የኢትዮጵያ ሊቃናት ይሁኑ ሊሂቃናት የማሰብ፤ የመናገር ነፃነታቸው ከተገደበ #አመክንዮ #ፎርምለስ ይሆናል።

 

የኢትዮጵያ ሊቃናት ይሁኑ ሊሂቃናት የማሰብ፤ የመናገር ነፃነታቸው ከተገደበ #አመክንዮ #ፎርምለስ ይሆናል።
 
ሁሉም የሚፈልገው ማስገበር ብቻ ነው።
"አንተ ምድር ነህና፤ እሷም ምድር ናትና፤
አንተ ትቢያ ነህና እሷም ትቢያ ናትና፤
አንተም መሬት ነህና፤ እሷም መሬት ናትና፤
ከእሷ የተገኜውን እህል ትመገባለህና
ወደ እሷም ትመለሳለህና፤ ያነሳህ ዘንድ እስኪወድ
ድረስ መሬት ትሆናለህና፤ የሠራኽውን ኃጢያት
እና በደሉንም ሁሉ ይመረምርሃልና።"
(መጽሐፈ መቃብያን ሣልስ ምዕራፍ ፭ ቁጥር ፫)
 
 
እንዴት ሰነበታችሁ ማህበረ - ቅንነት?
እኔ አምላኬ ክብሩ ይስፋ ደህና ነኝ።
 
ቢያንስ እኔ ላንሳው ብዬ እንጂ የኢትዮጵያ ሊሂቃን እንኳንስ ሃሳብ ሊያዋጡ፤ ይቅር እና በየዘመኑ መኖር በተፈቀደላቸው። ይህ ለረጅም ጊዜ በሰንሰለት የታሠረ ጉዳይ ነው። ዊዝደም ከታሠረ ድፍን ፷ ዓመታቱ ነው። 
 
የኢትዮጵያ ሊሂቃን እራስ እግራቸው ዊዝደም ናቸው። ጸጋቸው፤ በረከታቸው ከባችለር፤ ከማስተር፤ ከዶክትሬት ዲግሪ አይቀዳም። ከእዮር እንጂ። አልፎ አልፎ አስኳላየን አክለው ሲገኙ ደግሞ እራሳቸው #ፕላኔት ሊሆኑ ይችላሉ። 
 
የሆነ ሆኖ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዳጡ ይሁን ረግረጉ ይኽው ይመስለኛል። አንዱን ይዞ ሌላውን አንጠልጥሎ ስለሚሆን። የኢትዮጵያ ሊሂቃን አገር - ያበጁ፤ ፊደል - ቀርጸው ዕውቀትን መልክ ያሳያዙ፤ ቀለም ሠርተው ጥበብን አቆላምጠው ለኢትዮጵያ ስልታዊ ትንፋሽ መርኽ የሆኑ፤ ሥልጣኔን አበክረው መኖርን ያዘመኑ ናቸው።
 
ሳይንሱ፤ ፍልስፍናው፤ ምርምሩ ምጡቅ ዕይታው ጸጋውን ከባረከላቸው፤ ከሰጣቸው ይቀዳል። ግን ከኢትዮጵያ ፖለቲካ የተገለሉ ብቻ ሳይሆን #ተሳዳጅ በመሆናቸው በፈጣሪ ኃይል ምንጠራውን፤ ግለቱን፤ ጫናውን ተቋቁመው አሉ። ሰማዕትነትን የተቀበሉ፤ እየተቀበሉም የሚገኙ አሉ።
 
በተለይ የማንነት ቀውስ በማይለየው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሊሂቃናት ቢዋከቡም፤ እንዲጠፋ ቢበየንባቸውም፤ እንዲጠናቀቁ ቢታደምባቸውም፤ በወል ቢዶለትባቸውም ግን አሉ። በርከታቸው ይድረሰኝ። አሜን።
 
ዛሬ ኃያላን ሆነው ከወጡት አገሮች ቻይና፤ ራሽያ፤ ጃፓን የሥልጣኔ አንባ ከናቁት፤ ከአገለሉት #ቀዳማይ ስልጣኔ ጋር ይቅርታ ጠይቀው፤ ምህረት ለምነው፤ ወደ ቀልባቸው መመለስን ስክነት በማድረጋቸው ምክንያት በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ተፎካካሪ፤ ተደማጬ አገር ለመሆን ችለዋል። ኢትዮጵያ ግን ………????
 
በአስኳላው ሊቃናት በኩልም ቢሆን በየዘመኑ ከሥልጣን ምኞት ጋር በተያያዘ ወግነው ካልተገኙ በስተቀር የወጀብ ጠቀራ አሳራቸውን ያሳያቸዋል። ፍደኛ ናቸው። መጠጊያ ያሳጧቸዋል።
 
ኢትዮጵያ ስንት ወጪ አውጥታ ያስተማረቻቸው ሊቃናቱ በየዘመኑ በጅምላ - ሲረሸኑ፤ በጅምላ - ሲፈረጁ፤ በጅምላ - ሲሳደዱ፤ በጅምላ - ሲዋከቡ፤ በጅምላ - ሲታሰሩ በየዘመኑ #ሰማዕትነትን ተቀብለዋል። 
 
ዛሬም የሚታየው ይኽው ነው። ምረጥ ነው የሚባሉት በአንድ ወገን እንጂ በሁላችንም አይደለም። ወይ ይሄኛውን ወይ ያኛውን የመሆን ግዴታም ባልተፃፈ ህግ ተደንግጎባቸዋል። 
 
አንዱን ካልመረጡ በማዕበል ፈጣሪወች እንግልትት ሲሉ ይታያሉ። መገለሉ አልበቃ ብሎ ሲቃለሉ፤ ሲጣጣሉ፤ ቁሙ - ተቀመጡ ተብለው አሳራቸውን እንዲዩ ይደረጋል።
 
ሊቃናቱ - ልቅናቸውን ለማግኘት ባደረጉት የግል ጥረት፤ በልፋታቸው ውስጥ አንዲት #ደቂቃ በስጦታ ያላበረከተ ሰብዕና አገልጋይ፤ አቋም አራማጅ፤ ጉንብስ ቀና ባይ ሆነው እንዲገኙ ይፈለጋል። ድፍረቱ ይገርመኛል አሻቅቦ ሲናገራቸው። እነሱ በቀየሱት ፕላን ካልተካተቱ ወይንም ካልተገኙ እነሱን አያድርገኝ ነው። 
 
የአካዳሚ ነፃነት በተሰደዱበት አገር ያገኛሉ። ግን እናቴን፤ አገሬን ብለው ዕውቀታቸውን ለማጋራት ሲያቀኑ ያለባቸው ወጀብ፤ የሚገጥማቸው ወከባ እጅግ መራራ ገጠመኝ፤ አሳዛኝ ትዕይንትም ነው። 
 
የኢትዮጵያ ሊቀ ሊቃውንታት፤ ከአንዱ ቋያ ወጥተው ወደ ሌላው እስቲ ቢለም ሌላ #ላርባ ተጥዶ ይጠብቃቸዋል። የአገሬ ዓራት - ዓይናማ አንቱወች እንግልትት ብለዋል። ፕሮፌሽናል ሚዲያ በህብረት ማቋቋም ስለምን እንዳልቻሉ ይገርመኛል።
 
በነጮች በሰለጠኑት አገሮች፤ ሃሳባቸውም በሰለጠነው አገሮች ለተወሰነች #ደቂቃ ዩንቨርስቲ ሄደው ልምዳቸውን ለማጋራት ተከብረው፤ ትህትናን - ተመግበው፤ ተከፍሏቸው፤ ዕውቀት - ተመክሮ - ክህሎት - ለራበው - ለጠማው - ትውልድ ክህሎታቸውን ይመግቡ ዘንድ ይለፍ ይሰጣቸዋል። ለአንዲት አርቲክልም አያሌ #ባውንድ ያገኛሉ ከምስጋና ጋር - በፋጹም ትህትና ጋር።
 
እኛስ???? ---------/////-------? ኢትዮጵያ የከበደችን ለሁላችንም ነው። 
 
#ገለልተኛ ሚዲያ ስለማስፈለጉ።
 
ኢትዮጵያ እኔ እማውቃት - ኢትዮጵያ፤
እኔ የደረስኩባት - ኢትዮጵያ፤
እኔ ያያኋት ኢትዮጵያ #ገለልተኛ ሚዲያ የሚባል የላትም። አይፈቀድምም። 
 
የተከለከለ መንገድ ነው። ስለሆነም ሊቃናት ይሁኑ ሊሂቃን ዕውቀታቸውን፤ ልምዳቸውን፤ ተመክሯቸውን፤ ብልህነታቸውን የሚያጋሩበት ነፃ መድረክ ልሙጥ ነው። 
 
ለዚህም ነው በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ስንት ቁም ነገር የሠሩ ኢትዮጵውያን በዝምታ ውስጥ የሚገኙት። ኢትዮጵያን ቁም ነገር የማድረግ የወል የነጠረ አሰባሳቢ ሃሳብ እጥረት የገጠመንም። የወል ነው ያልኩት። አገርን ቁምነገር ለማድረግ የወል ንጥር አመክንዮ ግድ ይላል። ተጫኝ የሌለበት። የግል ሰብዕና ፋክክርም ትውር የማይልበት። 
 
ሁሉም - ነገር፤
ሁሉም - ኩነት፤
የትኛውም - አቅጣጫ፤
የትኛውም የህይወት ዘርፍ ከፖለቲካ ጋር በአንድም በሌላም ይገናኛል። 
 
ይህን መዝኖ በማስተዋል ለየዘርፋ ጠቃሚ የህሊና መኖ ለማቅረብ ፈጽሞ አልተቻለም። የሰው ልጅ በምግብ እና በመጠጥ ብቻ አይኖርምና። ማረፊያ #ርጉ ዋርካ ይመኛል። ካላገኜ ጊዜም - ሂደትም - አደራም - ታሪክም - ዕድሜም - ይባክናል። #ብክነት ስኬት አይደለም።
 
ሁሉም የሚዲያ ፎርማት አንዱን የመወገን ግዴታ አለበት። ይህ ማለት አዕምሮህን ሸልመኝ ነው። አንተ ቀለም እንደ ሌለው ስክርቢቶ ሁን #ኮድህን፤ ፓስወርድህን ግን ለእኔ ስጠኝ፤ እኔ እንዳሻኝ ልሾፍረው ነው ምኞቱም ግቡም። ድፍረቱ ይገርመኛል።
 
ሊቅ - ሆኖ፤ ከሊቅነትም - አልፎ ሊቀ ሊቃውንት ሆኖ፤ በምርምር ተግባር ላይ ስኩን የዕውቀት ባለቤት ሆኖ፤ እንደምን #በቀፎ ለመኖር አንድ ሰው ሊፈቅድ ይችላል? ስግብግነትም ነው። ስስታምነትም ነው አንድ ሰው የራሱ ህሊና እያለው፤ ህሊናህን አውሰኝ አይደለም #አውርሰኝ ሲባል። ጎምዛዛ ገጠመኝ ነው።
 
ስለሆነም ለትውልድ የሚያስብ ቅን ዜጋ ቢገኝ፤ የኢትዮጵያ ሊቃናት፤ የኢትዮጵያ ሊሂቃን የሚያስጎመጀውን ተመክሯቸውን፤ የማይጠገበውን ብልህነታቸውን ያጋሩ ዘነድ #ነፃ እና ገለልተኛ ሚዲያ በእጅጉ ያስፈልጋቸዋል። ኢትዮጵያ የላትም።
 
ስለላትም ኢትዮጵያዊ ትውልድ አማራጭ አዳጊ ሃሳቦችን፤ አማራጭ ብልህ ዕይታወችን፤ አማራጭ ዕውቀት ዘለቅ ትንበያወችን የሚያገኝበት መድረክ #ልሙጥ ሆኗል። ያስፈራል።
 
ይህም ብቻ ሳይሆን ወጣት ሙሁራን የጎልማሳ፤ የአዛውንት ተመክሮ ግርፊያ፤ ግልምጫ ስለሚበዛበት ፈለጉን ለመከተል የሥነ - ልቡና ጫና እንደሚገጥማቸው እያስተዋልኩ ነው። ይህ ደግሞ ነገ ከመምጣቱ በፊት ክው ብሎ ይደርቃል። ትውልዳዊ ድርሻም ለመወጣት መስመሩ መዘጋጋቱ አደጋ ላይ ኢትዮጵያ እንዳለች አመላካች ነው።
 
ይህ ደግሞ የኢትዮጵያን ፖለቲካ አመክኒያዊ #ፎርምለስ፤ ቅጥ አልቦሽ ያደርገዋል። ቢያንስ ውጭ አገር ሊቃናት ይሁኑ ሊሂቃን ሃሳባቸውን፤ ዕይታቸውን ካለ ፍጥጫ፤ ካለ እርግጫ፤ ካለግልምጫ - በትህትና፤ በፍጹም - ቅንነት፤ በፍጹም አክብሮት የሚያቀርቡበት ፎርማት ሊኖር ይገባል።
 
ጤናማ - የሆነ። አካሉ ያላነከሰ የሚዲያ ፎርማት በእጅጉ ያስፈልጋል። ወጀብ የማይንጠው። ማዕበል የማያጥለቀልቀው። ለማንም ለምንም ያላደረ። ለማንም ለምንም የማይወግን። ነፃ ፍጹም ነፃ ሚዲያ በእጅጉ ያስፈልጋል። ብዙ ሚዲያወች "ገለልተኛ፤ ያልወገነ" የሚል መግቢያ አላቸው። ግን ዕውነት አይደለም። ሁሉም ደንበር አለው። ሁሉም ወሰን አለው።
 
በዚህ ጎርበጥባጣ፤ በዚህ - የጓጎለ፤ በዚህ አባጣ እና ጎባጣ ገጠመኝ ትውልዱን በዕውነት ማህለቅ፤ በፋክት፤ በአደራ ማህለቅ ለነገ ሰው ሰውነት ለመቅረጽ ፈታኝ ገጠመኝ ነው። አሳሳቢም ነው። አሳሳቢነቱ #ኦክስጅን ከማጣት እኩል መሆኑ ይታየኛል።
 
#ወላዊ ልሳነወርቅ - እንደ መቋጫ።
 
መቋጫዬ ተጀምሮ እስኪጨረስ አድማ፤ ውግንና፤ ግልምጫን፤ ወከባ፤ ዘለፋ ሳይኖር እምናደምጠው #ሞጋች ሚዲያ የኢትዮጵያ ሊቀ - ሊቃውንት ያለ አድሎ፤ እንዲሁም ሊሂቃነ - ዊዘደሞችን በልዩ አክብሮት የሚያስተናግድ የተደራጄ፤ #ጦሮ የማይንጠው፤ ያገኜ ማማስያ የማያነኩረው፤ በራሱ ስለራሱ የቆመ፤ ተጠሪነቱ ለዕውቀት እና ለዊዝደም የሆነ አይበገሬ ሚዲያ ማቋቋም ያስፈልጋል ባይ ነኝ። አገር ቤት አይቻልም። ውጭ አገር ግን ይቻላል።
 
የደጋፊ፤ የተከታይ ብዛት ቢኖር ጥሩ ነው። ባይኖርም #ጥራት ስኬትን ስለሚያዋልድ፤ ነገን የሚያበራ ልዩ ማሾ የመሆን አቅሙ ዓራት ዓይናማ የመሆን አቅም ይኖረዋል። ትውልድን ለመቅረጽ ቅንነትን ቀለም ማድረግ በራሱ ብዙ ዥንጉርጉር ፍላጎቶችን የመግራት አቅም ያበቅላል፤ ያቀብላልም። ቅንነትን የሰነቀ ሊሆን ይገባል እያልኩኝ ነው። 
 
ይህ ማለት የግለሰብ - ሃሳብ፤ የግለሰብ - የማሰብ ነፃነት፤ የግለሰብ #የመተንበይ ነፃነት፤ የልምድ የተመክሮ ነፃነት፤ የዊዝደም የብልህነት ነፃነት ፍሰት በቅናዊ፤ ሰዋዊ፤ ተፈጥሯዊ ፍሰት የታወጀለት መድረክ ያስፈልጋል - እንደ ማለት። 
 
ታላላቆች - በዕድሜ፤
ታላላቆች - በዕውቀት፤
ታላላቆች - በክህሎት፤
ታላላቆች በሃሳብ የአወቃቀር እና አደረጃጀት ጥራት እና ብቃት፤ ከብረው የሚያስከብሩበት አንደበት #ልሳነወርቅ ያስፈልጋል። የሰሞኑ ሁኔታ ክፍተቱን አሳይቶናል። ለዚህ ነው እኔ ኢትዮጵያ የከበደችን ለሁላችንም ነው የምለው። 
 
በቅድሚያ ግን ሁሉም የጥሞና ጊዜ ቢኖረው ምርጫዬ ነው። ሲወጠንም፤ ሲደራጅም። ሲመራም ሲካሄድም ጥሞና ናልኝ ሊባል ይገባል ባይ ነው። ከጥሞና ውጪ ውድቀትን ነው አጭቶ የሚጸነሰው። አየሩ እራሱ እየተወራጬ ስለሆነ - ስክነትን ምራኝ ማለት በእጅጉ ያስፈልጋል። ከመጨመት እና ከጥንቃቄ ትርፍ እንጂ ኪሳራ የለምና።
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
 
ኑሩልኝ። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
22/10/2026.
 
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ሂደት ገመናን ገላጭ ነው።


አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።