ጨረቃ ክንፍ አውጥታ ሰማይ ላይ ብትበር፤ ጸሐይ በሠረገላ ወደ ምድር በሚያስፈራ ግርማ ብትመጣ፤ የሰማይ ታምራት እና ገድላት በምድራችን ላይ ቢገለጥ፤ ህወኃት ኢትዮጵያን የመምራት #ዕድል ፈጽሞ አይኖረውም።

 

ጨረቃ ክንፍ አውጥታ ሰማይ ላይ ብትበር፤
ጸሐይ በሠረገላ ወደ ምድር በሚያስፈራ ግርማ ብትመጣ፤
የሰማይ ታምራት እና ገድላት በምድራችን ላይ ቢገለጥ፤
ህወኃት ኢትዮጵያን የመምራት #ዕድል ፈጽሞ አይኖረውም። 
 
"እናንተ ሰነፎች ልበ ቢሶች፤ ዓይን እያላችሁ የማታዩ፤
ጆሮም እያላችሁ የማትሰሙ፤ ህዝብ ሆይ! ይህን ስሙ።
በዕውን እኔን አትፈሩምን? ከፊቴስ አትደነግጡምን?"
(ትንቢተ ኤርምያስ ምዕራፍ ፭ ቁጥር ፳፩ - ፳፪)
 
#ምዕራፍ ፲፱።
 
ተዘርዝረው የማያልቁ የሰው ልጅ የጭካኔ ዓይነትን ተቀብሏል ህዝብ በህወሃት። ያ የግፍ፤ ያ የስቃይ፤ ያ መተንፈሻ ያልነበረበትን የጭካኔ ዘመን መላ የኢትዮጵያ ህዝብ በወረፋ ቢደርሰውም በስሜን ጎንደር የደረሰው፤ በአዛውንት #ተጋሩ ዕውነት መስካሪነት የተፈጸመው አሰቃቂ ሰቆቃ ዕንባን ሰማይ አዳመጠ። መለሰም። 
 
ህወሃት ፈቅዶ እራሱም ድምጽ ሰጥቶ ሁለት ድምጽ ብቻ አግኝቶ ሥልጣነ - መንበሩን ሲለቅ፤ ከዚህ በላይ ዲስፕሊን የለም በማለት ውሃ በቀጠነ ህወሃትን አጀንዳ ያደረጉ ሚዲያወች ይሁን ግለሰቦች ሲሞግቱት እኔ እንደ ቋሚ ሞጋችነቴ ጸጥ ብዬ ነበር እምመለከተው።
 
የህወሃት እና የብልፄ ጦርነት ዱብ - ዱብ ሲልም፤ #ተው ከማለት ውጪ አንዳችም ቃል ብዕሬ አውጥታ እንድትናገር አልፈቀድኩም። እንዲያውም "መጤ፤ ጸጉረ ልውጥ" በሚሉ አገላለፆች ቅሬታዬን ጽፌያለሁኝ። የተገባ አልነበረም። ይቅርታም በይፋ ሊጠየቅበትም ይገባል። ለይቅርታ ቅድመ ሁኔታም ቀጠሮም ስለማያስፈልገው። ሰው በአገሩ፤ በባዕቱ - "መጤ፤ ጸጉረ ልውጥ" ፈጽሞ ሊባል አይገባምና።
 
በጦርነቱም ወቅት ጉዳቱን ከዓለም ዓቀፍ ሚዲያወች ብቻ የማገኜውን የግራ ቀኙን ሰብአዊነትን የሚመለከቱ ጉዳዮችን ዘግቤያለሁኝ። ጦርነት ለየትኛውም የችግር ዓይነት መፍትሄ ነው ብዬም አላምንም። ምንጊዜም እኔ የጦርነት ደጋፊ ልሆን አልችልም። በጦርነት ቀጠና ነው ተወልጄ ያደግሁት። ለዚህም ነበር የደቡብ አፍሪካው ድርድርን ስኬታዊ ዜና በደስታ የተቀበልኩት።
 
#ህልመኝነት መብት ነው።
 
የህወሃት አፈጣጠር "አግባብ ነው" የሚሉ ድምፆችን ሰምቻለሁኝ። የአገር ንደት አግባብ ከሆነ የሃሳቡ ባለቤቶች ይጠየቁበት። የኢትዮጵያ የችግር መሥራች ህወሃት ብቻ ባይሆንም፤ ህወሃትም ሰፊ ድርሻ አለው። ለጥፋቱም ይሁን ለልማቱ። 
 
ስለሆነም የህወሃት ጥንስስ ምሥረታው ኢትዮጵያን ጠላት አድርጎ ስለነበር፤ እስከ ቻለው ድረስ፤ የራሱን አገር ኢትዮጵያን #ተበቅሏታል። አሁንም ይህንኑ ትክክል ያልሆነ ጎዳና ለማስቀጠል እየፎካከረ ነው -- ህውሃትሻ። 
 
ህውሃት እንዳሻው እንደ ነዶ በትኖ፤ ያሻውን በአሻው ደረጃ የበለታቸው የፖለቲካ ድርጅቶች ሳይቀሩ፤ እንፎካከራለን ብለው የተደራጁትን ጨምሮ ስለ ህውሃት ጥብቅናውን በነፃ እየፈጸሙት ነው። ይቀጥሉበት …… ዕውነት #ስለማይደነግጥ
 
የገረመኝ ደግሞ ህወሃት ሳይሆን አፍቅሮተ - ህወሃታውያን የደቡብ አፍሪካ ስምምነት ደፍረው ምንም እንዳልፈየደ ይናገራሉ፤ ይጽፋሉ። ሁሉም ይቅር ትግራይ ላይ የሚወለዱ ህፃናት ከስምምቱ በኋላ የጥይት ድምጽ ሰምተዋልን? ህወሃት እራሱ ሳይጠናቀቅ እንደምን ተረፈ? ማንስ አተረፈው? አገግሞ #እንዲነሳ ያደረገው ማን ሆነ እና? 
 
ዕውነትን ድጦ፤ ዕውነት ተቃርኖ፤ ዕውነትን ጨፈላልቆ፤ ዕውነትን አሳዶ፤ ዕውነት ፈትኖ የሚገኝ የፖለቲካ ትርፍ ይሁን ተቀባይነት የለም። አይኖርምም። ያ ጊዜ የአሜሪካን መንግሥት ጨምሮ ጊዜን፤ መንፈስን፤ መዋለ ንዋይን፤ የሙሁራን ዕውቀት በገፍ የተሰጠበት ታላቅ ታሪካዊ ቀን ነበር። የምህረት፤ የይቅርታ፤ የመቀራረብ ሁነቱ ከተጠበቀው በላይ ነበር። አፈሙዝ ጸጥ #እረጭ አለ።
 
መከረኞቹ የትግራይ እናቶች ወህ ያሉበት፤ ከእህል ውሃ ጋር የተገናኙበት፤ ውዳቸውን ቤተ - መቅደሳቸውን ያዩበት ጊዜም ነበር። እህል ሲከፋፈል ነጠላቸውን እንደ ገመድ አድርገው #ተጎንብሰው ተሸክመው ሲሄዱ ያሳዝኑ ነበር። ፎቷቸውም አለኝ። በየበራቸው ለማድረስ ስለምን እንዳልተቻለ አላውቅም። በወቅቱም ጽፌበታለሁኝ።
 
ይኽ የእፎይታ ጊዜ ዕንቁ ጊዜ ነበር። የሚቃለል፤ የሚጣጣል አልነበረም። ከዋናው ስምምነት በኋላ ሁለት ጊዜ በኬኒያ፤ አንድ ጊዜ በኢትዮጵያ ተገናኝተው ነበር - ሊቃናቱ የብልፄው እና የህወሃት። የሆነውን አናውቅም።
 
ለብልፄው የታክቲክም ይሁን የስትራቴጂ ወዳጁ አጋሩ #ህውሃትሻ እንጅ የአማራ ብልጽግና አይደለም። የህውሃት አፈጣጠር በራሱ ለዚህ ለማህበረ - ኦነግ፤ ለማህበረ - ነፃ አውጪ ግንባር እንጂ ለአማራ አይሆንም። አማራን #መቅኖ ለማሳጣት ነውና የተደራጀው።
 
#የህወሃት ምኞት ከ እስከ ከ።
 
ህወሃትሻ ጦርነት #አቅዶ በዛ ውስጥ መኖር ምኞቱ ነው። "ከድል¡" ---- መልስ #አንጋቻችን ጋር ጦርነት አይቀሬ ነው። የፊቱን ወላፈን እና ቋያ አንጋች ይገበር፤ የእሳት እራት ይሁን። እኛ ግን #የሥርዕወ ዓድዋን ዳግሚያ ትንሳኤን ካወጅን በኋላ፤ አራት ኪሎ አድራሻችን ቢና ጢናውን እናወጣዋለን ባዮች ናቸው። ህውሃትሻ ግልጽነቱ፤ ቀጥተኝነቱ ሊያስመሰግነው ይገባል። ልዩ ስጦታም ነው ወደ አመድነት ለመቀየር ለፈቀደ ትንፋሽ።
 
……… ግን ህወሃትሻ ያለመው ቤተ - መንግሥቱን ፕላን A አድርገን ብንወስድለት፤ ፕላን B ደግሞ አገርነት። ፕላን A ያቀረበው ለአሳቻ አማራጭነት ይመስለኛል። ምክንያቱም ትግራይ ወልቃይት፤ ጠገዴን ካገኜ ይገነጠላል የሚል ስጋት ላለባቸው አጋሮቹ #ተረጋጉ ነው። በሌላ በኩል ግን የወልቃይት ጠገዴ፤ ጠለምት፤ አዳርቃይ አዲረመጥን #አዝሎ ትጥቅ የማስፈታት ስልትም ሊሆን ይችላል። 
 
የሆነ ሆኖ ህወሃት ኢትዮጵያን መልሶ በማዕከላዊ መንግሥት ደረጃ መግዛት አይችልም። በፍጹም። ህወሃትሻ ሥልጣን የለቀቀው ሳያስበው ነው። ለሌላው ተቃዋሚ ፖለቲከኛም ሂደቱ #ዱብ ዕዳ፤ ፈጣን፣ ቀልጣፋ እና ድንገቴ ነበር። 
 
ህወሃትሻ በምልሰት ይህን ቢያስበው መልካም ነው። የሚቻል ነገር ማለሙ ይበጀዋልና። በአናርኪዝም የያዘውን ሥልጣን አስረክቦ በልኩ ለመጓዝ ቢያስብ መልካም ይመስለኛል። እልህ ሳይሆን ብልህነት ነው የሚያተርፈው። 
 
ምድር በገድላት፤ በታምራት ተሞልታ እቴጌ ጨረቃ ስድስት ክንፍ አውጥታ ሰማይ ላይ ብትበር፤ ልዕልት ጸሐይ ደግሞ በክብር፤ በሞገስ በማዕረግ በሰረገላ ወደ ምድር ብትመጣ ህወሃት መቸውንም ቢሆን የኢትዮጵያ መሪ ሊሆን አይችልም። ተምሶ የተቀበረ ጉዳይ ነው። ህወሃት ታምኖ የሚፈሰው ማናቸውም አቅም ከንቱ ልፋት ነው። 
 
"ከንቱ፤ የከንቱ ከንቱ፤ ሁሉም ነገር ከንቱ ነው።" 
 
ህወሃት መልሶ ስልጣን ለመያዝ "ዕድል አለው" የሚሉም አዳምጫለሁኝ። ለዛውም ከፖለቲካ ሳይንስ ሙሁር። ህወሃት ኢትዮጵያን መልሶ የመምራት ዕድሉ #ልሙጥ ነው። ፈጽሞ አይችልም። ዓለም ከህወሃት ጋር ባነበረበት ጊዜ እንኳን አልተቻለም። እንኳንስ አሁን ተቀባይነቱ በዓለም አደባባይ እንደ አውሮፓ የክረምት ቅጠል #ሞክ እርግፍግፍ ባለበት ወቅት።
 
#ነገረ ወልቃይት።
 
የተመድን የጸጥታ ምክር ቤቱን ከ10 ጊዜ በላይ ያነጋገረ ወሳኝ ግሎባል ጉዳይ የትኛውም አካል ከሚወስንበት ደረጃ በላይ ዕውቅና የተሰጠው ጉዳይ ነው። ነገረ ወልቃይት #ቅብዓም አለበት።
 
"ወላቃይት ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ" ንቅናቄ ሲነሳ አንድ ወዲ ተጋሩ ሊቅ፤ አንድነትን የተቀላቀሉ፤ የአማርኛ ቋንቋ ሊቅ፤ ፖለቲከኛ ንቅናቄው ጎርፍ አመጣሽ እንደ ሆነ እና ተኩረፍርፎ እንደሚቀር፤ የአማራ ሊቃናትም ሊቀበሉት እንደማይችሉ በድፍረት ፃፋ።
 
እኔ ማንነት በገብያ ህግ አይተዳደርም በሚል እርዕስ ዘለግ ያለ ሙግት በአክብሮት ፃፍኩኝ። ፈጽሞ ጥያቄውን ማንም ሊያቆመው እንደማችል አበክሬ ነበር የፃፍኩት። አሁንም አዲስ ገብ - ታጋዮች "ቁራጭ" ሲሉ ይጠሩታል። የህወሃት ተጠማኞች ስለሆኑ አይደንቅም።
 
ሌላው በወልቃይት ትንፋሽ የተገኜው በአማራ ክንድ ነው የሚል ቃለ ምልልስ አዳምጫለሁኝ። #ፕላስ ቀርቶታል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሁለመናውን የሰጠበት ክስተት ነው። ኢትዮጵያ ከኤርትራም ይሁን ከሱዳን የምትዋሰንበት ቁልፍ ስትራቴጅክ ቦታዋ ነው። ለዛውም #የነጭ ወርቅ ባለቤት። ሰሊጥም- ነጭ፤ ጥጥም ነጭ፤ ደበርም ነጭ፤ እጣኑም ነጭ፤ ሸንበቆውም ነጭ። የነጭ ዕንቁ #ወደብም ነው።
 
በዚህ ጉዳይ ላይም ውሳኔ የሰጠ የፖለቲካ ድርጅት አድምጫለሁኝ። "ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ" ስለሆነ ከቻላችሁ #ሞካክሩት¡ ብለናል። በየቦታው መጣድ አቅምን ያባክናል፤ ተቃርኖን ያሰፋል፤ ማህበራዊ መሠረትን ያራቁታል። ጉዳዩ ቆቆች ስላሉበት። ትንሽ ግን ካለልኩ የተሰፋ ጥብቆው ጥበት ውሽክ አድርጎኛል። ግፍም ነው። የማይካድራ አምላክ ዕንባው ይፍረደው። አሜን። የጨካኞች ብዛት ይገርመኛል።
 
በነገራችን ላይ ህወሃትን ከ100 ዓመት ህልሙ የነቀለው ይህው #ነገረ ወልቃይት ነው። ነጩ ቤተመንግሥት ምዕራብ ዕለታዊ ገለፃውን ያቆመው ምዕራብ ትግራይ የሚለውን ሳይጨምር ነበር። ሰኔ መግቢያ 2023 ላይ። ማስተዋል ቢኖር ይህን አገናዝቦ በልክ አቅዶ ድምጥን አጥፍቶ፤ ጥቃትን ዋጥ አድርጎ፤ የልክን ለማግኘት መጣር የሁሉንም ነገር አላስፈላጊ መስዋዕትነት ያስቀራል።
 
ይልቅ ሥምረት ፓርቲ፤ ሥምረት ለኢትዮጵያ ብሎ ለቀጣዩ ምርጫ ጠንክሮ ከሠራ፤ ብልፄውን የሚፎካከር ሊሆን ይችላል። ተመክሮ ያላቸው እየመሩት ስለሆነ። ባያሸንፍ እንኳን ከብልፄው ጋር ተቀናጅቶ ኢትዮጵያን የመምራት ዕድል ይኖረዋል። ህውሃትማ መውቲ የሆነው መጋቢት 18/2010 ዓም። ዳግም ተንሳዔውም ተቀብሯል። 
 
ብቅ ጥልቅ እያሉ የተረጋጋን መንፈስ ማመስ፤ ህዝብን መንፈሱን ማዋለል፤ የላዩን ከታች፤ የታቹን ከላይ እንደ ካርታ እየሾከሾኩ ማተራመስ፤ በተጨማሪም አሽሙር የሚያሰኛቸው ሁሉ #ደመር ይቀጣጠሩ እና እርማቸውን ያውጡ። ህወሃት በዊዝደም ነው የተነቀለው። ሲነቀል ደግሞ እንዳያቆጠቁጥም ሆኖ ነው። ለምን? የንጹኃንን ዕንባ ያዳመጠ አማኑኤል ታምራቱን ያሳያበት ስለሆነ።
 
#ክወና።
 
ከልጅም፤ ከቤተሰብም፤ ከሁነትም፤ ከክስተትም ጸጋ ያለው አመክንዮ አለ። የማይደፈር፤ የማይነካ። ነገረ ወልቃይትም እንዲሁ ነው። ወልቃይትን ለቀቅ አድርጉ እና ከ50ሺህ በላይ የተፈናቀለ የራያ ወገን ጥቃቱን የሚያወጣለት ክንድ ይፈልጋል። አትኩሮት አይነፈገው። ያም አካል፤ ህዝብ ነውና። የለበጣው ነገር ቅርፊት ስለሆነ ቢቀር ጥሩ ነው። 
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
 
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
31/07/026.
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
See less

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።