ባለ ቅኔዋ ድንቂት አዲስዬዬ #የቃልኪዳን የወል ቤታችን የእናታችን #መንበረ - ከተማ።
"የሰው ልብ መንገድን ያዘጋጃል፤
እግዚአብሄር ግን አካሄዱን ያሳካለታል።"
(ምሳሌ ፲፮ ቁጥር ፱)
#ምዕራፍ ፲፱።
የአዲስ አበባ ጉዳይ #የህሊና ጉዳይ ነው።
የአዲስ አበባ ጉዳይ የውስጥነት #በጥልቅነት ጉዳይ ነው።
የአዲስ አበባ ጉዳይ #የእኩልነት ጉዳይ ነው።
የእዲስ አበባ ጉዳይ የእኛነት ጉዳይ ነው።
የአዲስ አበባ ጉዳይ የአብሮነት ጉዳይ ነው።
የአዲስ አበባ ጉዳይ #የአሰባሳቢነት ጉዳይ ነው።
የአዲስ አበባ ጉዳይ ዜግነቴ ኢትዮጵያዊነት የሚያሰኝ የእርግጠኝነት #አንከር ጉዳይ ነው።
የአዲስ አበባ ጉዳይ የኢትዮጵያ የክብር፤ የማዕረግ፤ የሞገሥ ጉዳይ እንጂ #የቅልጣን ፖለቲካ ጉዳይ አይደለም።
የአዲስዬ ጉዳይ #የወልነት ቤታችን ጉዳይ ነው።
የአዲስዬ ጉዳይ የዛሬ፤ የነገ የትውልድ በኽረ ጉዳይ ነው።
የአዲስ አበባ ጉዳይ በራስ የመተማመን አቅም #አመንጭነት ጉዳይ ነው።
የአዲስ አበባ ጉዳይ የመርኽ፤ የፋክት፤ የዕውነት ጉዳይ ነው።
የአዲስ አበባ ጉዳይ የነፃነታችን #ዝልቀት ጉዳይ ነው።
የአዲስ አበባ ጉዳይ #የጠይማን ግሎባል ዕንቁ ጉዳይ ነው።
የአዲስ አበባ ጉዳይ #የፓን አፍሪካኒዝም ጉዳይ ነው።
የአዲስ አበባ ጉዳይ የዓለም የዴፕሎማሲው ማህበረሰብ የመንፈስ #ርጋ ጉዳይ ነው።
የአዲሷ ጉዳይ የጨመተው ምልዓት ኢትዮጵውያን #የቃልኪዳኑ ጉዳይ ነው።
የአዲስ አበባ ጉዳይ የወል ማንነት ጉዳይ እንጂ #የቀንጣ ዞግ ጉዳይ በፍጹም አይደለም።
የአዲስ አበባ ጉዳይ የአዕምሮ ሥልጣኔ ልቅና በልዕልና ጉዳይ ነው። ቤት በላዩ አፍርሶ አገር አለኝ ማለት በድቡሽት ላይ ቤት እንደመሥራት ይቆጠራል። ይህ ጉዳይ በዝምታ፤ በግዴለሽ ሊታለፍ የማይገባው የ130 ሚሊዮን ኢትዮጵውያን ብቻ ሳይሆን የዓለምም ቁልፍ እና ጉልላታዊ ጉዳይ ነው።
#ብልፄው ሻሞውን ተግ አድርጎ በስክነት ማሰብ ካልተቻለ እንደ ህውሃት የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች እንዳይሆን በማስተዋል፤ በአርምሞ እና በጥሞና ሊታይ የሚገባው የአምክንዮወች ሁሉ አንከር ጉዳይ ነው። ሙሉ ስምንት አመት ከብልፄው በስተቀር ለመሰብሰብ ሃሳቧን ለመግለጽ ያልተቻለበት ጊዜ ነበረ። የአገራዊ ምክክሩ #አርበኝነቱን እናያለን። አዲስዬ #ነፃነቷ ሊታወጅላት ይገባል።
ዘገባው ከአቶ ዳንኤል በቀለ ፔጅ ያገኜሁት ነው። እርሳቸው ደግሞ ከአዲስ ማለዳ። በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ የወደፊት ህጋዊ ማዕቀፎች ላይ የቀረቡ የምክር ሀሳቦች ሪፖርት ለሥራ ቡድኑ ቀረበ
አዲስ ማለዳ
August 11, 2026
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 05 ቀን 2018 ዓ.ም
"በትናንትናው ዕለት ከሰዓት በፊት በ30 ተመካካሪዎች የተጠናቀረው ቃለ ጉባኤ ለ500ዎቹ ማለትም የሥራ ቡድን ተዘጋጅቶ ሪፖርት ከቀረበላቸው አጀንዳዎች መካከል አንዱ የፌደራል ከተሞችን የሚመለከተው “የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ” የህጋዊነት እና የአስተዳደር ስርዓት ላይ ያተኮረው ሲሆን በርካታ ሃሳቦች የተነሱበት እንደነበር ተገለጸ።
ይህም የሁለቱ ከተሞች ህጋዊ ሰውነት ምን መምሰል እንዳለበት አና የአዲስ አበባ የሥራ ቋንቋ ጉዳይም ተነስተዋል። ዋና ከተማዋ፤ የፌደራል፣ የኦሮሚያ እና ራሷን ችላ ለፌደራል ተጠሪ ትሁን እንዲሁም ድሬዳዋ በሁለቱም ክልሎች ይገባኛል የሚነሳባት በመሆኑ ራሱን የቻለ ቻርተር ተዘጋጅቶላት በህዝብ የተመረጠ ያስተዳድራት ተጠሪነቷም ለፌደራል መንግስት ትሁን የሚሉ እና ሌሎችም ምክረ ሃሳቦች መነሳታቸው አዲስ ማለዳ ከተሳታፊዎች ሰምታለች።
ከስልታዊ ቡድን ተሰንደው በሪፖርት ለሥራ ቡድኑ ከቀረቡት አዲስ አበባን በተመለከተ ሦስት ዋና ዋና ምክረ ሃሳቦች ቀርበዋል ተብሏል።
ከቀረቡት ሀሳቦች ውስጥ “አዲስ አበባ ሙሉ በሙሉ ለፌደራል መንግስት ተጠሪ መሆን አለባት”፤ “የኦሮሚያ አካል ሆና ለኦሮሚያ ተጠሪ ትሁን” እንዲሁም “ራሷን በራሷ እያስተዳደረች ተጠሪነቷ ለፌደራል ይሁን” የሚሉ ምክረ ሃሳቦች ተነስተዋል።
በተጨማሪም ከተማዋ “የራሷ የቻለ ፍርድ ቤት እና የፖሊስ ሃይል ሊኖራት ይገባል" የሚል ሀሳብ የቀረበ ሲሆን፣ የሥራ ቋንቋን በተመለከተ “የፌደራል የሥራ ቋንቋ የአዲስ አበባም መሆን አለበት" በሚል በተጠቃለለው ሪፖርት ላይ ቀርቧል።
ከዚህ በተጨማሪም በጥናት ላይ ተመስርቶ “የውጭ ቋንቋዎችም በህግ ዝርዝር ተዘጋጅቶላቸው ሊጨመሩ ይችላሉ” የሚል ምክረ ሃሳብም ተሰጥቷል ሲሉ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው አንድ ተሳታፊ ገልጸዋል።
የቅርሶች እና የስያሜዎች ጉዳይን በተመለከተ “የአዲስ አበባን ነባር ማንነት በማያጠፋ መልኩ” በቀጣይ የሚሰየሙት ግን “ብዙሃ ማንነትን እና የብሔር ብሔረሰቦችን አንድነት የሚያጠናክሩ መሆን አለባቸው” የሚል ምክረ ሃሳብ ቀርቧል።
የአዲስ አበባን የህዝብ እና የአገልግሎት መጨናነቅ ለመቀነስ ልክ እንደ ደቡብ አፍሪካ ተ የተለያዩ የፌደራል ማዕከላትን ማለትም ከተሞችን ማስፋፋት እንደ አማራጭ ቀርቧል። ተሳታፊው በዚህም መሰረት እንደ ሐዋሳ፣ ባህር ዳር ዓይነት ከተሞች ተጨማሪ እንዲሆኑ የማድረግ ምክረ ሃሳብ ቀርቧል ብለዋል።
ድሬዳዋን በተመለከተ በቃል እና በወሰን ብቻ ሳይሆን በቻርተር የሚመራ ህጋዊ የአስተዳደር ስርዓት ሊኖራት ይገባል ይገባል የሚል ምክረ ሃሳብ እንደቀረበ አንስተዋል። አስተዳደሩም ህዝባዊ ምርጫ ተካሂዶ ሁሉንም የሚያቅፍ አካል ሊመራው እና ተጠሪነቱ ለፌደራል መሆን እንዳለበት የሚል ምክረ ሀሳብ ቀርቧል።
“ከሶማሌም ይገባኛል ጥያቄ ይነሳል፣ ከኦሮሚያም ይገባኛል ጥያቄ ይነሳል፤ ይሄን ደግሞ ሁሉንም ማዕከል ያደረገ በምርጫ እና ምርጫ ህዝቡን የሚወክል፣ ሁሉንም የሚያቅፍ ምርጫ ተደርጎ የሚወክለው አካል የተመረጠው አካል ማስተዳደር አለበት” የሚል ሃሳብ ተነስቷል።
በተጨማሪም በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውስጥ ድሬዳዋ ውክልና ሊኖራት ይገባል የሚለው ነጥብ በስፋት እንደተነሳ በተጠቃለለው ሪፖርት ላይ ተቀምጧል።
በሌላ በኩል አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ ሁና በህገ መንግስቱ እውቅና ይሰጣት የሚለው ሃሳብ በስልታዊ ቡድኑ ወቅት በሰፊው የተነሳ ሃሳብ ነው።
“በብዙ ተሞካካሪዎች እና ብዙዎች እያሉ ያሉት ወይም እየተባለ ያለው፣ መሆን ያለበትም በቀጣይ አዲስ አበባ የሁሉም ህዝብ ሀብት ፈሶበት የተገነባች ከተማ ናት፤ የሁሉም መቀመጫ ናት። በቀጣይም ሁሉም የኔ ከተማ ናት ብሎ እንዲያስባት የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ እና የብዙ ትኩረት የስብኸት ማዕከል ናት፣ አዲስ አበባ አሁን ባለው ሁኔታ ነው መሆን ያለበት የሁሉም ከተማዬ ነች ብሎ እንዲመጣ ነው መሆን መቻል ያለበት” የሚልም ምክረ ሃሳብ በሪፖርቱ ላይ ተጠቀምጧል ብለዋል።
አክለውም “ስለዚህ ክልሎች ዋና መቀመጫችን ናት ብለው በህጋቸው በራሳቸው ምክር ቤት ሊያሳውጁ ይችላሉ፤ ልክ ኦሮሚያም አዲስ አበባ የኔ ዋና ከተማ ናት ብሎ ሊያሳውጅ ይችላል አሁን እየሰራበት ባለው ሁኔታ” እንደተባለ አንስተዋል።
እነዚህ የቀረቡት ነጥቦች ማለትም ሃሳቦች “የውሳኔ ሀሳቦች ሳይሆኑ ለመንግስት(ፓርላማ) የሚቀርቡ የምክር ሀሳቦች” መሆናቸው ተገልጾ፣ መንግስት ከሀገር ጥቅም እና ሉዓላዊነት አንጻር መዝኖ ወደ ተግባር ሊለውጣቸው እንደሚችል ተጠቅሷል።
ኮሚሽኑ በትናንትናው ዕለት ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጠበት ወቅት እሰካሁን የተወሰነ ውሳኔ እንደሌለ በማንሳት እየተካሄደ ያለው ምክረ ሃሳብ መሰብሰብ እንደሆነ ገልጿል። እንዲሁም የሦስት አጀንዳዎች ማጠናቀር በትናንትናው ዕለት የተጠናቀቀ ሲሆን ቀሪዎቹ በዛሬው ዕለት ተጠናቅቀው ለሥራ ቡድኑ ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።"

አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ