ንጉሥ እስከ ሠራዊቱ የተሰለፈበት #ሚስጢራዊ ክስተት።

 

ንጉሥ እስከ ሠራዊቱ የተሰለፈበት #ሚስጢራዊ ክስተት።
 
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።
 
#ምዕራፍ ፲፰።
 
 
 
 
እንዴት አመሻችሁ ማህበረ ቅንነት። የተፎካካሪ፤ የተደማሪ የፖለቲካ ድርጅቶች የፋና መድረክ የምዕራፍ ፩ የማጠቃለያ ቁጭት ፎቶ ይህን ይመስል ነበር። ስክሪን ላይ ያነሳሁት ነው።
 
ይህ ቃለ ምልልስ ከተካሄዴ በኋላ በርካታ ኢትዮጵውያን የግል አስተያዬታቸውን በአጭርም፤ በረጅምም፤ በቁጣም፤ በተግሳጽም፤ በክብርብርም - በኩሰትም፤ በቁጭትም - በተስፋ ምልዓትም የኢትዮጵያ የፖለቲካ መንፈስ ጥሩ አድርርጎ አገላብጥ ሲገመግመው ሰነባብቷል። በመጀመሪያ ላይ ይህን ያህል ይሆናል ተብሎ አልነበረም። 
 
የሆነ ሆኖ የብልጽግና ሁነኛ የሚባሉ አክቲቢስቶች፤ ሚዲያወችም ያልጠበቅኩት #አወንታዊ ዕይታ የሰጡትን አዳምጫለሁኝ፤ ጹሁፋንም አንብቤያለሁኝ። ብልፄው ለምን ተደፈረ ያሉም ፊት ለፊት ወጥተው ሲሞግቱ አይቻለሁኝ። ጥሩ ነው። አስደሳችም ነው። 
 
ወጣቶች በራሳቸው የዘመን ፖለቲካ በዚህን ያህል ፍጥነት ግሎባል ንቅናቄ መፍጠር ለቀጣዩ የምርጫ ጊዜ ምርጫው እኔንም ይመለከተኛል የሚል ጤናማ ዕድምታ ይፈጥራል። አክሰሱ ያላቸው ታዳጊ ወጣቶችም ነገም እኔ እንዲህ ብሆን የሚል ስሜት ሊያድርባቸው ይችላል። 
 
ስለሆነም እኔ ከጠበቅኩት በላይ የተሳትፎ ህብራዊነት በትጋት እና በተከታታይነት ስለየሁ አወንታዊ ስሜት ውስጤ ተመግቧል። በብልጽግና የፖለቲካ ፓርቲ መሪ አካላት እኔን የተሰማኝ ያህል ሊሰማቸው ላይችል ይሆናል። አገር ነገ ለሚሉ ኢትዮጵያዊ ዜጎች ግን የወጣቶቻችን ሙሉ ተሳትፎ አበረታች ነው።
 
በሌላ በኩል የለት ዕለቱን ከአፍ አፋ እየለቀሙ ትንታኔ የሚሰጡት ደግሞ ይህን መሰል የላቀ የህዝብ ተሳትፎ በአወንታዊም፤ በአሉታዊም የቀሰቀሰ ክስተትን አላየንም፤ አልሰማነም ብለው ኢግኖር ሲያደርጉት ደግሞ አስተውያለሁኝ። ምርጫ ደጋፊ ግን ምዕራፍ ፩ አላዬሁህም???
 
ብልጽግና ፓርቲ #አውራ ፓርቲ ነው። ህወሃትም ለ27 ዓመታት ዓውራ ነበር። ደህዴን፤ ኦህዴድ እና ብአዴንን ኢህአዴግ በሚባል ግንባር ሰጥ ለጥ አድርጎ የመራው አውራው ፓርቲ ህወሃት ነበር። አሁን ከመሃል አልታረስ፤ ከደንበር አልመለስ ብሎ ታምሶ እያመሰ የሚገኜው ህወሃት እኮ አውራነቴን ተቀማሁ ነው። ሌላ ነገር የለውም። 
 
የሆነ ሆኖ አውራነት??? ምን ማለት ነው ይሄ። አውራ ፖለቲካ ፓርቲ ማለት የሌሎች የፖለቲካ ፓርቲወች ማኒፌስቶ ተገዥ የማይሆን፤ ፈላስፊት ኢትዮጵያንም የመምራት ዕድል ያገኜ ማለት ነው። አውራነት #ገዢነት ኢትዮጵያ በመዳፋ ላይ ያለች እንደማለት ነው።
 
ይህ መሬት ላይ ሲኮን፤ ውጭ አገርም በርከትከት ያሉ አባላት፤ ደጋፊወች ያሉት፤ ተስፋ የሚጣልበት የፖለቲካ ድርጅት ሲገጥም ወይንም ንቅናቄ ወይንም ግንባር ላቅ ብሎ ሲወጣ አውራ ይባላል። በዘመነ ህወሃት የዲያስፖራ ፖለቲካን ይመራ የነበረው ዓውራ ንቅናቄ፤ በኋላ አርበኞች ግንቦት ፯ አውራ ነበር። ኢትዮጵያን ዕድል አግኝቶ አልገዛም፤ ግን የውጭ አገሩን ኢትዮጵያዊ ተወልጄ የለውጥ ፍላጎት፤ ራዕይ ይመራ የነበረ፤ መንፈስን የገዛ ነበር ማለት ይቻላል። ሞጋቾች ግን ነበሩበት። 
 
በየዘመኑ አውራ ሊፈጠር ይችላል፤ ኢህአፓ፤ መድህን፤ ቅንጅት፤ ህብረት ወዘተ …… የአንድ ፖለቲካ ሃሳብ ህሊናን ሲገዛ፤ ወይንም ዕድል አግኝቶ መዘዝ ብሎ ዘለግ ሲል አውራ ማለት ይቻላል።
 
#ሰሞናቱ በፋና መድረክ። 
 
ፋና ምዕራፍ ፩ መክፈቻው ከጠበቀው በላይ እንደ ደመቀለት አስባለሁኝ። እኔ ወድጄ ነበር ያዳመጥኩት። አልሰለቸኝም። በዚህ የውይይት ሙቀት፤ ፍትጊያ፤ ስበቃ እና ስበት ውይይቱ በቂ አትኩሮት ማግኜቱ የወጣቶችን የፖለቲካ ዕሳቤ የማነቃቃት አቅሙ አንቱ ነው። ይህም ሆኖ አውራው ፓርቲ ብልጽግና በጤናማ ዓይን ያዬዋል የሚል ግብረ- መልስ እስከ አሁን አላገኜሁም።
 
በውይይቱ ወቅት የብልጽግና ተወያዮች በሚኒስተርነት ማዕረግ በኢትዮጵያ ካቢኔ አባል ከፍ ባለ ደረጃ የሚመራ፤ የኋላ በቂ #ደጀን ያለው ቢሆንም በትብብር ለኢትዮጵያ የውይይት ጭብጥ አቀራረብ፤ የግልጽነት - አቅም፤ በተመጣጠነ የኮንፊደንስ መጠን፤ በብቁ የንግግር #ጥበብ ክህሎት፤ የድፍረት ላቂያነት እና ሃሳብን በአጭሩ አደራጅቶ በተፈቀደው ደቂቃ ልክ ዒላማን ማሳካት #መሰጠትም ነው። ተመሳጭ የሆነ አቅም ተመግቧል። ደርበብ ብለው የቀረቡት የትብብር ቤተኛም ሁለተኛው ተሟጋችም እረጋ ያለ የሃሳብ አቀራረባቸው ጥሩ ነበር።
 
ይህን ውይይት ብዙ የብልጽግና ሰወች የተከፋበት ነበር። ግን የተገባ ነው ብዬ አላምንም። ኢትዮጵያ እንዲህ ያሉ ወጣት፤ አንስት ፖለቲከኞች #ጥማት አለባት። ይህን ጥማቷን - ታቅዶ፤ ተሰልጥኖበት፤ እንክህ እንክህ ተብሎ እንክብካቤ ተደርጎለት፤ ድርጅታዊ ሥራ ተሰርቶበት ሳይሆን ጊዜው እራሱ የቅብዓው ደረጃ ልብን ገዛ። ዓይናችን ይህን ክስተት ያይ ዘንድ ተፈቀደለት። ለቀኑ ቀን ሲሰጠው ቀኑ እራሱ ለቀኑ ሽልማት ይኖረዋል። ጥሩ - አበረታች - ሳቢ እና አጓጊ ውይይት ነበር። 
 
በሌላ በኩል የፕረዘንቴሽን የአቀራረብ መበላለጥ ቢኖርም #ሦስት ተሟጋች የፖለቲካ ሊቃናት ሴቶችን እንደ ቀለማቸው በማየቴም እኔ ደስ ብሎኝ ነበር። በውነቱ የከረባት፤ የገበርዲን ውክልና ማዬት አድካሚው የትግል ምዕራፌ ነበርና። 
 
ሰላማዊ ትግልን የደገፋ፤ በሰላማዊ ትግል ህግን አክብረው በምርጫው ለመሳተፍ ለፈቀዱ ሁሉ እኩል መድረክ፤ እኩል አክብሮት፤ እኩል አያያዝ ሊሰጥ ይገባል። ለምን? ለማንስ ሲባል? #ለፈላስፊት ኢትዮጵያ ሲባል። 
 
ለሰላማዊ የሃሳብ ሞጋቾች ልዩ እንክብካቤ ሊደረግላቸው ሲገባ የተደራጀ የማህበራዊ ሚዲያው ወከባ እና ውረፋ ግን የተገባ አይደለም። በትጥቅ ትግልን ሃራም ብለው በብዕር ብቻ ለሚሞግቱ ይህን ያህል ዘመቻ በፍጹም የማያስፈልግ ነበር። ብልጽግና እንደዛች ያለች ዓራት ዓይናማን ማብቀል፤ ማጽደቅ፤ እና ማብሰል ግድ ይለዋል። በሌላ በኩል ፰ ዓመት ቀላልም አይደለም።
 
የገረመኝ ጎልጉል የአየር ላይ መጋዚንን እከታተላለሁኝ፤ ለምን በዛ ዕርዕስ እና ደጋፊ ፎቶ ያን ሐተታ እንደአቀረበ አላውቅም። ዴሞክራሲ ወዶ እና ፈቅዶ እስኪ ልምጣላችሁ ቢል በኢትዮጵያ የሚፈቀድለትም አይመስለኝም። 
 
ለአንድ አገር ዘላቂ ሁነት #ተቋማዊ ሂደት ወሳኝ ነው። ተቋማዊ ሁነት ደግሞ በስማበለው ሳይሆን አቅም፤ ክህሎት፤ ብቃት እና ልቅና ባላቸው ወጣቶች፤ ጎልማሶች ዕድሉን አግኝተው ሲመሩ ኃላፊነት እና ተጠያቂነትን በአንድ አገር ለማስፈን ሲችሉ ነው ተቋማት ጠንክረው እና በስለው መውጣት የሚችሉት። 
 
#አቅም የሚጠይቀው #አቅመኛውን ነው። 
 
አገር የምትቀጥለው አቅም ያላቸው ወጣቶች በመተካካት ባህል ካለምንም ጫና እና ተጽዕኖ የሚሳተፋበት መድረክ እንዲህ ሲፈጠርላቸው ነው። አቅም ያላቸው ወጣቶች ብቅ ሲሉ መደናገጥ አያስፈልግም። ፖለቲካ እኮ የተርቲም ጉዳይ አይደለም። ያሰበለ፤ የሰከነ ብልህ ህሊናዊ ብቃት የሚጠይቅ ሳይንሳዊ ፍልስፍና ነው። 
 
ኢትዮጵያ ----- ኢትዮጵያ:----: የነገ ኢትዮጵያ ------ የበለጸገች ኢትዮጵያ ማለቱ ብቻ በቂ አይደለም። ጥገኝነት እንደ #ላንቁሶ ሐረግ ሳያስፈልጋቸው በሙሉ የራስ መተማመን መቆም የሚችሉ ባለ ሙሉ አቅም ወጣቶች ብቅ ሲሉ ከመረባበሽ፤ በዘመቻ መልክ ተሰልፎ አቃቂር ከማውጣት አንዱ ያለውን ቀለም፤ ሌላው ከሌለው ቀለም ጋር አዋዶ፤ አንዱ የጎደለበትን የክህሎት ግድፈት በሌላው የዳበረ ክህሎት ጋር አስተጋብሮ አገረ ኢትዮጵያ ከፍ ትል ዘንድ የአቅም፤ የችሎታ፤ የጥንካሬ ህብራዊነትን ማፍለቅ ብልህነት ነው። ዊዝደምም ነው። ኢትዮጵያ #የቲም ወርክ ያስፈልጋታል። 
 
የብልጽግና ሚኒስትርም፤ ምክትል ሚኒስትሮችንም አቅማቸውን እያያን ነው። አክቲቢስት የሆኑም ምክትል ሚኒስተሮች አይቻለሁኝ። ተሳትፎውን ባልጠላውም ሰክና ማስከንን ይሻል ማንኛውም ፖለቲካዊ ኢሹ። #የጎደለ ነገር አለ። በአንድም በሌላም የጎደለውን ለመሙላት ፈጣሪ አዲስ አቅም ሲሰጥ እንኳን #ደህና መጣችሁ ሊባል ይገባል።
 
አንዲት ብላቴናን ከሆነ ካልሆነ ሰብ ጋር እያገናኙ መወረፋ አይጠቅምም። ብላቴናዋ ምርጫው ላይ #እንዳትሳተፍ ከአንከር ሚዲያ ጋር ጠንካራ ሙግት ነበረባት። ፍጥጫውን በአመክንዮ፤ በፋክት አሸንፋ ነበር የወጣችው። ያ ቲም #ቢፈቅዳት የልቡን ብታደርስለት ኖሮ የሚቀድመው አልነበረም ቃለ- ምልልሱን በተጋነኑ ቃላት ሞሻሽሮ ፍልቅልቅ ብሎ ይቀጥል ነበር። ግን ይህን ጹሁፍ እስከፃፍኩበት ድረስ ፔጁን ጎብኝቸዋለሁኝ የለም። እራስን ችሎ በራስ ህሊና ውስጥ ረግቶ ለዓላማ እና ግብ ማደር መታደልም ነው። ወጀቡ በግራ ቀኝ ነው ያለው። 
 
ኢህአፓ ምርጫውን ቢተው ጉሮ ወሸባዬ ነው። ይህ እንዳይሆን ኢህአፓ ዕድሉን እንዳያፈስ አበክሬ ጽፌያለሁኝ። በምርጫ አለመሳተፍ #ዘመንን ከማፍሰስ ውጪ ቅንጣት ፋይዳ የለውም። ስለሆነም በብስጭት ላይ ያላችሁ ሁሉ ከኤርትራ መንግስት ጋር ጋዜጠኛ ሚስጢረን አታነካኳት። እሷ ብትፈልግ አጋጅ የላትም፤ እንደ አስተዋልኳት ፕሮፖጋንዲስት የምትናፍቅ ወጣት አትመስለኝም።
 
ጋዜጠኛ ሚሥጢረ ስላሴ ታምራት ሁለት ጊዜ ከአንድ አፍታ ጋር፤ አንድ ጊዜ ከባይፈርስ ሚዲያ ጋር፤ አንድ ጊዜ ከአንከር ሚዲያ ጋር፤ ሌላ ጊዜ ከአንድ ለስላሳ ወጣት ጋዜጠኛ ጋር ያደረገችውን የተረጋጋ ቃለ- ምልልስ አዳምጫለሁኝ። በቂ አቅም አላት። ምን እንዳላትም የምታውቅ ይመስለኛል፤ የዕውቀቷ ልክ ግን ይህን ያህል ግሎባል ንቅናቄ የሚፈጥር መሆኑን እሷም በትክክል በልኩ የምታውቀው አይመስለኝም። ቅብዓ ሲኖር፤ #ጥሪ ሲኖር እንዲህ ነው። 
 
ፈተናው ብዙ ቢሆንም በቅብዓ፤ በጥሪ ውስጥ መሆንን መምረጥ ለእኔ የቁም ሰማዕትነት ነው። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ለሁሉም ቋያ ነው። ለገዢወችም መቀቀል ነው። ይህን ልጋራ ብላ ፈቅዳ ለተቀላቀለች ብላቴና ፈቃዱ የሁሉም ሊሆን ይገባል። በብሩህ ገጽ፤ በቅን ልቦና ትውልዱ ሊቀበላት ይገባል። ገና እኮ ውጥን ናት። 
 
#ሰዓቱ አሁን ቀኑም ዛሬ።
 
የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ድርጅት አባል መሆን ነውር እንደሌለው ሁሉ የኢህአፓ አባል መሆንም ሊነወር አይገባም። ስለ ጭካኔ ከተነሳ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከጭካኔ ጋር ተፋቶ አያውቅም። በዚህች ደቂቃ በታቀደም ይሁን ባልታቀደም ሁነት የሰው ልጅ በሰው እጅ ይሞታል። ይገደላል። ይሠወራል። ይታገዳል። ትልቅ ሱባኤ በልብ ንጽህና እና ቅንነት የሚጠይቅ ጊዜ ላይ ነው ህዝባችን።
 
ስለሆነም ከሳሽም፤ ተከሳሽ ይሆናል፤ ተከስሽም ከሳሽ ይሆናል። ጠቃሚ ባይሆንም በኢትዮጵያ ፖለቲካ የጥፋቱ ልክ ሊለያይ፤ የኃላፊነቱ ልክ ሊበላለጥ ቢቻል እንጂ የኢትዮጵያ እናቶች እና የየዘመኑ ትውልድ ዋጋ ከፍሏል። በቃችሁ እንዲለን አማኑኤል፤ እኛው እራሳችን ከጥላቻ፤ ከቂም፤ ከጭካኔ፤ ከመታበይ፤ ከአድመኝነት ነጽተን ለመገኜት ከራሳችን ለመጀመር ሰዓቱ #አሁን፤ ቀኑም #ዛሬ ነው።
 
#ምስክርነት እንዴት ከየትስ?
 
ሌላው ብልጽግና ሠራ ለሚባለው ተግባር ቁምነገሬ የሚሉት የብልጽግና አባላት፤ ካድሬወች እና አካላት ኩራትም፤ ራትም ብርሃንም ሊሆን ይችላል። መስካሪ፤ ዘካሪ፤ መወድስ ደርዳሪ ተጠቃሚው ሊሆን ይችላል። ለሌላው ደግሞ መራራ ከርቤ ሊሆንበት ይችላል።
 
ባለፈው ሳምንት የልጅ ሞገስን የሃሳብ ገበታ ሳዳምጥ አንድ ወጣት የህግ ባለሙያ "ኢትዮጵያ የባህር በር፤ ወደብ እንድታገኝ እመኛለሁኝ፤ ግን #በአብይ እንዲፈጸም አልፈልግም።" ሲል አዳማጨዋለሁኝ። የፈለገ ፕሮጀክት ተጀምሮ ቢጠናቀቅ የእኔ የሚሉ ላይኖሩ መቻላቸው ሊደንቅ አይገባም።
 
ሌላው ዕውነተኛ ተፎካካሪ እኮ የሚሞግተውን አጣጥሎ፤ አቃሎ፤ የእኔ ጊዜ ይህን ያሳካል፤ ያ ተስፋ ዕውን ይሆናል ብሎ ይሞግታል እንጂ፤ ጎሽ ተፎካካሪዬ በብልጫ እየመራህ ስለሆነ የእኔን ዕድል ውሰድ ሊል አይችልም። ብልጽግና ዕድለኛ ሆኖ ሊመክቱ የሚችሉ ፓርቲወች ከብልጽግና ሥር መሆንን የፈቀዱ ይኖራሉ። አሉም። 
 
#ይከወን።
 
የሆነ ሆኖ የኢትዮጵያን የምርጫ ፖለቲካ ውጥን ነፍስ ሆና፤ ነፍስ የዘራችበት ጋዜጠኛ ሚስጢረ ለወጣት ሴቶች፤ ለወጣት ፖለቲከኞች፤ ለሚዲያ ሴቶች እና ለሚዲያ አፍቃርያን ሁሉ ሃሳቧ ተደገፈም፤ አልተደገፈም ይጨርስላት እንጂ አጀማመሯ ጥሩ ነው። እኔ መስክሬ መስክሬ በመሰከርኩት ልክ የማግኜት ዕድል አልገጠመኝም። ስለሆነም ስጋት አለኝ። 
 
ትዕግሥቱ ካለ፤ መደማመጡ ከኖረ ነገን አፍላቂነቷ ለድርጅቷ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ የሃሳብ ፖለቲካ ጥራት እና ብቃት አስተዋፆ ሊኖረው ይችላል። ዛሬ ባላት አቋም። ነገን አናውቅም። 
 
እርግጥ ነው እኔ የማላምንበት ከሌላ የፖለቲካ ድርጅቶች የመጡት የፖለቲካ ድርጅት የማንነት ቀውስ ሊኖር ስለሚችል ለኢህአፓ ቀጣዩ የተግባር ጊዜ በዘለቄታ ከባድ ቻሌንጅ ይገጥመዋል ብዬ በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁኝ። 
 
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ችግር የፖለቲካ ፓርቲ አባልነት እንደ ቤት ወይንም እንደልብስ በቀላሉ የሚቀያዬር ነው። ትውልዱን አላስፈላጊ መስዋዕትነት የሚያስከፍለውም ይህ መሰል ተባደግ ጉዞ ነው።
 
ጠቅላይ ሚር አብይ እራሳቸው ኦህዴድ ነበሩ። ማህበረ ኦነግም ላይ መረጃ ይሰጡ እንደ ነበር ሲናገሩ ነበር። በቅንጅትም የመሳብ ነገር ነበራቸው ሲሉ ነበር አብረው የሠሩ ወዳጆቻቸው። 
 
አሁን ብልጽግና መሥራቹም መሪውም ናቸው። በዚህ ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲ የማንነት ቀውስ አይኖርም ማለት አንችልም። ወ/ሮ ሙፍርያት ካሜል ደህዴን ነበሩ፤ አቶ ዛይድ ህወሃት ነበሩ፤ እነኝህ ሰወች በዘመነ ኢህአዴግ መሪም ነበሩ፤ አሁን ደግሞ ብልጽግና ናቸው። ውጥንቅጡ የወጣ ራዕይ፤ ዓላማ እና ግብ እኮ ነው የትውልድ #ዋጮ የሆነው። የኢዜማ፤ የአብን፤ የባልደራስ አደረጃጀትም የተቀየጠ ነበር። ይህን ወጥ አድርጎ መርቶ ተልዕኮን ማሳካት ከባድ ነው። የፊት ለፊት የኢህአፓ ፈተና ይህ ሊሆን ይችላል።
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
 
ኑሩልኝ። አሜን።
ሰላም እደሩልኝ። አሜን። 
 
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
28/02/2026
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ዕውነት ወጌሻ አያስፈልገውም።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።