አሁን ያለው ብሄራዊ መዝሙር #ቢቀጥል ምርጫዬ ነው። #እፈርምለታለሁኝ።

 

አሁን ያለው ብሄራዊ መዝሙር #ቢቀጥል ምርጫዬ ነው። #እፈርምለታለሁኝ
 
"ልጄ ሆይ ጠቢብ ሁን ልቤንም ደስ አሰኜው።"
(መጽሐፈ ምሳሌ ምዕራፍ ፳፯ ቁጥር ፲፩)
 
 No photo description available.
 
#ምዕራፍ ፲፱።
 
የኢህአዲግ ትውልድ ያደገበትን ብሄራዊ መዝሙር ይወቀው፤ አይወቀው፤ ስሜት ይስጠው፤ ስሜት አይስጠው አላውቅም። እያንዳንዱ ክልል መለያ ዓርማ፤ መዝሙርም እንዳለ አዳምጣለሁኝ።
 
 የቅኝ ግዛት ምኞት ያላቸው አገሮች የኢትዮጵያን የጥንካሬ ሞተር የፈተኑበትን ህልም ያሳካው ህወሃትሻ ነው። ብሄራዊ መዝሙር፤ ብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማ የዜግነት አሻራ ነው። በቋሚነት የሚቀጥልበት የመቻል አቅም አምጠን ልንወልደው ይገባል። እራስን ማሸነፍ ያስፈልጋል።
 
አገር ስላለ ነው ሹመቱ ሽልማቱ፤ ምኞቱ ቅብጠቱ አና ያለው። ብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማ፤ ብሄራዊ መዝሙር፤ ብሄራዊ ቋንቋ አገር የፈጠሩ፤ አገራዊነትን የመገቡ። በራስ መተማመንን አፍልቀው ያጸደቁ ልዩ ስጦታወች ናቸው። ክብር ቀርቶባቸው እንግልታቸው ግን እንደ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ያቆስላል። እርሾ አልባ አየር ላይ ተንሳፎ ተጠንስሶ፤ የተወለደ፤ ያፈራ፤ ያሰበለ ምንም ነገር የለም።
 
የሆነ ሆኖ የኢህአዴግ ዘመን ብሄራዊ መዝሙር እንደአለ #ቢቀጥል ጥሩ ይመስለኛል። የጃንሆይ ትውልድ ነበረው፤ የደርግ ትውልድም ነበረው፤ የኢህአዴግ ትውልድም አለው። ይህን ሰርዞ እና ንዶ እንደገና "ሀ" ብለህ ጀምር ብዙ ንደት ያመጣል። የእስከዛሬው ግድፈታችን ይበቃል። የመቻል አቅማችን ፈታትሸን እራሳችነን ገስጸን ወደ ቀልባችን ልንመለስ ይገባል።
 
የግጥሙን ስንኝ በተደጋጋሚ አየሁት። የዜማ ቅኝቱን አዳመጥኩት። ስሜት ይሰጣል። አገራዊ ፍቅርን ይስባል። እኔ ህወሃትሻን በብዕር ሞግቸዋለሁኝ። መዝሙሩን በሚመለከት ግን ውስጤ ይቀበለዋል። ስሰማው ሰውነቴን #ይነዝረኛል። 
 
ውስጤን አግኝቶታል ማለት ነው። ከውስጤ ጋር ሲቀራረብ በተመስጦ ነው የማጣጥመው። ስለዚህ እኔን ያሸነፈ ጉልበተኛ ሥንኛት እና ዜማ ለእኔ መንፈስ ጣዕም አለው። ስለዚህ ቢቀጥል እኔ #እፈርምለታለሁኝ። 
 
ከኢትዮጵያ ቅደሚ ጋርም በቃና ይመጋገባል። የደርግ ጊዜ ብሄራዊ መዝሙር ስሰማው በጣም ብዙ አገራዊ ጠረኖች፤ ናፍቆቶች ይታገሉኛል። 
 
እርግጥ ነው በብሄራዊ መዝምሩ ያለ ኃይለ ቃል፤ መሪ ስንኛት ግን ተፃሮ የቆመው የህወሃት መራሹ ኢህዴግ የዞግ ግንባር " …… #የዜግነት ክብር፤ #ሰብዕናን ያልሻረ፤ #ለፍትህ ነፃነት፤ አለብን "#አደራ"" ወዘተ ኃይለ - ሥንኛት መሬት ላይ የመተግበር አቅሙ ስስነት ኢትዮጵያ የባህር በር፤ ወደብ አልባ፤ የመብት ጥሰት በግፍ የታየበት ዘመን ነበር። መዝሙሩ ግን መተግበር የሚያስችል የገቢር ፖሊሲ አቃተው እንጂ ፍሬ ነገሩ የውስጥነት ባህሬ አለው።
 
 
ደራሲው ጋሼ ደረጄ መላኩ መምህሬ ነበር። ግጥም መፃፍ የጀመርኩት በእሱ #መምህርነት ነበር። ጋሼ ደረጄ የግጥም መምህር ብቻ ሳይሆን የግጥም አነባበብም መሪ ነበር። ትዝ ይለኛል "የክረምት ማገዶወችን" ተውነታዊ አድርጎ ያቀረበበት መንገድ። 
 
በዛን ጊዜ አዲስ ብሄራዊ መዝሙር ሊዘጋጅም ነበር። እናም ቃላቱ፤ ስንኙ፤ ማረፊያ ቤቱ ተቀምሮ በቁጥር ተሰጠን። እና #ተወዳድሬም ነበር። ረቂቁ ስክሪፕት የእኔ ከእጄ ይገኛል። 
 
ሌላው መምህሬ የሥነ ጹሁፍ አቶ አበበ ኬሬ ይባል ነበር። ጋሼ አቤ ሥነ ጥበብ በማህበረሰቡ ጓሮ ይታፈሳል የሚል ዘይቤ ነበረው። ትምህርቱን በአመዛኙ እንግዶችም ተጋብዘው ያስተምሩን ስለነበር በቴፕ እቀዳው ነበር። ጋሼ ደረጄ አውሺኝ ብሎኝ እንደ ሰጠሁት ሳልቀበለው ስደት ጠራኝ።
 
#ንደት የስሜት ወጌሻ የለውም።
 
ስሜት ይገልጣል። ስሜት ይገዛል ይነዳል። ስሜት ራዲዮሎጂ ነው። ስሜት ከፍም፤ ዝቅም ይላል። ስሜት ርህርህናን፤ ብስጭትን፤ አዘኔታን፤ ፍስኃን፤ ቁጣን ይሁን መረጋጋትን ይመራል ያደራጃል። ይህ በዕለታዊ ኑሮ የገጠመኞች ሙቅተ እና ቅዝቃዜ፤ ለብታ እና ሽልብታ ሲሆን ላይከብድ ይችላል።
 
በአገራዊ፤ ብሄራዊ ጉዳይ ሲሆን ግን ምህንድስናው ለግንባታ ከሆነ ይበጃል፤ የዚህ ተቃራኒ ሲሆን ግን ይንዳል። በየጊዜው ብሄራዊ መዝሙር እየተዘጋጄ በዓለም ዓቀፍ መድረክ ሁልጊዜ ቅጥአንባሩ የጠፋ፤ መያዣ መገረዣ የሌለው የአቋም መለዋወጥ መከሰት ማንነትን - ያቆስለዋል፤ በተመሳሳይ ሁኔታም የኢትዮጵያን የፖለቲካ አቅም፤ የመቻቻል ሁነት፤ የመደማመጥ ባህል አቀጭጮ ገመናችን ለዓለም አደባባይ ያቀርባል።
 
ለየዘመኑ ትውልድም እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ ጸንቶ ለመቆም የውስጥ ስሜቱን ያፍረከርካል በየጊዜው እኛኑ የሚፈትን ፍርሻ በፈጠርን ቁጥር። ስለዚህ ይህ ብሄራዊ መዝሙር ቢዘልቅ፤ ከትውልድ ወደ ትውልድ #በቋሚነት ቢሸጋገር መልካም ይመስለኛል። 
 
አንድ በዚህ እንኳን ብንስማማ። አንድ ይሄን ብናስቀጥል ጉዳት የለውም ብዬ አስባለሁኝ። ምክንያቱም በእኛ ጓዳ ብቻ የማይቀር ስለሆነ። ኢትዮጵያን በወከለ አደባባይ ሁሉ አዳዲስ መዝሙር ልመዱ፤ አድምጡም ያሳፍራል። ትናንት የተፈጠሩ ቋሚ ብሄራዊ መዝሙር አላቸው።
 
ለአፍሪካ ህብረት መዝሙር የበቃ የሥነ - ጥበብ አቅም እንደምን ለአገራችን ለኢትዮጵያ #አንሰን እንገኝ? የኢህአዴግ ትውልድ ስሜቱ ይናዳል ብሄራዊ መዝሙሩ ቢቀየር። ለስሜት ንደት ደግሞ ብሄራዊ #ወጌሻ የለውም። በብልፄው አመራር ውስጥ ሁሉም ማለት ይቻላል የዘመነ ኢህዴግ ሊቅ ነው ያለው። ያን ሸፍትብኝ ማለት ይሆናል ብሄራዊ መዝሙሩ ቢቀየር።
 
ስሜትን ማድመጥ፤ ለስሜት ልዩ ጥንቃቄ ማድረግ #ብልጠት ሳይሆን #ብልህነት ነው። 
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
 
ደህና እደሩልኝ። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
27/07/026.
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
 
#የሶስቱ መንግስት ዘመን የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር በፅሁፍ ስክሪፕቱን የወሰድኩት ከታሪክ ወደ ኋላ ፔጅ ነው።
ታሪክን ወደኋላ
pdnSoosert 920ll1a01ue1fr,fub2r001uy9 mt73hu23Ffuu0f32503a2f · 
 
የሶስቱ መንግስት ዘመን የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር በፅሁፍ 
 
የኢህአዲግ ትውልድ ያደገበትን መዝሙር በቃሉ
 
▻» በኢ.ህ.አ.ዴ.ግ መንግስት ዘመን
የዜግነት ክብር በኢትዮጵያችን ፀንቶ
ታየ ህዝባዊነት ዳር እስከ ዳር በርቶ
ለሠላም ለፍትህ ለህዝቦች ነፃነት
በእኩልነት ቆመናል ባንድነት
መሠረተ ፅኑ ስብእናን ያልሻርን
ህዝቦች ነን ለስራ በስራ የኖርን
ድንቅ የባህል መድረክ ያኩሪ ቅርስ ባለቤት
የተፈጥሮ ፀጋ የጀግና ህዝብ እናት
እንጠብቅሻለን አለብን አደራ
ኢትዮጵያችን ኑሪ እኛም ባንቺ እንኩራ።»
• ግጥም:- ደረጃ መላኩ መንገሻ
• ዜማ:- ሰለሞን ሉሉ ምትኩ
• በ 1984 ዓ.ም 
 
Ethiopian national anthem - የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር 
 
 
▻» በንጉስ አፄ ኃይለሥላሴ መንግስት ዘመን
ኢትዮጵያዬ ሆይ ደስ ይበልሽ
በአምላክሽ ኃይል በንጉስሽ
ተባብረዋልና አርበኞችሽ
አይነካም ከቶ ነፃነትሽ
ብርቱ ናቸውና ተራሮችሽ
አትፈሪም በጠላቶችሽ።
ድል አድራጊው ንጉሳችን
ይኑርልን ለክብራችን።»
• ግጥም:- በቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴ
• ዜማ:- ኬቨርክ ናልባልዲያን
• በ1919 ዓ.ም 
 
ታሪክን ወደኋላ
▻ «በደርግ መንግስት ዘመን
ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ፡ ኢትዮጵያ ቅደሚ
በኀብረተሰባዊነት ፡ አብቢ ለምልሚ
ቃልኪዳን ገብተናል ፡ ጀግኖች ልጆችሽ
ወንዞች ተራሮችሽ ፡ ድንግል መሬትሽ
ለኢትዮጵያ አንድነት ፡ ለነፃነትሽ
መስዋዕት ሊሆኑ ፡ ለክብር ለዝናሽ
ተራመጂ ወደፊት ፡ በጥበብ ጎዳና
ታጠቂ ለስራ ፡ ላገር ብልፅግና
የጀግኖች እናት ነሽ ፡ በልጆችሽ ኩሪ
ጠላቶች ይጥፉ ፡ ለዘላለም ኑሪ።»
• ግጥም:- አሰፋ ገ/ማርያም
• ዜማ:- ዳንኤል ዮሐንስ
• በ1968 ዓ.ም 
 
National Anthem of Ethiopia (1974-1992) - "ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ቅደሚ" (1980s Authentic Vocal Version)

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።