#መለሲዝም ዕድለኛ ነው። ድምጡን አጥፍቶ ሥራውን ይሠራል። #ሌጋሲው ቀጥሏል። 2) ዝምታ #ከጩኽት ይከብዳል።

 

1) #መለሲዝም ዕድለኛ ነው። ድምጡን አጥፍቶ ሥራውን ይሠራል። #ሌጋሲው ቀጥሏል።
2) ዝምታ #ከጩኽት ይከብዳል።
 
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።"
 
 አቶ አህመድ ሸዴ የፓርላማ አፈ ጉባኤ። ወሮ ሙፍያት ካሚል የፌድሬሽን ምቤት አፈጉባኤ
 
 
ሁለት እርዕሶችን በአንድ ላይ አጣምሬ እስቲ ልሂድበት።
 
ከትናንት በፊት የሲዳማ የክልል ፕሬዚዳንት አቶ ደስታ ሌዳሞን ወደ #ፌድሬሽን #ምክርቤት አፈጉባኤ ሊሆኑ ይችላሉ ብዬ ጽፌ ነበር። የግምቴ አቅጣጫ ትክክል ነበር ማለት ነው።
 
"የአዲስ መንግሥት ምሥረታ።" መንግሥት በሌላት አገር የተፈጠሩ የአገር መሪወች? የሚገርሙ እኮ ናቸው። ኢትዮጵያ እኮ ከቀደምት መንግሥት ከመሠረቱ አገራት ተርታ የተመደበች አገር ናት። 
 
አየር ላይ ተተክሎ፤ በቅሎ እንደ ጸደቀ፤ እንደ አፈራም ሰብል ኢትዮጵያን #አብይዝም ሠራሽ አድርገው ባያቀርቧት ጥሩ ነው። ለነገሩ ኢህአዴግ ነፍሱ እንዳለ የሚያሳይ የምደባ ኩነት ተስተውሏል።
 
በሌላ በኩል #ስብጥሩንም በማስተዋል መመርመር ይገባል። ብልሁ ጉዳይ ያ ይመስለኛል። አዲስ ነገር ግን #አላየሁም። ሳሎን የነበረውን ወደ ጓዳ፤ ጓዳ የነበረውን ወደ በረንዳ፤ ከበረንዳ የነበረውን መኜታ ክፍል ሽግሽግ ነው። 
 
ለውጥ ለዛውም "#አዲስ" የት ላይ ይሆን ያለው። ይልቅ በቃላት፤ በሞቶ፤ በሥንኝ ውበት ከመጽናናት የተረሳው ቢሮክራሲ፤ ከፖለቲካ #ውክልና #ውጭ የሆነችውን #ቅድስት #ኦርቶዶክስ #ተዋህዶን ማሰብ። ምንም አያደርግም ተብሎ የተናቀውን ዝምተኛውን የማህበረሰብ ክፍል ሊያሳምን የሚችል የቁም ነገር ትጋትን አቅዶ መተግበር በእጅጉ ይገባል። 
 
በሌላ በኩል አባይ ማዶ ያለው መንፈስ #ሲፋቅ ወይ ሲገፋ የሚርቅ ክህሎት፤ በረከት፤ አቅም፤ ንጥረ ነገር ይኖራልም። ሦስት ቁልፍ አውታራዊ ቦታ የተደለደለበት አግባብ የኢትዮጵያን ህብራዊነቷን ይጠብቃል ወይ? ህብራዊነት #ሥልጣኔ ነውና። ራስን መግዛት፤ አደብ፤ ክህሎት በህብራዊነት ምርቃት እና በረከትም በዚህ ውስጥ የሚገኝ ፋክት ነውና። 
 
"ታላቅ አገር፤ ታላቅ ህዝብ፤ ታላቅ ራዕይ" የሰሞናቱ ሞቶ ነው። በስሱም ቢሆን ያጽናናል ተስፋ ይሰጣል። ለተስፈኛ የሰው ልጅ። ተስፋ ግን ብቻውን የጉሮሮ ማርጠቢያ ሊሆን አይችልም። ቢሮው አስተዳደራዊ ተግባሩን ኃላፊነቱን ሊሠራ ይገባል። ሚሊዮን የፓርቲ አባል በሚወጣለት በጀት ልክ ኃላፊነቱን በዲስፕሊን ቢወጣ እንዲህ ሰላም እርቆ ህዝብ ፈተናውን ችሎ ዛሬን እንደምን ሊያልፍ እንደሚችል ጭንቅ ጥብብ ሊል አይችልም ነበር። ሰላሙም እንዲህ #አይርቅም ነበር። "ከጎዳና ወደ ፓርላማ" የ2013 ዓም ሞቶ ያተረፈውን ባለሥልጣኖቹ እራሳቸው ይገምግሙት። ምን እንዳተረፋ፤ ምን እንዳከሰሉ?
 
በሌላ በኩል ደግሞ "ደሃ ለማኝ ነው። ክብርም ሉዓላዊነትም የለውም፤ ኦሮሞ ከኢትዮጵያ በላይ ነው።" ይህን ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ መስጥረው ሳይሆን በተለያዬ ጊዜ ተናግረውታል። "#ታላቅነት" የ7ወር ልጅ ሆነን? ለዚህ ነው እኔ ንግግርወት የተፃፈ ሊሆን ይገባል የምለው። ትውልዱ የቱን ይውሰድ? ግራ ያጋባል። 
 
ለአገር መሪነት፤ ለኖቤል ሽልማት ያበቃች አገር "ኦሮሞ ነፃ አልነበረም አሁን ነፃ ወጥቷል" የሚሉት እራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ናቸው። የኢትዮጵያ ጉስቁልና ለሚያጓጓቸውም መመከቻው እንዲህ ከተሰነጣጠረ አቅም የሚሆነው ለተቀናቃኞቿ ይሆናል። 
 
ወ/ ሮ ሙፍርያት ካሚል የፓርላማው አፈ ጉባኤ ነበሩ። የሰላም ሚር ነበሩ። በማህል ክህሎት መጣ ሥም ማውጣት፤ ሞቶ #መቀሸር ዛሬ ሳይሆን ጠቅላይ ሚር አብይ የተፈጠሩበት ነው። ይችላሉም። ግን ያ ሞቶ እና ተግባሩ ተገናኙ ወይ?
 
ሰው ምን ይላል? የምመራው ህዝብ ምን ሰንቋል? ጥረት ደስታው ለእኔ ብቻ ወይንስ ለህዝቤ??? ይህን ከዕውነት እና ከልብ መመርመር ያስፈልጋል። መፈተሽ ያስፈልጋል። 
 
1) #አጽናኝ ፈላጊው ሚሊዮን ነው።
2) አይዞህ፤ አይዞሽ መባልን #የናፈቀው ሚሊዮን ነው፤
3) በመፈናቀል ሙሉ 9 ዓመት የተንከራተተው ህዝብ #ደጋፊ ይሻል። እስኪ ደብረብርኃን ይሁን ሌላ ቦታ ተፈናቅለው ሁነኛ አጥተው ከርተት ለሚሉ ወገኖች ይደረስ እና ዕውነት እራሱ ቆሞ ይመስክር።
4) እስር ቤቶች ከፖለቲካ እስረኞች ብዛት፤
5) ቀየው ከድሮን ፍትጊያ ወህ የሚልበት፤
6) ሰው ለድህነቱ ማስታገሻ ወጥቶ የመግባት #ዋስትናው ይረጋገጥለት እስቲ።
7) ሰፊው የጠቅላይ ሚር ሥራ በወ/ሮ አለምጸሐይ ጳውሎስ እጅ ነበር የባጀው። ጠቅላዩ የወጣላቸው የመስክ እና የኮንስትራክሽን ሰራተኛ ናቸው። ቢሮውስ ------------ ???? ያ ወንበር በቃ ብቻውን ኮከብ ሲቆጥር ውሎ ይደርን? 
 
 የብልፄ መዋቅር ዲስፕሊን አሰባሳቢነት በከተሞች ያለው #አናርኪዝም፤ እገታ፤ ስወራ፤ ድንገተኛ ሰማዕትነት፤ መደፈር፤ የሃኪሞች መከራ፤ የሹፌሮች አሳር፤ የተጓዦች እንደ ወጡ መቅረት እጅግ ብዙ የተወሳሰቡ፤ የተተበተቡ ጉዳዮች አሉ።
 
መደራጀትም፤ ማደራጀትም፤ መምራትም #ቁጭ ብሎ መትጋትን ይጠይቃል። አየሩን መመርመር ይሻል። የሞጋቾችን ድምጽ መስማት ያስፈልጋል። አንድ የምርጫ ዘመን #ከነቦነሱ ተጠናቀቀ። በዚህ ውስጥ ምን ተከናውኖ ምን ተነዳድሎ ፈሰሰ???
 
የካቢኔ ለውጥ፤ የከተሞች የከንቲባ ለውጦች ለተከታታይ ተግባር #ዘባጣ መንገድ ነው። በየጊዜው ቅየራ። የአመራር ተከታታይነትን ስለሚያሳጣ የተግባር ድርቅ ይመታዋል። 
 
አየር ላይ፤ ሞገድ ላይ መሥራት ለፕሮፖጋንዳ ይሆናል ለዳቦ፤ ለልብስ፤ ለመጠለያ፤ በሰላም ውሎ ለማደር ግን አይሆንም። ህዝብ ማስተዳደር #የኢቤንት ጉዳይ አይደለም። ቆፍጠን ብሎ ሁሉኑም በእኩል ዓይን አይቶ በትክክል ማስተዳደር ይገባል። የምክክሩ የአጀንዳ ርክክብ ዕለት ምስራቅ አርሲ ሰማዕትነት ነበር። ህዝብን አድምጡ። ዝምታው እራሱ ብዙ ይናገራልና።
 
እርግጥ ነው ያልታቀዱ፤ ሊታቀዱም የማይችሉ የዓለም ዓቀፍ ችግሮች አሉ። ኢትዮጵያ እነዛ ችግሮችም ይነኳታል። ይጫኗታል። ይህን ለመቋቋም አላስፈላጊ ጊዜ፤ መዋለ ንዋይ፤ መንፈስ፤ ቲካ ቲኮ የሚፈስባቸው የአቅም ጅረቶችን ተግ አድርጎ የራስን ችግር ቅድሚያ መስጠት በእጅጉ ያስፈልጋል። በጣም በእጅጉ። ጥሪት መቆጠብ ያስፈልጋል። ነገ ምን ይዞ እንደሚመጣ ስለማይታወቅ። ለዛውም ባላባራ ጦርነት ውስጥ ላለች አገር። 
 
ብልፄው እርካታ ላይ ነው። ተመጋጋቢ የፖለቲካ ድርጅቶችም እንዲሁ። መግለጫቸውን ሳነብ ነበር። ግን ታች ያለው ህዝቡ ምን ይላል? በተለይ የሳይለንት ማጆሪቲው ልቦና ምን ሁኔታ ላይ ነው ብሎ አክብሮ ማጥናት ያስፈልጋል። ከጩኽት ይልቅ ዝምታ ያስፈራልና።
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
06/10/026.
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።