#ድንጋጤ ከእኛ ሲቀር #ምርቃት፦ ፡#ዊዝደምም ፦ይተናል። #ሰዋዊነት መጠጊያ ያጣል። #ተፈጥሯዊነት ይመንናል።
#ድንጋጤ ከእኛ ሲቀር #ምርቃት፦ ፡#ዊዝደምም ፦ይተናል። #ሰዋዊነት መጠጊያ ያጣል። #ተፈጥሯዊነት ይመንናል።
ለመሆኑ #ቅኑ ጎፋ እንዴት አደረ?
#ደጉ ጎፋ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል?
#ጭምቱ ጎፋ እንዴት እና እንዴት እዬሆነ ይሆን?
#አስተዋዩ ጎፋ በምን ሁኔታ ላይ ይሆን?
#ምራቁን የዋጠው ጎፋ እንደምን መሽቶ እዬነጋለት ይሆን?
#ርግብዬ ጎፋን እርግብዬ እመቤቴ ድንግልዬ እባክሽን???
እናንተስ ማህበረ ቅንነት እንዴት አደራችሁ? ለዚህ ነው እኔ ርህራሄ የነጠፈበት የኢትዮጵያ ፖለቲካን በሚመለከት ተፈጥሯዊ፤ ሰዋዊ #ቲም ከምንም ዓይነት የፖለቲካ ድርጅት ጋር ንክኪ የለለው፦ ከሳይለንት ማጆሪቲው ውስጥ የተውጣጣ #ሩህሩህ #አጽናኝ ኢትዮጵዬን ይምራት ብዬ እምሞግተው። ኢትዮጵያም ህዝቧም አጽናኝ፦ አይዟችሁ ባይ ልጅ ስለሚያስፈልጋት። የኢትዮጵያ ችግር ከአክቲቢስት፤ ከአንድ ጋዜጠኛ፤ ከአንድ ፀሐፊ፤ ከአንድ የፖለቲካ ድርጅት፤ ከተወሰኑ የሙሁራን ስብስብ በላይም ነው ብዬ እምሞግተው።
ለኢትዮጵያ ልኳ ያልሆነ #መጨካከን ነው ኢትዮጵያን እዬመራት የሚገኜው። ፋክክሩም የትኛው ጭካኔ ከዬትኛው ይበልጣል፤ ብዙ መወድስ ለማን ዘነበለት ነው። ጭካኔ ተመክሮ ሆኖ እዬተቀናበት? የመታመማችን ዓይነቱ ወዘተረፈ። ለዚህ እኮ ነው ጥቂት ሰባዕውያን ብርቃችን ድንቃችንም የሆኑት። መርዳት መራራት ማዘንም ያስወግዛል።
ተፎካካሪ፤ #ተጠማኝ፤ ተቀናቃኝ፤ ተዋህጂ፤ ተቃዋሚ የሚባለውም ከጭካኔ ጋር አልተፋታም። ወጉ ሙግቱ ሁሉም ነገር ክፋነት እና ጭካኔ። ውስጧን ህመሟን የመረዳት አቅም ነጥፏል። ኦሬንቴሽኑ ዘግናኝ ነው። ቀዳሚው ዝና እና ክብር፤፦ውዳሴ እና የተከታይ ብዛት ሆኗል። ይህ ድዌ ሁሉም ተጠቂ ሆኖበታል።
የምፃዕት - ዘመን።
የጭንቅ - ዘመን።
አስፈሪ - ዘመን።
ከደግነት ጋር የተራራቀ #አሳቻ ዘመን።
እኛነት በአረማዊነት የተወረረበተበት ዘመን።
ጭካኔ አጤ የሆነበት - ዘመን።
ሃዘኑ፦ ጭንቀቱ፦ መከፋቱ፦ መሰቃዬቱ ከውስጣችን ገብቶ #እንዲሞግተን የማንፈቅድበት ዘመን። እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሰምራ ይህ ታይቷት ይሆን እላለሁኝ ሰይጣንን እና አምላካችን፤ አላሃችን እርቅ እንዲፈጽሙ ከሰይጣን ጋር የጠዬቀችው። የተማፀነችው።
ለውጥ ተብዬው ብቅ ሲል ብርንዶ የጭካኔ የሆነው ነገረ ቡራዩ በሰው እጅ ማት ሲፈስበት፤ ዛሬ ደግሞ ጎፋ አባ ቅንዬ ደግሞ በተፈጥሮ እያዬ ያለው መከራ ደራሽ አጥቶ፤ በቅጡ #አጀንዳ መሆን ተስኖት የተፈጥሮው አደጋ "#ይበልኃ" ዓይነት፦ እግዚኦ ነው። ሙሉ ስድስት ዓመት በጦርነት የሚወርደው ማት የርግማን ነው። ችግር ያላስተማረ ምን ያስተምር?
መሪወቹ በዬለቱ ፋሽን ላይ ናቸው። የሜካፑ፤ የልብሱ፤ የመኪናው፤ የግብረ ሰላሙ ዓይነት የጉድ ነው። ሰርክ መዝናናት ግን አይሰለችም? ሰርክ በቅንጡ ሆቴል መዘባነን??? መልበስ፤ ማጌጥ ነውር አይደለም። ይገባል። ግን ሚሊዮን ደጅ አዳሪ፤ እራፊ ለማኝ፤ ቁራሽ ተመጽዋች ሆኖ? ቢኖር እንኳን ለዚህ ጊዜ የሚሆን ቅምጥ ሃብት በኖረ ነበር። የራስ ቤት እዬነደደ ሌላውን ጎረቤት አገር ማህበረ ሱዳናውያኑን ለማስታረቅ መንደፋደፍም ትዝብት ነው። #የውስጥን እሳት የሚያጠፋ #ትህትና ተሰደደ።
ፋክክሩ - ጭካኔ።
ጎልቶ መውጫም - ጭካኔ።
እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ፋክክሩም -- ጭካኔ። መሃከነ።
ሰሞኑን ብዙ መኪናወች አዬሁ። ለሠራዊቱ አቅም የሚፈጥሩ። ሌሎችንም ጉዳዮች ተመለከትኩ። ደቡብ የመሬት መንሸራተት ሁልጊዜ ይገጥመዋል። #አንቡላንሶች ቢሆኑ ምን ያህል የሰማይ ምርቃት በተገኜ ነበር። መጠለያ አልባ ለሆኑ ሚሊዮኖች መጠጊያ ማስሪያ ገንዘቡ ቢሆን ምን ያህል የእዮር ምርቃት በረበብን። ጦርነት አፍላሽ መሆኑ እዬታወቅ መሰናዶው ለዛ። ጥሩ ነገሩም ለዲታወች ዓይን ሰናይ በዓይነት ተሟልተው ይገነባል። #ትራፊ ገዝቶ ለሚያድረውስ?።። የራበው ህዝብ አስፓልት አይደለም የመጀመሪያ ጥያቄው። #እህል ውኃ ነው። የመኖር ዋስትና ነው። ዘንበል ብሎ የሚያደምጠው የመንግሥት አካል ነው የሚሻው።
ሚሊዮኖች ታቅዶ ይፈናቀላሉ። ሺወች ታቅዶ ይታሠራሉ፦ በመቶወች የሚቆጠሩት ታቅዶ ይታገታሉ፤ ሺወች በፍርኃት በተስፋ ማጣት ይሰደዳሉ። ቁጥሩ ያላነሱ ሴቶች ከፈቃዳቸው ውስጥ በኃይል ይደፈራሉ። ሰባዕዊ ቀውስ ኢትዮጵያን እዬናጣት ነው። ለዚህ ጥሞና ወስዶ ችግሩን ከሥር ለማስወገድ ጥረት የለም። በለት ደራሽ ጉዳይ ሁሉም ተጠምዶ ይደክማል። ሁልጊዜ ሰበር። ሰበሩ ቢዝነስ። ሰበሩ #ቋሚ የሥራ መስክ። ዘላቂም የመኖር #መጋቢ ሆነ።
የሚገርመኝ በበጋ እረፍት የሚንቆጠቆጠውም፦ ፈተናው ከውስጡ ሊወጣ ያልቻለውም እኩል??? ሙቱልኝም አለበት። የራሱን ቤተሰብ እያሸሸ ጀግና ሸተተኝም አለበት። ሞትህ አጀንዳ የፖለቲካ ሥልጣኑን ለቅንጡወች ተወው ባይም አለ። ህሊናም ተሰደደ። ይህ የራሳችን የውስጥ ገመናም ነው። እርማት ከራስ ከውስጥ ይጀመር እንደማለት።
አንጎልማ ድንቢጥም አላት። እኛ ህሊና የተሰጠን ከእነሱ እንለይ ዘንድ ነው። መላ የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድም በሌላም የችግሩ ተጠቂ ነው። ጥቁር ለባሽ ነው። የአገር ውስጥ ተፈናቃይ አስተናጋጅ ነው። ኑሮው ቋያ ነው። በዛ ላይ ስጋት፦ በዛ ላይ ጭንቀት፤ በዛ ላይ ወጥቶ መመለስ ጋዳ? በችግር ጠልቀን ችግር ውቅያኖስ ውስጥ ዋና ላይ። ክሽፈት። …… የሚታደግ የኖህ መርከብ??? ሰባዕዊነት ርህርህናን የተሸከመ ቲም ያስፈልገናል። በአንድ ካፒቴን ሳይሆን የወል ካፒቴን።
ሌላው ሥልጣን ላይ ያለው የጠቅላይ ሚር አብይ መንግሥት የፋሽን ሾውን ቢያስታግሰው እላለሁኝ። ደርግ ይህ እንዳይሆን ነበር ኢኒፎርም ያደረገው። ሰንበት እንኳን ሥራ ቦታ ሌላ ልብስ አይፈቀድም ነበር። የዘወትር ካኪ፤ የስብሰባም ካኪ። ግን ወሮ አዳነች አበቤ ስንት ቁም ሳጥን ይሆን ያላቸው? ሥልጣን ከያዙበት ጊዜ ጀምሮ ደግመው የለበሱት ልብስ አላዬሁምና። ሌሎችም እንዲሁ። #ዝምታዬ የሚበርድ ነገር ከኖረ ብዬ ነው። ግንስ መባስ ሆነ። #ይሉኝታ #የተመጠጠበት ሹማምንት ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው። አንስቶች ፖለቲካ ውስጥ አሉ። ግን???? ሰባዕዊነት አይጠመቅ ወይንም አይጨመቅ። ለሁሉ የተሰጠ ግን የተሸሸ።
ቀጣዩ ትውልድ አምቆ የያዘውን ካፈነዳው ሱናሜ ይሆናል። ሰሞኑን አንዲት ሳተና ወጣት ሀሌታ ላይ ቀርባ ነበር። ስለ ሴቶች ሞጋች ናት። በ2015 የሴቶች ንቅናቄ ከተነሳ ወዮልህ ወያኔ እል ነበር። ከሁለት የሀሌታ ጠያቄወች ጋር እዬተፋለመች አያለሁኝ። አቅሟ - አቅም እንዳይመስላችሁ። ወጣት ሳለሁ እኔ እንዲህ ነበርኩ። #ርህርሄው - አዛኝነት - አጽናኝነት - #አይዟችሁ ባይነት ይታከልበት ዘንድ ለወጣቶች አሳስባለሁኝ። ወጣትነቴን አመጣችብኝ። ልጅነት እና ኃላፊነት።
"እግዚአብሄር በአንድም በሌላም
ይናገራል፦ሰው ግን አያስተውለውም።"
እኔ ጭካኔን ማድመጥ አልሻም። የጭካኔ ነጋሪቶችን አላዳምጥም። ኢትዮጵያም በቃት። በቃት ጭካኔ። ሰበር የሚል ዜና፤ ዕርዕሱ በቀይ ከተፃፈም አላዳምጠውም። ትህትና የተነነበት መፎግላትንም አላዳምጥም። እርቃኑን የቆመ ቀረርቶ ነው።
ሆይ!
የሰማይ እና የምድር ጌታ ሆይ!
የሰማይ እና የምድር ንጉሥ ሆይ!
የሰማይ እና የምድር ልዑል አማኑኤል ሆይ! ለኢትዮጵያ የአይዟችሁ ዘመን ያምጣላት። አምጣላት እባክህን? አጽናኝ ሙሴም ስጣት? ድንግልዬም ትርዳን። አሜን።
ተስፋችን አምላካችን፦
ተስፋችን አላኃችን፤
የኔ ክብርች መሸቢያ ውሎ ቸር ያሰማን።
ቸር እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
27/07/202
"አቤቱ ይቀር በለን"
ምህረትህ ይቅረበን አሜን።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ