በአዲሱ ዓመት መንግስት ያቀረበውን የይቅርታ ሰነድ አንፈርርም ብለው በማረሚያ ቤት የቀሩ 30 ተከሳሾች ለሕይወታቸው አስጊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ አስታወቁ

 

በአዲሱ ዓመት መንግስት ያቀረበውን የይቅርታ ሰነድ አንፈርርም ብለው በማረሚያ ቤት የቀሩ 30 ተከሳሾች ለሕይወታቸው አስጊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ አስታወቁ
 
በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ የተመሰረተባቸው ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች ያልተገባ ዝውውርና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጸመብን ሲሉ ለአስቸኳይ ትዕዛዝ አቤቱታ አቀረቡ
 
አዲስ ማለዳ
October 7, 2026
ረቡዕ፣ መስከረም 27 ቀን 2019 ዓ.ም
 
በሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ችሎት ክሳቸው እየታየ የሚገኙ የፖለቲካ ሰዎች፣ ጋዜጠኞችና የተለያዩ ተከሳሾችች ያለ ምንም ምክንያት ከነበሩበት ማረሚያ ቤት ተወስደው ለአደጋ በሚያጋልጡ አስቸጋሪ ስፍራዎችና ልዩ የማግለያ ዞኖች መበተናቸውን በመግለጽ፣ ማረሚያ ቤቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽሞብናል ሲሉ ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ አቅርበዋል።
 
ተከሳሾቹ ፍርድ ቤቱ አስቸኳይ የእርምት ትዕዛዝ እንዲሰጥና የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽንና የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የሥራ ኃላፊዎችን በችሎት አስቀርቦ እንዲጠይቅ አመልክተዋል።
 
በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ችሎት ክስ የተመሰረተባቸው በእነ ዶክተር ወንደሰን አሰፋ፣ በእነ ዮሐንስ ቧያለው፣ በእነ ሚካዔል መላክ እና እሱባለው በለጠ መዛግብት ስር የሚገኙ ተከሳሾች፤ መስከረም 18 እና 20 ቀን 2019 ዓ.ም ለፍርድ ቤቱ በጠበቆቻቸው በኩል ባስገቡት አቤቱታ፣ በማረሚያ ቤት በኩል እየተፈጸመባቸው ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ዘርዝረው አቅርበዋል።
 
በቀረቡት ሰነዶች መሠረት፣ ተከሳሾቹ ቀደም ሲል በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት እንዲሁም በቃሊቲ ማቆያ በጋራ ታስረው ይገኙ የነበረ ቢሆንም፣ መስከረም 15 ቀን 2019 ዓ.ም ከቀኑ 11:00 ጀምሮ ያለ ምንም ምክንያትና ቅድመ ማስታወቂያ ከተለያዩ ዞኖችና ማረሚያ ቤቶች እንዲበተኑ ተደርጓል።
 
በቀረበው የአቤቱታ ሰነድ መሠረት የእስረኞቹ ዝውውርና የደረሰባቸው ችግር አዲስ ማለዳ እንደሚከተለው አሰናድታዋለች፡፡
አንደኛ፤ በቃሊቲ “ታንከር” ወደሚባለው ልዩ ቦታ የተዛወሩ ዮሐንስ ቧያለው (1ኛ ተከሳሽ)፣ ጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻው (9ኛ ተከሳሽ) እና እሱባለው በለጠ (የካናዳ ዜግነት ያለው) ሲሆኑ እነዚህ ተከሳሾች በድንገት ከነበሩበት ተወስደው በከባድ ወንጀል ከተፈረደባቸው፣ በማረሚያ ቤት ውስጥ ረብሻና ድብደባ ከፈጸሙ፣ ለማምለጥ ሲሞክሩ በጥይት ከተመቱና ከፍተኛ ጥፋት ካደረሱ አስፈሪ እስረኞች ጋር በተለምዶ “ታንከር” በሚባለው ልዩ ማግለያ ቦታ መታሰራቸውን ገልጸዋል። ድርጊቱ ሕይወታቸውን ለአደጋ ያጋለጠና ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሆነ አመለክተዋል።
 
ሁለተኛ፤ ወደ ቂሊንጦ ልዩ ልዩ ዞኖች የተዛወሩት ደግሞ ዶክተር ወንደሰን አሰፋ (1ኛ ተከሳሽ)፣ የጸጥታ ኃይላት ብቻ ከሚታሰሩበትና ለቅጣት ተብሎ ከተዘጋጀው የቂሊንጦ “ዞን 6” እንዲገቡ መደረጋቸውን ገልጸዋል።
 
ቦታው በቆርቆሮ የተከበበ፣ እጅግ ጠባብ፣ አይጠ-መጎጥን ጨምሮ ልዩ ልዩ ነፍሳት የሚገኙበትና ከፍተኛ ጠረን ያለው በመሆኑ፣ ቀድሞውኑ የደም ግፊት ህመምተኛ የሆኑት ዶ/ር ወንደሰን ለሕይወታቸው በመስጋት በሩ አካባቢ ተቀመጠው እንደሚገኙና ወደ ሌላ ዞን እንዲቀየሩ ጠይቀዋል።
 
ዶክተር ሲሳይ አውግቸው እና ዶክተር ቴዎድሮስ ኃይለማርያም፣ ወደ ቂሊንጦ ዞን 4፤ እስክንድር ሽፈራው እና መንበረ አለሙ፣ ወደ ዞን 5፤ አለልኝ ምህረቱ፣ ወደ ዞን 1፤ አሳምነው ታደሰ እና መለሰ ቸሩ፣ ወደ ዞን 3 መዘዋወራቸውን አዲስ ማለዳ ከሰነዱ ተመልክታለች።
 
ሚካዔል መላክ፣ ፍርዱ ተፈራ እና ያሬድ ግርማ፦ ወደ አባ ሳሙኤል ማረሚያ ቤት የተወሰዱ ሲሆን፤ ሚካዔል መላክ ቀድሞውኑ የእጅ ቁስለት፣ የጆሮ ጠጠር፣ የልብ ድካም፣ የማዞርና የእግር ወለምታ ህመም ስላለባቸው በፍርድ ቤት ትዕዛዝ አትክልትና ሻይ አዘጋጅተው እንዲመገቡ የተፈቀደላቸው ቢሆንም፣ አዲሱ ማረሚያ ቤት ከቤተሰብ ምግብና ቁሳቁስ እንዳይገባቸው በመከልከሉ ምክንያት ለከፍተኛ የጤና እክል መዳረጋቸውን አብራርተዋል።
 
ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ (11ኛ ተከሳሽ) እና ጋዜጠኛ አባይ ዘውዱ (49ኛ ተከሳሽ)፤ ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ጠያቂ ቤተሰብ የሌለው በመሆኑ ከዓባይ ዘውዱ ጋር ምግብ በጋራ የሚመገብ ቢሆንም፣ በአዲሱ ቦታ ፍሪጅ መጠቀም ባለመቻላቸው ምግባቸው እየተበላሸበት እንደሚገኝ ገልጻል።
 
በተጨማሪም ቀደም ሲል ፍርድ ቤት በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት በሳምንት 7 ቀን የመጠየቅና ምግብ የማስገባት መብታቸው እንዲከበር ጠይቀዋል። ዓባይ ዘውዱ በበኩላቸው የፍርድ ቤት ትዕዛዝ እያለ ከቤተሰብ የመጣላቸውን አልባሳትና ጫማ እንዳይቀበሉ መከልከላቸውን አመልክተዋል።
 
ቀደም ሲል በአንድ ክፍል ውስጥ በጋራ ታስረው የነበሩት መምህርት መስከረም አበራ፣ ጋዜጠኛ ገነት አስማማው፣ ሕይወት አለማየሁ እና ሐሊማ መሐመድ ሲሆኑ፤ ከእነዚህ ውስጥ ሕይወት አለማየሁ እና ሐሊማ መሐመድ ወደ ሌላ ቦታ ተወስደዋል።
 
ዝውውሩን ተከትሎ ጠያቂ ቤተሰቦቻቸውን ማግኘት እንዳይችሉ የተደረገ ሲሆን፣ አንደኛዋ የኩላሊት፣ ሁለተኛዋ ደግሞ የከፍተኛ እግር ህመምተኞች በመሆናቸው የተቀየሩበት ቦታ ህመማቸውን እንዳባበሰው ተገልጻል።
 
ተከሳሾቹ በአቤቱታቸው እንዳመለከቱት፣ በሕገ-መንግሥቱና በማረሚያ ቤቱ አዋጅ የተረጋገጠላቸው በሕግ ባለሙያ፣ በኃይማኖት አባቶችና በቤተሰብ የመጎብኘት መብታቸው በማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች እየተጣሰ ይገኛል።
 
በተለይም መስከረም 6 ቀን 2019 ዓ.ም የመጡ ጠያቂዎችን (ለምሳሌ፡- ሚስጢረ ሥላሴ ታምራት እና አብርሃም ኃይማኖትን) ኮማንደር አይናለም ሳህሉ እንዳይጠይቁ ከልክለው የመለሷቸው ሲሆን፤ ኢንስፔክተር ፍቃዱ አዱኛ የተባሉ የጥበቃ አባል ደግሞ ጠያቂዎችን ከመከልከል በተጨማሪ ክብረ-ነክ ስድብ በመሳደብና ለጥበቃዎች ትዕዛዝ በመስጠት ተዋክበው እንዲወጡ ማድረጋቸው በአቤቱታው ተጠቅሷል።
 
ተከሳሾቹ በፍርድ ቤቱ በኩል፤ በቃሊቲ “ታንከር” ከተባለው የቅጣት ቦታና ከቂሊንጦ “ዞን 6” አላግባብ የታሰሩት ተከሳሾች በአስቸኳይ ወደ ሌላ ደህንነቱ ወደተጠበቀ ዞን እንዲዛወሩ፤ የተከለከሉት የህክምና፣ የምግብ፣ የጫማና የፍሪጅ አጠቃቀም መብቶች እንዲሁም የቤተሰብ ጥያቄ በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መሠረት እንዲከበርላቸው፤ የተፈጸመውን ከፍተኛ የመብት ጥሰት በተመለከተ የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽነር ተክሉ ለታ እና የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ኃላፊ ምላሽ ኮማንደር ጣሰው ግዛው በችሎት በአካል ቀርበው ምላሽ እንዲሰጡና ፍርድ ቤቱ ተከታትሎ የእርምት ትዕዛዝ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።