ትውልዳዊ ድርሻውን #በልቀት ላጠናቀቀ ሰብዕና "#በቃ" ለማለት ዘግይቷል መባል ይችላልን?
"የቤትህ ቅናት በላኝ።"
እንዴት ናችሁ ውዶቹ ውቦቹ?
ባለፈው ሳምንት አንከር ሚዲያ ከልጅ መስፍን አማን ጋር ውይይት አድርጓል። በእግረ መንገድ ይሁን ታቅዶ የቀድሞ ጠሚር አቶ ኃይለማርያም ደስአለኝ "በቃ" ለማለት ዘግይተዋል የሚል ጭብጥ ከጋዜጠኛ መሳይ መኮነን አዳመጥኩኝ። ከሳቸው በላይ የቀደመ በራስ ላይ የወሰነ እስኪ አንድ ሰው በዘመናችን ይነገረን ልጅ መሳይ መኮነን።
ለመሆኑ አብይዝም ሥልጣኑ ህጋዊ ይሆን ዘንድ የምርጫውን መንፈስ ያገዘ ማን ይሆን? ቁልፋ ጉዳይ እኮ ይህ ነው። እኔ ከርዮት ቴዲ ሚዲያ ውጪ በሙሉ የኢትዮጵያ ሚዲያወች ቀን ከሌት ነበር የደከሙት ምርጫው እንዲሳካ። ያ ትልቁ "#የመደመር" ስኬት ነበር። በዚህ አግባብ ማን ያልዘገዬ ኖሮ ነውና ትውልዳዊ ድርሻቸውን በልቅና የተወጡ ተምሳሌት ሰብዕና ያላቸው አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በመዝግዬት ሊጠዬቁ፤ ሊወቀሱ የሚችሉት?
ጎንደሮች ባለ ቅኔ ናቸው እና ሥራ ያጣ መነኩሴ የሚሉት አይነት ነው የሆነብኝ። እሳቸው እኮ ድርሻቸውን በብቃት የተወጡ #ጀግና ናቸው። ሥልጣናቸውን ፈቅደው እና ወደው እንዳሻችሁ አድርጉት ብለው የፈቀዱ፤ ህዝብ እንዲፀልይላቸው የጠዬቁ #ትሁት መሪ ናቸው። ለፓልቶክ #አድሚነት ጠበንጃ በሚያማዝዝ የኢትዮጵያ ፖለቲካ የአንድ አገር መሪነትን ተረከቡ ያሉ፤ #ጤናማ መንፈስ ያላቸው ልዩ ሰው ናቸው እኮ። ሥልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ ለለማውም፤ ለጠፋውም ምስጋናም ይሁን ተጠያቂነት ሁሉ ሲጠዬቅ ይጠየቁበት።
አንከር በሆነው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ግን ፍፁም ልዩ የሆነ #በራስ መተማመን ላይ የተገነባ፤ #ስስታምነት ያልጎበኛው፤ #ኢጎይስት ያልሆነ ሰብዕና ያላቸው መሆኑን ቁጭ አድርገው አስተምረውናል። ከእንግዲህ ላለው የኢትዮጵያ ችግር #ግዴታም በፍጹም የለባቸውም። የሳቸው ፈቅዶ ሥልጣን መልቀቅ ለስንት ሰው #የመኖር ድልዳል እንደፈጠረ፤ መንፈሱ ለሆነች ኢትዮጵያዊ ስደተኛ የሐሴት ዘመን የሸለሙ፤ ከቤተሰብ ጋር፤ #ከአፈሩ ጋር የተገናኜበት ዕድል የፈጠሩ፤ ለአቅመ ቢሱ ማህበረ ኦነግ ሠርግ እና መልስ የሆነለት ዘመን አማጭ ሰው ናቸው። በርካታ ሚዲያም ጋዜጠኝነትም ሽልማትም ዕድል እንዲቀናቸው ያደረጉ አዲስ ጎዳና ናቸው። ምንም እንኳን ለአማራ ህዝብ የምጣት ዘመን ቢሆንም፤ ለትግራይ - ለአፋር - ለአማራም ህዝብ መራራ ጊዜ ቢሆንም። "አዲስ አበቤ፤" ለወላይታ፤ ለገዲዮ፤ ለጋሞ፤ ለጉራጌ፤ ለአማሮ፤ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ብዙ የመከራ ዶፍ ቢወርድም።
የሆነ ሆኖ የተከበሩ አቶ ኃይለማርያም ደስአለኝ #ትውልዳዊ #ድርሻቸውን ሥልጣናቸውን ፈቅደው ስለለቀቁ፤ ግዴታቸውን በሚገባ በላቀ ሁኔታ ስለተወጡ በፍጹም በመዘግዬት #መወቀስ ሳይሆን፤ ከማንኛውም አለ ይባል የነበረውን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅት ሆነ ኢሊት በጣም በርቀት የቀደሙ #የብልህነት #ማራቶኒስት ዋርካም ናቸው - ለእኔ። በእኛ ቤት ደግ ላደረገ፤ ለልዩ ታሪካዊ ወቅት የተሰጠው ተግባር የፈፀመ #ጉልላት ሰብዕና አክብሮቱም ዕውቅናውም የለም። በትክክለኛ ጊዜ፤ በትክክለኛ የአዬር ጠባይ በጥንቃቄ ነበር የወሰኑት። በዚህ ብቻ አንቱ ሊባሉ ይገባል። ከዚህ በላይ ግዴታም የለባቸውም።
የ6 ዓመቱ የእርስ በርሱ ጦርነት፤ ቀውስ፤ ፍጅት፤ የስጋት ናዳ፦ ወንጀሉ፤ ጥላቻው፤ ጭካኔው፤ ስደቱ ረሃቡ እኮ ድውለቱ ይሁን ጥብሱ፤ ጥብሱ ይሁን ቅቅሉ #ሥልጣን ለኢትዮጵያ ፖለቲካ እና ፖለቲከኛ። አጤ ሥልጣን "#በቃኝ" በእኛ ፖለቲካ ህልም እልም ነው። ጀግናው አቶ ኃይለማርያም ደስአለኝ ግን ተረጋግተው፤ ደስ ብሏቸው ፈጽመውታል።
ለእኔ የተከበሩ የአቶ ኃይለማርያም ደስአለኝ እርምጃ #ብሄራዊ #ቀኔ ነው። ክብራቸውን፤ ዕውቅናቸውን፤ ዕድላቸውን ፈቅደው አስረከቡ እኮ። አዲስ ካሪክለም ነደፋ - በድርጊት። ስለሆነም በሆነ ባልሆነው በፍፁም ሊነሱ አይገባም። ከእንግዲህ ከሳቸው የሚጠበቅ #አንዳችም ነገር የለም። እንጥፍጣፊ፤ ቅርጥምጣሚ #የሚወቀሱበት ጉዳይ ሊኖር አይገባም።
ተቀዋሚ፤ ተፎካካሪ፤ ተስፈኛ የፖለቲካ ድርጅት ይሁን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሊቅ ሁሉም የቤት ሥራውን ቢሠራ ያን ጊዜ አፍሞልቶ የሚያናግር፤ ሙሉ ሊቀ - ትጉኃንን ያቀፈ፤ ያሳተፈ #ተረካቢ ይኖር ነበር። ልሙጥ ነው የነበረው። ልባም ብልህ ቢኖር ኖሮ ዝቅ ብሎም ብቻ ሳይሆን ተጣድፎ ከኢህአዴግ #ቅሪተ አካል ጥገኛ ሊያደርግ የሚችል ምንም ነገር አልነበረም።
በክት እና በዘወትር ልጅነት ሲታመስ የተፎካካሪው /// የተቃዋሚው ጎራ "#ሱሴ" ጭልፊቱ ላጥ። አሁንም ተደጋግሞ የማዳምጠው "አልቆለታል፤ ቢገፋት ይወድቃል፦" ይባላል የአብይዝም አገዛዝ። ይህን እንደሚሉት እንደ አፋቸው ቢሆን #ምንአለ? #ማንስ አለ? ኢትዮጵያን በተፈጥሮዋ ልክ አክብሮ እና አውቆ፤ አፍሪካን በምትፈልገው ልክ ሊመራ የሚችል ተቋም ቀርቶ የተደራጄ ሃሳብ አለን??????? ምን አለ????
ተፎካካሪ፤ ተቃዋሚ፤ ተጠማኝ፤ ተደማሪ፤ ተለጣፊ የሆነው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅት ከአንዱ ላይ ኢትዮጵያ ብትወድቅ ይችለዋልን? ስምምነቱስ አለን? በነገራችን ላይ የኢትዮጵያን የመንግሥት ለውጥ ህልም እንደ አፍ የሚቀል አይደለም። ያማ ቢሆን ክንውኑ የዛሬ ፲፭ ዓመት በቀና ነበር። ረቂቅ እና ጥልቅ ጥበብ ይጠይቃል።
ይልቅ እዛው ውስጥ መፈንቅል ቢኖር እንደምን መቆጣጠር፤ እንደምን ያ ባለቤት የሌለው ህዝብ መኖሩ ሳይስተጓጎል ሽግግር ማድረግ እንደሚቻል ያስጨንቀኛል። በተለይ እስር ቤት ያሉ ወገኖቼ፤ ሆስፒታል የሚገኙ ወገኖቼ ያሳስቡኛል። ስለሆነም እግዚአብሄር ጥበቃውን ያደርግ ዘንድ አዘውትሬ እለምነዋለሁ።
"ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይልቀቅ እንጂ ")እዳው ገብስ ነው" የሚባል ነገርም እሰማለሁኝ። ይህ አቅላይ ጉዞ ከባድ መከራ ያዘለ ይመስለኛል። በሌላ በኩል ጠሚር አብይ አህመድ አሊ ፈቅደው ካልሆነ በስተቀር ዓለም ሰምታው የማታውቀው አደጋ ኢትዮጵያ ይገጥማታል።
ጠሚር አብይ አህመድ አሊ ከፈቃዳቸው ውጪ ለሚሆን የስልጣን ሽግግር ጫን ተደል ቀውስ ቻሉት የማለት ሙሉ አቅም አላቸው። እሳቸው አሳቻ ናቸው። ይህን መቋቋም የሚችል የፖለቲካ ስልት እና ስትራቴጂ ደግሞ በተቃዋሚው ጎራ የለም። እንተዋወቃለን እኮ። የዘለቀ፤ የትውልድ የሆነ የኢትዮጵያኒዚም ባለሟል ድርጅት ኢትዮጵያ አላትን????
ለደራሽ ፈረሰኛ ሱናሜ የሚሆን የፖለቲካ አቅም እና አቋም ይልቅ ለወር የዘለቀ የሃሳብ ጽናት እና ውስጥነት በአንድነት እኔ በግሌ አላይም። ትጥቅ ያነሱ ከፋኝ ያሉ ወገኖች እንደ አሉ አውቃለሁኝ። ኢትዮጵያ እና ፍላጎቷ፤ ኢትዮጵያ እና ዲስፕሊኗ፦ ኢትዮጵያ እና ፓን አፍሪካኒዝም ኃላፊነቷን የሚመጥን አቅም በግብር ይውጣ፤ በድረስ ድረስ የሚሆን አይደለም። አገር መምራት የገብያ ውሎ አይደለም።
ይህ ሁሉ ሲታሰብ ነው የተከበሩ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እርምጃ ከአልማዝ በላይ የሚያበራው። እዛው ከውስጣቸው የሚወጣ ኃይል መኖሩ ባይረጋገጥ ኖር ዕድሉ ያመልጥ ነበር። በሁሉ ዘንድ ይሁንታ ያገኜ የፖለቲካ አቅም ወቅቱ ይጠይቅ ስለነበር። ነገም ይህው ነው። ማነው 120 ሚሊዮን ህዝብን ኃላፊነት እና ተጠያቂነትን አሟልቶ የሚገኝ የሚለው ጉልላታዊ የምእራቡ አለምም፤ የአውሮፓ ፖለቲካ ጥያቄ ነው። ለምን? ኢትዮጵያ ቀደምትነቷ ብቻ ሳይሆን ጂኦ ፖለቲካል አቀማመጧ ተፈላጊነቷን ተመስጥሮ ስለሚገኝ። በህዝብ ቁጥር ብቻም ሳይሆን የወጣቱ ቁጥር መብዛትም ሌላው የውሳኔ ወሳኝ ክስተት ነው። የእራሷም የኢትዮጵያ መንፈስ በተፈጥሮው ተፈሪም ተከባሪም ነው። እያንዳንዳችን እንመጥናታለን ወይ ብለን እራሳችን እንጠይቅ።
በብዕሬ የምታውቁኝ ውዶቼ ቀደም ባለው ጊዜ የተከበሩ አቶ ኃይለማርያም ደስአለኝን በቋሚነት ከሚሞግቱት አንዷ ነበርኩኝ። ለዛውም ከገረጭራጫው ህውሃት ጋር መስራት ዳጥ መሆኑን እያወቅኩኝ። ሥልጣናቸውን በፈቃዳቸው ከለቀቁበት ደቂቃ ጀምሮ ግን የበለጠ አከበርኳቸው። ሁልጊዜም ቸርነታቸው ይገርመኛል። የሥልጣን ትርምሱን አስተውላለሁ እና።
ስለሆነም ስለ የቀድሞው ጠሚር ኃይለማርያም ደስአለኝ ውሳኔያቸው ለልጆች ካሪክለም ውስጥ ገብቶ ሊማሩት ይገባል ባይ ነኝ። በደስታ ነበር የመፍትሄው አካል የሆኑት። እንደሚገባኝ ሴራ ፖለቲካ ውስጥም የነበሩ አይመስለኝም። ከ60ወቹ ፖለቲከኞች ያመለጡ ስለሆነ። ሥልጣናቸውን ከለቀቁም በኋላ አንጃ ፈጥረው የእናት አገራቸውን የኢትዮጵያ ሰላም አላወኩም። ምስጉን ናቸው።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን። ማለፊያ ሌሊት። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
29/01/2025
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ