#ኢትዮጵያ #ሳይንስ ናት። ኢትዮጵያ ፍልስፍናም ናት። ቋሚ #ፍልስፍናዬ ነው። ወጀብ የማይነቀንቀው።
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።
እንዴት ናችሁ ውቦቹ - ቅኖቹ - #የኔወቹ - #የእኛወቹም። ዛሬ በርከትከት ባለ ጉዳዬ ላይ አብረን እንቆያለን የሚል ትልም አለኝ። እንዴት አደራችሁልኝ ብዬ ስገባ ይህን መሠረቱ ያማረ ዜና አገኜሁኝ። ደስም ብሎኝ ላጋራችሁ ወደድኩኝ።
ከአቶ ዳኛቸው ጥላሁን ፔጅ ያገኜሁት ነው። አመሰግናቸዋለሁም ይህን ተሰምቶ የማያውቅ እሸት መረጃ ስላጋሩን።
ሥርጉትሻ 28/02/2026
*****=======*********
"ኢንጂነር ክበበው በልሁ
[መስከረም 16፣ 1926 – መስከረም 21፣ 2011]"
"ኢንጂነር ክበበው በልሁ ተወልደው ያደጉት ሐረር ከተማ ውስጥ ሲሆን በሙያቸው ኤሌክትሪካል ኢንጂነር ነበሩ። ኢንጂነር ክበበው አምስት ልጆችና ሰባት የልጅ ልጆችን አፍርተዋል። ኢንጂነሩ ስለ ሐረረ ከተማ አሪፍነት ተናግረው አይጠግቡም ነበረ ይባላል። ለልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው ሁሌ ስለ ሐረር መልካምነት ያወጓቸው ነበር ።
ልጆቻቸው የእሳቸውን ፈለግ ተከትለው በሳይንሱ ዘርፍ ላይሰማሩ ይችላሉ የሚል ስጋት ያደረባቸው ኢንጅነር ክበበው፤ በልጆቻቸው ልቦና ውስጥ ገና በለጋ እድሜያቸው የሳይንስን ስሜት ለማስረጽ በማሰብ ነው፣ ባልተለመደ ሁኔታ ለልጆቻቸው ከኤሌክትሪሲቲ/አቶም ጋር የተያያዙ ስሞችን አውጥተውላቸዋል፡፡
አቶ ክበበው፤ ለአምስቱ ልጆቻቸው ያወጡላቸው ስሞች፦
ፕሮቶን፣
ኒውትሮን፣
ዲዩትሮን፣
ኤሌክትሮን እና
ፖሲትሮን የሚሉ ስሞችን አውጥተዋል፡፡
ዶ/ር ኤሌክትሮን በስማቸው ብቻ አይደለም የሚለዩት፡፡ ከስማቸው በላይ ብዙዎችን ያስገረመው፣ በህክምና ሙያቸው አለም አቀፍ ዕውቅናና ዝናን ያተረፉ መሆናቸው ነው፡፡
ከአስር አመታት በፊት “ዊኪኦርግቻርትስ” የተባለ ተቋም “የአመቱ የአሜሪካ መንግስት 1000 ከፍተኛ ደመወዝ ተከፋዮች” በሚል ባወጣው ዝርዝር ውስጥ፣ ዶ/ር ኤሌክትሮንን ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ቀጥሎ ከፍተኛ ደመወዝ የሚያገኙ የመንግስት ሰራተኛ በማለት በሁለተኛነት አስቀምጧቸዋል፡፡
በአዲስ አበባ በሚገኘው ቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት የተማሩት ዶ/ር ኤሌክትሮን ክበበው፤ በአሜሪካ ሳንፍራንሲስኮ ከሚገኘው ዪኒቨርሲቲ ኦፍ ካሊፎርኒያ በህክምና የተመረቁ ሲሆን የአሜሪካን ቦርድ ኦፍ ሰርጀሪን የቀዶ ህክምና ሰርተፊኬትም አግኝተዋል፡፡
ላለፉት 30 አመታት በሳንፍራንሲስኮ በኢንዶክሪንና ታይሮይድ ካንሰር ዘርፍ የአጠቃላይ ቀዶ ህክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙት ዶክተሩ፤ በአሜሪካ ብሄራዊ የካንሰር ኢንስቲትዩት፣ የካንሰር ምርምር ማዕከል የኢንዶክራይን ኦንኮሎጂ ቅርንጫፍ ሃላፊ ሲሆኑ የካንሰር ጄኔቲክስ ክፍሉንም በበላይነት በመምራት ላይ ይገኛሉ፡፡
ዶክተሩ በእስካሁኑ የሙያ ዘመናቸው ከሁለት ሺህ በላይ የተሳኩ ቀዶ ህክምናዎችን ያከናወኑ ሲሆን ከ150 በላይ የጥናት ጽሁፎችንና መጽሃፍትን ለህትመት እንዳበቁ “ብሬኪንግጎቭ” የተሰኘ ድረገፅ አመልክቷል፡፡
የዶ/ር ኤሌክትሮን ሁለት ልጆች ራስ ኤሌክትሮን እና ኢዛና ኤሌክትሮን ይባላሉ።"
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ