እስከ መቼ የአማራ እናት ማቅ ትልበስ? "በአማራ ክልል ሁለት ዞኖች በአንድ ቀን 20 የሚሆኑ ሰዎች መገደላቸውን ቤተሰቦች እና የዓይን እማኞች ተናገሩ" BBC

 

 https://www.bbc.com/amharic/articles/c05l75z6lnpo

 

"በአማራ ክልል ሁለት ዞኖች በአንድ ቀን 20 የሚሆኑ ሰዎች መገደላቸውን ቤተሰቦች እና የዓይን እማኞች ተናገሩ"

 የአለፋ ወረዳ ዋና ከተማ ሻሁራ፤ ጥቃት የተፈጸመበት አምቻሆ ቀበሌ 30 ሻሁራ 16 ኪ.ሜ ገደማ ይርቃል

"በአማራ ክልል ማዕከላዊ ጎንደር እና ምዕራብ ጎጃም ዞኖች "በመንግሥት ኃይሎች" በአንድ ቀን በተለያዩ ሰዓታት ውስጥ ተፈጸሙ በተባሉ ጥቃቶች 20 የሚሆኑ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን የተጎጂ ቤተሰቦች እና የዓይን እማኞች ለቢቢሲ ተናገሩ።

የጥምቀት በዓል በተከበረ በማግስቱ ሰኞ በማዕከላዊ ጎንደር፣ አለፋ ወረዳ እንዲሁም በምዕራብ ጎጃም፣ ቋሪት ወረዳ በዓል በሚያከብሩ እና በእርሻ መስክ ላይ ለከብቶች መኖ ሲሰበስቡ ነበሩ በተባሉ ሰዎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት ነው ግድያው የተፈጸመው።

በሁለቱም ዞኖች ውስጥ በአንድ ቀን የተፈጸመውን ጥቃት በተመለከተ ቢቢሲ የየአካባቢዎቹን ነዋሪዎች፣ የዓይን እማኞችን እና የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ቤተሰቦችን ያነጋገረ ሲሆን፣ የአካባቢዎቹ አስተዳዳሪዎችን ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

በክስተቱ ከተገደሉት ሰዎች መካከል አንድ ቄስ እና ታዳጊ ልጆች እንደሚገኙበት የተናገሩት የቢቢሲ ምንጮች ሁሉም ሰላማዊ ነዋሪዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ቢቢሲ ይህንን መረጃ ከገለልተኛ ወገኖች ማረጋገጥ አልቻለም።

በእነዚህ ሁለት ክስተቶች ተገድለዋል ከተባሉት ሃያ ያህል ሰዎች በተጨማሪ ሌሎች በርካት ያሉ ሰዎች በጥይት እና በድብደባ አካላዊ ጉዳት እንደደረሰባቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል

በተለያዩ የአማራ ክልል ክልል አካባቢዎች ከአንድ ዓመት በላይ በሆነው በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ ባለው ግጭት በሁለቱም ወገኖች በሚፈጸሙ ጥቃቶች በነዋሪዎች ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን የመብት ድርጅቶችን ጨምሮ በተለያዩ ወገኖች የሚወጡ ሪፖርቶች ያመለክታሉ።

ማዕከላዊ ጎንደር ዞን፣ አለፋ ወረዳ

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን አለፋ ወረዳ አምቻሆ ቀበሌ 30 በተባለ አነስተኛ ከተማ ሰኞ ጥር 12/2017 ዓ.ም. ነዋሪዎች "የመንግሥት ወታደሮች" ናቸው ያሏቸው ኃይሎች ሰዎችን ከቤት በማስወጣት እና መንገድ ላይ ግድያ መፈጸማቸውን ሁለት የዓይን እማኞች እና አንድ የሟች ቤተሰብ ገልፀዋል።

በዕለቱ ረፋድ 4፡30 አካባቢ የመንግሥት ኃይሎች ከወረዳው ዋና ከተማ ሻውራ ወደ ደልጊ እየተጓዙ ነበር ያሉት እማኞች፤ የአካባቢው ማኅበረሰብ ቃና ዘገሊላ በዓልን በማክበር ላይ ሳሉ ጥቃት ተፈጽሟል ብለዋል።

"ጥይት ሲጮህ ነው የሰማነው" በማለት ሁኔታውን የገለፁ አንድ የዓይን እማኝ፤ ከ100 በላይ ይሆናሉ ሲሉ የገመቷቸው የመንግሥት ኃይሎች በአካባቢው እንደነበሩ ተናግረዋል።

ጥቃቱን ሲፈፅም "ጥይቱ ፋታ የለውም። አንዱ ጊቢ ገብተን . . . ሕይወታችን ለማትረፍ ችለናል" በማለት እንዴት እንደተረፉ ተናግረዋል።

ተኩስ ሲከፈት በስፍራው ድንጋጤ እና መረበሽ መፈጠሩን የተናገሩት ነዋሪው ". . .ሰውም ተደነጋገጠ። ወደ ቤት የገባም አለ፤ ያልገባም አለ። እያባረሩ የገደሉትም፤ የመቱትም አለ፤ ከቤት እያወጡ እያናዘዙ. . . የገደሉት አለ" ብለዋል።

ወደ ዘጠነኛ ክፍል ያለፈ ልጃቸው እንደተገደለባቸው የተናሩ እና ለደኅንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዲጠቀስ ያፈቀዱ አባት ልጃቸው "ሥራ ቆይቶ ሲመጣ ነው ያለምንም ምክንያት የተገደለው" ሲሉ በምሬት ተናግረዋል።

"ተኩስ ፈነዳ። ምንድን ነው ብለን ተደበቅን። በኋላ ሲረጋጋ ብንወጣ [አስከሬን] ወድቆ አገኘን" ስሉ እማኝነታቸውን የተናገሩት የሟች አባት፤ አስከሬን ሲያነሱ "የአንተው ልጅም ወድቋል አሉኝ፤ እኔም ልጄን አነሳሁ" ሲሉ ልጃቸው ከሟቾች ውስጥ ይሆናል ብለው እንዳልጠረጠሩ ለበቢሲ ተናግረዋል።

ለጥቃቱ መንስኤ በአካባቢው የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጠው እና እግድ የተጣለበት ሞተር ሳይሆን እንደማይቀር ነዋሪዎች ጠርጥረዋል።

"'ሞተር ለምን ታንቀሳቅሳላችሁ? እዚህ ሞተር ካለ ፋኖ አለ' ብለው በዚህ ተበሳጭተው ነው ጨፍጭፈዋቸው የሄዱት" ሲሉ ለጥቃቱ ምክንያት የእንቅስቃሴ ክልከላ የተደረገበት የሞተር ትራንስፖርት ሳይሆን እንደማይቀር አንድ ነዋሪ ተናግረዋል።

ለክብረ በዓሉ ዘመድ ለመጠየቅ ወደ ከተማዋ በሞተር እየገቡ የነበሩ እና ከጥቃቱ ያመለጡ ሌላ የዓይን እማኝ "እኛ ላይ ተኩስ ጀመሩ። ሞተሩን፤ ሰዉንም ያገኙትን በሙሉ ነበር የሚመቱት" ሲሉ ስለ ጥቃቱ ቅፅበት ተናግረዋል።

እርሳቸው ሮጠው ሲያመልጡ ሞተሩን ሲያሽከረክር የነበረው ባለትዳር ጓደኛቸው ወዲያው መገደሉን የተናገሩት እማኙ፤ ሰባት ሠዎች መገደላቸውን እና ሌሎች ስድስት መቁሰላቸውን ለቢቢሲ ገልፀዋልባለሞተሩን እንደሚያውቁት እና ስለመገደሉም ማረጋገጫ የሰጡ ሌላ እማኝ፤ "በር እያስከፈቱ ነው [የገደሏቸው]፤ መንገድ ላይ የገደሉት ሞተረኛውን ብቻ ነው" ብለዋል።"አንዱ ልጁን ይዞ ወደ ጥምቀት ሊሄድ ሲል፤ ከልጁ ነጥለው ገደሉት። ሌላኛውም ልኳንዳ አራጅ ነው፤ ጠላ ቤት አግኝተው ነው የገደሉት። አንዱም የቀን ሥራ ነው የሚሠራው። ሁሉም ምንም የሌላቸው ደሆች ናቸው፤ . . . ንፁህ ሰው ነው የተጨፈጨፈው" ሲሉ ሌላ ነዋሪ ስለ ሟቾቹ ማንነት ተናግረዋል።

"ወርቅ ልጅ ነበር" ሲሉ ልጃቸውን የገለፁት የሟች አባት፤ ቢቢሲ ሲያገኛቸው ሠልስት (ሦስተኛው የሐዘን ቀን) ተቀምጠው የነበረ ሲሆን፣ ቃለ መጠይቁን እያለቀሱ መቀጠል አልቻሉም።

ከሟቾቹ ውስጥ ባለፈው ሳምንት ቀለበት ያሰረ ዘመዳቸው እንደሚገኝበት የተናገሩ ሌላ ነዋሪ፤ "ሁሉንም አውቃቸዋለሁ" ሲሉ ጥቃቱን "አሰቃቂ" ብለውታል።

አስከሬን ያነሱት የዓይን እማኙ ሰባት ሰዎች እንደተገደሉ ገልፀው፤ በማግስቱ ማክሰኞ ጡሩምባ ተነፍቶ የጠፉ ሰዎች ሲፈለጉ እንደነበር ጠቁመው፤ የሌላ አካባቢ ነዋሪ የሆኑ ተጨማሪ የሁለት ባል እና ሚስት አስከሬን መገኘቱን ገልፀዋል።

የሟቾቹ ቁጥር ዘጠኝ እንደሆነ የተናገሩት እማኙ አምስት ሰዎች በጥይት እና በድብደባ እንደቆሰሉም ተናግረዋል።

የመንግሥት ኃይሎች በ125 ሺህ ብር የገዙትን የእርሳቸውን ጨምሮ አምስት ሞተር ብስክሌቶችን አቃጥለው 13 ሞተሮችን ደግሞ መውሰዳቸውንም ተናግረዋል።

"ማንም የገጠማቸው የለም" ሲሉ በአካባቢው በመከላከያ እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ግጭት እንዳልነበረ የገለፁት ነዋሪው፤ "አንድም ፋኖ የለም። ከከተማችን ፋኖ፤ መከላከያ ሲመጣ አልፎ ነው የሚሄደው" በማለት የጥቃቱ ሰላባዎች ሰላማዊ ሰዎች እንደሆኑ ገልፀዋል።

የሟቾች ሥርዓተ ቀብር ማክሰኞ ጥር 13/ 2017 ዓ.ም. አምቻሆ መድኃኒያለም በተባለ ቤተ ክርስቲያን እንደተፈጸመ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።

"ስድስቱ አስከሬን አንድ ቤተ ክርስቲያን ነው የተቀበረው። ፍትሃትም በአንድ ነው" ያሉ አንድ ነዋሪ፣ ሟቾች በጅምላ መቀበራቸውን ገልፀው፤ "ተደርጎ የማይታወቅ" ነው ብለዋል።

"ለቅሶው በጣም አሳዛኝ ነው፤ አምስት አስከሬን አንድ ላይ ሲቀበር ሁሉም አንገቱን ነው የደፋው" ሲሉ የተናገሩት የሟች አባት፤ ከሟቾቹ ውስጥ ሦስቱ የባለቤታቸው ዘመዶች እንደሆኑም ጠቁመዋል።

ቢቢሲ ከነዋሪዎች እና ቤተሰቦች ባገኘው መረጃ በአምቻሆ ቀበሌ 30 የተገደሉ ናቸው በሚል የተመስገን መብራት፣ ጥጋቡ ታከለ፣ አይቼው፣ አዳነ ቢወጣ፣ ተገኘ ገበያው እና ነጋ ጎላ የተባሉ ሰዎችን ስም ያገኘ ሲሆን፣ ሌሎች ሁለት ሰዎች ከሌላ ቦታ መጥተው የተገደሉ እና ማንነታቸው ያልታወቀ እንዳሉም ተነግሯል።

በቋሪት ወረዳ በጥቃቱ የተገደሉ ሰዎች ቀብር
የምስሉ መግለጫ, በቋሪት ወረዳ በጥቃቱ የተገደሉ ሰዎች ቀብር

ምዕራብ ጎጃም ዞን፣ ቋሪት ወረዳ

በምዕራብ ጎጃም ዞን ቋሪት ወረዳ ሸባ በተባለ ቀበሌ በተመሳሳይ የከብት መኖ (ገለባ) እየሰበሰቡ የነበሩ 11 ሰዎች አውድማ ላይ መገደላቸውን ሦስት የዓይን እማኞች እና የተጎጂ ቤተሰብ ተናግረዋል።

ሰኞ ጥር 12/ 2017 ዓ.ም. ለማክሰኞ አጥቢያ ከሌሊቱ 7፡00 አካባቢ በጨረቃ ብርሃን መኖ እየሰበሰቡ የነበሩ ሰዎች በአካባቢው እያለፉ ነበር በተባሉ የመንግሥት ኃይሎች እንደተገደሉ ገልፀዋል።

የጥቃቱ ሰለባዎች የአራት ልጆች አባት እና 35 ዓመታቸው ነው የተባሉ አንድ የኃይማኖት አባት እና በአስራዎቹ አጋማሽ እና መጨረሻ የሚገኙ ታዳጊዎች መሆናቸውን እማኞች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጥቃቱ ሲፈፀም ሮጠው ማምለጣቸውን የተናገሩ አንድ የዓይን እማኝ፤ ከሟቾቹ ውስጥ የቤተሰቡ አራተኛ እና ብቸኛ ወንድ ልጅ የሆነ የ16 ዓመት የሆነ ቤተሰባቸው እንደሚገኝበት ለቢቢሲ አስረድተዋል።

"ገለባ በሕብረት ነው የምንሸከመው። ህፃናቱን ለማገዝ ሄደን ጨረቃ አልወጣልን ብላ እሷን ተቀምጠን ስንጠብቅ [መከላከያዎች] በአጋጣሚ መጡ። መጡና 'ምንድን ናችሁ?' አሉን። የከብት ገለባ እሰበሰብን ነው ስንላቸው ከበቡን። . . .ከዚያ 'ይህ ሁሉ ሰው ነው ገለባ የሚሰበስበው? በቀን እንጂ በጨለማ ነው ገለባ የሚሰበሰበው?'" በማለት እንደጠየቋቸው ተናግረዋል።

"የገብስ አጨዳ ደርሶብናል። ገለባውን ከብቱ ስለሚበላብን ብለን፤ [በማግስቱ ቀን] ለአጨዳ ለመመለስ ሌሊት ሄደን እናምጣት ብለን ነው" ሲሉ በሌሊት ወደ ሥራ ለምን እንዳቀኑ ተናግረዋል።

"ቄሱ መስቀሉን አውጥቶ ኧረ እባካችሁ ቢል፤ [መስቀሉን] ቢያነሳ ቢጥልም፤ 'ይመጣሉ ተብላችሁ [ነው]? እኛን ጠብቁ ተብላችሁ ነው?' እያሉ ሊሰሙን አልቻሉም" በማለት ለማስረዳት ያደረጉት ጥረት እንዳልተሳካላቸው እና ተኩስ እንደተከፈተባቸው ተናግረዋል።

ተኩሱ ሲከፈት እርሳቸው እና አንድ ሌላ ሰው ማምለጣቸውን የተናገሩት እማኙ፤ "ዝቅዝቅ ገደል አለ፤ በዚያ በኩል ነው የተንከባለልኩት" ሲሉ በድንጋጤ እንዴት እንዳመለጡ እና ሕይወታቸውን እንዳተረፉ ገልፀዋል።

"ጥይት ከመጠን በላይ ተተኮሰ። . . . ከታች [ገደል ውስጥ] ሆኜ ፈጅተዋቸው ሄዱ ብዬ ሳለቅስ ቆየሁ። እኔንም ይመቱኛል ብዬ ቀስ እያልኩ፤ እያዘገምኩ ሳዳምጥ ከሌላ ቦታ ሰው መጣ እና ጮኸ። ከዚያ ስሄድ አውድማው ላይ ሁሉንም፤ 11ዱንም ጥለውቻው [ገድለዋቸው] ሄደዋል" በማለት ምን እንደተፈጠረ አብራርተዋል።

ከባድ ድምፅ ሰምተው ከቤታቸው መውጣታውን የተናገሩ በአካባቢው የሚኖሩ ሌላ የዓይን እማኝ፤ የጥይት ድምፅ መሆኑን ሲያውቁ መሸሻታቸውን እና ከሰዓታት ቆይታ በኋላ ወደ ጥቃቱ ቦታ ማቅናታቸውን ተናግረዋል።

"ሰፈሩ እየተጯጯኸ፤ ሴቱ፤ ሁሉም [ከቤት] ወጣ። መጨረሻ ላይ ዳና እያዳመጥን፤ የጥይቱ ድምጽም እየራቀ እየራቀ ሲሄድ፤ ሄደን አስከሬኑን አነሳን። ሰው ሁሉ ተሰባሰበ" ሲሉ የነበረውን ሁኔታ የገለፁት እማኙ፤ "የአስከሬኑ ጉዳት በጣም ያሳዝናል። ህፃናት ናቸው። የተለያየ ቦታ ላይ ተመተዋል" በማለትም ስለጉዳቱ ተናግረዋል።

የጥቃቱ ሰለባዎች ግንባራቸውን ጨምሮ የተለያየ ቦታ ላይ በጥይት መመታታቸውን የተናገሩት ከጥቃቱ ያመለጡት እማኝ፤ "የቀራቸው ነገር የለም" ሲሉ ጥቃቱ "ርሸና" እንደሆነ ተናግረዋል።

ጥቃቱን የፈጸሙት የመንግሥት ኃይሎች ለመሆናቸው አካባቢው መተላለፊያ መሆኑን እና "መከላከያ" ወደ ቀበሌው መንቀሳቀሱን ከነዋሪዎች መረጃ በመስማታቸው እንዳረጋገጡ አንድ የተጎጂዎች ጎረቤት ገልፀዋል።

ከአንድ ቤተሰብ አራት ልጆችን ጨምሮ ሟቾቹ የሦስት ቤተሰብ አባላት እና "ቤተ ዘመድ" መሆናቸውን አንድ ነዋሪ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"እናቱ መሞት ብቻ ነው የቀራት። ሐዘኑ በጣም አማሯታል። 'የት አባቴ ልድረስ?' እያለች ነው። አንድ ፍሬ ወንድ ልጅ ያለው እሱ ብቻ ነበር። ሥራም የሚያግዘኝ እሱ ብቻ ነው። አንድ ልጄን አጣሁ። ከዚህ በኋላ ምን አለኝ? ብቻዬን ነው የቀረሁ። አጋዤን እንደዚህ አድርገውት ሄዱ" ሲሉ የቤተሰባቸውን ሐዘን ገልፀዋል።

የሟቾቹ ሥርዓተ ቀብር ማክሰኞ ጠዋት ጥር 13፤ 2017 ዓ.ም. ቄስ በላቸው አምባዬ በሚያገለግሉበት ሸባ ጊዮርጊስ በሁለት መቃብር እንደተፈፀመ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

"አዝመራ ለመሰብሰብ ሰው እየወጣ ከቀረ እንዴት እንኖራለን? ቀን ሲሄድ ከተገደለ፤ ሌሊት ሲገኝ ከተገደለ እንዴት ሆነን እንኖራለን? በጣም ተማረናል" ሲሉ አንድ ነዋሪ አክለዋል።

"በጣም አዝነናል። እንደዚህ ዓይነት [ጥቃት] አይተን አናውቅም። በጣም ነው የሚያስደነግጠው። በጣም ደንግጠናል፤ ተጨንቀናል" ሲሉ ማኅበረሰቡ ያለበትን ሁኔታ ገልፀዋል።

ቢቢሲ የደረሰው እና በገለልተኛነት ማረጋገጥ ያልቻለው ተንቀሳቃሽ ምስል ለቀስተኞች በርካታ አስከሬኖችን ከበው ሲያለቅሱ ያሳያል።

የጥር ወር ምርት የሚሰበሰብበት እና የሚዘራበት ወቅት እንደሆነ የጠቆሙ አንድ ነዋሪ፤ "ሰዓት የለንም" ሲሉ ሌሊት እና ቀን እንደሚሠሩ ተናግረው፤ ግድያውን ተከትሎ ግን ማኅበረሰቡ በስጋት ሥራ ማቆሙን ገልፀዋል።

"ሥራ ለመሥራት ጨንቆን ነው ያለው። [የአካባቢው ነዋሪ] እንኳን ለመሥራት ለመኖርም [ሰግቷል]። ዛሬ እንኳ አጨዳ የወጣ ሰው የለም" በማለት የአካባቢው ማኅበረሰብ መሸበሩን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቋሪት ወረዳ ፋኖ የሚንቀሳቀስበት ሲሆን፣ ጥቃት በተፈጸመበት ቀበሌ ግን የፋኖ ታጣቂዎች እንደሌሉ እና በአካባቢውም ምንም ዓይነት ግጭት በሁለቱ ኃይሎች መካከል እንዳልነበር ተናግረዋል።

ቢቢሲ ከነዋሪዎች እና ከሟች ቤተሰቦች ባለፉት ቀናት ያገኛቸውን መረጃዎች በማመሳከር በቋሪት ወረዳ ሸባ በተባለ አካባቢ ተገድለዋል ከተባሉት ሰዎች መካከል የተወሰኑትን ስም ዝርዝር ለመግኘት ችሏል።

በዚህም መሠረት ቄስ በላቸው አምባዬ፣ መላክ አምባዬ፣ አበባው ጋሻው፣ ያየህ ጋሻው፣ ደረጃው ጋሻው፣ ጊዜው ጋሻው፣ ተመስገን ገበያው፣ ዘመኑ ተሸራሽ፣ ላቃቸው ጎበዜ፣ ተስፋሁን አለሁበል እና አበበ በላይ ሲሆኑ፣ እነዚህ የመረጃ ምንጮቹ የሚያውቋቸው ሲሆኑ ተጨማሪ ሟቾች ሊኖሩ እንደሚችሉ ተናግረዋል።"

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።