ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከአማራ ክልል የሀገራዊ ምክክር ተሳታፊዎች Freedom Forall

 

"ይህ ለታሪክ የሚቀመጥ ነው‼
ነሐሴ 11 ቀን፣ 2018 ዓ.ም.
ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን
ከአማራ ክልል የሀገራዊ ምክክር ተሳታፊዎች
ጉዳዩ፦ በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ የታዩ የአሠራር እና የሂደት ጥሰቶች በሚመለከት ዝርዝር ቅሬታ ስለማቅረብ፤
ክቡራን የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አመራሮች፤ 
 
ሀገራዊ ምክክር (National Dialogue) ማለት በአንድ ሀገር ውስጥ የተፈጠሩ ጥልቅ የፖለቲካ፣የማኅበራዊ፣ የታሪክ፣ የማንነት እና የጸጥታ ችግሮችን በጦርነት ወይም በኃይል ሳይሆን በውይይት፣በመደማመጥ፣ በድርድርና በስምምነት ለመፍታት የመፍትሔ ሐሳብና ምክረ ሐሳብ የማመንጨት የሚካሄድ ሂደት ነው። በሌላ አገላለጽ፣ ሀገራዊ ምክክር በተለያዩና በተለያየ ጥቅም የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች መካከል እምነት በጠፋበት ሁኔታ፣ ሀገር አቀፍ ችግሮችን ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍሎች በማሳተፍ በነፃነት፣ በእኩልነት እና ፍትሐዊ በሆነ ምክክር ለመፍታት የሚደረግ ሂደት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ሀገራዊ ምክክር ያለፉት የታሪክ ቁርሾዎችን ለማከም፣ ለግጭትና ለጦርነት ምክንያት የሆኑ አንኳር ጉዳዮችን ለይቶ በአጭርና በረጅም ጊዜ እልባት ለመስጠት፣ መላው ኢትዮጵያውያን “የእኛ” የሚሉት፣ የሚያከብሩትና የሚያስከብሩት የጋራ የቃል-ኪዳን ሰነድ (ሕገ መንግሥት) እውን እንዲሆን ወዘተ… አስተዋጽዖው የጎላ ነው፡፡ ለዚህም ነው፣ በሀገራችን በተደጋጋሚ የብሔራዊ ምክክርና እርቅ አስፈላጊነት ሲነሳ የቆየው፡፡ 
 
በሀገራዊ ምክክር ሂደት የመንግሥት አካላት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የተለያዩ ማኅበረሰቦች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ሲቪክ ማኅበራት፣ ምሁራንና ተመራማሪዎች፣ ሴቶችና ወጣቶች፣ የግጭት ተጎጂዎች፣ሽማግሌዎች፣ ዲያስፖራው እና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት በጋራ በመሳተፍ የሀገራችንን ዋና ዋና ችግሮች በመወያየትና በመግባባት ተቀባይነት ያለው የጋራ መፍትሔ ለማፍራት ይጠቅማል፡፡
 
ከዚህ አንጻር፣ በኢትዮጵያ አውድ ሀገራዊ ምክክር ተደጋግሞ ሲጠየቅ የነበረ እና ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ጉዳይ ነው። ሀገሪቱ በረጅም ታሪኳ ውስጥ የተለያዩ ያልተፈቱ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚ፣ የማንነትና የጸጥታ ጥያቄዎች ያሏት በመሆኑ እነዚህን ዘርፈ ብዙ ችግሮች በሰላማዊና በዘላቂ መንገድ ለመፍታት ሀገራዊ ምክክር ማካሄድ አስፈላጊ ሆኗል።
 
በዚህም መሠረት በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1265/2014 መሠረት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል። የሀገራዊ ምክክሩ አስፈላጊነትና ወቅታዊነት ከፍተኛ በመሆኑ፣ ይህንን ሂደት የጀመሩና ያስጀመሩ አካላትም ሊመሰገኑ ይገባል።
 
ኮሚሽኑ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፎ የመጨረሻው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
 
ውጤታማ ሀገራዊ ምክክር ለማካሄድ ተሳታፊዎች የምክክሩ ሂደት አካታች፣ ግልጽ፣ ተዓማኒ፣ፍትሐዊና ዲሞክራሲያዊ መሆኑን በሙሉ እምነት ሊቀበሉት ይገባል። በተመሳሳይም ተሳታፊዎች ምክክሩን ለግል ወይም ለቡድን የፖለቲካ ጥቅም ሳይሆን፣ ለእውነተኛና ዘላቂ ሰላም መሠረት ለመጣል የሚደረግ ሂደት መሆኑን ተገንዝበው፣ የሌሎችን አመለካከት በማዳመጥና በመረዳት የጋራ መፍትሔ ላይ ለመድረስ መሥራት ይጠበቅባቸዋል። 
 
እኛም ከአማራ ክልል የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችንና ተቋማትን ወክለን በሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ለመሳተፍ ወደ አዲስ አበባ ስንመጣ ከኮሚሽኑ ገለልተኛ አመራር፣ግልጽ አሠራር፣ ሚዛናዊ ተሳትፎ ለተለያዩ ወገኖች እኩል የመናገርና የመደመጥ ዕድል እንደሚኖር እምነት አድርገን ነበር።
 
ሆኖም ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ እየተካሄደ በሚገኘው ሀገራዊ ምክክር በተሳተፍንባቸው የተለያዩ አጀንዳዎች ውስጥ ያለፍንበትንና እያለፍንበት ያለውን ሂደት ስንገመግም ከላይ የተገለጹትን መርሆች የሚጥሱ ሆነው ያገኘናቸውን ተግዳሮቶችና ቅሬታዎች በዝርዝር ከዚህ በታች በተመለከተው አግባብ እናቀርባለን። እነዚህን ቅሬታዎች የምናቀርበው የምክክር ሂደት አንዴ ተጀምሮ በአጭር ጊዜ የሚጠናቀቅ ሳይሆን፣ በባሕል ደረጃም መሠረት ሊይዝ የሚገባው ወሳኝ ሀገራዊ እሴት ነው ብለን ስለምናምንም ጭምር ነው፡፡ 
 
1. ሐሳቦችን ውድቅ ማድረግ እና ትኩረት መንፈግ እንዲሁም የተመካካሪዎችን ሐሳብ ማዛባት፤
 
ቃለ ጉባኤ ለመመዝገብ የተመረጡ አንዳንድ አባላትና በአመካካሪነት የተመደቡ አካላት ከኮሚሽኑ የአሠራር መመሪያና መርሆች በተቃራኒ የሚመስል አካሄድ ሲከተሉ ተስተውሏል። ጉዳዩን በተደጋጋሚ በቃል ለማስገንዘብ ቢሞከርም ከማስተካከል ይልቅ ችግሩ እየተባባሰ መጥቷል። ለማሳያ፦
 
1.1. የሕዝብና ቤት ቆጠራ ጉዳይ፡- 
 
የአማራ ሕዝብ ከሕዝብና ቤት ቆጠራ ጋር በተያያዘ ያቀረባቸውን ዝርዝር ማስረጃዎች፣ ቅሬታዎችና አስረጅ ሐሳቦች በአግባቡ መዝግቦ በማቅረብ ሂደት ላይ ጉዳዩ ተዳፍኖ እንዲቀርና ተገቢውን ትኩረት እንዳያገኝ ጥረት እየተደረገ እንደነበር ተስተውሏል። የአማራ ሕዝብ ከዐፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጊዜ ጀምሮ አማራዊ ማንነቱን ይዞ እንዳይቀጥል “አማራ ነኝ አትበሉ፣ እኛ ኢትዮጵያውያን ነን” በሚል መንገድ ሲቀጠቀጥ የቆየ በመሆኑ፤ ይልቁንም አማራነት እና እስልምና የተለያዩ ሆነው እንዲቀርቡ ሲደረግ የቆየ በመሆኑ፤ በዘመነ አብዮት/ደርግ አማራነትና ፊውዳልነት፣ አማራነትና ፀረ አብዮተኝነት እየተቆራኙ ይቀርቡ የነበረበት ዘመን በመሆኑ፤ በህወሓት ዘመን ደግሞ፣ ግልጽ በሆነ መንገድ የአማራ ሕዝብ በሕዝብ ብዛትም ሆነ በመሬት ስፋት (በጆግራፊም በዲሞግራፊም) ኮስምኖ እንዲቀርብ የተደረገ በመሆኑ፤ የአማራ ሕዝብ ቁጥር እየተባሉ የሚቀርቡት አሃዞች የማንቀበላቸውና መታረም የሚገባቸው መሆኑን ደጋግመን ለማስረዳት ብንሞክርም፣ እንዳናቀርብ ተከልክለናል፡፡
 
1.2. የሌሎች ሕዝብ የቆጠራ ጥያቄ፡- 
 
የአማራ ክልል ተመካካሪዎች ያቀረቡትን የአማራ ሕዝብ ከአሁን በፊት በነበሩት ቆጠራዎች ሁሉ በትክክል አለመቆጠሩን ማስረጃ በማቅረብ እና በ 1999ኙ ቆጠራ በመንግሥት በታመነው መሠረት ሊስተካከል ቃል ተገብቶ ሳይተካከል የቀረውን የሕዝብ ቁጥርን ታሳቢ ያደረገ የባለፉት ዓመታት የበጀት ማካካሻ ጥያቄን ተከትሎ የእኛም ሕዝብ እንዲቆጠር ጥያቄ በ10፤50 እና 250 አባላት በተደረገ ውይይት ባልተገለጸበት እና ባልተወያየንበት ሁኔታ ጥያቄው በኦሮሚያ ክልል በኩል እንደቀረበ በሚያሳይ መልኩ ከወይይቱ አውድ ውጭ ተዛብቶ 500 አባላት በተወያዩበት ቃለ-ጉባኤ ላይ እንዲመዘገብ መደረጉ በአማራ ተመካካሪዎች በኩል የቀረበውን ምክንያታዊ ጥያቄ ለማጣጣል የቀረበ በመሆኑና ሂደቱን ያልተከተለ ሆኖ አግኝተነዋል።
 
2. ከእኩል ወይም ፍትሐዊ ተሳትፎ ተግዳሮት ጋር በተያያዘ፤
 
በተደጋጋሚ በተደረጉ ውይይቶች ተመካካሪዎች ብዝሃነታቸውንና ቁጥራቸውን ከግምት ያስገባ የመናገር ዕድል እንዳልተሰጣቸው ተስተውሏል። በ50፣ 250 እና 500 ተሳታፊዎች ቡድኖች ውስጥ ከአንዳንድ ክልሎች የመጡ ተወያዮች ተደጋጋሚ የመናገር ዕድል ሲያገኙ ከአማራ ክልል የመጡ ተወያዮች ግን ከቁጥራቸውና ከብዝሃነታቸው ጋር የሚመጣጠን በቂ የመናገር ዕድል እንዳላገኙ ተስተውሏል።
 
 በተጨማሪም ከ50 ተሳታፊዎች ውስጥ ቢበዛ አምስት ሰዎች ብቻ ዕድል የሚያገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ተደጋጋሚ ዕድል የሚሰጣቸው ሰዎች ይበዛሉ። በመሆኑም አብዛኛው ተሳታፊ ከመታዘብ የዘለለ ሐሳቡን የመግለጽ፣ አጀንዳ የማስያዝ፣ የማብራራትና የመፍትሔ ሐሳብ የማቅረብ ዕድል አላገኘም።
 
3. ከአወያዮች/አመቻቸቾችና ሌሎች የኮሚሽኑ ባልደረቦች ገለልተኝነት ተግዳሮት ጋር፤
 
የመድረክ መሪዎችና አወያዮች በተደጋጋሚ የተወያዮችን ድምጽ የማፈን፣ የመናገር ዕድል የመንፈግና አንድን ወገን የሚደግፍ አቋም የሚያሳይ አካሄድ በመከተላቸው በምክክሩ ሂደት ላይ የመተማመን እጥረት እየተፈጠረ መጥቷል።ለማሳያ ያህልም፤
 
3.1. በአጀንዳ 6 (በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ የአርሶ አደርና የአርብቶ አደር ጉዳዮች) ንዑስ ቡድን 28ን እንዲያወያይ በኮሚሽኑ የተመደበው አቶ ብርሃኑ ክፍተው የተባለ አመቻች/አወያይ ከሐሳብ ማመንጨት ደረጃ ጀምሮ ጣልቃ ይገባ ነበር፤ አብዛኛውን ጊዜም እርሱ የሚናገር መሆኑን፣ በነፃነት እንዳንወያይ ተጽዕኖ የሚፈጥር መሆኑንና ከኮሚሽኑ አሠራር ውጭ እየሠራ መሆኑን በመግለጽ ከአመካካሪነት እንዲቀየርልን የኮሚሽኑ ባልደረቦች ለሆኑት ለዶ/ር የኋላሸት እና ለአቶ ተሰማ በተደጋጋሚ ቅሬታ አቅርበናል። ሆኖም 50 አባላት ካሉት ቡድን በኋላ ከአቶ ብርሃኑ ክፈተው ጋር ስለማትገናኙ 50 አባላት ያለውን የምክክር ሂደት ብቻ “ታግሳችሁ እለፉ” የሚል ምላሽ ከዶ/ር የኋላሸት እና ከአቶ ተሰማ ተነግሮን ነበር። በተግባር ግን አቶ ብርሃኑ ክፍተው ከ50 አባላት ቡድን በኋላም በ250 እና በ500 አባላት ቡድን ደረጃ እንዲቀጥል ተደርጓል። በዚህም በውይይት ሂደቱ ላይ ሐሳብ ለመስጠት ፍላጎት ያላቸውን ተመካካሪዎች የመምረጥ ሚና በማግኘቱ ከአማራ ክልል የመጡ ተናጋሪዎች የመናገር ዕድል እንዳያገኙ ጫና በመፍጠርና ከአማራ ክልል ውጭ ላሉ ተሳታፊዎች ደግሞ ተደጋጋሚ የመናገር ዕድል እንዲያገኙ በማድረግ ውይይቱ ሚዛናዊ እንዳይሆን ተጽዕኖ ፈጥሮብናል፡፡
 
3.2. ከክልሉ ተወላጆች ውጭ በሌሎች ክልሎች የሚኖሩ ዜጎች በሚኖሩበት ክልል የመሬት ባለቤት እንዲሆኑ፣ በሚኖሩበት ክልል የምክር ቤት ውክልና እንዲያገኙ፣ የባህል ምክር ቤት እንዲያቋቁሙና በቁጥራቸው ልክ በተለያዩ የአስተዳደር አካላት ተገቢውን ውክልና እንዲያገኙ በሚቻልበት ሁኔታ በተደረገ ውይይት በተለይ ከኦሮሚያ ክልል በመጡ አንዳንድ ተወያዮች “አንድ ሳንቲም ሜትር መሬት ከሌላ ክልል ለመጣ ዜጋ አንሰጥም”፣ “እንዲህ ዓይነት ጥያቄ የምታነሱ ከሆነ በክልላችን የሚኖሩ የሌላ ክልል ዜጎችን ጠራርገን ነው የምናስወጣቸው”
 
 የሚሉ እና መሰል ግጭት ቀስቃሽና የጥላቻ ንግግሮች ሲነገሩ መድረኩን በዋነኛነት ይመሩ በነበሩ አወያዮች ተናጋሪዎቹን ለማስቆም ወይም ለማስተካከል የሚያስችል ተገቢ እርምጃ አልተወሰደም፡፡ ተደጋጋሚ ዛቻዎችና ማስፈራሪያዎች እየተሰነዘሩ መሆኑን፣ ይህም ከሀገራዊ ምክክሩ ዋነኛ ዓላማ ጋር እንደሚጋጭ ብናሳስብም ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ አልቻሉም፡፡ ለሚመለከታቸው አካላት አቤት ብንልም መፍትሔ አልተሰጠንም፡፡
 
3.3. በተመሳሳይ ተሳታፊዎች የአካሄድ ጥያቄ በማቅረብ ጉዳዩ እንዲስተካከል ለማስገንዘብ እንዳይችሉ፣ “የአካሄድ ጥያቄ አንቀበልም” በሚል ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ከመድረኩ መሰጠቱ የተሳታፊዎችን አማራጭ የሚገድብ አካሄድ ነበር ብለን እናምናለን።
 
3.4. በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ የአርሶ አደርና የአርብቶ አደር ጉዳዮች 500 ተሳታፊዎች ባሉበት የውይይት መድረክ አጀንዳውን ለማጠናቀር ከተመረጡት 30 ሰዎች መካከል ሰብሳቢና ጸሓፊ በተሳታፊዎቹ ከመምረጥ ይልቅ ዶ/ር የኋላሸት እና ዶ/ር ተስፋዬ ጂልማ በተባሉ አመቻቾች/አወያዮች አማካይነት መድረኩ ሲመራ ተስተውሏል። ይህም ከሌሎች ቡድኖች በተለየ ሁኔታ እነዚህ አመቻቾች ከአመካካሪዎች ጋር በመሆን ለማን የመናገር ዕድል እንደሚሰጥ አስቀድመው በመወሰን፣ በተለይም ከአማራ ክልል የመጡና ጠቃሚ ሐሳብ የሚያቀርቡ ፖለቲከኞች፣ ምሁራንና ሌሎች ተወያዮች ሐሳባቸውን በነጻነት እንዳይገልጹ ተጽዕኖ ተፈጥሯል፡
 
3.5. በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ የአርሶ አደርና የአርብቶ አደር ጉዳዮች ላይ ከተመደቡት ሙያተኞች (ኤክስፐርቶች) መካከል አቶ ኢብሳ ጨመዳ የተባለው ፍጹም ገለልተኛ ያልሆነና የራሱን ሐሳብ በተወያዮች እና በቃለ ጉባኤ አደራጆች ላይ በተደጋጋሚ ጊዜ ሲያሳርፍ ተስተውሏል፡፡ ይህም በመሆኑ በአንዳንድ ጉዳዮች በተለይም በመሬት ባለቤትነት እና በሕዝብና ቤት ቆጠራ ጉዳይ ላይ የበለጠ እንዳንግባባ አድርጓል፡፡ ለማሳያ ያህልም መሬትን ያህል ልዩ የሕግ ጥበቃ የሚደረግልት ሀብት የግል ይሁን ማለት ልክ እንደ በግ እና ፍየል ይሸጥ፤ ይለወጥ ማለት እንደሆነ መግለጹ፤የሕዝብ ቆጠራ በገለልተኛ አካል እንዲደረግ ብንጠይቅም ከሉዓላዊነት ጋር በማያያዝ ሳይጠየቅ ገብቶ ማብራሪያ መስጠቱ ሙያዊ ሥነ ምግባርን ያልተከተለ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡
 
3.6. የምክክሩ ዓላማ ከታች ባሉት የውይይት ደረጃዎች የተነሱና ገንቢ የሆኑ ሐሳቦችን ማሰባሰብ እንጂ ከታች ባሉት ውይይቶች ያልቀረቡ አዳዲስ ሐሳቦችን በመጨመር አዲስ ክርክር መፍጠር ታሳቢ ያላደረገ ሆኖ እያለ በአጀንዳ 2 በተካሄደው ምክክር በ10 እና በ50 ቡድን ደረጃ ያልተነሱና ለአላስፈላጊ ክርክሮች በር የከፈቱ አዲስ ሐሳቦች 50 አባላት ካሉት የውይይት ቡድን በኋላ ባሉ ሂደቶች እንዲነሱ ተደርጓል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም የመድረኩም አመራር በበቂ ሁኔታ ገለልተኝነት ያላሳየ መሆኑ ተስተውሏል።
 
በተጨማሪም ውይይቱ በሰነዱ የተመለከቱትን 17 ንዑስ አጀንዳዎች፤ በጥቅሉ 53 የሚደርሱ የውይይት ነጥቦችን ወይም ጥያቄዎችን መሠረት አድርጎ መካሄድ ነበረበት። ሆኖም፣ መሪ አወያዩ ከነበሩት አጀንዳዎች መካከል “የማንነትና የወሰን ጥያቄዎችና ግጭቶች” የሚለውን በተለይ ለይቶ ተሳታፊዎች በዚህ ላይ ውይይትና ጥያቄ እንዲያቀርቡ በመጋበዝ መድረኩን ጤናማ እንዳይሆን የማጋጋልና ሥራ ተሠርቷል።
 
ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ነጥቦች እንደተጠበቁ ሆኖ ለተሳታፊዎች ዕድል ሲሰጥ ከአንዳንድ ወገኖች/ክልሎች የመጡና በተለይም ከአማራ ክልልና ከበአማራ ሕዝብ ጋር ከፍተኛ ተቃርኖ ያላቸው ተሳታፊዎች ቅድሚያ እና ተደጋጋሚ ዕድል እንዳገኙ ተስተውሏል። 
 
ለምሳሌ፣ የትግራይ ማኅበረሰብ አንቂ (አክቲቪስት) እንደሆነ ለተነገረው አንዶም ገብረሥላሴ የተባለ ግለሰብ ኢ-ፍትሐዊ በሆነ መልኩ በተደጋጋሚ ዕድል ተሰጥቷል። “እኛ እናንተ፣ ማለትም የአማራና ትግራይ ተወካዮች ከተዋጣላችሁ በኋላ ሐሳብ እንሰጣለን” እያሉ በተደጋጋሚ የመናገርና ከሀገራዊ ምክክሩ ዓላማ ውጪ የመንቀሳቀስ አካሄዶችም በስፋት ይስተዋሉ ነበር፡፡ 
 
ከዚህም በላይ ከገንቢ ሀገራዊ ሐሳቦች ይልቅ ስምን በመጥቀስ በአንድ ብሔር፣ በተለይም በአማራ ክልልና ሕዝብ ላይ የሚያነጣጥሩ ንግግሮች ሲቀርቡ አወያዮች በቂ ማስተካከያ አለማድረጋቸው መድረኩ እንዲታወክና እንዲቋረጥ አድርጓል። ምክክሩ እንደገና ከተጀመረ በኋላም አወያዩ ተገምግሞ፣ ለተወሰኑ ተሳታፊዎች የበለጠ ዕድልና ደቂቃ መስጠት፣ለሌሎች ደግሞ ዕድል መንፈግ፣ ንግግርን ያለአግባብ ማቋረጥና አላስፈላጊ ማብራሪያ መስጠት የመሳሰሉ አካሄዶች ቀጥለዋል፡፡ 
 
3.7. በምክክሩ ወቅት የአማራን ሕዝብ እንደ ሕዝብ የሚያንቋሽሹና በከባድ ወንጀል የሚከሱ ንግግሮች ሲሰነዘሩ፣ እንዲህ ዓይነት በሕዝብ ላይ ያነጣጠሩ አደገኛ ንግግሮች ከሀገራዊ ምክክሩ ዓላማ ጋር አብረው እንደማይሄዱ፣ ይልቁንም ችግር እንፈታለን ብለን ሌላ የጥላቻና የልዩነት ግንብ እንዳንገነባ መጠንቀቅ እንደሚገባን ለማስገንዘብ ብንሞክርም የሚሰማ አካል አልተገኘም፡፡ አመካካሪ ተብለው የተመደቡ ሰዎችም መፍትሔ የሚሰጡ አልሆኑም፡፡ 
 
4. ከተመካካሪዎች ምደባ ኢ-ፍትሐዊነት ጋር በተያያዘ፦
ከተወያዮች አመዳደብና ስብጥር ጋር በተያያዘ፣ ከአማራ ክልል የመጡ ተመካካሪዎች በተለይ በፌዴራል ከተሞች ጉዳይ በቂ ውክልና እንዳይኖራቸው ተደርገዋል የሚል ቅሬታ አለን። ማለትም ከአማራ ክልል የመጡ ተመካካሪዎች በአብዛኛው ከፌዴራል ከተሞች፣ ከመንግሥት አደረጃጀትና አወቃቀር፣ እንዲሁም ከሀገረ መንግሥት ግንባታ ጉዳዮች ውጭ ባሉ ሌሎች አጀንዳዎች ላይ ብቻ እንድንመደብ ተደርጓል።
 
ለምሳሌ፣ከደሴ ተወክለው ከመጡ 11 የማኅበረሰብ ተወካዮች መካከል አምስቱ በማኅበራዊ፣ኢኮኖሚያዊ፣ የአርሶ አደርና የአርብቶ አደር ጉዳዮች ላይ እንዲወያዩ ተመድበዋል። ከአማራ ክልል “ተጽዕኖ ፈጣሪ” ተብለው ከተመረጡ 12 ሰዎች መካከል ስድስቱ በሃይማኖት ጉዳይ ላይ ተመድበው፣አቤቱታ ከአንዴም ሁለቴ ቢያቀርቡም ሁለቱ ብቻ ወደ ሌሎች አጀንዳዎች እንዲዛወሩ ተደርገዋል።በተቃራኒው በቅድሚያ በሌላ አጀንዳ ላይ የነበሩ ከኦሮሚያ ክልል የመጡ ተወያዮች ከተመደበቡት አጀንዳ ተቀይረው ወደ ፌዴራል ከተሞች አጀንዳ የመግባት ዕድል አግኝተዋል።ይህም በተሳታፊዎች ምደባ ስብጥር ላይ የእኩልነትና የፍትሐዊነት ጥያቄ እንዲነሳ አድርጓል።
 
5. በኮሚሽኑ ከተወሰነው የምክክር ቦታና ጊዜ ውጭ ሌሎች ስብሰባዎችን ማካሄድ፤
 
በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲና በሌሎች ቦታዎች፣ በእረፍት ቀናት የተካሄዱ ስብሰባዎች ከአማራ ክልል የቀረቡ አጀንዳዎችን ለማጣጣልና በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ተገቢ ያልሆነ ዕይታ እንዲኖር ብሎም ከአማራ ክልል ውጭ ባሉ ተመካካሪዎች አቋም እንዲያዝ ለማድረግ ተጽዕኖ የፈጠሩ መስለው ታይተዋል። ይህም በዋናው የምክክር መድረክ ውስጥ ከመርህ የወጣ ክርክር እንዲፈጠር፣ አንዱ ወገን ተሸናፊ ሌላው ወገን አሸናፊ የሚሆንበት አካሄድ እንዲፈጠርና የምክክር ሂደቱ ከዋና ዓላማው እንዲወጣ ሊያደርግ የሚችል አካሄድ ነው ብለን እናምናለን።
 
6. የቃለ ጉባኤ ጸሓፊዎች ውክልና ኢ-ፍትሐዊነትና በቃለ ጉባኤ አያያዝ ላይ የተስተዋሉ ችግሮች፤
 
ከተሳታፊዎች የሚመረጡ የቃለ ጉባኤ ጸሓፊዎች አመራረጥ በግልጽና በተሳታፊዎች የሚታወቅ መርህ መሠረት ከመካሄድ ይልቅ ቀድመው በተደራጁ የውስጥ አደረጃጀቶች በመመረጣቸው ምክንያት የተሳታፊዎችን ብዝሃነት የሚያንፀባርቅ ፍትሐዊ ውክልና እንዳይኖር አድርጓል፡፡
በተጨማሪም፣ አጀንዳዎች ተመጣጣኝ ትኩረት አግኝተው እንዳይመዘገቡና በዝርዝር እንዳይቀርቡ በማድረግ አግባብ ያልሆኑ አካሄዶች ተስተውለዋል። በተለይም በአጀንዳ 2፣ ማለትም በ‹መንግሥት አደረጃጀትና ቅርጽ› ላይ በ10 እና በ50 ቡድን ደረጃ የተካሄደው ምክክር በአብዛኛው ጥሩ ሁኔታ ላይ እያለ፣ በ250 ቡድን ደረጃ ግን አዳዲስ ሐሳቦች ሲነሱ ጸሓፊዎች በተለየ ሁኔታ ጎላ አድርገው እንደተቀበሉ ተስተውሏል።
 
ለምሳሌ፣ በአጀንዳ 2.1.1 “ለኢትዮጵያ ተስማሚ የሆነው የመንግሥት ዓይነት የቱ ነው? ፓርላማዊ፣ ፕሬዚዳንታዊ ወይስ ከፊል ፕሬዚዳንታዊ?” በሚለው ጉዳይ ላይ የተለያዩ ሐሳቦች ቀርበው ነበር። አብዛኛው ሐሳብ ፓርላማዊ ሥርዓትን የሚደግፍ ሲሆን፣ ጥቂቶች ደግሞ ፕሬዚዳንታዊ ሥርዓትን ደግፈዋል። በ250 ቡድን ምክክር ላይ ግን አዲስ ሐሳብ ተነስቶ፣ ፓርላማዊ ሥርዓት ቢኖርም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬዚዳንት ሆኖ የመንግሥትንና የፕሬዚዳንቱን ሥልጣን በአንድ ላይ ይያዝ የሚል ሐሳብ ሲነሳ ሰፊ ተቃውሞ ከዝርዝር አመክንዮ ጋር ቢቀርብም፣ በጸሓፊዎች በኩል ይህ ሐሳብ በ500 ቡድን ደረጃ እንደ ዋና ሐሳብ ሲቀርብ ተስተውሏል።
 
በተመሳሳይ፣ አንዳንድ ተሳታፊዎች ያነሷቸውን ሐሳቦች በጸሓፊዎች በኩል የማሳነስ፣ አልፎ ተርፎም ያለመቀበል ሁኔታዎች ተስተውለዋል።
7. ከአዲስ አበባ ከተማ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የተስተዋሉ ችግሮች፤
 
ከሁሉም በላይ በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ አማራ ክልል ተሳታፊዎች ሐሳባችንን በነጻነት እንዳናቀርብ የመድረክ መሪዎች ተደጋጋሚ ዕድሎችን ነፍገውናል፡፡ ሐሳብ በምናቀርብበት ጊዜም የማቋረጥና የማስቆም ሁኔታዎች በስፋት ታይተዋል፡፡
 
 ከ10፣ 50 እና 250 ቡድኖች ውስጥ ያልነበሩ ተሳታፊዎች ተገኝተው መታወቂያ ተሰጥቷቸው ወደ መድረኩ መግባታቸው፣ እንዲሁም ከሀገራዊ ምክክር የሥነ ምግባር መርሆች ጋር የማይጣጣሙ የአንድ ብሔር ማንነትና እምነትን የሚያነሳሱ ንግግሮች ሲነሱ እንዲቆሙ አለመደረጋቸው የምክክሩን ገለልተኝነት እንድንጠራጠር አድርጎናል። አካሄዱ በአጠቃላይ፣ ሀገራዊ ምክክሩ ከተነሳለት (በማቋቋሚያው ላይ የተገለጸውን ዓላማ ልብ ይሏል) ፍፁም ተቃራኒ ነበር፡፡ 
 
የምክክሩ ተሳታፊዎች በመረጃና በማስረጃ ላይ ተመሥርተን፣ ጊዜ ወስደን፣ በነጻነትና በዲሞክራሲያዊ መንገድ ሐሳባችንን እያቀረብን በሐሳቦች ላይ ውይይት፣ ክርክርና ምክክር ማድረግ ሲገባን፤ የነበረው ሁኔታ በጥድፊያ የተሞላ፣ የተወሰኑ ሰዎች ብቻ እንዲናገሩ ዕድል የተሰጠበት፣ በድርጅታዊ አሠራር የተወሰኑ ኃይሎች የሚደጋገፉበት ሁኔታ ነበር፡፡ 
 
በእኛ በኩል አዲስ አበባ ታሪኳና የሕዝብ ብዛቷን መሠረት በማድረግ የማን መሆኗ ይመርመር ቢባል ግልጽ መሆኑን፣ ይሁን እንጂ የአማራ ሕዝብ አዲስ አበባ የለማችው በመላው ኢትዮጵያውያን ላብና ደም መሆኑን፣ የኢትዮጵያ ህልውናም የተቋጠረው አዲስ አበባ ላይ መሆኑን፣ ስለሆነም የአዲስ አበባ ባለቤት መላው ኢትዮጵውያን መሆናቸውን፣ በኦሮሚያ ክልል የሚቀርበው “የጋራ ተጠቃሚነት” የሚለው አጀንዳ እጅግ አደገኛና ሀገሪቱን ወደ ጦርነት የሚመራ መሆኑን፣ አዲስ አበባ ራሷን የቻለችና ራሷን በራሷ የምታስተዳደር ከተማ መሆኗ በግልጽ በሕገ መንግሥት ደረጃ መቀመጥ እንዳለበት ሐሳባችንን ለማቅረብ ሞክረናል፡፡ ይህንን ሐሳብ በማቅረባችንም ያልተገቡ ስድቦችና ዛቻዎች ደርሰውብናል፡፡ ይህም ከሀገራዊ ምክክሩ ዓላማ ጋር በግልጽ የሚጋጭ ነው፡፡ አካሄዱ እንዲታረም በተደጋጋሚ አቤት ብንልም ሰሚ አላገኘንም፡፡
 
በተጨማሪም፣ ዕድል ተሰጥቶን ሐሳባችንን በምናቀርብበት ወቅት የመድረኩ መሪ “ምን ማለት እንደፈለጋችሁ ገብቶናል” በማለት ሐሳባችንን ሙሉ በሙሉ ሳንገልጽ የማቋረጥ አካሄድ ታይቷል።በዚህ ምክንያት፣ በፌዴራል ከተሞች አጀንዳ ላይ የተመደብን ተመካካሪዎች፣ ከኮሚሽኑ ባለሙያዎች ጀምሮ አወያዮች፣የመድረክ መሪዎች፣ ታዛቢዎችና የፓናል ባለሙያዎች የአንድ አቋም ደጋፊዎች መስለው በመታየታቸው በኮሚሽኑ ገለልተኝነት ላይ ጥያቄ እንዲኖረን አድርጓል።
 
8. በቃለ ጉባኤ ከመፈረም ጋር በተያያዘ የተስተዋሉ ችግሮች፤
 
እያንዳንዱ ተመካካሪ ሊፈርም የሚገባው ተወያይቶ በተግባባቸው ነጥቦች አሊያም በልዩነት በግልጽ በተቀመጡ ጉዳዮች ላይ በዚያው ቃለ ጉባኤው በሰፈረበት ሰነድ ላይ መሆን ሲገባው የቃለ ጉባኤው ሰነድ በበቂ ሁኔታ/በተሳታፊዎች ቁጥር ልክ የመፈረሚያ ቦታ እንዲኖረው ተደርጎ ያልተዘጋጀ በመሆኑ በሰዓት ፊርማ ቅፆች ላይ የፈረምናቸው ፊርማዎች ልክ ቃለ ጉባኤው ላይ ተስማምተን እንደፈረምን በማስመሰል ከቃለ ጉባኤው ጋር የሰዓት መቆጣጠሪያ ፊርማ ወረቀቶቹ እንደሚያያዙ ተገልጾልናል፡፡ ይህ ደግሞ ባላየነው እና አንብበን/ተነቦልን ባላረጋገጥነው ቃለ ጉባኤ ላይ እንደፈረምን የሚስቆጥር እና የቃለ ጉባኤ አያያዝን/አፈራረምን መሠረታዊ ሂደት የሚጣረስ በመሆኑ በተወያየንባቸው አጀንዳዎች ላይ ተግባብተን ወይም በልዩነት ፈርመናል ሊባል አይገባም፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘም በሁሉም አጀንዳዎች ላይ መግባባት እንዳልተደረሰ ኮሚሽኑ እውነታውን እያወቀ ወይም ማወቅ ሲገባው እንዲሁም ከአማራ ክልል የመጣን ተመካካሪዎች ነሐሴ 5 ቀን፣ 2018 ዓ.ም. ለኮሚሽኑ ላቀረብናቸው ቅሬታዎች መልስ ይሰጠናል ብለን እየተጠባበቅን ባለንበት ሁኔታ በተጣደፈ ሁኔታ በሁሉም አጀንዳዎች ላይ ተመካካሪዎች መግባባት ላይ እንደደረሱ ለሚዲያዎች መግለጫ መስጠቱ አግባብነት የሌለው ሆኖ አግኝተነዋል፡፡
ኮሚሽኑን የምንጠይቃቸው ዋና ዋና ጉዳዮች፦
 
ከላይ የተገለጹት ቅሬታዎች በምክክሩ ሂደት የኮሚሽኑ መርሆች በሚጠይቁት መሠረት እንዳይካሄድ የፈጠሩብንን ተግዳሮቶች የሚያሳዩ ናቸው። በዚህም መሠረት እኛ ወክለን የመጣነውን ሕዝብ መብትና ጥቅም በአግባቡ ለማስጠበቅና ሀገራችን ያለችበትን ተጨባጭ ችግር በእውነተኛ ምክክር ለመፍታት በቂ ዕድል እንዳልተፈጠረ ተሰምቶናል። ስለሆነም የተከበረው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሚከተሉትን ጉዳዮች በድጋሚ እንዲያይና እንዲያስተካክል እንጠይቃለን፡፡
 
1. ከአዲስ አበባ ከተማ ጉዳይ ጋር በተያያዘ፤
 
አዲስ አበባ ከተማ የፌዴራል መንግሥቱ መቀመጫና የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ብቻ መሆኗን እና ከተማዋ ለመላው ኢትዮጵያዊ የጋራ ቤት መሆኗን በምክክሩ ወቅት የቀረቡት ሐሳቦች በግልጽና በሚዛናዊ መንገድ በቃለ ጉባኤው እንዲካተቱ እንጠይቃለን። በተለይም አዲስ አበባ ከተማ የፌደራል መንግሥቱ መቀመጫ፤ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ መሆኗ እና ተጠሪነቷም ለፌደራል መንግሥቱ ብቻ ስለመሆኑ እንዲሁም ከተማዋ ራሷን በራሷ እንድታስተዳደር የሚለው ነጥብ በቃለ ጉባኤው ላይ በግልጽ እንዲመዘገብልን እንጠይቃለን።
 
2. በክልሎች ውስጥ ተሰበጣጥረው የሚኖሩ ብሔሮችን ውክልና እና አካታች አስተዳደር ጋር በተያያዘ፤
ከአማራ ክልል ውጭ የሚኖሩ አማራዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ ከክልላቸው ውጭ የሚኖሩ ሱማሌዎች፣ኦሮሞዎችና ሌሎች ኢትዮጵያውያን በሚኖሩበት አካባቢ ተገቢ የአካባቢያዊ ውክልና እንዲኖራቸው፣ በራሳቸው ቋንቋ እንዲማሩ፣ አገልግሎትና ፍትሕ የማግኘት መብታቸው እንዲከበርና ሌሎች ተመሳሳይ መብቶች እንዲጠበቁ በውይይት መድረኩ ያቀረብነው ሐሳብ በአግባቡ እንዲመዘገብ እንዲደረግ እንጠይቃለን። በእኛ በኩል ይህ መሠረታዊ ሐሳብ መላውን የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች መብት የሚያረጋግጥ እና እውነተኛ ኅብረ-ብሄራዊ ዲሞክራሲን የሚያሰፍን ነው፡፡ 
 
3. የተፈጸሙ ግድያዎችና መፈናቀሎች በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ ካቀረብናቸው ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ፤
ከጣልያን ወረራ ዘመን ጀምሮ በተለያዩ ወቅቶች በአማራ ሕዝብ ላይ የተፈጸሙ ተብለው የሚቀርቡ ግድያዎች፣ መፈናቀሎችና ሌሎች ጥሰቶች በሽግግር ፍትሕ ሂደት ውስጥ በአግባቡ እንዲታዩ እንጠይቃለን። በተለይም ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ በጉራፈርዳ፣ በበደኖ፣ በቁርፍቱ፣ በወለጋ፣ በአሩሲና በሌሎች አካባቢዎች ተፈጽመዋል ተብለው የሚቀርቡ ብሔርና ሃይማኖት ተኮር ግድያዎችና መፈናቀሎች በሽግግር ፍትሕ አጀንዳ ውስጥ እንዲካተቱ እንጠይቃለን።
 
4. ከሕዝብና ቤት ቆጠራ ጉዳይ ጋር በተያያዘ፤
ከአማራ ሕዝብ አንኳር ጥያቄዎች ውስጥ አንዱ የሕዝብ ቁጥር ጥያቄ ነው፡፡ ከላይ ለማብራራት እንደተሞከረው በዐፄ ኃይለሥላሴም፣ በደርግም፣ በሕወሓት/ኢህአዴግም የተካሄዱት የሕዝብ ቆጠራዎች የአማራን ሕዝብ አይወክሉም፡፡ በዘመነ ሕወሓት የተካሄደውን ማለትም በ1999 ዓ.ም. የተደረገውን የሕዝብና ቤት ቆጠራ ውጤት በተመለከተ ራሱ መንግሥትም ያመነው ጉዳይ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በሕወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ የቀረበው ማብራሪያ ፈጽሞ ከእውነት የራቀ ነው፡፡ ከእውነት የራቀ መሆኑንና ሆን ተብሎ የተደረገ መሆኑን ለማረጋገጥ በወቅቱ ጉዳዩ በገለልተኛ ዓለም አቀፍ ተቋማት እንዲጣራ የቀረበው ጥሪ በሕወሓት/ኢህአዴግ ተቀባይነት ማጣቱን ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡
ከላይ እንደተገለጸው የሕዝብ ቁጥርን በሚመለከት የአማራ ሕዝብ ያለው ጥያቄ ግን በሕወሓት/ኢህአዴግ ጊዜ የነበረውን ሴራ ብቻ የሚመለከት አይደለም፡፡ ከዚያ በፊት በነበሩት ቆጠራዎች በሙሉ የአማራ ሕዝብ በውል አልተቆጠረም የሚል እንጂ፡፡ ስለሆነም ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች በተገኙበት ነጻና ገለልተኛ ቆጠራ መካሄድ ይኖርበታል፡፡ 
 
5. ከፖለቲካ እስረኞች ጋር በተያያዘ፤
 
ሀገሪቱ አሁን ካለችበት ችግር ለመውጣት ሁሉን አቀፍና አካታች ምክክር እንደሚያስፈልግ በመግለጽ፣ በእስር ላይ የሚገኙ የፖለቲካ እስረኞች ጉዳይ በምክክሩ አጀንዳ ውስጥ እንዲካተትና አግባብነት ያለው መፍትሔ እንዲፈለግለት እንጠይቃለን።
በአጠቃላይ፣ ከላይ የዘረዘርናቸው ጉዳዮች በምክክሩ ሂደት ውስጥ በቂ ትኩረት ያላገኙ ወይም በተገቢው መንገድ ያልተመለከቱ መሆናቸውን በመግለጽ የተከበረው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፦
 
1. ከላይ የተጠቀሱትን ቅሬታዎች ገለልተኛና ግልጽ በሆነ መንገድ እንዲመረምር፤
2. በሂደቱ የተፈጠሩ የአሠራር ችግሮችን እንዲያስተካክል፤
3. ከላይ የተዘረዘሩት አምስት ዋና ዋና ጉዳዮች በቃለ ጉባኤው እንዲካተቱ ወይም ተመልሰው በአግባቡ እንድንወያይባቸው እንዲደረግ፤
4. የተሳታፊዎች እኩልነት፣ ገለልተኝነት፣ የመናገርና የመደመጥ መብት እንዲረጋገጥ፤
5. በተለይም በተሳታፊዎች ላይ የሚፈጸሙ የጥላቻ፣ የማስፈራራትና የማንቋሸሽ ንግግሮች ተገቢውን እርምጃ እንዲወሰድባቸው፤
6. በሂደቱ ላይ የተፈጠረው የመተማመን እጥረት እንዲታረምና የምክክሩ ተዓማኒነት እንዲመለስ እንዲደረግ፤
7. በዚህ ሰነድ እና ነሐሴ 5 ቀን፣ 2018 ዓ.ም. ለኮሚሽኑ ላቀረብናቸው ቅሬታዎች ተገቢው ምላሽ እንዲሰጠን በማለት በአክብሮት እንጠይቃለን።
 
ይሁን እንጂ ከዚህ በላይ በዝርዝር የተጠቀሱት ቅሬታዎች/ጉዳዮች በአግባቡ ካልታዩና በተገቢው መንገድ መፍትሔ ካላገኙ፣ የምክክሩ ሂደት አካታች፣ ፍትሐዊና ተዓማኒ አለመሆኑን በማመን በሀገራዊ ምክክሩ ላይ ያለንን ተሳትፎ ለማቋረጥ የምንገደድ ስለመሆኑ በታላቅ አክብሮት እንዲታወቅልን እንጠይቃለን፡፡"
See less


አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።