#Timing.
#Timing. መረጃው ዘገዬ፤ የአብይዝም መንገድ ……… ምን ልበለው???
********
"Timing refers to the #strategic selection of the #exact #moment for an #action to #achieve the #best #result or the or the #regulation of when event occur."
https://www.youtube.com/watch?v=gWLfcwf1dS0
“የቀይ ባሕር ጉዳይ አይደለም ችግር የፈጠረው”
• ዛሬ የኤርትራ መንግሥት መልስ ስለሰጠ አያይዠዋለሁኝ። ለዳኝነትም ለታሪክም መንገዱ ይህ ስለሆነ። ሁለቱም የሚመሩት ህዝብ አለ። ህብራዊነት ውህድ ማንነትም አለ። ከስሜት የጸዳ ጠንቃቃ ተግባር መፈጸም ይገባል። ኃላፊነት የሁሉ ኃላፊነት ነውና። ****
እስከዛሬ ስለምን #አምቀው፤ #ተጭነውም አቆዩት ይህንን ሃቅ ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ጥያቄ ነው። በወቅቱ ተናግረውት ቢሆን ኖሮ፤ ብዙ መካረሮችን #ሊያረግብ ይችል ነበር። በተለይ መንግሥት እና ህዝብን #የሚያቃቅር ወሳኝ ጉዳይ ብዙ ነገር ስለሚያሳጣም። የሆነ ሆኖ #timing አጤ ጉግል እንዲህ ይተረጉመዋል።
"Timing refers to the #strategic selection of the #exact #moment for an #action to #achieve the #best #result or the or the #regulation of when event occur."
ጊዜን በጊዜው በሰጠው ጊዜ ማናገር ይገባል። ለቀኑ ቀን ሲሰጠው ለቀኑ ቀኑ እራሱ መፍትሄ ያመነጫል የሚል የእኔ ፍልስፍና አለኝ። ቀን ሲደመጥ ብዙ በጣም ብዙ ቁስለቶችን ይፈውሳል። አሁን የደቡብ አፍሪካ #ድርድር ዓለም ዓቀፍ ዕውቅና ቢኖረውም፤ እያንዳንዱ አንቀጽ #ዋጋ ለከፈለ ለህዝብ በሚገባው ቋንቋ ተተርጉሞ ግንዛቤ እንዲያገኝ ሊደረግ ይገባ ነበር። ሁለት ጊዜ ኬኒያ ላይ የተደረገው ሰበር ንግግርም እራሱን ለገበረ ህዝብ በግልጽነት ሊነገረው ይገባ ነበር።
ያን የበቀል እርምጃ ለመግታት፤ ዛሬ የነበረውን መንግሥታዊ ጥረት ጠቅላይ ሚር አብይ ገልጸው፤ ማስረጃ እንበለው ማጣቀሻም ሥም ጠርተው አቅርበዋል። #በጣም፤ እጅግ በጣም #የዘገዬ መረጃ ነው። ስንት ንጹህ መንፈስ ከተጎሳቆለ፤ ስንት ተስፋ አስቆራጭ #ንጥረ ነገሮች #ከመከኑ ወይንም #ከፋደሱ በኋላ ነው የሚነግሩን።
በእሳቸው እና በመንግሥታቸውም ላይ #ብዙ #ማት፤ ብዙ ወጀብን ከማስተናገድ ይልቅ ዕውነቱን በጊዜው #ፏ አድርጎ ማቅረብ ለትውልድ፤ ለታሪክ፤ ለአደራም ይጠቅማል። ይህ ከተነሳ በደቡብ ሱዳን በኩል በህወሃት ዘመን የጀመረው የጋንቤላ ህፃናት ዝርፊያ እንደቀጠለ አዳምጣለሁኝ፤ በዚህ ዙሪያ የተደረገ ጥረት ካለ ቢነግሩን ጥሩ ነው።
…… ወደፊትም ይህን መሰል #ሰብዓዊ ጉዳይ ባይታፈን እና ጠረጴዛ ላይ አውጥቶ ህዝብ የህሊና ዳኝነት ይሰጥበት ዘንድ ዕድል መስጠት ይገባል። ብዙ ነገር ያድናል። ሌላው ቢቀር #ዕውነት ቦታውን ባይለቅም፤ ይህን መሰል የዕውነት መጋዚን ውስጥ የማስቀመጥ ባህል ለዕውነት ፈተናውን ያባዛዋልና፤ ለወቅቱ በወቅቱ ግልጽነት እና ቀጥተኝነትን ካላገኝ።
ዕውነት ለመናገር ይህን ንግግር እያዳመጥኩኝ ለካንስ የሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን አመክንዮ፤ ሎጅክ፤ ፋክት፤ ትህትና፤ ዕውነት፤ ኃላፊነት እና ተጠያቂነትም silent discrimination እንዲህ ይፈጸምባቸዋል ወይ ብዬ ራሴን ሞግቻለሁኝ።
ዕውነትን በእጁ ይዞ መጠነ ሰፊ ወጀብን ስለምን ጠቅላይ ሚር አብይ እንደፈቀዱ አላውቅም። እሳቸው አስታግሰው ቢይዙት እንኳን ስለምን አቶ ደመቀ መኮነን ይሁኑ ዶር. ገዱ አንዳርጋቸው የመንግሥታችን ጥረት ይህ ነው ብለው አልገለጡትም? ብዙ ነገር ነበር የሚያድነው። ቅን ኤርትራውያን እራሳቸው ሊያደምጡትም - ሊበይኑበትም ይችሉ ነበር።
የእኔ ክብሮች ለዛሬ በዚህው ጉዳዬ ይከወናል። ስለምርጫም ያነሱት ነጥብ፤ ስለትራንስፖርትም ያለውን የጥረት ውጥን …… ሙሉውን ነበር ያዳመጥኩት። አቶ ደመቀ መኮነንም ሆኑ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ስለሆነው ነገር ማስረጃውን
ሀ. ዕውነት።
ለ. ሃሰት።
ሐ. መልስ የለም።
መ. ሁሉም ትክክል የሚል ማስረጃውን ቢበይኑበት ጥሩ ነው። ወሳኝ ጉዳይ ነውና።
በተረፈ እግዚአብሄር ይስጥልኝ። ሸበላ ጊዜ። ቸር ያሰማን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ሥርጉትሻ 03/02/2026
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
• የኤርትራ መንግሥት ከጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ለቀረበው ቅሬታ መልስ ሰጥቷል። የኤርትራ መንግስት ሚዲያ ላይ እንብዛም ነበር። አሁን ከሆነ ግን በተከታታይ ሚዲያ ላይ አያቸዋለሁኝ።
ትናንት የፓርላማውን ውሎ አስመልክቶ በሁለት ጭብጦች ላይ ሼር አድርጌ ነበር። አንዱ ነገረ ኤርትራ ስለነበር አቅርቦቱ እንዳያነክስ ከቢቢሲ ያገኜሁትን መረጃ ማያያዝ ስለሚገባ እንሆ። …
• ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በትግራይ ጦርነት የኤርትራ ወታደሮችን የተለያዩ ጥፋቶች በመፈጸም ከሰሱ
«ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት ትግራይ ውስጥ በኤርትራ ወታደሮች የተለያዩ ጥፋቶች መፈጸማቸውን እና በአገራቱ መካከል አሁን ለተባባሰው ችግር መነሻ መሆኑን ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥር 26/2018 ዓ.ም. ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት በኤትርትራ ወታደሮች ተፈጸሙ ስላሏቸው ውድመቶች ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መካከል አለመግባባት የጀመረው ኢትዮጵያ ቀይ ባሕር ጉዳይን ስታነሳ ነው የሚሉ ወገኖች መኖራቸውን በማንሳት ይህ ስህተት መሆኑን ተናግረዋል።
በሁለቱ አገራት መካከል አለመግባባት የተጀመረው በትግራይ ጦርነት ወቅት መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተለያዩ ጥፋቶች በኤርትራ ወታደሮች መፈጸማችን ተናግረዋል።
"ኤርትራ ከተፈጠረች ጊዜ ጀምሮ በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል ችግር ነበረ። እኛ ከመጣን በኋላ አያስፈልገንም ይቅርብን ብለን ለምነናል" ሲሉ ለምክር ቤቱ አባላት ተናግረዋል።
"ፀቡ የተጀመረው ብዙዎች እንደሚያስቡት የቀይ ባሕር ጉዳይ ሲመጣ አይደለም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ "በትግራይ ውጊያ ሲጀመር በመጀመሪያው ዙር ወጊያ ሽሬን ካስለቀቅን በኋላ የኤርትራ ጦር ከኋላ የአንዳንድ ግለሰቦችን ቤት፣ ፎቅ ማፍረስ ሲጀምር ፀብ ተጀምሯል፤ አልተናገርንም አንጂ።
"አክሱምን ይዘን ስናልፍ፤ አክሱም ገብቶ ወጣቶችን በጅምላ ሲረሽን ፀብ ተፋገፍሟል። አድዋን ይዘን ስናልፍ፣ አድዋ ሄዶ ፋብሪካዎችን ሲፈታታ፣ ሲሰርቅ ፀብ ተጋግሏል።
"አዲግራት ደርሰን የመድኃኒት ፋብሪካውን የሚነቀለውን ነቅሎ የማይነቀለውን ሲያፈራርስ ፀቡ ጫፍ ደርሷል።ግን ያኔ የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህም በዚያም ለመዋጋት አቅም አልነበረውም።"
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ከኤርትራ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር እንዲነጋገሩ የቀድሞውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸውን እንዲሁም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩትን አቶ ደመቀን ወደ ኤርትራ መላካቸውን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኢትዮጵያ ጦር ወደ መቀሌ ሲጠጋ የኤርትራ ጦር ልክ በሌሎች ከተሞች እንዳደረገው ሁሉ በመቀለም ተመሳሳይ ጥፋቶችን ሊፈጽም ይችላልበሚል ስጋት ከውቅሮ እንዳያልፉ መነጋገራቸውን እና የሚያልፉ ከሆነ ግን "ወደ እናንተ ነው የምንዞረው" በማለት በአካባቢው "የሚጠብቅ ኃይል አስቀምጠን ነው መቀለ የገባነው" ብለዋል።
ይሄ ጸብ ተፋፍሞ ሄዶ የፕሪቶሪያ ስምምነት ሲፈረም "እንዴት ህወሓት ሳይጠፋ እንዴት ትግራይ ሳይወድም ፊርማ ይደረጋል በሚል ነው ፀቡ ጫፍ የደረሰው" ሲሉ ተናግረዋል።
አክለውም ኢትዮጵያን መጉዳት የሚፈልጉ አካላት መኖራቸውን ተናግረው "ገንዘብ ፋይናንስ ያደርጋሉ እመኑኝ ግን ኢትዮጵያን ግን አይችሏትም። ገንዘባቸውን ያፈሳሉ፤ ይከስራሉ እኛ ጉዟችንን እንቀጥላለን።»
-----------------------------------------------------------------------
• «ኤርትራ፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ንግግር "የጦርነት አጀንዳን ምክንያታዊ ለማድረግ" የቀረበ ነው አለች»
ከ 6 ሰአት በፊት …
የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስለ ኤርትራ መንግሥት ያደረጉት ንግግር፤ የኢትዮጵያ መንግሥት "በኤርትራ ላይ ሊከፍት ያቀደውን የጦርነት አጀንዳ ምክንያታዊ ለማድረግ" የቀረበ ነው ሲሉ ተቹ።
የኤርትራ መንግሥት ቃል አቀባዩ ማክሰኞ ጥር 26/2018 ዓ.ም. ምሽት በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ጦርነት "ወቅት እና ከጦርነቱ ረጅም ጊዜ በኋላ ለኤርትራ ሠራዊት የክብር ሜዳይ" ሲሰጥ ነበር ብለዋል።
የማነ ይህንን ያሉት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ በትግራይ ጦርነት ወቅት የኤርትራ ወታደሮች የጅምላ ግድያን ጨምሮ የተለያዩ ግፎችን ፈጽመዋል በሚል ከወነጀሉ በኋላ ነው።
የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ግንኙነት መሻከርን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ በሁለቱ አገራት መካከል ግንኙነት ውስጥ ችግር የተፈጠረው መንግሥታቸው በቀይ ባሕር ላይ የባሕር በር የማግኘት ጥያቄን በማንሳቱ "እንዳልሆነ" ተናግረዋል።
"በትግራይ ውጊያ ሲጀመር በመጀመሪያው ዙር ወጊያ ሽሬን ካስለቀቅን በኋላ የኤርትራ ጦር ከኋላ ኋላ ተከትሎ ሽሬ ገብቶ የአንዳንድ ግለሰቦችን ቤት ማፍረስ፣ ፎቅ ማፍረስ ሲጀምር ፀብ ተጀምሯል፤ አልተናገርንም እንጂ" ሲሉ በሁለቱ መንግሥታት መካከል "ጸብ የጀመረው" ከትግራይ ጦርነት ጋር በተያያዘ መሆኑ ገልጸዋል።
በተጨማሪም የኤርትራ ወታደሮች አክሱም ውስጥ "ወጣቶችን በጅምላ መረሸናቸውን" እንዲሁም አድዋ እና አዲግራት ከተሞች ውስጥ ፋብሪካዎችን እንዳወደሙ እና እንደዘረፉ ለምክር ቤቱ አባላት ተናግረዋል። እነዚህን ድርጊቶች ለማስቆም ወደ ኤርትራ "በርካታ መልዕክተኞችን መላካቸውን" አክለዋል።
"ይሄ ጸብ ተፋፍሞ ሄዶ የፕሪቶሪያ ስምምነት ሲፈረም 'እንዴት ህወሓት ሳይጠፋ፣ እንዴት ትግራይ ሳይወድም ፊርማ ይደረጋል?' በሚል ነው ጸቡ የመጨረሻ ጫፍ የደረሰው" ብለዋል። "ከዚህ ኃይል ጋር ሆነው ነው እንግዲህ አንዳንድ የህወሓት ሰዎች ኢትዮጵያን ለማፍረስ እንሥራ ያሉት" ሲሉም ከስሰዋል።
ለዚህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በኋላ በኤክስ ገጻቸው ምላሽ የሰጡት የኤርትራ መንግሥት ቃል አቀባይ አቶ የማነ፤ የብልጽግና ፓርቲ "አስቀያሚ መለያ የሆነው ማጭበርበር እና አታላይነት ዛሬ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ታይቷል" ብለዋል።
"የብልጽግና ፓርቲ መሪ እና ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦቹ" በትግራይ ጦርነት እየተካሄደ በነበረበት ወቅት እና ጦርነቱን ከቆመ በኋላ "ለረጅም ጊዜ ለኤርትራ ሠራዊት ከፍተኛ ውዳሴ" ሲያቀርቡ ነበር ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት አመራር እና ወታደራዊ አዛዦች "ጥልቅ ምሥጋናቸውን ለመግለጽ በአገር ደረጃ ሜዳሊያዎችን ሲያበረክቱ እንደነበር በሕዝብ የሚታወቅ መሆኑ ይታወሳል" ሲሉም በኤክስ ገጻቸው ጽፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ባደረጉት ንግግር የዘረዘሯቸውን ጉዳዮች "ርካሽ እና ወራዳ ውሸት" ሲሉም አጣጥለዋል። በኤርትራ ላይ የቀረበው ክስ የኢትዮጵያ መንግሥት "ሉዓላዊ የባሕር በር ማግኘት በሚል ሽፋን በኤርትራ ላይ ሊከፍት ያቀደውን የጦርነት አጀንዳ ለመሸፈን እና ምክንያታዊ ለማስመስል በድፍረት የተቀረጸ" ነው ሲሉም ወቅሰዋል።
የማነ አስከትለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በፓርላማ ንግግራቸው ያነሱትን እስራኤል ከሶሪያ በወረራ የያዘቻቸውን የጎላን ከፍታዎች ጉዳይ ጠቅሰዋል።
ዐቢይ በማብራሪያቸው ስለ መንግሥታቸው የቀይ ባሕር ጥያቄን እንደ የብሔራዊ አጀንዳ እንደሚገነዘበው ተናግዋል።
"እስራኤል የጎላን ተራራን የያዘችው ለብሔራዊ ደኅንነቴ፣ ለህልውናዬ ችግር ያጋጥመኛል ብላ ስላመነች ነው" ያሉት ዐቢይ፤ አክለውም "ቀይ ባሕር እና ኢትዮጵያ ለዘላለሙ ተነጣጥለው መኖር አይችሉም" ሲሉ ተደምጠዋል።
ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ የባሕር በር ለማግኘት የምትፈልገው "በቢዝነስ ሕግ" እንደሆነ ተናግረዋል። በባሕር በር ምትክ የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ወይም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ድርሻ ሊቀርብ እንደሚችል ጠቁመዋል። ይህ ካልሆነም "በሊዝ" ወይም "በመሬት ልውውጥ" ሊከናወን እንደሚችልም አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ እያለ ያለው "በስምምነት በገበያ ሕግ፣ ሳንጠፋፋ አብረን ለማደግ በድርድር እንፍታው እያለ ነው" ሲሉም የመንግሥታቸውን አቋም ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ኢትዮጵያ አሰብ ላይ "ወደብ፣ አየር ማረፊያ፣ መንገድ፣ ነዳጅ ማጣሪያ" መገንባቷን አስታውሰዋል።
"ለእኛ የሚገባንን በሆነ በሆነ ምክንያት ዛሬ መከልከል ቢታሰብ በቀጣይነት ማስቀረት ስለማይቻል ወደ ማይፈለግ ነገር ሳይገባ በሰላም በድርድር መጨረስ ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ" ብለዋል።
ዐቢይ የጠቀሱትን የጎላን ከፍታዎች ምሳሌ ያነሱት የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር፤ ይህ ጉዳይ መነሳቱ የኢትዮጵያ መንግሥት አሥመራ ላይ ሊከፍት ያቀደውን "ግድየለሽ እና ሕገ ወጥ የጦርነት አጀንዳ ምክንያታዊ ለማድረግ" የቀረበ እንደሆነ ጽፈዋል።
"እንዲያውም [የብልጽግና ፓርቲ] መሪ በኤርትራ ላይ የያዘውን ግድ የለሽና ሕገ-ወጥ የጦርነት አጀንዳ ምክንያታዊ ለማድረግ [በሚል] በዚሁ ንግግሩ ላይ 'የጎላን ከፍታዎች ምሳሌን' ሲያነሳ ጨዋታውን ራሱ አጋልጦታል" ብለዋል።
ከፕሪቶሪያ ስምምነት መፈረም ወዲህ ግንኙነታቸው እየሻከረ የመጣው ኢትዮጵያ እና ኤርትራ፤ አንዳቸው ሌላኛቸውን ሲወነጅሉ ቆይተዋል።
ከሳምንት በፊት የፌደራል ፖሊስ የኤርትራ መንግሥት በአማራ ክልል ለሚንቀሳቀሱት ፋኖ ኃይሎች "ልኳቸዋልል" ያላቸውን የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል። ኤርትራ ግን ይህንን ውንጀላ ውድቅ አድርጋለች።»

አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ