#እነማንን ይሆን የሚል ጥያቄ ያስነሳል።
#ምዕራፍ ፲፱።
(መጸሐፈ እዮብ ምዕራፍ ፲፪ ቁጥር ከ ፯ - ፰።)

እንዴት ዋላችሁልኝ ክብሮቼ። እኔ አምላኬ ክብሩ ይስፋ ደህና ነኝ።
ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ የፓርላማው መደምደሚያ ቀን በንግግራቸው ማጠናቀቂያ ይህን ተናግረዋል። እርዕስ ያደረኩትን። ሃሳቡ ጥሩ ነው። ሃሳቡ ጥራት እና ብቃት ያለው ትውልድን ከዘመን ወደ ዘመን በተፈጥሮ ድልድይ ሊያሸጋገር የሚችል ነው።
"ሆደ ሰፊ እንሁን።" የወል ጉዳይ ነው --- አገላለጹ። #እነማንን ይሆን የሚል ጥያቄ ያስነሳል። ከሳቸው በተጨማሪ ማን እነማንን ይመለከታል። እነማንንስ ያካትታል? ሌላው #ከመቼ ጀምሮ የሚል ተከታይ ጥያቄም ያስነሳል።
የውሳኔው ተፈፃሚነት፤ የሳቸው ቃል ከተነገረበት ቅጽበት ጀምሮ፤ ወይንስ በቀጠሮ? በአሳቻ ቀንና ወር ይሆን? የሚልም ሌላ ጥያቄ ያስነሳል። በሌላ በኩል አስበውበት መጥተዋል ለማለትም የማያስደፍር ዕውነት አለ።
አንድ የፓርላማ አባል ጥያቄ ሲያቀርቡ በቀደመው የመከፋት ድባብ ውስጥ ሆነው ሲያዳምጡ አይቻለሁኝ። ጥያቄ አቅራቢውን ማየት አልፈቀዱም። በልቤ ዛሬ በመሰነባበቻ ቀን እንኳን ያለውን ነገር ቻል አድርጉ ለማሳለፍ ስለምን አቃታቸው። እያልኩ ይህን ሳስብ መጨረሻ መልሶች ከሰጡ በኋላ፤ አስቀጥለው " ጀግና፤ አብረን እንስራ፤ #ሆደ ሰፊ እንሁን" ሌላም አለ እምጽፍበት የሚሉ ኃይለ ሐረጋት ወይንም ሥንኛት የተናገሩት።
በዘመነ ህወሃት በተለይ ከጠቅላይ ሚር መለስ ዜናዊ በሥጋ ከመለዬት በኋላ፤ የህወሃት ማዕከላዊ አመራር እክል ገጥሞት ነበር። ሊቃናቱ በተናጠል የማድረግ አቅም በነፍስ ወከፍ እንደ ነበረ የሚያመላክቱ ሁነቶች ነበሩ።
ለምሳሌ የአቶ አባይ ወልዱ አማራ ክልል ገብተው የከፈቱት ጦርነት፤ አቦይ ስብኃት ነጋ፤ ወይዘሮ አዜብ መስፍን፤ አቶ በረከት ስምዖን፤ አንባሳደር ስዩም መስፍን፤ አቶ ጌታቸው አሰፋ የፈቀዱትን የመፈጸም የማስፈጸም አቅም ነበራቸው። ጄኒራል ሳሞራ ዮንስም እዛው ላይ በሰው ህይወት ወስነው እርምጃ ይወስዱ እንደ ነበር ሰሞኑን አንድ ቃለ ምልልስ ሳደምጥ ነበር። አዬ የኢትዮጵያ ህዝብ?
አሁን ይህ ኃይል ቃል ያን ጊዜ "ሆደ ሰፊ እንሁ - #ን" በወላዊ ውሳኔ ደረጃ ቢናገረው ህወሃትሻ ያምርበታል። ምክንያቱም በተናጠል አቅም ያለው የመወሰን፤ የማድረግም ሁኔታ ስለነበር።
#በብልፄው ይህን መሰል ተረብ የለም።
ብልፄው አንድ ሰው ያስባል፤ በአንድ ሰው ውሳኔ ይሰጥበታል። የተወሰነባቸው አመክንዮወች ሲቀናቸው ለፎርማሊቲ በፌድሬሽን ምክር ቤት፤ በፓርላማ፤ በብልፄው ሥራ አሥፈፃሚ፤ በካቢኔው የዕወቁት ሴሪሞኒ ይፈጸማል። ብልፄው ካላስፈለገው በእንደ ልቡነት ይከውነዋል።
ከዛ ባለፈ ከጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አንደበት፤ ዕሳቤ፤ ራዕይና ግብ ውጪ ማን #ምን አቅም አለው? ማን #ምን የማድረግ ችሎታ አለው? ማን በእርግጠኝነት ከሳቸው ውሳኔ ውጭ ተላልፎ፤ በፍላጎቱ የራሱን ኃላፊነት እና ተጠያቂነት ይወጣል? የሚለውን መልሱ ማንም ምንም መብት እንደሌለው ሂደቱ ይናገራል።
ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ለመጠየቅ እንኳን ፈቃደኛ አይደሉም። የጋዜጠኞች ኮንፍረንስ ወደ ሰማይ ቤት ተልኳል። በሎሬት ሽልማት እንኳን ፈቃደኛ አልነበሩም።
የሆነ ሆኖ በዘንድሮ የምርጫ ክርክር ወጥ የሆነ ቢጋር ተሰርቶ ስለተሰጠ በብፄው ከፍተኛ መሪ አካላት የተከናወነውን ክርክር፤ በመደጋገም ክርክሩን ሞናትነስ ከማድረግ ውጪ ለመጪው ጊዜ ብልፄውም ምን እንዳቀደ፤ ምን ለማሻሻል እንዳሰበ እራሳቸው የብልፄ ወኪሎች አያውቁም። ለእነሱም ህሊና እንደኛው #በደራሽ ዜና ሱናሜ ነው የሚጥለቀለቁት።
የኢትዮጵያ ሙሉ ካርታ፤ ንድፍ፤ ግብ እና መዳረሻ በጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ህሊና ውስጥ ተጠንስሶ፤ ጊዜው ሲደርስ ይወለዳል። ጊዜው ካልደረሰ ተከድኖ ይቆያል። ይህ በአወንታዊው ዘርፍ ሲሆን ……
በአሉታዊው ዘርፍም ህዝብ የሚጎዳበት፤ ሳይፈልገው የሚፈጸምበት፤ ግብታዊ እርምጃወች፤ መፈናቀል እና ወዘተረፈ ችግሮች ከሆደ ሰፊነት የራቁ ስሜታዊ፤ ግብታዊ እርምጃወች ሁሉ ከጠቅላይ ሚር አብይ ዕውቀት ውጪ አንድ #ስንዝር ተራምዶ የመከወን አቅም ማንም የለውም። ለዚህም ነው የብልፄው ወኪሎች ቃል ሁልጊዜ በተለመደው የኮሪደር፤ የጫካ ሥራ ተኮር ብቻ ወጥ የሚሆነው።
ስለሆነም ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ "ሆደ ሰፊ #እንሁን" ከማለት ይልቅ፤ "ሆደ ሰፊ #እሆናለሁ።" ቢሉ እኔን ያሳምነኛል። ኃይለ ቃሉ ወደ ሌላ ከመግፋት ይልቅ "ሆደ ሰፊ ያልሆነው" ማን ነው? ለሚለው መልስ በቅድሚያ ያስፈልገዋል።
ባለፈው ከንቲባ ወሮ አዳነች አበቤ "ጉዟችን መደመር ግባችን ብልጽግና" ሲሉ ሰምቻለሁኝ። ብልፄው አልተጀመረንም ብያለሁኝ። የማይገባ ስለሆነ። አገላለጹ እራሱ የፍላጎት መጓጎልን ስለሚያሳይ።
"ብልጽግና ይባል መደመር" ሁለቱም የአንድ ሰው ንድፍ ነው። በሂደቱ ለሚገኙ ህዝበ - ጠቀም ጉዳዮች ሆነ፤ ለሚፈጸሙ ግድፈቶች ተጠያቂው የአንድ ሰው ፍልስፍና ያስከተለው ውጤት ነው።
ስለዚህ በስሜን ይሁን በደቡብ፤ በምስራቅ ይሁን በምዕራብ የጠቅላይ ሚር አብይን "ሆደ ሰፊ እንሁን" ሞቶ ስፈታትሸው ከሳቸው ውጪ ይህ ነገር የሚመለከተው ይኖራል ብዬ አላስብም።
ዓውራው ፓርቲ ብልፄ ነው። አራጊ ፈጣሪ ብልፄ ነው። አሳኪው ይሁን ድክመት #ጠም ከሆነም ያው ብልፄው ነው። ስለዚህ ተጠያቂም፤ ተመስጋኝም ብልፄ ነው። ብልፄ ይሁን መደመር ደግሞ የጠቅላይ ሚር አብይ ፈጠራ ናቸው። ስለዚህ መሰረታዊውን አመክንዮ ለሌላ አሻግሮ ከመላክ ይልቅ የብልፄም ፈጣሪ፤ የመደመር ሂደት መሥራቹ እራሳቸው ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ናቸው።
ስለሆነም "የሆደ ሰፊነት" የደም ማነስ እጥረትን ለማካካስ፤ ይህን ኃላፊነት ሊያከፋፍሉት አይችሉም። በግለሰቦች ፈጠራ፤ ተቀባይነት፤ ትጋት፤ ዕውቅና ሳይቀር መንፈሳቸው የቤት ሥራ አለበት። የቤት ሥራውን እራሳቸው ናቸው የሰጡት ነው። ስለሆነም እሳቸው እራሳቸው ለራሳቸው #አቅል፤ #አደብ፤ ስክነት፤ መረጋጋትን መፍቀድ ይኖርባቸዋል ባይ ነኝ።
ሆደ ሰፊነት ባለ አደብነት መሆንን ይጠይቃል። ሙዚቃ፤ ፊልም፤ ቲያትር አዲስ ሲወጣ፤ ተወዳጅ ሲሆን እንኳን ቅጽበታዊ፤ ስሜታዊ መሆን የተባጀበት ጉዳይ ነው። ይቆማል። በስምንት ዓመት ውስጥ አንድ ተጽዕኖ ፈጣሪ ነው የተፈጠሩት። በአባዬ ጉዳይ። የፓርላማም አባል ነበሩ። አዛውንት ትውፊት፤ ታሪክ፤ ይተባህል አይፈልጉም።
#አዛውንት ሊቃናትን፤ ሊሂቃንንም አይሹም። በዚህ ውስጥ የአመራር ተከታታይነት ግሎባል መርኽ አድራሻ ቢስ ነው። መነሻ አልባ እሳቸው ከዚህ አልደረሱምና። አገር እየመሩ ይህ ጉዳይ ፈተናው ለራስ የሰብዕና አገነባብ፤ የመታመን አቅም መሠረት ጣይ ነው።ወይንም መሠረት ናጂ። አቅም ላቅ ብሎ ሊፈጠር አይፈቀድለትም። ካለም ይከረከማል። በተለይ ባለ አቅሙ ተባዕት ከሆነ። በአንስት ላይ እምብዛም ጫና የለም። ለራስ ከመሳሳት፤ እራስን ከመናፈቅ የሚመነጭ ይመስለኛል።
"#ሆደ ሰፊነት" በዘመናቸው ከመቼ ይጀመር?
"ሆደ ሰፊነት።" የሚመለከተው በቀጥታ ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድን የሚመለከት ነው ብዬ አምናለሁኝ። ከሳቸው በላይ ማንም የለም። ከሳቸው በታችም ማንም የለም። ብዙ መዋቅር ፋዬዳው እንቤዛም ነው። ቱሪዝም፤ ኮንስትራክሽን፤ ደን፤ ወዘተ ……
ከዚህ ቀጥሎ የሚመጣው በኽረ ጥያቄ ከመቼ ጀምሮ የሚል ይሆናል። ቃሉን #ካወጡበት ደቂቃ ጀምሮ ለማለት አልችልም። ምክንያቱም ሰሞኑን እሳቸው የደብረማርቆስን አውሮፕላን ማረፊያ መርቀው፤ የተናገሩት ነገር የእሳቸውን "የሆደ ሰፊነት" ምኞት የፈተነ ነበር። ይህም ብቻ ሳይሆን በዘመናት ይሉኝታ በሚባለው ልዩ ድንጋጌያችን በመቻቻል ድባብ፤ በሆደ ሰፊነት የላቀ አቅም ኢትዮጵያ እንደ አገር ቀጥላ እሳቸው መሪ እንዲሆኑ ያስቻለውን ትልቅ ትውፊት ጋር ንግግራቸው መስማማት አልቻለም። ውስጤም አዝኗል።
በውህድ ማንነት ውስጥ ለስላሳው ጠረን ማስቀጠል፤ የኢትዮጵያ መሪ መብት ብቻ ሳይሆን ግዴታ ነው። "ተፈቅዶ ተለያዩልኝ፤ የጥንት ነገርን አስታውሱ እና ተፈራቀቁ" ማንን ይጠቅማል? አይደለም አዲስ "የሆደ ሰፊነት" መንገድ ምህንድስና የቀደመው፤ የቆየውን ለማስቀጠል እንኳን አቅም ማነስ ታዝቤያለሁ???? ንግግሩን ስሰማ በጣም ነው የደነገጥኩት።
ከሳቸው ከራሳቸው ጋር አብረው የከተሙ የተጋሩ ልጆች እኮ አሉ። እሳቸውን በቅንነት የሚረዱ። ጡት የሚጠቡ፤ ወይንም የተጸነሱትስ? እንደ ህዝብም ተጋሩም አካል አምሳል ነው የኢትዮጵያ። ይህን ማስቀጠል ወይንስ መነጠል የቱ ይጠቅማል ለብልፄ አመራር???? ለምን ብልፄው በራሱ ለራሱ የእግር ብረት ሰንሰለት ያመርታል?
ሌላ አገራዊ ምክክሩ በብዙ ወጪ፤ በብዙ የመንፈስ ተዋፆ፤ በብዙ የተመክሮ ውጭጭ ዛሬ ጉባኤው ተከፍቷል። ዓላማው እርቅ፤ ምህረት፤ ይቅርታን ለማስፈን እንደሆነ ሲነገር ባጅቷል። ቂም፤ በቀል፤ ጥላቻን #ለመንቀል ነው የተደራጀው።
የደብረ ማርቆስ ንግግር ደግሞ በደልን ቆፍሩ እና አውጡት። ያወጣችሁትን በደል በቅሬታ አወራርዱት። ቅሬታው ደግሞ የማን ደም ፈሰሰ ወይንም ከመቃብርህ አያቁመኝ ምህላን አቅብጡት ዓይነት ነው።
እንዲህ ያሉ የማይገናኙ ምኞቶች፤ ፍላጎቶች እስከዛሬ ተቀጥተንበት፤ ከእኛ በኋላ ከተፈጠሩ አገሮች በኢኮኖሚ አቅማችን፤ በሰብአዊ መብት አያያዛችን እና አፈፃጸማችን ዝቅ ብለን መገኜታችን ዛሬ ካልጎረበጠን ለመቼ ይሆን ቀጠሮው?
በራስ መተማመን ጥሩ ነው። ልክን ጠብቆ። የሚያሳስበው ዝቅም ከፍም ሲል ነው። የፈለገ የንግግር ጥበብ ዕውቀት ይኑር የተመጠኑ፤ በተመጠኑ ልስሉስ ቃላት እና ሐረጋት የተዋቀሩ፤ እርምት የተደረገባቸው ንግግሮች ቀድሞ ማዘጋጀት በእጅጉ ያስፈልጋል። ያን በንባብ ማቅረብ ቢኖር ከዚህ መሰል #የገዘፈ ስህተት ይታደጋል።
ሌላው ሁልጊዜ መናገር፤ የአዘቦት ተናጋሪነት ያደርጋል። ይህ ደግሞ ለአንድ መሪ የተደማጭነት አቅም #ቀናሽ ይሆናል። ለዚህም የፕሮቶኮል አመራር እና አስተዳደር ቢኖር፤ መንፈስን ከሚያውኩ ትርፍ የንግግር ዘይቤወች መቆጠብ ይቻላል።
በቀል ሊናፈቅ --- ሊጠራ አይገባም።
ቂም ----- የትዝታ አንባር ሊሸለም አይገባም።
እያገላበጠ የመነጠረን ጥላቻም በተገኜው አጋጣሚ ሁሉ ተፈቅዶለት ሊመረት አይገባም። ትውልድን በጠራ ህሊና ለመገንባት በየትኛውም ሁኔታ ለሚናገሩት፤ ለሚጽፋት ልዩ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል በተለይ በመሪነት ላይ የሚገኙ የፖለቲካ ይሁን የሃይማኖት አቨወች።
#ምርቃታችን የተነሳበትን ምክንያት መርምሮ መፍትሄ ለመስጠት መፍቀድ ይገባል። መዋቅር ብቻውን ሰብአዊነት፤ ቅንነት ተፈጥሯዊነት ሊያስቀጥል አይችልም። ምግባር እና ተግባር ከመከነበቴ ሸንበቆ ይሆናል።
ከተደከመ ላይቀር አወንታዊነትን፤ ህብራዊነትን፤ ህግ አክባሪነትን ሊያበረታታ በሚችል ተግባር ላይ አቅም፤ መንፈስ ማፍሰስ ዛሬን ያሳድራል ነገንም ከጥፋት ያስምራል።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
15/07/026.
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ