#መቼን ደፍረን እንጠይቀው

 

#መቼን ደፍረን እንጠይቀው #የየለት ሰማዕትነት በኢትዮጵያ እስከመቼ ብለን።
#የሰቆቃዊ ኢትዮጵያ ድምጽን ማን ያድምጥላት።
 
"ድሃን በግድ አትበለው ደሃ ነውና፦ ችግረኛውንም በበር
አትግፋው ፦ እግዚአብሄር የእነሱን ፍርድ ይፈርድላቸዋልና፦
የቀሟቸውን ሰወች ሕይወት ይቀማላቸዋል።"
(መጽሐፈ ምሳሌ ምዕራፍ ፳፪ ቁጥር ፳፪ - ፳፫)
 
 
እንዴት አደራችሁ ውዶቹ ክብሮቹ። እኔ አምላኬ ክብሩ ይስፋ ደህና ነኝ። ጤና-ይስጥልኝ ኢትዮጵያ አገሬ እንዴት አደርሽ?
ጤና-ይስጥልኝ አጽናኛዬ እየኖርኩብሽ የማልጠግብሽ እምዬ ሲዊዝሻ።
 
#ወሩ እና አቤቱታው።
 
ወራቱ - ቀናቱ - ደቂቃት - ሰዓታት - ወቅታት እና ዓመታት በኢትዮጵያ #ሰማዕትነት ይቀናቸዋል። ለምን? የዓመታት ቀመር የውስጥ ሰላም ስለላቸው። የውጭም ጫናው በተመሳሳይ ነው። ስለሆነም ዕንባ በርከትከት ብሎ፤ መከፋት - ነግሶ፤ ጭንቀት ገኖ ይታያል በእናት አገር ኢትዮጵያ። 
 
ለዚህም ነው መቼን በኢትዮጵያ ሰማዕትነትን ሊያስቀር እንደሚችል እንጠይቀው ያልኩት። ሊጠየቅ ይገባል። ሁልጊዜ ዕንባ። ሁልጊዜ - መርዶ። ሁልጊዜ ደመር፤ ሁልጊዜ ጭንቅ ይጨንቃል፦ ተስፋን ያሳጣል፦ ነገን ያደርቃልና።
 
ደመር በጎንደር ክፍለአገር አፈር ማልበስ ያልቻሉ ቤተሰቦች ቀነ ቀጠሮ ተይዞላቸው በወል ዕርማቸውን በዕንባ የሚያወጡበት የውል ቀን ማለት ነው። የጋራ የዕንባ ውጪጭ፤ የሃዘን ሼር የማድረግ ባህል ነው። 
 
#ብልፄው ሆይ! የት ነው ያለህው?
 
አብቱ ብልፄው ማንን እየመራህ፤ ምኑን እየመራህ ነው ያለህው? ሞትን ወይንስ መፈናቀልን ወይንስ ጭንቀትን ወይንስ መሰወርን፤ ወይንስ መታገትን ወይንስ ፍርሃትን ወይንስ #ራህብን እኮ አይዋ ብልፄው ማንን እንድትመራ ይሆን ሰፊ በሆነ መሰናዶ ኮሮጆውን አሰናድተህ ድምጽን አፍሰህ አንተ ግን በቃልህም በምግባርህም የለህም?
 
የት ነው ያለህው ኡራኖስ፤ ጁቢተር፤ ሜርኩሪ እኮ የት ነህ። ዕንባ አጀንዳህ ሊሆን አልቻለም። ሚዲያወች አበባ፤ ሠርግ እና መልስ፤ ቅልቅል እና ግጥግጥን ነው ሲያሳድዱ የሚታየው። እና የአንተን ዕጹብ ድንቅነት ሲተራርኩ ………
 
የሆነ ሆን በመረጠህ ህዝብ ዘንድ ይህ ሁሉ ማት ሲፈስ አንተ እና ሚዲያወችህ የት ናችሁ? መራራ ስንብትን እስከ መቼ እየሸሸህ ኢግኖር አድርገህ ልትቀጥል አሰብክ? 
 
ምርጫውን በሚመለከት በሞገደኛው ህወሃት ምክንያት ትግራይ እና አማራ ክልል በ፰ የምርጫ ጣቢያወች ባይካሄድም በተካሄደባቸው ሁሉ ፊርማው ሳይደርቅ ነገር ዓለሙ የዕንባ ማህበርተኛ ሆኗል ቀዩ እና አድባሩ። እስከ መቼ? ኃላፊነት እና ተጠያቂነቱ የአንተ የዓውራው ፓርቲ የብልጽግና ነውና ተጠየቅ፤ መልስ ስጠኝም። 
 
ይህ ሁሉ እየሆነ የህዝብ ምሬት እና ሰቆቃ፤ ራህብ እና እንግልት የአንተ አጀንዳህ ፈጽሞ አይደለም። የወገኖችህ ጉዳይ ለትርፍ አጀንዳነት እንኳን አልበቃም። ስለ ራስህ ህዝብህን እንደ እንጀራ አባት እንኳን የማየት አቅምህ የተሰወረ ነው። ድግስ፤ ኢቤንት፤ ሴሪሞኒ ብቻ እና ብቻ። 
 
የገረመኝ። የትኛው አብነት ይሆን የአፍሪካ ፓርቲወች ጉባዔ በአድዮ ምንጣፍ ሽር ብትን እምትልበት? ውስጥህ እኮ በጦርነት በሞት በመፈናቀል በዞግ ቀውስ ንጠት ላይ ነው። በኮሬ፤ በውልቂጤ የወጣት #ምክነት፤ በወለጋ፤ በጎንደር ከተማ የወጣት #ምንጣሮ፤ በጋንቤላ፤ በቤንሻንጉል ጉምዝ የሰላማዊ ህዝብ እልቂት፤ በአርሲ የቅድስት ተዋህዶ ሰማዕትነት ኡኡታ ነገሰ። ብልፄው አንተ ግን የት ነህ? እኮ #ምንድን ነህ? 
 
1) መሪ ወይንስ አድፋጭ?
2) ተረብ ወይንስ ቁምነገር?
3) ፋንታዚ ወይንስ ክሱት እኮ መደብህ ምንድን ነው? ለሰው የተፈጠርክ ወይንስ #ለማይክ ማርዳ?
 
 
1) ኮሬ፤ ውልቂጤ፤ ወለጋ፤ ጎንደር ከተማ፤ ቤንሻንጉል፤ ጋንቤላ፤ ወለጋ፤ አርሲ የሰላማዊ ዜጎች ሰማዕትነት አለ።
2) ሙያሌ፤ ራያ የህዝብ መፈናቀል።
3) መቀሌ፤ ጋንቤላ፤ የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ።
4) አማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ መነሳቱ አልታወጀም።
5) ዋግኽምራ የምግብ እጥረት።
 
#የምስራቁ ሰላምስ እንዴት ሰላም ነሳህ? ስለምንስ ሰላም ነሳህ? መቆስቆስ ስለምን ፈለግህ?
 
እፎይ የምንልበት የምስራቁ ጠሃይ ስለምን እራስህ ትጋፋዋለህ? እራስህን እራስህ አጥቅተህ የቀጠናውን እንዲህ ስለምን ታባትለዋለህ? ጥሩዋ ጎረቤታችን ኬንያ ላይስ ስለምን በርደን ለመጫን ትጣደፋለህ? መካሪ የለህንም ወይ? ለነገሩ ጆሮ ገብያ የለው።
 
እንደ ወተቴ፤ እንደ አንከሊስ በየቦታው ጦሽ ጦሽ የሚል የጎረበ ቁስል ፈውስ መሆን ሲገባህ አዲስ ቁስል፤ አዲስ ትርምስ፤ አዲስ ዕንባ አዲስ ሴራ እና ሙሉ ክልሉን ሰላም መንሳት ለምን ያስፈልገሃል? የህወሃት አልበቃህ አለን? የሞያሌውን እንኳን ሃንድል ለማድረግ ስለምን አቅም አነሰህ? አገር እየመራህ ምነው ተሳነህ ከራስህ የግል ጉዳይህ መውጣት?
 
ከሥልጣን ልታነሳው የምትፈልገው ብቁ አቅም እንዳለ ወፊቱ ሹክ ትላለች። ጉባኤህ ግን መቼ ይሆን? የፈራህ ይመስለኛል። እናም ሱማሌ ክልል ላይ ያለው ሰላም ስለምን አስቀናህ? እኮ ለምን? ኃላፊነቱን በአግባቡ የተወጣ ሊሸለም እንጂ እንዲህ ሊታመስ አይገባም ነበር። እንሆ ባቀድከው ልክ ከ50 ሺህ ያላነሱ ወገኖቻችን ስደት ላይ ይንገላታሉ። ማህበረ ኦነጎች ቀመራችሁ ኦድ ነው።
 
ራያም ከ50 - 70 ሺህ ተፈናቃይ ነበር። መፈናቀሉን የፈጸመው ህውሃት ነው። አሁንስ እነዛ የተፈናቀሉ ወገኖች ሁኔታ በምን መልክ ይገኙ ይሆን? ከመፈናቀሉ በፊት ደርሰህላቸው ቢሆን ሰማዕትነቱንም፤ መፈናቀሉንም ባልተሸከሙ ነበር። በቸልታ፤ በአያገባኝም መንፈስ እንደ ዳር ታዛቢ ነበር ስታየው የነበረው። ከአጣዬ ቀጥሎ የተቀጠቀጠው የራያ ገራገር ህዝብ ነው።
 
#ትኩረት የተነሳቸው የእኛነት ጉዳዮች።
 
በሃኪሞች ላይ የባጀው የግፍ ግድያ በአማራ ክልል ተግ ብሎ አልፎ አልፎ ቢከሰትም፤ በጎንደር ከተማ የወጣቶች ተከታታይ #ምንጠራ አለ። ነጋቸው የሚቀሙ ወጣቶች ታቅዶ የሚከወን ይመስላል። ይህስ ከአቅምህ በላይ እንደምን ሆነ? የአህጉሩ አውራ ፓርቲ ለመሆን የምትጣጣረው ብልጽግና እስቲ ስለውስጥህ ግድ ይስጥህ። በአመዛኙ ታድነው የሚገደሉት #ባለማተቦች ናቸው። ለምን? እስከመቼ-------------ስ?
 
በውልቂጤም ንጹሃን ወጣቶች ከተስፋቸው ጋር እንዲነጣጠሉ የቹቻ፤ የሰኔል ቤተኛ እየሆኑ ነው። ለምን????? እስከ መቼ የውልቂጤ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ልጆች በጠራራ ጸሐይ መኖራቸው ይቀማል??? ግን አለህን በንግሥና ቦታህ አይዋ ብልፄው?
 
#የኮሬ ጉዳይ በኦሮምያ እና በደቡብ አዋሳኝ አካባቢ የሚፈጸም ግድያ ባለቤት የሌለው፤ ትኩረትም በእጅጉ የተነፈገው ነው። ህዝቡ በስጋት ውስጥ ነው። አጽናኝም አላገኜም። እስከ መቼም የራስህን ወገኖች፤ ሳያመናቱ የመረጡህን ንጹኃን ቸል ትላቸዋለህ አይዋ ብልፄም ……… ተጠየቁ? መልሱልንም እባክህን።
 
የተበተነ መንፈስ ነው እኔ የማዬው። ዳር ዳር፤ መስክ ለመስክ መሄዱ አያዋጣም። ደፍሮ ከችግሩ ጋር መፈለም፤ አቅም ካለህ መፍትሄ መሆን ነው። የፖለቲካ አቅም ማለቴ ነው። የየለ የአዘቦት ዲስኩር ቋት አይገፋም። 
 
አንድ ዕንቁ የህዝብ አካል አለ። ዝምተኛው፤ ጭምቱ፤ ግን አዋቂው ባለአቅሙ። ያያል። ይሰማል። ይታዘባል። ሲከር ይበጠሳል ሲሞላ ይፈሳል ከሆነ ይህ ከሁሉም በላይ ለመሆን የምትመኜው ምኞት በቅጽበት ልታጣው ትችላለህ። ውስጥ የሚረጋጋ የሰዋዊነት ጨዋነት፤ የተፈጥሯዊ ዕውነትነት ጋር ዘመንህ ሊገጣጠም አልቻለም። ኃይል ብቻውን ምንም ነው። ደርግ የደረጄ የፓርቲ አወቃቀር፤ ለዘመኑ ብቁ የነበረ የባህር፤ የአየር የምድር ኃይል + ኢትዮጵያዊነት ነበረው። 
 
በጋንቤላ ርዕሰ መዲና ከፍተኛ የጸጥታ መደፍረስ ነበር። ሰማዕትነትም ነበር። አሁን ደግሞ በአኟክ አካባቢ ስጋት በመኖሩ ይመስላል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል። 
 
ይህ ሲገርመኝ መቀሌም የሰዓት እላፊ ገደብ ተጥሏል። በብዙ የሚያሰጋው ከዚህም በላይ የሰይጣን ጆሮ ይደፈንና የቃጠሎ፤ የፈንጅ፤ የስወራ፤ የእገዳ ሁኔታ ሊቀጥል ይችላል። ፍልሚያው ከህወሃት ጋር ነውና። 
 
የህወሃት የአጭር ጊዜ ድል ለጊዜው ይሁን ለዘለቄታ ታምቋል። ዕምቁ የውስጥ ህመምን ጸንሶ ብስጭትን ያጎራርሳል። ብስጭት ተስፋ ማጣትን አጎልብቶ ወደ #አናርኪ ርምጃ ሊወስድ ይችላል። ስለዚህ የሰከነ፤ የተጠበበ በሳል አያያዝን የሚጠይቅ ብርቱ ጉዳይ ለባላደራው አካል ይጠብቀዋል።
 
አካላቱ ከንግግራቸው እንደተረዳሁት ስክን ያሉ ይመስላሉ። ግን ሰውዬው እልኸኛው ህወሃት ነው። ዘመኑን ሁሉ የተጋሩን ዕዝነ - ህሊና ተብትቦ መፈናፈኛ ያሳጣ ድርጅት። ይህን ለመቋቋም ይመስላል የሰዓት እላፊ የታወጀው።
 
የፌድራል ፖሊስ፤ መከላከያ፤ የሰላም ኃይል እያለ የሰዓት እላፊው ግን ግርም ብሎኛል። ምን ዓይነት ከአቅም በላይ የሆነ ነገር ቢገጥም ብያለሁኝ። በፍቅር የተቀበለ ህዝብ፤ ነገ ባለአደራው ለቆ ቢወጣ ምን ይደርስበት ይሆን ብዬ ሁሉ አስቤያለሁ። ሰግቼማለሁኝ። ለትግራይ ሰላም ጽዮንም ትርዳው። አሜን። 
 
በአማራ ክልል፤ በኦሮምያ፤ በትግራይ ጦርነት አለ። ይህ የውስጥ የርስበርስ ጦርነት የውጭ ስፖንሰር ማግኜቱን እሰማለሁኝ። ከዚህ ሳይደርስ ሁሉንም በመልክ መልኩ፤ ደረጃ በደረጃ በቂ ዕውቅና ሰጥቶ ችግሩን እንደ ባህሬው መፍታት ይቻል ነበር። ኢትዮጵያ ከውስጥ ካለች። ለዜጎቿ የውስጥ ሰላም እና መረጋጋት ከታሰበ። አልሆነም።
 
አለመሆኑ ለሌላ የውጭ ኃይል የበቀል #መዶሻ ዝግጅት #ማጫ ማጣፈጫ ሆነ። ብልፄው የሚፈልገው ዘለግ ያለ ጎልደን ብራንድ ተመኝቷል። ከዚህ በኽረ ጉዳይ ጋር ድልድይ ለመፍጠር ይመስላል የውስጡን ችግር እንዳላዩ ማየት ያስፈለገው። እርግጠኛ አይደለሁም ይመስለኛል።
 
ብልፄው ባለመው ልክ ሦስት ድምጽን በድምጽ የመሻር አቅም ያላቸውን ያሳተፈ ድልድዩ ተሠርቷል። የኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ ከባህር በር እና ከወደብ ጋር ተፋጠዋል። 
 
ዙሪያ ገባው ውጥረት የሆነበት አንድ መንግሥት አዳዲስ ችግሮችን ተሎ መልስ መስጠት አለመቻሉ ነው። ለዕንባ አፋጣኝ አጽናኝ እርምጃ መውሰድ ይገባ ነበር። ግን በውልቂጤ፤ በሞያሌ አዲስ ችግር ብልፄው እራሱ ፈብርኮ ቀውሱ ሙሉ ኢትዮጵያን ይንጥ ዘንድ ተፈቅዷል። ከስሜን እስከ ደቡብ፤ ከደቡብ እስከ ምስራቅ። 
 
#በዚህ መሃል የብልፄው #ቂቅታ።
 
ብልፄው ከረባቱን ቂቅ አድርጎ፤ ገበርዲኑን ፐ አድርጎ በራሺያ እና በአፍሪካ ጉባኤ ከመገኜት ጋር ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ሽመታውን አስከነዳው፤ በፈረንሳይም ተጨማሪወችን አክሎ አየር ኃይሉ ማዘመኑ የአይደፈሬነት ግርማውን ተላብሶ የአፍሪካ የፓርቲወች ጉባኤ ትዕይንት ተወነ።
 
ይህ ሁሉ ግን ……… እግዚአብሄር አላህ እስከ ፈቀደ ነው። የሰሞናቱ የአሜሪካ የግማሽ ተርም ምርጫ ሁሉ ያላትን የአሜሪካ መንግሥታዊ አካል፤ መሪ ዓውራ ፓርቲን ሪፓብሊክን 50+ በሆነ ውጤት ከመሸነፍ አላዳነውም። ፈጣሪው ሠሪውም ዴሞክራሲ ቢሆንም የህዝብ ሁሉን ነቅቶ በመከታተል የሚወስደው ሰላማዊ እርምጃ ትክ የለሽ መሆኑን አይተንበታል። ከዚህ ሂደት ለመማር መፍቀድ ብልህነት ይመስለኛል።
 
• #እስከ መቼን እናፋጠው?
 
በድግስ ብሽብሽ በሚያደርገው የብልፄው ዘመን ለለት ጉርስ ያልበቁ ሚሊዮን ወገኖቻችን አሉ። የአዳራሾች፤ የፓርኮች፤ የመንገዶች መኳኳል ብቻውን #ሰውነትን አይገልጽም። አንድ አገር ይሁን መንግሥት ሰለጠነ የሚባለው አገርን አገር ላደረገው ህዝብ ሙሉ አክብሮት፤ ሙሉ ትህትና፤ ሙሉ ታማኝነት ሲኖረው ነው። ወንበር እኮ እንጨት ነው። ህንፃውም የካብ፤ የብሎኬት፤ የስሚንቶ ድርድር። ሁሉንም በልክ አድርጎ #ራበኝ ለሚል ወገን መድረስ ያስፈልጋል።
 
ብጹዕ አባታችን አቡነ በርናባስ በረከታቸው ይድረሰኝ። አሜን። የዋግ ኽምራ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ በረከታቸው ይደርብን ለሁላችንም። አሜን። በአማራ ክልል የሚገኘው የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን በአሁኑ ወቅት በከባድ #ሰብአዊ ቀውስ፣ በድርቅ እና በጸጥታ እጦት( የአገው ነፃ አውጪ ነው ከዛ ደግሞ የሚበጠብጠው) ረሃብ ውስጥ መገኜቱን ገልጸው የድረሱልን ጥሪ አስተላልፈዋል።
 
ይህን መረጃ አስመልክቶም አዲስ ስታንደርድ ከሥር የለጠፍኩትን ዕርዕስ ሰጥቶ፤ አሳሳቢ ከሆነ ፎቶ ጋር ለጥፎታል። አሁን ከሆነ ቤተ ሥርጉትሻ ታዳሚወችን መንፈስ በጣም ላለማወክ በፎቶ ምርጫ ላይ ተጠንቅቄ ነው ፖስት የማደርገው። ህዝባችን - ተጎድቷል። ከሳቅ ይልቅ መርዶ ይበዛል። ለጸሐፊወችም እየቸገረን ነው ያለው።
 
“‘War is better than famine’ has come true for us”: Wag Hemra residents face severe hunger amid drought, conflict” 
 
ብልፄ ተኝቷል። ብልፄ ቸልታን ስንቁ አድርጓል። ማን ብልፄውን ከእንቅልፋ ይቀስቅሰው? የውነት ለሽ ብሏል። የስካንዳንብያን አገሮች ይመራ ይመስል መዝናናት፤ ቅብጥ ቅልጥ ማለትን አራጥ ይተውናል።
 
ግን አይጠቅም። የራሄል ዕንባ ያደመጠ አምላክ ለቤቱም ቀናዕይ ስለሆነ ቸል አይለውም። ሲበቃው በቃኝ ይላል አማኑኤልም። ከአቅም በላይ ሆነ ግፋም ለግፋም ኃላፊነት የሚወስድ አካል መጥፋቱ።
 
የእኔ ዕይታ እና መረር ያለ የብዕር ጠብታዬ ከሰብአዊነት አንፃር ነው። ሌላ ትርፍ ቅጥልጥል ፍላጎት የለኝም። ሊናረኝም አልፈቅድም። የህዝብ ሰላም ይመለስ። ለህዝቡ የኑሮ ዋስትና ይሰጥ። መንግሥት ነን የምትሉም አጽናኑት። አይዞህ በሉት። እባካችሁን።
 
ሊንኮችን በዚህ ወር ብቻ የሆነውን የሰቆቃዋ ኢትዮጵያ ድምጽ ሊንክ ለጥፌያለሁኝ። የቤንሻንጉል ጉምዝ አዲስ ስለሆነ የBBC ዘገባን ሙሉውን ለጥፌያለሁ። የሰነበተውን ሊንኩን ብቻ አያይዣለሁኝ። 
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
 
ኑሩልኝ። አሜን።
 
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
08/11/026.
 
ትዕግሥት ሲያልቅ ፍቅር ይሰደዳል።
ፍቅርም ሲያልቅ ትዕግሥት ይሰደዳል።
 
BBC.
«በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቡልዲግሉ ወረዳ በታጣቂዎች ጥቃት ከ50 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ፖሊስ ገለፀ»
 
«በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ዞን ቡልዲግሉ ወረዳ በምትገኘው ዳለቲ ቀበሌ ውስጥ ታጣቂዎች በፈፀሙት ጥቃት 52 ሰዎች መገደላቸውን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ለቢቢሲ ገለፀ።"
 
"የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ እድሪስ መሐመድ ለቢቢሲ በሰጡት አጭር ማብራሪያ፣ በስፍራው ጥቀቱ የተከፈተው ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ጥቅምት 26/2019 ዓ. ም. ንጋት 11 ሰዓት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
 
ጥቃቱን የፈፀሙት "የሸኔ ታጣቂዎች ናቸው" ያሉት ኮሚሽነሩ፣ ሲቪሎች እና የክልሉ መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ሰለባ መሆናቸውን ተናግረዋል።
 
በዚህ ጥቃት ባጠቃላይ ተገደሉ ካሏቸው 52 ሰዎች መካከል 21 ሰዎች ሲቪሎች ሲሆኑ፣ 18 የሚሆኑት የክልሉ አድማ ብተና አባላት፣ የተቀሩት 13 ሰዎች ደግሞ የአካባቢው ሚሊሻ አባላት መሆናቸውን በዝርዝር ገልፀዋል።
 
ጥቃቱ የተፈፀመባት ዳለቲ ቀበሌ ከኦሮሚያ ክልል ጋር እንደምትዋሰን እና በአካባቢው "ሸኔ" ሲሉ የጠቀሷቸው ታጣቂዎች እንደሚንቀሳቀሱ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ እድሪስ መሐመድ አስረድዋል። 
 
ታጣቂዎቹ ጥቃቱን የፈፀሙት "ድንገት ገብተው በመሆኑ ብዙ ጉዳት ሊደርስ ችሏል" ብለዋል።
 
ከጥቃቱ በኋላ የመከላከያ ሠራዊት እና ተጨማሪ የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች በአካባቢው መሰማራታቸውን የገለፁት ኮሚሽነሩ፣ በመሆኑም መረጋጋት መስፈኑን ተናግረዋል። ታጣቂዎቹ ጥቃቱን ከፈፀሙ በኋላ "ወዲያው ተሰውረዋል" ሲሉም አክለዋል።
 
አቶ እድሪስ "ሸኔ" ያሉት እና በኢትዮጵያ መንግሥት በሽብርተኝነት የተፈረጀው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ስለተፈፀመው ጥቃት እስካሁን ያለው ነገር የለም። 
 
ቢቢሲ የታጣቂ ቡድኑ ቃል አቀባይ ምላሽ እንዲሰጡ ጠይቋል። የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እስካሁን ድረስ የቀረበበትን ክስ በተመለከተ ይፋዊ ምላሽ አልሰጠም። 
 
በሌላ በኩል የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ባወጣው መግለጫ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዳለቲ ቀበሌ የተፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ፣ በዚያው ቀን በተመሳሳይ ስፍራ "43 ሲቪሎች" በመንግሥት ኃይሎች ተገድለዋል ሲል አመልክቷል።
 
የኦነግ ቃል አቀባይ ለሚ ገመቹ በፌስቡክ ገጻቸው ያጋሩት የድርጅታቸው መግለጫ፣ ጥቅምት 26 በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዳላቲ በተባለ ቦታ፣ "ሸኔን ትደግፋላችሁ" በሚል ክስ "የክልሉ ፖሊስ ሴቶችን እና ሕፃናትን ጨምሮ ከ43 በላይ የሆኑ የኦሮሞ ሲቪሎችን በጅምላ ገድሏል" ሲል ከሷል።
 
ቢቢሲ በሥፍራው ስለተፈፀመው ጥቃት እና ስለደረሰው ጉዳት ከገለልተኛ አካል ማጣራት አልቻለም።
የአካባቢውን ነዋሪዎች እና እማኞች ለማነጋገር ያደረግናቸው ጥረቶች እስካሁን አልተሳኩልንም።
 
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ማብራሪያ የሰጡበት እና ኦነግ መግለጫ ያወጣበት ጥቃት ተመሳሳይ አልያም ትስስር ያላቸው ስለመሆኑም ቢቢሲ በገለልተኛ ወገን አላጣራም።
 
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ እድሪስ መሐመድ፣ በዳለቲ በተፈፀመው የታጣቂዎች ጥቃት ጉዳት ደርሶባቸው በሕክምና ላይ የሚገኙ ሰዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።
 
ከጥቃቱ በኋላ "ሕዝቡን አወያይተን የተበተነውን ማኅበረሰብ ወደቦታው መልሰናል" ሲሉም ለቢቢሲ ተናግረዋል።
 
ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተደጋጋሚ በታጣቂዎች ጥቃት ከሚፈፀምባቸው ክልሎች አንዱ ነው። በክልሉ የሐሙሱ ጥቃት የተፈፀመው በኦሮሚያ ክልል አርሲ በሚገኘው ሮቤ ወረዳ የ"38" ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ ጥቃት በተፈፀመበት ተመሳሳይ ቀን እና ሰዓት ነው።»
 
«በአርሲ ሮቤ ወረዳ በታጣቂዎች በተፈፀመ ጥቃት 38 ሰዎች መገደላቸውን የተጎጂ ቤተሰቦች እና ነዋሪዎች ተናገሩ»
 
«በመቀለ ከዛሬ ጀምሮ የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ላይ የሰዓት እላፊ ገደብ ተጣለ»
 
«በኦሮሚያ ክልል ሽርካ ወረዳ "የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት" እና "ኢመደበኛ ታጣቂዎች" 48 ሰዎችን መግደላቸውን ኢሰመኮ አስታወቀ»
 
«ዘላቂ መፍትሔ ሳያገኝ የተደጋጋሚ ግጭቶች መነሻ የሆነው የሞያሌ ችግር»
 
«በጋምቤላ ከተማ የሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው ጥቃት እና ሁከት»

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።