#የሃሳብ #ጭስ እና ዓለማችን። #በእኛ ባልሆነ ጊዜ አለመኖራችን ያመሳጠረ ክስተት። #ፈጣሪ አምላክ በካህሊ ሥልጣኑ ለዓለማችን #ሰላም ያውርድ። አሜን።

 

#የሃሳብ #ጭስ እና ዓለማችን።
#በእኛ ባልሆነ ጊዜ አለመኖራችን ያመሳጠረ ክስተት።
#ፈጣሪ አምላክ በካህሊ ሥልጣኑ ለዓለማችን #ሰላም ያውርድ። አሜን።
 
#ምዕራፍ ፲፰።
 
"እግዚአብሄር በአንድም በሌላም
ይናገራል፤ ሰው ግን አያስተውለውምጽ።"
 
ግን ሦስት ዕርዕሰ ጉዳይን በአንድ የወግ ገበታ። እችለው ይሆን????
 
#የ27/02/2026 የደጓ ቪንተርቱር የጨረቃ ነገር።
 
ዕለተ አርብ ከውጭ ቆይቼ ወደ ቤቴ ስገባ ሰማይ ማዬት ስለምወድ ዋና በራችን እዬከፈትኩ ሰማይን ተመለከትኩ። #ጨረቃ ወጥታለች። በእስልምና ዕምነት ዘንድ ረመዳን ተናፋቂ ፆም ነው። ፆሙ መጠናቀቁ የሚታወቀው ጨረቃ ከወጣች ነው። አሁን ፆሙ አጭር ጊዜ ላይ እያለ ስለምን ጨረቃ #እንደወጣች በቀን አልገባኝ ስላለ ቲክቶክም፤ ፌስቡኬ ላይም አጋራሁኝ። ጨረቃ ከወጣች ፆሙ ይቀጥላል፤ ወይንስ ይጠናቀቃል? እሱ ግራ ገብቶኝ ነበር ፖስት ያደረኩት።
 
የሆነ ሆኖ ሰላምሽ #ይባካን ወይንም አይረጋ የተባለችው ዓለማችን ጭስ ውስጥ ናት። በሃሳብ #ጭስ ውስጥ። ወይንም በዚህ ሂደት ዘላቂ ሰላም ይረጋገጣል ይሁን የፋመ ጦርነት ላይ በሁሉም አቅጣጫ ዓለማችን ተወጥራ ትገኛለች። ጦርነት ከማባራት ይልቅ እራሱን እያራባ፤ እራሱን እያሰፋ የዓለም ህዝብ በጦርነት ስጋት ላይ ይገኛል። ፈጣሪ አምላክ የዓለምን ሰላም መርቆ ያጽናልን። አሜን።
 
#የዕለቱ መሪ ዕርዕስ። 
 
የኢራኑ ቁንጮ የሃይማኖት መሪ በሥጋ እንደተለዩ የዓለማችን በኽረ መሪ ዜና ሆኗል። ከምን ተነስተው የት እንደደረሱ፤ ፍፃሜውን አካቶ BBC ዘግቦታል። ይህን ዜና በብሥራትነት የሚዩት የመኖራቸውን ያህል፤ ይህን ዜና ሲሰሙ የሚደነግጡ፤ የሚያነቡ፤ የሚበሳጩ፤ እንደ ጥቃት አይተው የሚቆጩም፤ ጥቁር የሚለብሱም ይኖራሉ። በኢራን እንደ አገር የ40 ቀናት የሐዘን ቀን ታውጇል። 
 
ሃማስ በመስከረም 26 በዕለተ ጽጌ ፆም የፈጸመው መብረቃዊ ጥቃት በእስራኤል ላይ መዘዙ እዚህ አድርሷል። ያ ውሳኔ፤ ያ በፍጹም ጥንቃቄ የተደራጀ ኦፕሬሽን የፍልስጤምን ህዝብ ድቅቅ አድርጓል። ጦርነቱ በግራቀኙ ብቻ ሳይሆን በአጋር አገሮች፤ በጎረቤት አገሮችም ብዙ ህዝብ አልቋል። ብዙ እናቶች ትዳር አልባ ሆነዋል። ብዙ እህቶች ጥቁር ለብሰዋል። ብዙ ህፃናት መከራቸውን አይተዋል። የዓለም ፖለቲካም ፈተና ውስጥ ገብቷል።
 
ጥቃት ለመሰንዘር ሲታሰብ አጸፋውን ለመቀበል የተመሰጠረ ግዴታ ሊኖር እንደሚችል ፖለቲከኞች ከእርምጃ በፊት በጥንቃቄ ሊዩት የሚገባ ጉዳይ ነው። ሰበቡ በንጹኃን ላይ፤ በቀጣይ ትውልድ ላይ የሚፈጥረው ሰቆቃ ልብ ሊባል ይገባል። ከባድ መሳሪያወች መርዝ ነው የሚመግቡት ለመሬት። ስለሆነም የዛሬው ትውልድ ብቻ ሳይሆን የነገ ትውልድ ተስፋው ሞቶ እንዲመጣ የሚያደርግ ነው። 
 
የከባድ መሳሪያወች ግጥግጥ የዕለታዊ የጥቃት ሁነት አይደለም። የነገ አካሉ ያልተሟላ ትውልድ የመፍጠር ፈቃድም አለበት። ዛሬም ድኖ አይድንም ቁስለኛ ነው። ነገም በቃሬዛ ነው የሚመጣው። አካሉ፤ አዕምሮው ያልተስተካከለ ትውልድን ነገ የመፈለግ መከራ ነው የጦርነቶች ጋድም ስብርባሪ ስኬቶች።
 
በጦርነት ወቅት በድል ዘገባ እየፎካከሩ የሚሠሩ ዝልኝ ነፍሶች፤ ዛሬን ለማግኜት እርግጠኛ በማያደርግ መንደቅደቅ ነገን እሬሳህን አስረክበን ስለመሆኑ ሚዛን ውስጥ አይገባም። የሚበቅለው ትውልድ ያልሞላለት፤ የሚያበቅለው እህልም ዘረ መርዝ ይሆናል። ጦርነት አክሳይነቱ የተከታታይ የዘመናትን ተስፋ እየቀማ ይሆናል። ይህን ለማስቀረት ፍጹም ሰዋዊ፤ ፍጹም ተፈጥሧዊ፤ ፍጹም ኃላፊነት እና ተቀባይነትን የመቀበል ብቃትን ይጠይቃል። ጦርነት ተፈቅዶ እከሌ፤ እከሊት ትሁት ናት፤ ትሁት ነው ፋንታዚ ይሆናል።
 
ይህን ስጽፍ በአገሬ በኢትዮጵያ በመካሄድ ላይ ባለው ጦርነት፤ ጦርነቱ በሚካሄድባቸው ቦታወች ያለው የድሮን ፍልሚያ ነገን እንደሚገድለው እዬጎመዘዘኝ፤ እያሳዘነኝም ነው። ብልህነት አብሮ አልተፈጠረም፤ ወይንም ተሰዷል ማለት ይሆናል ጦርነትን ላለመጀመር መጠነ ሰፊ ትዕግሥት ሲጠይቅ፤ ከተጀመረም የተገኜውን ቀዳዳ ተጠቅሞ ወደ ምህረት፤ ወደ ሰላም መምጣት #መመረቅ ነው። መመረቅን መፃረር #እርግማንን መቀበል ይሆናል።
 
#በጦርነት ሥልጣኔን ሥልጣኔ አጥፍቶታል።
 
ጥላቻ ነግሷል። በቀል አገርሽቷል። ቂም ፋፍቷል። የሃማስ ድንገተኛ ጥቃት የሃማስን መሪወች አስበልቷል፤ በኢዝቦላ የደረሰው ውድቀትም ቀላል አልነበረም። በአካባቢው ያሉ አማጽያንን አስተባብሯል። የዓለምን ፖለቲካ #ገማምሷል። ወንጀልም ተበረታቷል። ክፋ ሃሳብ ፋፍቶ ጥላቻን አስብሏል። 
 
ይህ በየቦታው ያለው የጠሽ ጠው ፖለቲካ መቼ ይቆማል? #አናውቀውም። ምን - አተረፈ? {}። በጦርነት አትራፊ አለ ብዬ እኔ አላስብም። አትራፊ አለ ከተባለ #ጭስ#አመድ#ጥላቻ እና #በቀል ይሆናሉ የሚያተርፋት።
 
መሬት እራሱ ስትቃጠል፤ ስትነድ፤ ኤሉሄ አድነኝ ብላ አምላኳን ስትማጠን፤ ወደ አመድ ቅርሶቿ ሲቀየሩ መሬት ታነባለች። በተለያዩ ኬሚካሎች ስትቃጠል መሬት ታዝናለች። ነገ የሚወለዱ ልጆች #አካላቸው ብዙ እክል ሊኖርበት ይችላል ----- እና።
 
ዛሬ ችለው የሚያስተናግዱት ስደተኛ ተቀባይ አገራት በቃን! ሊሉም ይችላሉ። በዚህ ወቅት በገፍ ጦርነቱ በሚካሄድባቸው አገሮች የጦርነት #ሽሽት ወይንም መኖርን ጥለው ሊሰደዱ ይችላሉ። #የማይሸሹት እስራኤሎች ብቻ ሊሆኑ ይችላሉ። እንዲያውም ስደት ላይ ያሉት አቅም ለመመገብ ወደ አገራቸው ለመሄድ ይፈቅዳሉ - የእስራኤሎች ባህል ከመከራ መማር ነውና።
 
#ኢትዮጵያ ከዚህ ምን ትማራለች???
 
ይህ ሁነት ለኢትዮጵያ ትልቅ ሌሰን የሰጠ ይመስለኛል። ልብ ላለው፤ ህሊና ላለው የፖለቲካ መሪ። የመኖር ቀን እንዲህም፤ እንዲያም ብሎ ይጠናቀቃል። የእግዚአብሄር ቃል "የመዳን ቀን ዛሬ ነው" ይላል። ዛሬን - አክስሮ፤ ለነገ ኪሳራ ላለማውረስ "ልብ ያለው ሸብ" የጎንደሮች ቅኔ ነው። አሁን አያቶላ ከ5 ዓመታት በፊት በዚህ መልክ ፍፃሜያቸው ይሆናል ብሎ ማን አስቦ ያውቃል። 
 
ሰሞኑን እምዬ ሲዊዘርላንድ በጄኔባ ተከታታይ ውይይት ነበር። ለካንስ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ብቻ አይደለም ሰው የማትረፍ ልማድ የሌለው። በአገራቸው ያ ሁሉ ነፃነት ፈላጊ በግፍ አልቆ፤ የቆሰለው ቀጣይ ቅጣቱን ፈርቶ ስቃዩን አቅፎ ተቀምጦ መዳን ለማደን የተከፈተውን በር ተጠቅሞ ማትረፍ ሲገባ ሌላ የእልህ ጥሪ መሪ አልባ ሁነት ፈጠረ። 
 
የኢራንውያን የሰሞናቱ የለውጥ ፈላጊነት እና የጅምላ ፍጅት ዕንባ፤ የኢራንን ተከባሪ የሁለመና መሪውን እና ቤተሰቡን ከሞት አላዳነም። መሪወች በቆሙባት ሰከንድ ላይ #ሰዋዊነትን ቀምረው፤ ፖለቲካ ለሰው መሆኑን ተረድተው፤ ሥልጣኑም ክብሩም በቃን! ሊሉ ይገባል። ይህን ባይችሉ እንኳን ለእነሱ ስልጣን ማቆያ ፋፍሪካ የዜጎች ጥቃት ሊሆን እንዳይችል ማስተዋልን ምራኝ ሊሉ ይገባል ባይ ነኝ።
 
በሁሉም ዘርፍ ያለውን ውጥረት ለማርገብ ህዝብን ይቅርታ ጠይቆ ጊዜውም የፆም ነው ጠንካራ የፆለት ጊዜ ዓውጆ ከህዝብ መንፈስ ጋር ብቻ ሳይሆን ከፈጣሪ ጋርም ለመታረቅ ዝቅ ብሎ ይቅርታ መጠየቅ ይገባ ነበር። ከ40 የሃዘን ቀን በፊት 40 የጸሎት እና የድዋ ቀን አትራፊነቱ ረቂቅ ነበር። ፖለቲካ ከትዕግሥት፤ ከብልህነት፤ ከዊዝደም እና ከሰዋዊነት ጋር ከተራራቀ መጨረሻው ይኽው ነው።
 
የኢትዮጵያ የፖለቲካ መሪወች የመንግሥት ይሁኑ ከፋኝ ያሉ ታጣቂወችም፤ በድጋፍም በተቃውሞ ያሉ ይሁኑ ማዕከላቸው #ሰዋዊ እና #ተፈጥሯዊ ማድረግን ምራኝ ቢሉ፤ ሰው ማዳን፤ ሰው ማትረፍ ላይ ተግተው ቢሠሩ ጥሩ ነው።
 
ከሁሉ በላይ ህዝብን ይቅርታ መጠየቅ ሊከብዳቸው አይገባም። በጠፋው ጥፋት ላይ ከምር እራስን ወቅሶ ምህረትን ከፈጣሪ እና ከህዝብ መጠየቅ ብልህነት ነው። ዛሬ ሳይሆን ጊዜ ያለው፤ ይህቺ ደቂቃ ብቻ ናትና ያለችው።
ቀጣዩ ደቂቃ ምን ሆኖ፤ እንዴትም ሆኖ እንደሚመጣ ማንኛችንም አናውቀውም።
 
 https://www.bbc.com/amharic/articles/c7vr51471vqo
 

አያቶላህ አሊ ኻሜኒ፡ ከልጅነት እስከ ዕውቀት፣ ከእስር እስከ ስደት፣ ከአብዮተኝነት እስከ መሪነት

 
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
01/03/2026
ምህረት ለዓለማችን ይሁን። አሜን።
አያቶላህ አሊ ኻሜኒ፡ ከልጅነት እስከ ዕውቀት፣ ከእስር እስከ ስደት፣ ከአብዮተኝነት እስከ መሪነት - BBC News አማርኛ

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።