ስለ ሚኒስተር ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ዕይታየ። #የጨከነ #ሃሳብ። ሰብዓዊነት የተራቆተበት። ርህርህናም የመነነበት።
"እግዚአብሄር በአንድም በሌላም
ይናገራል፤ ሰው ግን አያስተውልም።"
#ምዕራፍ ፲፰።
ስሰማው የዘመኑ ሁነት አሳሳች ስለሆነ ከዛ ጋር ይሆናል ብዬ አሰብኩኝ። ይህን ስል ግን ሚኒስተር ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ይህን መሰል ጨከን ያለ ሃሳብ ተዚህ ቀደም አላቀረቡም በሚል አልነበረም።
በውነቱ ደጋግሜ ሃሳቡን በውስጤ ሳዘዋውረው እኒህ የብዕር፤ የቤተ - ክርስትያን ሊቀ - ሊቃውንት እንዲህ #ያስጨከናቸው ምን መንፈስ ተጠግቷቸው ይሆን አልኩኝ።
ስደት እኮ ጣፍጦን፤ ደልቶን፤ ተመችቶን፤ ተሳክቶልን #ንፍቅ ብሎን አይደለም የሚያኖረን። ስደት የዕንባ ኑሮ ነው። የተሳካላቸው ሊኖሩ ይችሉ ይሆናል በቁሳዊ ይሁን፤ በትምህርት ወይንም በኢኮኖሚ። ያ ግን ግንጥል ጌጥ ነው። አይሞላም። እናት አገር ወዟ፤ ጣዕሟ፤ ቃናዋ ትክ የለውም። ለዛውም ፈላስፊት ኢትዮጵያ።
ስደት ቢመገቡት ሆድ የማያሞላ። ቢጠጥቱ ጥም የማያስታገስ፤ ቢሞላ ቢተርፍ እርካታ #የመነነበት የክልትም ህይወት ነው። አንድ ጊዜ መነኩሲት እናቴን እቭዬ ሆዴን ሱባዬ አስይዥልኝ አልኳት። "ኑሮሽ #ሱባኤ ነው አያስፈልግሽም" አለችኝ። ስደተኛ መዋዕለ ዕድሜው የሱባኤ መሆኑን የተማርኩት ከእርሷ ዘንድ ነው።
አንድ ቀን ይሁን አንድ ማዕልት፤ አንድ ሳምንት ሆነ አንድ ወር፤ አንድ ወቅት ሆነ አንድ ዓመት በስደት ህይወት ነፍሳችን ተረጋግተን ወህ ብለን አናውቅም። ለዛውም ኢትዮጵውያን። የመንፈስ እርካታ የለንም። ኢትዮጵውያን ከሌላው ዓለም ዜጎች በአኗኗር ዘይቤያችን፤ በባህላዊ ልምዶቻችን፤ በሃይማኖት ሁነታችን እንለያለን።
እኛ በውነት እንለያለን። በብዙ ነገር በጣም እንለያለን። አገራችን ጥሪኟ #መሪያችን ነው። ይሉኝታ ገዢያችን ነው። አክብሮት መሃንዲሳችን ነው። ትጋት መለያችን ነው። ታማኝነት ማለያችን ነው።
ያለማጋነን #በየደቂቃው ኢትዮጵያ በእኛ ውስጥ አለች። ስለ እሷ እናስባለን። ስለ እሷ እንጨነቃለን። ስለወገኖቻችን እናስባለን። ስለወገኖቻችን እንጨነቃለን።
አገራችን ፈላስፊት ኢትዮጵያን እስኪ ልርሳት፤ እስኪ ልተዋት የሚል የኢትዮጵያኒዝም ቤተኛ ይኖራል ብዬ አላስብም። በተገኜንበት፤ በምንኖርበት ቦታ ሁሉ አገራችን መሪያችን መርሃችን ዶግማ እና ቀኖናችን አድርገን ነው። ጠፈፍ ያልን። #ቁጥብ። የተከረከምን። ዲስፕሊንድ ኃላፊነት እና ተጠያቂነት የሚሰማን ነን።
ለአገራችን ሰላም፤ ለህዝባችን ደህንነት፤ ለትውልዱ አደራ የበኩላችን ሳንሰት አቅማችን በፈቀደ እናደርጋለን። ኢትዮጵያ የቆመችው በዲያስፖራ ፃዕዳ መንፈስ ነው ብል ማጋነን አይሆንም። እኛን ከኢትዮጵያ ከወላጅ እናታችን ከእትብታችን፤ ኢትዮጵያን ከውድ ልጆቿ መነጠል ለመምህር፤ ለሚኒስተር ለዲያቆን ዳንኤል ክብረት ሰብዕና #የወንጀል ያህል ነው።
እንደምንስ የዚህ ክፋ ሃሳብ ናዳን አሰቡት። በውነቱ ለጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ አሊ ዘመነ መንግሥትም ይህን መሰል ለያይ ክፋ ሃሳብ ቢጎዳው እንጂ አይጠቅመውም።
ጭካኔው ሙቱ የራሳችሁ ጉዳይ። ለመሞት ያብቃችሁ እንጂ ብትን አፈር እንደማታገኙ አውቃችሁ መንፈሳችሁ በግዞተኝነት ይኑር። እግዚኦ! ይህ #አረማሞ ሃሳብ ከጤና የመጣ በፍጹም አይመስለኝም።
ትዳርን በከበረው ቅዱስ ቁርባን የፈጸመ፤ ሐዋርያ ሆኖ ስንት ሃይማኖታዊ ጉዳዮች የፈጸመ፤ የጥበብ ጥሪን ተቀብሎ የድርሻውን የተወጣ ሊቀ - ሊቃውንት በዚህ ሊሰሙት፤ ሊያስቡት በሚከብድ ድጥ እና ምጥ ሃሳብ ውስጥ መገኜት #የምርቃት መነሳት ይመስለኛል።
እያንዳንዱ ቤተሰብ ውጭ በሄደ ወገኑ ትንፋሽ ይቀጥላል። ስደተኛ ኢትዮጵውያን በሚልኩት ገንዘብም ኢትዮጵያ ትጠቀማለች። በአቻ ሁኔታ ከመንግሥት እርዳታ እንዳይጠይቅ ስደተኛ ወገን ቤተሰቡን ቢደጉም፤ እገዛ ማደረጉም ልዩ ስጦታ ነው። ይህ ሊከበር፤ ይህ ሊመሰገን እንጂ በዚህ መሰል #ጎምዛዛ ምኞት ሊከስል ፈጽሞ አይገባም።
እኔ ተቻኩዬ ያልፃፍኩት ውሃ ቁልቁል እንጂ ሽቅብ አይወጣም። መምህር፤ ሚኒስተር፤ ጸሐፊ ዲያቆን ዳንኤል ክብረትን #አሻቅቤ ለመናገር ከማተብ አንፃር እጅግ ነው የከበደኝ። እንዲህ የሚከብዱኝ አመክንዮወች አልፎ አልፎ ይገጥሙኛል።
ለነገሩ ከክፋ ሃሳብ በላይ ምን የከፋ፤ የሚከብድስ ገጠመኝ ይኖራል? በዕውቀት እና በልቅና እንደ ታናሽ እህትነቴ #ይቅርታ ቢጠይቁ፤ ሱባኤ ቢያደርጉ፤ ጥሞና ቢወስዱ ይጠቅማል ብዬ አስባለሁኝ።
ከባድ ውሳኔ፤ የገዘፈ የጭንቀት #ዶፍ ለስደተኛ ኢትዮጵውያን ስላሳለፋ፤ እንደገና አድምጠው ከራስ ጋር መታረቅን ቢፈቅዱ እወዳለሁኝ። ለእርስወም፤ ለቤተሰበወም አይጠቅምም።
ለትውልድም ቢሆን አብነትነቱ #አልቦሽ ነው። የምር አልቦሽ። እኔ በአንድ መጽሐፌ ላይ በቀደመው ሰብዕናወ አብነት አድርጌ ጽፌዋለሁኝ። ያ ምስክርነት የት ይቀመጥ???? ዳኝነት ለራስ ነውና ይዳኙት።
አገርን አስከብሮ በማቆዬት እረገድ አብዛኛው የእኔም ከእኔም የቀደመው ትውልድ እሚቶቹ፤ አያት ቅድመ አያቶቹ አርበኞች ሊሆኑ ይችላሉ። ስለዚህ ከአንድ ቀንጣ እኩል ዜጋ የምንጠወረው የኢትዮጵያዊነት የዜግነት መብት የለም። አገርን ሰጪም ነሽም የአንድ ሥልጣን ላይ ያለ #ተማላ ሰብዕና መብት አይደለም። ሊቀ ሊቃውንትም፤ እጬጌም ይሁን ጠቅላይ ሚኒስተር የአንድ አገርን የመወለድ ዜግነትን ሰጪም ነሽም ሊሆን አይገባም።
ይህ የዘመን #ሬት ንግግር በውነት ያስምጣል። ዲቁና ጥሪ ነው እዮራዊ፤ ቅብዓም ነው። ይህ ከእግዚአብሄር የተሰጠ ማዕረግ እና ክብርስ የት ይጠጋ ይላሉ? እኔ በአክብሮት እና በትህትና ነው የምጠይቀወት።
እርስወ በጠቅላይ ሚኒስተር አብይ ዘመን የቅርብ ሰው ነወት። ለመንግሥት ሥልጣን ለውጥ ይባል ሽግግር አብዛኛው የዲያስፖራው ዜጋ አስተዋፆ አለበት። ኢትዮጵያ ላለው ትላልቅ ፕሮጀክትም የዲያስፖራው ተሳትፎ #ቀና ነው።
አብዛህኛው የእናቱን ጉዳይ የእኔ ብሎ የሚያስጠጋ ነው። ጥቃቷን አይፈልግም። ሁልጊዜ እናታችን ከብራ፤ ደምቃ፤ ስቃ ማዬት ነው ምኞታችን። እንጃ ማፍቀርም፤ መውደድም ከልኩ በላይ ነን።
ሌላው የተከበሩ ሚኒስተር ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ለቁልፋ የህወሃት ፈቅዶ መንበሩን የመልቀቅ ታምራዊ ክስተትም የዲያስፖራው ጥበብ የከወነው ረቂቅ ተግባር ነው። ህወሃት ወደ መንበሩ ለመመለስ ባደረገው መጠነ ሰፊ ጦርነትም #ዲያስፖራው የጨመተ ተግባር ከውኗል።
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ በአገሩ ፖለቲካ ንቁ ተሳትፎ ማድረጉ ቢጠቅም እንጂ የሚጎዳው ነገር አይኖርም። ሃሳብን በነፃነት መግለጽ ወንጀል አይደለምና። እንዲያውም ዲያስፖራው በለት ኑሮ ተጠምዶ እናቱን ቢረሳ ነበር ሊወቀስ የሚገባው።
"አትምጡብን? ብትን አፈራችን አትቀምሱም" ወዘተ በጣም የከረፋ አስተምኽሮ ለኢትዮጵያ ዲያስፖራ መስጠት አይጠቅምም። ይህ #መራራ ውሳኔ ለታሪክ፤ ለትውፊት፤ ለትሩፋት፤ ለአደራ ሊበቃ የማይችል።
ሃሳቡ ዲያስፖራ ላይ ሁለተኛ ትውልድን፤ ሦስተኛ ትውልድን አገር አልባ የሚያደርግ ጨካኝ ሃሳብ ነው። ክፋ ሃሳቡ ይቆጠቁጣል። ያንገበግባል። ይጋረፋል። ዶፍ በአውሎ ቀላቅሎ አገራዊ ተስፋን #መጠጊያ ያሳጣል።
በእኔ በኩል የዛሬ 15 ዓመት እትብቴ ከተቀበረበት በዕቴ ውዷ ጓደኛዬ እናቴን ሄዳ ልታያት ስታቅድ "ምን ላምጣልሽ" ስትለኝ "#አፈር" አልኳት። በጣም እጅግ በጣም ደነገጠች። እና እኔ ሞቴን ተሰናድቼ እየጠበቅኩ ነው። አፈሬን አስመጥቻለሁኝ።
በዛው ዘመን ከዚህ ካለሁበት ከተማ እንደምቀበር #ኑዛዜዬን ለመንግሥት አስረክቤያለሁኝ። ያን ጊዜ ለዛውም ወጣት ነበርኩኝ። ይህ ዓዋጅ እኔን አይመለከትም። ችግር የለብኝም። በህይወትም እመጣለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም።
የህወሃት ፈቅዶ ከሥልጣን የመልቀቅን ጉዳይ በብዙ ሁኔታወች ምክንያት እንዴት እንደተፈጸመ እርስወ ሳይሆኑ እግዚአብሄር ያውቀዋል። እርስወ የሰናፍጭ ታክል ተሳትፎ እንዳልነበረወት ዓለም ያውቀዋል። ተሿሚ፤ ተሸላሚ፤ ተከባሪ ደግሞ እርስወ ነወት። እኔ በግሌ ሥልጣን የሚባለውን ጉድ አስቤው አላውቅም። በየትኛውም አገራዊ ተቋም በአባልነት፤ በአካልነት ተሳትፌ አላውቅም። የኢትዮጵያ እናቶች ዕንባ ብቻ እንዲቆም መጣር ነው ጉዳዬ።
ያን ጊዜ ብዙው የዲያስፖራ ወገኔ አገሩ ሲገባ፤ በዕድሉ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ባህል #ስለማላምነው አገር መግባትን አስቤው አላውቅም።
ጉዳዬ የትውልድ ስለሆነ ውጭ አገር ተወልደው ያደጉ፤ ከሌላ አገር ዜግነት ጋር ጋብቻ ተፈጽሞ ውህድ ማንነትም ያላቸው የነገ የአገር ተስፋወች ይህን ለወላጆቻቸው የተላለፈውን አግላይ መርዶ ሲሰሙ ተስፋቸው ሊቀጭ ይችላል። ይህ ለአገረ ኢትዮጵያ ቀጣይ ትውልድ ፈጽሞ አይጠቅም። ስለዚህ በይቅርታ ትልልፋን ቢያስተካክሉት ለማሳሰብ ነው የፃፍኩት።
#መሪነት አጽናኝነት፤ አይዟችሁ ባይነት፤ ርህርህና፤ እኛዊነት፤ ሰብዓዊነት፤ ተፈጥሯዊነት፤ ነገን ማሰብ ወዘተ ያስፈልግ ይመስለኛል። ይህ ዓዋጅ ግን ውሃ ያዘለ ተራራ ነው። እባከወትን ይሰቡበት። ይቅርታም ይጠይቁበት። ሥርዓተ መንግሥት ያልፋል፤ ክፋ ሃሳብ ግን ቂምን ቋጥሮ፤ በቀልን አጭቶ ጥላቻን ያጋባል።
ስንት የሚያቀራርብ በጎ ነገር ሞልቶ ስለምን የሚያቃቅር ክፋ ሃሳብ ምራኝ ይባላል። ለሁላችንም የምናስተውልበት ልብ አምላካችን ይስጠን አሜን። ሁሉም እናት አለውና፤ እናቶችን ከማስከፋት ብንቆጠብም መልካም ነው። እባካችሁን የነገን ትውልድ እንሰብ። መልካምነትን እናውርስ።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ዕውነት ወጌሻም ጋራጅም አያስፈልገውም።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ