Prinz Harry und Meghan. (Braun Diamond.)

                    
                  የቡኒ ሚስጢር የብሌን ድምጽ ነው፤ 
                         የጠይም ዕንቁ ቅኔም ነው!

                                        ከሥርጉተ ሥላሴ 19.05.2018 (ከገዳማዊቷ ሲዊዘርላንድ)
           
                  „የሰው ልብ መንገድን ያዘጋጃል፤ እግዚአብሄር ግን አካሄዱን ያቃናለታል።“ (ምሳሌ ምዕራፍ ፲፮ ቁጥር ፱)
·         



  •        መኖር ሲያምርበት።

ዛሬን እጅግ ሐሤት ወደ አገኘሁበት ነጥብ አብረን ብያለሁኝ። የንጉሣውያን ታሪክ የምመሰጥበት ዋነኛ መስክ ነው። በዛ ውስጥ ያለው ሀገራዊ፤ ሃይማኖታዊ፤ ታሪካዊ፤ ትውፊታዊ ቅርስ ሰብዕናን በማነጽ ረገድ ያለው ሞራላዊ አመከንዮ ቀልቤን ይገዛዋል። አውሮፓ ላይ የሚኖሩ ንጉሣዊ ሥርዓቶችን፤ መሰናዶዎችን ሁሉ አቅጄ ፕሮግራም ይዤ እከታተላቸዋለሁኝ። በዚህ ዘርፍ ኢትዮጵያ ዲታ ነበረች ግን ፈቅደን አነደድነው። የ3 ሺህ ዘመናት ታሪክ አለን ስንል ያወራረድነው ኩራታችን በማንደድ ነው። ማንደዱም ብቻ አይደለም - አገለልነው። ማግለልም ብቻ አይደለም ተጸዬፍነው። ግን የክብር ክብር፤ የልዕና ልዕልና የዕንቁ ዕንቁ የቡኔ ዕንቁ ቅኔያዊ የሚስጥር ዕዮር ነበር። ብልሆች አይደለንም። ታላቁን ዓለም አቀፍ የመንፈስ የገብያ አዳራሸን ነው የደረመስነው - ፈቅደን። በአሁኑ የሥልጣን ሽግግር ትንሽ ወደ ራሳችን ተመልስን ግራማችን ሁንበት ያልነበት መንፈስ እና ምልክት ታይቷል። በዚህ ተጽናንቻለሁኝ። መልካሙ ነገር መልካምነት እንጂ ክፉነትን አይደለም የሚያሰረክበን። ብናውቅበት! ስስነታችን አሳስቶ ብቄተ ቢስ አደረገን። እንኳንስ ልንወዳደር ቀርቶ ጭንቅላታችን አንገታችን ችሎት ለመቆም እንኳን ጋዳ በገዳዳ ሆነ።
 
የሆነ ሆኖ ኑሮን በሥርዓት ለመመራት ያለው ጥበባዊ ጌጥኛ ሁለ አቅፍ የብልህነት የብቃት ህላዊነት ዓይን ያሰዬኛል። ከሁሉ በላይ የፍቅር ተፈጥሮ እና ህግጋቱ ገዢነቱን፤ ያለውን ጉልበት እንደ ማውጫ ስለምመለከትበትም የተለዬ አትኩሮት አለኝ ለአቤቱ ዓይነ ብሌን። ዓይን የተፈጥሮ ፓስተኛ ነው። ትናንት ለዛሬ ሁለመናዬን አሰናድቼ መንፈሴን በተሟላ ሁኔታ አስከ አሁን ከተከታተልኳቸው የንጉሣውያን የሠርግ ሥርዓቶች ሁሉ በጉጉት የጠበቅኩት ነበር። ልዩ አክብሮት አለኝ ለዚህ የሰዋዊ አንባሳደር ልዑል። የሰብዕዊነት ትጉሃኑን የልዑል ሄሪ ቻርልስ የጋብቻ ሥርዓት ለእኔ ፍጹም የሆነ ልዩ የታሪክ ምዕራፍ ነው። ስለምን? የቡኒ ሚስጢር ዓይን ላይ ስለመሆኑ ተረገጡን ማግኘት ናፍቆኝ።

ዛሬ ታላቋ ብርታንያ የነጮች ፖፕሊስትነት በሰፈነበት ዘመኗ በታላቁ ብልህ ጀግና ልጇ በልዑል ሄሬ ቻርልስ ምከንያት ታላቅ ገድል ተፈጸመባት። ዛሬ ዓለም ጉማም ናት። ነገ ዓለም ከዛሬው በባሰ ሁኔታ የምታስጨንቅ የምጥ ቀን ናት። ዓለም ከሰው ይልቅ በማሽን ፍቅር እና በግለኝነት ፍቅር ጡፋለች። የፍቅር ዓይን ሚስጢር ግን መልክዕ ምድራዊ አቀማመጥ፤ አይዲዮሊጂያዊ ፍልስፍና፤ ወግ፤ ልማድ፤ ባህል፤ የኑሮ ደረጃ ልዩነት አይገድበውም። ለምን? የፍቅር ሚስጢር ያለው ከዓይን ህሊና ማህጸን / አብራክ ውስጥ ነው። ዛሬ ዓለም በቀለም፤ በሃይማኖት፤ በሃብት፤ በርዕዮት ዓለም ልዩነት፤ በሥልጣኔ ደረጃ ከፍና ዝቅ በሚልበት ዘመን ዓለም ስለ ነገዋ ተቆርቋሪ ልጅ አገኘች ልዑል ሄሪ ቻርልስን። ለእኔ የመቻቻል ንጉሥ ብለው ይቀለኛል። የዓለም መዳኛዋ መፈወሻ መዳህኒቷ የፍቅርን ተፈጥሮ ካሪክለም ነድፋ በት/ ቤት ደረጃ መስጠት ስትጀምር ብቻ ይሆናል። ይህም ቢሆን የሂደትን ህግጋት መከተል ግድ ይለዋል። መልካም ሰብዕና በዓዋጅ መገንባት ስለማይቻል። ዛሬ ዓለም ታስፈራለች፤ የነገዋ ስትታሰብ ደግሞ ይጨንቃል።
  • ·         እንዲህም ሆነ - ዛሬ ዕለተ ቅዳሜ ግንቦት 19.2018 …

በዛ በተንጣለለው የታላቋ ብርታንያ የዘመናት ገናን ቤተ መንግሥታዊ የጋብቻ ሥርዓት የጠይም  ዕንቁ ወር እነሆ ግንቦት 19፣ 2018 ዓዋጁን ድንጋጌውን ህግጋቱን አጸደቀ ስለመቻቻል፤ ስለመከባበር፤ ስለ አብሮነት፤ ስለፍቅር፤ ስለ የሰው ልጅ እውቅና።
ሙሽሪት የጥቁር አፍሮ አሜሪካዊቷ ዕንቋዋ ተዋናይት ሜገን ማርከል ሚዜ አልነበራትም። በታወቀ ቤተሰብ ደረጃ ወላጅ እናቷ ብቻ ነበር የተገኙት። የባለቤቷ አባት ልዑል ቻርልስ የአባትነቱን ቦታ በመተካት ብቻ ሳይሆን፤ የወላጅ እናቷን ብቸኝነት በማስታገስ ደረጃ ታሪክ የማይረሳው ትህትናዊ፤ ልዑላዊ፤ ሰዋዊ፤ ተፈጥሯዊ ተግባርን ከውነዋል። የልባዊነት ፍሬ ነገር። ሥርዓቱ በጣም በርከት ያሉ ለዬት ያሉ ጥበቦችን የተከተለ ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ ከካቶሊክ ሃይማኖት ውጪ ያሉ የክርስትያናዊ ሃይማኖት አቮው በጋብቻ ሥርዐቱ ላይ ቃለ ምህዳን እንዲሰጡ ተደርጓል። በዜማም ደረጃ ቀለማም የሆኑ ትዕይንቶች ነበሩበት። ሌላው አውርፓውያን የነገሥታት ቤተሰቦች በሠርጉ ላይ ለምልክት አልተገኙም። መቼስ ካሜራ ጉደኛ ነው በልባቸው አስበውት ግን ሳያገኙት የቀሩ ደረጃውን የጠበቀ ኑሮ የሚኖሩ አንስት እንግሊዛውያን የልቦናቸውን ምኞት ምን እንደ ነበር ሹክ ብሎኛል - ለእኔ። 
  • ·         የቡኒ ቀለም ጥምረት በሰዋዊነት ቅኔ!

ሁለቱም ተጋቢዎች ለቡኒ ቀለም የተለዬ ፍቅር እና የልብ የሆነ አትኩሮት አላቸው። ተዋናይት ዕንቁዋ ሙሽሪት ራውንዳን ውሃ አጥታላች። ይህን ሳስብ የራውንዳ አምላክ ዘንድሮ ታምረኛ መሆኑን፤ ራውንዳ ህዝቡ የመንፈስ ዲታ መሆኑን፤ ምርቃቱ ጠብ የማይል መሆኑን ተረድቻለሁኝ። ጠ/ ሚር አብይ አህመድ እኮ ወጣትነት ጊዜያቸውን መከራውን የተጋሩት ከዛሬ ከ23/24 ዓመት በኋዋላ የኢትዮጵያ ብሄራዊ መሪ ሆኑ። ዛሬ ደግሞ ውድ ልጇ ተዋናይት ዕንቁ ሙሽራ በሃሳብም ታስቦ የማያወቀውን የነጮችን ቤተ መንግሥት ክብር ባለሙሉ አንባሳደር ሆነች። ሁለት ሦሰት አህጉራት ውል አሰሩ። ኪዳን ፈጸሙ። „ጋብቻ ቅዱስ መኝታውም ንጹህ“ ይላል ቅዱስ ወንጌል።

ይህ የመቻቻል አርበኛ የፍቅር ንጉሥም፤ ለአፍሪካ አብነታዊ ተግባራትን በመፈጸም ረገድ አንቱ ተግባራትን በመከወን ብቻ ሳይሆን አፍጋን በውትድርና ህይወት በነበረበት ጊዜ ዓለም አቀፍ ግዳጁን የተወጣ፤ የነበሩት የቅርብ ጓደኞች የውስጥ ቀረቤታ ለቡኒ የነበረው ልዑል የሥጦታ ያህል ነው። ከሁሉ በላይ ለአካል ጉዳተኞች የመንፈስ ሚስጢራቸው ነው። የትዳር አጋሩም እንዲሁ ይህን የመሰለ የርህርህና አቅም ያላት ድንቅ፤ በራሷ ላይ ሙሉ ዕምነት ያላት፤ መሆን ከፈለገችበት ደረጃ የደረሰች የደግነት ልዕልት ናት። በራስ የመተማመን ብቃቷ በሠርጓ ዕለት እንኳን ቤሎዋን፤ ውበቷን የሚከታታል ተጨማሪ ሃይል አላስፈለጋትም። ራሷን ራሷ ነበር የጠበቀችው። ምን ዓይነት ብርቱ ሴት ናት። ከእንዴት ያለ ቤተሰብ ነው ያደገችው? ነገስ? ጥርጥር የለውም! ልክ አንደ አርንጀንቲናዋ ኢቫ ፔሩ መሆንን ትሆንበታላች። ኢቫም መድረክ የጀመረችው በቲያትር ትውና ነው ሙሽሪትም እንዲሁ። 

ሌላው ድንቁ ነገር ይህን አዲስ ህይወት የተቀበለችበት ቀለሙ ህብሩ ርጋታው ይመስጣል። ጋብቻውን ስትቀበል ድምፆዋ ጎልቶ ነበር የወጣው። የምታደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ሁሉ እሷነቷን፤ ተከለ ቁመነዋን፤ ተክለ ስብዕናውን የሚያሳይ የቡኒነት ታሪካዊ ቋሚ ሥነ - ሙዚዬም ነበሩ። ጠይሟ ልዕልት የመጀመሪያዋ የታላቋ ብርታንያ ልዕልት ብቻ ሳትሆን ለአውሮፓ መቅድም ናት። ሲዊዲን፤ ዴንማርክ፤ ሆላንድ፤ ቤልጄም፤ ኖሮውይ፤ስፔን በቤተ መንግሥት ጋብቻ ውስጥ በጠይም የተቀመረ፤ የተጠለፈ ህብረ ቀለማም ታሪክ የላቸውም። እርግጥ ነው ሞናኮ ላይ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ጋብቻ አለ። ግን ቀለሙ የነጭ ለነጭ ነው። ሌላው ቀሪው የፈጣሪ ሥራ ነው። ፍሬ እንዲሰጣቸው እመኛለሁኝ። ያ ፍሬያቸው ዓለም በዬዘመኑ እያገረሸ የሚነሳበትን የቀለም ልዩነት በሽታ በፈዋሽነት ቃለ ምህዳን ይሆንል/ ትሆናለች የሚል ሩቅ ህልም አለኝ። እኔ ነገረ ዓለም ያስጨንቀኛል። አስፈሪዬ ነው።
  • ·         Cesar Sampson፤ 


ከግንቦት 8 እስከ ግንቦት 12 / 2018 በዚህ ዓመት ለ63ኛ ጊዜ በታካሄደው የአውሮፓዊ የሙዚቃ ውድድር ኦስትርያ ዕወቅና የሰጠችው ያው ቡኒውን ዕንቋዊ ሚስጢር ነበር። እኔ መከታተል የጀመርኩት ወደ 10 ዓመት ይሆናዋል። ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር ይህን የቡኒ ቀለም ምርጫ ያዬሁት በአውሮፓዊ የሙዚቃ ውድድር  Eroovision Song Contest። ይህ ውድድር በዬዓመቱ አሸናፊ በሆነው አገር ላይ የሚዘጋጅ ሲሆን የሙዚቃ ብቻ ሳይሆን የሥነ - ጥበብ ግሎባል የሥልጣኔ ደረጃ የደረሰበትን ዕድገት የሚታይበት ነው። ውድድሩ ከባድ ነው። ተወዳደሪዎች የሚያቀርቡበት የቋንቋ ዓይነት፤ የባህል ዓይነት ደንበር የለውም። በዬአገሩ ተወዳድረው አሻናፊዎች ሲገናኙ በሁለት ተከፍሎ ማክሰኞ እና ሃሙስ ማጣሪያ አለ። እርግጥ ማጣሪያው ሳይነካቸው የበለጸጉ ሐገሮች በቀጥታ ይሳተፋሉ እንደ ጀርመን ያሉ። የመጨረሻው ቀን ቅዳሜ ነው። አውሮፓ ብቻ ሳይሆን ወደ ሦስት/ አራት ዓመት የሆነው ይመስለኛል አውስትራልያም ትሳተፋለች። ቻይና ዝግጅቱን በቀጥታ አዬር ላይ ታውለዋለች። ሚሊዮኖች ነው የሚከታተሉት።
 
ባለፈው ዓመት በተለዬ አቀራረብ ከዬትኛው የሙዚቃ መምሪያ እንደሚመደብ አላውቅም፤ ለእኔ እንደ ሜድቴሽን ነበር ያዬሁት ፖርቹጋል ነበር ያሸነፈው። ለመጀመሪያ ጊዜም ነበር ፖርቹጋል ያሸፈነፈው። ዘንድሮ ደግሞ ካልተሳሳትኩ ለመጀመሪያ ጊዜ እስራኤል ነበር ያሸነፈችው። ልብ ነው የሚያንጠለጥለው የድምጽ አሰጣጡ ሁኔታ፤ መሃል የነበረው ላይ ሲወጣ፤ ላይ የወጣው ታች ሲሆን፤ ታች ያለው ወደ ላይ ሲወጣ በራሱ ልዩ ስሜት አለው። የጥበብ አይነት፤ የጸጉር ስታይሊንግ፤ የአለባበስ ዓይነት፤ የመድረክ ቅንብር ዓይነት፤ የቋንቋ ዓይነት፤ የልብስ ዓይነት፤ የባህል የወግ የልማድ አይነት፤ የአንሜሽን ሥልጣኔ ዓይነት፤ የሥነ - ግጥም አይነት፤ የፈጠራ ዓይነት፤ የጋዜጠኛ ዓይነት ይታይበታል። የአቀራረብ፣ የአገላለጽ፣ ፕሮግራም የመምራት ጥራት ሁሉም ዓይነት የመንፈስ ድርጁ አቅም ይገኝበታል። ትልቅ የሥነ ጥበባት ት/ ቤት ነው። አፍሪካስ መቼ?

ESC 2018

የዘንድሮው የአውስትርያ ተወዳደሪ Cesar Sampson  እኔ እንዲያውም ያሸንፋል የሚል ተስፋ ነበረኝ። ዩቱብ ላይም ምኞቴን ጽፌ ነበር፤ ግን ሦስተኛ ወጣ። በዚህም እጅግ በጣም ደስተኛ ነኝ። ይህ የሚያሳዬው የመቻቻል ደረጃ በህዝቡ ውስጥ ፍላጎት እንዳለ ነው። ኦስትርያ ራሱ ለእሱ ዕድሉን መስጠቱ ገርሞኛል። ባለፉት ዓመታት የፖፕሊስት አውሎ ሲንጠው ነበር አዬሩን፤ አብሶ በፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ የነበረው ጉግስ ቀላል አልነበረም፤ ለሁለተኛ ጊዜ ሁሉ ምርጫ እንዲካሄድ ያደረገ ወጀብ ነበረበት።
የሆነ ሆኖ የመጨረሻው ዕለተ ቅዳሜ ዬሐገሮች ዳኝነት ነጥባቸውን በቀጥታ ነው የሚሰጡት፤ በዚህም አንደኛ ነበር ኦስትርያ። ባልተጠበቀ ሁኔታም ነበር ማክሰኞ ዕለት በነበረው የማጣሪያ ውድድር ላይም አንደኛ የወጣው። ራሱ የኦስትሪያ ጋዜጠኛ ሂደቱን እየገለጸ ውጤቱ ሲናገር ደንግጦ ነበር። እርግጥ ነው ቅዳሜ ላይ በሌሎች ሦስት የድምጽ አሰጣጥ ሥርዓቶች ነው ወደ ሦስተኝነት ዝቅ ያለው። የዘንድሮ ልዩ ነበር። ተወዳደሪዎች ከ43 አገሮች የነበሩ ሲሆን ለመጨረሻው ውድድር የቀረቡት 26 አገሮች ነበሩ፤ ዝርዝር ታሪኩን ካስፈለጋችሁ ፊታውራሪ ጉግል ይጎለጉልላችሁዋል። እኔ በዚህ የመቻቻል፤ የአብሮነት ጥበባዊ ጉዞ ላይ የተለዬ አትኩሮት ስላለኝ በተመስጦ ነው የምከታታለው። ግንቦትንም በተለዬ ናፍቆት ነው በዬዓመቱ የምጠብቀው።
  • ·         Toni Loba የፍቅር ጠይም ዕንቁ!



ሌላው በሦስተኛ ደረጃ አሁን የፊታችን ሃሙስ እንደ አውሮፓወያኑ አቆጣጠር ግንቦት 24. 2018 ወደ 15ሺህ ተመልካች ታዳሚ በሚገኝበት የጀርመን የ2018 የሞድ አሸናፊ Germeny Next Topmodel 2018 (GNTM) ውድድር በደም ሐረግ ዘሯ አፍሪካዊ ናይጀሪያዊቷ በጀርመን ሽቶትጋርድ የምትኖረውን ቶኒ ትሆናለች ብዬ ነው እማስበው፤ ሦስት ተጨማሪ ተፈታኞችም አሉባት አንዷ እንደሷ ከጠይምነት ወደ ዳማነት ያደላች ናት። ለነገሩ ጥርጣሬም የለኝም። ይህ ውድድር ለረጅም ጊዚያት ከቦታ ቦታ እዬተነቀሳቀሱ በጋራ በመኖር የሚካሄድ ሲሆን ወላጆች ሥራቸውን በአግባቡ ስለማይሰሩ ፕሮጀክቱን ለሚመረቱ ለዓለም አቀፍ ሞዴሏ፤ የቴሌቪዠን ሞደሬተሯ፤ ለዳኛዋ ለወይዘሮ ሃይዲ ክሉም እና ለአጋር ዳኞቻቸው እንዲሁም ለተሳታፊ የካሜራው ቲም ሁሉ ብዙ ፈተና በዬዘመኑ ይገጥማል።

ሰብዕናቸው ያልጠኑ ተወዳዳሪዎች ከዘርኝነቱ ጋር ተዳምሮ ወይንም ከበታችነቱ ጋር ታክሎ ፈተናው በጣም ያዬለ ነው። ለዚህም ነው እኔ ወላጆች ልጆቻቸውን እንዴት ማሳደግ አለባቸው፤ የልጆቻቸውን ራዕይ ለማሰካት ምን ላይ ቢያተኩሩ መልካም ይሆናል የሚለውን „ የተስፋ በርን“ እንድጽፍ የተገደድኩበት አብዩ ምክንያት። ልጆች የማይገኘውን ዕድላቸውን በሥነ - ምግባር አቅም ማነስ፤ ወይንም ራስን ችሎ በመቆም አቅም መሳሳት፤ ወይንም በህሊና እንጻ ድህነት ምክንያት ወርቁን አጋጣሚ ያጡታል። እኔ ስለመጪው ነገረ ዓለም ያስጨንቀኛል። ትውልድ በአግባቡ ካልተገነባ አህጉርም፤ ዓለምም፤ አገርም እንዳለ አይቆጠርም።

እኔ የማዬው ግድፈት በሠለጠነው አለም ይሁን ባልሰለጠነው ዓለም በትውልድ አገነባብ ላይ ያለው ትጋት አንድ አቅጣጫ ብቻ የተከተለ እንጂ ህይወትን ተርጉሞ በዛ መልክ በሁለመናነት በማነጽ ረገድ ዓለም ራሷ ብዙ ነገር ይቀራታል። የተነጠለ፤ ወይ የተዘነጠፈ፤ ወይ ቅርንጫፍ የሆነ የአኗኗር ስልትና መንገድ ይዘው ነው ልጆች የሚያድጉት። ወላጆችም በዛ መልክ ስለመጡ ልጆቻቸውን አሟልተው የሁለገብ አቅም ባለቤት አድርገው አያሳድጓቸውም።

ቀደም ባሉት ዓመታት በዚኸው የሞድ የተክለ ሰውነት ውድድር ኤርትራ፤ ብራዚል መሰል ዕድሉን አግኝተው ግን ሊጠቀሙበት አልቻሉም። የኤርትራዋ ውብ ወጣት በጣም አግሬስብ ነበረች፤ የብራዚል ደግሞ አጋሮቿን ላለማዬት በጋዜጣ መጋረጃ የምትሰራ ነበረች አንድ ዓመት ላይ፤ ሌላ ዓመት ላይ ደግሞ በቃ እንደ ታንቡር ተረራ ሆነ በአዬር የተሞላች ነበረች። ትዕቢቷ ዳር ደንበር አልነበረውም። አንዳንድ የኦስትርያ የጀርመን ተወዳደሪዎች ደግሞ ከዘረኝነት ጋር የተያየዙ መቧደኖች በመፍጠር የህሊና ሽብር ይፈጥራሉ አብሱ በቡኒ ቀለማት ላይ፤ ከሁሉ በላይ ካሜራ እዬወደዳቸው የሚመጡ ተወዳዳሪዎች በርካታ ሥራ ስለሚያገኙ፤ በአድማ የሚደርስባቸው መገለል ሌላው ፈተና ነው።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ሌላም ውድድር ላንሳ። ባለፈው ዓመት የጀርመን ኮከብ የሙዚቃ ዕድል ያገኜ አንድ የ16 ዓመት ታዳጊ ወጣት ሃበሻ ነበር። የድምጹ መክሊት የሰማይ ሆኖ ግን ወላጆች ልጁን ሲያሳድጉ መኖርን ሳያስጀምሩ ነበር። ስለሆነም ያን የመሰለ ዕድል ተንከባሎ ቀረ። ታዳጊ ወጣቱ በቀን ቢያንስ ወሳኔውን 6 ጊዜ ይቀይራል፤ እመለሳለሁ ይላል፤ ሊመለስ ነው ተብሎ የሽኝት መስናዶ ሲጀመር እቀጥላለሁ ይላል፤ ሊቀጥል ነው ተብሎ ሥራ ሲጀመር እሄዳለሁ ይላል፤ ጥዋት ተነሳ አትነሳ መከራ ነበር። በጣም ብዙ ባለ ዕድሎችን ተሻምቶ ዕድሉን ካገኘ በኋዋላ መከራ።
  • ·         ስለ እናትዬ እና አቨይ ትንሽ።

እኛን እናታችን ስታሰድገን እጃችሁን እጣታችሁን እዩት አወፋፈሩ፤ ቁመቱ፤ ቅርጹ ይለያያል። ግን እጅ ሆኖ መኖርን ይሰራል ትለናለች። መበላለጡን፤ በቅርጽና በቁመት መለያዬቱ እጅን መዳፍ ከመሆን አይገድበውም፤ ስለዚህ አትቅኑ ትለን ነበር። አንዱ የበለጠ ሌላው ያነሰ ሊኖር እንደሚችል እመኑ፤ በጋብቻ ላይም ግማሽ ሹረባ፤ አንድ ጆሮ ጉትቻ ያምራልን? ጉትቻዋን አውልቃ ሁሉ ታሳዬናለች፤ አሁን እኔ አምራለሁን በአንድ ጆሮ ጉትቻ ብሄድ ጎንደር አበደች አይለኝንም? አንድን ብቻ ወገን ማቅረብ ግንጥል ጌጥ ነው። ዝምድና ተፈልጎ ነው አበልጅነት፤ ጉርብትና፤ ማህበርተኛነት የሚኮነው። ጋብቻም የሚፈለገው ለዝምድና ነው ትለን ነበር፤ ልጆቻችሁን የአባቶቻቸውን ሆነ የእናታቸውን ወገኖች እኩል እንዲዩ እናንተ ማስተማር አለባችሁ። ሁሎችም ያስፈልጓቸዋል። ጌጥ ጌጥ የሚሆነው ሙሉ ሲሆን ነው ትለን ነበር፤

አሁን እኔ ሙሉ ዕድሜ ላይ ነኝ። በዛ ዘመን ጨርቅ በጫማዋ ውስጥ ጨምራ አረማመድ ታስተምረኝ ነበር። ጎንደር ላይ። ስለሆነም በልጅነቴ ስጦታ ምን እናምጣለሽ ሲሉኝ መስታውት እል ነበር። የሞድ መጋዝንም አሳድጄ አይ ነበር። አባቴ 7 ዓመቴ ላይ ጠረጴዛ ላይ አቁሞ መጽሐፍ እንዳነብ ያደርግ ነበር። ያነበብኳቸውን እርእሶችን፤ ጸሐፊዎችን፤ የተጻፉበትን ዘመን፤ ጭብጦችን፤ የወደድኳቸውን አረፍተ ነገሮች እና ቃላትን፤ የአባባል ዘይቤዎችን እንድመዘገብ ያደርግ ነበር። ለዚህም ነው ምጻዕተ እስራኤልን፤ ፍቅር እስከ መቃብርን፤ እና ፊያሜታን እያንዳንዳቸውን 15 ጊዜ ያነበብኳቸው። አንብቤ አልሰለችም ነበር።

ወላጆች በት/ ቤት ብቻ ሳይሆን ቤታቸው ት/ ቤት እንዲሆን መትጋት አለባቸው። ማህበረሰብ በዚህ መልክ ነው የሚታነጸው። ከእኛ ቤት ቅናት አይታወቅም፤ አንግዳ አይጠላም ስንሸኘው መንገድ ላይ ይነጋል፤ ከማንኛውም ሰው ጋር ተላምዶ መኖር አይከብደንም። ለጓደኛ ሰብዕና እንጂ ምንም መስፈርት የለንም። ስጦታ መስጠት በሽሚያ ነው።

ስለዚህ ወላጆች ልጆች ሁለገብ ዕውቀት እንዲኖራቸው፤ ቀናተኛ እንዳይሆኑ፤ ሰብዕናቸው ሙሉዑ እንዲሆን ቤት ውስጥ መስራት አለባቸው። ይህን ስለማይሰሩ የጋራ ኑሮ፤ በራስ የመተማመን ዝቅተኝነት፤ ሃላፊነትን የመወጣት ብቃት፤ የናረ ቁጠኝነት፤ ከልክ ያለፈ ትዕቢት፤ ዘረኝነት፤ ሌሎችን ለመጨቆን መሻትን፤ የማይታይ የባህሪ ዓይነት የለም። ለሞድ ውድድር ሄደው ለነገሩ ውድድር ብቻ ሳይሆን ስልጠናም ነው ለዛ ወስነው ሄደው ግን ራሱ ጸጉራቸውን ለማስተካከል በሽምግልና፤ በቁልምጫ ነው። ሺዎች ተወዳድረው ዕዱልን ሳያገኙ ይቀሩና፤ ዕድሉን ያገኙት ናቸው እንደዛ የሚዘባነኑት። ይህን እምጽፈው በተለያዬ ሁኔታ ዕድል የሚያገኙ ልጆች በዕድል መጠቀምን እንዲያውቁ ወላጆችም በዚህ ዙሪያ ሥራ መሥራት እንዳለባቸው ለማስገንዘብ ነው። ጉዳዬ ነው እንደዚህ ያሉ የትውልድ ቀረጻ መሰረታዊ አመክንዮዎች። 
  • ·         ቶኒና ተጋድሎዋ፤

በዚህ ዓመት የነበረውን የተደራጀ የዘረኝነት ሰንሰለት በፍቅር፤ በችሎት፤ በበዛ ትዕግስት፤ በአሳታራቂነት ንጽህና አስማምታ ለመጨረሻው የፋይናል ውድድር የበቃችው ቶኒሻ ናት። በጣም የሚገርመው አንድ ወጣት ሲወዳደር የራሱን ፓተንቶች መደበቅ አለበት። እሷ ሰብስባ ለሚጠሏት ሁሉ ታስተምራለች። እንዴት መሰናዳት እንደሚገባቸው ሁለገብ መረጃ ትሰጣቸዋለች። ሌላው ደግሞ ቡድኑ ጥቁርና ነጭ በሚል የተደራጀ ሲሆን እሷ ከነጩ ከዳኛ እና አማካሪ አቶ ሚኬኤል ቡድን ስትሆን ሆነ ለጥቁሮችም ለዳኛ እና አማካሪ ለአቶ ቶማስ ቡድን አባላትም ጭምር ነው ሁለመናዋን የምትሰጠው። ሁለቱ ቡድኖች እንደ ቡድንም ውድድር አለባቸው። በዬቡድኑ ውስጥም እርስ በርስ ውድድር አለ። እሷ ግን ትህትናን፤ መከባበርን፤ ፈጣሪን ስለመፍራት ብቻ ሳይሆን በራስ መተማመን፤ መድፈርን፤ የገጽ አቀራረብን፤ የመፍጠርን ጥበብን ሁሉን በግልጽ ትነግራቸዋለች። ሲከፋቸው የሚጠሏትን፤ ጥቁረነቷን ማዬት ለማይሹት ሁሉ፤ የሚዋጓቱን እቅፍ አድርጋ ታባብላለች። ለሁሉችም ለዕናባቸው ቅርብ ናት። ወጣቶቹ ረዘም ላለ ጊዜ ከቤተሰብ ስለሚለዩ ናፍቆት ሲያጠቃቸው ቀርብ ብላ እያሻች ጭኗን አስደግፋ ታባብላቸዋለች። የቶኒ ልዩ ነው። ሁሉንም ሰጥቷታል። ከፍቅር በላይ ናት። ከባድ ውድድር ሲኖርባቸው ሰብስባ ጸሎት አድርጋ በአሜን ታሳርገዋለች። ፍጹም የሆነች የአፍሪካ ብርሃን ጥቁር ዕንቁ ናት።

ኢትዮጵያዊ ወጣቶች የማህበራዊ ሚደያ ታታሪዎች አፍሪካዊነትን የምትውዱ ዕንቡጦች እባካችሁ ኢትዮጵያን እዬጻፋችሁ የምትችሉትን ያህል ድምጻችሁን ፍቅራችሁን ስጧት - የእኛ ብትባል አታሳፍርም። የምትሰጧት ድጋፍ እንድታሸንፍ አቅም ይሆናለታል፤ ስለ አፍሪካም እንድታስብ የቤት ሥራ እግረ መንገዳችሁን ትሰጧታላችሁ።

እንዴት ካለ ከተባረከ ፈጣሪን ከሚፈራ ቤት እና መንፈስ እንዳደገች እጅግ ይገርመኛል። በሚሰጣት የቤት ሥራ ውስጥ ብቻ ሳይሆን የተፈጥሮም ልዩ መክሊት አላት። ሁሉ ነገር ከእሷ ሲደርስ ያምርበታል። በፓን አፍረካኒዘም ስሜት አብሶ ጀርመን ያላችሁ የቡኒነት / የጠይምነት ፍቅረኞች ልትረዷት ይገባል። የአፍሪካን ሥም ባልተጓደለ ሁኔታ በመልካም ምግባር እና ሙሉ ብቃት ወደፊት በዓለም አቀፍ ደረጃ ታስነሳለች ብዬ አስባለሁ። በሷ ያለኝ ትምህክት ሆነ ተስፋ በጉልሁ ነው። ባታሸነፍም ጥላቻን ያሸነፈች ብርቅዬ አፍሪካዊት ወጣት ናት። የፍቅር ዕንቁ!

የእሷ ትልቁ ኮሊቲዋ ያገኘችውን ዕድል ዕውቅና መስጠቷ ነው። ያገኘቸውን ዕድል መንከባከቧ ነው። መነሻዋን ያወቀቸው መድርሻዋን ያስገኝላታል። ዝቅ ብላ ዕድሏን አከበረችው። ለትንሿ ስጦታ ነገር ሁሉ ያላት አክብሮት እና አድናቆት እዮራዊ ነው። ታኮራለች። ሰብዕናዋ የትም የማይገኝ ነው። ዕድሜዋ እኮ ገና 18 ነው። በዚህ ዕድሜ ነው የሚያገሏትን ሁሉ ወዳ እና አጽናኝ ሆና የምታዮዋት። ፈርጣም ጠይሟ ዕንቁ አንድታሸንፍልኝ እኔም እጸልይላታለሁኝ። መልካም ዕድል የእኔ ውብ!
  • ·         ክውና።

የቡኒ ዕንቁ ጠይማን ግንቦት ላይ በምድረ አውሮፓ እንደ ጠሐይ። ሐሤት!

ጥቁርነት አዲስ ቀለም ነው!

የኔዎቹ ቅኖቹ ለነበረን የጠይማም ደማማዊ ጊዜ ኑሩልኝ ልሸልም። መልካም ሰንበት።
  • ·         የፎቶ ምንጭ ከጉግል ጋላሪ።

           እግዚአብሄር ይስጥልኝ
ESC 2018: Das Finale in voller Länge (mit Gebärdensprache)


አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።