ዕለተ አርብ ዕለተ ኢትዮጵያ! ዕለተ አርብ ዕለተ ኢትዮጵያ! ርጋ እንበለው ዕለተ ኢትዮጵያን በጎንደራዊ ትውፊት።

 

ዕለተ አርብ ዕለተ ኢትዮጵያ!
በከበቡሽ የቁራሽ እንጀራ ብራና
በሰብለ ህይወት አዝመራ
ለራህብ የሚራራ።
 
„የእግዚአብሔር ቃል ሁሉ ተፈትናለች
እርሱ ለሚታመኑ ጋሻ ነው።“
(ምሳሌ ምዕራፍ 29 ቁጥር 6)
 
 
 
• ርጋ እንበለው ዕለተ ኢትዮጵያን በጎንደራዊ ትውፊት።
 
ሥጦታው ለኮከብሻ ይሁንልኝ። ኮክብሻ „ጸሐፊ ቡና ያፈላል ወይ?“ ብለሽኛል። ጸሐፊ ሞሰብ ሰፊ መሆኑንም ልነግርሽ እሻለሁኝ። ይህ በፎቶ የምታይው ሞሰብ የእኔ ሦስተኛ ሞሰቤ ነው። የጎንደር ከተማ ልጅ ሞሰብ መስፋት ግዴታዋ ነው። መፍተልም። 
 
7 ዓመት ላይ ነው ዶሮ መበለት፤ ጭለሃ እንጎቻ መጋገር፤ መስፋት ውጥን ሰበጤራ ወይንም ሰፌድ፤ ፈትል እንድትማር ይደረጋል። ማጫዋ ነው። ቤትሽን ወዳድ እንድትሆኝም ነው ትውፊቱ። ከቤተ እግዚአብሄር ቀጥሎ ከቤቴ ውጪ እሚያስደስተኝ አንዳችም አመክንዮ የለም። ምንም። አደራጅነት መቀመጥ በእጅጉ ይሻል። ማሰብም መጻፍም አደብ ይጠይቃል። ለዚህ ሁሉ የረዳኝ አስተዳደጌ ነው። አብዝቶ መቀመጥ። አብዝቶ የሰከኑ ተግባራትን መከወን። 
 
እንደ ቤተሰቡ ደግሞ ይለያያል ልቅናው። ለምሳሌ የሽንብራ አሳ በዘመናዊ ወፍጮ የተፈጨውን የማይጠቀሙ፤ ነጭ እና ቀይ ስልጆ በዘመናዊ ወፍጮ የተፈጨውን የማይጠቀሙ፤ በእጅ የተፈጨውን የሚጠቀሙ ቤተሰቦች አሉ።
 
ጣዕሙ ቃናው ይቀዬራል ማሽን የነካው የሚሉ። ይህ የልቅናው ጥራት ነው። እኔ ያደግኩት ከዚህ ቤተ ሰብ ነው። ተፈጥሯዊውን ሙያን የሚመሰጡበት ቤተሰብ ማለት ነው። ለምሳሌ ጠጅ በእርጥብ ጎሾ እና በደረቅ ጎሾ ልዩነት አለው። ከእኛ በእርጥብ ዛላ ነው የሚዘጋጀው። ድፎም በውሃ የሚበስል። በኮባም አለ። አሁን ምቸት አብሽ እና ጥብስ ወጥ እንደ ቤቱ ይለያያል። 
 
ወደ ቀደመው ምልሰት ሳደርግ ይህን ሞሰብ እፊያውን የጨረስኩት ጎንደር ባታ በህወሃት እስር ቤት ሆኜ ነበር። አንዲት ውዴ ይህን ተግባር ለአንዲት ሥም ጥር ዓለም አቀፍ ጋዜጠኛ ነግራት ተቀጣጥረን መጥታ ተዋወቀችኝ። ፎቶውም አለ እኔ እና እሷ አብረን የተነሳነው። ሲለኝ ቀን እለጥፈዋለሁኝ። 
 
ሌላም ልንገርሽ አንድ ጊዜ በሚገባ የሚውቀኝ ሰው፤ አስተርጓሚ የማይፈልግ እጮኛ ነበረኝ። አዎንታዬን ከሰጠሁት በኋላ ጭንቅ ብሎት ለእህቱ እንዴት አድርጌ ነው እንደ ሚስት እማዛት ይላታል፤ ሥርጉተ ቤት ውስጥ እንደ ቢሮዋ አይደለችም „ታቸርም ለባሏ ሚስት ናት“ አለቸው። እሺ።
 
 
 
ሌላ ግጥሞቼ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለዬ ስልት የተከተለ ነው። በሞድ የተሠራ ነው። የሰው ሥጦታ ነው ወለቃ የሚሆነው። የላይኛው ከሆነ ቃናው የላይኛው ነው። በሰላማዊ ሰልፍ፤ በአመራር አስተዳደር፤ በበቤተ እግዚአብሄር፤ ስብሰባ በመምራት እና በማደራጀት፤ በማህበራዊ ኑሮ፤ በቤት ውስጥ ያለችው ሥርጉተ እንደ ጸጋዋ ህብራዊ ናት።
 
ሌላ ኮከብዬ በህይወቴ ሙሉ ቀልቤ አልባ ወጥቼ አላውቅም። በልብሴ፤ በፖርሳዬ ልክ ነው ቀልቤ ያለኝ በዚህ በሰለጠነውም ዓለም። ዛሬ ሙሉ ወርድ ቀሚስ የአማራ ሴቶች የእኔ ብለውታል። እኔ ወጣት እያለሁኝ በተለያዬ ቀለም እማሰራው እና እምለብሰው ነበር። ስለምን ብለሽ ብትጠይቂኝ አላውቀውም። ጉትቻው የገጠሬው ነው። 
 
ግን ከቤተሰብ በተለዬ ሁኔታ ለባህሌ ቀናዕይ ነበርኩኝ ማለት እችላለሁ። ዛሬ ሙሉ ወርድ ቀሚስ የሚሊዮኖች ሲሆን እህቶቼ ይገርማቸዋል። ዛሬ ላይ ሁሉ እንዲህ በፍቅር ልቡ ሲጠፋ ለሙሉ ወርድ ቀሚስ አይደለም ሌላው እኔንም ይገርመኛል።
 
ቤት ውስጥ በአንድ ቀለም የተሠራ አለሽ አይደለ ለምን ሦስተኛ አራተኛ እያሉ ቤት ይሞግቱኝ ነበር። ብቻ በርቀት የሚታዩኝ ነገሮች ነበሩ ይሆን? አላውቅም አንዱን ለጥፌልሻለሁኝ። ይህም ላንቺ ነው። 
 
እና የእኔ ንግሥት ኮከብይ ሞሰቤን ለአንቺ ክብር እንሆ ብያለሁኝ። 
 
ውዶቹ የኢትዮጵያ ቀንን አዘክርን ስንብት ላይ ነን።
ነገ መኖሩ ከተገኜ ሰንበትን በርትህ ፍለጋ የአቤቱታ አንባ እንገናኛለን።
 
ቅኖቹ የአገሬ ሲሳዮች ለነበረን መልካም ጊዜ አብሮነታችን ያዝልቀው እያልኩ ልሰናበት።
ኑሩልን ለእኔም ለቅኒት ኢትዮጵያም። አሜን። አይለያዬን። አሜን። 
 
እግዚአብሔር ይስጥልኝ።
ሥርጉተ - ሥላሴ (Sergute©Sselassie)
ዕለተ አርብ ዕለተ ኢትዮጵያ!(ከጭምቷ ሲዊዚርላንድ።)
ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር ነው።
ጎዳናዬ በጸጋዬ ውስጥ ያለችው ኢትዮጵያ ናት!

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።