#ይቅናሽ እናትዓለም።
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።
#ምዕራፍ ፲፰።
ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ በነገረ - ወልቃይት - ጠገዴ - አዲአርቃይ - አዲረመጥ - ጠለምት፤ ራያም ታክሎ የአማራ ክልል ቤተኛ ቢሆኑ የሚያስገኜውን ኢኮኖሚያዊ፤ ፖለቲካዊ፤ ስትራቴጅካዊ ጥቅም ስለሚያውቁ፤ ለዚህ በኽረ ጉዳይ #በጋድም ዕይታ፤ ጋድም ውሳኔ ሊሰጡ ይችላሉ። ዛሬ ላይ ማን አቅም ያለው ሊቀ - ሊቃውንት አለና ይፍሩ? የቲም አንባቸው ሰማዕትነት በአንድም በሌላም ከብዙ ፖለቲካዊ ሁነቶች ጋር ውህድ ነው።
ከውጥኑ በዶር አብይ አህመድ በ100 ቀናቸው ወደ ትግራይ ሲያቀኑ ጥያቄው ቀርቦላቸው ይህ የዲያስፖራው እንጂ የጎንደር ጉዳይ አይደለም ካሉ በኋላ ጎንደር ላይ ሲገኙ ደግሞ "#የአፍ ወለምታ ነው" አሉ። ያን ጊዜ ምልዓት ይደግፋቸው ስለነበር በቅጽበት ወጀብ ተነስቶ ነበር። በኋላ ግን የአፍ ወለምታ በሚል ኳሏት እና ሁሉም ተረጋጋ። አንድ ተጋሩ እሳቸው ወደፊት ከመምጣታቸው በፊት በነበረው ፍልሚያ አንዲት ሐረግ የፃፈ የሞገተ ሁንልን ያለ አልነበረም። ግን እማራዬ እጁ ስለምን አመድ አፋሽ ሆነ????
ወደ ቀደመው ምልሰት ሲሆን፤ ጉዳዩን ያዝ ለቀቅ እያደረጉ የልባቸውን በልባቸው ይዘው #ቅጣቱን አና አሉት። እሽት አድርገውታል ባዕቱን። እንደ አስፈላጊነቱ የነጠረውን ሃቅ እንደ ልጆች ጢባጢቦሽ ጨዋታ ትልቁን አመክንዮ ወለም ዘለም ሲያደርጉት ሰነባበቱ። መስቃም ነበረበት። "የተወላገደ ትግረኛ የተወላገደ አማርኛ እያሉ።"
እሳቸውን ለዚህ ሁሉ ዕድል ያበቃው ሚስጢር ያለው ፍሬ ነገር ግን ከወልቃይት ጠገዴ ንቅናቄ ጋር በእጅጉ #የተመሰጠረ ነው። ጎንደሮች ባለ ቅኔ ሙያ በልብን የከተሙት ትጋት ፈቃደ እግዚአብሄርም ታክሎበት፤ የአማራ ልጅ ሆ! ብሎ ደግፎ፤ ሙሉ ድምጹንም ቢሰጣቸውም የጠቅላይ ሚር አብይን #ውስጥነት ግን ገራገሩ የአማራ ልጅ ሊያገኝ ከቶ አልቻለም። በጣም ጫና የሚያበዝቱ፤ ሲናገሩም በሰጨኝ የሚሉት፤ ለማየትም፤ ለማድመጥም የማይፈልጉት ድምጽ ቢኖር የነገረ #አማራ ጉዳይ ነው።
ባለፈው ፓርላማ ላይ ዶር ደሳለኝ ጫኔ ሲናገሩ ዓይናቸው እንዴት ይይ? ሁኔታው ዝብርቅርቅ ስላለ በማስተዋል መራመድ ስለሚገባ ነው ዝም ያልኩት። አቅጣጫው የማይታወቅ ምኞትና ፍላጎት ላይ ዘው ሊያደርግ ይችላል አቅም ማዋጣቱ ብዬ በጣም በመቻል፤ በተደሞ ውስጥ ሆኜ ነው እየተከታተልኩ ያለሁት። ትናንት ልጅ ሞገስ ዘውዱ አንድ ጥሩ ሥንኝ ፈጥሯል "#ማንን እንደሚጠቅም ስለማናውቅ" ብሎታል። ውስጤን ነው ያገኜሁት በዚህ አገላለጽ፤ እንጂ ብዙ ሆድ የሚያስብሱ መገለሎችን አስተውላለሁኝ።
አንድ የአገር መሪ አባትም እናትም እኮ ነው፤ ለዛውም የሰላም አባት በአደባባይ እራሱን እንደዛ ሲያጋልጥ ከውስጤ ነበር ያዘንኩት። ያን ያህል የሰው ልጅን ከውስጥ #መጠየፍ ለምን ይሆን ብዬ ከራሴ ጋር ሞገትኩኝ። የፖለቲካ ሊቃናት ትዳር ያላችሁ አንስት እህቶቼ ትዳራችሁን ብትከረክሙ ይበጃል። ሁሉ ይተው፤ እግዚአብሄር ይከፋል።
እሳቸው ወደፊት እንዲመጡ፤ አቅማቸው - እንዲደረጅ፤ የህሊና ትጥቅም የመንፈስ ደጀንም ከቅኑ የአማራ ህዝብ በገፍ ዛሬም ተለይቷቸው አያውቅም። በሳቸው ውስጥ ግን ነገረ አማራ እእ። {} ነው። ለምን የሚለውን እዮር የሚፈታው ሃቅ ይመስለኛል። ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስተር ሳሉ #ብቃት ብቻ መስፈርታቸው እንደነበር በዛን ጊዜ በብዙ አደምጥ ነበር። የእኛ ትጋት ምንጩም ሰዋዊነት ገዢ ከሆነ ግፍ የተፈጸመበት የአማራ ህዝብ ዕውነተኛ ፍትህ ያገኛል የሚል ነበር።
የሆነ ሆኖ ህወሃት መንበሩን ለቆ ለከፈተው ጦርነትም እጃቸውን #መሰስ አድርጎ ያወጣው፤ ከጥቃት ያወጣቸው፤ በሎቢም በግንባርም የቅን አማራወች ተሳትፎ ልክ አልነበረውም። በተከታታይ በንግግራቸውም፤ በድርጊትም የከፋ የአማራ መገለል እያለ ግን እሳቸውን ለመደገፍ ብዙ የአማራ ልጆች ሲታትሩ ነበር። ምዕራባውያን ህወሃትን መልሰው መንበሩን ሊሰጡት ሲያስቡ ህልሙ #ምክነት የገጠመው በአማራ ልጆች ትጋት እና ጥረት ነበር።
ይህም ሆኖ ግን አንድም ቀን ስለአማራ ልጆች ጥረት በቅንነት ምስክርነት ሲሰጡ ሰምቼ አላውቅም። የራያ፤ የጠለምት፤ የአዳርቃይ፤ የማይጠምሪ፤ የአዲ ረመጥ እንግልት ፈጽሞ ውስጣቸውን ጎርብጦ እንደመሪ #አለኋችሁ፤ #አይዟችሁ የሚል አጽናኝ ቃል ተደምጦ አያውቅም። ታጋሹ የአማራ ልጅ ሳይለንት ማጆሪቲ ላይ ያለው በመጠነ ሰፊ ትዕግሥት ቢታገሳቸውም እሳቸው ግን ውላቸውን ፈጽሞ አይረሱም።
በጀት አልባ ሲንከላወሱ የቆዩት በዕቶች ዘንድሮ በጀት ተመደበላቸው ተብሎ አዳምጬ ነበር። በቅርቡም አውሮፕላን መብረር ጀመረ ተብሎ ሰማሁ። የተሰናዳው ግን ሞገድ ላይ ለመሰረቱት የህወሃት ፍንካች "#ስምረት" ፓርቲ ማህበራዊ መሠረት ስለሌለው ደማቸውን ገብረው ያቆዩትን በዕት፤ በግፍ የተጨፈጨፈውም ሰራዊትም፤ ሁለት ትውልድ አልቆበት ተበትኖ የኖረው ህዝብ የቀረውም ደክሞ ተሰልፎ ያገኜውን #እፎይታ ሊነጥቁ ባጉም ባጉም እያሉ ነው ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ።
#በዚህ ሂደት ትርፍ ያገኙበታል።
1) ከወያኔ የተገነጠለው ፍንካቹ "ስምረት ፓርቲ" መሪው የዲፕሎማሲ ዕውቅና ስላላቸው በዛ ለመሸቀጥ፤
2) የአማራ ህዝብ የአንጡራ ባለርስትነትን ከሥር ለመንቀል #ዘመናዊ ባርነት ዳግም ለማደራጀት፤
3) እንደተለመደው ነኮር ነኮር ያደርጉና እራሳቸው፤ #ገላጋይ ሆነው ይገቡ እና #በማዕከላዊ መንግሥት ይተዳደር የሚል ዕድምታ እንደ ቅዱስ ሲኖዶስ ለመፍጠር እናም በሞፈር ዘመት #ለመጠቅለል፤ ለነገሩ ይህንንም እኮ በጎርደር ከተማ የከንቲባ አስተዳደር ሲፈጽሙት ኖረዋል። ትጋት ካዩ ንቅል ነው። በርክተው አያውቁም የጎንደር ከተማ ከንቲባወች።
የጎንደር ከተማ ከንቲባ በእሳቸው ምደባ ነው የሚከወነው። ተከታታይነት ያለው #የረጋ ሁነት አይፈልጉም። ኦሮምያ፤ ሱማሌ፤ ቤንሻንጉል ጉምዝ ፕሬዚዳንቶችን እዩ፤ ከዛ ያለውን አንፃራዊ ሜጋ ፕሮጀክቶችንም እሰቡ። ጎንደር ላይ ደግሞ አራጊ ፈጣሪው እሳቸው ናቸው። ከጥቂት ቀናት በኋላ አዲሱ የጎንደር ከንቲባ ይነሳሉ፤ እንደ #ቀናተኛ የትዳር አጋር ያደርጋቸዋልም። ለምን? የሰከነ አመራር ሲኖር ጎንደር ከተማ ላይ ውስጣቸው እንደሚረበሽ አላውቅም። አይገባኝም። በራሳቸው ጊዜ እራሳቸውን ታግለው ከማዕቀፋ ይወጣሉ።
4) ዘመነ አስተረዬ እና ሰናዩን እክል ፈልጎ ማስደንገጥ፤ ሐሤቱን ለማደፈራረስ ይህን ያህል ጥድፊያ ስለምን???
5) መጩውን የነነይ እና የሁዳዴ ፆምም ማህበረ ምዕመኑ በአህቲ ልቦና #እፎይ ብል ሱባኤውን እንዳይዝ መንፈስ መበታተን ያተርፈኛል ብለው ይሆናል፤ የሳቸው የመሪነት አስኳል የመሻታቸው አቅጣጫ ሃይማኖታዊ ይዘትም አለው።
ከነኝህም የተሻለ ብጥቅጣቂ ትርፋ ትርፍ ይገኝ ይሆናል። መበቀል፤ የቂም መወጣጫነት፤ የአማራ ክልልን #ማጫጫት፤ ተስፋው እንዲሸበሸብ ለማድረግ ይረዳቸው ይሆናል። ግን በዝምታ፤ በእርጋታ የጸሎት፤ የድዋ ውጤት ጣጣው ብዙ ነው። እኔ እራሴ በጣም ነው ያዘንኩባቸው። አንድ የሰላም ዞን አማራ ክልል ተገኝቶ እሱንም እንዲህ ማሳቀቅ፤ ስጋት ውቅያኖስ ውስጥ መዶል? መጥኔ።
ውጭ አገር የሚኖሩ፤ የማገኛቸው ስለ ሰቲት ስጠይቃቸው አንድ ዓይነት ነው መልሳቸው። ሸፍጥ በሌለበት ሁኔታ የአብይዝም ፈን ናቸው። ልክ የበሻሻ ያህል ሙሉ ደጋፊ ነው ያላቸው። ይህንን አቅም የትም አይሄድም ብለው ተደማሪያቸውን "ስምረት ፓርቲን" መሠረት ለመስጠት ጎንደርን ቀብድ ያቀረቡት። ምረጡልኝ የህወሃትን ቅርንጫፍ፤ የልቡን አድርሱለት ነው።
ልክ ትራንፒዝም በጋዛ እና በእስራኤል የምዕራፍ ፩ ስምምነት ለኮኦርድኔተሯ ለግብጽ ውለታ አባይ ግድብ ይገበር እንዳሉት ሰቲት ላይ ያለው ዕውነትም ይኽው ነው። ርግማን ያመጣል። የፈሰሰው ደም የከብት፤ የፍዬል፤ የበግ አይደለም። የሰው ልጅ ነው። የሰውም ግፍ አለውና።
እስከ ዛሬ ድረስ ወሎን በፈጣጣ ጎንደርን በለበጣ ተቆዬ። አሁን ዕውነቱ ግልጥልጥ ብሎ አፍጥጦ የመጣበት ጊዜ ነው። የጭምቱን ማህበረሰብ ሚዛናዊ አቋም ባይበርዙት፤ ባይበክሉት፤ ባይፈታተኑት፤ ባያሳዝኑትም ጥሩ ነው። ጎንደሬን ከጎንደር መነጠል ሲኦላዊ ጉዞ ነው። ሊያመጣ የሚችለው የውስጥ መከፋት ሁነት ማንኛችንም ልንገምተው አንችልም። ከሁሉ በላይ ማይካድራ እንደምን ተረሳ? እንዴትስ ይረሳል? ኦ! አምላኬ።
ዕውነት እንዲህ በግፍ ሲታጠር ትውልድ አያበረክትም። ለነገሩ ስለወልቃይት ጠገዴ ሲናገሩ በሙሉ ኮንፊደንስ የማያቸው ዶር ዳኛቸው አሰፋም ከአንድ አፍታ ጋር በሰሞኑ በነበራቸው ቆይታ እንደቀደመው ሆነው አላየኋቸውም። እንዲያውም ለጎንደሬወች "#ዘፈናችሁ" ተሰጥቷችኋል ዓይነት ተረብ ይሁን ቁምነገር የመረጃ ውልብልቢት ጣል አድርገው ነበር።
የሆነ ሆኖ "የቂጣም እንደሆነ ይጠፋል፤ የልጅም ከሆነ ይገፋል" እናያለን። መዝለቅ በጠራ ዕውነት፤ በነከረ መታመን እንጂ በማህረሜን ያያችሁ የሚሆን አይመስለኝም። ይህ እርምጃ የሚጠቅመው እነማን እንደሆን ልበወት ያውቀዋል።
ማህበረ ቅንነት ሸበላ ምሽት ይሁንልን። አሜን።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
02/02/2026
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ዕውነት ወጌሻ አያስፈልገውም።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ