የአማራ እናት ተስፋ በዬዘመኑ ለቃጠሎ።
የአማራ እናት ተስፋ በዬዘመኑ ለቃጠሎ።
"የቤትህ ቅናት በላኝ።"
የአማራ እናት ኢትዮጵያዊ አይደለችምን? የአማራ እናት ልጇን ልዑላዊነትህን አስከብር ብላ መርቃ፤ #ሰንቃ አላበረከተችምን? ነበረ በሚባለው የአገር ጉዳይ በግንባር ቀደምትነት ባትላ ያሳደገቻቸውን ልጆች ፈቅዳ አልሰጠችንም? የአድዋ፤ የጉንዲት፤ የመተማ፤ የካራማራ፤ የባድመ ጦርነቶች ላይ ማህፀኗን እማ ቅንዬ የአማራ እናት አልገበረችንም???
ስለምንድን ነው የአማራ እናት በዬዘመኑ መጣ ለሚባል ሥርዓት ሁሉ ተስፋዋ #ማገዶ የሚሆነው? ለምን? ትናንት ቢቢሲ የአማርኛው ዜና ባወጣው ዘገባ ጥምቀት ሙሽሪት ሲባልላት በመንግሥት ሚዲያ ሲሸበሸብላት የሰነበተችው ጎንደር እና በቅኔው ጎጃም በመንግሥት ታጣቂወች ከፍ ያለ ጉዳት ደርሷል ይላል ዘገባው። "አጥንት ውስጥ፤ ደም ውስጥ አለች" ለምትባል ኢትዮጵያ መጠኑ ያለፈ ግፍ እና መበደል ሰርክ የሚደርስበት የአማራ ልጅ የዳር ልጅ ስለሆኑ ይሆን የአማራ ልጆች እንዲህ በመታገት፤ በመሰወር፤ በባሩድ፤ በካቴና፤ በመገለል፤ በስጋት፤ በጭንቀት፤ በበቀል፤ በጥላቻ የአማራ እናት ማህፀን የሚቀጠቀጠው ስለምን ይሆን።
የማነሳው እጅግ መራራ ነገር ነው። ሂደቱ ጎምዛዛ እና ድቅድቅ በመሆኑ የእኔ ማህፀንም እርር ኩምትር እያለ ነው። በመተከል የተገደሉት ተገድለው የተረፋት የት እንደደረሱ አይታወቅም። በወለጋ በደንቢ ዶሎ ዩንቨርስቲ 17ቱ ታግተው አንዷ ተለቃ መረጃ ከሰጠች በኋላ ገራገሯ አስምራ ሹምዬ ተሰወረች፤ ከጓደኞቿ ጋር ትሁን ወይንም ተነጥላ? በህይወት ትኑር አትኑር የሰይጣን ጆሮ ይደፈንን እና የሚታወቅ ነገር የለም። ጄኒራል ብርኃኑ ጁላ ለንግግራቸው ቄንጥ ሲጠቀሙበት አዳምጫለሁኝ ክንውኑን እንደ ማዕረግ።
በህወሃት ዘመን በስሜን ሽዋ፤ በራያ፤ በወልቃይት ጠገዴ፤ በጠለምት፤ በአዳርቃይ፤ በማይጠምሪ፤ በመሃል አዲስ አበባ የአማራ ልጆች ሰፊ የሆነ የግድያ፤ የእገታ፤ የእስር፤ የመሰወር አደጋ ሲደርስ ያችው መከረኛ የአማራ እናት በማቅ #ተቀቅላ ዕንባ የለት አዳሯ ሆኖ ግን በፈቃደ እግዚአብሄር ህወሃት መንበሩን ለቀቀ። ከዛ በኋላስ???? የባሰ፤ የገዘፈ እንደ #እስስት ቀለማቱ በሚቀያዬር አዳዲስ የአረማዊነት ስልት አሁን የአማራ እናት ማህፀን #ቄራነት ተበዬነበት። እስከ መቼ ነው ይህ የሚቀጥለው? ይህ ግፍስ መቼ ይሆን የሚያቆመው????
ወጣት አክቲቢስት አቶ ጥበቡ ታደለ ለእኔ የፌቡ ጓደኛዬ ነው። ለቤታችንም አባል ነው። ፁሁፎቹ ጠፈፍ ያሉ፦ በቀደሙ የኢትዮጵያ ታሪክ ቀመስ ላይ አተኩሮ የሚታትር ሊቀ - ትጉኃን የነበረ ወጣት ነው። ፁሁፎቹን ተግቼ አነብ ነበር። ትናንት ሌሊት ሳነብ #መሰወሩን ሰማሁኝ። ቁጭ ብዬ አልቅሻለሁኝ። አልቅሻለሁኝ። አዝኛለሁኝ። ይህን የመሰለ ግርማ ሞገስ ያለው ሸበላ ወጣት የፈጠረ ማህፀን እና አብራክስ ምን ይሰማው ይሆን? እንደምንስ መሽቶ ይነጋላቸው ይሆን??? እኔን ከአንጀቴ ገብቶ እንዲህ ያንሰፈሰፈኝ። የአማራ ወጣቶች ተስፋ በእጅጉ ያሳስበኛል። የአማራ እናቶች እንባም ውስጤን ያባባዋል።
ቀደም ባለው ጊዜ በትጋት ድምጽ አልባ ለሆኑ የኢትዮጵያ እናቶች ሃዘን መቆሚያ ፍለጋ ስባትል ነበር። ታስታውሳላችሁ በነቀምት አቅራቢያ ወ/ሮ ታደሉ የሚባሉ እናት ልጃቸው ተገድሎ፤ #ከሬሳው ላይ #አስቀምጠው ደበደቡኝ በማለት ከቢኦኤ በኦሮምኛ ቃል - ምልልስ እንዳደረጉ፤ የሬቻ ጭፍጨፋ ማን ይፈጽመዋ ማን ያስፈጽመው ሰው የሆነ ሁሉ መከራውን መጋራት ይገባ ነበር። በጣም ተግቼበት ነበር። ምንም እንኳኳን የኦሮሞ ፖለቲከኞች #ይሉንታ ቢስ ቢሆንም። ከቅንጣቷ እስከ ገዘፈው መከራ በትጋት ሁለመናችን እኔን መሰል ሩህሩኃን ገብረናል። የቆሼ መከራንም …///
ስለሆነም ህወሃት መንበሩን ፈቅዶ ሲለቅ ደግሞ ከደስታ በላይ ሐሴት ነበረኝ። ለዚህም ነው ከለቀቀ በኋላ ዝምታዬ የጸናው። ከዚህ በላይ ከህወሃት የምጠብቀው የገዘፈ ጉዳይ ስላልነበረ። ስለሆነም ይህ እናቶችን የማሳዘን መከራ ይቆማል የሚል ሙሉ ተስፋ ነበረኝ። ብሶ ጭካኔው #ከርፍቶ ተገኜ እንጂ - በዘመነ አብይዝም። ሚዲያ ላይ የነገሡ አክቲቢስቶች እንደሚናገሩት አይደለም ለውጥ ተብዬው። መሰረታዊ በሆነ የእናቶቼ መከፋት ለስኬት የበቃ ተግባር ፈጽሜያለሁኝ። ውዳሴ ከንቱውም ሆነ ሽብሸባውን ስለማልሻ ነው -- ዝምታዬ።
በሌለኝ አቅም መኖሬን ሰላም ነስቼ፦ ቤተሰቦቼን አሳዝኜ ፈቃዳቸው ሳላሟላ የተጋሁት ግን ለኢትዮጵያ እናቶች ሰላማዊ የደህነት ዋስትና ሰላማዊ ኑሯቸው ነበር። የኢትዮጵያ እናቶች ዘመናይ አይደሉም። #ማቅ ለባሽ ናቸው። ጉልት ላይ ተስፋቸው የተመሰረተ ነው። የጥቂት ከያንያን ኑሮ መመቸት የአብዛኛውን የኢትዮጵያ ኑሮ ወካይ አይደለም። በዚያ ቅብጥ እና ቅልጥ የሚሉ ስላሉ። እሱን ማሽሞንሞን ተግባራቸው የሐሴታቸው መገኛ አድርገው የሚዩ ወገኖች አሉን።
በዚህ ሙሉ ስድስት አመት በሙሉ አቅም በአዳዲስ ውሃ ባልነኩ የፖለቲካ ሴራወች የበቀል ቅዬሳ ዒላማው #በአማራ #እናቶች ላይ ያተኮረ ነበር። የአማራ እናቶች ተጎድተዋል። የአማራ እናቶች መኖራቸው #ሰቀቀን እንዲሆን ተበይኖባቸዋል። የአማራ እናቶች ተስፋ ቢስ፤ ተስፋ ቆራጭ እንዲሆኑ እና በሥነ - ልቦና በሽታ እንዲጠቁ ተገምድሎባቸው። ወልደው መዳር፤ ወልደው ማስመረቅ፤ ወልደው የልጅ ልጃቸውን መሳም እዬራቃቸው ነው። ይህ የሁሉም ተፈጥሯዊ ሰብዕና በኽረ አጀንዳ ሊሆን ይገባል።
ወላጅ አልባ የአማራ ልጆች ሺወች ናቸው። ትምህርት ቤት የማይማሩ የአማራ ልጆች ሚሊዮኖች ናቸው። በስጋት ውስጥ ያሉ ሚሊዮኖች አማራወች ናቸው። በእናት አገራቸው ባይታዋርነት እንዲሰማቸው የሚደረገት ረቂቅ ሴራ ትብትብ ጥቃት ውስጥ ያሉት የአማራ ልጆች ናቸው። የአማራ እናቶች ተስፋቸው ተሰርዟል። መኖራቸው በግፍ ተቀምቷል። ሰላማቸው በስጋት ተውጧል። የት ይሂዱ ግፋአን የአማራ እናቶች? የት ይድረሱ ምንዱባኑ የአማራ ልጆች።
አክቲቢስት ፀሐፊ ወጣት #ታደለ ጥበቡ የት ነው? ወጣት #ገራገር የሰባዕዊ መብት ሞጋቿ አስምራ ሹምዬ የት ደረሰች? የደንቢደሎ ወጣቶች ምን ሁኔታ ላይ ናቸው? አስተዋሽ ያጡት #የመተከል ተሰዋሪወች አድራሻ የት ነው። ሰው ሲጠፋ መንግሥት የማይጨንቀው የፕሮጀክቱ ባልደረባ ስለሆነ ነው፤ እንጂማ መንግሥት ህዝብ አልባ ምኑ መንግሥት ሊባል ይችላል?
የአማራ ልጅ እጣ ፈንታ ታሞ ከሆስፒታል መመለስ የለም በዛው ይቀራል፤በእግሩ ወይ በመኪና ሄዶ ሆስፒታል እሬሳ ተረከቡ? ታስሮም ሬሳ ተረከቡ? ይህም መታደል ከተገኜ? ለቀብር ያልተፈቀደላቸው ፋኖ ናሆሰናይ እና አባሌዘርስ አሉ አይደል?
ምን ይሁን? ምን? ከከፋኝ ታጣቂወች በላይ መንግሥት መንግሥትነቱን የማረጋገጥ አቅሙ #ፍቅፍቅ ነው እኔ ሳስተውለው። መሻል የሌለበት። ከቤቱ ውስጥም ተኝቶ መነሳት ተናፋቂ ሆኗል ኢትዮጵያ ላይ። በአንዲት ቃል በቅሉ ቻሉኝ ነው። ያ ማመሃኛ "የስኳር በሽታ" ሆኗል። በዚህ መስመር ጥቃት የተፈፀመባቸው የአማራ እናቶችም አሉ። በጠንካራ ልጆቻቸው ምክንያት #ሰማዕትነትን የተቀበሉ። ጊዜ ራዲዮሎጂ ነውና፤ ለቀኑ ቀን ሲሰጠው ይወጣል። ይህ ግራጫማ ዘመን እንደ አካፋ አይቀርም። #ብራ ይመጣል።
ምክክሩ ንግግሩ እንደ እንሴክት የሚታዬው የሚታደነው የአማራ ሌጅ መከራ እንዴት ይቁም ሊባል ይገባል። ኢትዮጵያ ለአማራም እናት ከሆነች። "በደም እና በአጥንት የዘለቀ ፍቅር ከኖረ፦ ሱሱም ከሆነች። ልትፈርስም ስጋት ከሆነ" ደፍሮ አማራ አይፈጅ፤ አማራ አስምሌሽን አይፈፀምበት። አማራ አይሳደድ። አማራ አይገለል የሚል ድምጽ ጎልቶ ሊደመጥ ይገባል።
ገመናን ገላልጦ አፍረጥርጦ መነጋገር ካልተቻለ ነገም ድርቀት ነው። ድርቀቱ የአስተሳሰብ ነው። ለሰው ያልሆነ ዕውቀት ለማን ሊሆን ይችላል??? የተሰወሩ ልጆች ካለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ ማድረግ የአገራዊው ምክክር ኮሚሽን ቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል። ጭካኔን እና ጨካኝን በመንበሩ ይቀጥል ዘንድ ከማስታመም፤ ከማቆላመጥ ይልቅ።
የአማራ እናቶች እንባ እንደ ራሄል እንባ የፈጣሪውን፤ የአላህን ደጅ ያንኳኳል። ምላሹ ደግሞ የማያዳግም ይሆናል። ጠብቁት። ሊመከር ……ሊዘከር የሚገባው በሰው ተፈጥሮሊሆን ይገባል ከቁስ ይልቅ።
«በአማራ ክልል ሁለት ዞኖች በአንድ ቀን 20 የሚሆኑ ሰዎች መገደላቸውን ቤተሰቦች እና የዓይን እማኞች ተናገሩ»
ቸር አስበን፦ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
24/01/2025
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ