#ሽኝት ሆድ ያረባብሻል። ይገባልም።

 

#ሽኝት ሆድ ያረባብሻል። ይገባልም።
 
ገዳይዚም ተመስጥሮ ሳይሆን ተገልጦ ነው የተጀመረው። መሪወቹ ነግረውናል እኮ።
ስለዚህም ከገዳይዝም ከተፈጥሮው የሚመነጩ አስደንጋጭ ክስተቶች የግድ ይሆናሉ። 
 
"እኔ ሰምቻለሁ፤ ልቤም ደነገጠብኝ፤
ከድምጹ የተነሳ ከንፈሮቼ ተንቀጠቀጡ፤
መንቀጥቀጥ ወደ አጥንቶቼ ገባ
በስፍራዬ ሁኜ ተናወጥሁ፤
በሚያስጨንቁን ህዝብ ላይ
እስኪመጣ ድረስ፤
የመከራን ቀን ዝም ብዬ እጠብቃለሁኝ።"
(ትንቢተ ዕንባቆም ምዕራፍ ፫ ቁጥር ፲፮።)
 
 May be an image of text
 
 
መነሻዬ ከዋዜማ ራዲዮ አቶ ዳንኤል በቀለ
ሼር ያደረጉት ቁምነገር ነው።
 
የፈለገ ነገር ይደርደር፤
የፈለገ ነገር ይቀመር፤
የፈለገ ነገር ይሽሞንሞን፤
የፈለገ ነገር ግጥግጥ ላይ ይሁን የአዲስ አበባ ሁነት እንዲህ በጎሼ፤ በአጎረፈ፤ በአጎፈረ ሁኔታ እልል ተብሎ
አሸኛኜቱ ሊጸድቅ አይገባም። አንበሳው አብዲሳ አጋ፤ አርበኛ አብርኃም ደቦጭ፤ አርበኛ ሞገስ አስጎደም፤ አርበኛ ዘርዓይ ደረስ፤
ሰማዕቱ ብጹውወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ
"ኃይለማርያም ማሞ የጦሩ ገበሬ፤
ፈረሱን እንደ ሰው አስታጠቀው ሱሪ"
እንዲህ በለብ ለብ፤ በግብር ይውጣ ሁነቱ ስክነት አንሶት ብይን ሊሰጥበት አይገባም። 
 
በባዶ እግር ቤቱን ትዳሩን ትቶ፤ ሞፈር ተፈቶ የፈሰሰው ደም እና አጥንት፤ ሰማዕትነት
አጥንት ወጥቶ ሊጠቀጠቅ አይገባም።
 
ይቺ አገር የኩባ፤ የራሽያ፤ የየመን፤ የአርመኖች መንፈስ የተገበረላት የዘጠኙ ቅዱሳን
የመንፈስ ማረፊያ፤ የነብዬ መሐመድ የነብይነት ልክ የተገለጠባት ጠይም ዕንቁ ናት።
 
በአንድ ዞግ ባህል እና ትውፊት፤ ፍላጎት እና ግብ ልትመራ አይገባም። ህብራዊ -
ሥናዊ፤ ቅባዕዊ ጸጋዋ ይፈገፈጋልና።
 
አያያዙ ውስጣችን የሚያቀራርብ ሳይሆን ህመምተኛ ያደርጋል። ውስጤ የምንለው
እኛነትም ይሸበሸባል፤ ይኮፋተራል ይሰደዳልም። ነገረ አዲስ አበባ በሚመለከት
በዓዋጅ እርምጃ ቢወሰድ አይገድም። በዚህ መልክ ግን የተገባ አይደለም።
 
ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ እንደነገሩን "መደመር ከገዳ የመነጬ ነው" ብለዋል። እኔ በጥዋቱ ሃሳቡን ከ፮ ዓመት በፊት ሞግቸው ነበር። ለምን? ኢትዮጵያ በገዳ ሥርዓት የምታገኜው ጥቅም እና ጉዳት፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ድምጽ ሊሰጥበት የሚገባ ጉዳይ እንጂ #ሊጫንበት በፍጹም ስለማይገባ። የገዳ ሥርዓት ኢትዮጵያኒዝምን እንዲመራ #ሪፈረንድም ሊዘጋጅለት ይገባ። ህዝብ ከፈቀደ ስደተኛ ኢትዮጵውያን መቀበል የግድ ይሆናል። ምክክር ኮሚሽኑ አገርን በዚህ መልክ የመዳፈር መንፈስ ሊመራ አይገባም።
 
ኢትዮጵውያንን በሙሉ ተስፋቸውን መቀማት፤ ምርኮኛ ማድረግ፤ እንደ ኩርድሾች ብትን አፈር ለማኞች ለማድረግ የውሳኔ ሃሳብ በሚል ሰላቢ ቃል ማናጋት አይገባም። ሙሶሎኒስ ከዚህ በላይ ምን አደረገ? የአቡነ ጴጥሮስ ሰማዕትነትስ አድራሻው የት ይሆን? ምን ሁን፤ ምን አድርግሥ ይሆን የቀደምት የኢትዮጵያ አርበኞች። የፓን አፍሪካኒዝም ቅኔወች???
 
ኢትዮጵያ ስታሊንዝም፤ ማዖኢዝም፤ ሌሊኒዝም፤ ማርክሲዝም፤ አልባኒዝም ሲፈትኗት ባጅተው አሁንድ ደግሞ በገዳ ሥርዓት ጫና መንፈሷ መሰቃዬት የለበትም። አልነበረበትም። ያን ጊዜ ስሞግት ከ፮ ዓመት በፊት አልገባኝ ያሉ ጉዳዮችን ስመረምር ነበር ኢትዮጵያ በገዳዊ ሥርዓት ውስጥ መሆኗን የገባኝ።
 
በኢትዮጵያ ያሉ ተቋማት ሁሉ አዛዥ ናዛዣቸው የገዳ ሥርዓት ነው። "የአገራዊ" ምክክር ኮሚሽኑም ከዚህ ሊያመልጥ ፈጽሞ አይችልም። ሥርዓቱ ከኢትዮጵያዊነት ጋር ተስማምቶ - ሳይሆን፤ ተራርቆ የቆዬ ሥርዓት ነው። ስለዚህ ዘመኑን አንብቦ፤ ከቆዩ የኢትዮጵያኒዝም ይትብኃል ጋር ተቀራርቦ ይሁን ተዋውጦ የመቀጥ አቅም የለውም። አገራዊ የሚለው ሥያሜም ለኮሚሽኑ ባዕድ ይሆናል። የባህር በር እና ወደብ ህወሃት አሳጣን፤ የምክክሩ ኮሚሽን እናታችን፤ አናታችን አጽናኛችን ሊያሳጣን ነው።
 
የገዳ ሥርዓት ከኢትዮጵያኒዝም በላይ እንጂ በአቻ ሊሆን የሚፈቅድ አይደለም የታሪክ ሙሁራን እንደሚገልጹት። ጠቅላይ ሚ/ር አብይም "ኦሮሞ ነፃ ወጥቷል (መንፈሳቸውን፤ የአካል እንቅስቃሴያቸውን እዩት፤ ዘመናቸው በውስጥ ጉዳት ውስጥ እንደነበር ያመሳጥራል)፤ "ኦሮሞ ከኢትዮጵያ በላይ ነው።" ሲሉ ያጠየቁት ኢትዮጵያኒዝም በገዳ ሥርዓት መተካቱን ነው የገለጹት። የምክክር ኮሚሽኑ የፈለገው ዓይነት ጣፋጭ ነገር ለመወስን ቢያስብም የተመሠረተበት የገዳ ሥርዓት ፍልስፍና ይጫነዋል።
 
የታሪክ ተመራማሪወች የውጮቹ እንደፃፋት "ገዳ መስፋፋት፤ ማስገደድ፤ ማግለል" ባህሪው እንደሆን ጽፈውታል። ይህ በኢትዮጵያ ድጋሚ ዕድል አግኝቶ ርዕሰ መዲናን እስከ መቀማት ያደርሳል ተብሎ አልታሰበም ነበር። የገዳ ባህሬ ይህ ስለሆነ ነገ ሌሎችም ሂደቶች አጠንካሮ እንደሚቀጥል መጠበቅ ከድንጋጤ ይፈውሳል። ብዙ ሰው ደንግጧል። 
 
"አይዟችሁ የሚፈራው፤ ማጽናናት የሚሸሸው" ከገዳ ዶክትሪን ጋር ያለው ተፈጥሯዊ አመክኒዮ አስገዳጅነት የሚመነጭ ነው። የዛሬ ፭ ዓመት ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ገዳን አዘምነው እየፈጸሙ ነው ብዬ ጽፌ ነበር። ልብ ያለው የለም። "በአገራዊ " ሥም የገዳ ሥርዓትን በይፋ በአደባባይ አሽሞንሙኖ እንዲጸድቅ ለማስደረግ ነበር የኮሚሽኑ አመሠራረት ላይ እንደዛ የነበረው። ማንኛውም ተቋም የአመሰራረት ችግር ካለበት ሁከትን ጸንሶ፤ አለመረጋጋትን እንዳስረገዘ ሳያገላግል አሸክሞ እብስ ይላል።
 
መቼም ጥቅሙን የሚፃረር ተጠቃሚ አለም አስተናግዳ አታውቅም። በኮሚሽኑ አወቃቀር ላይ የነበረው ሁነት አብዛህኛው እኛነትን ሳይሆን #እኔነትን የሰነቀ ስለነበር እዚህ ተደረሰ። ኢትዮጵያን ያህል አገር፤ ኢትዮጵንይዝም አንሶ፤ ተሳዶም በገዳ ሥርዓት መሪነት ርዕሰ መዲናውን አስረክባ እንብርት አልባ #ሉዓላዊ፤ ምንትርሶ ቅብጥርሶ ያከትምላታል።
 
የምርጫ ጊዜ ተርሙ የገደ የሰለጠነ ነው። በአወንታዊ አየዋለሁኝ። ግን አወቃቀሩ ሰንሰለቱ ከዛው በዛው ነው። ወደ ሌላ እንዲሸጋገር አይፈቅድም። ፰ ዓመት ሁለት የምርጫ ተርም ነው። ይህ በጎ ነገር ነው። ጠቅላይ ሚር አብይ ፰ ዓመታቸውን አጠናቀዋል። ለተተኪያቸው ያስተላልፋሉ ወይ ቢባል ይህን ይሁንታ አይሰጡትም ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ። የገዳ ህግ ግን ያስገድዳል። ሌላው የገዳ መንፈስን እንደፈቀዱ ሁሉ፤ ይህን በራሳቸው ላይ ከፈጸሙ የገዳ አባትነቱን ሊወስዱ ይችላሉ። ከሳቸው የገዳ ዶክተሪንን አሸሽተው ለ130 ሚሊዮን ህዝብ ከጫኑት ግን አብነትነት ይተናል። 
 
ሌላ የማህበረ ገዳ ቤተኛ ዕድሉን አግኝቶ ቢሆን ፰ ዓመት ቀርቶ ፰ ወር አይችልም ነበር። ይጨነግፍ ነበር። ለምን ጠቅላይ ሚ/ር አብይ አህመድ በሄዱበት #የመንትዮሽ ጉዞ መሄድ ስለሚሳነው።
 
ጠቅላይ ሚር አብይ የኢትዮጵያኒዝም መንፈስ ሰረገላቸው አድርገው በውስጣቸው ነግሶ የቆየውን የገዳ ሥርዓት አሰረጹት። የሆነው ይሆናል። እሳቸውን ደግፈው ጸንተው የቆሙትን የኢትዮጵያዊነት አቀንቃኞች ውስጣቸውን መዳፋቸው ላይ አስቀምጠው የልቦናቸውን ያደርሱ ዘንድ ሙሉ አቅም እየተመገቡ፤ ጎሽም እየተባሉ ዛሬ /// ዛሬን በገዳ ዶክተሪን በልጽጎ አገኜ። 
 
#ዛሬ ዛሬን ያገኜበት ሁነት
 
1) ለኢትዮጵያኒዝም መራራ ስንብት፤
2) ለፓን አፍሪካኒዝም መራራ ስንብት፤
3) ለዓለም የዲፕሎማሲ ግንኙነት መራራ ስንብት ይሁን ጣፋጭ ጊዜ ሂደት የሚናገረው ይሆናል። ኢትዮጵያኒዝም ሲደምቅ በሰጨኝ ዕልፍኝ ታዳራሽ የሚለውም ለዚህ ነው። 
 
አንድም የኦሮሞ ሊቅ በጠቅላይ ሚር አብይ ልክ ቁጭቱን፤ እልሁን በድርጊት ለማግኜት ይህን የመሰለ ዕድል ማግኜት አይችልም። በሰሞናቱ ቃለ ምልልሳቸው ላይ ውስጣቸውን ያሳዩት ዶክተር አብይ አህመድ ድል ርካብ ላይ መሆናቸውን በማረጋገጥም ነበር። በሌላ በኩል እኔ እስከዚህ አድርሼኃለሁ ቀሪውን ጉዞ በአለ በሌለ ኃይልህ "ተከተለኝ" ያሉት የኦሮሞ ህዝብን ነው።
 
"ኮንቢንስ እና ኮንፊውዝድ አድርገን ባህርዳር ተሻግረን የልባችን አደረስን" ሲሉ ኢትዮጵያዊው ጉግል አቶ ሽመልስ አብዲሳ የለት ጉዳይ ተደርጎ ነበር የታለፈው። አቅምን በገፍ፤ ያለ ደንበር የቀለቡ ወገኖቻችን ዛሬ አንዳንዶቹ ተቃዋሚያቸው ሆነዋል። "ቀድሞ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ አሁን ምን ያደርጋል፤ ወጪት ጥዶ ማልቀስ" ይተባህልን ከመሼ አድምጠው፤ እራሳቸውን ቢያጽናኑ ጥሩ ይመስለኛል። "ተከፋን፤ ተጫኑን፤ አገለሉን፤ ጨቆኑን" የሚሉ ሁሉ አቅሙን ማኔጅ ያደረገበትን ዘዴ ይመርምር። 
 
ባሌ ላይ ጠቅላይ ሚር አብይ? "ይጠይቁናል ብልጽግና የማን ነው ብለው፤ እኛም እንመልሳለን፤ ብልጽግና #የኦሮሞ ነው ብለን። ዓለም እያወቀን ነው። እኛ ዝሆን ነን፤ እንቀረጥፋለን" ወዘተ ሲሉ ተረብ አልነበረም። ጠቅላይ ሚር አብይ "ክዶናል" የሚሉ ሊቃናት አሉ። 
 
በየጊዜው እሳቸው ይሁኑ አቶ ሽመልስ፤ አልፎ አልፎ ከንቲባ ወሮ አዳነች አበቤ እኮ ጠፈፍ አድርገው ይገልፃሉ። ሰሚ፤ አድማጭ ጠፋ እንጂ የሸሸጉት አንድም ፍላጎት የለም። ስለሆነም ተወቃሽ አይደሉም።
 
አዲስ አበባን ከሁለት ከፍለው ሸገር ሲቲ ሲያደርጉ፤ ደንበር ሲያካልሉ፤ አዲስ አበባ በትምህርት ቤት ላይ፤ በዙሪያው አሉታዊ ዴሞግራፊ ሲፈጽሙ እኮ በምሽት አይደለም። በአደባባይ በጠራራ ጸሐይ ነው። 
 
ምደባ ላይ፤ መዋቅር ላይ፤ የአሰራር ሂደት ላይ ማዕከሉ በሚያምኑበት መርህ ላይ ስለመሆኑ ይታያል። ይደመጣል። ከምርጫ አንድ ዓመት በፊት ቀውስ ተፋፍሞ አመድ ሲሆን። በዝምታ፤ በጸጥታ ምርጫ ይቀጥላል። ሰላማዊ ምርጫ ተከወነ ብለው ተቃዋሚወቻቸው ሁሉ ይመሰክራሉ። ብልፄው በሙሉ ድምጽ ይመረጣል። አዲስ አበባ ላይ። እና ያሻቸውን በአሻቸው ጊዜ መፈጸማቸው ጥፋቱ የማን ነው? በተፈቀደላቸው የሥልጣን ዘመን ትልማቸው ላይ ይተጋሉ። ያሳካሉ። 
 
በአንድ የሬቻ ዋዜማ አቶ ሽመልስ አብዲሳ ያደረጉት በኦሮምኛ ንግግር። "የተሰጠን ፭ ዓመት ነው። ፭ ዓመቱን እንደ ፳፭ (25)ዓመት ወስደን እንሰራበታለን አሉ። ዕድላቸውን አላፈሰሱም። ይተጋሉ። ያቅዳሉ ይፈጽማሉ። ኦሮምያ ላይ "ጋሜ" በሚባል ሚዲያ ልጆቻችን ገዳን እያስተማርን ነው ሁሉ ብለው መግለጫ ሰጥተዋል። የገዳ ሥርዓት በቀጣዩ ትውልድ በዕውቀት ዳብሮ ይቀጥል ዘንድ ተግተዋል።
 
የደብረዘይት አየር መንገድ፤ የአርሲ የንፋስ ኃይል ማመንጫ፤ ዘመናዊ የመንደር ምስረታ፤ ወደብ፤ የባህር በር ፍላጎት፤ የጫካ፤ የኮሪደር ፕሮጀክት ሌሎችም ሜጋ ፕሮጀክቶች ላይ ቀን ከሌት እየተጉ ነው። #በጣምራ ፍላጎት። በኢትዮጵያ አንጡራ ሃብት ወጥ ኦሮማይዜሽን በመንታ መንገድ አጣጥተው እየፈጸሙ ነው። የአባይ ግድብ የመዋቅር ለውጡ፤ ከቤንሻንጉል ጉምዝ ጋር ያላቸው የውህድነት መንፈስ በቀጣይ የሚታይ የወርቅ እንክብል ነው። አልባሌ፤ ሰነፍ አይደሉም ዶር አብይ። የሚበልጣቸው ቀርቶ የሚመጥናቸው እስኪ አቅርቡ።
 
እነ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በማይመለከታቸው የኢትዮጵያዊነትን በርደን ይዘው ወደ አገር የገቡትን ፖለቲከኞች የካባ ሽልማት፤ የመድረክ ሥጦታ ላይ ሲረባረቡ ብልሁ እና ጭምቱ ዶር ለማ መገርሳ የተበተኑ የኦነግ አንደበቶችን ያሰባስቡ ነበር። አቅም እንዲሆኗቸው። እነሱ እንዳይናገሩት የኦሮማራ "ኮንፊዩዝድ እና ኮንቢንስ" ትልማቸው እክል ሊገጥመው ነው። ስለዚህ አንደበቶቻቸውን አሰባሰቡ። ሊናገሩ የሚፈልጉትን እነርሱ እንዲናገሩላቸው ያስደርጋሉ። ከዚህ በላይ ጥልቅ ዕሳቤ የለም። ብልህ መንገድ።
 
ቲም ገዱ ከፊሉ አፈር፤ ከፊሉ ስደት ሆነ። ቅንጣት ለአማራ ህዝብ ኦሮማራን አትራፊ፤ ሞጋች፤ ኃይል አመጣጣኝ ሳይሆን የምርኮኝነት ሰልፋን አሳምሮ እንደ አውሮፓ ክረምት - ገብ ቅጠል ረገፋ።
 
ይህም ሆኖ ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ "አቅመ ቢስ እየተባሉ፤ ሲቃለሉ፤ ሲጣጣሉ" አደምጣለሁኝ። እሳቸውም ፬ኪሎ ሳይሆን መስካቸው ላይ ሆነው በተቃዋሚያቸው ተረብ ውሽክ ይላሉ። ስለ ገዳ ዳግሚያ ትንሳኤ ተግተው እየሠሩ ነው። አቅደው ያልፈጸሙት፤ ወይ የሳቸው ፕሮጀክት ሆኖ ክትትል ያነሰው አልሰማሁም እስካሁን ድረስ።
 
"በረንቱም፤ ባህረ ነጋሽም" የትልማቸው አቅጣጫ መሆኑንም ጠቁመዋል። ኦሮማይዜሽን የአፍሪካን ኢኮኖሚ፤ ባህል፤ ትውፊት ፓን አፍሪካኒዝምን እንዲወርስ ሆቴል ጉብኝት ላይ የሚሰጡ ማስተዋወቂያወች መንፈሱን አጎልምሰውታል። ጉዞው ወደዛ ስለሆነ። "አገራዊ" ከሚሽኑ ከዚህ ያለፈ ሚና የለውም። አይኖረውም። የገዳዊ ሥርዓት ተፈጥሮ ስለማይፈቅድ።
 
ለዚህ ያደረሳቸውን አቅም ደግሞ ያሰናብቱ እና ሸልመው ይሁን ወቅሰው ወደ ጡሮታ ይልኩና፤ በአዲስ አቅም በሙሉ ኮንፊደንስ ቀጣዩን የገዳ ካቢኔ ያደራጃሉ። ይመራሉም። 
 
ይህን የሚመክት አቅም ሞገድ ላይ ነው ያለው። ያም ዛሬንም ሆነ ነገንም ይታደጋልን? በዚህ ውስጥ ተስፋ እኔ ላደርግ አልችልም። የማውቃቸው የፖለቲካ ኢሊቶች ናቸውና። ጠንካራ ቢሆኑ እንኳን ያን የመሰለ ጽድት ያለ፤ ቋሚ ደጋፊ የነበረው ዕድል "ለኢትዮጵያዊ ሱሴ፤ ለጣና ኬኛ" አይፈቀድም ነበር። በሌላ በኩል ኢትዮጵያኒዝም በህወሃት ካፒቴንነት ትንሳኤው ይሆናል ብዬም አላስብም።
 
#እና? እናማ እና ይጠበቃል።
 
ለዛሬም ለነገም ሠሪው አማኑኤል ነውና። ለኢትዮጵያም ያላት አምላካችን፤ አላኃችን ብቻ ነውና። ሁልጊዜ ኢትዮጵያ ትከዳለች። ሌላም ቢመጣ ማህበረ ኦነግ ይከቡ እና #ያዝሉታል - ያንዛዙታልም። ያጓጉሉታልም። እነሱ ታዝለው ይሁን አሽኮኮ ተደርገውም የኢትዮጵያ ብሩህ ነገ አይጠበቅም። ደርግም ላይ ነበሩ። ህወሃት ጋርም ነበሩ። ዕድላቸውን አያፈሱም። ድሮ ኤርትራውያን ሊቃናቱ እንደዛ ነበሩ ይባላል።
 
ከተቃዋሚውም፤ ከተፎካካሪውም፤ ከተቀላቹም፤ ከተግባቢውም ውስጥ ማህበረ ኦነግ ሳይንቁ፤ ሳያቃልሉ በትጋት ይሳተፋሉ። የአማራ ሊቃናት እራሳቸውን ያገላሉ፤ ያርቃሉ፤ ወይንም እንደ ቲም ገዱ ፈሰውም /// አፍስሰውም ይሰናበታሉ።
ርዕሰ መዲና አልባ አገር? ይመረምራል። ይፈታትሻል። የላይኛው መልስ ይስጥበት።
 
እኔ ረጅም ጊዜ ሆነኝ ለኢትዮጵያ ተፈጥሮ የፖለቲካ ድርጅት ከኦርጋኒክ ተፈጥሮ ጋር አይመጣጠንም። ስለዚህ በተፈጥሯዊነት፤ በሰዋዊነት የኢትዮጵያኒዝም መሪነትን ኢትዮጵያ #በቲም ትመራ ዘንድ ነው የሚናፍቀኝ። ጭካኔ እና ጨካኝ መንፈስ ለኢትዮጵያ ኦርጋኒክ ተፈጥሮ ልኩ ነው ብዬ አላምንም። በነገራችን ላይ ኢትዮጵያዊነት የከበደው ለሁላችንም ነው። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ይሁን ገዳይዚም ጭካኔን ይደፍራል። እኛነትን ያሳጣን ይህ መንገድ ነው። 
 
ማህበረ ቅንነት እንዴት አድራችሁ አረፈዳችሁ። እኔ ደህና ነኝ።
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
20/08/026.
 
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
 
ከአቶ ዳንኤል በቀለ ፔጅ ያገኜሁት ነው። እርሳቸው ደግሞ ከዋዜማ።
 
በጸጥታ ጉዳይ የክልል መንግስታት ጥሪ ሳያቀርቡ የፌደራል መንግስት ጣልቃ የሚገባበት አጀንዳ ቀርቧል
ዋዜማራዲዮ
August 20, 2026
 
ዋዜማ- "በስምንት አጀንዳዎች ዙሪያ እየመከረ የሚገኘው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በስምንቱ የሥራ ቡድኖች የቀረቡ 476 ምክረ ሀሳቦችን ለማጽደቅ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሷል። በ96 ንዑስ አጀንዳዎችና በ225 መሪ ጥያቄዎች መሠረት ምክክር ሲያደርጉ የቆዩ ተመካካሪዎች ያቀረቧቸው ምክረ ሀሳቦች በልዩነት የተያዙና አማራጭ የቀረበላቸው ነጥቦችን ያቀፉ መሆናቸውን ምንጮች ነግረውናል።
በሀገር ግንባታ አጀንዳ ዙሪያ የቀረቡ ምክረ ሀሳቦች በሀገር ግንባታ አጀንዳ ዙሪያ በተመካከረው የሥራ ቡድን ከቀረቡ ምክረ ሀሳቦች መካከል፤
 
ሀገር የብሔረሰቦችና የዜጎች ናት፣ በሕገ መንግስቱ መግቢያ ላይ “እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች” የሚለው አገላለጽ “እኛ የሕብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያ ሕዝብ” በሚል እንዲተካ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ ምሁራንን ያሳተፈ ገልለተኛ ኮሚሽን ተቋቁሞ እንዲጻፍ፣ ታሪክ ከፖለቲካ መጠቀሚያነት እንዲወጣ፣ የጭቆና ታሪክን የሚያንጸባርቁ ነጠላና ከፋፋይ ትርክቶችን በማረም የወል ትርክት ይዘርጋ፣
 
ቋንቋን መሠረት ያደረገ ጉዳትና ጥቅም እንዳይኖር ማድረግ፣ ብሔራዊ ቋንቋን ተግባራዊ ለማድረግ ተጨማሪ ጥናትና ምርምር እንዲካሄድ፣ ግዕዝ ቋንቋን የጥናትና ምርምር ቋንቋ ማድረግ፣ የፌደራል መንግስት አምስት የሥራ ቋንቋዎች (አማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ፣ አፋርኛ) እንዲኖሩት ማድረግና ሌሎች ቋንቋዎች በጥናት ላይ ተመስርተው የሥራ ቋንቋ መሆን የሚችሉበትን አሠራር መዘርጋት፣ ሁሉም ክልሎች ከሚጠቀሙበት የሥራ ቋንቋ በተጨማሪ ከፌደራል የሥራ ቋንቋዎች መካከል አንዱን በሥራ ቋንቋነት እንዲጠቀሙ ማድረግ፣ 
 
ብሔራዊ በዓላትን ሊውስን የሚችል ዝርዝር ሕግ እንዲዘጋጅ፣ በዩኔስኮ የተመዘገቡና ወደፊትም የሚመዘገቡ በዓላት ሕዝባዊ በዓላት ሆነው እንዲከበሩ ማድረግ፣ በክልሎች መዝሙሮች ላይ ያሉ አሉታዊ ይዘቶች እንዲስተካከሉ ማድረግ የሚሉት እንደሚገኙበት ሰምተናል። 
 
የሰንደቅ ዓላማ ጉዳይን በሚመለከት ሁለት አማራጭ ምክር ሀሳቦች መቅረባቸውን የነገሩን ምንጮች፤ ሁለቱም ምክረ ሀሳቦች በሥራ ላይ ያለው ሰንደቅ ዓላማ የመደብ ቀለማት ባሉበት እንዲቀጥሉ የሚያደርጉን መሆናቸውን ገልጠዋል። 
 
የመጀመሪያ አማራጭ በሰንደቅ ዓላማው ላይ ያለው አርማ ባለበት እንዲቀጥል የሚጠይቅ ሲሆን፤ ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ አርማው ሕብረ ብሔራዊነትን በሚያሳይ መልኩ እንደ አዲስ እንዲዘጋጅ የሚጠይቅ መሆኑን ተረድተናል።
 
በመንግስት አደረጃጀት አጀንዳ ዙሪያ የቀረቡ ምክረ ሀሳቦች
በመንግስት አደረጃጀትና ቅርጽ ዙሪያ የተመካከረው የሥራ ቡድን ካቀረባቸው ምክረ ሀሳቦች መካከል፤
ፌደራላዊ የመንግስት ሥርዓት እንዲቀጥል፣ በሥራ ላይ ያለው የፌደራሊዝም ሥርዓት ክፍተቶቹ ተጠንተውና ግብዓት ተጨምሮበት ሕብረ ብሔራዊ ፌደራሊዝም ተግባራዊ እንዲደረግ፣ ራሳቸውን በብሔር ማንነት መግለጽ የማይፈልጉ ዜጎች እንደ ኢትዮጵያዊ ብቻ እንዲታዩ ማድረግ፣ የተለያየ የብሔር ማንነት ካላቸው ወላጆች የተወለዱ ዜጎችን የማንነት ጉዳይ የሚመለከት ሕግ ማዘጋጀት፣ ወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮችን የሚመለከት “ሕብረ ብሔራዊ የአንድነት ኮሚሽን” ማቋቋም፣
 
በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 39 ንዑስ አንቀጽ 1 “ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ ፣ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከመገንጠል ያለው መብቱ በማናቸውም መልኩ ያለ ገደብ የተጠበቀ ነው” የሚለው ድንጋጌ ውስጥ “እስከመገንጠል” የሚለውን ቃል ማስወጣት፣
 
“ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች” የሚለውን አገላለጽ “ብሔረሰብ“ በሚል መተካት፣ ክልሎች መደበኛ ፖሊስ ብቻ እንዲኖራቸው ማድረግ (የልዩ ኃይል አደረጃጀትን ሙሉ በሙሉ ማፍረስ)፣ በክልሎች ግጭቶች በሚከሰቱበትና አስገዳጅ በሆነበት ጊዜ ክልሉ ጥሪ ባያቀርብም የፌደራል መንግስት ጣልቃ መግባት የሚችልበትን አሠራር መዘርጋት፣
 
የሕዝብ ቆጠራ በማካሄድ አዲስ የድጎማ በጀት ቀመር ተግባራዊ ማድረግ፣ የአካባቢ አስተዳደሮች በአካባቢው ያሉ ማንነቶች የሚወከሉበት እንዲሆኑ ማድረግ፣ የአካባቢ ምርጫ እንዲካሄድ ማድረግ፣ ንቁ የአስተዳደር ወሰን ጥያቄዎች መፍትሄ እስኪያገኙ ድረስ የፌደራል መንግስት ጸጥታ የማስከበር ኃላፊነትን እንዲወስድና በሌሎች ጉዳዮች የፌደራል መንግስትና ክልሎች በትብብር እንዲሠሩ ማድረግ፣
 
የኢትዮጵያ ሕጋዊና ታሪካዊ ደንበር ቀይ ባሕር መሆኑን ማረጋገጥ፣ ሕግ የመተርጎም ስልጣን ያለው የሕገ መንግስት ፍርድ ቤት ማቋቋም፣ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 105 ከሕገ መንግስት ማሻሻያ ጋር ተያይዞ “ሁሉም የክልል ምክር ቤቶች የቀረበውን ማሻሻያ በድምጽ ብልጫ ሲያጸድቁት” የሚለው ድንጋጌ “ሶስት አራተኛ ክልሎች በድምጽ ብልጫ ሲያጸድቁት” በሚል እንዲተካ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በአዋጅ ዕውቅና እንዲሰጠው፣ አዲስ የሕዝብ ቆጠራን መሠረት ያደረገ የምርጫ ክልል አደረጃጀት ተግባራዊ እንዲደረግ የሚሉት እንደሚገኙበት ዋዜማ ሰምታለች።
 
ከመንግስት አስተዳደር ሥርዓት ጋር በተያያዘ ሁለት አማራጭ ምክረ ሀሳቦች መቅረባቸውን የገለጡልን ምንጮች፤ በሥራ ቡድኑ ውስጥ ከሚገኙ ተመካካሪዎች መካከል “አብዛኛው” ፓርላመንታዊ ሥርዓት ቀጥሎ፣ መሪው ከፓርላማ የሚመረጥ ፕሬዝዳንት እንዲሆን የሚለውን አማራጭ መደገፋቸውን፤ “የተወሰኑ” ተመካካሪዎች ደግሞ ፕሬዝዳንታዊ ሥርዓት ተግባራዊ እንዲደረግና መሪው በሕዝብ የሚመረጥ ፕሬዝዳንት እንዲሆን ምክረ ሀሳብ ማቅረባቸውን ነግረውናል። 
 
ይሁንና “አብዛኛው” እና “የተወሰኑ” በሚል የተቀመጡ አገላለጾች፤ የድጋፍ መጠናቸው በቆጠራ ሳይረጋገጥ የተሰጡ ናቸው የሚል ቅሬታ መቅረቡን ሰምተናል።
 
የፌደራልና የክልል መንግስታት የሥልጣን ጊዜ ስድስት ዓመት እንዲሆን በጠየቀው ምክረ ሀሳብ፤ አንድ መሪ ከሁለት የስልጣን ጊዜያት የበለጠ እንዳያገለግል ገደብ መቀመጡን አውቀናል። የምርጫ ሥርዓትን በሚመለከት ደግሞ “ቅይጥ ትይዩ” የምርጫ ሥርዓት ተግባራዊ እንዲደረግ ምክረ ሀሳብ መቅረቡን ምንጮች ገልጠዋል። ሥርዓቱ በዝርዝር በሚወጣ ሕግ መሰረት ተግባራዊ እንዲደረግ የጠየቀው ምክረ ሀሳቡ፣ መንግስት መመስረት የሚያስችለው የወንበር መጠን በሚዘጋጀው ሕግ እንዲደነገግ አቅጣጫ አስቀምጧል።
 
በሃይማኖት ጉዳይ የቀረቡ ምክረ ሀሳቦች
በሃይማኖት ጉዳዮች ዙሪያ የተመካከረው የሥራ ቡድን ካቀረባቸው ምክረ ሀሳቦች መካከል፤
ከሃይማኖት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የሚመለከት “የሃይማኖት ኮሚሽን” እንዲቋቋም፣ የጎዳና ላይ ሃይማኖታዊ ተግባራት ሚዛናዊ በሆነ መንገድ እንዲከናወኑ ማድረግ የሚያስችል መመሪያ እንዲዘጋጅ፣
 
ተቋማት አርብ ቀን ለጁምዓ ጸሎት ከ5 ሰዓት እስከ 8 ሰዓት ያለውን ጊዜ የዕረፍት ጊዜ እንዲያደርጉ፣ በዓለ ሀምሳ የዘመን መቁጠሪያ (ካላንደር) ላይ ዕውቅና ያለው የበዓል ቀን እንዲሆን፣ የአዳዲስ ሃይማኖቶች ምዝገባ ጥብቅ እንዲሆን፣
የአደንዛዥ ዕጽ እርሻን በሌሎች ምርቶች መተካት የሚያስችል ሀገራዊ ንቅናቄ እንዲካሄድ፣
 
ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት ማህበራዊ ሚዲያ እንዳይጠቀሙ የሚያደርግ ገደብ እንዲጣል፣
ፍትሃዊና ቦታ ቆጣቢ የሃይማኖት ተቋማት ቦታ አሰጣጥን ተግባራዊ ማድረግ፣ ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ሕገ ወጥ የሠውና የመሳሪያ ዝውውር እንዳይካሄድ ማድረግ፣
 
የሃይማኖት አባቶች በቂ ክብርና ቅድሚያ እንዲሰጣቸው ማድረግ፣
የሃይማኖት ተቋማት ኦዲት ተደርገው የፋይናንስ ግልጸኝነት እንዲፈጠር ማድረግ የሚሉት እንደሚገኙበት ምንጮች ነግረውናል።
የምክረ ሀሳቦቹ ቀጣይ ሂደት
 
120ዎቹ የጋራ ማረጋገጫ ቡድን አባላት ያዘጋጁትና ከተመካካሪዎች በቀረቡ አስተያየቶች መሠረት ለመጨረሻ ጊዜ የተስተካከለ ምክረ ሀሳብ ነሐሴ 14 ቀን 2018 ዓ.ም ለምክክሩ ጠቅላላ ጉባኤ እንደሚቀርብ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አስታውቋል።
 
በጠቅላላ ጉባኤው የሚጸድቁ ምክረ ሀሳቦችን የሚረከበው ኮሚሽኑ፤ ምክረ ሀሳቦቹ በተግባር ላይ ሊወሉ የሚችሉበትን ስልት የሚገልጽ ሰነድ በማዘጋጀት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለአስፈጻሚ አካሉ እና ለሚመለከታችው የመንግስት አካላት እንደሚያቀርብ የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ 1265/2014 ደንግጓል። 
 
ኮሚሽኑ ከሚረከባቸው ምክረ ሀሳቦች መካከል በተለያዩ ምክንያቶች ሳቢያ ወደ ቀጣዩ ሂደት የማያሳልፋቸው ምክረ ሀሳቦች ሊኖሩ እንደሚችሉ የዋዜማ ምንጮች ጠቁመዋል [ዋዜማ]"

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።