#ሚዛኑ ቢጠበቅ።
#ሚዛኑ ቢጠበቅ።
"ስለ ኃጢያትህ ንሰኃ መግባትን አትፍራ
የእግዚአብሄር ቸርነቱ ብዙ ነው እያልክ፤
በኃጢያት ላይ ኃጢያት አትሥራ።"
(መጽሐፈ ሲራክ ምዕራፍ ፭ ቁጥር ፭)
#ምዕራፍ ፳።
ፕሮፌሰር ብርኃኑ ነጋ ዓለም አሁን ባለበት ፈታኝ ወቅት ተባብረንም አገር ማዳን ከቻልን ዕድለኞች ነን የሚል ዕድምታ ያለው ጉልበታም ሃሳብ አንስተዋል። የዘመኑን የፖለቲካ ባህሬ ከግሎባል ጉዳዮች ጋር አያይዘው ስጋታቸውን ገልጸዋል። አገር እንዳናጣ ዓይነት።
ጥቅስ ውስጥ ያላስገባሁት ግንቦት 7 የተስፋ ማዕከል በነበረበት ጊዜ፤ በራሴ ላይ ይደርሱ የነበሩ ወጣ ገብ ጫናወች ተነስቼ፤ በህወሃት አገዛዝ የነበረው የሰብዕዊ መብት ጥሰት ለማዳን አይደለም #ተነጣጥለን ተባብረንም ኢትዮጵያ ማዳን ከቻልን ዕድለኞች ነን የሚል ጹሁፍ በዘሃበሻ እና በሳተናው ድረ ገጽ ላይ እጽፍ ነበር።
እሳቸው የማህበራዊ ሚዲያ ደንበኛ ስላልሆኑ የእኔን ጹሁፍ ከቁጥር አስገብተው ላያነቡት አይችሉም። ትናንትም ይሁን ዛሬ እዩኝ እዩኝ የሚል ሰብዕና ፈጽሞ አይቸባቸው አላውቅም።
ጭራሽ ማህበራዊ ሚዲያማ ደጋፊወቻቸው እንጂ እሳቸው የሉም። ይሄ ጥሩ ምግባር ይመስለኛል። ተግባር ይናገር ዘንድ መፍቀድ በሳል ስልት ነው - ለእኔ። የሳቸው መንፈስ የራቃቸው ጓዶቻቸው ይፈልጓቸዋል። እሳቸው ግን በአመኑበት የፖለቲካ አቋም ውስጥ ይገኛሉ።
የሆነ ሆኖ ግንቦት 7 ይጎድልበታል ተብሎ #ተነቅሶ የሚሰነዘርበትን ሙግት ትችት በሰለጠነ ሁኔታ ዕውቅና ተሰጥቶት ቢሆን ---- ኖሮ? ያን ጊዜ ታች ያለው "እረኛ ምን አለ" የሚለው የአባቶቻችን ይተብኃል ቢያደመጥ ----- ኖሮ? ዛሬ ያለው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሁኔታ ሌላ መልክ ይኖረው ነበር።
ከአብይዝም የተሻለ ወይንም የባሰ የሚለውን #መተንበይ አልችልም። ቢያንስ ግን የአዲስ አበባ ጫና ላይኖር የሚችልበት ሁኔታ ይገጥም ነበር። አዲስ አበባ ሙሉ ነፃነቷን ትቀዳጅ ነበር። አዲስ አበባ ከስጋት ትገላገል ነበር። እንዲህ ማንነቷም የገብያ ውሎ ሳይሆን እራሱን ችሎ፤ ዕውቅናም ክብርም ይሰጠው በነበረ።
ግን በተለይ የታችኛው አካል አይደለም ተቋምን አጋዥ የአንድ ባተሌን አቅምን የማሳደድ፤ የመቅበር ስልት ይከተል ስለነበር ንቅናቄው ዕድሉ አመለጠው። አሁንም ቢሆን እኛን ሳይሆን የትምህርት ሚኒስተሩን ፕሮፌሰር ብርሃኑ ከተደመጡ መደማመጡ ጤናማ መንገድ ነው። አሻቅቦ መናገር ቢከብድም ጥረት ማድረግ ይገባል። በመልካሙም፤ ደግ ባልሆነውም ጉዳይ የካቢኔ አባልነቱ ኃላፊነት እና ተጠያቂነቱ አይቀሬ ነው።
#ችግሩ።
ብልፄው ከራሱ ፈቃድ ውጪ ምንም አያደምጥም። ለማድመጥም ፈቃደኛ አይደለም። ከትልሙ አንዲት #ጋት ፈቅ ማለትንም ፈጽሞ አይፈቅድም። ይህን ብልፄው እንዲያስተካክል ፕሮፌሰሩ በነካ እጃቸው ለብልፄው ቢነግሩት፤ ማሳካቱን ቢቆጣጠሩት መልካም ይሆናል። በስተቀር ግን የናቁት ይወርሳል ይላሉ ቅኔኞቹ ጎንደሮች።
ትናንት ባልተደከመበት መስክ የሎሬት ሽልማት ያስገኜው ዕድል ቁሞ አይጠብቅም። መፍጠን የሚያስፈልገው እራስን ለማረምም ጭምር ሊሆን ይገባል። ፍጽምናን የሙጥኝ ማለቱ ጠቃሚ ጎዳና አይደለምና። ምሳሌ ላንሳ መሰል ………
1) አዲስ አበባ "የማትፈለግ፤ ያነሰች፤ የማትጠቅም ከተማ እናረጋታለን" መባሉን አቶ ሽመልስ አብዲሳ ነገሩን። ከሁለት ተከፈለች። የዳበረው ልምድ፤ ትውፊት፤ ታሪክ እና ባህልም #ተገመሰ - ተነቀለ። ሸገር እንደ አዲስ አበባ በከንቲባ እንድትተዳደር ሆነ። በአንድ ከተማ ሁለት ከንቲባ። የአዲስ አበባም የሸገርም ከንቲባ የኦሮሞ ሊቃናት ናቸው። የሚያሳዝነው አዲስ አበባ እንደ ድፎ ዳቦ ስትቆረስ ነዋሪው ሳይመክርበት፤ ሳይነጋገር በአንድ ምሽት "አንተ ሸገር ነህ" ተባለ።
2) አገራዊ ምክክር በብዙ ወጪ፤ በብዙ ድካም፤ በብዙ ልፋት፤ ብዙ የመንፈስ፤ የመዋለ ንዋይ የጊዜ ሁኔታ ተገብሮበት በነሃሴ ፲፮ ተፈጠመ። በርቀት እኔ ስታዘበው የነበረው ሂደት ነበር። 4000 ተሳታፊወች ነበሩ። የፈለጉትን አዲስ አበባን በኦሮምያ የመጠቅለል ምኞት 4000 ተሳታፊ ከነፍሱ ጋር ስለተያያዘችው የራሱ ህብራዊ መጠሪያ አዲስ አበባን ለአንድ ዞግ #ለመሸለም አልፈቀደም።
3) እራሱ ለውሳኔ ሃሳብ የቀረበው አዲስ አበባ "የፌድራሉ ወይንስ የኦሮምያ " ተብሎ ነው። አዲስ አበባ #የክልል፤ አዲስ አበባ #ራስገዝ ደረጃ ይሰጣት የሚለው አስቀድመው ሰረዙት። 4000 ታዳሚ የፌድራል የሚለውን እንዲቀበል ተገደደ። በካድሬወቻቸውም አስቀድመው አስነግረዋል - ለፌድራል ተጠሪ ትሁን የሚለውን።
ከዛ ምን ሆነ? ከዛማ #የተጣላ ወይንም ግጭት የናጠው አመክንዮ ሳይኖር #አሸማጋይ የሚል ቁሮ አዲስ #ልጥፍ ተቀየሰ። እሱንም 4000 ተሳታፊ አሻም አለ። አልፈርምበትም አለ።
ሁሉም የብልጽግና ምኞት ተሳክቶ አንዲት ነገር #ተሸርፋ እንድትቀር አልተፈቀደም። ይህንን ሊያስረዱ ይገባል ፕሮፌሰር ብርኃኑ ነጋ ለጠቅላይ ሚ;ር አብይአህመድ።
#ይቅርብኝ የምትለው አመክንዮ ሊኖር ይገባል። ሹመቱ ላይ የዴሞክራሲ ግንባታ ይላል፤ አብዝኃኛው ሳይሆን ሙሉ ድምጽ ለመቀበል ብልፄው ፈቃደኛ አይደለም። መጠቅለል፤ መጨፍለቅ መዳጥ ነው የሚፈለገው።
ይህ በሆነ ማግሥት ለስልት ኦሮምያ ብቻውን ተለይቶ ምስራቅ፤ ምዕራብ ማዕከላዊ ወዘተ በሚል ፮ዋና ዋና ዞኖችን እራሱን አደራጄ።
1) የሸገሩ ርዕሰ መዲና #አዲስ አበባ፤
2) የኦሮምያ ማዕከል አዲስ አበባ፤
3) የማዕከላዊው የኦሮምያ ዞን መቀመጫ ደግሞ ሸገር። ሁሉም አይቀርም። የውጭ አገር ኢትዮጵያን ቢወር ከሚፈጽመው የሚተካከል ሂደት ነው እኔ የማስተውለው። የምታዘበውም።
ህወሃት ሥልጣን ከያዘ ጀምሮ እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ አማራም ጉራጌም የአዲስ አበባ ከንቲባ ሆነው አያውቁም ወደፊትም አይሳካም።
ብልፄው ሳይጎዳ፤ እንደ ነገሩን የገዳ አመራር ምንም ኪሳራ ሳይደርስበት፤ ሌላው ይተባበር፤ ጥያቄ ይሳካል ወይ???? ችግሩ ይሄ ነው።
በጣም በምሬት የአማራ አክቲቢስቶች ሲናገሩ አዳምጫለሁኝ። ኢትዮጵያን አግልለው አይደለም። ከፍቷቸው ነው።
በአመራር ይሁን በአደረጃጀት፤ በዳኝነት ይሁን በፍትህ ትርጓሜ እና አፈፃጸም #ሚዛን አልቦሽነት ለለት ቢደላም፤ አድሮ ውሎ ግን አናርኪዝም ይፈጥራል። አናርኪዝም አስፈሪ ሱናሜ ነው።
በሌላ በኩል ሲከር መበጠሱ፤ ሲሞላም መፍሰሱም አይቀሬ ነው። ይህን ዕውነት ያጎሉ ሊቃናት የሹመት ተንሳፋፊነት፤ ዲል ያለ ቅጣት ገጥሟቸዋል። በዚህም ከታለፋም ዕድለኞች ናቸው። ሰማዕትነት፤ መሰወር ወይንም ካቴና ካልገጠማቸው። ፈቅዶ ጠቅላይ ሚር ዕድሉን አልፈልግም ብሎ ለራሱ ቀራንዮ የፈቀደ፤ ጥቅሙን የሚፃረር ተጠቃሚ ቢኖር የአማራ የፖለቲካ ሊቃናት ናቸው።
የሰሞናቱ በሹመቱ ስብጥር የተንሳፋፊ ሹመኞች ጉዳይ፤ የተገለለው የተዋህዶ ሃይማኖት፤ ከቁጥር ያልገባው የማህበረሰብ አቅም እንደምን ሊያዋጣ ይችላል?
በጣም ከባዱ ገጠመኝ የህዝብ ልቦና፤ ህሊና #ሲሸፍት ነው። የህሊና ዝምተኛ ሽፍትነት አይታይም። ለምን? ዝምታ ስለነገሰ። ዝምታ ከጩኽት በላይ ልዩ አቅምም ክህሎትም አለው። የሰሞኑ የኢትዮጵያ መከላከያ የዝምታ ጉዞ የሚደንቅ ነበር። ፍላጎቱን በዝምታ በመጨመት እያሳካም ነው። የዝምታ አቅም ከፕሮፖጋንዳ በላይ ነውና።
"ጥምዶ" የሚባል መዋቅር ሲመጣ #ብልፄያውያን ተረባብሸው ነበር። እኔ ፃፍኩ። ጥምዶ #አስፈሪ ተቋም አይደለም። የህውሃት ተመልሶ ሥልጣነ - መንበሩን መያዝም ጨረቃ ጸሐይን፤ ጸሐይ ጨረቃን የመተካካት ያህል ነው። በምንም ታምር፤ ፈጽሞም ህወሃት ወደ ማዕከላዊ መንግሥት ጠቅላይነት መንበረ - ሥልጣኑን፤ የኢትዮጵያን የመረከብ ዕድል አይኖረውም ብዬ ፃፍኩኝ። ዕድሉ አልቆበታል። ተጠናቋል። እማምንበት ዕውነት ነው። ተኝተው የማይጠብቁ ልጆች ኢትዮጵያ --- አላትና። ተደማጭም።
ይልቅ ለብልፄ የሚያሰጋው የዕየለቱ የቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ #ሰማዕትነት ነው ብዬም አበክሬ ፃፍኩኝ። ዕንባው የእዮርን በር የማንኳኳት፤ ይሁን የማስከፋት አቅም አለው ብዬ ስለማምን። እርግጥ ነው ዶር. ዮናስ ብሩ የኢኮኖሚ ችግር በራሱ ሥርዓቱን ሊያስወግድ ይችላል ብለው ያምናሉ። አሁን በተዋህዶ ጉዳይም እየሠሩበት ይገኛሉ።
ሌላው የፖለቲካ እስረኞች ጉዳይ፤ የአማራ ህዝብ የፖለቲካ ውክልና ጉዳይ፤ የአማራ ህዝብ ከክልሉ ውጪ የመኖር ዋስትናው ጉዳይ፤ የአዲስ አበባ የዜጎቿ የመሆን ጉዳይ፤ የተዋህዶ መገፋት - መገለል፤ በአማራ ክልል ለሁሉም ውክልና ተሰጥቶ፤ አማራ ግን ተነቃይ የመሆኑ ጉዳይ ……… አማራን አርቆ የማየት፤ አቅልሎም የማየት ኩነት ………
የወልቃይት፤ የጠገዴ፤ የአዳርቃይ፤ የማይጠምሪ፤ የጠለምት፤ የራያ መከራን የመጠናቀቅ ጉዳይ ወዘተ መልስ የለም። ሲዳማ ሳይጠይቅ ሲደረግለት ለኦህዴድ መንበርን የማግኜት ዕድል በር ከፋቹ፤ ሁሉንም የሰጠ አማራ ግን መገፋቱ፤ ጫናው መበራከት ቀጥሏል።
ይህን ነው ፕሮፎሰር ብርሃኑ ነጋ ለሚያምኑበት መንግሥት ነግረው #ሚዛኑን ማስጠበቅ የሚኖርባቸው። ለኦህዴድ ያልተደረገለት፤ ያልተሰጠው ምንም ነገር የለም። #እርካታ ግን የለውም።
ሁልጊዜ በሙላት፤ ሁልጊዜ በአሸናፊነት ልዘናከት ነው የሚለው ብልፄው። ይሉኝታ የሚባል ኢትዮጵያዊ የህሊና ህግ ለማህበረ - ኦነግ ፖለቲካ ምንም ነው። የአማራ ህዝብ ሙሉ ድምጹን የሰጠበት የመጋቢት 18/2010ዓም ብቻ በቂ ነበር። ከቋያ መሰስ አድርጎ እጁን ይዞ ያወጣ መንፈስ #ተቀጠቀጠ። ሙግቱ ከባድ ስለነበር የአማራ ልጆች ይለፍ ያንጊዜ ባይሰጡ ዕድሉ ልሙጥ ይሆን ነበር።
ይህ ደግሞ ሁልጊዜ አይሆንም። ይደክማል። ሰሞኑን ብልፄ በዲፕሎማሲው ዘርፍ #አሸናፊ ሆኖ በየአቅጣጫው የምሥራች ዜና እያዳመጠ ነው። ከሉዓላዊነት አንፃር ሸጋ ነው። ቋሚ ግን ላይሆን ይችላል።
ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ሲመጡ ዓለም እኮ አጀንዳው ይህ ነበር። ሁሉ ነገር ለአብይዝም ሰገደ፤ አደገደገ። ያ ተቀይሮ ህውሃት ውጊያ ሲጀምር አብይዝም #ዓይንህ ላፈር ተባለ። አባ ቅንዬ አማራ እንደ ልማዱ ሁሉንም ሰጥቶ ለተንገዳገደው ብልፄው ምሰሶ እና ማገር ሆነው። ግን ተካደ።
ጉዳዬ ክደቱ አይደለም። የአሁኑ የአብይዝም የዲፕሎማሲ ሙሉ ድጋፍ፤ ነገ ምን ሊገጥመው እንደሚችል መተንበይ አይቻልም። ለዚህ ነው እኔ ደስታን መጥኖ መያዝ፤ ደስታን በቅጡ ሳያንጠራሩ መያዝ አስፈላጊነት አበክሬ የምገልጸው።
ከላይ ለማስታወስ እንደሞከርኩት በምሬት የሚናገሩ የአማራ ልጆች ኢትዮጵያን ጠልተው አይመስለኝም። መገፋት፤ መገለል፤ #መናቅ፤ ሰሚ ማጣት ሃሞት ስለሆነባቸው ነው።
ገፊ ምክንያቱን በአስቸኳይ ተጠንቶ፤ የመፍትሄ ሃሳብ አመንጭቶ የአጭር ጊዜ፤ የመካከለኛ ጊዜ የረጅም ጊዜ ትልም ተነድፎ፤ ሥራ ላይ ሊውል ይገባል። የአማራ ህዝብ ተገፍቷል። ተበድሏል። ተጎድቷል። #ተርቋል። ይህን ሚዛን ማስጠበቅ የብልፄ አማኞች፤ ደጋፊወች እና ረዳቶች ሊሆን ይገባል። አማራን በቅንነት የማየት ሥልጣኔ ሊኖር ይገባል።
ህወሃት 100% ዴሞክራሲያዊ ምርጫ አሸነፈ ተብሎ ነበር። ታላላቅ የዓለም ፖለቲከኞችም ተናግረውት ነበር። ግን የምርጫ ዘመኑ
ሳይጠናቀ ፈቅዶ ተሰናበተ። መንበሩ ከለቀቀ በኋላም የማይድን #ጠቃጠቆ ሙከራውም ቀን አላወጣውም። ታች ላይ እንዲገኝ ተገዷል አይዋ ህወሃት።
አስተማማኙ ከውስጣችን ድርስ የሚል የተግባር ቋጠሮ ብቻ ነው። ግን ጠቅላይ ሚ/ር አብይ አህመድ ስለ አማራ መስማት፤ ማሰብ፤ የእኔ ብሎ ከውስጥ ማየት ይችሉበታልን??? በዚህው ይከወን።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
15/10/026.
ፍቅር ሲያልቅ ትዕግሥት ይሰደዳል።
ትዕግሥት ሲያልቅም ፍቅር ይሰደዳል።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ