"ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኽ።" "ቀድሞ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ አሁን ምን ያደርጋል ወጭት ጥዶ ማልቀስ።"
"ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኽ።"
"ቀድሞ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ
አሁን ምን ያደርጋል ወጭት ጥዶ ማልቀስ።"
"አገራዊ" ምክክር ኮሚሽኑን ሳስብ ሟቹ ተስፋዬ ገብረአብ ታሪክን እንዳይደግመው እሰጋለሁኝ። የሆነ #ልብወለድ ታሪክ በአዲስ እንደ ቡርቃ ዝምታ ኮሚሽኑ ይፃፍ ይሆን እላለሁኝ። ኢትዮጵያን #ተቀላች፣ #ተጠማኝ፣ #ጥገኛ፣ #ምርኮኛ የሚያደርግ የታሪክ ዝገት በራስ አገር ልጅ እንዳይፈጠር ያሰጋኛል። አዲስ አበባ "ክልል ትሁን፣ አዲስ አበባ ራስ ገዝ" ትሁን ከውድድር ውጪ የሆነበት ሁኔታን ከውስጤ ሳስበው።)

#ምዕራፍ ፲፱።
1) #የአብን እና የብልፄው ፍቺ በአገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአቅም ኩነት ላይ።
2) "#የአገራዊ" ምክክር ኮሚሽን አብን ስላቀረበው ቅሬታ የሰጠው ማስተባበያ።
3) "#የአገራዊ" ምክክር ኮሚሽኑ የመብት ልክን ያጋለጠው የአቶ ያሬድ ኃ/ማርያም መረጃ (የህግ ባለሙያ እና የሰባዕዊ መብት ተሟጋች።)
BBC የኮሚሽኑን ማስተባበያውን ይዞ ወጥቷል፣ የአቶ ያሬድን መረጃ እና የአብን #ደፋር መግለጫ ከፌስቡካቸው ያገኜሁት ነው።
"ልብህን በምግባር አቅና፣
መከራውንም ታገስ፣
አትጠራጠር በመከራውም
ብትጠራጠር አትጠራጠር።"
(መጽሐፈ ሲራክ ምዕራፍ ፪ ቀጥር ፩)
አቅምን መጥኖ ማስተዳደር ይገባል። የኦሮሞ ብልጽግና ፍላጎቶን በግልጽ ሲያሳውቅ ነው የኖረው።
ያን አድምጦ አቅምን በቅጡ መያዝ፣ የአቅም መግቦቱንም ማመጣጠን ይጠበቅ ነበር።
ሌላው ወሳኝ ጉዳይ ለመደገፍ ይሁን ለመቃወም እንዲሁም እንደ እኔ #ለመሞገት የዘመኑን የፖለቲካ ባህሬ አጥንቶ መነሳት ይገባል።
ዴሞግራፊን እኔ #አሉታዊ እና #አወንታዊ ብዬ በሁለት እከፍለዋለሁኝ። እኔ ግማሽ ሚሊዮን ነበር የሰማሁት አሁን ከመሼ አንድ ሚሊዮን እንደሚሆኑ ከሱማሌ ክልል ወደ ሽዋ ጠቅላይ ግዛት እንደተዛወሩ አድምጫለሁኝ።
ይህ አሉታዊ ዴሞግራፊ ነበር። ረዘም ላለ ጊዜ ሠርቸበታለሁ። ከዚህ ጋር የአዲስ አበባን የነፃነት ቁመና ሳጠናው፣ አዲስ አበባ #ነፃነቷን ለኦሮምያ ክልል እንደ ተሰጠ ስለገባኝ፣ ከመስከረም 5/2011 ዓም ጀምሮ አዲስ አበባ በኦሮምያ ሥር ናት። ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ የምትሹ ኦሮምያ ክልልን ፈቃድ ጠይቆ ወይ አሳውቁ ስል ተረብ ይመስል ነበር።
ሌላው ነገረ አዲስ አበባ ጎላ ብሎ ሲነሳ ነፃ እርምጃ አለ። በ2011 መስከረም ላይ አዲስ አበባ ላይ 5 ነዋሪወች ነፃ ርምጃ ተወስዶባቸዋል። ሰሞኑን በማዕከላዊ ኢትዮጵያም ሦስት ባተሌወች ነፃ እርምጃ ተወስዶባቸዋል። ይህ በራሱ ውስጥን ሰላም ይነሳል።
የሰው ልጅ ጊደር፣ በግ፣ ፍየል፣ ዶሮ አይደል። ደም የሚሻ ባህል ከኖረ የእንሰሳት ቢሆን ምን አለ? ውጭ ከወጣሁ በኋላ የእንሰሳትን እርድ በዓይኔ ማየት አልችልም።
ሌላው በአዲስ አበባ ጉዳይ ጠቅላይ ሚር አብይ #ብስጩ ናቸው። ይህ በራሱ የሚሰጠው ግብረ መልስ ነበር። የአቅም መግቦቱን ይሁን የመተማመን አቅሙን በልኩ ለመያዝ። ቆርጦ መጣላት ጥሩ አይደለም። ጠቅልሎ መግባትም እንዲሁ። ሙቀቱን እያዳመጡ እንዳይናቁ በልክ ማድረግ ይገባ ነበር።
የሰማይም የምድርም ቁጣ ነበር። ያን ማድመጥ ቢሳን …
1) ሌላላው ይቅር አዲስ አበባ ላይ በ6ኛው ይሁን በ7ኛው አገራዊ ምርጫ አብን እራሱት ችሎ እጩ ለማቅረብ ለምን ተሳነው? "አዲስ አበባ የአማራ ናት፣ በራራ የዳዊት ከተማ ሲል አልነበረምን?"
2) "በአገራዊ" ምክክሩ ላይ አብን አዲስ አበባ የማናት ለሚለው የራሱን አቋም ለምን አላቀረበም?
3) በመጠነ ሰፊ የተከወነው #አሉታዊ ዲሞግራፊን አብን እንደምን አስተናገደው?
በአብን ዙሪያ ብዙ በጣም ብዙ አመክንዮ አንስተን ልንሞግተው እንችላለን።
የሆነ ሆኖ የሰሞናቱ የአብን መግለጫው #ደፋር ነው። ጥንቅቅ፣ ጥርቅምቅም ያለም ነው። "አይጥ ለሞቷ የድመት አፍንጫ" ታሸታለች ሁኖ ሌላ ነገር ካላስከተለበትም ዕድለኛ ነው።
ሰላማዊ ትግል ከዘለፋ፣ ከማቃለል፣ ከማጣጣል፣ ተላቆ በፋክት ጉዳዮች ላይ ህገ - መንግሥቱ ቢታመንበትም ይሁን ባይታመንበት አክብሮ ገዢውን የፖለቲካ ድርጅት ብልፄውን መሞገት አያግድም። አይከለክልም።
አብን እራሱን #እረስቶ ነው የባጀው። በውነቱ እኔም አብን እና ባልደራስን ረስቻቸዋለሁኝ። ያ ሁሉ ሰብ ለካቴና፣ ሰማዕትነትን የተቀበሉም አሉ። ለዚህ ነው ሰሞኑን የሁሉም አጀንዳ አብን ሲሆን ዝም ያልኩት። ዛሬም ኮሚሽኑ በቅሬታው ዙሪያ መልስ ስለሰጠ ነው ለንጽጽር ያቀረብኩት።
"አገራዊ" ምክክሩ የአብን ቅሬታ ውድቅ ማድረጉን ቢቢሲ አስነብቦናል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ያሬድ ኃ/ማርያም ደግሞ "#ሁነኛ" ያሉትን መረጃ አቅርበዋል። "አገራዊ" ምክክር ኮሚሽኑ ጉዳዩን አሰባስቦ ለጉባኤ ካበቃ በኋላ የመንፈሱ ማዕከላዊ #ካፒቴን ሌላ አካል ያስረከበ ስለመሆኑ አበክሮ ያብራራል መረጃቸው።
ከዚህ አንፃር "የአገራዊ" ምክክሩ ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርያ ለአብን ቅሬታ የሰጡትን መግለጫ ሚዛን አልቦሽ ያደረገው ማህል ላይ የአቶ ያሬድ መረጃ አለ። ኢዜማም በስሱ መጣሁ ቀረሁ የሚል የአካላቱ ቅሬታ ስለአዳመጥን። ጉርምርምታ ነው የኢዜማ ፈራ ተባ እያለ። በድርጅት ግን የቀረበ የለም።
የኦሮሞ ብልጽግናን ፍላጎት ለማሟላት ይህን ያክል ወጪ፣ ይህን ያክል ድካም በሌለ ጎኗ ኢትዮጵያ መባተል አይገባትም ነበር። ሃሳብ የሰጡ፣ የሞገቱ ሰብዕናወች ሊጎዱ ይችላሉ። አላስፈላጊ መስዋዕትነትም ሊከፍሉ ይችላሉ።
ብልፄው የሚፈልገውን በፈለገው ጊዜ ዓውጆም ይሁን #አዞ መፈጸም ይችላል። ፎርማሊቲ አያስፈልግም።
ምርጫ 100% ብልፄው አሸንፎ ለተጠማኞች #ምደባ አድርጓል። ልክ እንደዛ፣ ወይ እንደ ጫካ፣ ኮሪደር፣ ሆቴል ፕሮጀክቶቹ ወጭ ገቢ አትጠይቁኝ ብሎ የፈቀደውን ማድረግ ይችል ነበር።
ፈጣሪ አምላክ ይህን አሳቻዊ ዘመን #ረብ የሚያደርግ መላ ይፍጠርለት። ቅኑ ህዝባችን ወህ የሚልበት ዘመንን የላይኛው ይለግሰው። አሜን።
#የምክክር ኮሚሽኑ ሎጎ የኢትዮጵያዊነት ውስጥነት የለውም።
የምክክር ኮሚሽኑ ሎጎው እኮ ይናገራል። ኢትዮጵያን የሚመስል አንድም ጠረን የለውም። #የኢነርጂ ንድፍ ነው። እኔ ቀለሙን የዶር አብይ ቀለም እለዋለሁኝ በእሱ ተቀምሮ የቀረበ ነው። ምን አልባት ብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማ ላይ ቀለሙ ሊመጣ ይችል ይሆናል። ዲዛይኑም።
ሎጎ ኢትዮጵያን - ያሰበ፣ ውስጡ - ያደረገ፣ የእኔ ያለ ህዝባዊ ይሁን መንግሥታዊ ተቋም ኢትዮጵያዊ የሆነ ጠረን ሊኖረው ይገባ ነበር። "የአገራዊ" ምክክር ኮሚሽኑ ሎጎው ልሙጥ ነው። መንፈሱ እኛን ፈጽሞ አይመስልም። ባዕድ ነው። ከኢትዮጵያዊነት በፍጹም ሁኔታ የራቀ።
ይህም ቢሆን ግን ዘመን ባመጣው ጉዳይ በስማ በለው ከሚሆን ዕድሉን ያገኙ ወገኖቻችን መሳተፋቸው የተገባ ነው። በተሳትፎ ውስጥ ያላቸው ሚና ነው ወሳኙ።
በሌላ በኩል መንግሥትነት ወቅትን ማዳመጥ የብልህነት መለኪያ ሊሆን ይገባል። የማህበረ - ኦነግን የኖረ ፍላጎት ለማሳካት እራስን አጣብቂኝ ውስጥ መክተት አያስፈልግም ነበር።
አሁን መንፈስ የሚበትን ሳይሆን፣ አሰባሳቢ የሆነ #ንጽህና ይጠይቅ የነበረበት ጊዜ ነበር። ኢትዮጵያ ላይ ፊት ለፊት የተደቀነው አደጋ ግዙፍ ነው። አማኑኤል ይሁናት። አሜን።
ክብሮቼ ሁሉንም ብታነቡት ጥሩ ነው። ኑሩልኝ። አሜን።
ቸር አስበን፣ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፣ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
17/08/026.
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ
ታትሟል ከ 2 ሰአት በፊት
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ
• "የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ በምክክሩ ሂደት ላይ "ከተራ የአሠራር ግድፈት" የዘለሉ "ተደጋጋሚ እና የተደራጁ ጥፋቶች ተፈጽመዋል" ሲል ያቀረበውን ክስ ውድቅ አደረገ።"
"አብን ቅዳሜ ነሐሴ 09/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በሀገራዊ ምክክሩ "ገዢው አካል መዋቅራዊ ጥሰቶችን" እንደፈጸመ በመጥቀስ በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ "የከተማዋ ነዋሪዎች ድምፅ እና ፍላጎት በአግባቡ ሳይወከል" ታልፏል ብሎ ነበር።
ፓርቲው በዚሁ መግለጫው ላይ ሂደቱ ውስጥ ታይተዋል ያላቸውን "አግላይ እና አፋኝ አካሄዶች" በተመለከተ ለሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በደብዳቤ አቤቱታ ማቅረቡን ገልጿል።
ይህንን የአብን መግለጫ በሚመለከት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሰኞ ነሐሴ 11/2018 ዓ.ም. በሰጠው ምላሽ የምክክር ሂደቱ "አካታች እና አሳታፊ አይደለም የሚለውን የአብን አቋም ኮሚሽኑ ተገቢውን ምርመራ እና ማጣራት" ማድረጉን ገልጿል።
ኮሚሽኑ አክሎም ባደረገው ምርመራ እና ማጣራት የፖለቲካ ፓርቲውን ድምዳሜ "የማይጋራው" መሆኑንም አስታውቋል።
አብን ቅዳሜ ዕለት ባወጣው መግለጫ በምክክር በሂደቱ ውስጥ የታየው ሁኔታ ከተራ የአሠራር ግድፈት ወይም ከመደበኛ የፓለቲካ ልዩነት የዘለለ ሆኖ እንዳገኘው ጠቅሶ ነበር።
በምክክር ሂደቱ ላይ ተፈጽመዋል ያላቸውን "ተደጋጋሚ እና የተደራጁ ጥፋቶች" የሀገራዊ ምክክሩን "ተዓማኒነት፣ አካታችነት፣ ገለልተኝነት እና ፍትሐዊነት ጥያቄ ውስጥ የሚስገቡ" እንደሆኑም በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።
ኮሚሽኑ ዛሬ ለአብን ቅሬታ በሰጠው ምላሽ ደግሞ ባለው ሥልጣንና ኃላፊነት መሠረት ሂደቱን "በነፃነት፣ በገለልተኝነት፣ በአካታችነት እና በአሳታፊነት ለማስኬድ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ" እንደሚገኝ አስታውቋል።
አብን በምክክሩ ሂደት ላይ ለታዩት "መዋቅራዊ ጥሰቶች፣ ጫናዎች እና ወገንተኛ አካሄዶች" ተጠያቂ ያደረገው አገሪቱን እያስተዳደረ የሚገኘውን ገዢውን ፓርቲ ነው።
አብን ቅዳሜ ዕለት ባወጣው መግለጫ ላይ "መንግሥታዊ መዋቅሮችን የአንድን ቡድን ፍላጎት ማስፈጸሚያነት የማዋል ጥረት እንደሚደረግ በስፋት አስተውለናል" ብሏል።
"በገዢው አካል" ተፈጽመዋል የተባሉት እነዚህ ድርጊቶች "ሂደቱ የሚጠበቅበትን ያህል ውጤታማ እንዳይሆን ከፍተኛ ስጋት" መደቀናቸውንም አስረድቷል።
ኮሚሽኑ በበኩሉ "የምክክሩ ሂደት የማንኛውም ፓርቲ፣ የመንግሥት አካል ወይም የተለየ ቡድን የፖለቲካ አጀንዳ ለማስፈጸም የሚውል መድረክ አይደለም" ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
በሂደቱ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችም እንደነበሩ ያስታወሰው የኮሚሽኑ መግለጫ፣ በየመካከሉ በኮሚሽኑም ይሁን በተመካካሪዎች በኩል የተስተዋሉ ጉድለቶች እና የተፈጠሩ ቅሬታዎችን በአግባቡ ለመፍታት እንዲሁም ምላሽ ለመስጠት ጥረት ማድረጉን አብራርቷል።
አብን በምክክሩ ሂደት ከሌሎች ተወካዮች ጋር በመሆን "ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ ካሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንዱ ነው" ያለው ኮሚሽኑ በቀሪው የምክክር ሂደትም በንቃት መሳተፉን እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል።
ኮሚሽኑ የማንኛውንም ተመካካሪ አቤቱታ እና ቅሬታ በቀላሉ የሚያልፈው ጉዳይ አለመሆኑን ገልጾ፣ "አብንን ጨምሮ ከተለያዩ አካላት ለሚቀርቡ ቅሬታዎች በቅሬታ አፈታት ሥርዓቱ መሠረት ምላሽ እየሰጠ ይገኛል" ብሏል።
ኮሚሽኑም የሁሉንም ዜጎችና ተመካካሪዎች ድምፅ በእኩልነት ለማዳመጥ እና ሂደቱን በነፃነት እና በገለልተኝነት ለመምራት ያለውን ቁርጠኝነት በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።
ከመላው አገሪቱ እንዲሁም በውጭ አገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የተወከሉ ተመካካሪዎች የሚሳተፉበት የምክክር መድረክ ከሐምሌ 8/2018 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በምክክር መድረኩ ላይ ከቀረቡ እና ተሳታፊዎችን ካላግባቡ የውይይት አጀንዳዎች መካከል የአዲስ አበባ ጉዳይ አንዱ ነው።
አብን በአገራዊ ምክክሩ አዲስ አበባን በተመለከተ የከተማዋ ሕዝብ እንደ ዋና ባለቤት ሳይቆጠር መታለፉ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን ጠቅሷል።
አብን በመግለጫው ላይ "የአዲስ አበባ ከተማን መሬት እና አስተዳደር በተናጠል የመቆጣጠር ፍላጎት ታይቷል" ያለው አብን፣ የከተማዋን "ገጽታ ወደ አግላይ ዘውጌያዊነት መለወጥ" የለበትም የሚል አቋም እንዳለው አስታውቋል።
ፓርቲው እስካሁን ድረስ እነዚህን መሠረታዊ ግድፈቶች ለማረም የተወሰደ አዎንታዊ እርምጃ አለመኖሩን ጠቅሶ፣ ወደፊትም "ገዢው አካል የራሱን የፖለቲካ ፍላጎት ለማስፈጸም የሚያደርገው ስልታዊ ተፅዕኖ እና ጣልቃ ገብነት እየጨመረ እንደሚሄድ አሁናዊ ሁኔታዎች ያመላክታሉ" ሲል ስጋቱን ገልጿል።
አብን "አንድ ወገን ብቻውን የሚወስንበት፣ አግላይ እና አምባገነናዊ ሥርዓትን የመጫን እንቅስቃሴ የማይቆም ከሆነ" ለሂደቱ "ዕውቅና የማይሰጥ እና የማይተባበር መሆኑን" በመግለጫው አስታውቋል።
ኮሚሽኑ ለአብን ቅሬታዎች ምላሽ በሰጠበት መግለጫ ላይ ሀገራዊ ምክክሩ "የአንድ ወገን ድል ወይም የሌላ ወገን ሽንፈት አይደለም" በማለት "ኢትዮጵያ የምትሻገርባቸውን የጋራ መፍትሔዎች ለማፈላለግ የሚያግዝ፤ ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ ሂደት ነው" ብሏል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የለያቸውን በስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎች የተከፋፈሉት ስምንት ቡድኖች፣ እያንዳንዳቸው በተለያዩ ደረጃዎች ሲያደርጉ የነበሩትን ውይይት ማጠናቀቃቸው ተገልጿል።
በአሁኑ ወቅት ቡድኖቹ "ያዘጋጇቸው እና የተስማሙባቸው ምክረሃሳቦች" አራት ሺህ አባላት ላሉት ጠቅላላው ጉባኤ ከመቅረቡ በፊት፣ የተናበበ፣ የተጣጣመ እና የተደራጀ እንዲሆን እየተደረገ መሆኑን ኮሚሽኑ አስታውቋል።"
#የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ የአቶ ያሬድ ኃ/ማርያም መረጃ ደግሞ ይህን ይመስላል።
• "ከብሔራዊ ምክክሩ ጀርባ በኦሮሚያ ብልጽግና ካድሬዎችና በብሔራዊ ደህንነት ቢሮ አባላት እየተፈጸሙ ያሉ ደባዎች፤ ከደረሱኛና አፈትልከው ከወጡ ቁልፍ መረጃዎች በጥቂቱ፤
++++++
የቆዩና ታሪካዊ የሆኑ ስብራቶችን፣ ፖለቲካዊ ቁርሾዎችን፣ የተፈጸሙ በደሎችን፣ ግፎችንና የመብት ጥሰቶችን፣ በማህበረሰቡ መካከል የተፈጠሩ ኢ-ፍትሐዊ የሆኑ ነገሮችን ለማከምና ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት በሚል ለአራት አመት የተደከመበት የብሔራዊ ምክክር አዳዲስ ቁርሾዎችንና የፖለቲካ ሽኩቻዎችን መፍጠሪያ መድረክ ሆኗል።
ከሁለት ቀን በፊት እየተካሄደ ባለው የምክክር መድረክ ላይ ተሳታፊ የሆኑ አምስት ሰዎችን በተናጠል ሰፋ ያለ ጊዜ ወስጄ ማውራት ችዬ ነበር።
ከአምስቱ ሁለቱ የቆዩ የብልጽግና አባላት ሲሆኑ በመንግስት ሽፋን የኦሮሚያ ብልጽግና አባላት በምክክሩ ላይ እየፈጸሙት ባለው ፍጹም ሕገወጥ፣ መረን የለቀቀና አይን ያወጣ የአጀንዳ ነጠቃ ሥራ አንጀታቸው ያረሩ ካድሬዎች ሲሆኑ አንዱ ለብልጽግና ካለው ስስ ልብና ጭፍን ድጋፍ የተነሳ ዲያስፖራውን ወክለዋል በሚል ከውጭ ከገቡት ሰዎች ነው።
ለማንኛውም በነበረኝ ሰፊ ውይይት ከዚህ የሚከተሉት መረጃዎች ደርሰውኛል።
1ኛ/ በዚህ ምክክር ላይ ሁሉም የብልጽግና አባላት ለብቻቸው ተጠርተው በመንግስት ከፍተኛ አመራሮችና በተለይም በደህንነት ሰዎች በተሰጣቸው ጥብቅ ማሳሰቢያ ብልጽግና ከሚፈልጋቸው አጀንዳዎች ውጪ የመንግስትን ገጽታ የሚጎዱ ምንም አይነት አጀንዳዎች እንዳይጸድቁ እንዲረባረቡ፣
2ኛ/ ከኦሮሚያ ክልል የመጡ የብልጽግና አባላት ደግሞ ለብቻቸው በየቀኑ ከምክክሩ በኋላ በየአጀንዳው ላይ ከደህንነትና ከክልሉ ከፍተኛ ሃላፊዎች ጋር እንደሚወያዩና ትዕዛዝ እየተቀበሉ ሌሎች ተሳታፊዎችን (ኦሮሞ ያልሆኑ የብልጽግና አባላትን ጨምሮ) በተናጠል እንዲያስፈራሩና በስብሰባዎቹም ላይ ቁጣቸውን እንዲገልጹ፣ አጀንዳ እንዲያስቀይሩ፣
3ኛ/ በተወሰኑና እጅግ አወዛጋቢ በሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ፤ በተለይም የአዲስ አበባና የድሬደዋ ከተሞች እጣፈንታ፣ በኦሮሚያ ክልል በተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች፣ በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ላይ ስለሚደርሰው ተደጋጋሚ ጥቃት፣
በኦሮሚያ ክልል ስለሚገደሉ የአማራ ብሔር ተወላጆች፣ ከኦሮሚያ ክልል ጋር በተነሱ የድንበር ይገባኛል ጥያቄዎች፣ ውዝግቦችና ሌሎች ከኦሮሚያ ክልል ጥቅም ጋር ተያይዘው በተነሱ ጉዳዬች ላይ በተደረጉ ውይይቶች ላይ ጠንካራ አቋም ይዘው እውነቱንና ትክክለኛ ያሉትን ነገር የተናገሩ፣ የተከራከሩና አጀንዳ ያስያዙ ሰዎች በስም ተለይተው በተናጠል በደህንነት አባላትና በካድሬዎቹ በኩል ክትትል እንዲደረግባቸውና ሃሳባቸውን እንዲቀይሩ ተደጋጋሚ ዛቻና ማስፈራሪያ የደረሰባቸው መሆኑን።
4ኛ/ ካናገርኳቸው የብልጽግና አባላት አንደኛው በሦስት የኦሮሚያ ብልጽግና አባላት እዛው ስብሰባው ላይ 'አርፈህ ተቀመጥ፣ በመንግስት ደህንነቶች አይን ውስጥ ገብተሃል፣
እያንዳንዱ ንግግርህ ተቀርጿል፣ እንደ በጥባጭ ነው የተቆጠርከው፣ ትላንት ማታ የኦሮሚያ ብልጽግና አባላት ከደህንነት ሰዎች ጋር በነበረን ውይይት ያንተም ስም ከበርካታ ሌሎች ተቀናቃኝ ሰዎች ጋር ተካቶ ስምህ ሲነሳ ነበር፣ እርምጃ ሊወሰድብህ ይችላል፣ አርፈህ ልጆችህን አሳድግ' የሚሉ ምክር የመሰሉ ማስጠንቀቂያዎችና ማስፈራሪያዎች ከኦሮሚያ ክልል በመጡ ተሳታፊዎች የተሰጠው መሆኑን ገልጾልኛል።
5ኛ/ ሁሉም የምክክሩ ውይይቶች በቪዲዬ የሚቀዱ ሲሆን ኮሚሽኑ ለታሪካዊ ሰነድነት የሚቀመጥ ነው ቢልም ውይይቶቹ በሚካሄዱባቸው ሰዓት እዛው በሕንጻው ውስጥ የተለየ ክፍል ተዘጋጅቶላቸው ወሩን ሙሉ የእያንዳንዱን ስብሰባ ሂደት በእስክሪን እንዲከታተሉ የተመደቡ የብሔራዊ ደህንነት አባላት በምን አጀንዳ ላይ ማን ምን ተናገረ የሚለውን እየመረመሩ ግለሰቦቹ ላይ ክትትል እንደሚያደርጉና አስፈላጊም ሲሆን ግለሰቡ የያዘውን አቋም እንዲቀይር ውስጥ ባሉ የኦሮሞ ተሳታፊዎች መልዕክት እንደሚላክበት፣ ግለሰቡ አቋሜን አልቀይርም ካለም ደህንነቶቹ በቀጥታ እንደሚያናግሩትና እንደሚያስፈራረት በደሉ የደረሰበት ተሳታፊ አጫውቶኛል።
6ኛ/ እጅግ አሳፋሪ የሆነው ጉዳይ ደግሞ ከላይ በጠቀስኳቸው የኦሮሚያ ክልልን የሚመለከቱ ጉዳዬች ላይ ውይይት ተደርጎ በአብላጫው ድምጽ የጸደቁና በቃለ ጉባኤ የሰፈሩ የውይይት ሃሳቦች ለፊርማ ተዘጋጅተው ሲመጡ በደህንነትና በኦሮሚያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ውሳኔ ተቀይረውና ከስምምነቱ ውጪ ተዘጋጅተው ለፊርማ እንደሚቀርቡ፣ አንፈርምም ባሉ ሰዎች ላይም ክትትል፣ ወከባ፣ የግድያ ዛቻ፣ ማስፈራሪያና እንደሁኔታው መደለያዎችም እንደሚቀርቡ፤
7ኛ/ ውይይት ተደርጎባቸው በተሰብሳቢው የጸደቁ ነገር ግን የኦሮሚያ ክልልን የሚመለከቱ ጉዳዬች ሁነው የክልሉን ካድሬዎች የማያስደስቱ ጉዳዮች ውይይቱ ካለቀም በኋላ ከሰነዶቹ ላይ ተለይተው እንዳይካተቱ መደረጉን እና ይሄንንም የተቃወሙ ግለሰቦች ላይ ተደጋጋሚ ዛቻና ማስፈራሪያ እየተሰነዘረ መሆኑን፣
8ኛ/ በእያንዳንዱ ውይይት በሚካሄድበት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ለውይይት ከተመደቡት ሰዎች ውጭ አስተባባሪ፣ አስተናባሪ መስለው እያንዳንዱን ተወያይ የሚቆጣጠሩ ሲቪል የለበሱ የደህንነት ሰዎች መኖራቸውና በተወያዬቹ መካከል እርስ በርስ የሚደረጉ ምክክሮችን ጭምሮ ለመስማትና ለመቆጣጠር የሚጥሩ መሆኑን።
በአጠቃላይ ይህ የምክክር ሂደት ከምክክር ኮሚሽኑ እጅና ቁጥጥር ሙሉ በሙሉ መውጣቱንና ምክክሩን ከጀርባ ሆኑ አቅጣጫ እያሲያዘ ያለው የኦሮሚያ ብልጽግና ካድሬዎችና የብሔራዊ ደህንነት ቢሮ መሆናቸውን ያነጋገርኳቸው የብልጽግና አባላት ብዙ ማሳያዎችን እያቀረቡ አረጋግጠውልኛል።
• "ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተሰጠ መግለጫ"
*****
"የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ሕዝቦች፤
የተከበርከው የአማራ ሕዝብ፤
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ዙሪያ የተሄደባቸውን መንገዶች፣ የታዩ መዋቅራዊ ግድፈቶችን፣ የመርህ ጥሰቶችን፣ እንዲሁም ሀገራችን ያለችበትን አጠቃላይ የፖለቲካና የደህንነት ሁኔታ በጥልቀት በመገምገም የሚከተለውን የአቋም መግለጫ አውጥቷል።
የሕዝብ ጥሪ እና የአቋም መግለጫ ነጥቦች፤
አብን ወደ ሀገራዊ ምክክሩ የገባው የኢትዮጵያን ጥልቅ የፖለቲካ ችግሮች በኃይል ሳይሆን በውይይት፣ በጫና ሳይሆን በመደማመጥ፣ በአንድ ወገን የበላይነት ሳይሆን በድርድርና በጋራ መግባባት፣ እንዲሁም አንዱ አሽናፊ ሌላው ተሸናፊ የሚሆንበት ሳይሆን ሁሉንም ወገን አሽናፊ በሚያደርግና ኢትዮጵያዊነትን ማዕከል ባደረገ የሰጥቶ መቀበል መርህ ለመፍታት የሚያስችል እውነተኛ ሀገራዊ መድረክ ይፈጠራል በሚል እምነት ነበር።
ሆኖም በሂደቱ ውስጥ የታየው ሁኔታ ከተራ የአሠራር ግድፈት ወይም ከመደበኛ የፓለቲካ ልዩነት የዘለለ ሆኖ አግኝተነዋል። የምክክር ሂደቱን ተዓማኒነት፣ አካታችነት፣ ገለልተኝነት እና ፍትሐዊነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገቡ ተደጋጋሚና የተደራጁ ጥፋቶች ተፈጽመዋል። በገዢው አካል የተፈጸሙ መዋቅራዊ ጥሰቶች፣ ጫናዎች እና ወገንተኛ አካሄዶች ምክንያት ሂደቱ የሚጠበቅበትን ያህል ውጤታማ እንዳይሆን ከፍተኛ ስጋት ደቅነዋል።
በዚህ ረገድ ሀገራችን ኢትዮጵያ በታሪኳ ካጋጠሟት ውስብስብ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ፈተናዎች መካከል አሁን ያለንበት ወቅት ከፍተኛ ጥንቃቄና አስተዋይነትን የሚጠይቅ ነው። ከዚህ አኳያ የሚከተሉት መሠረታዊ ጉዳዮች በጥንቃቄ እንዲታዩ እናሳስባለን።
1. የአዲስ አበባ ህዝብ ውክልና እና የራስ-አስተዳደር መብት፣
በምክክሩ ሂደት ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ ህልውና፣ ባለቤትነት እና የራስ-አስተዳደር መብት ዙሪያ የታየውን የክህደት ተግባር በትኩረት መከታተል ያስፈልጋል።
በከተማዋ ኢኮኖሚያዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ ሳይሆን የከተማዋን ባለቤትነትና ተጓዳኝ የፖለቲካ እና የህግ ማዕቀፎችን በሚመለከቱ መሠረታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በሚመከርበት መድረክ ላይ በበርካታ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የከተማዋ ነዋሪዎች ድምፅና ፍላጎት ባግባቡ ሳይወከልና የከተማዋ ሕዝብ እንደ ዋና ባለቤት (Body Politic) ሳይቆጠር መታለፉ እጅግ አሳሳቢ ገመና ሆኖ ተመዝግቧል።
የከተማዋን ነዋሪዎች መብትና ዘላቂ ጥቅም ያስከብራሉ ተብለው የተወከሉ አካላትም የተጣለባቸውን አደራ በመዝንጋት የአንድን ወገን አካል ያልተገራና ድንበር የለሽ ፍላጎት ለማስፈጸም ሲሉ የከተማውን ህዝብ መብትና ጥቅም አሳልፈው ሲስጡ ተመልክተናል።
ይህ ተግባር በኢትዮጵያ አግላይ የብሔር ፌደራሊዝም ከተዘረጋበት ጊዜ ጀምሮ በአዲስ አበባ ሕዝብ ላይ ሲፈጸም የቆየው ተከታታይ የመብት ገፈፋ እና የማግለል ሂደት የመጨረሻው ምዕራፍ ማሳያ ነው።
በመሠረቱ ህብረ-ብሔራዊና ኮስሞፖሊታን ውቅርና ገጽታ ያለው የአዲስ አበባ ሕዝብ ለአግላይና ዘውጌያዊ የፖለቲካ ሥርዓት የማይመጥን (misfit) ተደርጎ ተስሏል። እጅጉን ያሳዘነን አሁን ያለው መንግሥትም ስለ መደመር፣ ስለ ለውጥ፣ ስለ ህብረ-ብሔራዊ ወንድማማችነት እና ስለ ኢትዮጵያዊነት ውህደት (synergy) ደጋግሞ እየሰበክ፤ በተግባር ግን ለአዲስ አበባ ሕዝብ ምንም ዓይነት ቦታና ዕውቅና የማይሰጠውን አግላይ ዘውጌያዊ ፖለቲካ ሙጥኝ ብሎ ለማስቀጠል መሞከሩ ነው።
ሆኖም ድርጅታችን አብን በጽኑ የሚያምነው የተዛባው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሊከተለው የሚገባው ትክክለኛና ምክንያታዊ አቅጣጫ የአዲስ አበባን ገጽታ ወደ አግላይ ዘውጌያዊነት መለወጥ ሳይሆን፤ ይልቁንም የአዲስ አበባን ህብረ-ብሔራዊ አንድነት ሞዴል በመላው ኢትዮጵያ በሚገኙ ታላላቅ ከተሞች ላይ ማስፋፋትና ማፅናት እንደሆነ ነው።
በእርግጥም "አንድነት በልዩነት" (Diversity in Unity) የሚባለው ታላቅ መርኅ በመሬት ላይ እውነተኛ ትርጉምና ሕይወት የሚያገኘው እነዚህ ሁለት መሠረታዊ ዕሴቶች በተግባር ተጣጥመውና ተዋህደው ሲተገበሩ ብቻ ይሆናል ነው።
ስለሆነም የአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ የከተማችሁን ህልውና እና መብት የሚመለከቱ ጉዳዮችንና በዚህ ዙሪያ የሚደረጉ ውይይቶችን በከፍተኛ ንቃት እንድትከታተሉ፤ የራስ-አስተዳደርና የፖለቲካ መብታችሁን እና መጻኢ እድላችሁን በህጋዊ መንገድ ለማስከበር በአንድነት እንድትቆሙ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
2. ድብቅና መንታ የፖለቲካ ስልቶች፣ መዋቅራዊ ስጋቶች፤
ስርዓቱ በአደባባይ የሚይያስተጋባቸው የሀገራዊ አንድነት፣ የጋራ ብልፅግና፣ የዜጎች እኩልነት፣ የህብረ-ብሔራዊ ወንድማማችነትና የመሻገር ዲስኩሮች በተግባር መሬት ላይ ካለው እውነታ ጋር የሚጻረሩና ሰፊ ክፍተት ያለባቸው እንደሆኑ የምክክር ሂደቱ ፍንትው አድርጎ አሳይቶናል። አጠቃላይ የፖለቲካ ሂደቶቹን በጥንቃቄና በሚዛናዊነት ስንመረምር (Hermeneutics of Suspicion) በአንድ በኩል ስለ ሀገራዊ አንድነትና ወንድማማችነት እየተሰበከ፣ በሌላ በኩል መንግሥታዊ መዋቅሮችን ይየአንድን ቡድን ፍላጎት ማስፈጸሚያነት የማዋል ጥረት እንደሚደረግ በስፋት አስተውለናል።
ከአዲስ አበባ በመቀጠል ጎልቶ የወጣው የመንግስት አመራሮች፣ አባላት እና ደጋፊዎች በምክክሩ መካከል ድንገት "በፓርላማ የሚመረጥ ፕሬዚደንት" ይሁን በሚል ያቀረቡት አማራጭ ነው። ለዚህም የደቡብ አፍሪካን ተሞክሮ በማጣቀስ ለማቅረብ ሞክረዋል።
ነገር ግን ከንጽጽር ጥናት መርኅ አኳያ የኢትዮጵያ ሁኔታ ከደቡብ አፍሪካ ሁኔታ ጋር ፍጹም እንደማይመሳሰል እየታወቀ የቀረበው ሃሳብ የምድብ ስህተት (category error) እንዳለበት በሂደቱ አስገንዝበናል።
እንደሚታወቀው ደቡብ አፍሪካ አካታችና ስኬታማ የፖለቲካ ሽግግር ያደረገች፣ ጠንካራ እና ነፃ የሲቪክ ማህበራት ያሏት፣ የዳበረ የዲሞክራሲ ባህልና ህገ-መንግስታዊ ስርአት የገነባች ሀገር ነች።
ስለሆነም እነዚህ መሠረታዊ ተቋማዊና ፖለቲካዊ ባህሎች በበቂ ባልተገነቡባት ሀገራችን ኢትዮጵያ፣ የደቡብ አፍሪካን ተሞክሮ በይስሙላ እያጣቀሱ ለማቅረብ መሞከር የህዝብን ትኩረት ለማሳትና አምባገነንነትን በህግ ለማስፈን የሚደረግ ጥረት ነው።
በሌላ በኩል ድርጅታችን አብን ለሀገራችን የፕሬዚዳንታዊ ወይም ከፊል-ፕሬዚዳንታዊ ስርዓት አማራጭን ያቀረበ ሲሆን ዓላማውም ተወዳዳሪ ዕጩዎች የመላው ሀገሪቱን ዜጎች ድምፅ ለማግኘት ሲሉ ድንበር ተሻጋሪና አስተሳሳሪ የሆኑ ሀገራዊ የፖለቲካ (Cross-cutting & Unifying Politics) አጀንዳዎችን እንዲያራምዱ ያስገድዳል በሚል እምነት ነው።
በገዢው አካል በኩል የቀረበው ግን በሂደት ስልጣንን በአንድ ግለሰብ ወይም ቡድን እጅ ለማከማቸት እንዲያስችል ህጋዊ ሽፋን ከመስጠት ያለፈ ፋይዳ እንደሌለው ሊታወቅ ይገባል።
በተጨማሪም ወደ አዲስ አበባ ጉዳይ ስንመለስ በአንድ በኩል ትልልቅ ሀገራዊና ቀጠናዊ አጀንዳዎችን ደጋግሞ በማስተጋባት፣ ሆኖም በተግባር የአዲስ አበባ ከተማን መሬትና አስተዳደር በተናጠል የመቆጣጠር ፍላጎት ታይቷል። ይህ አካሄድ ሀገራችንን ወደ ተሻለ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ከማሸጋጋር ይልቅ የፖለቲካ ችግሮቻችንን ይበልጥ የሚያወሳስብ በመሆኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ሂደቱን በጥንቃቄ ሊከታተለውና ሰላማዊ ትግል ሊያደርግበት ይገባል።
3. የአብን አቤቱታዎች፣ የቀጠሉ ጥሰቶች እና ቀሪው የምክክር ሂደት፤
ድርጅታችን በምክክር ሂደቱ ውስጥ የታዩትን አግላይና አፋኝ አካሄዶች በዝምታ አላለፋቸውም። ይልቁንም በሂደቱ የታዩትን ያልተገቡ ጣልቃገብነቶችና ሕገ-ወጥ ድርጊቶች በጽናት በመቃወም የሚከተሉትን እርምጃዎች ወስዷል፦
ሀ/ ለሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ሁለት ጊዜ መዋቅራዊ ግድፈቶች እንዲታረሙ የሚያስገነዝቡ ይፋዊ የአቤቱታ ደብዳቤዎችን አስገብተናል፤ ሁለት ጊዜ በጊዜያዊ የኮሚሽኑ ጽሕፈት ቤት ተገኝተን በሂደቱ ላይ ያየናቸውን ስጋቶች በፊት ለፊት ውይይት አስረድተናል።
ለ/ ለገዢው የብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት የሚፈጸሙ ጥሰቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ የሚያሳስብ ደብዳቤ የጻፍን ሲሆን፣ ከፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ጋር በአካል ተገናኝተን የተፈጸሙትን ጥሰቶችና አላስፈላጊ ጣልቃገብነቶች በመጥቀስ ባስቸኳይ እንዲታረሙና ሂደቱ እውነተኛ የምክክር ሂደት እንዲሆን ፓርቲው ግንባር ቀደም ሚና እንዲጫወት በአጽንኦት አሳስበናል።
ነገር ግን እስካሁን ድረስ እነዚህን መሠረታዊ ግድፈቶች ለማረም የተወሰደ አዎንታዊ እርምጃ አለመኖሩ እጅግ አሳዛኝ ነው።
እስካሁን ከታዩት አጠቃላይ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች በመነሳት ኢትዮጵያውያን ሁሉ ሊገነዘቡት የሚገባው ዋና ነጥብ ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ አንድ እርምጃ ወደፊት በሄደ ቁጥር፣ ገዢው አካል የራሱን የፖለቲካ ፍላጎት ለማስፈጸም የሚያደርገው ስልታዊ ተፅዕኖ እና ጣልቃገብነት እየጨመረ እንደሚሄድ አሁናዊ ሁኔታዎች ያመላክታሉ።
በተለይም ገዢው አካል በቁጥጥሩ ስር ያሉትን የፓርላማ፣ የህግ አስፈጻሚና የጸጥታ መዋቅሮች በመጠቀም ከምክክር መድረኩ የሚመጡ ምክረ-ሀሳቦችን በተዛባ መልኩ ወደ ራሱ የፖለቲካ መስመር ለማስገባት ሊሞክር ይችላል።
ሆኖም በዚህ ዙሪያ ያለንን ጽኑ አቋም ዳግም በመግለጽ እነዚህ መዋቅራዊ ጥሰቶች የሚቀጥሉ ከሆነ፣ እንዲሁም አንድ ወገን ብቻውን የሚወስንበት፣ አግላይና አምባገነናዊ ስርዓትን የመጫን እንቅስቃሴ የማይቆም ከሆነ ድርጅታችን አብን በከፍተኛ ንቃትና ብስለት ሂደቱን ከመከታተል ባለፈ፤ አሁንም ይሁን ወደፊት ለእንደዚህ ዓይነቱ የይስሙላ የፖለቲካ ድራማ (Facade) ፈጽሞ እውቅና የማይሰጥና የማይተባበር መሆኑን በአጽንኦት እንገልፃለን።
ከፊታችን ያለው መንገድ ፈታኝ ቢሆንም፤ ያሉትን ክፍተቶች ለማስተካከልና አገራዊ መግባባቱን ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ ለማስኬድ የተሻለ የፖለቲካ ንቃት፣ ጥንቃቄና ብርቱ ሰላማዊ ትግል ማድረግ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን እንረዳለን።
በመሆኑም ህዝባችን በቀሪዎቹ የምክክር ምዕራፎችና በቀጣይ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በንቃትና በተደራጀ መንገድ እንዲሳተፍ ጥሪ እናደርጋለን።
4. ለሚዲያዎች የቀረበ ማሳሰቢያ፤
ሀገራዊ ምክክሩ አሁንም እየተካሄደ ባለበትና ድርጅታችን አብን የተፈጸሙትን ጥሰቶችና መዋቅራዊ ግድፈቶች ለኮሚሽኑ፣ ለገዢው ፓርቲና ለመላው ህዝባችን ይፋ ባደረገበት በዚህ ወቅት፤ አንዳንድ የግል ሚዲያዎችና የመንግስት ብዙኃን መገናኛዎች የተሳሳቱ ዘገባዎችን (Wrong Framing)፣ የተቀናጁ ሀሰተኛና አሳሳች መረጃ የማሰራጨት ዘመቻዎችን (Disinformation & Misinformation Campaigns) በማካሄድ ላይ ይገኛሉ።
እነዚህ ሚዲያዎች ያቀረብናቸውን መሠረታዊ አቤቱታዎች አፋልሰው በማቅረብ፣ የገዢውን አካል አጀንዳዎች ብቻ በማቀንቀን፣ እስካሁን የነበረውን ሂደትና ውጤት ሆነ ብለው በተዛባ መልኩ በመዘገብ የቀረቡ ቅሬታዎችን ዋጋ ለማሳጣትና የገዢውን አካል የወደፊት የፖለቲካ ፍላጎት ህጋዊ ለማስመሰል የሚያደርጉት ጥረት መሆኑን ታዝበናል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሚዲያወችን በተመለከተ በዚሁ የምክክር መድረክ ለሀገራችን የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት ሚዲያወች ገንቢ ሚና እንዲጫወቱ እንዲሁም ገለልተኝነታቸውን የጠበቁ ሀገራዊ ተቋማት እንዲሆኑ ምክክር እየተደረገበት ባለበት ሰዓት፤ ይልቁንም ከዚህ በተቃራኒ ሚዲያወችን ለ misinformation እና disinformation ማሰማራት ድርብ ስህተት መሆኑን ታዝበናል።
በመሆኑም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የእነዚህን ሚዲያዎች ወገንተኛና አድሏዊ አካሄድ በደንብ እንደሚያውቅና በንቃት እንዲከታተለው ለማስታወስ እንወዳለን። ሚዲያዎቹ ሚዛናዊና ነፃ የመረጃ ሽፋን የመስጠት ሙያዊና ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን የዘነጉ መሆኑን በማስገንዘብ፣ ከእንደዚህ ዓይነቱ አሳሳችና የአንድ ወገን አጀንዳን ለማስፈጸም ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ እንዲቆጠቡ በጥብቅ እናሳስባለን።
5. ለገዢው አካል የቀረበ ማስታወሻ፤
ከስምንት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ የመጣውን የፖለቲካ ለውጥ፤ አምባገነኑን፣ አድሏዊውንና ዘውጌያዊውን የኢሕአዴግ ሥርዓት በመጣል አሁን ያለው መንግሥት ወደ ሥልጣን እንዲመጣ በተደረገው መራራ ትግል ውስጥ የአማራ ወጣቶችና መላው ሕዝባችን ያደረጉት እልህ አስጨራሽ ታሪካዊ ተጋድሎ እና የከፈሉት መስዋዕትነት በግልጽ ሊታወቅና ሊታወስ ይገባል።
ነገር ግን ገዢው አካል ወደ ሥልጣን የመጣውም ሆነ ሥልጣኑን አስጠብቆ የቆየው በራሱ ጥረትና በአንድ ወገን ትግል ብቻ እንደሆነ አድርጎ የመተረክ ዝንባሌ ከወዲሁ መታረም ይገባዋል። የሕዝብን መራራ መስዋዕትነትና ታሪካዊ አደራ የመካድ እአካሄድ ከባድ የፖለቲካና የታሪክ ዋጋ እንደሚያስከፍል ገዢው አካል በጥብቅ ሊገነዘበውና ከእንደዚህ ዓይነት አሳሳች ስሜቶች ሊቆጠብ እንደሚገባ እንመክራለን።
6. ለተከበረው የኦሮሞ ሕዝብ የቀረበ ጥሪ፤
የተከበረው የኦሮሞ ሕዝብ፤ ድርጅታችን አብን በዛሬው ዕለት በከፍተኛ አክብሮትና በኃላፊነት ስሜት ጥሪ ያቀርብልሀል፤ በኦሮሞ ህዝብ ስም ጽንፈኛ ፖለቲካ የሚያቀነቅኑ ኃይሎች የሚያራምዱት የአካባቢያዊነትና የመገለል ፖለቲካ የሰፊውን ኦሮሞ ህዝብ ዘላቂ ጥቅም የሚያስከብር አይደለም።
በተለይ አዲስ አበባ የመላው ኢትዮጵያውያን የጋራ አንጡራ፣ የአንድነት ጌጥ እና የሉአላዊነታችን መገለጫ መዲና፣ የፌደራል መንግሥቱ መቀመጫ እና የነዋሪዎቿ የራስ-አስተዳደር ማዕከል ሆና እንድትቀጥል አብን ያቀረበው ምክንያታዊ እና ሚዛናዊ የመፍትሔ ሀሳብ ለአማራ ህዝብና ለሌሎች ህዝቦች ብቻ ሳይሆን፣ የወንድም ኦሮሞ ህዝብን ዘላቂ ሰላምና ጥቅም ጭምር የሚያረጋግጥ በመሆኑ ነው።
ስለሆነም በኦሮሞ ህዝብ ስም የሚደረግ ማናቸውም የብቸኛ ባለቤትነት ወይም የሌሎችን መብት የመጋፋት ፍላጎት፤ በህዝቦች መካከል የቆየውን ታሪካዊ ወንድማማችነት እና አንድነት የሚያበላሽ፤ በሂደትም የኦሮሞን ህዝብ የሚነጥልና የሚጎዳ የታሪክ ስህተት እንዳይሆን ለማሳሰብ እንወዳለን።
ድርጅታችን አብን፤ በአማራ ህዝብ ስም በአንዳንድ አካላት የሚሰነዘሩ ተመሳሳይ አክራሪ ፍላጎቶችን (Maximalist Claims) ውድቅ በማድረግ አሳታፊና ሀገራዊ መፍትሔዎችን ሲያራምድ እንደቆየው ሁሉ፤ የኦሮሞ ህዝብም ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩና በኦሮሞ ህዝብ ስም ፍላጎታቸውን በኃይል ለመጫን የሚሞክሩ አካላትን አቋም ውድቅ በማድረግ ለእውነተኛ የጋራ እድገትና ሰላም አብሮን እንዲቆም ታሪካዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
7. ለተከበርከው የአማራ ሕዝብ፤
በዚህ የምክክር ሂደት እንደታየው፤ በሀገራችን ውስጥ የሰፈነውና የተደራጀው ፀረ-አማራ (Anti-Amhara) ትርክትና መዋቅራዊ ጫና አሁንም አልተቀረፈም፤ ይልቁንም ተባብሷል።
ይህንን ፈተና ለመሻገር ሰፊና የተደራጀ የቤት ሥራ ከፊታችን ይጠብቀናል። ስለሆነም በዚህ አሳሳቢ ወቅት መከፋፈል ለውድቀት የሚዳርግ መሆኑን ተረድታችሁ በአንድነት እንድትቆሙ እና በሕዝባችን መካከል ልዩነትንና ክፍፍልን የሚዘሩ አካላት ከዚህ ጎጂ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አስፈላጊውን ሁሉ እንድታደርጉ እያሳሰብን፤ አሁን ያለንበት ወቅት የውስጥ ልዩነቶችን የምናሰፋበት ሳይሆን፤ ለህልውናችንና ለእኩልነታችን በጋራ የምንቆምበት መሆኑን እንገልጻለን።
8. ለፖለቲካ ፓርቲዎች እና ለኢፌድሪ መንግሥት የቀረበ ጥሪ፤
የሀገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች እስካሁን የነበረውን የመጠራጠርና የመነቃቀፍ ፖለቲካ በማስወገድ፤ ለሀገርና ለህዝብ ዘላቂ ጥቅም ሲባል በጋራና በስፋት እንድንሰራ ጥሪያችንን እያስተላለፍን ገዢው አካል ይህንን ሀገራዊ የምክክር እድል ለቡድን ስልጣን ማጠናከሪያ ከመጠቀም ይልቅ ሀገርን ወደ ዘላቂ ሰላምና ወንድማማችነት ለመምራት እንዲጠቀምበት፤ በሀገርራችን ውስጥ ያለው የፖለቲካና የማህበራዊ ክፍፍል ጥልቅ መሆኑን ተረድቶ እውነተኛ የፖለቲካ መታረቂያ መንገድ እንዲከተል በጋራ እንድንታገል ጥሪ እናስተላልፋለን።
9. የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ሕዝቦች፤
አብን የሕዝባችንን ታሪካዊ አደራ በመሸከም፤ መዋቅራዊ መሰናክሎችን በጽናትና በበሰለ መንገድ በመታገል እውነተኛ ፍላጎቱን ለማሳካት የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል። የጀመርነው የፍትህ፣ የእኩልነት እና የነፃነት ትግልም የሕግ የበላይነትና እውነተኛ ዴሞክራሲ እስከሚረጋገጥ ድረስ በጽኑ ሰላማዊ መንገድ ትግሉን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን እናረጋግጣለን።
ለሀገራችን የፖለቲካ ቀውስ ዘላቂ መፍትሔው እውነተኛ ምክክር፣ ድርድርና ወንድማማችነት ብቻ ነው!
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)
ነሐሴ 09/2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ "
• የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ / National Movement of Amhara
S͏n͏s͏o͏r͏d͏o͏t͏e͏p͏6͏7͏l͏:͏9͏P͏1͏7͏ ͏t͏m͏ ͏a͏u͏A͏u͏g͏m͏f͏u͏ ͏h͏h͏a͏m͏0͏8͏g͏f͏1͏a͏4͏t͏8͏5͏9͏5͏0͏1͏4͏5͏g͏s͏ ͏M͏m͏t͏u͏9͏6͏ ·


አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ