው። ግን እቴጌ ብዕሬ ከፈቀደችልኝ ነው። በዚህን ያህል ልክ እሳተፋለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር። ዕውነተኛ ተፎካካሪወች እናት እና ኢህአፓ በምርጫ መሳተፋቸውን 100% አምንበታለሁ። ጽፌበትም አለሁኝ። ግን በተደጋጋሚ በትጋት እጽፋለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር።
የአህጉራችን አንከር፤ የዓለም ዓይን፤ የኢትዮጵውያን የተስፋ ከተማ እቴጌ አዲስ አበባ ከመንፈሷ አማራ ከሚባል ገር፤ ቅኑ፤ ቀና፤ የውስጧ የሆነ፤ ታታሪ እና ትጉህ፤ እርስተኛም የሆነን ህዝብ #ቀለም እያጣች ስትሄድ ነገ ይደምናል። ነገ ይደርቃል። እግዚአብሄርም አላህም ያለቅሳል። በለቅሶው #ምርቃት ይነሳል። ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ መንግሥትም ጠቃሚ አይደለም። ለትውልድም ዕዳ ነው።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ቅኒት ኦርቶዶክስ ተዋህዶም እየተገለለች ነው። እየሸኜነው ባለው ሳምንት ልጅ ሞገስ መረጃውን ሲያቀርብ አዳምጫለሁኝ። የፖለቲካ ውክልናው ስብጥር ውስጥ ተዋህዶ እየተገፋች ነው። ይህም ብልፄውን አያበረክትም። ሊታሰብበት ይገባል።
ማስተዳደር የማይቻል ማዕበል ሲነሳ ዛሬ ጸጥ ለጥ ብሎ የሚገዛው ህግ አቅም ሊያጣ ይችላል። ሲከር ይበጠሳል፤ ሲሞላም ይፈሳል እና። በተለይ ሳይለንት ማጆሪቱ በሙሉ አቅሙ ንቅናቄ በጸሎት ቢጀምር ከበድ ያሉ ሁነቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ።
ማንኛውም ሃይማኖት እኩል የፖለቲካ ውክልና፤ ነፃነት እና እኩል ሊታይ ይገባ ነበር። በሙሉ ፰ ዓመታት በዘርፋ ያለው ሚዛናዊ አስተዳደር ከማይክ ያለፈ አይደለም። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስተርነት እንኳን እዮቢት ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አለማግኜቷ ብቻ ሳይሆን ይህን ለማስቀጠል መታቀዱ የተገባ አይመስለኝም።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie.
28/03/026.
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ዕውነት ሽሽት አልተፈጠረበትም!
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ