ሆድ ለባሰው #ማጭድ አታውሰው።" መቸኳኳል። #የመርገብገብ ፈተና።

 

ሆድ ለባሰው #ማጭድ አታውሰው።"
መቸኳኳል። #የመርገብገብ ፈተና።
ፈተናን #የማዳቀልና የማራባት ናፍቆተኝነት።
 
"እንደ ኃጢያታችን አላደረግብንም፤
እንደ በደላችንም አልከፈለንም።"
(መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ ፻፪ ቁጥር ፲)
 
ምዕራፍ ፳።
 
«የእነ ሌተናል ጄነራል ጻድቃን ምክር ቤት ከአሁን በኋላ "በተቋቋመበት አደረጃጀት" እንደማይቀጥል አስታወቀ»
 
"የቸኮለ አፍሶ ለቀመ።"
"የእነ ቶሎ ተሎ ቤት ግድግዳው ሰንበሌጥ።"
"ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ ይፈታል።"
"የቆጡን አውርድ ብላ የብብቷን ጣለች።" (የደፂን ህወሃት በትክክል ይገልፃል)
"የጅብ ችኩል ቀንድ ይነክሳል።"
 
እነኝህ የህሊና ቀዳሚ የመሰናዶ #አስተውሎቶች ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ማንነት ገላጭ ይመስሉኛል። ሁሉ ነገር ጥድፍድፍ፤ ሁሉም ነገር ችኩልኩል፤ ይልና አካባቢውን በወጀብ፤ በማዕበል፤ በጦሮ ንፋስ ይንጠዋል። ደጋፊ እና ተቃዋሚም እንቅልፍ አጥቶ አቅሙን በገፍ ይመግባል። ተስፋ አያልቅም እና።
 
ስክነት - ማጣት፤ እርጋታ ጋር አለመገናኜት፤ ማስተዋልን አለማድመጥ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሁልጊዜ ተፈታኝ ያደርገዋል። በፈተናው ውስጥ ማገዶ ይኖራል። #ማገዶ ደግሞ የሰው ልጅ ነው። መኖር፤ ሰላም ፦ እንደ አቅሚቲ ያለችው ሥልጣኔም ሁሉ አብሮ ይሾቃል። አንድ ፔና ያልገዛ ግን ሰውን ያቅዳል፤ ያጠምዳል፤ አንጋች ያደርጋል፤ መኖር ይቀራል።
 
የትግራይ የሰላም ኃይል እና ዘላቂነቱን በሚመለከት ያለኝን ስጋት ጥፌያለሁ ከዚህ ቀደም። ትናንት ባለ አደራ አስተዳደር መዋቀሩን ይፋ መረጃ ወጥቷል። አናርኪዝምን አጥብቄ ስለምፈራ ዜናውን በቸርነት ነው የተቀበልኩት። ጽፌበትማለሁኝ።
 
ከመተኛቴ በፊት የዓለም ዜናን በጨረፍታ የማየት ልማድ አለኝ። ልተኛ ስል ያገኜሁት ኢትዮጵያ ነክ ዜና የትግራይ የሰላም ኃይል ከ16/10/2026 ጀምሮ ሥራውን ማጠናቀቁ ይገልፃል። ቸኮለብኝ።
 
የአውሎ ንፋስ ያህል ነገሮች ተለዋወጡ። ገና ያረገረገ ሁኔታ ላይ ተሁኖ፤ መዋቅሩ እስከ ወረዳ በቅጡ ተደራጅቶ የእዝ ሰንሰለቱ መሠረት ሳይዝ፤ የትግራይ ህዝቡም የአፍታ እፎይታ ሳያገኝ እንደ ገና #የመርገብገብ ፈተና።
 
የሰላም ኃይሉ ከኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ጋር ሆኖ ህዝብን የማረጋጋት ተግባር ሲፈጽም እንደ ነበር በስፋት ሲዘገብ ነበር። ህዝቡም ልጆቹን ሲይ በተስፋ እንኳን ደህና መጣችሁልኝ ብሎ ስቆ ሲቀበል አይቻለሁኝ።
 
እርግጥ ነው የሰላም ኃይሉ ራያ ላይ የተቀባይነት ችግር እንደ ገጠመው አድምጫለሁኝ። ይህም ችኮላ ስለነበር ይመስለኛል። የራያ ህዝብ ተስፋ እና መከራ የተፈራረቀበት ህዝብ ስለሆነ ቀዳሚው ተግባር ህዝብን አግዞ ወደ መደበኛ ጢስ ጢንቢስ የተለመደው ኑሮው ማስገባት ሲገባ፤ ሌላ ግብግብ የተገባ አልነበረም። 
 
ከ50 - 70 ሺህ ተፈናቃይ ነበር በሰሞናቱ ጦርነት ብቻ። አላማጣ ላይ በነበረው የከተማ ውስጥ #ጨካኝ ውጊያም ብዙ ጉዳት ስለደረሰ ማጽናናት፤ አይዟችሁን ማስቀደም ይገባ ነበር። ቁርሾ ቀደመ ህዝቡ ከፋው። 
 
ምን አልባት ፌድራሉ የተጣደፈበት ምክንያት አንዱ ይህ ሊሆን ይችላል። ሌላው አቶ ጌታቸው እረዳም ከማዕከላዊ መንግሥትን ቀድመው የሰጡት አስተያዬት ያልተገባ እና የቸኮለ ነበር። 
 
ብዙ ጊዜ ዶር አብርኃም በላይ ይህን መሰል #ናጭ እና ላጭ ሃሳብ ያቀርባሉ፤ ወጀብ ይነሳል፤ ከዛ የተባለው ነገር ይቀር እና ሁሉ ነገር በነበረው መልክ ይቀጥላል። መረጃ #በማዕከል ብቻ ቢቀርብ ህዝብ ከመሸበር ይድናል። የመረባበሽ ዶፍ ነው ያለው አወዛጋቢ በሆኑ ቦታወች ላይ (በወልቃይት በጠገዴ በራያ በአዳርቃይ በጠለምት፤ በሰቲት በአዲረመጥ።) 
 
የትግራይ የሰላም ኃይል በትናንትናው ዕለት ተግባሩ መጠናቀቁ ሲገለጽ፤ ሆድ የባሰው መንፈስ ያስተጋባል። የአደራ አስተዳደሩ ላይ የጄኒራል ፃድቀን ፎቶ አላየሁም። ጉዳዩን ተመካክረው ይፈጽሙት፤ አይፈጽሙት፤ የቀደመ የውል #ሰነድ ይኑራቸው አይኖራቸው የሚታወቅ ነገር የለም። በዚህ መግለጫ ግን ፍንጭ አይቻለሁኝ። ፍንጩ መሰንጠቅን እንዳያመጣ ያሰጋል።
 
ሦስቱም አካላት እየተረዳዱ፤ እየተመካከሩ ፌድራሉ፤ የአደራው፤ የሰላም ኃይሉ ያረገረገውን የትግራይ ሁኔታ #ረብ እስኪል ድረስ በንጽህና፤ በእርጋታ፤ በአይዟችሁ ባይነት አብረው ሊሠሩ ይገባ ነበር። በተለይ ባለ አደራው መሠረቱ ጸንቶ ቀጣይ ተልዕኮውን እስኪያሳካ ድረስ ፍጹም የሆነ የተረጋጋ ሁነት በትግራይ ሊቃናት ሊኖር ይገባ ነበር።
 
ቀጣይ ተልዕኮው ግዙፍ ነው። የኮሪደር ጉዳይ አይደለም። የቅንጡ ሪዞልት ጉዳይ አይደለም። በማዕከላዊው መንግሥት የፖለቲካ ውክልና ነውና። #ምርጫ። በ2013/2018 ትግራይ ተሳትፎ ምንም ነው። በአገራዊ ምክክሩም ከፋም ለማም ውክልናው ስስ ነበር። የፈቀዱ 200 ፈቃደኞች በጎ ፈቃደኞች ተዳብለው ተሳትፈዋል። 
 
በሌላ በኩል በፓርላማ፤ በፌድሬሽን ምክር ቤት የትግራይ ንጥረ - አመክንዮ በትክክል ውክልና ማስገኜት አውራው ጉዳይ ነው - ለእኔ። ኢትዮጵያ ሊጎድልባት አይገባም ---- እና። 
 
ይህን ለማድረግ ደግሞ ህዝብን በመዋቅር ሳይሆን በመንፈስ #የማብቃት ተከታታይ ተግባር በትጋት ሊከወን ይገባ ነበር። የሰላም ኃይሉ፤ ፌድራሉ፤ ባለ አደራው አንድ ሆነው፤ ተረዳድተው እንኳን የትግራይን ማህበራዊ ሰላም መልሰው፤ ህዝቡ እፎይ የሚልበት ዕለት ማወጅ ከቻሉ ዕድለኝት ነው። አይደለም እንዲህ ግንጥልጥል ተብሎ። ህወሃት እኮ #ቤርሙዳ ትርያንግል ነው።
 
ሌላው ጄኒራል ፃድቃን ለጠቅላይ ሚ/ር ታጭተው ነበር። በአፍሪካ ብቁ መኮነን ተብለው ሲወደሱ ሰምቻለሁኝ። በነገራችን ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው በሳቸው ላይ እምጽፈው። በአማራ ህዝብ ላይ ያላቸውን አቋም ጠንቅቄ አውቃለሁኝ። 
 
በዘመነ ህወሃት የነበረውን የኃላፊነት እና ተጠያቂነትም ጉዳይ አውቃለሁኝ። በፌድራሉ እና በህወሃት በነበረውም ጦርነት የነበራቸውን ሚና ተከታትየዋለሁኝ።
 
ሁሉም እንደ በደሉ አንድ ቀን ይጠየቅበታል። የእኔ ዋናው ጉዳይ ዘላቂ ሰላምን ለትግራይ እናቶች ለማምጣት፤ ለጎረቤት አማራ ክልል እና አፋር ክልልም ጠንቅ የሆኑ ግብግቦችን ለማስታገስም፤ የትግራይ ጉዳይ በሰከነ ማስተዋል ሊታይ ይገባል የሚል ቅን ዕይታ ነው ያለኝ። 
 
ሌላው የአማራ ክልል የመንፈስ ህውከት አብዛህኛው የህወሃት የእጅ ሥራ ነው ብዬ የማምነው። ህወሃት ቤርሙዳ ትርያንግል ነውና።
ለሞላው ቀን ጥድፊያ አያስፈልግም። ሰክኖ፤ አስተውሎ፤ ተመካክሮ፤ አስቦ #ሃሳብን አደራጅቶ በንጹህ ህሊና ቅንነትን መግቦ ተግባር ላይ ለመገኜት መቻኮል አይገባም።
 
የሚያመልጡ አጋጣሚወች ይኖራሉ። የኢትዮኤርትራ ጉዳይን የመሰለ ፈጣጣ አመክንዮ ሲገጥም፤ ቆፍጣና ዓላማ እና ግብ ቀን ከሳታቸው ያልፋል፤ ዕድልም ይደፋል። የኢትዮኤርትራ ሊቃናት በተፋቀሩበት ጊዜ ብዙ ነገር በሆያ ሆዬ አምልጧል። እንደዛ ለማለት ነው።
 
አሁን መሬት ላይ ላለው የትግራይ ሁኔታ የሊቃናቱ ሃሳብ መሰበጣጠር ዘላቂ ሰላም አያመጣም። አንዱን አቅርቦ ሌላውን ማራቅ "ሆድ ለባሰው ማጭድ አታውሰው" ይሆናል። ህወሃታውያን ኢትዮጵያ 27 ዓመት የመሩ ናቸው። ኢትዮጵያን መምራት አፍሪካንም መምራት ነው። አሜሪካን መምራት ዓለምን መምራት እንደሆነው ሁሉ። ያ --- አለፈ። ተዚህ --- ተደረሰ። "የፈሰሰ ያልታፈሰ ሆነ።" ቁጭቱ እና እልሁ ግን በወበቅም ቢሆን አለ። ወርቅ ከቀለጠ ይፈሳል። ሲበቃ ያበቃል። 
 
/// ልባምነት መስዋዕትነትን መቀነስ።
/// አኩራፊን መቀነስ።
/// ጊዜን ማድመጥ።
 
ዕውቅና ሰጪን ማድንቅ ባይቻል፤ ማድመቅ ባይቻል ማከብር፤ ማረጋጋት ያስፈልጋል ባይ ነኝ። መሪነት ብዙ ወዘተ ፈተናወች አሉበት። ፈተናን #መፍጠር የመሪነት ኳሊቲ አይደለም። ፈተና እንዳይፈጠር ማድረግ፤ ፈተናን እንዳይዋለድ ማድረግ መሪነትን ይገልጣል።
#ፈተናን የማዳቀል፤ የማራባት፤ የማዋለድ ልማድ።
 
ህወሃት ግንዱ የኢትዮጵያ ፈተና ነው። 
 
የሰላም ኃይሉ ብዙ ፍርጃን አስተናግዶ፤ ቅራኔ ውስጥም ተማግዶ እንደ አማራ የጸጥታ ኃይል፤ እንዲህ እንደዋዛ ሲበተን ሌላ ፈተናን ያዋልዳል። ሌላ ችግር ጠሪ ይሆናል።
 
ሌ/ጄ ታደሰ ወረደ እና ቲማቸው፤ ደጋፊያቸው አዲስ ነገር እያዳመጥኩ ነው። በነገራችን ላይ ጄኒራል ታደሰ ወረደ እና አቶ ዳውድ ኢብሳ ይመሳሰሉብኛል። ሃሳባቸውን ለመግለጽ #ምጥ ናቸው። ስለ እሳቸውም ዛሬ ነው የፃፍኩት። ጽፌ አላውቅም። እሳቸውን እና አቶ ዳውድን ማዳመጥ ጭንቅ ነው። ጭንቅን ፈቅዶ መሸመት። ዜናን የሚወጥሩ በቁንጣን አንባብያንም አሉ። 
 
የሆነ ሆኖ መረጃ ተገኜባቸው ሲባል ሰምቻለሁኝ። መረጃውን ማዘግየት ሲቻል ለወ/ሮ ፈዲላ አባብያ ተሰጠ አዳረሱት። "የጅብ ችኩል ቀንድ ይነክሳል" የሚሉት አቨው ይህን ነው።
 
መረጃው በፌድራሉ መንግስት በጥብቅ #ሚስጢር መያዝ ነበረበት። በፍጹም በዚህ ወቅት መንፈስን የሚያሸፍት መረጃ ሊሰራጭ አይገባም ነበር። ግድፈት ነው ድክመትም ነው። የተመክሮ ማነስም። 
 
ተገኜ የተባለው ጹሑፍ ዕውነት ቢሆን እንኳን አደባባይ እንዳይወጣ ማዕቀብ ሊጣልበት ይገባ ነበር። ብልህነት ሾለከ። የሳቸው ደጋፊወች የብልፄው ደጋፊ ነበሩ። አሁን ግን ከሁለት ይተረተራሉ። ፈተናን ማዳቀል።
 
#መሸንሸን በስሱ።
 
ለአንድ ተልዕኮ እና ግብ ……
1) ቲም ዶር አብርኃም በላይ አለ።
2) ቲም ጌታቸውወፃድቃን ነበረ። (ወ የእኔ የአፃፃፍ ስታይሌ ነው የውራጅ አይደለም ለማወአብይ ደመቀ ወገዱ እያልኩ ስጽፍ ነበር)
3) ቲም ታደሰዚም አለ።
4) ቲም ባለ አደራው እየመጣ ነው።
5) ቲም #ደፂወኢሱ አለ።
6)ቲም ደፂን ብቻም የሚሹ ይኖራሉ።
7) ጥምዶ እና ቤተሰቡም አለ።
ጸረ ጥምዶ ህወሃታውያንም አሉ።
 
1.5 ሚሊዮን የትግራይ ህዝብ ደግሞ የዕለት እርዳታ ጠባቂ ነው። ቢያንስ ለመጠለያ፤ ለምግብ፤ ለከፈና ህዝብን አብቅቶ ከዚያ በኋላ ፖለቲከኞች ቢዥጎረጎሩ በሆነ። ጉሮሮ ማርጠቢያ ለሌለው ህዝብ ይህን ያህል በተበተነ ሃሳብ ህዝቡን ሰላም መንሳት አድራሻው ያሳስባል።
ይህን አረጋግቶ፤ አስክኖ ወደ ተፈጥሮው መመለስ ይገባ ነበር። የትግራይ ስፕሪት ረቂቅ ነው።
 
 በአግባቡ ቢያዝ፤ ወከባ ባይበዛበት፤ በራስ አቅም ቢሰክን ቅዱሱ ስፕሪት መድህን በሆነ ነበር። በአጤ ሚኒሊክ ጊዜ ችግር ተከስቶ እቴጌዋ ብልህነት የሰጣቸው ናቸው የተከበሩ ልዑካን ከድንግል ማርያም መንፈስ ጋር አድርገው ልከው አሳኩ። በዛን ወቅት መሬት ሲንቀጠቀጥ አበው አዳመጡ ይሁንታ ሰጡ። መጋቢት 18/2010 ተመሳሳይ የመሬት ንጠት በአቅራቢያ መከሰቱን ታሳቢ አድርጌ ለህወሃታውያን ጽፌ ነበር። አልሰሙም። 
 
ፋክክር፤ የበለጠ መመኜት ጤናማ ነው። ግን ጊዜን የማንበብ፤ የመተርጎም፤ የማመሳጠር አቅም ይጠይቃል። አማራ ክልልም በእነ ካፒቴን ማስረሻ የሚመራ መሰል ነገር ተመሰረተ ሲባል ሰምቻለሁኝ። ከትግራይ ሰላም ኃይል ሊማር ይገባዋል። ዕጣ ፈንታው ከአማራ ልዩ ኃይሉ ቢብስ እንጂ ይሻል ጉዳይ አይኖረውም።
 
ምን አልባት ይህ መሰል አወቃቀር ለክልሉ ተጨማሪ ልዩ አቅም ሊሆን የሚችለው ኦሮሚያ ላይ ሊሆን ይችላል። እሱበእሱ ስለሆነ። ከዚያ በተረፈ ግን ለገብያ ውሎ መሰዋት፤ ቅራኔ ውስጥ መማገድ የሚገባ አይመስለኝም።
  
እኔ በየለቱ ተፈጠረ፤ ተደራጄ በሚባል የብልጼ ይሁን የተቃዋሚ ተቋማት አቅም ላፈስ አልፈልግም። ሲፈጠሩ ስሜት ይፈጥራቸዋል። ልደታቸውን ሳያከብሩ የፈጠራቸው ስሜት እራሱ ያከስማቸዋል። 
 
የሰው ማገዶ በገፍ ተቀልበው መጨረሻቸው አይሆኑ ይሆናል። ስለሆነም አቅሜ የወንዝ ዳር አሽዋ ስላልሆነ፤ በዚህ ዙሪያ የሚባክን አቅም የለኝም። ፕሮፖጋንዳ ለእኔ ስለማያስፈልገኝም ትውር አልልም። ግን የሚያሳዝነኝ የወጣቶች ህይወት መኖርን ናፍቆ ሳይሳካለት እንደ ፋኖ ናሆሰናይ ሰማዕትነት ሲቀበሉ ነው።
 
የኢትዮጵያ የተቋማት ውጥን #ከደራሽ ከስሜታዊነት የሚወጣበት ዘመን ይናፍቀኛል። ለየትኛውም ስሜታዊ ቤተኛ አለመሆኔ፤ ቁጥብ መሆኔ ደግሞ ከደስታ በላይ ሐሤትን ይመግበኛል። "አድርገህልኛል እና አመሰግንኃለሁኝ።" አሜን።
 
ውዶቹ ክብሮቹ እንዴት ናችሁልኝ?
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
 
ኑሩልኝ። አሜን።
 
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
17/10/026.
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
========()==============
የBBC ዘገባ።
በእነ ሌተናል ጄነራል ጻድቃን ገብረተንሳይ የሚመራው እና በትግራይ ክልል የሽግግር ሂደቶችን ለማመቻቸት ሲንቀሳቀስ የነበረው "የትግራይ ሰላም እና ለውጥ ምክር ቤት" ከአሁን በኋላ "በተቋቋመበት አደረጃጀት" እንደማይቀጥል አስታወቀ።
ምክር ቤቱ የማይቀጥለው፣ ፌደራል መንግሥት በክልሉ ቀጣይ የሽግግር ተግባራትን የማከናወን ተግባርን "ራሱ ሊይዘው በመወሰኑ" እንደሆነ የምክር ቤቱ የሚዲያ እና ሕዝብ ግንኙነት አስተባባሪ ከበደ አሰፋ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ምክር ቤቱ፣ አሁን በትግራይ ክልል የሚታየው "ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ድል" እንዲገኝ የበኩሉን መወጣቱን ዛሬ አርብ ጥቅምት 6/2019 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስገንዝቧል።
ግንቦት 2018 ዓ.ም. የተመሠረተው ይህ ምክር ቤት ከህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የተለዩ እና የተቃረኑ ፖለቲከኞች እንዲሁም የትግራይ ፖለቲካ ፓርቲዎችን የያዘ ነበር።
የምክት ቤቱ አባል ከሆኑት ስምንት ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ ፓርቲ (ስምረት) ከምክር ቤቱ አባላት አንዱ ነው።
ከህወሓት በተለዩ አመራሮች የተመሠረተው ሌላኛው ፓርቲ ወለዶ ትግራይ እንዲሁም አረና ትግራይ ለዴሞክራሲ እና ሉዓላዊነት (አረና) እና ትንሳኤ ሰባ እንደርታ ፓርቲዎችም ይጠቀሳሉ።
ከፖለቲካ ፓርቲዎች በተጨማሪ "ከአስር በላይ የሲቪል ማኅበራት፣ የሚዲያ አካላት እና የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ተደራዳሪ ግለሰቦችም" የምክር ቤቱ አባል እንደነበሩ መግለጫው ያስረዳል።
በምክር ቤቱ ሥር የተቋቋሙ ኮሚቴዎችን የሚመሩት ሌተናል ጄነራል ጻድቃን ገብረተንሳይ ናቸው።
ይህ ሰላም እና ለውጥ ምክር ቤት እስካሁን ሲንቀሳቀስበት በነበረው አደረጃጀት እንደማይቀጥል ያሳወቀው፣ የፌደራል መንግሥት ዛሬ አርብ ጥቅምት 6/2019 ዓ.ም. ትግራይ ክልልን ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት የሚመራ ባለአደራ አስተዳደር ማቋቋሙን ካስታወቀ ከሰዓታት በኋላ ነው።
"በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት እስከሚቋቋም ድረስ" የሚቆየውን ይህ ባላአደራ አስተዳደር አራት ዋና አስፈጻሚዎች የተሾሙለት ሲሆን ለመቀለ ከተማ ከንቲባም ተሰይሟል።
የሰላም እና ለውጥ ምክር ቤቱ በዛሬው መግለጫው፣ "በተሠራው የተቀናጀ ሥራ፤ ወንጀለኛው የፖለቲካ እና ወታደራዊ ኃይል ከሥልጣን ተወግዶ" በፌደራል መንግሥት የባለ አደራ አስተደዳር ሹመት መሰጠቱን ጠቅሷል።
ምክር ቤቱን "ትግራይ ውስጥ የፖለቲካ ሥልጣን በኃይል ተቆጣጥሮ የነበረውን የወንጀለኞች ስብስብ በማጋለጥ፤ አሁን የተገኘው ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ድል እንዲገኝ የበኩላችንን ተወጥተናል" ብሏል።
በክልሉ "የሰላም፣ መረጋጋት እና ሽግግር ወቅቱ የተሳካ ይሆን ዘንድ በተናጠል እና በተደራጀ መንገድ" ድጋፍ እንደሚያደርግ የገለጸው ምክር ቤቱ የነበረበት አደረጃጀት ግን እንደማይቀጥል አስታውቋል።
ምክር ቤቱ እንደማይቀጥል ያወጀው፣ ፌደራል መንግሥት በክልሉ ቀጣይ የሽግግር ተግባራትን የማከናወን ተግባርን "ራሱን ሊዘይዘው በመወሰኑ" እንደሆነ የምክር ቤቱ የሚዲያ እና ሕዝብ ግንኙነት አስተባባሪ ከበደ አሰፋ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የሚዲያ እና ሕዝብ ግንኙነት አስተባባሪው "የሰላም እና የማረጋጋት እንዲሁም ጊዜያዊ አስተዳደር የማቋቋም ስራውን ፌደራል መንግሥት ራሱን ሊዘይዘው በመወሰኑ ምክንያት የዚህ ጊዜያዊ ስብስብ ቀጣይነት አላስፈላጊ ሆኖ ስለተገኘ ማብቃቱን ማወጅ [አስፈልጓል]" ብለዋል።
የምክር ቤቱ አባላት በቀጣይ በፌደራል መንግሥቱ የሚከናወኑ ተግባራትን "በየአደረጃጀታቸው በጋራም በተናጥልም እንደሚደግፌ" ከበደ አስረድተዋል።
ይህ አቋም በምክር ቤቱ መግለጫ ላይም ተጠቅሷል። መግለጫው "በተቋቋመበት አደረጃጀት የማይቀጥል ሲሆን" አባላቱም "የቆሙለት ዓላማና የራሳቸውን አሰራር ተጠቅመው ፤ የሃገሪቱ ሕግ በሚፈቅደው መሰረት ፤ ስራቸውን በየራሳቸው መንገድ የሚቀጥሉ ይሆናል" ሲል ቀጣይ እርምጃቸውን ምን እንደሚሆን አስረድቷል።
ትግራይ ክልል ከመስከረም አጋማሽ አንስቶ በፌደራል መንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ውጊያ እየተካሄደ ነው።
ከትግራይ ኃይሎች በወጡት ወታደራዊ አዛዦች የሚመራው የትግራይ ሠላም ኃይል ከፌደራል መንግሥት ጎን ተሰልፏል።
በእስካሁኑ ውጊያ መዲናዋ መቀለን ጨምሮ የተለያዩ የክልሉ ዋና ከተማዎች በፌደራል መንግሥት እና አጋሮቹ ቁጥጥር ስር ሆነዋል።»
See less

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።