ኢትዮጵያን ቁም ነገር የማድረግ ዓላማ በመሆን ውስጥ ይታያል።

 

ኢትዮጵያን ቁም ነገር የማድረግ
ዓላማ በመሆን ውስጥ ይታያል።
 
ዕለተ አርብ ዕለተ ኢትዮጵያ!
በከበቡሽ የቁራሽ እንጀራ ብራና
በሰብለ ህይወት አዝመራ
ለራህብ የሚራራ። 
 
„እግዚአብሄር የርስቴ እድል ፈንታና ጽዋዬ ነው።“
(መዝሙር ፲፭ ቁጥር ፭)
 
 
• መቅደመ ነገር።
ቅኖቹ እኔ የምጽፈው ለቅኖቹ ብቻ ነው። የሰከኑ የረጉ መንፈሶች ብቻ ናቸው የመንፈስ ኃብታቴ ስኩን ታዳሚዎች። የቁጥር ተማሪ አይደለሁም። ለቁጥር ነዶ አይደለም እኔ እምተጋው። ለጥራት ፍሬ ዘር እንጅ።
 
በሌላ በኩል ጠማማ እቃናለሁ ካለ መብቱ ነው። ውሃ በቀጠነ ካለ አቅሙ እዬመጣ የአቲካራ አርኬቡ እክፍታለሁ ካለ ግን እልፍኜን ጥሎ ወለቅ ነው። የእኔ የህይወት ፍልስፍናም አይገባውምና። በመደዴ አይደፈርም። ስለዚህ ሜዳውም ፈረሱም …
 
… እልህ ፖለቲካ አይደለም። እልህ ምቹ ያልሆነ ገረጭራጫ የገረዘዘ ድወዬ በሽታ ነው። የእኔ ዕልፍኝ የጎንድ ተክለኃይማኖት ጠበል የለውም። ምን አልባት ለተደማሪ እና ለግንቦት 7 ቅሪተ አካል እዛ ኦዳ ቤተ -መንግሥት የተከፈተ የሥነ - ልቦና ማገገሚያ አለና ብቅ ይበል … ብራናዬን ለቀቅ። 
 
• እፍታ። 
 
አዎን ይታያል። አዎን የሚታይ ነው። አዎን መልክ ቅርጽ ገጽ አቋም አለው። አዎንታዊነት መነሻው ከአዎን ነው። አዎንታዊ ሰብዕናዎች ኢትዮጵያን ቁምነገር የማድረግ ዓላማ እና ግብ ያላቸው አሉ።
 
በአስተዳደግ መበደልም ይሁን በማላውቀው ሁኔታ ሙሉ ገጸ ባህሪያቸው አሉታዊ የሆኑ ደግሞ ይገጥማሉ። አዎን የሚሉት ጥፋትን ሊሆን ይችላል። ወይንም ክፋትን። ወይንም ጦርነትን። ወይንም ግጭትን። እንደዚህ ዓይነት ሰብዕናቸው ለአገር መድካማቸውም አይቀርም። ግን ድካማቸውም የውርንጫ ድካም ነው። አልቦሽ ናቸው። በውስጥ ያለው የመቀበል፤ የማድነቅ፤ የመቻል አቅማቸው ፍግፍግ ነው።
 
ኢትዮጵያ በተፈጥሯዋ የአዎን ልዕልት ናት። ለዚህ ነው ኢትዮጵያ የአብሮነት አንባ ምድር የሆነችው። ይህን ስላችሁ አሁን ያለውን ሰው ሰራሽ ችግር ረስታችሁ አፈጣጠሯ ላይ ተነሱ እያልኩ ነው። 
 
ጀግናዬ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የኢትዮጵያን አፈጣጠር ሲገልጽ የኢትዮጵያ አፈጣጠር ኦርጋኒክ ነው ይላል። ለዚህም ነው ዘጠኙን ቅዱሳን በጸጋ ተቀብላ አክብራ ጽላቷ ያደረገችው። 
 
በእስልምናም ሃይማኖት ቢሆን በነብዬ መሃመድ ሂዱ ወደ ሃበሻዊት አገር ሰላማችሁን እዛ ታገኛለችሁ የሚል ዕድምታ በተደሞ ሲገልጹ የኢትዮጵያ አፈጣጠጠር ለተፈጥሯዊነት ሆነ ለሰዋዊነት ምቹ፤ አወንታዊ አገር ስለመሆኗ በማመሳጠር ነው።
 
ቅድስት አገር ለሁሉም ችግሩ መፍትሄዋ በመዳፏ ነው። ችግሩ በሚጠሏት፤ በሚያቃሏት እጅ መውደቋ ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያን ክብሬ የሚል፤ እኔ ኢትዮጵያኒዝም አቀንቃኝ ነኝ የሚል ሁሉ ማድረግ ያለበት ቁጥር አንድ ቁም ነገር ቢኖር „አዎንታዊነት በመሆን“ በልቡ ውስጥ ለተጻፈ ኢትዮጵያን ቁምነገር የማድረግ ዓላማ ካለው። 
 
ይህም ማለት „አዎንታዊነት የመሆን ህግ“ በልቡ ለተጻፈ ኢትዮጵያን ቁም ነገር የማድረግ ዓላማ ያለው ብቻ ነው ተግባራዊ ማድረግ የሚችለው። „አዎንታዊነት በመሆን“ ውስጥ መኖር አለ። በመኖር ውስጥም „መሆን“ አለ። በመኖር ውስጥ ያለው „መሆን“ ራሱን „መኖርን“ ለማኖር የተፈጠረ መሆኑን ያውቃል።
 
አንድ ሙሉዑ ሰብዕና ማለቴ የሞራል ስብራት የሌለበት „አዎንታዊ መሆንን“ ለማኖር በቅድሚያ „በአዎንታዊ መሆን“ ረቂቅ ምግባራዊ ስበት ውስጥ በዘላቂ ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ይጠበቅበታል። „መሆንን“ „መሆን“ የሚያደርገው „መሆን“ በዕውን „መሆንን“ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥርዓቶችን መከተል ሲቻል ብቻ ነው። ዲስፕሊኑን መሸከም። 
 
አሁን የህልውና ተጋድሎች ችግራቸው ይህ ነው። እያንዳንዱ የመኖር ክስተተ - ነገር የዬራሱ ሞራላዊ ወይንም ኢ - ሞራላዊ ሥርዓት አለው። ሞራላዊ ሥርዓት በራሱ የሚለግሰው ቁም ነገር ዓላማን ለማሰካት በክስተቱ ውስጥ ሥርዓተ አልበኝነት ወይንም ኢ - ሞራላዊነት እንዳይከሰት የሚያደርግ ጥንቁቅ ወታደሩ ነው። 
 
እርግጥ የተጻፈም// ያልተጻፈም መንግሥታዊው // መንግሥታዊ ወጋዊ ወይንም ልማዳዊ፤ ወይንም ባህላዊ // ዕሴታዊ ሊሆን ይችላል። የሃይማኖት ዶግማ እና ቀኖናም አለ። የማህበረቡ ይተባህልም አለ። 
 
አንዱ በአንዱ ላይ ተጽዕኖ ፈጣሪ እንዳይሆን ወይንም አንዱ በሌላው ላይ የክስተቱ ተፈጥሮ ጨቋኝ እንዳይሆን እንደ አፈጣጠሩ እንያንዳንዱ ክስተት በሁሉም የህግጋት ሂደቶች በውርርስ ጥሰት ሳይኖር መከወን ይኖርባቸዋል። ተፈጥሯዊ ተጓዥነት ልንለው እንችላለን።
 
ይህ ማለት እንዴት ነው? ያነሳሁት „መሆንን ማኖር“ ነው። „መሆን“ አንድ የሙሉዑ ሰብዕና ግንባታ ጥሬ ዕቃ ነው። መዋዕለ ጥሪት። ይህን ጥሬ ዕቃ ወደ ሰብዕና ግንባታ ስናመጣው „በመኖር“ ውስጥ ያሉ፤ የነበሩ ሰማያዊ ይሁኑ ሰው ሰራሽ፤ ሰማያዊ በጎ ሥርዓትን ለመከተል መፍቀድ ይኖርበታል።
 
„መሆን“ አዎንታዊ ነው። አዎንታዊ ሊሆን የሚችለው ግን „ምቀኝነት“ የሚባለውን አሉታዊ ጥላሸት የሥርዓቱን፤ የህግጋቱን፤ ድንጋጌ መጠዬፍ ሲቻል ብቻ ነው። ሥራዐቱን ስል የአገረ - መንግሥቱን እያልኩ አይደለም። እያንዳንዱ የመኖር አኗኗሪ ወይንም ተጋፊ ከስተቶች የራሳቸው ህገ - ሥርዓት ቀለል ባለ አገላለጽ ደንብ አላቸው። ያው ሥርጉትሻ ፈንገጥ ያለ ፍልስፍና ያላት ሴት ናት እና። 
 
• አዎንታዊነት መሆን ነው። 
 
ሥርዓት ሲባል ለእኔ ትክክለኛም ትክክለኛም ያልሆኑ ሥርዓተ ምግባሮች አንዳሉ ነው የሚገባኝ። ለፍቅር ሥርዓት እንዳለው ሁሉም ለጥላቻም፤ ለትዕግስት ሥርዓት እንዳለው ሁሉ ለማጣቱም አሉት ብዬ አምናለሁ። 
 
አፈጻጸም ሂደታቸው፤ ጊዜ እና ሁኔታ የሚያደርሱት ተጽዕኖ እንደ ተጠበቀ ሆኖ። ጊዜ እና ሁኔታ ስል ዘመን የሚያልፍባቸው የሥልጣኔ እርከኖችን ሁሉ ያጠቃልላል። በምልሰት ዓለም ከመፈጠሩ በፊት እና በኋላ ያሉ የመኖር ክምችቶችን ሁሉ ዘለግ አድርጎ ይዳስሳል ምልከታዬ። 
 
• ቆራጣ ምሳሌ … 
 
ጦርነት እኮ ሰው መግደል ነው። አይደል? ሰው ለመግደል ይከፈታል በሩ። ወደ በሩ ገብቶ ለማሸነፍ ሥርዓት ህግ፤ አደረጃጀጀት እና አመራር አለው። የትኛው ትክክለኛ ጦርነት የትኛው ኢ - ትክክለኛ መሆኑ አይደለም መሰረታዊ ነገር። 
 
ለምሳሌ ጣሊያን ኢትዮጵያን አጥቅታ ለመውረር ስተነሳ ትክክለኛ ያልሆነ የጦርነት ውሳኔ ነበር። ለእኛ ትክክለኛ ያልሆነው ለጣሊያን ታላቅነት ግን ጦርነቱ የተገባ ተደርጎ ስለ ተወሰደ በሥርዓት ተደራጅቶ ነው የተንቀሳቀሰው። 
 
እኛም ይህን ትክክለኛ ያልሆነ ጦርነት አስገድዶ ትክክለኝነት ማሸነፍ እንዲችል ተደራጀን። በማሸነፍ እና በመሸነፍ ውስጥ ያሉትን ትርፎች ማስላት ይገባል። 
 
ሁለቱንም የጦርነት ዓይነቶች የተማራው ደግሞ በሥርዓት ነው። ተዚህ ላይ አንድ ነገር አዎንታዊ መሆን እንዳለ ሁሉ አሉታዊ መሆንም አለ። ደንበር ጥሶ ወረራን በእብሪት ማካሄድ አሉታዊ መሆን ነው። ድንበርን አላስጥስም ብሎ መከላከል ባለፈም ማጥቃት ደግሞ „አዎንታዊ መሆን“ ነው።
 
አሁን ወደ ቀደመው ስመለስ „ምቅኝነትም“ አንደ ተፈጥሮው የራሱ ኢ - ሞራላዊ ሥርዓት አሉት። ስለዚህም „ምቀኝነትን“ አላስጠጋውም ለማለት የምቀኝነትን ኢ - ሞራላዊ ሥርዓቶችን ለማውቅ መፍቀድን፤ ሥርዓቶች የሚያመጡትን ማህበራዊ ትውፊታዊ ዕሴታዊ ቀውሶችን መረዳትን ይጠይቃል። 
 
ምቀኝነት ገዢ መሬትን ሳያገኝ ሙት መሬት ላይ እንዲቀር ማድረግ የሚቻለው „የምቀኝነትን“ ኢ - ሞራላዊ ሥርዓቶቹ የሚያስከትሉትን ቁስለቶች እና ኪሳራዎችን የእኔ ብሎ መመርምር፤ ማጥናት ግድ ሲል ብቻ ነው። ይህም ማለት በራስ ውስጥ ያሉ ህፃፆችንም ነቅሎ ለማውጣት መፍቀድን ይጠይቃል። ትልቁ የህይወት ፈተና እራሰን ማሸነፍ ነው። 
 
አብሶ ሐገራዊ ሲሆን ደግሞ ግዙፍ ንደቶችን ስለሚያስከትል አትኩሮቱ ሙሉዕ፤ በዕወቀትና በስልት መሆን ይኖርበታል። ዙሮ ደግሞ ተሸናፊ አድርጎ ባሪያው እንዳያደርግም አይዋ ምቀኝነት በእጅጉ መጠንቀቅ የሚያስፈልገውም የጉዳቱ ልክ፤ የጦሱን መጠን „የምቀኝነት መዳረሻውን“ መመርምር በተደሞ ሲቻል ብቻ ነው። ማንኛውም ክፉነት ያገረሻል። ክፉነት መሸታ ነውና። 
 
• ቅኗ እብዬ ሆዴ!
 
እናቴ እብዬ ሆዴ በልጅነታችን በመደበኛ የምታስተምረን ነገር ትዝ አለኝ። እጃችሁን ዘርጉ ትል እና እጣታችን እንድናስተውል፤በጣታችን ላይ እንድናተኩር ታደርጋለች። ከዛ ትንሿን እጣት እና አውራ ጣትን፤ ማህከለኛውን እና ጠቋሚ እጣትን፤ ጠቋሚ እጣትን እና ቀለበት እጣትን እያሳያችን የውፍረት መጠናቸውን፤ የቁመት መጠናቸውን እንድናስተውል ታደርግ እና መበላለጣቸውን ትነግረናለች። እንደማይጣሉም ትንገራናለች። እንደማይቀናኑም ታስተምረናለች።
 
… ግን ተበላልጠው በአብሮነት በውል በህብረት መዳፍ ተብለው መኖርን እንደሰጡን ትገልጣለች። እጣቶች እንደማይቀናኑ ግን አንድ ላይ ሆነው ሠርተን እንድንበላ እንዳደረጉን ታስተምረናለች። 
 
ሁሉም ነገር በእጅ እንደሚሠራ ታስረዳናለች። ይህ ሲሆን ግን እጣቶች አይቀናኑም። ስለዚህም እኛን አኖሩን ትላለች። በማንም ህይወት አትቅኑ። መቅናት መኖርን ያሳጣል ትለናለች። አትሰለችም አዘውትራ ነው እምታስተምረን። መቅናት የመዳፍ ጠላት እንደሆነ።
ከዚህ ተነስቼ ነው እኔ እናት የመጀመሪያዋ የህይወት የፊደል ገበታ፤ መምህርም እምለው። እናቴ እብዬ ሆዴ የመኖር ፍልስፍናው ጥልቅ ነበር። እሰኪ ሳቁ ሁሉ በማለት ሳቅ ታለማምደን ነበር። ሳቅ በርም ነው ትለን ነበር። 
 
እሷ በሳቅ ነው እምትታወቀው። በጣም ሳቂተኛ ናት። እናቷ ጽግሽ አፏ ምግብ ለማጉረስ ጠባብ ነበር የሰፋው በሳቅ ብዛት ነው ትል ሁሉ ነበር።
 
ይህ ማህበራዊነትን ለስላሳ አጓጊ፤ ተናፋቂ ያደርገዋል። እናቴ እንደ ምቀኝነት የምትጠላው ነገር አልነበረም። ምቀኛ ሰው መኖርን ያፈርሳል የምትለው አባባል ነበር። በጣም በእርግጠኝነት እምናገረው ለሰከንድ ይህ በሽታ ዞር ብሎብኝ አያውቅም። መላ ቤተሰቡ። ጥሩ አድርጋ ነው የቀረጸችን። 
 
እንደ እኔ ስለ ሰው የሚመሰክረም የሚጽፍም የለም። ከራሴ በላይ አልቄ መንበር ላይ ነው እማወጣው። ድንቅ ወገኖቼን ሳገኝ ስስት ነው እምልላቸው። ለምን ብትሉ ጠጥቼ ያደግኩት ወተት ከምቀኝት የራቀ ባህሪን ስለሆነ። 
 
ምቀኝነት ከሰው በእጅጉ ያሳንሳል። የፈለገ አይነት ብቃት በብቃት ይነባበር ምቀኝነት ያለው ሰብዕና ከሰብዕነት ደረጃው መመጣጠን አለመቻሉ ነው የምቀኝነት ሎሌ የሚያደርገው። የፈለገ አንደበት ቢኖረው፤ የፈለገ ቢከሸን ምቀኛ ሰው ጉድጓድ ነው። ጉድጓዱ የሱም ነው። በሌለው ላይ ተክኖ ያለውን ሲያሳድድ ይሰባራል። 
 
ያለው አለው ግን „ምቀኝነትን“ ምራኝ ካለ አለኝ የሚለው ዋጋው የሚወራረደው በዛው በወረደው ስብዕና ልክ ይሆናል። ስብራቱ ቀና ብሎ ለመቆም ወጌሻም አይኖረውም። ስለዚህም „ከምቀኝነት“ አዟሪት አለመውጣት ክብርን ቅርፊት መድረጉን ጠንቅቆ ማወቅ ያስፈልጋል።
ኢትዮጵያ መዳኛዋም ይህው ጎዳና ብቻ ነው። አሁን በሞቴ በአቶ እስክንድርን ነጋ ምን ያስቀናል? 
 
ይህ የምናዬው ትራጀዲ በሁለት የተቀናጄ ኦፕሬሽን የተከወነ ነው። በምቀኝነት እና በፍርኃት። መንግሥታዊ አካሉ ፍርኃታዊ ኦፕሬሽኑን በ አፈሙዝ ይማራል፤ ምቀኛው ደግሞ በእስስት ጃርታዊው ፖለቲካው ይንዳል። ይህ ሆኖ ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ሲውለበለብ ደግሞ እኔ ነኝ አጋፋሪው ይመጣል። ትራጀዲ በዓይነት።
 
እራስን በማሸነፍ ውስጥ ብቻ ነው አገር የምትገኜው። በዚህ ሂደት ማለፍ ከልተቻለ „ምቀኝነትን“ በመጥላት ብቻ „ምቀኛ“ አለመሆን አይቻልም። እደግመዋለሁኝ ምቀኝነት በመጥላት ብቻ ምቀኛ አለመሆን አይቻልም። መጥላቱ ተግባር ላይ መዋል ይገባዋል። እኔ ምቀኛ የሆነ ሰውን አጥንቼ ካገኜሁት በኋላ ሰው አይመስለኝም። ፈጽሞ። እሬሳ እዬተንቀሳቀሰ፤ እሬሳ እዬተነተነ፤ እሬሳ እዬሞገተ ያለ ነው የሚመስለኝ። 
 
አንድ የማህበራዊ ሥነ - ተፈጥሯዊ ክስተት ለመቀበልም ሆነ ለማግለልም መጀመሪያውን ነገር እራሱን እንደ ተፈጥሮው ማድመጥ ግድ ይላል። አውንታዊ ይሁን አሉታዊ የሚፈጥራቸውን መጠራቅቅ በማስተዋል መመርም ያስፈልጋል። የሰው ልጅ ደመነፍስ አይደለም እና። የነቃውን የህሊና ክፍል ተነቃነቅ ማለት ይጠይቃል።
 
ትርፍና ኪሳራው ሚዛን ሊገዛለት ይገባል። በስሜቱ ውስጥ ያሉና ሊገጥሙ የሚችሉ የፈተና አይነቶችን መፈተሽ የግድ ያስፈልጋል። ራስንም በዛ መጠራቅቅ ውስጥ ላለማስገኝት ወይንም ለማራቅ ከተፈለገ።
 
„ምቀኝነትን እጠላዋለሁ“ ማለቱ በቂ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን „የምቀኝነት“ ተባባሪ ላለመሆን ሊያድን ስለማያስችል „ኢ - ሞራላዊ የሆነውን ምቀኝነት“ ጠንቅቆ ከሥረ - መሰረቱ ማወቅ ያስፈልጋል። የኢትዮጵያ ቁምነገር ሊቀዳ የሚችለው ከዚህ ፏፏቴ ነው።
ተባባሪ አለመሆንን ለመፍቀድ ክፉውን ምቀኝት እና መረቦችን ለመበጣጣስ ማወቁ ነው ቀዳሚው በኽረ ሰው የመሆን ፍሬ ጉዳይ ሊሆን የሚገባው - እንደ ሥርጉተ። 
 
ምቀኝነት ከበታችነት ስሜት የሚመነጭ ብቻ ሳይሆን አቅምን ያልመጠነ ምኞትም የሚያመጣው በመሆኑ ሳይኖሩበት ቆይቶ ስሜትን የሚነካኩ ነገሮች ሲከሰቱ ተጠቂ ሊያደርግ ይችላል። በሽታም ነው። ፈውሱ ግን በእጅ ነው። „አውንታዊ“ መሆን።
 
ሌላ አንድ ምሳሌ ተዚህ ላይ ልከል „ሀዘን“ አይወደድም። ግን ሰውና „ሀዘን“ ተለያይተው አያውቁም። ሊለያዩም አይችሉም። „ሀዘን“ የበለጠ የውስጥ የሚሆነው ወይንም የሚታወቀው ግን በራስ ውስጥ ሲደርስ ብቻ ነው።
 
ምሳሌ /// እስረኛ ያለው ቤተሰብ እስረኛውን ባዬ ቁጥር፤ ወይንም ስለ እስረኛ በሰማ ቁጥር፤ ወይንም ስለእስረኝነት ህግጋቱን ባጠና ቁጥር ውስጡ ሰላም ያጣል። መንፈሱ በእኔነት ይተዋካል - እኔ ብሆን ብሎ የእኔ ይለዋል። ሰቀቀኑን ባሻጋሪ አይደለም የሚመለከተው።
ያ የእስረኛ የቅርብ ሰው ኑሮው ራሱ የሚተነፍሰው በነገረ እስረኛ ቧንቧ ይሆናል። ስለዚህ እሱም እራሱ የእስረኝነት መንፈስ ቀጥተኛ ቤተኛ // ቤተሰብ ነው ማለት ነው። በኑሮው፤ በህይወቱ መኖሩ በራሱ። እስር በተፈጥሮው ጣዕሙ መራራ ስለመሆኑ ያውቀዋል። ስለምን አካሉ የእኔ የሚለው ታስሯል እና። ይህ እንግዲህ ለቤተሰቡ ነው።
 
ለራሱ የግብረ ምላሽ ዳታው ለካቴና ቤተኛው ደግሞ ከዚህ የላቀ ከቤተሰቡም፤ ከቅርብ ሰዎችም፤ ከተሟጋቾቹም በላይ በጥልቅነቱ ይለያል። ተጠቂ ነውና።
 
በዚህ መንፈስ ዙሪያ ለሚታደሙ ታዳሚዎች ደግሞ የዳታው ቀረቤታ እና እርቀት በሰው ልጅ የሰብዕና አገነባብ ልክ የሚወስን ይሆናል። ሚዛኑን የሚሰጠው የሰው ተፈጥሮ ሰዋዊነት እና ተፈጥሯዊነት ስለሆነ። ሰብዕናው ለተኮላሸበት ሰቀቀኑን ታይቶም፤ ተደምጦም በአካል አይቶትም ቢሆን ከምንም ላይቆጥረው ይቻላል። አሽዋነት።
 
ተፈጥሯዊነት በብዙ መልኩ ስስነቱ ወይንም ደንዳነቱ እንደ አስተዳደጉ ወይንም እንደ ስብዕና የስሜት ውስጣዊ አወቃቀር አደረጃጀት እና አመራር እና ተመክሮ ስለሆነ።
 
አላዝንም ካለ አንድ ሰብዕና አለማዘን፤ አላስተውሰውም ካለ አለማስታውስ ስለሚቻል። የራስ ፈቃድ ጉዳይ ነው። ለዚህ ነው ቀደምቶቹ „ድርብ አንጀት“ የሚሉት፤ በዚህ ዙሪያ ፆታ አይለይም - ለእኔ። 
 
ስሱን ደግሞ ተባዕትም ቢሆን „እናት አንጀት“ የሚሉትም ለዚህ ነው አቨው/ እምው። „ሀዘኔታ“ በተፈጣሮ ለሴቶች በልጦ የተሰጠ ይምሰል እንጂ ከሴቶች የተሻሉ ስስ አንጀት ያላቸው ተብዕትም አሉ ግን ውስጣቸው የአደባባይ አይደለም።
 
ይህን ዘመን እኔ የመገለጥ ስለምለው አንድ በአደባባይ ሃዘናቸውን የገለጡ ክስተት አይቻለሁኝ። ምስባክነት። የቅኔው ልዑል ብላቴ የተቀኜው ፈተና ገጥሞታል። ውስጣቸው ሲያለቅስ ያየኋቸው ዘኢትዮጵያ አሉ። እዬመለስኩ - እዬደገምኩ - ሰለስኩት ጣዕሙን ጠጣሁትም። ያውም በዚህ ዘመን። 
 
የቅኔው ልዑል ብላቴ ሎሬት ጸጋዬ ገ/ መድህ „ወንድ ብቻውን ነው እሚያለቅስ“ በማለት ጥልቅነቱን አመሳጥሯል። ልዑሌ ትንሹን ልዑል አፍርቷል። ትንሽ እስኪ ከቅኔው ንጉሥ ስንኛት …
 
• ሎሬቱ የተፈጥሮ ስዋሰው። 
 
„… ‘ርቅ ነው ወንድ ልጅ እንባው
ደም ነው፣ ፍም ነው እሚያነባው፤
ንጥር ህዋስ ነው፣ ሰቆቃው
ረቂቅ ነው ምሥጢር ነው ጣሩ፣--- ብቻውን ነው የሚፈታው።“
ይህ ልቅና ይህ ክስተታዊ ትርጓሜ ብላቴው እያንዳንዱን የተፈጥሮን ስሜታዊ አመክንዮ ሆነ ክስተት ውስጣዊነት በፍልስፍና ጥበብ ነባቢት ያነበበት ምስባኩ ነው። ይህን ለተቀበለ ሌሎች ሥርዓቶችን ማወቅን ይጠይቀዋል።
• ለምሳሌ „ርህርህና“ ለምልክት ልውሰድ - ማያያዣም
እንዲሆነኝ … ኢትዮጵያም ርህርት ናት። 
 
„ርህርህናም“ ስለተፈለገ የሚታፈስ አይደለም። ፈተናው ብዙ ከመሆኑም በላይ ራሱን ያሸነፈ ብቻ የሚያገኘው ፍሬ ነገር ነው። አሁን በዚህ „ርህርህና“ ውስጥ „የመሆን አዎንታዊነት“ ተፈጥሮ ስበቱ እና ግጭቱ በራሱ ጊዜ የሚፈጥረው ውብ ትዕይንት አለ። 
 
ነገረ ትግራይ ላይ ያለው ኩነት እያንዳንዱን ሰብዕና ምን ያህል እንደፈተነው ተመልክተናል። በቀለኛ፤ ቂመኛ አይደለሁም ምራቅ እንደሆነ አስተውለናል። ሩህሩህ አይደለም ብሎ የወቀሰ ሰብዕና ተዚህ ላይ እሱም እዛው ተጨምሯል። ቤተኛ ሆኗል። 
 
ርህርህና ጸጋም ነው ተፈጥሮም ነው። በተፈጥሯቸው ሩህሩሃን ቋሚ ሰብዕና ነው ያላቸው። የማይናወጥ። ተፈጥሯዊነቱ ለሁላችን የተሰጠን መሆኑ ሲሆን፤ ጸጋነቱ ደግሞ በመሆን መብቀል ማስበል ማፍራት ውስጥ የመተርጎም አቅምን ያመለክታል። በዚህ ጥልቀት ነው እኒያን አዲሱን የኢትዮጵያንዚም የአይዟችሁ ቅኔ ያስተዋልኩት። ህልም እስኪመስለኝ ድረስ። 
 
ጭካኔ የተጫነው ተፈጥሮ „ርህርህናዊ“ ተፈጥሮውን ደምስሶ እና ቀብሮ ነው። „በርህራሄ“ መቃብር ላይ ነው የጭካኔ የማህበረተኞች አግናባት የሚገነቡት።
 
• ምሳሌ ወያኔ ሃርነት ትግራይን ማንሳት ይቻላል። 
 
አሁን ደግሞ የኦሮሙማን መሳፍንታት እና እቴጌዎችንም በተተኪነት ብብልጫም። 
 
ጭካኔን እያዩ ዝምታ በራሱ ከፈፃሚው ያልተለዬ ማህበርተኝነት ነው። በዚህ ዙሪያ የሚታደሙ ወይንም የሚሸከረከሩ ነገሮች ሁሉ ዕውነትን ግርዶሽ ማልበስ ሊሆን ይችላል። 
 
ያው „ርህርህናን“ አመድ አድርጎ፤ „ርህርህናን“ ግጦ ንግሥናውን ለጭካኔ፤ እጬጌነቱን ለአረመኔነት እንዲሆን መፍቀድ ማለት ነው። ይህ ማለት በተባባሪው ሥነ - ልቦና ውስጥ የተሰጠው ሞራላዊው ርህርህና አረም ወይንም ሙጃ ውጦታል ማለት ነው። „በርህርህና“ ውስጥ ኢትዮጵያን ማዬት ሲቻል ኢትዮጵያን ማዳን ቀዳሚ ዓላማ ይሆናል።
 
ቀዳሚው ዓላማ ሐገር አለኝ ከሚል ይነሳል። ሐገር አለኝ ሲባልም ዓለም አቀፍ ዕውቅና በተሰጠው መልከ ምድራዊ አቀማመጥ ውስጥ ያለ የሰወች ማህበርተኛ አባልተኛ ነኝ ብሎ ማመንን ይጠይቃል። በዛ መልክዕ ምድር ውስጥ የማህበር ብቻ ሳይሆን የተፈጥሮ ማህበራትም አሉ። ሁሉም እንደ አፈጣጠሩ፤ እንደ ዞጉ እንደ ማለት። 
 
… ለምሳሌ የእንሰሳት ማህበር፤ የወንዞች ማህበር፤ የተራሮች ማህበር፤ ዬእጽዋት ማህበር፤ የማዕድናት ማህበር፤ የወቅታት ማህበር፤ የዘመናት ማህበር ወዘተ … ስለዚህ ኢትዮጵያ ስትባል በዚህ ሁሉ የተፈጥሮ ቅመም የተቀመመች ምጥን ንጠረ ነፍስ ናት ማለት ነው።
 
ኢትዮጵያን ቁም ነገር የማድረግ ዓላማ ኢትዮጵያዊ መሆንን ይጠይቃል ሲባልም፤ በሁለመናዋ ውስጥ ባለማበላለጥ መክተምን ይጠይቃል ማለት ነው። አውንታዊ መሆን! ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ ማመንን። ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ መቀበልን። በዚህ ጥልቅ ግንዛቤ አቶ ልደቱ አያሌውን አዘውትሬ አያቸዋለሁኝ። ሁሉኑም በልኩ የማዬት ጥበብ አላቸው። 
 
ኢትዮጵያዊነት ያሉትን ሥርዓቶች ማጥናትን ከልብ ይጠይቃል። ኢትዮጵያ የሥርዓት አገር ናት። ለምሳሌ የአድዋ ድል አንዱ የአዎንታዊነት መሆን መለኪያ ነው። በዓደዋ ድል ውስጥ ሰዋዊነትም ተፈጥሯዊነትም የሚሰጡት ማናቸውም ክስተታዊ አመክንዮዎች ሥርዓታቸው፤ ውህደታቸው፤ ወጥነታቸው „አውንታዊ መሆን“ መቻላቸው በዓላማቸው ውስጥ መገኘታቸው ነው የድሉ ፊደል ገበታ።
 
ድል ይወደዳል። ድል ይናፈቃል። ድል የምኞት ሚዛን ነው። ድል ዬህሊና ግድግዳ ነው። ድል የመፈልግ ፍላጎት ነው። ድል የመኖር „መሆን“ የመጨረሻው እርከን ነው። ድልን ማግኘት የሚቻለው ግን „በመሆን“ ውስጥ ነው። በቅንነት በተቀመረ ውስጥነት ነው።
በመሆን ውስጥ መልካም የሆኑ/ ያልሆኑም ገጠመኞች ሊኖሩ እንደሚችሉም ልብ ማለት ያስፈልጋል። „ በአዎንታዊ በመሆን“ ውስጥ ያሉ የድንጋጌዎች አንቀፃት በመልካም አጋጣሚዎች ብቻ የተደወሩ አይደሉም። „መሆን“ ጌጡ መከራም ነውና።
 
„በአዎንታዊ መሆን“ ውስጥ ያሉ ሥነ - ምግባሮችን በመቀበል፤ በመወደድ፤ በመፍቀድ፤ በማጥናት፤ በመመርመር በህገ - ልቦና ጽፎ ምራኝ በማለት የሚገኝ መሆን ነው ለምለም ሊሆን የሚችለው።
 
ኢትዮጵያዊነትን በልቡ ለጻፈ ኢትዮጵያዊ ድል ማድረግ የሚያስችለውን መሳሪያ በአእምሮው ሥልጡንነት መከወን አያቅተውም። ኢትዮጵያዊነት ቁምነገር ነውና። ቁምነገሩን ቧልት የሚሆነው ከሚስጢር መነሳት ሲያቅት ወይንም ሲሳን፤ ሲንሳፈፍ ወይንም ሲፋድስ ብቻ ነው። እንደ ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ እና እንደ ቲማቸው ማለት ነው። ማቃት። እንደ ስውርም ደም መላሾቻቸውም።
 
• አድዋ የሚስጢራዊነት ድል ነው።
 
አድዋ ሚስጢር ነው። የ አድዋ ድል አፍሪካን አበጅታቷል። አሽሞንሙኗታል። የአድዋ ድል እኛን ሠርቶናል ብሎ በመቀበል ተሚስጢር አብራክ እና ማህጸን ለፈቀደ የመሆን አርበኛ ኢትዮጵያን ቁምነገር የማድረግ ዓላማው ስኬታማ ይሆናል። የሂሳብ ሳይንቲስትም አያስፈልገውም። አድዋን አጠቁራለሁ ላለ ደግሞ ጥሰት የዘፈነበት ሰባራ ገል ነው። ሰባራ ገል አገልግሎቱ ለሳት መጫሪያ ነው።
 
ይህ ውስጥን የሚፈትሽ፤ የሚመረምር፤ የሚያግባባ፤ የሚያማትር፤ የሚያደምጥ፤ „አውንታዊ መሆን“ „መሆን“ የሚችለው ከዐድዋ ድል መነሳት ሲቻለው ብቻ ነው። መሆን የሚገለጠው ድሉን ድል ያደረገው „የመሆን“ አርበኞች ትንግርታዊ ክስተታቸውን አንድ በአንድ በተናጠል ከእነ ሙሉዑ ሥርዐታቸው ማጥናት ሲቻል ብቻ ነው። ዕውቅና በመስጠት - በአክብሮት እና በትህትና።
 
የአድዋ ድል ብቻውን እኮ አፍሪካውያን፤ እኛ ጥቁሮች በዩንቨርስቲ ደረጃ እንደ አንድ የሙያ ዘርፍ ልክ እንደ ቁጥር፤ እንደ ተፈጥሮ እና ማህበራዊ ሳይንስ የትምህርት ሥርዓት ተነድፎለት እንደ አንድ የቀለም ትምህርት ሊመረቁበት የሚገባ ንጥር ክስተት ነው።
 
የዓድዋ ድል ፍልስፍና ነው። የ ዓድዋ ድል የሳይንስ ቀመር ነው። የ ዓድዋ ድል መንፈሳዊ እና ገኃዳዊ ትንግርት የጰጰሰበት ነው። ለዚህ የተፈጠረ አንድ ኃያል ነፍስ አለን። ፓን አፍሪካኒሰቱ ሊቀ - ሊቃውነቱ፤ ትውልድ የማይተካቸው ፕሮፌሰር ማሞ ሙጬ። ግን በኢትዮጵያ ሚዲያ፤ ፖለቲካ የተገለሉ የአፍረካ የፍጽምና ጌጥ እና ልዩ ክህሎተ ቀንዲል። 
 
• „ታሪክ“
 
ታሪክ ማለት በሥርጉተሻ ዕድምታ በ አንድ የጊዜ ማዕቀፍ ወይንም ፍሬም ወርክ ውስጥ በጎም፤ በጎም ያልሁኑ የሰዎች ተግባራት ዕድሜ ጠገብ ሲሆኑ ታሪክ ይሆናል ብዬ አስባለሁኝ።
 
የዓድዋ ድል ጉልሁ ታሪክ ነው። ትምህርት ውስጥ ዓድዋ ድል ነበር ቀደም ባለው ጊዜ። ግን ራሱን ችሎ መሰጠት ይኖርበታል ነበር የእኔ ሙግት። ኢትዮጵያን ከፍ ወደ አለ ደረጃ ማሸጋገር ዓላማም ግብ ከሆነ። አልጀመርነውም።
 
የችግራችን አታካችነት ምክንያታዊ ጭብጥም ከዚህ የመነሳት አቅማችን ስልብነት ነው። ሙግቶች የመንፈስ ማህለቃቸውን የሳቱ ናቸው። የኖኽ መርከባቸውን ጥለው ነው ኢትዮጵያን ለመግዛት የሚታሰበው። ኢትዮጵያዊ ታጋይ ነኝ የሚባለውም።
 
ግሎባል ክስተቱ በማለት ወይንም በሚዲያ ማሟቂያነት ወይንም ዕለቱን በጭብጨባ አጅቦ ለማሳለፍ ሳይሆን „በመሆን“ ውስጥ መስረጥን ይጠይቃል። መፈተሽ አለበት እኛ እና መሆን። ክብር ተረግጦ ክብር የለም። ክብርን ጨፍልቆ ሞገስ የለም። ክብርን ድጦ ግርማ የለም። 
 
የአድዋ ድል የሰሚናሮች፤ የሚዚዮሞች፤ የመጸሐፍቶች፤ የኪናዊ ታምራቶች፤ የወርክሾፖች ሁሉ አንጎል ብቻ ሳይሆን ስሜት የሚሰጥ አዕምሮም መሆን አለበት። ትምህርተ - ዓድዋ ድል የሰማይ የአምልኮ የገደል መጸሐፍ ነው - ለእኔ። ታቦት ሊቀረጽለት የሚገባ የድንቀት ብልጫ ያለው የፍጽማና መክሊት ነው ለኢትዮጵያዊነት። ኢትዮጵያ ማለት የ ዓድዋ ድል፤ የዓድዋ ድል ማለት ኢትዮጵያ። 
 
አድዋ የጥቁሮች ዓይን ነው። ዛሬ ላይ እኔ ስለ አድዋ በአምክንዮ ስጽፍ አላፍርበትም። ለምን ብትሉ እኔ ከጦርነቱ ቤተሰባዊነት ውጭ ያለሁኝ ነኝ እና። አፌን ሞልቼ መናገር፤ መጻፍ እችላለሁኝ። ጦርነቱ ሲታሰብ ጀምሬ አድዋ ጥሰት የህግ፤ የተፈጥሮ እንዳይፈጸምበት በ አጽህኖት ገልጫለሁኝ። ጸጸት የለብኝም። 
 
አንድ ሰብዕና ተዛሬ ላይ ቆሞ ዛሬ ላለበት መሬት ያበቃው ሰንደቁን የአሻቦ መቋጠሪያ በማድረግ አይደለም። ወይንም የካቴና ራት ተደርጎ አይደለም። ወይንም የቁንጫን ማወራረጃ፤ የዱላህ ጅራፍ መወጣጫ ሆኖ አይደለም። ክብሩ የተገኘው የመለከቱ ግርማ እና ጃኖ ከሆነው በብሄራዊ ሰንደቅዓላማው ነው። 
 
ንጡሁ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማው ነው አንተን/ አንቺን ሰው አድርጎ ፈጥሮኃል/ ሠርቶሃል። ጠቅላዩ ንጹሁን ሰንደቅ ዓላማ ብታለብሷቸው ኮማ ውስጥ ይገባሉ። በውሳጣቸው የሌለችውን ኢትዮጵያ ነው ምራቅ ላይ ማሳዥ የሚሠሩላት። አገር ማለት ሁለመናው ነው። ማህበረ ተፈጥሮው። ያላፈበት ሂደቱ። 
 
• ሰንደቅ „በመሆን“ ውስጥ መፈተሽ አለበት።
 
የኢትዮጵያ ቁምነገር ያለው ከዚህ የሰማይ ጸጋ ብቻ ነው እና። የአፍሪካ የጥቁር ህዝብ የነፃነት ግርማ ሞገስ ያለው ከዚህ ጥልቅ ረቂቅ ነፍስ ውስጥ ነውና። ዛሬ የአፍሪካው ህብረት ጽ/ቤት መዲና መሆን ያስቻለው ይሄው የማይገሰስ ገናና ታሪክ ነው። የታሪኩ ሐዋርያ ደግሞ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ መለከት ነው።
 
አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ነጋሪት ነው። አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ የሰማይ ድንጋጌ ነው። አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ህግ ነው። ሊደፈርም ከጫፉ ሊደረስም የማይገባ የነፍሳት የሥነ - ልቦና ገነታዊ ማደሪያ ማህደር ነው። 
 
ዛሬ ስንሰደድ ዜግነት ስንባል „ኢትዮጵያዊ“ የሚያስበለን ሌላ ምንም ሳይሆን ያ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ የሰጠን ሰማያዊ ጸጋ ብቻ እና ብቻ ነው። ቁመው ሲያቃጥሉት እያዬሁ ነው። በማን ላይ ቁመሽ እንዲሉ። እነኝህ ደመነፍሶች ኢትዮጵያ አገሬ አይደለችም ካሉ የስደተኝነት ኩነታቸው ኤክስፓዬርድ ሊደረግ ይገባል። ግን ጀግና ሲኖር ነው። ሁነኛ ሲኖር። በቀጨር መጨሬው ከማለቃቀስ መመከት። 
 
ዛሬ ዶር. ቴወድሮስ አድሃኖም የዓለሙ የጤና ጥበቃ ሚ/ር ያደረጋቸው ትግሬነታቸው ወይንም ዶክተሬታቸው ወይንም ዓይነ ገብ መሆናቸው አይደለም። በፍጹም። ለዛ ሁሉ የልቅና ሞገስ ያበቃቸው ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ብቻ ነው። 
 
ኢትዮጵያ ከምትባል ሐገር ውስጥ በመፈጠራቸው በዛም የዜግነት ዕድሉ ኑሯቸው ውጪ ሐገር ሄደው በመማራቸው፤ ተመልሰውም በኖረችው ሐገር ውስጥ ዕድል አግኝተው በመሥራታቸው ነው። ይህን ያደረገው ጉግል ወይንም ዩቱብ አይደለም። 
 
ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድን የኖቤል ተሸላሚ የሁለት ዓመት የዓለም ሚዲያ ነጋሪት ሰንደቅ ያድርጋቸው የነበረው ኢትዮጵያዊነት ብቻ እና ብቻ ነው። ኢትዮጵያዊነት ስታከብረው ያከብርኃል፤ ስትንቀው ከፎቅ አውርዶ ይፈጠፍጥኃል። ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ናቁት፤ አዋረዱት ከሄሮ ዜሮ ሆኑ። ታምሩ ገድሉ ረቂቅ ነው።
 
ከዚህ ጋር እሳቸውን በስውር ደግፈው በስውር ንደትን የሚያበረታቱትም ቢሆኑ ቀን ይጠብቁ። ዛሬ በግርዶሽ የተገነባው ሰብዕና የ እንቧይ ካብ ይሆናል። ክህደቱን የሚበቀለው የላይኛው ይሆናል እና። 
 
ወደ ቀደመው ምልሰት ሳደርግ የዶር ቴወድሮስ አድሃኖም የዓለም የጤና ሚኒስተርነት ሆነ የጠቅላዩ ባለበኖቤልነት የዚህ ሚስጢር አናት „በመሆን“ ውስጥ የከተመው የዓደዋ ገድል ለእኛ ሙሉ ዜግነት ስለፈረመልን ብቻ እና ብቻ ነው።
 
ያ ድል ሜዳ ላይ የታፈስ ወይንም ወንዝ ዳር የተቸረፈስ አሽዋ አይደለም። አልነበረምም። መኖር ያፈራቸው፤ ተፈጥሮ የለገሳቸው የሰው ልጆች በሙሉ „አመላቸውን በጉያቸው“ አድረገው ግን ሞራላቸውን ከእነ ሙሉ ሥነ - ምግባራቸው በብሄራዊ ቅንነት ቀምረው፤ እንሳሳት ሳይቀሩ በፈጸሙት የወል ሰማያዊ የፍቅራዊነት፤ የሐገራዊነት ሃመራዊ ተጋድሎ የተገኘ የደም እና የአጥንት ነባቢት ነው። ዓድዋ ቫወል ነው።
የዚህ ምግባር ሊጋባው፤ አሳላፊው፤ አሰላፊውም ደግሞ ንጹሁ ገናናው ደፋሩ ጀግናው ቅዱሱ አረንጓዴ ቢጫ እና ቀይ ብሄራዊ ሰንደቃችን ብቻ ነው። 
 
ያ ድል አብሮ አንድ ሆኖ ኢትዮጵያን ቁም ነገር አድርጎ የመነሳት የአብሮነት ዓላማ ያስገኘው እጹብ ድንቅ „የመሆን“ ረቂቅ ሥርዓታዊ አፈጻጸም የልቅና አመራር፤ የልዕልና አደረጃጃት፤ የሰማያዊ ጥበብ በረከት፤ ክህሎታዊ የጦር ስልት አዋቂነት፤ ተፈጥሯዊ ሩቅን የማሰብ ተስጥዖ ክንውን ያስገኘው የገድሎች ገድል፤ የታምሮች ታምር፤ የሊቆች ሊቅ፤ የትንግርቶች ትንግርት ነው። በንጉሦች ንጉሥ በአጤ ሚኒልክ እና ዘመን ባልተካቻቸው በእቴጌ ጣይቱ ያፈራ ታመራት።
 
„መሆን“ በዚህ በዓድዋ ድል ውስጥ ችሎት ላይ ቢቀመጥ ከእነ ሥርዓቱ ብቻ ሳይሆን ከእነ ሙሉ ምግባሩ ተገኝቷል። ቀድም ብዬ ያነሳሁት „ርህርህናም“ ዓለምን ያስደመመ የአመራር „ርህርህና“ ተከውኗል። ምርኳኛ የተሰተናገደው ኢትዮጵያ መሬት ላይ „ርህርህና“ በተፈጥሮው በተቀዳጀው ሥርዓተ - ህግ ነበር የተዳደረው። ዛሬ ግን በሁለት ጥጋበኞኢ በተካሄደው ጦርነት ፍዱስ ነው። ዜሮ። 
 
• እርገት።
 
ወደ ማጠቃለያው ስመጣ ኢትዮጵያን መውደድ ብቻ በቂ አይደለም። ቁጭቱ ኢትዮጵያን ቁም ነገር የማድረግ ዓላማ ላለው ኢትዮጵያዊ ዜጋ አድዋን በልብ መጻፍ ይጠይቃል። ቁጭ ብሎ ማጥናት። ዓድዋን በመደበኛ ት/ ቤት ለመማር መፈቀድን በአጽህኖት ይጠይቃል።
 
በኢትዮጵያ ውስጥ ባለድርሻ አካል ነኝ የሚል ማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ይሁን ሊሂቅ ይህን ሳይቀብል ቢያስበው ጥረቱ የእንቧይ ካብ ነው። ታሪክ አልባ ነው የሚሆነው፤ ውጤቱም የሚለካው በዚኸው ልክ ነው። ስለሆነም „መሆንን“ እንደ ተቋም በውስጡ ሊማረው ሲፈቅደው ብቻ ነው የልቡ ድል።
 
መፍቀድም ብቻውን በቂ አይደለም። ስንዱ መሆንን ይጠይቃል። ስንዱ መሆን ብቻ አይበቃም እንደ ኮርስ መጸሐፍት ማጥናትም ይጠይቃል። ይህም አይበቃም ወደ ድርጊት ለማሸጋገር መቁረጥ ይጠይቃል። ይህም ግብ አይሆንም። 
 
የቆረጡለትን ነገር „በመሆን“ ውስጥ ማፍራት ያስፈልጋል። ለዕለቱ ይብቃኝ ስለታደማችሁ በቀለሜ ውስጥ ያለውን ኑሩልኝን በፍቅራዊነት ልሸልም።
 
እግዚአብሔር ይስጥልኝ።
 
ሥርጉተ - ሥላሴ (Sergute©Sselassie)
26.02.2021 (ከጭምቷ ሲዊዚርላንድ።)
ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር ነው።
ጎዳናዬ በጸጋዬ ውስጥ ያለችው ኢትዮጵያ ናት!
No insights to show

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።