#አለልን እንደምን እንበል?

 

#አለልን እንደምን እንበል?
ግን ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የት ይሆን ያለው?
 
"ጥበብ ከቀይ ዕንቁ ትበልጣለችና
የከበረ ነገር ሁሉ አይተካከላትም።"
 
 
እንደምን አደርን ሁላችንም? በዓታችንም?
 
#እፍታ ለአንድ አፍታ።
 
«#የሽብርተኝነትን ድርጊት ለመፈፀም ማቀድ፤ መዘጋጀትና ማነሳሳት።»
 
1) ይህ የምታዩት የክስ ምክንያት አቶ ዮናታል ተስፋዬ ረገሳ በዘመነ ህውሃት የታሠረበት የክስ ጭብጥ ነው። ወጣቱ የድል አጥቢያ አርበኛ አይደለም። ታግሏል፤ አታግሏልም። 
 
2) ለነፃነት ተጋድሎ ከደረሰበት ዕድሜው ጀምሮ ትጋት ያለው ተግባር የፈፀመ ወጣት ነው። አልፎ አልፎ ያልተገባ ሃሳብ ስለምመለከት ነው፤ ተከሳሽም፤ ታሳሪም እንደ ነበር ለማጠየቅ ነው የተከሰሰበትን ጭብጥ ማስቀደም የፈለግሁት።
 
3) ሌላው ፎቶወቹ ናቸው። ፎቶወቹ ትናንት በምን ዓይነት ብሄራዊ ፍልስፍና ውስጥ መንፈሱ የተሰናዳ እንደ ነበር ይገልፃል። በሌላ በኩል ቁልፍ ቦታ በነበረው የሰማያዊ ፓርቲም ከወጣት እህት እና ወንድሞቹ ጋር አብሮ የደከመ፤ የተንገላታ፤ የበኩልን ድርሻ የተወጣ ብቻ ሳይሆን የመራም ስለመሆኑ ያመላክታል። ዝም ብሎ ከመሬት የተነሳ እና አጋጣሚ ሰጥቶት ሹመት ያገኜ አለመሆኑን በማስተዋል መመርመር ይገባል።
 
ወጣቶች የዘመናቸውን ታሪክ የማወቅ፤ በሂደቱም ውስጥ የነበራቸውን ድርሻ ተገኝቶም ይሁን አልተገኝቶም ዕድሜያቸውን ያበረከቱበት የተሳትፎ ሁነትን በአጽህኖት ሊዘግቡት፤ ሊማሩበት ይገባል ባይ ነኝ። በየዘመኑ በወጣቶች የመኖር #ማገዶነት፤ የዕድሜ ግብር ውስጥ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ማዳበሪያ መሆኑን በጥልቀት ሊገነዘቡት ይገባል። ለዕፍታ ይህን ካልኩ ቀጣዩን ንዑስ ዕርስ ላስለጥቅ እንዲህ ……
 
የእኔ ዕይታ የትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ተቃዋሚ፤ ተመጋጋቢ፤ #ተቀላች፤ ተፎካካሪ ይሁን የሚታገለው ለፖለቲካ ሥልጣን ነው። በየትኛውም ሂደት የፖለቲካ ሥልጣን ዕድል ሲገኝ መድፋት ይገባል ብዬ አላምንም።
 
ምክንያቱም በፋክክር ውስጥ ጫና አለ፤ እንደ ኢትዮጵያ ባለ አገር ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሥርዓት አይታሰብም። ስለሆነም ጫናው ዕድሜን #አንሳፎ ከአንዱም ሳያደርስ፤ ልምድም፤ ተመክሮም፤ ችሎታም፤ ክህሎትም ፈሶ ሊቀር ይችላል። ከእንግልቱ ባሻገር።
 
እንግልቱ ካልቀረ ዕድልን ልሞክረው ማለት ይገባል። በተለይ በመንበረ - መንግሥት ውስጥ የመሥራት ዕድል የሰብዕናን #ተቋማዊነትን ያበራክታል። #መታዘዝ እና ማዘዝን ያሳውቃል። 
 
ኃላፊነት እና ተጠያቂነትን ሙሉዑ ባይሆን በደርበቡ ያስገኛል። ልዩ የሆነ የልምድ ተመክሮን ይሰጣል። እኔ ስላየሁት፤ ስለኖርኩበት ነው። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል እርካታ የለሽ ነው። በሰው ማገዶነት ተፈጥሮ፤ በሰው ማገዶነት ትርታውን አስቀጣይም ነው።
 
የሆነ ሆኖ የወጣት ጊዜዬን ብተላለፈውም ግን በአገሬ ጉዳይ ቁመናዬን ቀለም የሰጠው፤ እርግጠኛ - ያደረገው፤ የመንፈስ እርካታን ያጎናጸፈው፤ አነሰም አደገም ምን አደረኩ ለሚለው መልስ የሚሰጠኝ ያ ጊዜዬ ነው።
 
ዕድል ቀንቶ እጅግ የማይገኙ ብቁ ሊቀ - ሊቃውንታት ጋር የ@መስራት አጋጣሚ ከተገኜ የመዋዕል ዕድሜ #ጣዕምን ይቀርፃል። ከዚህ አንፃር በብልፄው ዘመን በችሮታም ይሁን በልግስና የተገኜውን ዕድል መጠቀም ከዕድሜ ብክነት ስለሚታደግ በአወንታዊ የማዬው ገጠመኝ ነው። አወንታዊ ጥያቄ ውስጥ የሚገባው ለታገሉለት ዓላማ ተሿሚወች ተቃርኖ ላይ ሲገኙ ነው። አሁን ይህ አመክንዮ ወደ ዋና በኽረ ዕርሴ ይወስደናል።
 
#አለልን እንደምን እንበል? 
 
በትግል ውስጥ የነበሩ ወገኖቼ ዕድል ሲያገኙ ኢትዮጵያ የጎደለባትን ታሟላ ዘንድ አቅም ይሆኗታል። እኛ ባንኖርም እነሱ የእኛን ውስጥ ውስጣቸው ያደርጋሉ ብዬ ስለማምን ነው ዕድሉን በአወንታዊነት የምመለከተው።
 
ስለሆነም በመናገር - በመፃፍ - በመደራጀት - በሃሳብ ማፍለቅ - በሰብዓዊ መብት አፈፃጸም በህፃናት፤ በሴቶች፤ በሃይማኖት ነፃነት ላይ ከእኛ በተሻለ ዕድሉ ስላለ ዋቢ ይሆናሉ ብዬ አስብ ነበር።
 
ወንድም አቶ ዮናታል ተስፋዬ የተመደበበት ቦታ ዘለግ ላለው የትግላችን ራዕይ ወሳኝ ቦታ ነው። የታሠረበት፤ በክፋ ዓይን የታዬበት፤ የተገፋበት ለዚህው ነበር። እንዲህ እራሱ የታገለለትን ዓላማ ተጭኖ፤ ተቃርኖ ሲቆም አዘንኩኝ። እሱ ታሥሮ ሳለ ቀን ከሌት ከሚተጉት ወገኖቼ አንዷ እኔ ነበርኩኝ። ብዕርና ብራናዬ ሁሉም ቦታ አቤቱታውን ተግቶ ያቀርብ ነበር። የመደመጥም አቅም ነበረው።
 
ያ የመደመጥ አቅም ቀን በእኩሌታ ይሁን በርቦ አግኝቶ ያን የወል ልፋት እና ድካም ሲታገል ማየት ማሕጸንን እንደ ዱባ #የሚቀረድድ ገጠመኝ ነው። አሁን ላሉ የፖለቲካ እስረኞችም በሚደረገው ትጋት ላይም በእጅጉ ተጽዕኖ ያሳድራል። በዘርፋ #አለልን የምንለው #የራሳችን የእኛው መንፈስ እኛኑ ብቻ ሳይሆን የራሱን መገለጫ ሰብዕና ሲታገል #ከርቤ ነው ለእኔ።
 
ይህን ስል አገር ቤት ያሉ ለብልፄው ቅርብ የፖለቲካ ድርጅቶች የተሰጣቸው የኃላፊነት ቦታ ችሮታ መሆኑን አውቃለሁኝ። የችሮታ ወንበር ምህንድስና የሰጪውን ዓላማ እና ተግባር ለማስፈጸም መሆኑ ጠፍቶኝ አይደለም።
 
ነገር ግን አንድ ሰው ደንበር ሊኖረው ይገባል። እራሱን ሙሉለሙሉ #አውልቆ መስጠት ፈጽሞ አይገባም። መደራደሪያ በኽረ ጉዳይ ሊኖር ይገባል። ልምዱ ተመክሮው የሚጸድቀው መቋሚያው #ዕውነት እና መርህ ሲሆን ነው።
 
#በመተንፈስ ጉዳይ ድርድር ሊኖር አይገባም። እሱ ከተዘጋ ቀጣዩ #ዲዳ ዘመን ወይንም መውቲ ዘመን ይሆናል። በራስ መድረክ፤ በራስ ስልጣን ላይ ይህን መፍረድ ብልሃት የሌለው ቅላት ይሆናል።
 
#ሚዲያ የኖኽ መርከብ ነው።
 
የሪፖርተር ጋዜጣ ከህትምት ውጪ መሆን የገዘፈ ኢ - ሰባዊ ውሳኔ ነው። ሚዲያወች #የኖህ መርከቦች ናቸው። ትውልድን ከትውልድ የሚያሸጋግሩ ካፒቴኖች ናቸው።
 
የትኛውም የክህሎት ዓይነት መነሻው ጥበብ ነው። የጥበብ አስኳል ደግሞ ማሰብ ነው። ማሰብ የሚገለጸው ደግሞ በመፃፍ፤ በመሳል ነው። ተውኔት ይሁን ማንኛውም የፈጠራ ሥራ ከሥነ ጹሁፍ ይቀዳል። ሥነ ጹሁፍ ፏፏቴ ነው። በየትኛውም ዕውቀት መማርም መመረቅም ፕሮፋሽናል ሳይንቲስት፤ ፈላስፋ፤ ኤክስፐርት በተፃፈ የዕውቀት ዘርፍ ነው። ይህን መቅጣት ማለት ጥበብን #ማነቅ ነው።
 
ጥበብ አልቦሽ ጉዞ ደግሞ #ዳፍንታም ነው። ዳፍንትነት የዐዕምሮ #ድፍንነት ያመጣል። የዕዕምሮ ድፍንነት ኋላቀርነትን ያመጣል። ኋላቀርነት ለእኔ የኢኮኖሚ አለመመጣጠን ብቻ ሳይሆን የሃሳብ ድህነትንም ያካትታል።
 
በኢኮኖሚ ኋላቀር መሆናችን አልበቃ ብሎ በሥልጡኑ፤ በሊሂቀ ሊቃውንቱ በጥበቡ ዘርፍ የሃሳብ፤ የምልከታ፤ የምርምር ዳፍንትነትን መናፈቅ ድውይነት ነው። ልታመም ብሎ መፍቀድ፤ ልቅር የኋሊት ብሎ መፍረድ የተስፋ ግብዓተመሬት ይሆናል። በሥነ - ጹሁፍ ውስጥ ንድፍ አለ። ትልም አለ። ምህንድስና አለ። ግብ አለ። ሥልጣኔ አለ። ይህን ከርችሞ ነገን ማሰብ ዕብንነት ነው።
 
ከወዘተረፈ ደጋፊ ሚዲያ አንድ ሞጋች ሚዲያ በብዙ ሁኔታ ለመንግሥት፤ ለህዝብ፤ ለአደራ፤ ለትውፊት፤ ለትውልድ ካሪክለም ነው። መዳንን - ያድናል። የጎበጠ - ያቃናል። የሻከረን - ልጎ መስመር ያስያዛል። ይህ ካልተፈቀደ ትውልድ ልሙጥ ይሆናል። ፈሪ፤ እርግጠኛ ያልሆነ፤ በራሱ መተማመን ያቃተው ይሆናል --- ነገ። ይህ ሊፈቀድ ፈጽሞ አይገባም።
 
ነገን ስለሚያስር ----- ኩፍትርትር አድርጎ ስለሚያሳርርም። ከነገ በስቲያን የጨለማ አቀባበል ስለሚያደርግ። አንድ ወጣት የየትኛውም ድርጅት ይሁን ተቋም፤ መሪ ከእሱ ካለበት ዘመን የተሻለ ትውልድ ለመፍጠር ሊተጋ ይገባል። በስተቀር መፈጠሩን ሊጠይቅ ይገባል። የኋሊት የሚወስድ ጎድጓዳ ጉዞ እንጦርጦስ ነው።
 
እያንዳንዱ ትውልድ ጥሪ አለበት እና። እያንዳንዱ ትውልድ ለዘመኑ መልዕክተኛ ነውና። እያንዳንዱ ትውልድ የተፈቀደለት ጊዜ አለና። በተፈቀደለት የጊዜ ማዕቀፍ ዛሬን አቅንቶ ነገን የማብራት ተልዕኮ ሊኖረው ይገባል። ኃላፊነት #የለት ጉዳይ አይደለም። ከነገ ተሻግሮ ለነገ በስቲያ ማሾ የመሆን አቅም ሊኖረው ይገባል። ከዚህ ዝንፍ ካለ ዕድሜው ብክነት ላይ ያለ ስለመሆኑ ሊረዳ ይገባል።
 
#ትንታጉ ዓራት ዓይናማው ጋዜጠኛ የት ነው?
 
የዘመን አቻወች ናቸው ጋዜጠኛ ተመስገን ደስአለኝ እና ፖለቲከኛው ዮናታን ተስፋዬ ረጋሳ። በዘመናቸው ብዙ ፈተና አብረው አሳልፈዋል። አሁን አንዱ ተሿሚ ሌላው የት እንዳለ እንኳን አናውቅም።
 
ብዕረኛው ተሜ ለሥነ - ጹሁፍ የተሰጠው ነው። ለእሱ የተሰጠው ጸጋ ይለያል። #ተፈጥሮበታል። መክሊቱ እናቱን ወ/ሮ ፋናዬ ደስአለኝ እና ወንድሙ ብዙ ዋጋ ከፍለውበታል። ያ ብዙ ዋጋ የተከፈለለት የእዮር ስጦታ ዕገታ ላይ ነው። ወንድሜ አቶ ዮናታል ተስፋዬ ረጋሳ ጋዜጠኛ ተመስገን ደስአለኝ የት ነው ያለው?????? ----- 
 
ተሜ ልቅና ፍትህ ወዘተ የሚባሉ ነፍስ ሆነው ነፍስ የሚዘሩ መጽሄቶችን አሳታሚ ነበር። ዛሬ ግን ማዕቀብ፤ ግዞት ይሁን እስርቤት መክሊት፤ ጸጋ፤ እዮራዊ ጥሪ ዕጣ ፈንታቸው ሆኗል። ተሜ ጥምቀትን ሄዶ ጎንደር ለማክበር እንኳን የተፈቀደለት አይመስለኝም። በ2026 የጥምቀት በዓል ጎንደር አላየሁትም።
 
"ፍትሕ መጽሔት” (Feteh Magazine) በኢትዮጵያ ውስጥ በዋናነት በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የሚመራ፣ በልህቀት የህትመት ኮሚዩኒኬሽንና ብሮድካስት ሥራዎች ኃ/የተ/የግ/ማህ ስር እየታተመች ዘወትር ቅዳሜ ለአንባቢያን የምትደርስ ሳምንታዊ የፖለቲካ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች መጽሔት ነች።"
 
እስፔን የባቡር አደጋ ሰሞኑን ተከስቷል። ሚኒስትሩ ሹፌር አይደሉም። ግን የሰለጠነ አዕምሮ ስላላቸው ከስልጣናቸው በፈቃዳቸው ለቀቁ የሚል ዜና አዳምጫለሁኝ። 
 
ሪፖርተር፤ ፍትህ መጽሄቶች የታሪክ ምዕራፎች ናቸው። በክፋ ሃሳብ ማህበርተኞች ሊዘጉ አይገባም። እራስን የሚገልጽ ንጹህ ተግባር ከንጹህ ውሳኔ ከመድረስ ጋር መገናኜት ያስፈልጋል። እኛንም ባታሳዝኑን። በአገሬ ልጆች እስረኝነት ጉዳይ ብዙ በጣም ብዙ ደክሜያለሁ፤ ለፍቻለሁኝ። 
 
"እግዚአብሄር በአንድም በሌላም ይናገራል። ሰው ግን አያስተውለውም።"
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን መስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን። 
 
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
05/11/026.
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
See less

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።