#ሌላው …
#ከእናት ይሆን የተፈጠሩትን?
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ። " አሜን።
የአንድ ከተማ ህዝብ #ምጥጥ ያደረገውን አረመኒያዊነት ከሴቶች በላይ ማን ግንባር ቀደም ተሟጋች ይሁን? በዘመነ ህወሃት እታገልበት የነበረው ሞቶ የኢትዮጵያ ሴት የፖለቲካ ሊቃናት ከፖለቲካ ሥልጣን ስለተገለሉ የኢትዮጵያ እናቶች ዕንባ አባሽ አጡ። የኢትዮጵያ ፖለቲካ የገበርዲን እና የከረባት ያደረገው ሁነት ሊቀየር ይገባል ነበር ሙግቱ። ይህም ተቀባይነት ብቻ ሳይሆን የህወሃትን መንበረ - ሥልጣን የነቀለ ጉልበታም አመክንዮ ነበር።
ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድም 50% ካቢኔያቸው በሴት ሊቃናት የሆነው የዛን ጊዜ ከወንዝ ዳር የታፈሰ ዝቀሽ ጉዳይ ሆኖ አልነበረም። ለስልጣነ - መንግሥታቸው የዲፕሎማሲ ማህበረሰቡን ቅቡልነት፤ ቀልብ በመሳብ የዓለም ተጽዔኖ ፈጣሪ ፖለቲከኞች የተረጋጋ #ታማኛዊ መንፈስ እንዲቀልቧቸው አስበው የፈጸሙት ጉዳይ ነበር። ከለወጡ ከሚፈለጉ መሰረታዊ ጉዳዮች የሴት ፖለቲከኞች ዕውቅና እና የፖለቲካ #ውክልና በእጅጉ ያስፈልግ ነበር።
ዕውነት ለመናገር አሁን እንዲህ ዓይነት ሙግት አላነሳም። ከላይ እስከ ታች በሴት የፖለቲካ ሊቃናት ተሞልቷል። ነገር ግን አንድም ሊቅ #እናትነታዊ ጥሪው አነሳስቶት ከቅርባቸው ያለውን የደብረብርሃን #የተፈናቃይ ማዕከል ሄደው አይተው አያውቅም። በሌሎችም የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ላይ ምንም ዓይነት ሰዋዊ፤ ተፈጥሯዊ ድርጊት ላይ ሲገኙ አላስተውልም። አቤቱታ ሳቀርብም አያዳምጡኝም። ትንሽ ዶክተር ሊያ ታደሰ የቀድሞዋ የጤና ሚር ያዳምጡ ነበር።
እኔ ቀን ከሌት "አብይ፤ አብይ" እያልኩ አልባንንም። ካቢኔ አለ። ህግ አውጪ፤ ህግ ተርጓሚ እና ህግ አስፈፃሚ አካል አለ። እነኝህ አካላትም በያንዳንዱ ሰብዕዊ ጉዳይ ላይ #ተጠያቂ ናቸው። በግልም በጋራም። አካላቱ በራቸውን ዘግተው አብረው #ከመስመጣቸው በፊት ሊመክሩ ይገባል። እራሳቸውን ሊያርሙ ይገባል። ቲም ሊደራቸውንም ዶክተር አብይ አህመድን #ሊሞግቱ ይገባል። በተለይ አንስት የፖለቲካ ሊቃናት በሰብዓዊነት እና በተፈጥሯዊነት ጉዳይ ሊተጉ ይገባል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ ከአብይዝም መምጣት ጋር የሚወስዳቸው እርምጃወች እንደተፈጠረ #ሬሳዊ ሁነቶችን ናፋቂ ሆኖ ስላየሁት ከመቅድሙ የጨነገፈ ብዬ ጽፌ ነበር። መርህ የሚሠራው ለሚሠራለት ብቻ ነው። መርህ ግን ሁሉንም እኩል ሊገዛ ይገባ ነበር። የሚሰረዙ ነባር የፖለቲካ ፓርቲወች እና ምንም ሳያሟላ ዕውቅና ለብልጽግና ሲሰጥ ነበር የሞገትኩት ቦርዱን። በፍልሰቲትም የምርጫ ሰሌዳ አውጥቶ ነበር፤ ቅድስት ተዋህዶን የሚጫን ውሳኔ ስለነበር በዚህ ዘርፍም ሞግቼ ነበር።
#ሌላው ……
በምርጫ ጉዳይ በዘመነ ህወሃት መድፊያቸው "#ጫ" ያሉባቸው ብዙ ሞጋች ሃሳቦችን እኔ አነሳ ነበር። በዘመነ አብይዝም ግን ጸጥ ብዬ ነበር የተከታተልኩት። አሁንም በዝምታዬ እቀጥላለሁኝ።
#ለምን?
ምርጫ ማካሄድ አንድን ሥርዓት የማስቀጠል አቅም እንደለለው ተረድቻለሁኝ። ምርጫን ቦይኮት ማድረግም አንድን ሥርዓት አያሰናብትም። ይህንን በተጠሞነ - ተግባር የገመገሙኩት ጉዳይ ነው። እንዲያውም ምርጫን ቦይኮት ከማድረግ ይልቅ አትኩረት በምርጫ ንቅናቄ ህዝብን የማግኜት፤ የሚዲያ አክሰስ የማግኜት፤ ሃሳብን የማስተዋወቅ፤ #የዛሉ ሁነቶችን የማነቃቃት፤ አላስፈላጊ ቅራኔ ከገዢው ፓርቲ ጋር ላለመግባትም ይረዳል። በተጨማሪም አዳዲስ ተመክሮም የማግኜት ዕድል ይፈጥራል፤ የተለያዩ ፈተናወችን በቅደም ተከተል የመፍታት ገጠመኝ ሊኖረው ይችላል። የህይወት አዲስ ተመክሮ ነው። የመማሪያ መድረክም ነው።ዕድልን በስሜታዊነት ማክሰል የተገባ ነው ብዬ አላምንም።
አንድን ሥርዓት የሚያስቀጥለው ሆነ የሚያሰናብተው ተጨባጭ የፖለቲካ አቅም፤ የኮርድኔሽን ጥራት፤ የአደረጃጀት መርሃዊነት፤ የዓላማ እና የግብ ብቁ አስተዳደር፤ የታማኝነት እና ቅንነት ልምድ፤ ተከታታይ እና ፈጣን የአትኩሮት ልቅና፤ እራስን #አሳምኖ ለማሳመን ሌላውን ያለው ተነሳሽነት፤ ከህልማዊነት እና ፋንታዚ ግርግር ይልቅ የሚጨበጥ፤ የሚዳሰስ ሰብዓዊ እና ተፈጥሯዊ የድርጊት ሂደት፤ የፍትህ እና የነፃነት #ነፃነት ወዘተ ጉዳዮች ናቸው።
ወደ ቀደመው አስተውሎቴ ስመለስ አንድ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ #የተያዘ ጉልላታዊ በኽረ ጉዳይን፤ ህወሃትን ከመንበረ ሥልጣኑ #የነቀለ ጉልላታዊን አመክንዮ እንደ ተራ ኢቤንት ማዬት ሥም የለሽ የኢትዮጵያ ፖለቲካ #ዕዳ ነው። የየዘመኑን የፖለቲካ ባህሬ መጥኖ የማይገኝ ውሳኔ ዕጣ ፈንታው ዳጥ እና ምጥ ይሆናል።
ሌላው ከሰው ውጪ የሚያደርግ #ጨካኝ እርምጃ ነው የምርጫ ሰሌዳው። ከሰዋዊነት ዕሳቤም የሚያወጣ የምንግዴለሽነት ውሳኔ ነው። እነሱ ምን አገባቸው? እናታቸው፤ አክስት አጎታቸው እህት ወንድማቸው ያን የሦስት ትውልድ መከራ ስሜን ጎንደር ላይ አልደረሰባቸው። "ያልተነካ ግልግል ያውቃል" እንዲሉ።
አሁን ያለው ብሄራዊ የምርጫ ኮሚሽን ይሁን ካቢኔ ውስጥ ከፕሮፌሰር ዶር ብርሃኑ ነጋ በስተቀር ብዙው ባለሥልጣን ህወሃት ሠራሹን የዞግ ፖለቲካ የተጠመቀ ነው። ድሉ የቀናቸው ናቸው። አንዲትም አቅም ሳያዋኩ ቁብ አሉ። በሌላ በኩል መዋቅሩ እንዳለ ህወሃታዊ ነው። ስልክ ቁጥሩ አልተቀየረም። እንደአሻው ቀውስ እያደራጄ ህወሃት ሲያምስ የባጀው በራሱ መንፈስ ድልድይነት ነው። ህገ - መንግሥቱ እንዳለ ነው። ፈላስፊት ኢትዮጵያ ከሌሎች ትናንሽ አገሮች አንሳ #በትውስት አይዲኦሎጂ ነው የምትመራው። ጭካኔውም የሚፈልቀው ከዛ ነው።
እኔ ሴት የፖለቲካ ሊቃናት፤ ጸሐፍት፤ አክቲቢስት፤ ጋዜጠኛን መሞገት ግጥሜ አይደለም። ብዙውን ጉዳይ እንዳላየሁ አልፈዋለሁኝ። እንዲህ በሰው ልጅ የከፋ ጭካኔ ላይ #እናትነት ጸጋን የተጎናጸፋ አንስቶች ቤተኛ ሲሆኑ ግን ዝም ብሎ ማለፍ የተገባ አይደለም። ሃጢያትም ነው። የግፋ ቤተኛ መሆንም ነው። ህወሃት በዘመንህ በጎንደር ላይ ለፈጸምከው የግፍ ቡፌ ተመስገንልን እኮ ነው። እግዚኦ፤ ሎቱ ስብኃት፤ ማህከነ።
ምርጫ ቦርድ አቅም ከነበረው የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን #ከበጀት ወጭ ሲሆን ለምን አብይዝምን አልሞገተም???? ሙቀት የሚያስፈልጋቸው የሰቲት ህፃናት #በከሰል ምድጃ ሙቀት ይሰጣቸው እንደነበር አንድ ጊዜ አዳምጫለሁኝ። #ዝግትግት ብለው ነው የባጁት። አሁን በጀት የተመደበው፤ ይሁን በረራ የተጀመረው ማህበራዊ መሠረቱን ሳያገኝ አየር ላይ ተንጠልጥሎ ለሚገኜው አብይዝም ሠራሽ #የሞገድ ስምረት ፓርቲ ድልዳል ለማመቻቸት ነው። ፍሬ ነገሩ ይህ ነው።
ጠቅላይ ሚር አብይ ሙሉ ድጋፋቸውን ለስምረት ማዳበሪያ እንዲሆን ፈቅደዋል። ጎንደርን #ቀብድ ሰጥተዋል ለህወሃት ቅርንጫፍ ትናንት ለተፈጠረ -- ለስምረት። የእኛ ድካም ሁሉ አጋግመው አቃጥለው አመድ አድርገውታል። ተየን የለውም ድካማችን።
ለዚህም ነው አቶ ጌታቸው እረዳ ጠላዋ እንዳማራላት ሴት ሽር የሚሉት ሰርክ ሰቲት ላይ። ሌላው አማራነት ላይ የስውር ዲስክርምኔሽን ዓላማን ያነገበ ሂደትም ነው። አማራነት ሰፋ እንዲል፤ በቂ ደንበር እንዲኖረው አይፈለግም። እለቁ እና እንያችሁ፤ መሬታችሁን፤ ጂኦ ፖለቲካችሁን እንጂ እናንተ አታስፈልጉንም ነው። ለዚህ ተልዕኮ ደግሞ እመ ወራው የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ነው። ባለፈው ምርጫው አላካለላቸውም። አሁን ግን አቤቱ ስምረት ታቅዶ ተደራጄ ነውና የጎንደር ህሊና #እጅ መንሻ ቀርቦለታል።
ድጋሚ በገጀሞ፤ በካሬያ - መታረድን፤ ድጋሚ እንደ ጤፍ ነዶ - መታጨድን፤ ድጋሚ አፍ ባለው መቃብር የሰቲት የወልቃይት፤ የጠገዴ፤ የራያ፤ የአዲ ረመጥ፤ የማይጠምሪ፤ የአዳርቃይየማይካድራ ህዝብ ማገዶነቱ ታቅዶ እንዲህ ሲሰራበት የአበው ዕንባ፤ የእመው ዕንባ እዮርን ያንኳኳል። ይደመጣልም።
ስለተደመጠም ነው በህይወት እያለን የህወሃት ትዕቢት እንዲህ እርቃኑን ሆኖ ያሳየን። ስንት የሰሜን ጎንደር ትንታጎች እየታናቁ ተሰውረው ቀርተዋል? የተጋሩ የዕውነት አርበኛ ታሪክ ዓዋቂወችም። ቤት ይቁጠረው። በዚህ አጀንዳ ላይ የሚያላግጡ ቀለጤወችን አዳምጫለሁኝ። ኮሜቴው እንዴት ለማዕከላዊ መንግሥት ፃፈ ተብሎ ደልቀቅ ብሎ ልጅ ቴወድሮስ አስፋው ሲተች ነበር። ባይቶና ግሎባልን እንዳዳረሰ አላዳመጠም? ዘመናይ የሆነ ወጣት ነው። እግዚአብሄር በፈጠረው የሰው ልጅ ላይ የቅልሞሽ ጨዋታው ማት ያመጣል።
የኢትዮጵያ ሴት የፖለቲካ ሊቃናት ለአቻቸው ሴት እናቶች ያስቡ ዘንድ ልብ ፈጣሪ ይስጣቸው። አሜን። ከሰው ልጅ ፖለቲካ አይበልጥምና። ይህ አሳዛኝ ትራጀዲን ከተሰማ በኋላ ውስጣችሁ ለተጎዳ ወገኖቼ መጽናናትን እመኛለሁኝ።
ትናንት ያደረገልን አምላክ ዛሬም አለና ዕንባችሁን በቅንነት ወደ ፈጣሪ ላኩ። መጭው ሱባኤ ስለሆነ አትኩሮቱን ከ፶ዓመት በላይ ለፈሰሰው የወገኖቻችን ደም ፍትህ ይሰጥ ዘንድ አዶናይን ለምኑ። " አንኳኩ ይከፈትላችኋል" የጠበንጃ ትግል እኔ አልመክርም።
በነገራችን ላይ ስምረት ፓርቲ ተፈቅዶለት ሁለገብ ትግል እያደረገ ነው። ታጣቂ አለው። ብዕረኛም አለው። ለምን? #የውጭጭ ቀረመት አብይዝም ስለናፈቀው። በጥልቀት - እሰቡት። እኛም ተሰውተናል እንደ ቅራቅር ዳንሻ ነው፤ የሞት ተሳትፎ ተወጥኖ እዬተከወነ ነው። ለዚህም ነው እኔ ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ አሳቻ መሪ ናቸው የምለው። ማንም ሊተረጉማቸው አይችልም። በጥንቃቄ መያዝ ያስፈልጋል፤ ነገን ለሚያስብ አደባዊ ትውልድ። በሳት መጫወት አይገባም።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
02/02/2026
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
በሰው ልጅ ሰቆቃ ማላገጥ ይቁም!


አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ