"በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የሚፈጸም የንፁኃን ግድያ መባባሱን ኢሰመኮ አስታወቀ" ሪፖርተር።

 https://www.ethiopianreporter.com/137742/

 በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የሚፈጸም የንፁኃን ግድያ መባባሱን ኢሰመኮ አስታወቀ

ቀን:


"የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባወጣው የሩብ ዓመት ሪፖርት፣ በኢትዮጵያ በግጭት ዓውድ ውስጥ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ በአሳሳቢ ሁኔታ መጨመራቸውን ይፋ አደረገ፡፡ ከእነዚህ አሳሳቢ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ውስጥም ከሕግ ውጪ የሚፈጸሙ ግድያዎች (Extra Judicial Killing) እንደሚገኙበት የገለጸው ኢሰመኮ፣ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የሚደርሰው የሲቪሎች ሞት በአሳሳቢ ሁኔታ መባባሱን አስታውቋል፡፡

ሲቪሎችን ለሞትና ለአካል ጉዳት ከሚያጋልጡ ዕርምጃዎች በተጨማሪ፣ የዘፈቀደ ጅምላና የተራዘመ እስራት፣ የተፋጠነ የፍትሕ ዕጦት በኢትዮጵያ መበራከታቸውን ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡

አስገድዶ መሰወር፣ ዕገታና ያሉበት ቦታ ሳይታወቅ ሰዎችን አስሮ ማቆየትም በእጅጉ መስፋፋቱን ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡ የአገር ውስጥ መፈናቀል አለመቆሙን የሚገልጸው ሪፖርቱ፣ በዜጎች የመዘዋወር ነፃነት ላይ የተጣሉ ሕገወጥ ገደቦች በአንዳንድ ክልሎች አሉ ሲል አማራ ክልልን ጠቅሶታል፡፡

የዳኝነት ነፃነት መሸርሸሩን ጨምሮ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ከቀጠሉ የትጥቅ ግጭቶች ጨምሮ በአፋርና በሶማሌ ክልሎች መካከል በየጊዜው እስከሚያገረሹ ደም አፋሳሽ ግጭቶች ድረስ፣ በሩብ ዓመቱ ተከሰቱ ያላቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዘርዝሯል፡፡

በአማራ ክልል በፋኖ ኃይሎችና በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች መካከል የቀጠለው የትጥቅ ግጭት የብዙዎችን ሕይወት እየቀጠፈ ስለመሆኑ ባለ14 ገጹ ሪፖርት አመልክቷል፡፡ ከድሮን ድብደባዎች ጀምሮ በገጠርና በከተሞች በሚደረጉ የመሣሪያ ግጭቶች ብዙ ሲቪሎች መገደላቸውን ዘርዝሯል፡፡

በደቡብ ጎንደር ሊቦ ከመከም ወረዳ ከፋኖ ኃይሎች ጋር ውጊያ መደረጉን ተከትሎ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ቤት ለቤት በመሄድ በወሰዱት ዕርምጃ፣ አንዲት የዘጠኝ ወር ነፍሰ ጡርን ጨምሮ ሦስት ሴቶችና አንድ ሕፃን ተገድለዋል ይላል ሪፖርቱ፡፡

በምሥራቅ ጎጃም ከመስከረም አጋማሽ ጀምሮ 11 ሲቪሎች መገደላቸውን ይገልጻል፡፡ በመስከረም 8 ቀን 2017 ዓ.ም. በደቡብ ጎንደር ፎገራ ወረዳ አሥር ሰዎች ገድለዋል የተባሉት የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች፣ በመንገድ ላይ ሲያልፉ ያገኙትን መምህር አማረ ባይሌን ይዘውት እንደሄዱና ጫካው ውስጥ ተገድሎ ተጥሎ መገኘቱን ነዋሪዎች እንደመሰከሩ ከትቦታል፡፡

በመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች ብቻ ሳይሆን በፋኖ ታጣቂዎችም ግድያ መፈጸሙን ሪፖርቱ ከትቧል፡፡ መስከረም 8 ቀን 2017 ዓ.ም. ምሥራቅ ጎጃም ስናን ወረዳ መምህር ጌታ እንዳለና አትንኩት ሁነኛው የተባሉ መምህራን በፋኖ ታጣቂዎች መገደላቸውንም በሪፖርቱ ተካቷል፡፡

በኦሮሚያ ክልል እየተፈጸሙ ናቸው የሚላቸውን ከሕግ ውጪ ግድያዎች የተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎችን ገጠመኞች ከእነ ቀናቸውና ከእነ ስማቸው በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በስፋት እየተተገበረ ያለው የወቅታዊ ሁኔታ (ሃላ የሮ) የተባለው ዕርምጃ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ታጣቂ፣ አማፂ ወይም ደጋፊዎቻቸው ናቸው በሚሏቸው ላይ በስፋት እየፈጸሙት ነው ሲልም ገልጿል፡፡

በቄለም ወለጋ ጎጃ ወለል ወረዳ የላሎ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ዳግም ኢገዙና አቶ ፀጋ ተክሎ ከኦነግ ሸኔ ጋር ግንኙነት አላችሁ ተብለው በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ተገድለዋል ይላል፡፡ መስከረም 28 ቀን ዳግም በደቡብ ምሥራቅ ሸዋ ዞን አመያ ወረዳ በሦስት ቀበሌዎች አምስት ሲቪሎች መገደላቸውን ሪፖርቱ አክሏል፡፡

ጥቅምት 21 ቀን ደግሞ ምሥራቅ ሸዋ ዱግዳ ወረዳ ቢርቢርሳና ጋሌ ቀበሌዎች የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች መንግሥትን ተባብራችኋል ብለው፣ 17 ወንዶች 21 ሴቶች በድምሩ 38 ሲቪሎችን የገደሉ ሲሆን ወደ 78 ቤቶችን አቃጥለዋል ይላል፡፡

በኢትዮጵያ መንግሥት ከታጣቂ ኃይሎች ጋር በሚያደርገው የትጥቅ ግጭት የተነሳ በተለያዩ ክልሎች ሲቪሎች ለበርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተጋለጡ መሆናቸውን አረጋግጬያለሁ የሚለው ኢሰመኮ፣ ችግሮቹ ሰላማዊ የግጭት አፈታት መፍትሔ ይኑራቸው ሲል አሳስቧል፡፡"

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።