ከንቲባ አዳነች አበቤ ወደ #ፌድሬሽን ምክር ቤት ጎራ ይሉ ይሆን?
ከንቲባ አዳነች አበቤ ወደ #ፌድሬሽን ምክር ቤት ጎራ ይሉ ይሆን?
"ቀን የሚያመጣውን ምን እንደሆነ
አታውቅም እና ነገ በሚሆነው አትመካ።"
(መጽሐፈ ምሳሌ ምዕራፍ ፳፯ ቁጥር ፩)

ምዕራፍ ፲፱።
#በር።
በምን ቀመር አዲስ አበባ እራስ ገዝ ትሁን፤ አዲስ አበባ ክልል ትሁን ተሸንፎ አዲስ አበባ በኦሮምያ ሥር ትተዳደር የሚል የውሳኔ ሃሳብ እንዳለፈ አይታወቅም። ብልፄው ለካንስ የቁጥርም ስፔሻሊስትም ነው።
በዘመነ አብይዝም የማይመች ገጠመኝ አንድ ሰብዕና ከአብይዝም ልቆ #ዘለግ ብሎ ማደግ ነው። ወይንም ገነን ያለ ተቀባይነት ማግኜት ፈጽሞ የማይመች ጉዳይ ነው። በኢትዮጵያ እያደገ፤ ከፍ እያለ፤ እየደረጀ እንዲሄድ የሚፈቀድለት የአብይዝም መንፈስ ብቻ ነው።
ነገረ አዲስ አበባ እና የኮሪደር ልማቷ፤ ተጨማሪ የውበት ፕሮጀክቶቿ ሲጠሩ የሚጠቀሱት ከንቲባ አዳነች አበቤ ናቸው። #መጠሪያቸው ሁናለች ለከንቲባ አዳነች አበቤ አዲሷ።
ለነገሩ ሥራውን ሁለቱ ቢሠሩትም፤ ግን የአዲስ አበባ ተጠሪ ከንቲባዋ ስለሆኑ፤ መንትያው ሥያሜ ይረሳል፤ ወይንም ይዘነጋል። ይህ ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አቅደው ለሚፈጽሙት፤ ለሚደክሙለት የውሃ ዳንስ ትዕይንት በሌላ ስኬቱ ሲጠራ አይፈልጉም። #የኮፒራይት © ጉዳይ ነዋ!
በዚህ ሂደት በሰጨኝ አይቀሬ ነው። መጋቢት 1/2011ዓም የአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍ እና የባልደራስ ምሥረታ ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ እራሳቸውን ሳይደብቁ አደባባይ ላይ ብስጭታቸውን ያዬንበት ዕለት ነበር።
እኔ በወቅቱ በሰጨኝ ለጠቅላይ ሚኒስተር አይመችም ብዬ ወግ ቢጤ ጫጭሬ ነበር። አዲስ አበባ መጠሪያዋ አብይዝም እንጂ #ሌላይዝም እንዲሆን ፈጽሞ አይፈለግም።
ያን ቀን ኢትዮጵያ የቦይንግ አውሮፕላን አደጋን ኢትዮጵያ አስተናግዳ ነበር። ከአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍ ጋር ተያይዞ በቤተመንግሥት አቶ ንጉሡ ጥላሁን በሰብሳቢነት የመሩት፤ የዛሬን አያድርገው እና አቶ ጃዋር መሃመድ እና ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና የተጋበዙበት የሚዲያ ኮንፍረንስ በቤተ መንግሥት ተካሂዶ ነበር። ነገረ አዲስ አበባ ለጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ #የህቅታ ጉዳይ ነው።
ግን የቀድሞ የኮምኒኬሽን ሚ/ር አቶ ንጉሡ ጥላሁን አሉን ባገር? የሆነ ሆኖ ከእስኬው ጋር የተካረረ ሁነት የተፈጠረውም በህቅታ ጉዳይ አትምጣብኝ ዓይነት ይመስላል። ከዛም በኋላ አግሬሲብ የሆነ መንፈስ አዲሷን ሲንጣት ነበር።
#የምክክር ኮሜሽኑ እና የአዲስ አበባ ልዕልና።
የአዲስ አበባ ልዕልናዊ ተስፋ "ባርነት ወይስ ነፃነት" በሚል መንፈስ ውይይት እንደተካሄደ ነው የገባኝ። ነገረ አብን በራራ የአማራ ነው የሚለውን ጥያቄውን ሴብ የት እንዳደረገው አልታወቀም። ወይ እርገት ወይ ስምጠት ልኮት ይሆናል።
የኦሮሞ ብልጽግና ግን የማህበረ ኦነግን መንፈስ አሽኮኮ አድርጎ ለድል በቅቷል። ዲል ያለ ድል ነው ለእኔ። ለነገሩ እኔ ከመስከረም 5/2011 ዓም ጀምሮ አዲስ አበባ ለኦሮምያ ፈቃድ በስውር እንደተሰጠው ነበር እማምነው።
ስለሆነም መረጃውን ስሰማ አልደነቀኝም። በለማ ሁኔታ አዲስ አበባ ላይ ያለው የኗሪው፤ የብሄራዊ በዓላት አከባበር ጋር የነበረው ስቃይ፤ ከባልደራስ ጋር የነበረው ገረጭራጫ መንፈስ፤ ለመስቀሉ እሮጣለሁ ሲታገድ፤ ሰላማዊ ሰልፍ ለብልፄ ብቻ መፈቀዱ ተጨባጩ የሚነግረን ሃቅ ስለነበረ አዲስ አበባ የመንፈስ ነፃነቷ ጉዳይ በዘመነ አብይዝም #ለዘዝ ያለ ነበር።
በምክክር ኮሚሽኑም ከብልፄው ፍላጎት ውጪ አንዲት ስንዝር መራመድ እንደማይቻል አውቃለሁኝ። መጀመሩ ግን ደፋር እርምጃ ነው። ደፋር እርምጃው ለማህበረ ኦነግ መንፈስ የሚያሳኩለት በኽረ ጉዳዮች ይኖራሉ። ኢትዮጵያዊው ጉግል አቶ ሽመልስ አብዲሳ እኮ ተናግረዋል። ለፎርማሊቲ 4000 ተወያይ መሰብሰቡን።
የኢትዮጵያ ልጆች በአንድ መዕድ መተያዬታቸው፤ መቀራረባቸው፤ መተዋወቃቸው ብቻ ሳይሆን ልምዱም ቀላል አይደለም። ቀኝም ነፈሰም - ግራ፤ ግራም - ነፈሰም ቀኝ፤ የብልፄው የውስጥ ፍላጎት ተደላድሎ ህጋዊ ዕውቅና ያገኛል በኮሚሽኑ ጉባኤ። ከአሁኑ ኢትዮጵያ በዚህ ፕሮሰስ ላይ ስለመሆኗ ጉግል ይለፍ እየሰጠ ነው። እንደ አንድ የታሪክ ምዕራፍ።
በዚህ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ አፍሪካ መናህሬዬ፤ መላ የኢትዮጵያ ህዝብ ቤቴ፤ ዓለምም የዴፕሎማሲ ፬ኛ ከተማዬ የሚላት አዲስ አበባ፤ ስንት ዘመን ሚሊዮኖች የደከሙላት፤ ሰማዕትነትን የተቀበሉላት ከተማ በአንድ ክልል ሥር ትሁን የሚል አማራጫዊ ብይን ማሳለፍ ለኮሚሽኑ ማንነት እጅግ ሰቅጣጭ ውሳኔ ነው። ለታሪኩ አወቃቀር ብልዘት ይሸልማል።
#የእኔ።
የእኔ ፍላጎት ራስ ገዝነት አይደለም። ራስገዝነት እብጠት ስለሚያመጣ። ዕብጠት አናርኪዝምን ስለሚያዋልድም። ክልልም አይመቸኝም። ክፍለ አገር ነው የሚመቸኝ። ክልል ህወሃት - ወረስ በታኝ ሴራ ስለሆነ። ክልል ለሳር ግጦሽ እንጂ ለሰው ልጅም አይመጥንም።
የሆነ ሆኖ ክልል ከቀጠለ አዲስ አበባ "የፌድራሉም" የኦሮምያም ሳትሆን እራሷን የቻለች፤ ሙሉ ሥልጣን እና ሙሉ አካል ያላት፤ ነፃነቷ የማይገፈፍ ወይንም ጫና የሌለባት የናፍቆት ከተማ እንድትሆን ነበር። ነገ ምን አልባት ቢዛም ሊጠየቅባት ይችላል? ማን ያውቃል?
አዲስ አበባ ግሎባል ከተማ ናት። ከአንድ ክልል ጋር የሚያጣብቃት ታሪካዊ ሆነ ሞራላዊ ሁነት የለም። በፌድራሉ ሥር የምትሆነው ማንነቷ ተድጦ ይሆናል።
አዲስ አበባ የራሷ ማንነት ያላት የደግ፤ የሩህሩህ፤ የታታሪ ህዝብ አንባ ናት። አንበልም ናት። የከተሞችም ሞዴል፤ ካፒቴንም ናት። ቀደምቶችን በታሪክ ባትቀድምም ለዘመኑ ሥልጣኔ ግን የቅርብ ናት። ነፃነቷ ባይታገት ምርጫዬ ነበር። የአገራዊ ምክክሩ ትልቁ የግድፈት መነሻ የሚጀምረው የአዲስ አበባ ማንነት አልባ ከመደረጉ ላይ ነው። ሌላ አሸናፊ ሲመጣ ደግሞ ይህ ይበወዛል። ወይንም ይሻራል።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ የሚዘነጋው ሳይለንት ማጆሪቲ የሚባለውን የጨመተ ማህበረሰብ ነው። ይህ ሳይለንት ማጆሪቲ + ውህድ ማንነት መጠጊያ የለውም።
አለ ከተባለ አዲስ አበባ ብቻ ነው። ይህን አብሰንት ማድረግ ስንት ሐረግ እንደሚጠነዝል ማሰብ ያስፈልጋል። ከመጠንዘል በፊትም ምን ሊያመጣ እንደሚችል አይታወቅም። የመንፈስ ማረፊያ ማዕከል ያስፈልጋል ለዜጋ። የመንፈስ መጠጊያ አስኳል ያስፈልጋል የእኔ የሚለው ዞግአልቦሹ ማህበረሰብ፤ የፖለቲካ ድርጅት አልቦሹ ማህበረሰብ።
ይህን ማሳጣት ለማግሥት የምሥራች ዜና ሊሆን ፈጽሞ አይችልም። የሰማሁት በአዲስ አበባ ጉዳይ ብልጽግና ከሁለት ተከፈለ ነው። ወጥ ፓርቲ እንዴት? እንዴት ሊከፈል ይችላል። አቋቷም ሳይዝ ነው ጉባኤውን ብልፄ የተቀላቀለውን? ብልፄው ወጥ ነኝ ስለሚል።
ዞጋዊ ዝንባሌው አይሏል። የሰሞናቱ ሁኔታ ከኢህአዴግም የባሰ ነገር ነው የሚደመጠው። በቀደመ ጊዜ እራሱን የቻለ አካል ያላት አዲሷ ተጠቀለለች። ሁለቱም አማራጮች በኢትዮጵያዊነት ላይ የተቃጣ ፈታኝ ገጠመኝ ነው።
በምንም ተዓምር የአንድ ክልል ፍላጎት እንዲህ አሸናፊ ሁኖ ሊወጣ አይችልም። በቁጥር ውክል እና ማጣፋት ካልሆነ። ነግሶ የወጣው መንፈስ ጠረኑ አቶ አባይ ወልዱን ይመስላል።
#አምሮባቸዋል ከንቲባ አዳነች አበቤ።
ሞደኛ ናቸው። እንደ ገና ተፈጥረዋል ማለት ይቻላል። በጣም አምሮባቸዋል። ተመችቷቸዋል። አሁን ደግሞ ለሌላ ኃላፊነት ይታጫሉ። የቋንቋው ነገር እንጂ ውጭ ጉዳይም ከሳቸው የሚቀርብ የለም፤ ያ ቢቀር ፌድሬሽን ምክር ቤት ነፍሱ ከቀጠለ ለዛ ይታሰቡ ይሆናል። የመሰላቸት ነገር በዛ አካባቢ ስለማስተውል። ጠቅላይ ሚር አብይ ሁሉ ነገር ይሰለቻቸዋል።
አዲስ አበባ ከንቲባ በቀጣይ ይኖራታል። ግን የፓወር ተጠማኝ ትሆናለች። ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ እና አቶ ሽመልስ አብዲሳ የሚስማሙበትም ሁለቱም ማህበረ ኦህዴድ ናቸው። የሥም ቅይይር ካልሆነ አዲስ አበባ በፌድሬሽን ትሁን በኦሮምያ እሱበእሱ ነው። ሎጅኩ ይህ ነው።
ከፍ -- ባለ፤ ጫን ---- ባለ፤ አስተማማኝ በሆነ ተጠቃሚነትን ለኦሮምያ የሚያስገኝ ውሳኔ በቀጣዩ ይበየናል። ይህ ብይን አባይ ምንጩ ከእኛ ነው። ስለዚህም ለእኛም ይህ ይታሰብ ሌላው ቀጣዩ የአማራ ፖለቲከኞች ጥያቄ ይሆናል። አንድን ነገር ይሁንታ ስትሰጥ ሌላም ተከታይ ጥያቄ እንዳለ ማሰብ ይገባል።
በአዲስ አበባ ላይ የተጣለው ቀንበር የወልቃይት ጠገዴ የራያም ዕጣ ፈንታ ከዚህ ውጭ ይሆናል ብዬ አላስብም። መጠቅለል የአብይዝም የፖሊሲ አቅጣጫ ይመስላል።
የምክክክር ኮሚሽኑ ተፈትኗል። ደክሟል። ብዙ የኢትዮጵያ ሙሁራን እየተሳተፋ መሆኑንም አዳምጣለሁኝ። ይህ ታሪካዊ ገጠመኝ ግን የአንድ ዓውራ ፓርቲ መሻትን ለማሳካት ብቻ ከሆነ፤ ብልፄው የሚፈልገውን ብቻ ለማስፈጸም ከሆነ ድካሙም፤ ትጋቱም ይሁን ትትርናው ……… ከኮሚሽኑ ታሪክ ጋር ምን እና ምን ሊሆኑ ይሆን? አጤ ሂደት ይበይነው።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
27/07/026.
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ