ግን የት ደረሰ?

 

"ኑ አገራችሁን ግቡ።" ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ። "ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ ነን።" ግን የት ደረሰ?
 
"ቀን የሚያመጣውን ምን እንደሆነ
አታውቅምና ነገ በሚሆነው አትመካ።"
(መጽሐፈ ምሳሌ ምዕራፍ ፳፯ ቁጥር ፩)
 
#ምዕራፍ ፲፱።
 
"ኑ አገራችሁን ግቡ። #ስንኖር ኢትዮጵያዊ፤ #ስንሞት ኢትዮጵያ" በምልሰት የሚጠይቅ አገላለጽ ነው። ብለህ ነበር፤ ያልከው ሆኖን፤ ምን አሳካህ፤ ምንስ አጎደልክ የሚል የህሊና ሙግት ጋር እራስን #ያገጣጥማል
 
ስንኙ - ያማልላል። ውስጥን - ይደላል። ግን ገቢር ላይ ተፈትኖ የወደቀ ጽንሰ ሐሳብ ነው። በውስጡ የሌለ ጭብጥ ዕውንነቱ ከመፈጠሩ በፊት #ክስመቱን ስለሚያውጅ።
 
ቀድሞ ነገር ኢትዮጵያ #የማን ናት?
ኢትዮጵያን #የሚያዝባትስ ማነው?
ለኢትዮጵያዊነት ዜግነት ሰጩ፤ #ነሹስ ማን ነው?
#ኢትዮጵያዊነት በገብያ ንግድስ ይተዳደራልን?
 
የገዘፋ ጥያቄወችን በዚህ ዙሪያ በብዙ ማንሳት ይቻላል። መላሽ ካገኙ። እንደ እኔ እምነት ኢትዮጵያዊነት በገብያ ህግ ሊተደደር አይችልም።
ኢትዮጵያም የኢትዮጵውያን ናት። ኢትዮጵያን የሚያዛት፤ መታዘዝ ካለባት ህዝቧ ብቻ እንጂ አንድ የፖለቲካ ድርጅት ወይንም፤ አንድ ዞግ ሊሆን አይችልም። 
 
ለኢትዮጵያ ዜግነት ሰጩም ነሹም፤ ውጡ ግቡም ብሎ የመበየን የአንድ የፖለቲካ ድርጅት መሪ ሥልጣን በፍጹም አይደለም። ሊሆንም አይችልም። 
 
በማንነት ጉዳይ የሚሰጠው ብይን የግንዛቤ እጥረት ወይንም አቃሎ የማየት፤ ወይንም የውስጥ ቀውስን ለማስታገስ ካልሆነ በስተቀር የማንነት ጉዳይ አገር፤ አህጉር፤ ሉላዊ በሆነ መንፈስ ስናዬው ለሰው ልጅ የተሰጠው የነፃነት መንበር፣ ላዕላይ የሆነ የክብሩ መገለጫ፣ ረቂቅ ሚስጢር የሚዋቀረው በጽንሰቱ ቅጽበት ነው። 
 
አገር ግንባታ፤ አህጉራዊ አወቃቀር፤ ሉላዊ ሁነት የሚነሳው ከአንድ ግለሰብ መፈጠር ጋር አህዱ ብሎ የሚጀምር የመሠረት ፍሬ ነገር ነው።
ሰው ከሌለ የሰማይ የምድር፤ የአገር የአህጉር፤ የዓለም አፈጣጠር፤ የሁሉም ዓይነት የዕውቀት ዘርፎች #አውታር አልቦሽ ይሆናሉ።
ስለዚህ በሰው ልጅ የመፈጠር ነፃነት፤ የመኖር መብት ድፍረት ካልሆነ በስተቀር አንድ የአገር መሪ፤ አንድ የፖለቲካ ድርጅት የሚበይነው ጉዳይ አይደለም። ሊሆንም አይችልም።
 
ልሁን ቢልም አመክንዮው በራሱ ካለልኩ የተሰፋ ጥብቆ ወይንም #ልቅ ቦላሌ ይሆናል። እርግጥ ነው የሰው ልጅ ሥርዓት ካልተመቸው፤ መኖሩ ስጋት ላይ ከወደቀ አገር ለቆ ሊሰደድ ይችላል። ይህም የራስ ውሳኔን የሚጠይቅ እንጂ የአንድ የፖለቲካ ድርጅትን ፈቃድ ወይንም ይሁንታ ሊጠይቅ የማይችል ጉዳይ ነው።
 
አገር መስጠት ወይንም አገርን መንሳት ከግልሰብ ሥልጣን #በላይ ነው። ለነገሩ "ሙቱልን፤ #ቅበሩን አትበሉ" የሚል ደፋር ትልልፍን በዝምታ ላየው የብልጽግና ፓርቲ አገር፤ ማንነት፤ ዜግነት የሚለው የሁለመና ማዕከላዊ ጉዳይ አዛዥ ናዛዥ እኔ ነኝ ብሎ ሊያስብ ይችላል።
እያለም ያለው ይህን ነው። በዜግነት እኩልነት ደረጃ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ እና ከአንድ ዜጋ የበለጠም ያነሰም መብት የላቸውም።
 
ይህም ሆኖ በህወሃት የተከፋ፤ የተገፋ፤ የተንገላቱ፤ የተሰደዱ፣ ጫካ የገቡ፣ ሁለት ጊዜ ሞት የተፈረደባቸው፤ ህወሃት ፈቅዶ መንበረ ስልጣኑን ሲያስረክብ፤ ደስ ብሏቸው ወደውም አገራቸው ገብተዋል። 
 
መሬታቸውን ጉንብስ ብለው ተሳልመዋል። እናት እና ልጅ በሲቃ አጋፋሪነት ፍንሽንሽ ብለዋል። ፈክተዋል። አብበዋል። ያም የአንድ ሰው ስጦታ አልነበረም። በማይመረመር ስልጣኑ #የፈጣሪ ታምር የተገለጠበት የገድል ጊዜ ነበር። አቀባበሉ ላብዛኛው የከበረ፤ ለጥቂቶች ግለት የነበረበት ነበር። በጥቅሉ ግን መልካም ነገሩ ያመዝናል። 
 
"ያ ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ፤ ኢትዮጵያዊነት ሱሴ ነው" በሚሉ አገላለፆች አምነው አገራቸው የገቡ፤ እዛም የሚኖሩ፤ እየተመላለሱም ያሉ እናያለን፤ እንሰማለን።
 
ከገቡት ውስጥ ማን በህይወት ቀጠለ? ማንስ ባልታወቀ የመብት ቅርቅር ሁኔታ ይኖራል? ይህን ከፈጣሪ በስተቀር የተጣራ መረጃ የለም። በስማ በለው፣ በራሳችን ጥርጣሬ ይህ ይሆናል ልንል እንችላለን።
 
አገር ከገቡት ውስጥ ጋዜጠኛ ደምስ በለጠ፤ ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ወይሳ፤ በሥጋ "#በድንገተኛ" ተለይተዋል። አቶ ኦባንግ ሜቶ፤ አቶ ክንፋ አሰፋ፤ ዶር ኮንቴ ሙሳ፤ ኮነሬል ጎሹ ወልዴ ወዘተ አገር መግባታቸውን ሰማን፤ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ስለ እነሱ መረጃ የለንም።
 
ከዚህ አንፃር ከሆነ ብልፄው የአገር ሰጪነት እና ነሺነት አይቶት ከሆነ መብቱ ባይሆንም ባለሥልጣኑ እሱ ስለሆነ #በደህንነት ዙሪያ ዋስትና ከመስጠት እና ከመንሳት አንፃር አንፃራዊ የሆነ የሥልጣን ሁነት ሊኖረው ይችላል።
 
ያው እሱን አምኖ ለሚሄድ ጥበቃ እንደ መደበ ቀደም ባለው ጊዜ አደምጥ ነበር። ከዚህ ባሻገር በማንነት የዜግነት ክብረ ውሳኔ ሥልጣኑ የግለሰብ ወይንም የአንድ ሊቅ ጉዳይ ሳይሆን #የባለቤቱ ነው። ዜጋ ነኝ - ኢትዮጵያዊ ነኝ። አገሬ ኢትዮጵያ ናት ለሚል ሁሉ ብይኑ የባለቤቱ ነው። ይህ ሊታወቅ ይገባል።
 
እርግጥ ነው ያዬነው ነገር አለ። የሃይማኖት አቨው ጳጳሳት ሳይቀር፤ የዕድሜ ዘመን ፖለቲከኛን ጨምሮ አገር ለመግባት አስበው #የማገድ ሁነት ነበር። ይህ የተገባ አይደለም። ትርታችን፤ ህቅታችን፤ ሩኃችን አዛዥ አለባት ከተባለ #ፈጣሪ ብቻ ነው። ዕምነት ሃይማኖት ላለን።
ስንሰደድ ግን ለመኖራችን ፈቃዱ የተሰደድንበት አገር ህግ እና ድንጋጌ በሚፈቅደው ልክ ይሆናል። 
 
በአገራችን ግን አገር የመግባት፤ በአገር የመኖር፤ በአገር ኢንቤስት የማድረግ፤ በተመላላሽነት የአኗኗር ዘይቤ የመኖር ባህልን በሚመለከት በኢትዮጵያዊነት ዜግነት ያለ ሙሉ #መብታችን ነው። ኢትዮጵያዊ ዜግነታችን ሰጪም፤ ነሽም የግለሰብ ጉዳይ አይደለም። 
 
ከኢትዮጵያዊ #ደም ሐረግ ስንጠነሰስ ቅጽበት ጀምሮ የተሰጠን ነው። ኢትዮጵያም ተወለድን፤ ውጭም ተወለዱ። ግዴታም አለብን። በአገራችን ሉዓላዊ ክብርና ማንነት ዙሪያ ስንቀሳቀስ ህግ አክባሪነትን መፈጸም ይገባናል። መብት ካለ ግዴታም ይኖራል። ይህን መቀበል ያስፈልጋል።
 
ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ፤ ከሙስና ጋር በተያያዘ፤ ከወንጀል ጋር በተያያዘ ጉዳይ ስጋትም፤ ፍርሃትም፤ ጭንቀትም ይኖራል። ይህ አይኖርም ዋስትና እሰጣለሁ #ብልፄ ሊል ከቻለ ያስማማል። 
 
ከዚህ በዘለለ የአገር ባለቤትነት፤ የዜግነት ክብር እና ልዕልና ስፈጠር የተሰጠኝ ሙሉ መብት እና ብቸኛው ነፃነቴ ነው። ማንም በማንቆርቆሪያ በብርሌ #አንቆርቁሮ የሚሰጠኝም፤ የሚነሳኝም ሊሆን አይችልም።
 
በጋራ አመራር የሚያምን የፖለቲካ ድርጅት ቢያንስ የወላዊ መሻትን ያካትታል። በብልፄው ግን ኢትዮጵያ ተጠቅልላ ያለችው በአንድ ሰው ህሊና ውስጥ ብቻ ስለሆነ፤ ከዜግነት ማንነት፤ ከአገራዊነት ማንነት ጋር በተያያዘ የሚሊዮኖች መብት #ተኮርኩዶ የሚከዘንበት ምንም የመርኽ፤ የህግ አግባብ የለውም። ከዚህ አንፃር ጉዳዩን ሰፋ አድርጎ ማየት ይገባል። መሪ እኮ ጌታ ሳይሆን የህዝብ አገልጋይ እኮ ነው።
#የ2010 ወርኃ መጋቢትን ድባብ የመናፈቅ።
 
በነባሩ ፓርላማው ስንብት ላይ የቀደመውን የአብይዝም የሚሊዮኖች ድምጽነት የመናፈቅ ስሜቱን ያዳመጥኩ ይመስለኛል። ኢህአፓ የቅንጅት መንፈስን ለመፍጠር ሞካክሯል።
 
ጊዜ ይፈሳል። ዕድልም ጥሩ ማኔጅመንት ካጣ ይፈሳል። በፍጹም ያን ልዩ ክስተታዊ ጊዜ አይደለም በውን በህልምም ማግኜት አይቻልም። #ኦርጋኒክ፣ የተሰጠው - የተመረቀ - የተባረከ ነበር። ፈጣሪ ህወሃትን በፍቃዱ ሲያሰናብት ሥጦታውን አሟልቶ ነበር።
 
ሺህ ካድሬ፤ ሚሊዮን ፕሮፖጋንዲስት ያልተሰለፉበት ለቀኑ ቀኑ ፈቅዶለት ለጥቂት ቀናትም ቢሆን ለኢትዮጵያ እናቶች ዕንባን በማስቆም እረገድ ለምንባትለው ሳይቀር #እፎይታን የሰጠ #አልማዛዊ ጊዜ ነበር። የፍቅር ተፈጥሮ፤ የመታመን ተፈጥሮ፤ የቅንነት ተፈጥሮ ብቁ አስተዳዳሪ ካላገኜ ያመልጣል። አምልጧል--- ም።
 
ይልቅ አሁን ባለው ዕድል "ላም እረኛ ምን አለን" ማድመጡ ቢፈቀድ የፈሰሰ - ባይታፈስ፤ የሞተ - ባይመለስ ለዛሬ ለቀኑ የውስጥ ሰላምን ማጽናት፤ ለዛም መትጋት ቀና ጎዳና ይመስለኛል። 
 
1) ካለሰብዓዊነት መዋቅር ፋይዳው እምብዛ ነው።
2) ካለ አጽናኝነት የላይኛው ምርቃን አይቀጥልም።
3) ካለ አይዟችሁ ባይነት ነገን ማግኜት አይቻልም። 
 
መታመን በከንፈር ብቻ ሳይሆን ሆኖ መገኜትን አጥብቆ ይሻል። አሁንም ወደ አገር የሚያስቡ፤ ወጣ ገባ የሚሉ ሚዲያ ላይ ሁሉ የውስጣቸውን ስሜት በጉልህ ለመግለጽ ስጋት ያለባቸው ወገኖች አሉ። 
 
ቢያንስ ይህ ስጋት እንዳይኖር የተደራጄ ተግባር ይጠይቅ ይመስለኛል። አገርን መናፈቅ ወንጀል አይደለም እና። ስለ አገር መቆርቆርም እንዲሁ።
 
ውዶቹ ክብሮቹ ቤተ - ሥርጉትሻ እንደም ዋላችሁልኝ። በጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ የፓርላማ ውሎ ላይ ሦስት ጉዳዮች ከውስጤ የገቡትን አጠናቅቄያለሁኝ።
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
16/07/026.
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።