ነገረ መሠረት ቋሚ #ብራንድ ሊሆን ይገባል።።

 

ነገረ መሠረት ቋሚ #ብራንድ ሊሆን ይገባል።።
 
"የብልህ ሰው ልቦና ምሳሌን ይተረጉማል፤
የአዊቂ ሰው ጆሮም ጥበብ መስማትን ትወዳለች።"
(መጽሐፈ ሲራክ ምዕራፍ ፫ ቁጥር ፳፯)
 
#ምዕራፍ ፲፱።
 
 
 May be an image of one or more people
እንዴት ሰነበታችሁ ማህበረ ቅንነት? እኔ አምላኬ ክብሩ ይስፋ ደህና ነኝ። ሰሞናቱ በአገረ ምክክር ላይ አጀንዳወች በርከትከት ብለዋል። ስለሆነም በጥቂት ጉዳዮች ላይ ሰሚ እንደለለ ባውቅም ግን ውስጤ የሚለውን ባጋራ መልካም ነው። 
 
የነፃ አውጪ ግንባር መንፈስ ሁሉ #ቀደምትነትን ይሸሻል። #አዛውንት ታሪክን እንደ ጦር ይፈሩታል። ትውፊት እንደ ደመኛ ያዩታል። መቅድመ ሥልጣኔ ጸጉራቸውን ያቆመዋል። የማንነት ቀውስ ሲኖር እንዲህም፤ እንዲያም ያደርጋል። የነፃ አውጪ ግንባር መንፈስ ተስንሳፎ፤ እርሾ አልባ ከሌላ ዓለም የመጣ ዓይነት ዘመናይነት፤ ቅልጣንም ብዙ ጊዜ ይታይባቸዋል። 
 
አጥብቀው ከሚጠሉት በኽረ ጉዳይ #ብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማውን ነው። አፍሪካውያን አክብረው የሚነሱት ደግሞ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ሰንደቅ ዓላምን ነው። ብዙ አገሮች እሱን መሠረት ያደረገ መለያቸው አድርገውታል። ለአፍሪካውያን፤ ለቡኒያውያን፤ #ለጠይማን ዕንቋቸው የምንጊዜም ዕንቁ ነው።
 
ብሄራዊ ሰንደቅ ዓለማችን ወደ ጋድም አረንጓዴ፤ ቢጫ ቀይ ሲሆን ሦስቱም በስፋት ይሁን በቁመት #ተመሳሳይ ናቸው። አረንጓዴ ከቢጫው አያንስም አይወፍርም፤ ቢጫው ከቀዩ አይቀጥንም አያጥርም። 
 
አቀማመጡም ከላይ ወደ ታች አረንጓዴ፤ ቢጫ፤ ቀይ ነው። አንዳንድ ድርጅቶች አረንጓዴን ከሥር ያደርጋሉ መሠረትን በሚሉት ድርጅት ውስጥ ያ #ዝበት ነው። ግድፈቱ ግዙፍም ነው።
 
አገራዊ ምክክሩ ከሚነጋገርባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች ብሄራዊ ሰንደቅ ዓለማችን አንዱ ነው። ኮሚሽኑን ያደራጀው፤ የሾመው፤ በጀት መድቦ የሚያስተዳድረው ብልፄው ነው። ለእኔ የምክክር ኮሚሽኑ #የበላይ ጠባቁ ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ እንደ ሆኑ ይገባኛል። 
 
ለዚህም ነው የኮሚሽኑን ጉባኤ ከፋች እሳቸው የነበሩት። ያማ ባይሆን ዶር አብይ ድርሽ አይሉም ነበር። ቢገኙ እንኳን እንደ አንድ ዜጋ ቁጭ ብለው ከማድመጥ ውጪ ሌላ የመሪነት ሚና ባልነበራቸው። ሎጅኩም አያስኬድም። ነፃ ኮሚሽን እሳቸው በሚመሯት አገር? ራስ ገዝ የሆነ ተቋም? እእ። 
 
የብልፄ መንፈስ ደግሞ በቀደምትነት፤ በትውፊት፤ በታሪክ፤ በአዛውንት ታሪክ ላይ የውስጥነት ዝንባሌ እንደሌለው በሥራ ዘመኑ ተመልክተናል። በቀላሉ ትውልድ የሚቀረጽባቸው ፕሮጀክቶች #ሎጎን ተመልከቱት። ለምሳሌ ፋና ላምሮትን እዩት። በኢትዮጵያ ውስጥ ታይቶም፤ ተሰምቶም የማያውቅ ሎጎ ነው ያለው። 
 
እንዲያው ይሁንባችሁ እና የጠቅላይ ሚር አብይ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ሎጎ እስኪ አስተውሉት። ቀደምትነትን ሽሽት ላይ የሆነ ዝንባሌ ያለው ነው። ከቀለማት ግራጫ፤ ጥቁር እርድ፤ ጥቁር አረንጓዴን ይጠቀማል። ሎጎወችን በሙሉ ጠረጴዛ ላይ ዘርጉ እና ጊዜ ወስዳችሁ እዮቸው። እኔ ዝንባሌያቸውን ፍለጋ ብዙ ጊዜ በሎጎቻቸው ላይ አተኩራለሁኝ። እንደ አልባሌ አላያቸውም። ሎጎወቹ #የአብይዝም ፖሊሲ ማስተርጎሚያ ቱሎች ናቸውና። 
 
ተሟልቶ የኢትዮጵያ ቤሄራዊ ሰንደቅ ዓላማትን የያዘ የጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ሎጎ በፍጹም አታገኙም። #ቀይ የሚባል አይጠቀሙም። ፈጽሞ። ጥቁር አረንጓዴ፤ ጥቁር እርድ ይጠቀማሉ፤ ቀይ አልቦሽ። ሙሉዑ የሆነው የኢትዮጵያ መንፈስ ሁልጊዜ በሎጓቸው ላይ ስደት ጠማኝ ወይንም #ተጠማኝ ነው። 
 
……#የለም
 
ከዚህ ስነሳ አገራዊ ምክክሩ የኢትዮጵያን፤ የፓን አፍሪካኒዝም መነሻ የሆነውን አረንጓዴ፤ ቢጫ፤ ቀይ ቀለማትን ህብራዊነት ምንም ደባል ነገር ሳይጨመርበት የምስራች ያስደምጣል የሚል ተስፋ የለኝም። 
 
የራሱ የአገራዊ ምክክሩ መለያ ዓርማ #ኢትዮጵያዊ የሆነ መንፈስ የለውም። ቀለሙም ይሁን ዲዛይኑ። እራሱን አርቆ ነው የኢትዮጵያ ችግርን መፍቻ ቁልፍ ፍለጋ ኮሚሽኑ እየደከመ፤ እየባተለ የሚገኘው። እንኳንስ 4ሺህ 100 ሰብ ሰብስቦ ወጥ ሃሳብ አፍልቆ ድርጊት ላይ ለማዋል ይከብዳል። እኛ አስቸጋሪወች ነን። 
 
#እንደ እኔ #ብራንዱ ምንም የሌለበት አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቢሆን ምርጫዬ ነው።።
 
እንደ እኔ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማ ግራንድ ቀለማት አረንጓዴ፤ ቢጫ፤ ቀይ በጋድም የተሠራው ለዘለቄታ በቋሚነት ሆኖ ቢጸድቅ መንፈስን የማሰባሰብ አቅሙ ብርቱ ይሆናል። የማጽናትም ክህሎት ይኖረዋል። የውስጥነት ማህተም የመሆን አቅም አለውና።
 
ብልፄው ካሰኜው ለራሱ መለያ ፒኮክ፤ ኦዳ፤ ኢነርጂ ገብ ምስሎች ወይንም የአምልኮ ምኞቱን ቢቀጣጥልበት መሪ አይደል ሥልጣኑ እስካለ ድረስ ይችላል። ቢያንስ ካድሬወቹ፤ እና ደጋፊወቹ፤ የነፃ ዓውጪ ግንባሮቹ ይደግፋለት። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶን ከብሄራዊ ሰንደቋ የለየ እርምጃ ወስዟል። ያን ዘመን ጠገብ አቅም ብልፄው ያስቀየረው እኮ በዘመኑ ንጹሁ ሰንደቅ ዓላማን ማየት ስለማይሻ ነው። ሽሽት። ኢትዮጵያን እየመሩ ከእሷ ውስጥነት ይልቅ #ስደተኝነት ………
 
አብዝኃኛው በተለይ ሳይለንት ማጆሪቲው ክንፍ ብሎ የሚወደው ግን ንጹሁን አረንጓዴ ቢጫ እና ቀይ ህብረ ቀለማቱን ነው። አረንጓዴ፤ ቢጫ ቀዩ ህብረ ቀለማቱ ብሩህ ናቸው። 
 
ብዙ ወገኖቼ ፋኖ በቋሚነት ብሩሆቹን መጠቀም ከጀመረ ወዲህ፤ በኢትዮጵያኒዝም ውስጥ ያሉ ሳይቀሩ፤ ፋኖ አይደለሁም ለማለት ይመስላል፤ በፍርኃትም ጭምር የኢህአዴግን መርጠዋል። ኦላ ይሁን ህወሃት፤ ብልፄው ይሁን ሌላው #ግራንዱን ህብረ ቀለማት የነፈጋቸው የለም። የከለከላቸው የለም።
 
ብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማችን ሃብትነቱ #የሁላችንም ነው። ማን ሰጪ ማን ነሺ ሊሆን? ሁሉም ዜጋ መነሻ ብራንዱን ከፈቀድነው በፍቅር ተቀብሎ አክብሮ ያስከብረናል። በየትኛውም ሁኔታ፤ በስደትም አገር ድምቅ የሚያደርገው አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ነው። እኔ አንድ ጊዜ ኢትዮጵያን ወክዬ በተገኜሁበት የፎቶ ኤግዚቢሽን ስንት ተሞክሮ የጸደቀው ያሰበለውም አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለም ቲ ሸርት ነበር። የሆነ #ቅዱስ መንፈስ አለው። ፈተናው የበዛም ለዚህ ነው። ሲያሰባስብ ከውስጥ ነው። ሲማራም ለድል እና ለስኬት ነው።
 
#ለዜጋ መብት ጥንቃቄ።
 
የአንድ አገር ዜጋ እራሱ አገር ነው። አገርነቱን የሚገልጹ ሁነቶች መብቱ ሲጠበቅለት ነው። የፈለገ - ዜጋ፤ የፈለገ - ተቋም አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን ይልበሰው፤ ያዋህደው፤ ያምልክበት። 
 
ያልፈለገው ደግሞ የብልፄን ይጠቀም። ግራንዱ ግን ቀደምቱ ምንም የሌለበት #ኦርጅናሉ ይሆን ዘንድ ከደከመ ላይቀር አገራዊ ምክክሩ ሁለቱን አማራጮች ቢያሳልፍ ብልፄን ቢያሳምን የአቅም አደረጃጀት፤ አመራርን ክህሎት ያጸድቅለታል። ተመሳሳይ ግድፈት ከመጣ ግን ያው በሸፈተ ልቦና ከሂደት ጋር መጪ ነው። 
 
ቀለሙ ሳይቀየር አድዮ፤ የኢነርጂ ምልክት፤ የብልፄን የአምልኮውን፤ ወዳጁን ፒኮክሻ፤ የኦዳ ዛፍ ወዘተ ቢደረግበት ታጥቦ ጭቃ ነው። ከዛ ለዛ የኢህአዴጉ ምን አለና? በየዘመኑ የዜጎች ነፃነት በስውር ጫና ውስጥ እስር ቤት ሊፈረድበት አይገባም ባይ ነኝ።
 
ብሄራዊ ሰንደቅዓላማችን ነፃነት ጠምቶታል። ነፃነት ጠምቶታል። ተጋድሎ ላይም ነው ያለው። ምክክሩ የተጎዳን ለመጠገን፤ ለማጽናናት ከሆነ ለሚፈልጉት ፍጥጫ፤ ዘለፋ፤ ግድያ፤ እስራት፤ እንግልት፤ ቃጠሎ ሳይደርስ በአገራቸው መሬት እንዳሻቸው አድርገው ይጠቀሙበት ዘንድ ነፃነቱ ሊታወጅ ይገባል።
 
ህመምተኛው ፈውሱ ያለ ከራሱ ነው። ከማንነት ቀውስ እራስን ማዳን በመዳፍ ያለ ብልህነት ነው።
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
27/07/026.
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
See less

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።