አዲስ አበባ #ቅዱስ መንፈስ ናት። ብልህነት ዊዝደም ነው። ብልጥነት ግን ለእኔ እንቅጩን ስናገር #ማጭበርበር ነው።

 

ብልህነት ዊዝደም ነው። ብልጥነት ግን ለእኔ እንቅጩን ስናገር #ማጭበርበር ነው።
 
የምርጫ ተርሙስ ከ6ኛው አገራዊ ምርጫ ይጀምራልን???? ሁለት የምርጫ ተርም ወደ ሦስት ማህበረ እንደ ልቡ ካላስደረጉት።
የምርጫ ተርሙስ ከሁለት ወደ ሶስት ይሸጋገራልን? ከ7ኛው ምርጫስ ይጀምራልን?
በዞግ ፖለቲካ ፕሬዚዳንታዊነት??? በቋንቋ "ፌድራሊዝም" እንደ አሜሪካ ዲሞክራሲ?
 
"ንጉሥ በፍርድ አገሩን ያጸናል፤
መማለጃ የሚወድ ግን ያፈርሰዋል።"
መጽሐፈ ምሳሌ (ተግሳጽ )
(ምዕራፍ ፳፰ ቁጥር ፬)
 
#በፓርላማ ምርጫ ፕሬዚዳንታዊ???? እንዴት ሊሆን ይችላል?
 
በቃ ኢትዮጵያ የተፈጠረችው የአንድን ዞግ ፍላጎት፤ ምኞት መሻት ብቻ ልታስፈጽም ነውን? ሌላው ጥያቄዬ ደግሞ መንግሥታዊ አደረጃጀትን ፓርቲያዊ ዲስፕሊን ውስጥ ተዘፈቀን? 
 
ግን ክብረቶቼ እንዴት ናችሁልኝ? 
 
እኔ ሁሉንም ነገር መጀመሪያ ላይ በቅንነት ስለማይ ይህ የፕሬዚዳንታዊ መሻት #በስምንተኛው አገራዊ ምርጫ በእያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያ አቶ ሀ፤ አቶ ለ፤ አቶ መ ሴት አይታሰብም ይወዳደሩ እና ያን ጊዜ ፕሬዚዳንታዊ መሆን ይቻላል የሚል ዕሳቤ ነበረኝ።
 
እንዲህ በአቋራጭ እንደ አየር ላይ ትምህርት ዶክተሬትነት በፍጹም አላሰብኩም። አንድ እንፍራንዝ ከምትባል ትንሽዬ ከተማ የምርጫ ጣቢያ፤ ወይንም አርሲ ከሚገኝ ዲክሲስ ከሚባል የምርጫ ጣቢያ የተመረጠ አቶ ሀ አቶ ለ አቶ መ የአገር ፕሬዚዳንት ልክ እንደ አሜሪካኖች ዲሞክራት፤ ሪፓብሊካን ወይንም ኢንዲፔንደት ልሆን ብሎ ማሰብ ብዙ የገዘፋ የመንግሥት አደረጃጀት መርሆችን የሚሰባብር፤ የሚያቆሳስል፤ የሚገርፍ መከራ ይሆናል። 
 
ብዙ የገዢው ፓርቲ የብልፄው ዝንባሌው የመጫን መንፈስ ከኖረው አየሩ ይወጠራል። የተወጠረ አየር መተንፈሻ ቧንቧ ሲያጣ ይፈነዳል። አሁን ባለው ግሎባል ይሁን አህጉራዊ፤ አህጉራዊ ይሁን ብሄራዊ ትብትብ ሁለገብ ችግር አብዝቶ ማስተዋልን፤ አብዝቶ አርቆ አሳቢነትን፤ አብዝቶ ብልህነትን እንጂ #ብልጥነትን አይጠይቅም። ብልጥነት ለእኔ #አጭበርባሪነት ነው። ማጭበርበር ከገብያ ሂደት ጋርም መራራ ነው እንኳንስ በመንግሥት አደረጃጀት። 
 
ይህ እኮ የገበጣ ጨዋታ አይደለም። መንግሥታዊ አደረጃጀት የ130 ሚሊዮንን ህዝብ አደራ በመዳፋ የያዘ ነው። ሰውን ያህል ታላቅ ፍጡር፤ ተፈጥሮን ያህል ግዙፍ እዮራዊ ጸጋ መምራት ከጥበብ ውጪ በብልጠት ልጠቅልልህ ቢባል ዝበትን ፈጥሮ ተቃርኖን ያፋፋል። ተቃርኖ ደግሞ አሻምን አጭቶ #በቃን ያውጃል። 
 
ለበቃን ዝግጅቱ "መጨራረስ" መሆኑን በጄኒራልነት ማዕረግ የኬንያ ባለሙሉ አንባሳደር አንባሳደር ባጫ ደበሌ እንቅጩን ነግረውናል። ይህ የመጨራረስ ትልም ሰብአዊነትን ይሁን ተፈጥሯዊነትን ይጫናል። 
 
በታጣቂወች በኩልም በምክክር ኮሚሽኑ ላይ #እርምጃ እንደሚወሰድ መወሰኑን አድምጫለሁኝ። መሪነት ከክፋ ሃሳብ ጋር #መፋታትን ይጠይቃል። ጭካኔ ክፋ ሃሳብ ነው። ክፋ ሃሳብን አጭቶ የሚነሳ ዲያቢሎስ ብቻ ነው። ለባለ ማተብ ይህ???
 
በሌላ በኩል ቢያንስ በሃሳብ ለሚሞግቱ ትዕግሥት ቢጤ ከእዮብ ዶግማ ለመማር ማሰቡ ይጠቅማል። የጭካኔ ዓዋጅ ምርቃትን አስነስቶ እርግማንን እንዳያሸክም። የላይኛው። 
 
#ህም? ለፕሬዚዳንታዊ ይሁንታ ሙሉ ኢትዮጵያ መሳተፍ ግዴታ ነው። ጥሰት የመርህ ዕዳ ከሜዳ ነው።
እቴጌ ትግራይ እኮ በምርጫው 100% አልተሳተፈችም። በብሄራዊ ምርጫውም ይሁን በምክክር ኮሚሽኑ። ይህ ግንጥል ጌጥ ይሆናል በተለይ ለፕሬዚዳንታዊነት እጩነት።
 
በሌላ በኩል አማራ ክልል 8 የምርጫ ጣቢያወች የፓርላማ ምርጫ ላይ አልተሳተፈም። ኦሮምያ ላይም ምርጫ ያልተቻለባቸው የምርጫ ጣቢያወች አሉ። 
 
በዚህ ሁኔታ በመላ ኢትዮጵያ ከምርጫ በፊት ህገ - መንግሥቱ ማሻሻያ ተደርጎለት፤ ህዝብም ተስማምቶ 7ኛው አገራዊ ምርጫ ፕሬዚዳንታዊነትን ተቀብሎ፤ እጩወች ቀርበው በእያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያ እጩወች ተወዳድረው ያሸነፈ ፕሬዚዳንት መሆን ይችላል። ይህ በአገረ አሜሪካ የሚከናወን ሥርዓት ነው። የውሳኔ አቅሙን የሚያግዙ ተጨማሪም መርሆች ቢኖራቸውም። 
 
ይህ ሳይሆን፤ ሂደቱ ሳይጠበቅ የሚከወን ከሆነ የ6ኛኛውን አገራዊ ምርጫ እና የምደባ ሂደት አናርኪዝም እንዲወረው መፍቀድ ይሆናል። በምርጫው በብልፄው ቡራኬ የተሰጣቸው ተመጋጋቢ ፓርቲወች ተወዳድረን አሸነፍ ሲሉ አዳምጫለሁኝ። ስጦታው ለአዲስ ዓመት የብልፄው ነው። ጉቦው ይህን የአቋራጭ የመጠቅለል ሃሳብን ለማጽደቅ ጉርሻ ነው። በፖለቲካ ቋንቋ ምደባ ነው።
 
ወደ ቀደመው ስመለስ የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሥርዓት ተጥስ ከተከወነ አናርኪዚም ይሆናል። አናርኪዝም ደግሞ የሚያተርፈው አንድም የሥርዓት ኩነት የለም። ለመምራት ይሁን ለማስተዳደር ከአቅም በላይ ይሆናል። መቆጣጠር አይቻልም። ዛሬ ጸጥ ብሎ የሚሠራው ህግ ዋጋ ያጣል። ሲከር ይበጠሳል ሲሞላም ይፈሳል።
 
ህወሃት ፈቅዶ መንበሩን ሲያስረክብ፤ የቀድሞ ጠቅላይ ሚ/ር አቶ ኃይለማርያም ደስአለኝ ፈቅደው ሥልጣናቸውን ሲለቁ ታላላቅ የዓለም ዕንቁ መሪወች በርጋታ፤ በማስተዋል በዊዝደም ሂደቱን መርተው ሽግግሩ ከህወሃት ወደ ኦህዴድ ማዕቀፋ ኢህአዲግ ሆኖ እንዲፈጸም፤ ሰላማዊ፤ ሥርዓታዊ እንዲሆን ተደረገ። 
 
አሁን የአብይዝም የማያልቅ ፍላጎት፤ ኢንፊኒት ምኞት፤ አጥር የለሽ መሻት ገደቡን ጥሶ በዚህ መልክ ከቀጠለ #አገር ይኑረን ብለው በዝምታ ውስጥ ጨምተው የተቀመጡትን የሳይለንት ማጆሪቲውን መንፈስም በእጅጉ የሚውክ፤ በእጅጉ የሚበጠብጥ፤ በእጅጉም በውስጣቸው ረብሻ የሚፈጥር ይሆናል። የኢትዮጵያዊነት ሙሉ አቅም ከእነ ግርማ ሞገሱ የሚገኜው ሳይለንት ማጆሪቲው ላይ ነው። ለመምራት አይቻልም። ለመቆጣጠር አይቻልም። ምን እንደሚያስብም አይታወቅም። መዋቅር የለውም። መሪ የለውም።
#ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ከሥር እንጅ ከላይ የሚጫን አይሆንም። 
 
ሊሆንም አይገባም። የጠቅላይ ሚር አብይ ፎቶ በያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያ ተገኝቶ ድምጽ ሊያገኝ ይገባል። ይህን መሰል የብሄራዊ #መብት ወረራ እንደ ተለመደው በብልጽግናቸው ያድርጉት። ሌላውም የፖለቲካ ፓርቲ የሚያደርገው ነው። ፓርቲ ሲመሠረት እራሱን መሪ አድርጎ መሥራቹ ይፈጥረዋል። ይህ በጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ አልተጀመረም እንደ ማለት።
 
ብልፄው በ6ኛው አገራዊ ምርጫ ካሸነፈ በኋላ በጉባኤው የራሱን ፕሬዚዳንት ካለ ተወዳዳሪ የአስመራጭ ኮሚሽን ሰብሳቢ ሆኖ እራሱን አወዳድሮ አስመረጠ። የሰውነት እንቅስቃሴው የስጋት፤ የጭንቀት ሁነት ሁሉ ነበረው። በየትኛውም የስብሰባ ሥርዓት የምርጫ ኮሚሽን ከውድድር ውጪ ነው የሚሆነው። ብልፄው ህግ አይገዛውም።
 
በ6ኛው ይሁን በ7ኛው አገራዊ ምርጫ እቴጌ ትግራይ አልተሳተፈችም። በዚህ መስመር ፕሬዚዳንታዊ ምርጫን ማምጣት ሲታሰብ ትግራይ 100% ባልተሳተፈበት ሁኔታ በጫና ይህን ማስፈጸም ነገን ሙሉለሙሉ #ማንደድ ይሆናል። 
 
አሁን ግልጽ ነው አገራዊ ምክክሩ የተደራጀበት፤ ከአዲሱ ፓርላማ ጉባኤ በፊት ጥድፊያው ለዚህ መሆኑ ይፋዊ ዓዋጅ ነው። ይህ ሁሉ የጊዜ፤ የመዋለ መንፈስ፤ የመዋለ ንዋይ ወጪ ሳይወጣ ይህን በቀላሉ በነጋሪት ጋዜጣ #በዓውጅ ማድረግ ይቻል ነበር። እንደ ልቡ ለሆነ መንፈስ የሚገድበው የሚያግደው የለም እና። ያው የዲፕሎማሲው ማህበረሰብ ተፈርቶ ነው። 
 
በውነቱ በአገር ጉዳይ ግለት የተገባ ባለመሆኑ የተወሰነ ብሄራዊ ትርፍ ከተገኘ መሳተፋ ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁኝ። ምርጫ ላይም እንዲሁ ትውልዱ ዕድሉን #እንዳያፈስ አበክሬ ሳስገነዝብ ነበር። በምክክር ኮሚሽንም መረጃን በስማ በለው ከመስማት፤ በአካል ተገኝቶ ማድመጥ በእጅጉ ይሻላል። 
 
ይህ ሆኖ ግን ማንኛውም መሻት ይሁን ራዕይ ሂደቱ ብልህነትን የሚያስቀድም እንጂ #ብልጠትን ምራኝ ግዛኝ ንዳኝ ሊል አይገባውም።
በሌላ በኩል ሁሉም ነገር #እኛ ብቻ ያልነው ይሁን እራስነትን #ይደፋል። 
 
አሁን የአዲስ አበባ ጉዳይ ይህን ያክል የአንድ ዞግ ባለቤትነትን ማወጅ የሚያስፈልገው አልነበረም። ፈጽሞ። ኢትዮጵያዊ ዜጋን፤ ኢትዮጵያን እራሷን #ተጠማኝ#ተቀላች ነው የሚያደርገው። 
 
በ8 ዓመቱ የኦህዴድ ሊቃናት መሪነት ብዙ በጣም ብዙ የተንጠራሩ፤ ለግል ብቻ ታሳቢ የሆኑ ብሄራዊ መብቶች ተጥሰዋል። መስቃው፤ ሽሚያው የሰው ልጅ ለመኖር ብቻ ሳይሆን ለሞትም መፈጠሩን የዘነጋ ነው። በአንድ መንፈስ ብቻ የተጠለለ መሻት ነገ ባለተራው ሲመጣ ይንደዋል። ይህን በሥጋ በተለዩት የህወሃት ጭንቅላት በአቶ መለስ ዜናዊ ታይቷል።
 
ዝምታው አገር ይኑርን ተብሎ ነው። ለብዙ የተለያዩ መሻቶች አቅም ለመመገብ የተቆጠቡ ሰብዕናወችን ማክበር ይገባል። "ማምሻም ዕድሜ" ነው ይላሉ ጎንደሬወች። ግን መንፈስን ፈቅዶ አክብሮም መስጠት ይሉንታ ላልፈጠረለት የማህበረ ኦነግ እልቀተ ቢስ ፍላጎት በዝምታ ተችሎ መታለፋ ከዚህ አደረስ። ዜጋን የጋራ ቤት አልባ የሚያደርግ ውሳኔ #ግማድ ነው። ከርቤ ነው። ሲኦል ነው። ነገን ያደርቃል።
 
አዲስ አበባ መንፈስ ናት። አዲስ አበባ #ቅዱስ መንፈስ ናት። አዲስ አበባ ፃዕዳ የህሊና ስንቅ ናት። አዲስ አበባ ለግሎባሉም የዓይን ማረፊያ አንባ ናት። አዲስ አበባ የእቴጌ ጣይቱ ምርቃታችን ናት። ኦህዴድ ለዚህ በቅቶ እሷንም እንጠቅል??? መሃከነ። አንድም የዲፕሎማሲ አካል እኮ ከቲም ለማ በፊት ኦህዴድ የሚባል ሥምን አያውቀውም ነበር። 
 
ቀዳዳው ሁሉ ተደፋፍኖ፤ አሁን ህወሃትሻን እንሞሽር እኔ ወርቅ፤ እኔ ቤሎ አቀርባለው በሚል ይፋዊ ባይሆንም "ኢትዮጵያ ሱሴ" ትወናውን አሳካ። እንደ ቅዱስ ቁርባን ነበር የታዬው። ወጣትነታቸውም ዕድሉ ይሰጥ እና ይታዩ ተብሎ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሁሉም ዓይነት አቅም ተገበረለት ለይሉኝታ ቢሱ።
 
መጨረሻውም እንዲህም እንዲያም እንደዚያም ሆነ ……ብዙ የማይታወቁ ሽግሽጎች፤ ድለዛወችም ይኖራሉ። "አያያዙን አይቶ ሸክሙን ይቀሙታል" እንደሚባለው። መራራ ነው፤ ጎምዛዛ ነው፤ ሬት ነው፤ መቃብር ነው አንድ የዓለም ፬ኛ ከተማ፤ ለአፍሪካ ፩ኛ ከተማ ለአንድ ዞግ ****ማስማማት፤ ቃሉን አሻሽየው ነው።
 
#የምርጫ ሰላማዊነት የንጥረ ነገሩ ምንጩ ከምን?
 
6ኛው ይሁን 7ኛው አገራዊ ምርጫ በሰላም ተካሄደ ሲባል አደምጣለሁኝ። እእ። በቀውስ፤ በስጋት፤ በፍርኃት፤ በጭንቀት ነው ሁለቱም የምርጫ ሂደቶች የተከወኑት። በዚህ ውስጥ ማህበረ ኦነግ፤ ማህበረ ህውሃትም ታዳሚ ናቸው። 
 
6ኛው ምርጫ ተረጋግቶ ይካሄድ ዘንድ ዝም ነው ያልኩት። ከዛ በኋላ በሰላም ተከወነ ሲባል ፍርሃት፤ ሽብር፤ ጭንቀት ቀውስ አዝመራ ማሳ ላይ ተቃጥሎ፤ ፖለቲከኞች፤ አንቂወች ታሥረው፤ ሚዲያወች ተዘግተው፤ ሻሸሜኔ ደቃ፤ ሽዋ ሮቢት ተጣጥላ፤ አጣዬ ነዳ፤ በህርዳር ከተማ በየጊዜው ቃጠሎ አስተናግዶ፤ በከፋ የእርስ በርስ ጦርነት ቋያ በወዘተረፈ ጭንቀት - መር ሁነት ምርጫው ተካሄደ። በምርጫው ሰሞናት እገዳ፤ ስወራ፤ ቃጠሎ፤ እስራት አልነበረም። 
 
ሂደቱ በ2012 ዓም ቀድሞ ተጠናቋል። አብይዝም ሙያ በልብን የሰነቀ ነው። እስከ አሁን ዝንፍ ያለ መሻት የለም። የፒኮክ አምላክ የት ሄዶ። ለማሸነፍ ከዚህ በላይ ሙያ በልብን አሰልጥኖ፤ አዘምኖ መገኜትን ይጠይቃል። አታቃሉ! አታጣጥሉ! እንደ ማለት። ከማህበረ - ኦነግ ዶር ለማ መገርሳ ካልሆኑ ሌላ በአቻነት ለአብይዝም የለም። ከሌላ ሊኖር ይችል ይሆናል። ለመሪ አትሰቡ አይጠፋም ሲል ልጅ ቴወድሮስ አስፋው ሲናገር ሰምቻለሁኝ። 
 
7ኛው አገራዊ ምርጫ ትኩረቱ በኢትዮጵያ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ላይ ነበር። ምክንያት ከ6ኛው አገራዊ ምርጫ በኋላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ መፈንቅለ ሲኖዶስ ተደራጀላት፤ ሰፊ የሆነ የማህበረ ምዕመናኑ ዲስፕሊን የዋጠ ብሄራዊ ንቅናቄ ተካሄደ። አሳረኛው ሻሻመኔም እንደ ፈረደበት ማት ወረደበት። ይህ ስላለ ለ7ኛው አገራዊ ምርጫ አርሲ ላይ በተዋህዶ ላይ ጭፍጨፋ፤ ቃጠሎ፤ የህዝብ ምንጠራ ቀጠለ።
 
 በአማራ ክልል ከፋኖ ጋር ባለው ጦርነት የአብነት ትምህርት ቤቶች እና ገዳማት ነደዱ። ከዛ ምርጫው በሰላም ተጠናቀቀ ተባለ። በነገራችን ላይ አርሲ ላይ የሚደመጠው ጭካኔ ፖለቲካ ሠራሽ ነው። አርሲን ደግነቷን፤ እምዬነቷን ኑሬ አይቻታለሁኝ። 
 
#የብልፄው የምርጫ ስጋት።
 
እኔ እኮ ስታስቲክሱን ሠርቼ ነበር። ብልፄው ረብሻህን አቁም። ቀውስህን ተው። ካለምንም ተጨማሪ የቀውስ አዙሪት 50+ በሆነ ውጤት ታሸንፋለህ። ስጋት አይግባህ፤ ማስጨነቁን አቁም ብዬ በትህትና በተደጋጋሚ ጽፌያለሁኝ። 
 
ለሰላማዊ ምርጫ የቀውስ ድግስ አያስፈልገውም። ልትሠራ ያሰብከውን ታቀርባለህ፤ ትወዳደራለህ ታሸንፋለህ ወይንም ትሸነፋለህ። ሁላችሁም ለመሪነት እራሳችሁን ያጫችሁት ሁሉ፤ ቀዳማዊ እመቤትነትን ያጩ አሉ፤ አደባባይ ላይ ስላላችሁ ህሊና ላለው አገር ለማስቀጠል ለሚፈልግ ቅን፤ ካለው ዓለም ዓቀፍ ውጥረት፤ ካለው አህጉራዊ ሁነት ማን ይሻላል? የሚለውን መምረጥ አያቅትም። ሁሉም የፖለቲካ ሊቃናት አደባባይ ላይ ናችሁ ያላችሁት። ማን - ምን እንዳለው ይታወቃል። ለብቃቱ ተግባር ራዲዮሎጂ ነው።
 
ሌላው መታወቅ ያለበት ግን ሁልጊዜ በብልጠት ማሸነፍ አይቻልም። ፕሬዚዳንት መባልን ሥሙን ነው የፈለጉት ዶክተር አብይ አህመድ እንጂ ሥልጣኑማ እኮ ተጠቅልሎ በአንድ ሰው እጅ ነው። የካቢኔው ይሁን የፓርላማው መንፈስ እኮ በአንድ ሰብ ህሊና ብቻ ነው ያለው። ክርክሩ ላይ እኮ አየን። ሚኒስተሮች ሳይቀር ሲፈተኑ።
 
የአብይዝም መርሁም "ገዳ ነው።" ነግረውናል። ለዚህም እኮ ነው የማይገባው። ተሰውሮ የተያዘ ሌላ መርኽ ስላለ። እኔም በጥዋቱ ጽፌበታለሁኝ። ለምርጫ ውድድር የብልጽግና ውክል አካላት ወጣ ያለ ጥያቄ ሲቀርብ ጭንቀታቸውም ይህ ነበር። አንገታቸውን ነበር የሚደፋት። በይፋ መርኃችን ገዳ ሥርዓት ነው ተብሎ አልተነገረም። ስለሆነም የቀረቡት ለክርክር ሁሉ ያው መነሻቸውም መድረሻቸውም ኮሪደር ነበር። ውይይቱ እራሱ አጀንዳው #ኮሪደር ቢባል ይሻል ነበር። ከዚህ ሁሉ ድካም ዓዋጅ አውጥቶ እንዳሻ መቧረቅ ይቻላል እኮ።
በአዲስ አበባ ጉዳይ ምልጃ መያዙን እያዳመጥኩ ነው። ወደ ፕሬዚዳንታዊ ለመሄድም ምልጃው ቀጣይ ይሆናል። አገርን፤ ማንነትን፤ ብሄራዊ ክብርን፤ ብሄራዊ ሞራልን በምልጃ? በጉቦ? ለእነሱ ለብቻ የተሰጠ መብት እንዳለ ሁሉ ቀጣይ ጥያቄያችሁን እንድናስፈጽም እራሳችሁን መሠረት አልባ አድርጋችሁ ወስኑልን። የኢትዮጵያዊነት ማንነት እራፊ ያጣል። ቃሎችን እያሻሻልኩ እያለዘብኩ ነው የምጽፈው እንጂ ምኞቱ እራሱ ገደል ነው። 
 
ምንም ሳያደርጉ፤ ማንንም ሳያውቃቸው ቲም ለማ ግሎባል ዕውቅና፤ ግሎባል ተቀባይነት በኢትዮጵያዊነት ማንነት ብቻ ለድል ይበቁ ዘንድ ተደረገ። የኢትዮጵያ ህዝብ እጁ አመድ አፋሽ ነውና የሰጠውን መታመን በልኩ ቀርቶ እንጥፍጣፊ ወይንም ቅርጥምጣሚ አላገኜም። ሁልጊዜ መከዳት ብቻ ………
 
ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ የፕሬዚዳንት እጩ ሆነው በ7ኛው ምርጫ ቢቀርቡ ጋዳ እንደሚሆን ይታወቃል። በተለይ ትግራይ እና አማራ ክልል ላይ? አሁን በሌላ መንገድ? ለዚህ ነው እኔ ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድን አታቅልሏቸው የምለው። #አሳቻ ናቸው ብዬም አውዲዮ ሠርቻለሁኝ። ብዙ ያልተለመዱ፤ ብዙም የማይገመቱ እርምጃወች አላቸው። የኢነርጂ አምላካቸው ደግሞ ያሳካላቸዋል። እንዲህ ሆኖ መፈጠርም ስለአለ። ያቀዱት ሁሉ ለስኬት ይበቃል። ነገን መተመን ባይቻልም። 
 
"ትህትናቸው፤ ሰብአዊነታቸውን" አምነዋለሁ ሲል ፖለቲከኛው አቶ ክንፋ አሰፋ፤ ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ግን እኔ አላምናቸውም አለ። ባለፈው ጽፌያለሁኝ አቶ ክንፋ አሰፋ የት ነው ያለው ብዬ። የእሱ ምስክርነት የእሱን የመኖር ዋስትና አላረጋገጠም። 
 
ባጠቃላይ የማህበረ ኦነግ ሊቃናት ኢትዮጵያን አራጠው እየመሩ፤ ኢትዮጵያን #አስማሙን ዓይነት ሆነ መጨረሻው። ኢትዮጵያን ስጡን ብቻችን እንጠቅልላት ነው። ኢትዮጵያ ኦርጋኒካዊ ተፈጥሮዋ በገቢያ ህግ ይተዳደር ነው። በዚህ ጉባኤ በምክክሩ ይሁን በፓርላማ የሚገኙት ሁሉ መኖራቸው በምን ሞራል ይቀጥል ይሆን? 
 
የተከበሩ ፕሮፌሰር መስፈን አርእያ እና ቲማቸውም ድካማቸው ……… ያሳዝነኛል። ፕሮፌሰሩ ትህትናቸው፤ ቀስታቸው ይመስጠኛል። እናም ነገን ያዩ ይሆን እላለሁኝ? ፕሮፌሰር መስፍን ማብራሪያ ሲሰጡ #ዝለው ነው የማያቸው። ደክሟቸዋል። እስከ መቼ እንደሚፈቀድላቸውም አይታወቅም። ከእኛ በተሻለ ብዙ የመረጃ ሙዚዬምነት በህሊናቸው አለ --- ና።
 
አዱኛወቼ ማለፊያ ጊዜ።
 
አቶ ዳንኤል በቀለን አመሰግናለሁኝ። ከሳቸው ፔጅ ነው የዋዜማ ራዲዮን ዘገባ ያገኜሁት። መረጃው ከስር ይገኛል። 
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
11/08/026.
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
 
"ቀጣዩ የመንግስት አስተዳደር ሥርዓት ፓርላመንታዊ ሆኖ ፕሬዝዳንቱ ከፓርላማው ይመረጥ የሚል ምክረ ሀሳብ በብልፅግና ቀርቧል"
ዋዜማ ራዲዮ
August 11, 2026
 
"ዋዜማ- በሀገራዊ የምክክር ጉባኤ 27ኛ ቀን በሥራ ቡድኖች ደረጃ እየተካሄደ የሚገኘው ምክክር ቀጥሎ ውሏል። በሰባቱ የሥራ ቡድኖች ቅዳሜ ነሐሴ 02 ቀን የጀመረው የተጠናቀሩ የአጀንዳ ምክረ ሀሳቦች ላይ አስተያየት የመስጠት ሂደት የቀጠለ ሲሆን፤ የፌደራል ከተሞች ጉዳይን እየተመካከረበት በሚገኘው የሥራ ቡድን 7 ደግሞ የተጠናቀረው የአጀንዳ ምክረ ሀሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ ተነቧል።
 
 የሥራ ቡድኑን ምክረ ሀሳብ እንዲያጠናቅሩ ኃላፊነት የተሰጣቸው 30 ተመካካሪዎች፤ ከሌሎች የሥራ ቡድኖች አንጻር ረዘም ያለ ጊዜ ወስደው ያጠናቀሩት ምክረ ሀሳብ በአመዛኙ ስምምነት ላይ የተደረሰባቸውን ጉዳዮች ያካተተ መሆኑን የገለጡልን ምንጮች፤ “አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ እና መቀመጫ ትሁን” የሚለው ምክረ ሀሳብ አሁንም የልዩነት ማዕከል መሆኑን ጠቁመዋል።" ስምምነት ላይ ያልተደረሰበት ምክረ ሀሳብየአዲስ አበባ ከተማ ሕጋዊ አቋም ጉዳይ አሁንም በተመካካሪዎች ዘንድ ልዩነትን ፈጥሮ የቀጠለ ጉዳይ ሲሆን፤ ተጠናቅሮ በቀረበው የሥራ ቡድኑ ምክረ ሀሳብ ላይ “አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ መሆኗ በሕገ መንግስቱ ይስፈር” የሚለው አማራጭ ምክረ ሀሳብ መካተቱ ተቃውሞ አስከትሏል።
 
 ይህንን ምክረ ሀሳብ ደግፈው የተከራከሩ ተመካካሪዎች፤ ይህ ድንጋጌ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 49 እንዲሰፍር መጠየቃቸውን ሰምተናል። የሕገ መንግስቱ አንቀጽ 49 ንዑስ አንቀጽ 5፤ ኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ስለሚኖራት “ልዩ ጥቅም” የሚደነግግ ሲሆን፤ በምክክሩ “ልዩ ጥቅም” የሚለው ድንጋጌ እንዲቀር ስምምነት ላይ መደረሱን የገለጡልን ምንጮች፤ በንዑስ አንቀጹ “አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ” ትሁን የሚል ድንጋጌ እንዲካተት መጠየቁን ነግረውናል። 
 
ለተመካካሪዎች የቀረበውን ምክረ ሀሳብ ተከትሎ በተሰጡ አስተያየቶች፤ በሁለቱም ወገን “ማሳመኛ” ያሏቸውን ነጥቦች ያነሱ ተመካካሪዎች ቢኖሩም፤ አሁንም ስምምነት ላይ አለመደረሱን ሰምተናል። በተመካካሪዎች የተነሱ አስተያየቶች ተካተው የአጀንዳው ምክረ ሀሳብ ዳግም እንዲቀርብ መወሰኑን የጠቀሱልን ምንጮች፤ በዋናነት የከተማዋን ሕጋዊ አቋም በሚመለከት የቀረቡት ሁለት አማራጮች አከራካሪ ሆነው መቀጠላቸው አይቀሬ መሆኑን ጠቁመዋል። 
 
የመንግስት አደረጃጀት አጀንዳ አራቱ ጉዳዮች የመንግስት አደረጃጀትን ጉዳይ እየተመካከረበት በሚገኘው የሥራ ቡድን፤ አራት ጉዳዮች ስምምነት አልተደረሰባቸውም በሚል መለየታቸውን ምንጮች ነግረውናል። የአጀንዳ ምክረ ሀሳቦችን አጠናቅረው እንዲያቀርቡ ኃላፊነት የተሰጣቸው ተመካካሪዎች ያቀረቡት የምክረ ሀሳብ ሰነድ በርካታ አስተያየቶችን ማስተናገዱን የገለጡልን ምንጮች፤ “ቀጣዩ የመንግስት አስተዳደር ሥርዓት ምን ይሁን? መሪውስ በምን አይነት መንገድ ይመረጥ?”፣ የፌደሬሽን ምክር ቤት አወቃቀር፣ የፌደሬሽን ምክር ቤት አባላት ምርጫ እንዲሁም የሕገ መንግስት ተርጓሚ ፍርድ ቤት ጉዳይ ስምምነት ላይ አልተደረሰባቸውም በሚል መቅረባቸውን ጠቁመዋል።
 
ቀጣዩ የመንግስት አስተዳደር ሥርዓት ፓርላመንታዊ ሆኖ ፕሬዝዳንቱ ከፓርላማው ይመረጥ የሚል ምክረ ሀሳብ በብልጽግና ፓርቲ አባላት እየተቀነቀነ የሚገኝ ምክረ ሀሳብ መሆኑን የገለጡ ምንጮች፤ ፕሬዝዳንቱ በቀጥታ በሕዝብ መመረጥ አለበት የሚል ሀሳብ የሚያነሱ ተመካካሪዎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል። በሁለቱ ምክረ ሀሳቦች መካከል ያለው ልዩነት፤ ስምምነት ላይ ያልተደረሰበትና ቀጣይ ምክክር የሚደረግበት መሆኑንም ሰምተናል።
 
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አወቃቀር ጉዳይ ሌላኛው ስምምነት ላይ ያልተደረሰበት ጉዳይ መሆኑን የገለጡልን ምንጮች፤ “ሁሉም ብሔሮች በምክር ቤቱ ዕኩል ውክልና ያግኙ” የሚል እና “ብሔሮች በአንድ ሚሊዮን ሕዝብ ተጨማሪ ወንበር ያግኙ” የሚሉ ሀሳቦች በአማራጭነት መቅረባቸውን ጠቁመዋል። 
 
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት የሚመረጡበት ሁኔታ ደግሞ ሌላኛው ስምምነት ላይ ያልተደረሰበት ጉዳይ ነው። የምክር ቤቱ አባላት በቀጥታ በሕዝብ ይመረጡ የሚል እና አሁን ባለው አሠራር የክልል ምክር ቤቶች የፌደሬሽን ምክር ቤት አባላትን የሚመርጡበት ሂደት ይቀጥል የሚል አማራጭ መቅረቡን ሰምተናል።
 
የሕገ መንግስት ተርጓሚ ፍርድ ቤት እንዲቋቋም የሚጠይቅ ምክረ ሀሳብ በአጀንዳው መካተቱን የገለጡልን ምንጮች፤ የፍርድ ቤቱ እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የኃላፊነት ድርሻ ክፍፍል ስምምነት ላይ ያልተደረሰበት አራተኛ ጉዳይ መሆኑን ጠቁመዋል። 
 
ፍርድ ቤቱ ያለ ፌደሬሽን ምክር ቤት ጣልቃ ገብነት “ሙሉ’ ስልጣን ይሰጠው የሚሉና፤ “በጉልህ” ጉዳዮች ዙሪያ ሕገ መንግስቱን የመተርጎም ስልጣን ለፌደሬሽን ምክር ቤት ይሰጥ የሚሉ ተመካካሪዎች መኖራቸውን አውቀናል። ሁለቱ ምክረ ሀሳቦች በአማራጭነት መቅረባቸውን የጠቆሙ ምንጮች፤ በጉዳዩ ዙሪያ ተጨማሪ ምክክር ይደረጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጠዋል።
 
አጠናቃሪዎች በሌሎቹ ጉዳዮች ስምምነት ላይ መደረሱን “በራሳቸው” በይነዋል የሚል ቅሬታ መኖሩንም የሰማን ሲሆን፤ ነሐሴ 05 ቀን፣ 2018 ዓ.ም የሥራ ቡድኑ ምክክር እንደሚቀጥል ምንጮች ነግረውናል።
 
በሥራ ቡድን ሰነድ ላይ አንፈርምም ያሉ ተመካካሪዎች የሥራ ቡድናቸው አጀንዳ ላይ የሚያደርጉትን ምክክር እያጠናቀቁ የሚገኙ የሌሎች ሥራ ቡድኖች ተመካካሪዎች፤ በፌደራል ከተሞች ጉዳይ ላይ እየተመካከረ የሚገኘው የሥራ ቡድን ውጤት ሳይታወቅ፤ በሥራ ቡድናቸው የምክረ ሀሳብ ሰነድ ላይ እንደማይፈርሙ መግለጣቸውን ሰምተናል። በሥራ ቡድን ደረጃ እየተደረገ የሚገኘውን ምክክር አስቀድመው የጀመሩ ቡድኖች፤ ምክረ ሀሳባቸውን አጠናቅረው ሲያጠናቅቁ፤ የአዲስ አበባን ጉዳይ እልባት እስኪያገኝ በምክረ ሀሳቡ ላይ ከመፈረም ለመቆጠብ የወሰኑ ተመካካሪዎች መኖራቸውን ምንጮች ነግረውናል። [ዋዜማ]"


አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።