Par two, ብርድብርድ ያለው የትናንት የፋና የ2018 የምርጫ መድረክ የቤተ - ዳዊት መወደሪያ ምሽት።

 

ብርድብርድ ያለው የትናንት የፋና የ2018 የምርጫ መድረክ የቤተ - ዳዊት መወደሪያ ምሽት።
 
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።
 
#ምዕራፍ ፲፰።
 
ሴት የፖለቲካ ሊቃናት የፖለቲካ ውክልና አጡ ብዬ ስሞግት ኖሬ፤ ዕድሉ ሲገኝ እንዲህ እና እንዲያ ማለት ስለሚፈትነኝ እንዲህ ካልበዛ በስተቀር እንዳላየሁ አይቼ የማልፋቸው ብዙ ጉዳዮች አሉ። የሆነ ሆኖ ያን ግዙፍ ተቋም የሚመሩ የፍትህ ሚር ትናት በነበራቸው የብልጽግና ፓርቲ ወካይ የሙግት ቆይታ የብልጽግና አቅም እጅግ #ፈተና ውስጥ ገብቶ ነበር ማለት ይቻላል። እንደ አለፈው ጊዜ በዕለቱ የማያፈናፍኑ ንቁ እና ትጉህ ሞጋቾች ቢኖሩ ምን ይበጃቸው እንደነበር አላውቅም።
 
ባለፈው ጊዜም ቢሆን ለጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ በጣም የቅርብ ሚር የሆኑት፤ በወሳኝ የጠቅላይ ሚሩ ልዑካዊ ጉዟቸው የማይለዩ፤ ለግሎባል መሰናዶ ተመራጭ የሆኑት፤ በዘመነ አብይዝም የመጀመሪያው የካቢኔ አወቃቀር ላይ የነበሩት ቁጥር ፩፤ በሲነሪቲ ደረጃ መቅድም የሆኑት ዶር ፍጹም አሰፋም እንኳን ከፋክት፤ ከጭብጥ ይልቅ #ፕርፖጋንዳዊ ሁነቶች ላይ ነበር ያተኮሩት። ይህም ቢሆን ይሻላል ከትናንቱ ብርድ ብርድ ከአለው የፋና የትናንት መድረክ።
 
እርግጥ ነው በዚህ የሙግት መድረክ ዕቅዳችሁ ምንድን ነው። የዕቅዳችሁ ፖሊሲ በምን ላይ ያተኩራል፤ ለአፈፃጸሙ ምን ያህል መሰናዶ አላችሁ? በፋይናንስ፤ በሰው ኃይል፤ በመንፈስ፤ በኮኦርድኔሽን ወዘተ ጥያቄው ይህ ነው። ቲም ሚር ዶር ፍጹም አሰፋ ግን ባለፋት የመምስት ዓመታት ክንውን ዘገባ አቅራቢ ነበር የሆኑት።
 
ለነገሩ የብልጽግና ፓርቲ ሁለቱ ምክትል ፕሬዚዳንቶችም ማኒፌስቶ ለቀጣይ፤ ትልም ለቀጣይ፤ ራዕይ ለቀጣይ ሲጠየቁ ማኒፌስቷቸው ከ2013 እስከ 2018 ዓም ያከናወነውን የዘገባ ሪፖርት እንደያዘ ነበር እንደመልካም ነገር ያቀረቡት። ጽፌበትምአለሁ። የመወዳደሪያ ምልክታቸው ትርጉም አሻሚነት በተነተንኩበት ጹሁፌ። ትንንት አንፖሎች ዛሬ ነዶውያኑን ዘርዘር አድርጌ ሞግቻቸዋለሁኝ። የትናንት የብልጽግና አንፖል እና ስኬቱ ተናፋቂ ሆኖ የዶር ራሄል ባፌም አልሸሹም ዞር አሉ የእጅ ባትሪ ነው የመወዳደሪያ ምልክታቸው። 
 
#ሂደት ጋር በትይዩ። 
 
ታስታውሱ እንደሆን ዶር ፍጹም አሰፋ ጀርመን ትምህርት ላይ ሳሉ ነበር በጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ሹመት የተሰጣቸው። ያንጊዜ በጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ሹመት ቀርቶ ሥሙ የተነሳው ሁሉ የሰማይ በረከት እንደሚዘንብለት ይቆጠር ነበር። እንኳንስ ሚኒስተርነት፤ እንኳንስ የካቢኔ አባልነት።
 
የሆነ ሆኖ በሲነሪትም ይሁን በቀለም ዕውቀት፤ በቆይታም ይሁን ዘለግ ያለ ልምድ በማግኜት፤ ልዩ አቅም በሚሰጠው የጠቅላይ ሚኒስተሩ የቅርብነት አመክንዮ ታክሎ ያገኙት ሚር ዶር ፍጹም አሰፋ በሙግቱ ወቅት #አንገታቸውን ያቀረቀሩበት ወቅት ነበር። አጋራቸው ፈዘው ነበር። ሞጋች ጋዜጠኛውም ደንግጦ አቅሙ ሁሉ #ራድ ላይ ነበር። ግብረ- መልሱ እንደነገረኝ። ከትናንት ምሽት ጋር ሳነፃጽረው እሳቸው ተሻሉኝ። 
 
ትናንት አስተያዬት መስጫውን ከርችሞ ግን ላይፍ ላይ ነኝ ብሎ አጤ ፋና የ2018 የምርጫ ሁለተኛ ዙር ሙግት አካሂዶ ነበር። አንድ "ሰላም" የሚል የትብብር መድረክንም ጨምሮ ነበር ውይይቱን አህዱ ያለው። ትብብር፤ ኢዜማ፤ ብልጽግናም ነበሩ። እጅግ የበረደው ደመመን ጫን በል ያለው፤ የውይይት ክፍለ ጊዜ ነበር።
 
በዕለቱ ውይይት #ኢዜማ ሻል ብሎ አግኝቼዋለሁኝ። ለነገሩ ኢዜማ ፖሊሲ የማመንጨት ችግር የለበትም። በአደረጃጀትም መርሃዊ ነው። ሙሉ አቅም ያላቸው አካላት አሉት። እራሱን ችሎ ቢቆም ተመራጭነቱ አያጠያይቅም። ኢዜማ ዕድል አላባክንም ያለውን እየደገፍኩ እቀጥላለሁ ብሎ ተቦርን እንደሚለው፤ "እኛ ሙሽራ እንዲሆን ተመኜን እሱ ሚዜነቱን ፈቀደ።"
 
ያው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ይሉኝታ ቢስ ስለሆነ እንጂ እሱ በግራ ቀኝ ወጀብ እየተቀቀለ የብልጽግናን ነፍስ ያስቀጠለ ዶር ኢዜማ ነው። ኦክስጅን ለብልጽግና አምራቹ ዶር ኢዜማ ነው። ዶር ኢዜማ እራሱን እንደ ክርስቶስ ለብልጥግና ፍቅር የገበረ እጅግ ባለውለታ፤ ከኢጎ ጋር የተፋታ ክብሩን፤ ግርማ ሞገሱን፤ ተቀባይነቱን፤ ድካሙን እና ሰብሉንም ፈቅዶ የሰጠ #ለጋስ የፖለቲካ ድርጅትም ነው።
 
እሱን በፖሊሲ ጥራት፤ በአደረጃጀት ንጥረ ነገር የፋና መድረክ ሞጋች ልጅ ዳዊት ……? አቃቂር ሲያወጣለት ውሽክ አድርጎኛል። ለብልጽግና ኢዜማ ልዩ ሽልማት ነው። ቢያውቁበት ይሉኝታም ቢኖራቸው ለዚህ እርከን አብቃዩ ዶር ኢዜማ። ዶር ኢዜማ በፈቀደው ቦታም የተሰጠውን ዕድል ሳያባክን ከታሰበው በላይ በአዲስ ቅኝት፤ እሸት በሆኑ አዳዲስ ኃሳቦች ለብልጽግና ታማኝነቱን በፍጽምና አሳይቷል ገልፆአልም። 
 
#የትናንት ብርድብርድ ያለው ምሽት ተሟጋቾች ………
 
ትብብር ሲሮጡ ቆይቶ ትንፋሽ ለመሰብሰብ የሚመጣ የተቆራረጠ ድምጽ ነበረው። #ማለህለህ ይባላል። ይህን መሰል ሁነት ገጥሞታል። ለብልጽግና አስደንጋጭ ምሽት አልነበረም ነገረ ትብብር እና ቆይታው። ያው እኔ ሁለመናን ነው እማዬው ከውስጤ፤ ከህሊናዬም። የሆነ ሆኖ የመግቢያ ንግግሩን ያደረጉት ትብብራዊው እንደዛ ሃሳባቸው ያለመረጋጋት እና የተቆራረጠ ነበር።
ሁለተኛው የትብርውያን ተሟጋች በውስጣቸው ዕውቀት አለ። ይህን ታዝቤያለሁኝ። የውስጣቸውን አቅም አድራጅቶ የመግለጽ ችግር ነበረባቸው። 
 
የሰላሙ በቃ "ሰላም" የሚለው ኃይለ ቃልን አክብሮ ማለፍ ይበቃል። ፋና መድረክ ያለፈው ውይይት መዝጊያው አናት የሚበጠብጥ ስለሆነበት ይመስላል። በዕጣ ቅደምተከተሉ እንደተሠራ ነግሮናል። ግን ፋና ለምንድን ይሆን ነገረ ብልጽግና የልቡ ትርታ የሆነው? ያልገባኝ ይሄ ነው። ፋና የህዝብ ወይንስ እንደ ዘመነ ህወሃት #የብልጽጌው???? 
 
የሆነ ሆኖ ብልጽግና በሁለት ውስጦቹ ተወክሏል። አንዷ የኢፌድሬ ፍትህ ሚኒስቴር ወ/ሮ ሃና አርያሥላሴ ነበሩ። #እንግዳ ነበር የሚመስሉት። ወይንም እቃ አድርስ ተብሎ የተላከ ኩታራ። አቅሙም፤ የመናገር ተመክሮም፤ የውስጥ በራስ የመተማመንም ክህሎትም፤ የፖለቲካ ፓርቲያቸውን የነፍስ #ትንፋሽ ለማብሰር ተቸግረው ነው ያዬኋቸው። ድምፃቸው እራሱ ቃናው ሳቢነት አልነበረውም። ንግግር አዋቂ ተሆኖ እንኳን የድምጽ ቃና እና ፍሰቱ፤ ለዛ እና ወዙ፤ ውብ ካልሆነ ለአድማጭ አሰልቺ ይሆናል። ይህ ገጠመኝ ነበረበት ብልጽግና።
 
በዚህ ወሳኝ ቀን የሚቀርብ ወኪል የየትኛውም የተፎካካሪ፤ የተጠማኝ፤ የተደማሪ፤ የተቀላች፤ የአውራ ብልጽግና ፓርቲ ይሁን፤ መድረክ ላይ ከመቅረቡ በፊት #ሪህርሳል ሊሠራ ይገባዋል። ብልጽግና አውራ ፓርቲ ነው። አገር እየመራ ነው። ከሚኒስተር ሚኒስተር ቢቀያይርም በሁለቱም መድረኮች ሊያሳካ ያሰበው ፍሬ ___ ???? በጣም አሰልቺ እና አስደንጋጭ ነው የነበረው። የፖለቲካ ድርጅቶች መሪ አካሎቻቸው የተደራጁበትን ዓላማ እን ግብ መግለጽ ከተሳናቸው እንደምን መሪ ሊሆኑ ይችላሉ??? በዚህ ልክ ኢትዮጵያ ትመዘናለች፤ ትሰፈራለች፤ ትለካለች። በዛሬ ውስጥ እኮ ነው ነገ የሚጠነሰሰው። 
 
ብልጽግና መንግሥት ሆኖ እየመራ በራስ የመተማመን አቅሙን ሚኒስተር ወንበሩ ላይ አስቀምጦ፤ ለሙግት የአቅም ስስነት እራሱን ሚዛን ላይ ያስቀመጠ ሆኖ አግኝቸዋለሁኝ። በዚህ ውስጥ የአፍሪካ አንከር በሆነች አገር ሚዛንን ያህል የፍትህ ተቋም ቁንጮን የወከለ ተቋም በዚህ አነስተኛ መድረክ እራሱን መግለጽ ያልቻለ፤ በአህጉራዊ፤ በሉላዊ ጉዳዮች ጉባኤወች፤ ሲሚናሮች ላይ ኢትዮጵያ ብቁ ልሳን አላት ወይ ብለን ስንጠይቅ "#መ" መልስ ይሆናል ማሳረጊያው።
 
#መጨረሻውን ያዬው ሰው።
 
ሙግቱ እየጦፈ ሲሄድ ብልጽግና እንደልቡ ስለሆነ #ወኪል አላሰናዳሁም ብሎ ከጨዋታው በፎርፌ ሊወጣ ይችላል ባይ ነኝ። እንደ የኢትዮጵያ መንግሥት መሪነቱ ብልጽግና በአንድ ሰው አቅም ብቻ ሙላቱን፤ ወጀቡን፤ ሱናሜውን ለመሻገር ጋዳ ሊሆንበት ይችላል። አንድ ሰው የርዕሰ መዲናው ከንቲባ፤ የፕሮጀክት ኮኦርድኔተር፤ የኮንስትራክሽን መሃንዲስ፤ የአገር ውበት ቀያሽ፤ የመድረክ መሪ፤ የልዑክ አንበል፤ የኮሪደር መብት አስከባሪ፤ የየትኛውም ኢቤንት አንደበት፤ የኢኮኖሚ፤ የማህበራዊ፤ የባህላዊ፤ የዲጅታል መሪ ሆኖ እንደምን ይቻላል። ጸጥታውም ደህንነቱም አለ። አህጉራዊ ሉላዊው የፖለቲካ ትኩሳት አለ። ታምቆ የተያዘው የጦርነት ፍጥጫም አለ። በውነቱ ኢትዮጵያ እራሱን ችሎ መቆም የሚችል ተቋም በእጅጉ ያስፈልጋታል። 
 
የዓለም ይሁን የአህጉሩ ፖለቲካ በተወሳሰበ ቁጥር ተተክቶ የሚሰራላቸው ቦታ ክፍተት ሊገጥመው ይችላል። እርግጥ ነው ፍትህ ሚር በጉልቻ ነው የሚመራው። ዶር ጌዲዮን ጢሞቲወስ ውጭ ጉዳዩንም፤ ፍትህ ሚሩንም ደርበው እንደሚመሩት አስባለሁኝ። ለዚህ ጊዜ ግን በስልክም በጉልቻም የማይዳኝ ነገረ ገጠመ እና #ተያዬን። ተፈታተሽን።
 
የሆነ ሆኖ ለየትኛውም ቁልፍ የመሪነት ኃላፊነት #የንግግር ጥበብ ክህሎት በእጅጉ፤ በጣም በእጅጉ ያስፈልጋል። በአገርኛ ቋንቋ ይህን ያህል የከበደ በሌላ አገር ዓለም ዓቀፍ ቋንቋ ቢኮን ምን ሊሆን ይሆን? 
 
ሌላው ባለፈው ጊዜም ጽፌበታለሁኝ የኢትዮጵያ ህዝብ #እንግሊዘኛ ቋንቋ ተናጋሪ አይደለም። በእንደዚህ ዓይነት ስብሰባወች፤ ጉባኤወች፤ መድረኮች፤ የሙግት ዓውዶች በአማርኛ ቋንቋ መግለጹ ለመራጩ፤ ለደጋፊው ቀና መንገድ ነው። አንዳንድ ቀጥተኛ ፍቺ የሚጠፋላቸው ቃላት ቢገጥሙ፤ የበለጠ ይገልጽልኛል የሚባል ጉዳይ ከገጠመ እንግሊዘኛውን ተጠቅሞ ከጎኑ አቻ ትርጉሙን መስጠት በእጅጉ ያስፈልጋል። 
 
#ነገረ ፌድራሊዝም።
 
ሞጋቹ የፋና የልብ ሰው ከኦነግ፤ ከህወሃት ጋር በወል ቁጭ ብሎ ህወሃትወኦነግ ዘለቁን ህገ - መንግሥቱ ስክሪፕቱን የፃፈ ይመስላል። የህወሃትወኦነግ ህገ - መንግሥት ወይንም ሞት ባይ ነው። የሰራ አካላቱ፤ ዕዝነ ነፍሱ ጥምቀተ - ህወሃትወኦነግ ህገ- መንግሥት ነው። ስለሆነም ሙግቱ ከአብይዝም ዘመን ጋር ብቻ ሳይሆን ከዘመነ ህወሃት ናፍቆትም ጋር ተዋህዶ ቃር ቃር እያለን እናደምጥ ዘንድ ተፈርዶብናል። እግዜብሄር ይይልህ። 
 
ሌላው የዓለም ህዝብን ህወሃት የሚያታልልበት መንገዱ ፌድራሊዝም ፈጥሬያለሁ ነው። በነገራችን ላይ በደርግ ጊዜም ፌድራሊዝም ነበር። የነበረው ፌድራሊዝም የቋንቋ ብቻ አልነበረም። የመልከአምድራዊ ፌድራሊዝም ነው። በተጨማሪም በደርግ ጊዜ ህገ - መንግሥታዊ ጉዳዮች በስፋት ህዝብ ተወያይቶበት የጸደቀ ህገ - መንግሥት ነበር። ሌላው የብሄረሰቦች ጉዳይ በኢሠፓ መዋቅር ውስጥ የድርጅት መምሪያ፤ የርዕዮተዓለም መምሪያ ወዘተ ነበሩ። ልክ እንደሌሎች መምሪያወች ሁሉ #የብሄረሰቦችም መምሪያ ነበር።
 
ይህም ብቻ ሳይሆን በሙሁራን የተደራጄ የብሄረሰቦች #ኢኒስቲቲዩት የምርምር እና የጥናት ላቅ ያለ ተቋም ነበር። በኢቲቪም ከማጀት እስከ አደባባይ የሚል የእያንዳንዱን ብሄረሰብ ሴቶች የዕለት ሁነት የሚዘግብ መሰናዶ ነበር። ይህን እኔ እማነሳው በኢህአዴግ ትውልድ ይሁን፤ አሁን ባለው የብልጽግና ትውልድ የነበረው አለመታወቁ እንደ ልዩ የህወሃት ችሮታ ስለሚታይም ነው። የፋናው ሞጋች የዚህ ግንዛቤ ሰለባ ነው።
 
ወደ ዕርዕሴ ስመጣ የጎበጠ ማቃናት፤ የጎደለን ማስተካከል ስለሚገባ ለሚያደምጡ አካላት ኢትዮጵያ ውስጥ ፌድራሊዝም ያለው አንድ #አማራ ክልል ብቻ ስለመሆኑ አብክሬ ጽፌላቸዋለሁኝ። አረጎባ፤ ቅማንት፤ ኦረሞ፤ አገው የራሳቸው ዞን ወረዳ አላቸው። የቀድሞው የኮምኒኬሽን ቁንጮ የአማራን ውክልና በአማራ ክልል ይዘው እኮ ነው ያን ያህል ፈርሰስ የሚሉት። በኦሮምያ፤ በቤንሻንጉል ጉምዝ አማራ ነኝ ማለት ወንጀል ነው፤ እንኳንስ የፖለቲካ ውክልና።
 
ህወሃት ይህን ያደረገበት ሁኔታ የአማራ ህዝብን ልቅና እና ልዕልና #አጫጭቶ ለመበቀል ነው። አማራ ክልል ሁሉም እንደ አቅሙ ውክልና፤ ዕውቅና አግኝቶ የትኛውም ክልል ግን የአማራ የፖለቲካ ውክልና #ልሙጥ ነው። ምራቅ ሆኖ የቀረው አቤቶ አብን ይህን እንኳን ማስከበር አልቻለም።
 
ለብልጽግና የወልቃይት፤ ጠገዴ፤ የጠለምት፤ የማይጠምሪ፤ የአዳርቃይ፤ የአዲረመጥ፤ የራያ ጉዳይ እንዲህ ትራጀዲያዊ ተውኔት እየፈጠረ በወጀብ ቅዘፍ የሚለው መሠረታዊ አመክንዮ ከአማራ ጋር ባለው የውስጥ የመበቀል ሁነት የተነሳ ነው። ይህ ደግሞ ከህወሃት የተፈጠረ ችግኝነት ከተፈጠረበት ንጥረ ነገር ሊወጣ አያስችለውም። ከሊቅ እስከ ደቂቅ የህወሃትን መንፈስ ታቅፎ ነገን እናድናለን ማለት፤ ታጥቦ ጭቃ ነው። ሙሉ ፰ ዓመት የህወሃትን መርዝን እየነቀሱ #መሻሪያውን ማሳካት ሲገባ ኤንም እንዳይከፋው፤ ቢንም እንዳይከፋው ተብሎ መሠረቱ እያረገረገ ይገኛል የአጤ ተስፋ። 
 
ፌድራሊዝም ኢትዮጵያ ላይ የለም። ለፋንታዚ ከሆነ ያስማማናል። ለኩሸት ልዕልና ከሆነ ሊሆንላቸው ይችላል። የሚገርመው ይህን ጥንዙል መርዝ ጠጥቶ የተቀመረ ህገ - መንግሥት ተሸክሞ ህወሃትን ማሸነፍ በድቡሽት ላይ ቤት እንደመገንባት ይሆናል።
 
#ሰብዓዊ መብት እና ብልጽግና ይተዋወቃሉ ወይ???
 
አዋን ሆኖልን ሰብአዊ መብት አጀንዳው ቢሆን ብልጽግና ሥርጉትሻ ሁሉን ነገር እርግፍ አድርጋ በልጆች፤ በታዳጊ ወጣቶች፤ በወጣቶች ጉዳዮች ብቻ ላይ አተኩሬ በሰራሁ ነበር። የተስተካከለ የጤናም ሁኔታ በኖረኝ።
 
እስኪ የትኛው ካቢኔ፤ እስኪ የትኛው የካቢኔ አባል፤ እስኪ የትኛው የፓርላማ አባል፤ እስኪ የትኛው ሚኒስተር ሆነ፤ ምክትል ሚር በእስር ላይ የሚገኙ ወገኖችን ሄዶ እስር ቤት ጠየቀ? 
 
ከቅርቡ ደብረብርሃን እንኳን ሄዶ የተፈናቀሉ ወገኖቹን ማን አጽናና? በመተከል፤ በኦሮምያ ወላጆቻቸውን ያጡ ልጆች ሁኔታን ማን አጠና? ማንስ ደረሰላቸው? ቀድሞ ነገር ህፃናትን፤ ልጆችን በሚመለከት ባሊህ ባይም የለም እያልኩ ሁሉንም የፖለቲካ ድርጅት ማኒፌስቶ ስሞግት ነበር። በቅርቡ ህግ ረቂቅ ላይ ተወያያን የሚል ዜና ሪፖርተር ላይ ሰምቻለሁኝ። እሰየው ነው። መታሰቡ በራሱ ጥሩ ነገር ስለሆነ።
ጦርነት በተካሄደባቸው ቀየወች፤ በኮሪደር ልማት ፕሮጀክት፤ ከተማን ከሁለት ገምሶ አዲስ ከተማ ለመፍጠር በተከናወነው ሂደት ልክ የለሽ ዕንባ፤ ሰቆቃ፤ ፍርሃት እና ጭንቀት በህዝባችን ላይ ደርሷል። ማን አጽናና? ማን አይዟችሁ አለ? አንድ ቀን የሃዘን #ብሄራዊ ቀንስ ታውጆ ያውቃልን????
 
የጭካኔ ፋክክር ነው እኔ የማስተውለው። የጭካኔ ቅርስ እና ውርስ ይኖር ዘንድ ነው በስፋት የተሠራበት። የማይታወቁ አፋኝ ቡድኖች፤ የማይታወቁ እስር ቤቶችየማይታወቁ አጋቾች፤ የማይታወቁ አስገድዶ ደፋሪወች፤ የማይታወቁ ሠዋሪወች እንዳሉ ሁሉ ይደመጣል። ከቦታው ስለለሁኝ ነው አይደለም ማለት ባልችልም አሰቃቂ ዜናዋችን ግን አዳምጣለሁኝ። የህወሃትን መዋቅር ተሸክሞ፤ ማህበረ ኦነግን አማካሪ እና ሚር አድርጎ ሹሞ እራስን በትኩሳት ማጣደፍ ተፈቅዶ ስለሚከወን፤ የእኔ መልዕክት እግዚአብሄር ይማራችሁ ነው።
 
ማረሚያ ቤት ያለው ሁነት የተሻለ ነው ሲባል ሰምቻለሁኝ። ልጅ ተክለሚኬኤል አበበ ሲናገር ሰምቻለሁኝ። ግን ህግ በዋስ የፈታውን አፍኖ መውሰድ እንደምን ልብን በጦር እንደሚወጋ ብታውቁት። የሰሞናቱን የረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ አውግቸውን የትናቱን ትራጀዲ ማንሳት በቂ ነው፤ የባጄ ፕሮፋይል ከምናገላብጥ። በተለይ ውጭ ለምንኖር፤ አገራችን አፈራችን ለምንል እንዲህ ዓይነት ዜና ህመማችን ነው። አዘኔታ የለም። መተዛዘን የለም። ርህርህና የለም። ተሰደንም በምንሰማው አሰቃቂ የመብት ጥሰት ኑሯችን ይጎሳቆላል። 
 
የሆነ ሆኖ አይዟችሁ የከበደው፤ አጽናንቶ ለማያውቅ ሥርዓት እንደ መወያያ አጀንዳ "ሰብአዊ መብት" እንኳን ለዋና ምርጫ ለማሟያ ምርጫም ሊሆን አይችልም። በቀል እና ጥላቻ እስካለ ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰብዓዊ መብት ሊከበር ይችላል ብዬ አላስብም።
 
 

·       https://www.youtube.com/watch?v=s4OP-7caHbI

«ፌዴራሊዝሙ ምን ይሁን? ሕገ መንግስቱስ? -የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሞገቱበት አጓጊ መድረክ |ምርጫ2018| ማኒፌስቶ| manifesto| General Election»

 

 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
 
ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
28/02/2026
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።