አድርሽኝ በጎንደር። ልዕልት ጎንደር ደንብ፤ ድንጋጌ፤ አንቀፃት የሚደመሙባት #ህግ ናት። ጎንደር ለእኔ መነኩሴ ናት። ጎንደር ከተማ የምትመስጥ ገዳምም ናት።

 

አድርሽኝ በጎንደር። ልዕልት ጎንደር ደንብ፤ ድንጋጌ፤ አንቀፃት የሚደመሙባት #ህግ ናት።
ጎንደር ለእኔ መነኩሴ ናት። ጎንደር ከተማ የምትመስጥ ገዳምም ናት።
 May be an image of text
 
#ምዕራፍ ፲፱።
 
ሳይሽ እውላለሁ
ከልቤ አስቀምጬ
ሳይሽም አድራለሁ
እቅፍ አንተርሼ
አወሳሳሻለሁ አድርሽኝ ለብሼ
አንችን እየሳሳሁ ናፍቆትን ደቁሼ
መቼም አይሻለሁ
ተፈጥሮን አቅስሼ
እሳሳልሽ- አለሁ እቅፍ አንተርሼ
እንደ ወጣሁ አይቀር
አይቀር እንደ መሼ።
#ለህትምት የበቃ።
 
"የሰው ልብ መንገድ ያዘጋጃል
አካሄዱን እግዚአብሄር ያሳካለታል።"
(ምሳሌ ፲፮ ቁጥር ፱።)
 
የአብሮነት --- እመቤት
የልቅና --- ማህሌት
የመቻል ----- ተምሳሌት
የጽናት ------ መሠረት
የድንጋጌ --- #አናት
የሥልጣኔ ------እናት
ኦ! ጎንደርዬ ህይወት።
 
አድርሽኝ በጎንደር ልዩ ቃና፤ ልዩ ማዕዛ፤ ልዩ ጥርኝ፤ ልዩ ናፍቆት፤
ልዩ ቤተሰባዊነት፤ ልዩ የምህላ፤ የሱባኤ የአኃቲነት በማህተም
የሚረጋገጥበት ወቅት ነው።
 
እቴጌ ጎንደር #የተሰጣት ባዕት ናት። እርግጥ ፈተናዋ ብዙ ነው።
ፈተናዋ ምንጩም በርከት ያለ ነው። 
 
ዕውነት ቦታውን ለቆ፤ ሌላውንም ተጋፍቶ የማያስለቅቅ በመሆኑ በጊዜ
ሰሌዳ ውስጥ ልዕልት ጎንደር ክብሯ፤ ሞገሷ፤ ደርባባነቷ፤ ውይዝርናዋ
ሳይወዛወዝ፤ #ሳይብተከተክ ወይን ብል እንደበላው ጨርቅ #ብትንት ሳይል ቀጥሏል።
ወደፊትም ይቀጥላል። 
 
እመቤት ጎንደር #ማንጠግቦሽነቷ ከዕውነት፤ ስለዕውነት የጠራ፤ ስኩን
የሆነው የአቨው፤ የእመው ምርቃቷ እቴጌዋን ፈጥሮ አጽድቆ #አስብሎም አስቀጥሏታል።
የእቴጌዋ አድማጭነት፤ የልዕልቷ ስክነት የተፈጥሮዋ ድንግልናዋ የፈጠረው
ረቂቅ መሰጠት ነው። እቴጌ ጎንደር ክስተትም ናት። ሽልማትም።
 
የባህል አውራነቷ ይሁን፤ የዕምነቷ ሥርዓታዊ ጉዞ ሰውን ከማቅረብ፤ ሊቅነትን
ከመናፈቅ በመሆን #ካስማ የተቀመመ ስለሆነ ዝልቅ የህሊና ብቃቱ አንቱ ነው።
 
ዓራት ዓይናማዋ ጎንደር በመኖር ውስጥ ህልዊነትን በተደሞ #ከሽና የምትለግሰው ዕውነቷ
የትኛውንም ፈተና፤ የትኛውንም ወጀብ፤ የትኛውንም ጦሮ የመቋቋም አቅሟ ከተፈጠረችበት
የሊቀ - ሊቃውንት ጥበብ እና ዊዝደም ይፈልቃል።
 
እናቱ ጎንደሪና ፍልሰታዊ ሱባኤን በሚገርም፤ እጅግም በሚደንቅ ልዩ ድባብ ተቀብላ
የምታስተናግድበት ኩነት የመሰጠቷን ሁነት ያመሳጥራል።
 
ፍልሰቲ ጎንደር ላይ ከልጅ እስከ አዋቂ ፍጹም በሆነ የውስጥ ሐሤት በጋራ፤ በወል
ይስተናገዳል። 
 
ለልጆች የመክለፍት #ከረጢት የሚዘጋጀው ቀድሞ ነው። እያንዳንዱ ልጅ ከረጢት ይዘጋጅለታል።
ከረጢቱ ከአንገት የሚገባ ነው። 
 
ከረጢቱ ከቁርባን በኋላ ልጆች እህል #ሳይቀምሱ መናገር ስለማይፈቀድላቸው በየቤተ - እግዚአብሄሩ
የሚዘጋጀው መክለፍት ሥርዓቱ ሙለ ለሙሉ ከተጠናቀቀ በኋላ ስለሚታደልም፤ ለልጆች ልዩ መክለፍት
በልዩ ሁኔታ ይዘጋጃል።
 
ያቺ ከረጢት ዛሬ ውጭ አገር በአንገት አስገብተው የሞባይል ስልካቸውን የሚይዙበት ዓይነት ናት።
በከረጢቷ #ቤት ያፈራውን፤ በቆልት ይሁን ቆሎ፤ ቆሎ ይሁን ዳቦ ብቻ ለልጆች የራህብ ማስታገሻም፤
መናገር እንዲችሉም ይለፍ ይሰጣል።
 
የፍልሰቲት ፆም ፊት ለፊት ያለውን የአድዮ ንግሥና፤ የአዲስ ዓመት የምስራች ውል የሚያዋውል፤
የቃልኪዳን #የየምሥራች ዜና ነው።
 
ፍልሰቲት ባአመዛኙ የልጆች የአትኩሮት፤ የልጆችን መንፈስን የሚያሰባስብ ፆም ነው። ለአዋቂወችም
#የንስኃ ጊዜ ነው።
 
ህፃናትም ዕለተ ሰንበትን ተንተርሶ ይቆርባሉ፤ ዓዋቂወችም ቅዱስ ቁርባንን የሚቀበሉት ባመዛኙ
ሰንበት ላይ ከህፃናት ጋር ነው። 
 
ከቅዳሴ መልስ አመሻሽ ላይ #አድርሽኝ የሚባል ልዩ መሳጭ ባህል እቴጌ ጎንደሪ እና አላት።
የሰፈሩ ሰው ማታ ማታ ይገናኛል። አንድ #ሙሴ ይኖራል። ሂደቱ በቋሚነት የሚከወነው በሙሴው
ቤት ነው። ሁሉም ተራ ይደርሰዋል። መክለፍቱን ይዞ ወደ ሙሴው ቤት ይሄዳል።
 
ሰዓት አይታለፍም። የተቀናጣ ድግሥም አይፈቀድም። የእመቤቴ ወዳጆች ቀን አብረው አስቀድሰው
ከማታ በፊት የወንጌል ስብከትም ተካታትለው፤ ከዛ መልስ ወደ ሙሴ ቤት ነው።
 
ፍቅሩ ልዩ ነው። ቃል- ኪዳኑም የጸና ነው። ከህብራዊነቱ ቆይታ በኋላ ወደ ቤት ሲኬድ ሌላ
ቤተሰባዊነት #ህብሬ ይጠብቃል።
 
መሬት ላይ ይነጠፋል። ምህላ ይጀምራል። የምህላው ዜማ ከየትኛውም የዜማ ዓይነት ይለያል።
ትንሽ እስቲ …… 
 
#ኦ! ማርያም፥
እለምንሻለሁ ባሪያሽ
እስኪ አንድ ጊዜ ስሚኝ ቀርበሽ
ከአጠገቤ ቁመሽ ………
 
ምህላው ከእመቤት ይጀምር እንጂ የቅዱሳን ገድላት፤ የመላዕክታኑ የአማላጅነት ተደሞ ሁሉም
በዜማ፤ መምህር በሆነ አስተምህሮ ቤተሰቡ በአንድ ላይ ሲለው የዜማ፤ የቅኔ ልዩ መሰጠትም
#ይቆምሳል። ድባቡ ልዩ ፍጹም ልዩ ነው። ከዚህ አንፃር በምልሰት የዜማውን አቅም ሳስበው
ሙሉ ቤተሰቡ ዘማሪ የመሆን አቅም ነበረው። 
 
ከምህላ በኋላ መነጋገር፤ መውጣት መግባት አይፈቀድም። ከተሰናዳልን ቦታ ገደም ብለን
እናሸልባለን።
 
ቤተሰቡ የካህን ከሆነ ሌሊት ደግሞ ወደ ቤተ - እግዚአብሄር ከአባቶቻችን፤ ከሚታወቻችን ጋር
አብረን እንሄዳለን። የሂደቱ ሥርዓት እራሱ #የፍልሰቲት ህገ - መንግሥት ማለት ይቻላል።
 
ሱባኤው ሲጠናቀቅ ደግሞ #ርጋን በጋራ ሁሉም እንደዬ አቅሞ አዋጥቶ በወል፤ በመከባበር
ውስጥነት ከሙሴው ቤት ፆሙ ይፈታል። 
 
ይህን አድርሽኝ ወደ ማህበርም የሚያሳድጉት ነበሩ። ጎንደር እራሷ #ህግ ናት። ጎንደር እራሷ ድንጋጌ ናት። 
ጎንደር እራሷ አንቀፅ ናት። ይገርመኛል እኔ ከፖለቲካ ጋር ቀያይጠው መንፈሷን የሚዲፈሩ ሰብዕናወች ሳደምጥ። 
ለማዘዝም ሲቃጡ። የጎንደር መንፈስ ድባቡ ፍጹም ልዩ ነው። 
 
ጎንደር ለእኔ መነኩሴ ናት። ጎንደር ለእኔ ገዳምም ናት። #እንደባቲካን ልትሆን የሚገባት የመጨመት፤
የመረጋጋት፤ የመስከን ልዩ ዓርማ ናት። 
 
የእኔ ክብሮች የቤተ ሥርጉትሻ ቤተኞች ይህን የምታውቁት ልዕልት ጎንደርን አግልሎ በመጫን ሳይሆን
ከውስጣችሁ ተቀብላችሁ ጎንደር ማን ናትን "ሀሁ፤ ለሉ" ብላችሁ፤ ፊደል ዘርግታችሁ፤ አቡጊዳን ሄውዞ
ቀጥላችሁ መልዕክተ የኋንስን መዝለቅ ሲቻል ብቻ ይሆናል።
 
ጎንደር እራስ እግሯ ዕውቀት እና ቅኔ ናት። ልዕልት ጎንደር #ማህባዋ ይስባል፤ ፍቅሯ ይጣራል፤
ሁለገቡ ብቃቷ ልቅናን - በልዕልና ያውጃል።
 
የልብ የሆኑ ሲዊዛዊ ወዳጅ አሉኝ። በዘመኑ ፈተና ላይ ስንወያይ ይህማ አይሆንም አሉኝ።
የእኔ የቆዳ ቀለም የለወትም። ከአፍሪካም አልመጡም። ባልኖሩበት ህይወት ሊያውቁት
አይችሉም። ራህብን የማያውቅ ራህብ ምንድን ነው ብሎ ቢጠዬቅ እራሱ ተጠያቂው
ራህብ ምንድን ነው ብሎ መልሶ ይጠይቀወታል አልኳቸው። እውነት ነው አሉኝ።
 
ስለ ጎንደር የሰውነት ልክነት በመኖር ውስጥ የሚገኝ እንጂ በስማ በለው የሚሆን አይደለም።
የሚበረግጉ፤ የሚክለፈለፋ፤ እንደ ፌንጣ - #የሚዛለሉ፤ ፈርሶ ሲሠራ፤ ተሰርቶ ሲፈርስ፤ ወይንም
ተለቅሞ ሲፈስ፤ ፈሶ ሲለቀም ውሎ የሚታደረው ማናቸውም ክስተት "ሙያ በልብን ልብ።"
"ልብ ያለው ሸብን" "ልክን ማወቅ ከልክ ያደርሳልን" ሰንቃ ለኖረች ለአፍሪካ ብቸኛዋ ፓላስ
ለጎንደር አይመጥነውም።
 
እኔ ተወልጄ አድጌባት።
ለሥራም ደርሼ አገልግያት።
ቆላ * ደጋ * ወይናደጋ #በእግሬ ከርተት ብዬ፤
ዳገት ቁልቁለቱን፤ ዳጡን ሙላቱን አይቻት ግን የጎንደርን ውስጥ አውቀዋለሁ ብዬ ልንጠራራ አልችልም።
በፍጹም። የጎንደር - ሙዳዮዋ፤ የጎንደር - አገልግሏ፤ የጎንደር - ሞሰቧ ሁሉም አለው። 
 
ሌላው ቀርቶ አክርማ፤ ሰበዝ ሽሮ፤ በርበሬ፤ እልበት - አብሽ፤ ማበሻ፤ ማገዶ የምታዘጋጅበት ቋሚ የተግባር #ሰሌዳ
ልዕልት ጎንደር አለት። 
 
የሆነ ሆኖ ዘልፈው የማይጠቅማቸው ያላዮዋት፤ የማያውቋት እሷም እማታውቃቸው ልምራሽ
ማለታቸው የሚቻል አይደለም። የፋክት ግጬት አለና። 
 
ጎንደር በእንግድነት ታይታ፤ ወይንም ሳትታይ ቀርቶ ሲዳፈሯት ይሰቀጥጣል። እቴጌ ጎንደር እኮ!
#መጸሐፍ ናት። መጽሐፏን ማንበብ መቻል መታደል ነው። ይህም ቢሆን ጎንደርን አንብቦ ያጠናቀቀ
የለም። መተርጎም ማመሳጠር ግን ለተሰጣቸው ብቻ እንደ ጸሐፊ አቶ አለማየሁ ገላጋይ፤ ወይንም
እንደ ተጓጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ለንጥር ማንነቷ ውስጥነት ውስጧ ስለሆኑ ብቁ ናቸው። 
 
/// ልከውነው። ///
 
ዝምታው አቅም ጠፍቶ አይደለም። የሚበጀው መታገስ ስለሆነ ብቻ ነው። አንድ ቀን ግን ትዕግሥት
ሲያል ፍቅር ይሰደዳል፤ ፍቅር ሲያልቅ ትዕግሥት ይሰደዳል።
 
ክብረቶቼ እንዴት ናችሁ።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergutte©Selassie.
15/08/026.
ኑሪልኝ በክብርሽ ልክ ጎንደሯ። አሜን።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።