#ባራክስ።
"የመዘመዷ ቸርነት ወደ እግዚአብሄር ያቀርባልና።
ደም ግባቷ ን የምወድ ሆንኩ። የእግዚአብሄርን
ሚስጢር ለማወቅ መካር ናትና ሁሉን የሚገዛ
እርሱ ወደዳት፤ ከፍጥረቱም ሁሉ ትበልጣለች።"
(መጽሐፈ ጥበብ ምዕራፍ ፰ ቁጥር ቁጥር ፫ - ፬)
#ምዕራፍ ፳።
እንዴት አደራችሁ ውዶቹ ክብሮቹ። እኔ አምላኬ ክብሩ ይስፋ ደህና ነኝ።
#ጠብታ።
ትናንት የምርጫ መያዣ በየዓምስ አመቱ ሆኖ ዓመታትን ያስቆጠረው የመገጭ ግድብ ሙሉ ለሙሉ ሳይጠናቀቅ ለምረቃ መቅባቱን ተከታትያለሁኝ። የጎንደር ውጥን ፕሮጀክቶች ቁሞ ቀሮች ናቸው።
ይህ ለምን ሆነ?
ይህ እንዴት ሆነ? የሚለው በተወላጆቹ ዘንድ ይታወቃል።
በነፍስ ወከፍ አቅማችን የምንሳደድ ጎንደሬወች ጎንደርን እንደ ክ/አገር የሚጠናወታት መጥናቱ የማይደንቀኝም ለዚህ ነው። ብዕር እና ብቻ ያለኝ እኔ እንኳን ያለብኝን ዕድሜ ሙሉ ውሃ ያዘለ ፈተና ጠንቅቄ አውቀዋለሁኝ። ህይወቴም እሱ ነውና።
የማንነት ቀውስ ያለበት ሁሉ አንጡራ ጠላቱ ጎንደር እና ጎንደሬ ነው። ይህ ደግሞ አይደንቅም። የሌለው ባጣው ነገር ላይ በራሱ የቀውስ ካብ ቢሰራ እግዚአብሄር ይማርህ ከማለት ውጪ ቅንጣት ጊዜ የሚጠፋበት፤ ከዓለማችን እና ከግባችን አንዲት ስንዝር ፈቅ የሚያደርገን የለም። ትናንትም ይሁን ዛሬ ክፋ ሃሳብን፤ የክፋ ሃሳብ ቤተኞች ከመታገል የገደበን ማንም የለም።
እኔ በር ቢዘጋ በመስኮት፤ መስኮት ቢዘጋ በጣሪያ፤ ጣሪያ ማዕቀብ ቢጣልበት በምድር መተንፈሻ ቧንቧ አፈላልጌ በጥሪዬ ልክ በመትጋት እረገድ መቀጠሌ አይቀሬ ይሆናል።
እኔ #የማንም አይደለሁም። ልሆንም አልፈቅድም። እኔ የራሴ ነኝ። ብቁ አሻራ ያለኝ በመሆኑም እራሴን አፍርሼ በአፍላ ብቅ ጥልቅ በሚሉ ጊዜ ሰጥ፤ ግን ለእግረ ተከልነት ሳይበቁ በሚሰናበቱ ተቋማት ዘው የምል አይደለሁም።
ደረጃ መዳቢወች ወይ ይሄን ወይ ያነን ሲሉ አዳምጣለሁኝ። ይህንንም ይሁን ያነንም መሆን የማንፈቅድ በራሳችን ግንድ ጸንተን የቆመን ሰብዕናወች እንዳለን አይገነዘቡም።
ይህን የሚያደርገው በራስ የመተማመን አቅማችን በተፈጠረበት #ልክ ትክክል የሆነ የጸና መሠረት ስላለው ነው። ስለሆነም ለደርሶ መልስ #ተርቲመኞች የማይመች ሰብዕና፤ ለራሱ ቋሚ አሻራ እና ራዕይ ግን ተማላው ሳይሆን ፍፁማዊ ታማኝነቱ የጸደቀ ነው።
የዛሬ የጭብጤ አናት የተከበሩ የጋናው ፕሬዚዳንት ጆን ድራማኒ መሃማ በመገጭ የከፊል ተግባር መጠናቀቅ ምክንያት ጎንደር ላይ ተገኝተው የኢትዮጵያዊነትን ሚስጢር የገለጡበት አግባብ መሰጠኝ እና ቤት - ለንቦሳ አልኩኝ።
ጎንደር እና የጋናው #ባራክስ በዚህ ውስጥ የነፃነት አብሳሪ የደህንነት ተቋም በኽረ ሥያሜ በጎንደር ሥም ጋና ላይ ዕውቅና አግኝቶ፤ ተከብሮም መሰየሙ የኢትዮጵያዊነት ሚስጢራዊነት ነገር #ድንበር የለሽ መሆኑን ያመላክታል።
ጋናውያን ምን ብልሆች ቢሆኑ የነፃነት በኽረ እስትንፋስ አስኳላቸውን ኮራቸውን፤ የጠቅላይ ማዘዣ ጣቢያቸውን በጎንደር ሥም እንደሰየሙ ሳስብ ስጦታው #የመንፈስ ቅዱስ ነው ብዬ አመንኩኝ።
የአፍሪካ የነገሥታት ድንቅ ፓላስም ያለው ጎንደር ላይ ነው። ፓን አፍሪካኒስቶች የአፍሪካ መሪወች ይሁኑ ፓን አፍሪካኒስቶች ጠይም ዕንቁውያን ጎንደር ላይ ጉባኤ ቢያካሂዱ፤ ኢቬንት ቢኖር ብዬም እመኛለሁኝ።
"ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመገጭ የመስኖ ግድብ ምረቃ ላይ ያስተላለፉት መልዕክት"
"የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ አረጋ ከበደ በመገጭ መስኖ ግድብ ፕሮጀክት ምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ያስተላለፉት መልዕክት" @ethiopiannewsagency
"የጋናው ፕሬዚዳንት ጆን ድራማኒ ማሃማ የመገጭ መስኖ ግድብ ፕሮጀክት ምርቃት ላይ ያስተላለፉት መልዕክት" ETV | EBC | EBCDOTSTREAM.
ብዙ የመገጭ ግድብ እርዕስ በመንግሥት ሚዲያ የተሰጠው ሥያሜ ገርሞኛል። እንዲህ ዓይነት የግነት ግርግሮችን የሚያሰክን ኤዲተርያል ቦርድ የሚያስፈልጋቸው ይመስለኛል። ጥሩ ጅምር ነው። ግን #የርብ ዕጣ ፈንታ፤ ወይንም የዳቦ ብሉ ተብላችኋል ዕጣ ፈንታ ይግጠመው የሚታወቅ ነገር የለም። እርግጠኛ የሚያደርግ ነገር የለውም። አልተጠናቀቀም። ተጠናቀቀ የተባለውም ወደ ሥራ ለመግባት ያለው ሁነትም የምናውቀው ነገር የለም። ስለሆነም ርዕስን በልኩ ማድረግ የሚገባ ይመስለኛል።
በጣም የሚገረምኝ፤ የሚደንቀኝ ገጠመኝ ጎንደር ለስራ ይሁኑ ለባዕል አከባበር የሚሄዱ ወገኖቼ የሚሰጡት ወጥ ዕይታ ነው። ሬድሜድ ነው። ሁሉም በአንድ ድምጽ የጎንደርን ህዝብ አክብሮት፤ ፍቅር፤ ትህትና፤ አቅርቦ የማየት ጸጋ፤ እንግድነት እንዳይሰማ የማድረግ ጥበብ ሲገልጽ #በዓዋጅ የተነገረ ይመስላል።
ስለሆነም የጋናው የነፃነት አብሳሪ የደህንነት ጠባቂ መንፈስ፤ ትንፋሽ በጎንደር ሥም መጠራቱ የመንፈስ ቅዱስ የፈጸመው ታላቅ ገድል ነው ብዬ አመንኩኝ።
በጎንደር ሥም መንገድ፤ ተቋም በሚመለከት ጣሊያንም፤ በብሪቴንም እንዳለ አድምጫለሁኝ። ይህን መሰል ጸጋ አክብሮ ለመነሳት የተደላደለ፤ ደርባባ እና በራስ የመተማመንን አቅም ይጠይቃል።
ይህ ሲጠፋ ነው እራስን አሳንሶ፤ የእራስን ነገር አኮስሶ ወይንም እራስን ጠልቶ #ክስ ላይ ጊዜ የሚቃጠለው። ጸረ የኢትዮጵያ መንፈስ ደርጅቶ እራስን ወደማክሰም፤ እራስን ወደ መንቀል፤ ቀደምትነትን ወደ መጠየፍ የሚወስደው ጎዳና መቅድሙም ይሄው ነው።
ለዚህም ነው እኔ አዘውትሬ ኢትዮጵያ የከበደችን ለሁላችንም ነው የምለው። ኢትዮጵያዊነት የዕውቀት ዘርፍ ነው። በዩንቨርስቲ ደረጃ ሊማሩት የሚገባ፤ ሌላ ፍልስፍና ለኢትዮጵያ ፖለቲካ አያስፈልገንም፤ እራሳችን እኛነታችነን ልንማረው ይገባል ብዬ ለረጅም ጊዜ የምሞግተውም ለዚህ ነው።
ሁልጊዜ እኛ ስላለን ነገር አቅልለን፤ እንዲያውም ከሳሽ ሆነን፤ ሌሎች አፍሪካውያን ይሁን አውሮፓውያን፤ አውሮፓውያን ይሁኑ ምዕራባውያን፤ ምዕራባውያን ይሁን እስያውያን ስለ ኢትዮጵውያን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ቁጭ አድርገው ፊደል ስለራሳችን ክብር፤ ልዕልና እና ልቅና ያስተምሩናል። አንዳንዶች ሥሟ ሲጠራ የሚንገፈግፋቸውን ቁጭ አድርገው ያስተምራሉ።
በየዘመኑ የሚነሱ የፖለቲካ ርዕዮቶች ከኢትዮጵያ በላይ ሆነው፤ ኢትዮጵያዊነትን የሚራገጡበትን ሁነት ግድፈታቸውን አርመው ወደ ቀልባቸው ይመለሱ ዘንድ በዚህ አጋጣሚ በትህትና ላሳስባቸው እወዳለሁኝ። ኢትዮጵያን ተቀበልን ሲሉም የኢትዮጵያን መንፈስ ወስደን ከእሷ በላይ እዩን ዓይነት ነው። ቀላል ነጋዴወች አይደሉምና።
ኢትዮጵያ ከየትኛውም የፖለቲካ ርዕዮት፤ ከየትኛውም ህዝብ፤ ከየትኛውም መሪ በላይ ናት። ሊለካኩ፤ ሊፎካከሩ የሚችሉ ሁነቶች ተቀራራቢነት ሲኖራቸው ብቻ ነው። ትንፋሽ ከማን ጋር ይወዳደር? በዚህ ልክ እሰቡት?
በመገጭ ውስጥ ኢትዮጵያ አለች። በመገጭ ውስጥ ኢትዮጵውያን አሉ። ይህን ፋክት ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚለው ሁሉ በልበ ሙሉነት ይቀበለዋል ወይ????
#ለምን?
ማይክ የያዘ የድል አጥቢያ አርበኛ፤ መናገር የሞከረ አዲስ ተናጋሪ መድረክ ሲያገኝ የሚጀምረው ክፋ ሃሳብ በጸረ ጎንደርነት ነው። ትግል የጀመርኩትም በዚህ ነው የሚሉም ይገጥማሉ። መነሻቸው ይሁን መዳረሻቸው ቁልቁል ዘቅጦ ኢትዮጵያዊነትን በቀጠሮ የሚለው መንፈስ ምንጩም ይኽው ነው።
ይህም ብቻ አይደለም ከአማራ ሊቃናት ተለይተው በየዘመኑ የሚቀጠቀጡት ጎንደሮች ብቻ ናቸው። ሰማዕትነትን የሚቀበሉትም እነሱው ናቸው። በግለሰብም ደረጃ መድረክ የሚነፈጉት፤ የሚሳደዱት በአድማ የሚዋከቡትም ዲስፕሊንድ የሆኑ ጎንደሮች ናቸው።
የሚያጠፋ፤ የሚገድፋ ሊኖሩ ይችላሉ። ግን ለሌላው ግድፈት ጽድቅ ለጎንደሬ ኩነኔ የሚሆንበት ጉዳይ አይገባኝም። በዚህ ድብልቅልቅ ጉሽ ገጠመኝ ታልፎ የመገጭ ፕሮጀክት በከፊልም መጠናቀቁ ጥሩ ነው።
ጎንደርን በሚመለከት ብዙ ትብትብ መከራ ነው ያለው። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሊቃናት በተለይ የነፃ አውጪ ግንባር መሥራቾችም ይሁኑ መሬወች ኢትዮጵያን ሳይሆን ጎንደርን እንዴት ያዮዋታል ተብሎ ጥናት ሊሰራበት የሚገባ ይመስለኛል። ጎንደር ጽንሷም ውስጧም ትርትዋም ኢትዮጵያ ናት።
የሆነ ሆኖ ያን ትሬኮላታዊ የቢሮክራሲ ትብትብ ተቋቁሞ ጎንደር አስቦ መሥራት ከባድ ነው። አሰልቺ ነው። ዳጥም ነው። በክፋ ዓይን የምትታዬው እቴጌ ጎንደር በአብዛኛው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሊቃናት ነው። ለምን? መንፈሷ #ያስቀናልና።
#ሰላም።
በ100 ቀናቱ የጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ የተግባር ጊዜ አንድ ረጅም ጹሁፍ ግንቦት 5/2010 ዓም ጽፌ ነበር። ጎንደር ሰላሙን መጠበቅ ይገባዋል የሚል። አልሆነም የመጀመሪያው 80 ሺህ ተፈናቃይ ማዕከላዊ ጎንደር ላይ ነበር። የስሜን ፓርክ ቃጠሎም እንዲሁ።
ሌላው በጠቅላይ ሚር አብይ የ100 ቀናት ጉብኝት ከተደረገባቸው ከተሞች አንዷ ጎንደር ነበረች። አንድ ተሳታፊ "ለእኛ ወደ ደቡብ ሄዶ መኖር ይሻለናል ተረስተናል" የሚል ጥያቄ ቀርቦ ነበር።
ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ሲመልሱ "እርስወ ሌላ መኖሪያ ሲያልሙ እኛ ደግሞ ጎንደርን አልምተን መኖሪያችነን ወደ ጎንደር እናደርጋለን።" በማለት ቃል ቢጤ ሰጡ።
ምንም አዲስ ፕሮጀክት፤ ነፍስ ያለው እሸት ፕሮጀክት አላቀዱም፤ አልፈጸሙም ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ። ጎርጎራ የማሻሻል፤ የማዘመን ፕሮጀክት ነው። በፊትም ነበር።
ከእሳቸው ቀድሞም ሻለቃ ኃይሌ የወጠነውን ወስደው ነው እሳቸው ጎርጎራን የሠሩት፤ ፋሲል ግንብንም በሚመለከት የነበረውን አዘምነው ነው፤ መገጭም ቁሞ ቀር የነበረ ያውም ያልተጠናቀቀ ነው ለምርቃት የበቃው።
በደርግ ጊዜ የአንገረብ ፕሮጀክት ነበር። ያ ተለውጦ መገጭ ይሁን አይሁን አላውቅም። የአንገረቡ ሥሙ በመገጭ ሆኖ ከሆነማ ወደ 36…37 ዓመታት ሊሆን ይችላል።
ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ለትውልድ የሚሆን ሜጋ የሚባል ፕሮጀክት የወጠኑት የት ላይ እንደሆነ የሚታይ ነው። 12.5 ቢሊዮን$ አሁን ባለው ምንዛሬ አምስት ዓመት ሲታከልበት ሊጨምር ይችላል፤ የነዳጅ ማጣሪያ፤ የመኖሪያ ዘመናዊ አንባ፤ የንፋስ ኃይል ማመንጫ የሚታዩም /// የማይታይም የተነገረንም /// ያልተነገረንም #ግዙፍ ፕሮጀክት በቃላቸው መሠረት ለአንድ መሪ እና ቤተሰቡ ምቹ የሆነ በዕት የት ላይ መቼ? #መብራት እና #ውሃ እንኳን የለም። ለማን ከውስጣቸው እንደሚቆረቆሩ ቃለ ምልልሳቸው ላይ ማንን አክብረው፤ በትኩሮት እንደሚያቆላምጡ ይታወቃል። "ሁሉን ቢናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራል ይላሉ" ባለቅኔወቹ ጎንደሮች።
ይህ ቀርቶ የጎንደርን መንፈስ ዳይበርስ የማድረግ ተልዕኮም እታዘባለሁኝ። የ፵፬ቱ እናት መባሏ ይመቻቸዋል ብዬ አላስብም። የትም ቦታ በተዋህዶ አማንያን ላይ የሚፈጸም ጥቃት ሲኖር ማወራረጃ ክስ የሚጠነሰሰው፤ የሚፈጸመውም ጎንደር ላይ ነው። ጥፋቱ ማንም ይፈጽመው ማን።
ሌላው የኮሪደር ልማቱ ለሌሎች ከተማ እንደተደረገው ተከውኗል። የጎንደር ከተማ መናኽሪያ ፒያሳ ቀለሙ ለእኔ "ገድሎ እግዚአብሄር ይማርህ" ዓይነት ነው። ፒያሳ #ደማና ነው የለበሰው። እንኳን ሊናፍቀኝ ሲመጣ ቢዲዮ ላይ ያመኛል። የቀድሞ ቅርሱ ቀለሙ የምናውቀው፤ የምንሳሳለት ፒያሳ ዛሬ የለም። ለተወላጆቹ እርካታችን የነበረው ቅርሱ በአለበት እንዲሆን ነበር። ይህ ቢስተካከል ምርጫዬ ነው።
የመንገዱ መታደስ ፊት ለፊት ያለው ብቻ ነው። በስተጀርባ ከመንበረ - መንግሥት መዳህኒዓለም እስከ አደባባይ እየሱስ ያለው መንገድ የ13ኛው መቶ ክ/ዘመን ይመስላል። አስፓልቱ አልቆ፤ አፈሩም የላይኛው ጠፍቶ ጉድጓድ ሆኗል። ለገበጣ ጨዋታ የተዘጋጄ ይመስላል።
የፋሲል ግንብ ፊት ለፊት ታድሶ፤ የጀርባው ደግሞ ቅጣቱ ቀጥሏል። ጥርት ያለ፤ አፍ ሞልቶ የሚያናግር ጥረት እና ስኬት ቢወደስም፤ ይሁን ቢጋነን ይሁን ይባል። እንደዚህ በተባደግ ግን ………
በሌላው በኩል አድያም ሰገድ እያሱ ታቦት የተሸከሙለት ደብረ ብርሃን ሥላሴ የቱሪስት መዳረሻ ነው። ከጉምሩክ እስከ ደብረብርኃን ሥላሴ፤ ከቆባስጥል እስከ ህብረት ፩ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያለው መንገድ አይተውትም አያውቁም። ታቅዶም አያውቅ። የለብ ለብ ሥራ አያስፈልግም። "ወይ ባልዘፈንሽ ከዘፈንሽም ባላሳፈርሽ።" አንዲት ነገር ያላገኜ ጎንደር "#ያማች አገር፤ እስኳድ" እየተባለ ነግቶ እስኪመሽ ድረስ ሲቀጠቀጥ ውሎ የሚያድረው በሳቸው ምክንያት ነው። ሁለት ያጣ ጎመን።
ስለ ሰላሙ ያነሱት ነገር ግን ትክክክል ነው። ፕሮጀክት ሰላም ከሌለ ሊታቀድም፤ ሊከወንም አይችልም። ይህም ቢሆን ድፍርስርስ ያደረጉት እሳቸው ናቸው፤ ዶር አብይ አህመድ።
እንዴት ማለት ጥሩ ነው ይላል የጎንደር ሰው። በዘመነ ኮረና ትጥቅ ለማስፈታት ጎንደር ከተማ እና #ላስታ ነጥለው ያልተመረመረ ሰራዊታቸውን አዘመቱ። ጎንደር ከተማ በግርግሩ አንድ ታዳጊ ሙቷል የቀበሌ 18 ልጅ ይመስለኛል። አስታውሳለሁኝ አክቲቢስት የፖለቲካ ሳይንስ ሙሩቁ አቶ ሙሉነህ የኋንስ ፒቲሽን ሁሉ ሲያስፈርም ነበር።
እሰቡት በኮረና ጊዜ ነው። ስንት ጥንቃቄ በሚያስፈልግበት ጊዜ። ወገራ ላይ የአውሮፕላን ቅኝት ሁሉ ነበር። ጎንደር ጥሞና ላይ ሆኖ ዝም ሲልም እራሳቸው አይወዱም። እራሳቸውም ዶር. አብይ አህመድ ለላስታ እና ለጎንደር ጸጥታ ቀናዒ አልነበሩም። ከዛ በኋላ የሆነው ሌላ ጉዳይ ነው። አጨምቼ ባልፈው ምርጫዬ ነው።
እን ራሴ በተለያዬ ጊዜ ስጽፍ አገር በቀል ባህል አለ። ገጠር እራሱን ያስታጥቃል። የአገር መከላከያ የገበሬ መንደርን ሁሉ ሊጠብቅ አይችልም። ባህሉ የአካባቢው ሰው ነው የሚጠብቀው። በመተማ በሰቲት ደንበር የሚጠበቀው በአገሬው ነው። ትጥቅ አስፈታለሁ እንዳይሉ ብዬ ሁሉ ጽፌያለሁ። አልሰሙም። አስቀድሜ ሥልጣን በያዙ በመባቻው።
ሌላው እሳቸውን ለዚህ ሁሉ ዕድል ያበቃው "ወልቃይት ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ።" መወሰን ተስኗቸው እየቀጡት፤ ህወሃት ይሻለና እስኪል ድረስ እየገፋት እንዳለ እሳቸውም ያውቁታል፤ እኛም እናውቀዋለን። በየለቱ ያለው ዲሞሽን እና ትራጀዲ እጅግ ያሳዝናል። ለማን መንፈስ ልዩ ጥበቃ እንደሚያደርጉ፤ ማንን እንደ ተጫኑት ጎንደሬው ሁሉ ይጠፋዋል ብዬ አላስብም። ያዳላሉ፤ ያገላሉ።
"በዕድል ተጠቀሙ ንቁ" ሲሉ አዳምጫለሁኝ። ቢናቃም፤ በዕድል ልጠቀምም ቢል ጎንደሬ ይሁን የአማራ ህዝብ በህሊናቸው ውስጥ ድርሻ አለ ወይ???? ይህን ጠቅላይ ሚሩ ይሁኑ የቅርቦቻቸው ይገምግሙት ። አይተናል እኮ በመንግሥት ሚዲያ ለቃለ ምልልስ ቀርበው ደቡብ አፍሪካ አምነው የላኳቸው፤ ዛሬም ቁልፍ ኃላፊነት የሰጧቸው ሊቆቻቸው አማራን በሚመለከት በምን ያህል ኪሎሜትር እርቀት እንዳላቸው ሲያናንቁ፤ ሲያጣጥሉ ሊቃናቱን። ዝምታችን ብዙ ነገር ሰንቆ እንዳለ ቢያውቁ ጥሩ ይመስለኛል።
ዕውነቱ ግን ዛሬ ላለው ሥርዓት፤ ለሹመቱ ይሁን ለሽልማቱ ያበቃው ገራገሩ የአማራ ህዝብ #ይሁንታ ነው። ይህን ዘመንም፤ ሂደትም፤ ቁልፍ የዓለም ፖለቲካ የጀርባ አጥንቶች ጠንቅቀው ያውቁታል። አባ ቅንዬ አማራ እጁ አመድ አፋሽ ነው እንጂ።
#ቁሞ ቀር ፕሮጀክቶች።
በቁሞ ቀር ፕሮጀክቶች ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድን መውቀስ አልችልም። እሳቸው ለሚያቅዷቸው ፕሮጀክቶች ጀምረው የመፈጸም አቅማቸውን አያለሁኝ። ትጉህም ናቸው። የመሪነት አቅማቸው ያለው ኮነስትራክሽን ተኮር ነው።
የአባይ ግድብን ፕሮጀክትም በዚህ ሁሉ ውስብስብ ፈተና አጠናቀዋል። የጎንደር ልጅ ኢንጂነር ስመኜው በቀለም ሰማዕትነት ተቀብለውበታል።
የመገጭ ግድብ ከፊል ነው የተጠናቀቀው። ሳይጠናቀቅ ለምን መመረቅ እንደ ተፈለገ አላውቅም። አይገባኝምም። ርብንም እንዲሁ ሳይጠናቀቅ ተመርቆ ቁሞ ቀር ሆኗል። ሞልቶ በህዝብ እንዲያውም ተመረቀ ከተባለ በኋላ በንብረት ላይ እና በህዝብ ጉዳት ማድረሱን ሰምቻለሁኝ።
ታስታውሱ እንደ ሆነ ስለ ጣና እንቦጭ እና ስለ ላሊበላ ጥገና የአማራ ህዝብ ሰላማዊ ሰልፍ ወጥቶ ነበር። በዛው ቀን ነበር ርብ በድንገቴ ሁነት ምረቃት የተከናወነለት። ግን ርብ እስታሁን ተጠናቀቀ ወይ?
#የአዘዞ መናህሪያም እንዲሁ ቁሞ ቀር ፕሮጀክት ነው። ውሹንም የሚያነሳው የለም። የደብረታቦር አየር ማረፊያም በተመሳሳይ መልኩ ተንጠልጥሎ የቀረ ፋንታዚ ነው። ሰሞኑን እስቴ አንድአቤት አካባቢም የድሮን ጥቃት እንደነበረ አድምጫለሁኝ።
ፋሲለደስ ትምህርት ቤት የሶርያ የጦር ዓውድማ ይመስል ነበር። ልጆቿ ነፍሱን የታደጉት ይመስለኛል። ትናንት የንጉሦች ንጉሥ የአጤ የኋንስ ትምህርት ቤትን አቶ አሰፋ አብርኃም ከአደራው አስተዳዳሪ ጉብኝት ጋር ተያይዞ አየሁት። ዩንበርስቲ ነው የሚመስለው። በነገራችን ላይ የአቶ አሰፋ አብርኃ ርጋታቸው ስቦኛል።
የመቀሌ ከንቲባውም እርጋታ እንዲሁ። ማደመጥ ይቻላል የተረጋጋ መንፈስ ያላቸውን ወገኖቻችን ወደፊት ሲመጡ። ሃሳቡ ቢስማማንም ባይስማንም ለማድመጥ ፈተና አለና። ንግግሩን ምጥ ላይ የሚጥዱ ተናጋሪወች ጋዳ ናቸውና። አዲስ ፊትም መሆኑ የረዳ ይመስለኛል። የሆነ ሆኖ ንግግሩን እያዳመጥኩኝ ፋሲለደስን በምናቤ አምጥቼ ገመገምኩት። ሰፊ ልዩነት ነው ያለው። ይህም ሆኖ ጎንደሬ ኢትዮጵያ ትርታው ናት።
ሌላው በአብይዝም ካቢኔ ይሁን ከካቢኔ ውጭ ያሉ የአብይዝም ሹመኞች ጽኑ የሆነ አፍቅሮተ ህወሃት የሆኑ የኢህአዴግ ቤተኞች በቁልፍ የኃላፊነት ደረጃወች ስላሉ ስውር በቀል ጎንደር አይደርስባትም የሚል ዕምነት የለኝም። በትግሉ ውስጥም ያሉ ቢሆኑ ነገ ለጎንደር ምን ተስፋ ሊያመጡ ይችላሉ ሲባል ልሙጥ ነው።
ለዚህ ነው እኔ ጎንደር አስቦ ሊነሳ ይገባል፤ ከጭምቱ ደቡብም ሊማር ይገባል ያልኩት። ሁሉም ለጎንደር የተሻለ ዕድል አቅራቢ አይደለም። ግን ቢያንስ የተሻለውን ለመምረጥ አደብን መሰነቅ የሚያስፈልግ ይመስለኛል። የመደመር መንግሥትም የህወሃትን ትውልድ ያቀፈ ነው። የጥምዶ መንፈስም በህወሃት አውራነት የተንጠለጠለ ነገን ያሳናዳ ነው ????
በየትኛውም ዘመን ጎንደር የተገፋ ነው። ጎንደር ሲነሳ ጸጉራቸው የሚቆም ሰብዕናወች እንዳሉ አዳምጣለሁኝ። ከእነ ችግሮቿ ጎንደር ግን ክብሯ በተፈጠረበት ልኩ አለ እንዳለ። ወደፊትም ይቀጥላል። ስጦታው የላይኛው ስለሆነ።
እኔ ሳድግ መብራት እና ውሃ በኽረ ችግር ነበር። ዛሬም ቀጥሏል። ዘጠኝ ዓመት ብዙ ነው። ጥረት ቢደረግ የጣና እናት ጎንደር መብራቱም ይሁን ውሃው ጥማቱ እንዲህ አሳሯን አያሳዮዋትም ነበር።
ከአነስተኛ ግንባር ማሳያ ፕረጀክቶች ይልቅ ነፍስ ያለው ዘላቂ ችግር ፈቺ ፕሮጀክት የትውልድ ፕሮጀክት፤ ጥም አርኪ ፕሮጀክት ሠርቶ ማሳየት ያስፈልጋል። ማገዶነቱን በየዘመኑ ማካካሻ እንደማለት።
እኔ ሳድግ መብራት ስለለ ተማሪወች መንገድ መብራት ሥር ቁጭ ብለው ያጠኑ ነበር። ለሴቶች ስለማይፈቀድ ለተባዕት ግን የነበረው አማራጭ ውጭ በውርጭ እየተገረፋ ማጥናት።
ወፍጮ በ15 ቀን አንድ ጊዜ ነበር ዕድሉ። እህሉም ይጠፋል። ይሰረቃል። ውሃ ቀበሌ አንድ ብቻ ነበር የሚያገኜው። ከፍተኛ ሁለት፤ ከፍተኛ ሦስት፤ ከፍተኛ አራት መጥኒ ነበር። ውሃ ጥማትም ይሁን የመብራት ናፍቆትም በዚህ ልክ የ16ኛው መቶ ክ/ዘመን የኢትዮጵያ ርዕሰ መዲና ይቀጠቅጣታል።
አሁንም ቢሆን ለመስኖ የተባለው ነገ ምን እንደሚገጥመው አላውቅም። የመብራቱ ነገር ተንጠልጥሎ የቀረ ነው። መገጭ የርብ ዕጣ ፈንታ ወይንስ የአባይ ግድብ ዕጣ? ሂደት ይፍታው።
በጣም አሳሳቢው ነገር የጎንደር ብቁ ወጣቶች እየተገደሉ ነው። ይህ አሳሳቢ፤ እጅግ አሳሳቢ ችግርም እልባት ሊያገኝ ይገባል። ሊቃናቱ የጎንደር እየተመተሩ ነው።
ሌላው ግልገል መገጭ የሚባልም አለ። በመገጭ ፕሮጀክት ይጠቃለል አይጠቃለል አላውቅም። በበቅሎ ስሻገር ከላይ ሞልቶ ሳናየው ስለነበር ለመሻገር የሞከርነው የሞት አደጋ ገጥሞኝ ነበር። በጥበቡ ተረፈኩኝ። ተርፌም በነገረ መገጭ ጉዳይ ልጥፍ ቻልኩኝ። "አድርገኽልኛል እና አመሰግንኃለሁኝ።"
ሰላም የሁለት ወገን የተከባበረ ስምምነት ይጠይቃል። ሰላም ከሌለ አይደለም የመገጭ፤ የአባይ ግድብም አስተማማኝ ሁነት አይኖረውም። ሰላምን ለማምጣት ቁርጠኝነቱ ከልብ እና ከዕውነት ሊሆን ይገባል።
ህወሃትን ያህል ፈታኝ የዞግ ድርጅት የተካ ድርጅት በእጅጉ አደብ፤ በእጅጉ ለህዝብ ታማኝነት፤ በእጅጉ ህዝብን አክብሮ የመነሳት አቅም፤ በእጅጉ ኢትዮጵያዊነትን ያለማቅለል አቅም፤ በእጅጉ ዕውነት ሆኖ የመገኜት አቅም ያስፈልገዋል።
በሌላ በኩል አንዱን የውስጥ አድርጎ፤ ሌላውን በማግለል፤ አንዱን አቅርቦ ሌላውን በማራቅ የሚመጣ ሰላም አይኖርም። ሰሞኑን የተካሄዱ ሰላማዊ ሰልፎች አይቻቸዋለሁኝ።
የአማራ ህዝብ ፍጹም ኢትዮጵያዊነት እና መታመን በጠቅላይ ሚር አብይ ካቤኔ ይሁን ተቋማት በደህንነቱ፤ በጸጥታው፤ በጠቅላላ ተቋማዊ ሁነት በአክብሮት ይታይለታል ወይ? የሚበሳጩ ቁልፍ ኃላፊነት ላይ ያሉ ይኖራሉ።
ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ሲመጡ የባህርዳር ትዕይንት ለጠቅላዩ የውስጥ አልነበረም። ሌሎችን ነበር ያመሰገኑት። ለተፎካካሪወቻቸው ግን ቁርሾ ጠንስሶ ሌላ ችግር አቃጣይ ክብሪት ነበር። ለዛ ድንቅ ገራገር ድጋፍ ምን ተገኜበት ትናት፤ በዛሬውስ ነገ ምን ያስገኛል? ዓጤ ሂደት ይመልሰው። አሜን።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
24/10/2026.
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ