"የሰይጣን ጆሮ ይደፈን።" አሜን። "#እንጨራረሳለን።" አንባሳደር ባጫ ደበሌ በኬኒያ የፈላስፊት ኢትዮጵያ ባለሙሉ አንባሳደር (ጄኒራል)

 

"የሰይጣን ጆሮ ይደፈን።" አሜን። "#እንጨራረሳለን።" አንባሳደር ባጫ ደበሌ በኬኒያ የፈላስፊት ኢትዮጵያ ባለሙሉ አንባሳደር (ጄኒራል)
 
"ስለዚህም ነገር ፆምን፥ ወደ
እግዚአብሔርም" ለመንን፤ እርሱም ተለመነን።"
(መጽሐፈ ዕዝራ ምዕራፍ ፰ ቁጥር ፳፫)
 
ምዕራፍ ፲፱።
 
“ጦርነት ከተጀመረ መንግሥታት ይለወጣሉ፤ ድንበሮች ይቀየራሉ”| BBC News አማርኛ
(በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ባጫ ደበሌ)
 
«ቢቢሲ በኢትዮጵያ እና በቀጣናዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ባጫ ደበሌ ጋር ቃለ መጠይቅ አድርጓል። የኢትዮጵያ አሁናዊ ሁኔታ፣ ከህወሓት ጋር ያለው ውዝግብ፣ የባሕር በር ጥያቄ እና የቀጠናዊ የጦርነት ስጋቶች በቃለ መጠይቁ ተዳሰዋል።»
 
ደንግጬ ነው ያዳመጥኩት። በሚሊተሪ፤ በባንክ፤ በመንበረ - መንግሥት፤ በአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ እጅግ ቁጥብ ነኝ። በሰባዕዊ መብት ጉዳይ፤ ወይንም በፖለቲካ ፓርቲ አደረጃጀት እና አመራር ነው ገፋ ያለ ጊዜየን የምመግበው። 
 
"#እንጨራረሳለን።" አንባሳደር ባጫ ደበሌ (ጄኒራል።)
 
ማነው ጨራሹ?
 
ማንስ ይሆን ተጨራሹ? እጅግ አስጨናቂ አገላለጽ ነው። "የሚጨራረሰው" የሰው ልጅ ነው። ኢትዮጵያዊው ሰው። ሰሞኑን ብልፄው የግሪን ሌጋሲውን ሂደት የመራበት ሞቶ "ተስፋን #እንትከል ነው።" ለሞቶ #ቅሸራ ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ A+ ናቸው። 
 
ሳይንስ እና ቴክኖሎጂም ሚኒስተር በነበሩበት ጊዜም "ከእርምጃ ወደ ሩጫ" የሚል ሞቶ እና ኮንፍረንስ ነበራቸው። ለትውልድ የሚሆን ቋሚ የሥራ ባህል የተከሉበት ተቋም ነበር ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ። በዘመነ ህወሃት ከማዳምጣቸው ጥቂት ሊቃናት አንዱም ነበሩ። የዛን ጊዜው ሰዋዊነት ትህትና ዛሬ የለም። በአዲስ ማንነት አዲስ ሰብዕና።
 
የሆነ ሆኖ "ተስፋ እንትከልን" ፊርማው ላይደርቅ በአናቱ ዘቅዝቆ የተከለው ደግሞ "የእንጨራረሳለን ሞርት" ነው። "የሰይጣን ጆሮ ይደፈን።" አሜን። የሰው ልጅ በተስፋ ስለተስፋ ይፈጠራል። በተስፋ ስለተስፋ ይኖራል። ተስፋ ከሌለ ቀጣዩ መኖሪያ #መውቲነት ይሆናል።
 
እኔ እንደማስበው የአንባሳደር ባጫ ደበሌ የጦር ኃይሎች ምክትል አዛዥነታቸውም የተነሳ #አይመስለኝም። ክፍት ነው። አንድ ነገር ቢፈጠር ወደ ቀደመው ቦታቸው ለመመለስ ይቻላል። አሁንም ቢሆን ከምክሩ ይለያሉ ብዬ አላስብም። ሁለቱን ቦታ አጣምረው እንደሚሠሩ ነው እኔ እማስበው።
 
#ህም። እምምም - ህም።
 
አንድ መንግሥት ስንብቱን በሙታን ሰማዕትነት ሊያቅድ ፈጽሞ አይገባም። ያን ያህል የተደራጀው እድሜ ጠገቡ ህወሃት እንኳን ለ109 ዓመት ያለመው ሥርዕወ ዓድዋ አገዛዙን እራሱ ቁጭ ብሎ፤ #ሁለት ድምጽ አግኝቶ ቢሸነፍም እራሱን አወዳድሩ በሰላም ነበር ሥልጣነ - መንበሩን ያስረከበው። ብልፄው ይህ ሁኔታ ቢገጥመው ፕላን A // B /// C /// D አዘጋጅቶ እየጠበቀ እንደሆን ፍንጭ ይሰጣል የአንባሳደሩ አገላለፅ። 
 
በበኽር የታቀደው ፕላን B ግን "መጨራረስ" የሚለው ይመስላል። ለምን? "መፍታት ሳለ መሞት" ይላሉ ባለቅኔወች ጎንደሮች። "እልፍ ሲሉ እልፍ ያለ" ይገኛልም ይላሉ ጎንደሬወቹ። ከሞት በመለስ መኖር የሚሰጠው ብዙ ደግ ነገር አለ እኮ። ልጆች ያላቸው ባለ ሥልጣናት ልጆቻቸውን ሲድሩ፤ ሲኩሉ እሚታ (አያት) ሲሆኑ እኮ ምድራዊ ገነት እኮ ነው። መኖር ትግሉ ቢበዛም ይጣፍጣል። ከመተላለቅ ማን ምን ያተርፋል? {}።
 
ከፍተኛ መኮነኑ በመኖራቸው መሰለኝ አንባሳደር የሆኑት። የግል የአኗኗር ዘይቤን ማዘመን ባይቻል ማስቀጠል ብልህነት ነው። ተትቶ ለሚኬድ አንድ ወንበር ተብሎ ይህን ያህል የህዝብ እልቂትን መመኜት ደፍሮ ማቀድ እና መወሰን ደግ አይደለም። አንባሳደርነት ደግሞ ቁጥብነቱ መሰለኝ ማንነቱ። የውትድርናው ሥልጣን ስላለ ሊሆን ይችላል መንፈሱ ጉልበት ያገኘው።
 
ትውልዱ የሚጠብቀው ይሁን የሚገነባው ሙሉ የኃላፊነት እና የተጠያቂነት ውህድ ማንነትን በእኛነት ሰውኛነት ሲጸድቅ በውስጥነት ነው። ለድምጽ አልባወቹ የኢትዮጵያ እናቶች ዕንባስ ማን ባለቤት ይሁነው???
 
አንድ የህዝብ ኃላፊነት እና ተጠያቂነት ያለው አካል ወይንም ሰብ ……… ሊሆን የሚገባው አቅጣጫው፤ በዚህ በዚህ ጠንክረናል፤ በዚህኛው ደክመናል፤ ጥንካሬያችን ስናስቀጥል ይህን ለህዝባችን እና ለአገራችን እናሳካለን። 
 
የደከምንበትን ደግሞ በዚህ መልክ አስተካክለን የመረጠን ህዝብ ፍላጎት እናሟላለን። በሥራ ስምሪት፤ በአፈፃጸም ሂደት፤ ህግ በማስከበር ሁነት ወዘተ ህዝባችን ያስከፋንበትን እናስተካክላለን።
 
የኑሮ ውድነቱ፤ የአስተዳደር በደል እንዳለ እናውቃለን ይህን እናርማለን። ከፋን ያሉ ወገኖቻችን ልጆቻችን ጋርም ተቀራርበን ተነጋግረን ችግሩን ለመፍታት እንጥራለን፤ የታሰሩ፤ የታፈኑ ወገኖቻችን ጉዳይ አተኩረን እንሰራለን። የሰላም እጦትን በሚመለከትም ችግሩን አጥርተን መፍትሄ እንሰጣለን ሊባል ሲገባ ዋዮላችሁ ዓይነት ሟርት ገዳይ ሃሳብ ነው። ድጋፋችሁም ጸሎታችሁም እንዳይለየን አክብረን እንጠይቃለን። ጨዋ፤ የተረጋጋ፤ ታጋሽ፤ ፈርኃ እግዚአብሄር እና ፈርኃ ያለው ህዝብ አለን። 
 
#መጨካከኑ እኮ ተኖረበት።
 
ሁሉም - ተሞክሯል። ሰው ተገድሎ ተዘቅዝቆ ተሰቅሎ ህዝብ ተሰብስቦ ሰናዩን ሼር ሲያደርግ እኮ አየን። ተገድሎ መቃጠል። ታስሮ መቃጠል። ህፃናት ተደፍረው መገደል፤ የሰው ልጅ የመዳህኒት መፈተኛ መሆን ምን ያልታዬ፤ ምን ያልተደመጠ ነገር አለና።
 
ፈላስፊት ኢትዮጵያ በራሱ ጊዜ የሚተጋ ሠራዊት አላት። ሳይለንት ማጆሪቲ የሚባል። እሱ ነው ከፈጣሪ ጋር #ማስትሽ ሆኖ አያይዞ በየዘመኑ የሚነሱ ወጀቦችን #ረብ እያደረገ የኢትዮጵያ ባላ እና ወጋግራ ሆኖ ዘብ አደር የሚሆነው።
 
እንጅማ - የሽብሩ ቡፌ፤ የግድያው ዓይነት፤ የግለቱ ጣሬያ፤ የእገታው መጠነ ሰፊነት፤ የውድመቱ ብዛት፤ የቃጠሎው ላንቃ፤ የእላፊ ንግግሩ ግዝፈት፤ የሰው ልጅ ስወራው፤ የሰላሙ መጥፋት፤ የሃይማኖት ፈተናው በተለይ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ፤ የመስቃው መጎማዘዝ፤ የጫናው ማየል ባለቤት የሌላቸው የወንጀል ዓይነቶች እኮ ተንሰራፍቶ ተለምዷል። 
 
ሃይማኖት ባላት አገር፤ በህገ መንግሥት በተፃፈ ባልተፃፈም ይትባህል በምትመራ በሳይንቲስቷ ኢትዮጵያ ያልሆነ ነገር የለም። የከተሞች ነዲድ፤ ምንም የማያውቁት የእንሰሳት ቃጠሎ፤ የትንፋሽ ማደሪያው የገበሬ ምርት በማሳው አመድነት፤ የመፈናቀሉ መራራ ገጠመኝ ……… የሙሁራኑ ባለሥልጣናት ህግ ተላላፊ ንግግር …… 
 
ሰበር፤ የሰበር ሰበር ዜና እኮ የተጀመረው ከመጋቢት 18/2010 ዓ.ም ጀምሮ እኮ ነው። ዜናውም እራሱ ሞራልን፤ ተስፋን፤ ትውልድን #እንኩት የሚያደርግ ሰባሪ እኮ ነው። አይደለም - ድርጊቱ። 
 
ሁልጊዜ ስለሽግር መንግሥት ሲነገር የምለው እኔ ጠቅላይ ሚር አብይን ማሳተፍ በቅድሚያ ያስፈልጋል እላለሁኝ። ምክንያቴ በጣም እምፈራው ለሱዳን እና ለአልሸባብ ኢትዮጵያ እንዳትሸለም ትልቅ ስጋት ስለአለኝም ነው። 
 
ለአንድ ወንበር የሰው ማገዶ። የኢትዮጵያ እናቶች ማህጸን ቄራነት። ሰውኛ፤ አገርኛ፤ ተፈጥሮኛ መንፈስን የማወራረስ ሂደት ለመጀመር ዛሬ ካልተደፈረ ቀጠሮው ለመቼ ይሆን????
 
#የደቡብ አፍሪካ ስምምነት እና ስኬቱ።
 
"ለሞራል" ሲባል አልተፈጸመም። ግን የትኛውም ህግ፤ የትኛውም የህግ ድንጋጌ ከሞራል በታች ነው ወይንስ ላይ?
 
ኬኒያ ላይ በነበረው የብልፄው እና የህወሃት የጫጉላ ጊዜ አንባሳደሩም ባጫ ደበሌ በአካል ነበሩ። ምን አልባትም ሞደሬተር ሊሆኑ ይችላሉ። የአማራ ተወካይ ግን አለነበረም።
 
ለመሆኑ ምን ተነጋግረው ነበር? ምን ---- አሳኩ???? እራሳቸውን ይጠይቁት - አንባሳደሩ። ወይንም ፓርቲያቸውን አቤቱ ብልጽግናን ይጠይቁ። ይህ ትእዛዝ አይደለም። በትህትና ነው እማሳስበው። 
 
እኔ እምለው የማስፈጸም አቅም #ማነስ እንጂ ለህወሃት ሞራል አይደለም። በዛ ሁሉ መሳሪያ ሲቀጣቀጥ የነበረ የአገር ልጅነት ያን ጊዜ ሞራል አልታሰበለት ይሆን?
 
ሌላው የአማራ ክልል ትጥቅ እንዲፈታ ሲጠየቅ፤ ለአማራ የሞራል ጉዳይ #እንጀራ አባት ነበርን ብልፄው???? አንዱ ልጅ አንዱ እንጀራ ልጅ፤ አንዱ የቤት ሌላው የእዳሪ ልጅ???
 
"#ትግራይን ለመያዝ እንችል ነበር። ግን ………"
"ተረጋግተው እንዲያስቡ ብለን ነው"። አይመስለኝም። የዲፕሎማሲው ጫና ነው ይህን እንድትፈጽሙ ያስገደዳችሁ። የዛሬን አያድርገውና በዛን ጊዜ የዲፕሎማሲው ማህበረሰብ ተጎጂ ህወሃት እንደሆነ ብቻ ነበር የሚያምነው። ዲፕሎማሲው ህውሃት በአንድም በሌላም በህይወት #እንዲቆዬ ይፈለግ ስለነበር። መንበረ መንግሥቱን እንዲመራም እጩ ነበር። ይህን ያስገለበጠው ፈጣሪ //
 
አላህ ሁለተኛ ታምር ሠርቶ ነበር። እጩ ጠቅላይ ሚር እኮ ተሰይሞ ነበር። የሃሳብ መዋቅርም ተዘርግቶ ነበር።
በተመድም ዋናው አጀንዳ የህወሃት ዘገባ ነበር የሚደመጠው። ያን ጊዜ ህወሃትን ስለማዳን እንጂ ህወሃት ስለበደለው በደል ትንፍሽ የሚል አልነበረም። እራሳቸው ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ የዲፕሎማሲው ማህበረሰብን ከህውሃት መሪወች ጋር እንጂ ከአማራ፤ ከአፋር መሪወች ጋር እንዲነጋገሩ ምንም ሁኔታ አያመቻቹም ነበር። ይህን ለምን ያደርጉ እንደ ነበር የሚያውቁት እሳቸው ብቻ ናቸው። 
 
በሌላ በኩል ግን ገፍቶ መከላከያ ቢሄድ የቤርሙዳ ትርያንግሉ ህወሃት እንደ ለመደበት አዲሱን #እስክሪፕት አዘጋጅቶ ይፈጽም ነበር። የደረቅ ወንጀለኞችን ከእስስር ለቆ ያን መከረኛ #የመቀሌን ህዝብ ቁም ስቅሉን ያሳይ ነበር። ያን ሻብያ - ብልጽግና - የአማራ ኃይል ፈጸመው ብሎ የሆሊውድ ትወናውን ያስኬደው ነበር። 
 
በዛን ጊዜ ለብልፄውም የውጭ ባለ አቅሞችን ጫናውም አይቻል ነበር። የመቀሌ ሰቆቃውም የከፋ ይሆን ነበር። ፈጣሪ በዚህም ታዕምር ሠርቷል። ስለሆነም ብልፄው ሂደቱ እየቀናው የነበረ ቢሆንም፤ #ተግ ብሎ አስቦ መቀሌን ለመያዝ ሙከራ አለመደረጉ ጫናው የዲፕሎማሲ ማህበረሰቡ ቢሆንም፤ ያን ሳይጥስ እራሱን ከእርምጃ መቆጠቡ ለእኔ እራስን የማትረፍ #ብልህ ውሳኔ ነበር ብዬ አምናለሁኝ።
 
ህወሃት እና ትራጀዲ ተዋህደው የተፈጠሩ ናቸው። አዲስ ትራጀዲ ነበር የሚፈጸመው ህወሃትሻ የሚፈጽመው። መቀሌን ድንግል ጠበቀች። ተመስገን ነው። 
 
#ነገረ ጥምዶ።
 
ለአንባሳደር ባጫ ደበሌ ከውስጣቸው የገባ አመክንዮ ሆኗል። ይህ በጣም የገረመኝ ክፍል ነው። ከህወሃትም፤ ከኦላም ፋኖን ውስጣቸው እንደምን እንደሚያው እንቅጩን አንባሳደር ባጫ ነግረውናል።
 
ዶክተር ዮናስ አበክረው የሚገልጹት የኢኮኖሚ ችግሩ በኢትዮጵያ ለውጥ እንዲኖር አስገዳጅ ሁኔታ እንደ ሆነ ይናገራሉ፤ ይጽፋሉ፤ ያስተምራሉ። እኔ ደግሞ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ያለው ግልጽ እና ስውር መከራ የእዮርን ዋና የህሊና በር ሊያንኳኳ፤ ሊያስከፍትም ከቻለ ከባዱ ፈተና ከእግዜሩ የሚመጣው ቅጣት ይሆናል ብዬ እሰጋለሁኝ።
 
በነገራችን ላይ ዘንድሮ ዝናብ በጊዜው ያልመጣላቸው አካባቢወች እንዳሉ ሰምቻለሁኝ። ይህ ከባዱ ፈተና ነው። ሌላው ዝናብ ባለበት ቦታም ጦርነቱ፤ ስጋቱ፤ ሃዘኑም ሌላው ሰንሰለታማ ፈተና ነው። 
 
ቀጣዩ አመት ከዓለም ካለው ውጥረታዊ ጫና ጋር ኢትዮጵያ ምን እና ምን እንደምትሆን ፈጣሪ ይወቀው። ይህን ሁለገብ አስፈሪ ጊዜ ተስማምተን፤ ተፈቃቅደንም መወጣት ብንችል ማን እንደ እኛ ጌታ በሆነ ተበር?
 
#ነገረ ኤርትራ።
 
ህወሃት ሥልጣኑን ከለቀቀ በኋላ አሁን ከሆነ በዚህ ዙሪያ ጽፌ አላውቅም። ሻብያ ይሁን ህወሃት ጉዟቸውን እያዬሁ ነው ያደኩት። አይጠፋኝም እንደ ማለት። የሆነ ሆኖ የኬኒያ ባለሙሉ አንባሳደር ባጫ ደበሌ (በጄኒራል ማዕረግ) ስለ ኤርትራ የገለጹበት ሐረግ እንደ አንድ ዲፕሎማት ቁጥብነት ያነሰው ይመስለኛል። 
 
አገላለጹ ከአንድ የዲፕሎማሲ ባልደረባ የሚጠበቅ ነው ብዬ አላምንም። እሳቸው መደበኛ የብልጽግና ፓርቲ ሠራተኛ አይደሉም። ቢሆኑ እንኳን እራስን፤ ውስጥን #ፏ ፍንትው አድርጎ የሚገልጽን አመክንዮ በድፍረት መግለጽ አትራፊ መንገድ አይደለም። "ሆድ ከአገር ይሰፋል" የሚባለው እኮ ለዚህም አይደል???? "#ሙያ በልብ ይለዋል" የጎንደር ባለቅኔ።
 
"#ገንዘብ ከፈለጉ መንግሥት ጋር ተነጋግረው ይስጣቸው።"
 
ጠቅላላ የፖለቲካ ድርጅት የሚደራጅበትን ዓላማ እና ግብ የናደ ሃሳብ ነው። የፖለቲካ ድርጅት ይሁን ንቅናቄ፤ ንቅናቄ ይሁን የነፃነት ትግል፤ የነፂነት ትግል የህልውና የቢዝነስ ተርቲመኛ ሆኖ ሲቀርብ እጅግ ያስደነግጣል። 
 
ከአንድ የፖለቲካ ፍላጎት ካለው ተቋም ጋር በቋሚነት ስለአልሠሩ ሊሆን ይችል? ምን አገናኛው ገንዘብ እና የነፃነት ትግል? ኢትዮጵያስ ሸቀጥ ናትን፤ እንደ ፍራንክ የምትዘረዘር፤ የምትመነዘር የዶላር ዋጋ ከፍ እና ዝቅ ባለ ቁጥር መንበረ መንግሥቷን ለጭረታ የምታቀርብ? እንዴት ሃሳቡ መጣላቸው? 
 
ቀላሉ መንገድ ተቀራርበው መነጋገር፤ መደራደር፤ መቀበል እና መስጠትን ማመን ነው። ከፋኝ ያሉ ታጣቂ ኃይሎችን አቃሎ ከማየት አቅርቦ፤ አክብሮ፤ ማነጋገር። አገራዊ ምክክሩ እየተካሄደ አይደል። ገና ስድስተኛ ዓመቱ ያልሞላ ብልጽግና አገር እየመራ፤ አፍሪካን እየመራ፤ ኢጋድን እየመራ አዲስ አበባን በቁሟ ካልወረስ ብሎ በሰጨኝ እያለ ያለው በገንዘብ እንደራደር ዓይነት ይሆን????
 
የአንድ የፖለቲካ ድርጅት ይሁን ንቅናቄ፤ የማንነት ተጋድሎ፤ የህልውና ተጋድሎ በፖለቲካዊ መፍትሄ እንጂ በገብያ ህግ አይተዳደርም። የፖለቲካ ድርጅት የባንክ ተቋምም አይደለም። ምን አልባት ቃለ ምልልሱን የሰጡበት ቀን የሳቸው የነበረ አይመስልም። የእመቤቴን ሱባኤ በጥሞና ፈጽመው ቢቀርቡ በብዙ የተሻለ አሰባሳቢ፤ አቀራራቢ፤ ቁጥብ፤ ተስፋን የሚኮተኩት ሊሆን በቻለ ነበር።
 
#የቢሮው ባዶነት።
 
ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ወንበሩ ባዶ ነው ብዬ ጽፌ ነበር። ህልም አይቼ ስለነበር። ብሎጌ ላይም ሊኖር ይችላል። ሌላ ቀን ወንበሩ ጠርዝ ላይ ሆኖ በህልሜ በድጋሜ አየሁኝ። ይህንንም ፃፍኩኝ። ከሁሉም በፊት ብረት ሳጥን ቁልፍ የሌለው የቀድሞው ጠቅላይ ሚር ኃይለማርያም ደስአለኝ ከተቀበረበት ሲያወጡ አየሁኝ። መክፈቻ ግን አልነበረውም። ሁሉንም ብሎጌ ላይ ጽፌዋለሁኝ።
 
ጠቅላይ ሚር አብይ የመስክ ሠራተኛ እንጂ የቢሮ ሠራተኛ አይደሉም። ምን አልባት "ቢሮው ባዶ ነው፤ ውሰዱ ብትባሉም አትደፍሩትም" ያሉት አንባሳደሩ ከዚህ አንፃር ይሆን አልኩኝ።
 
ጠቅላላ ቃለ ምልልሱ በራስ የመተማመን አቅሙ፤ የውስጥ የመረጋጋት ሁኔታ፤ ብልፄው በሰጠው ተስፋ ልክ የማስቀጠል ሁነትን፤ ኃላፊነት እና ተጠያቂነትን በመወጣት እረገድ ወዘተ በሚመለከት ብልፄው ያለበት ተጨባጭ ሁኔታን ይጠቋቁማል።
 
የአንባሳደር ባጫ ደበሌን በስሱ የገለጹትን የሰላምን ምኞታቸውን ወድጄዋለሁኝ። ግን ሁሉም አይቅርብኝ ብሎ ሰላም አይመጣም። የጠበቀውን - በማላላት፤ የጎደለውን - በመሙላት። የተሰበረውን ወጌሻ በመሆን። የናቁትን አክብሮት በመስጠት። ያጠረውን በመደጎም፤ ያራቁትን በማቅረብ፤ የተዘጋጋውን በር - በመከፋፈት… የዕንባማ ድምፆችን በመስማት።
 
የተከፋን በማጽናናት። ይቅርታን በመድፈር፤ ያዘነን አይዟችሁን - ተግቶ በመመገብ። የፖለቲካ እስረኛን በመፍታት፥ የጎደለበትን መኖር ያስመረረውን ህዝብ ቢያንስ የመናገር፤ የመፃፍ፤ የመደራጀት መብቱን በመጠበቅ። የኢትዮጵያን ህዝብ በሙሉ የእኔ ብሎ በማቅረብ ወዘተ ……… የተሻለ ጎዳና ይመስለኛል። 
 
ከመኮንኖች ጋር በተያያዘ ሃሳብ መስጠት አልፈልግም። ተመችቶኝም አይደለም የፃፍኩት። እኔ በተስፋ ላይ ትጉህ ነኝ። በትውልድ ጉዳይም እንዲሁ። ከፊደል ተን፤ ከሥም ተስፋን፤ ከእዮር ሥጦታወች ተስፋን እጅግ እወደዋለሁኝ። 
 
የመጀመሪያ የአዋቂወች የግጥም መድብሌ "ተስፋ" የመጀመሪያው የጸጋዬ ድህረ ገጽ ላይ ለልጆች "የሎሬት ተስፋ፤" ስድስተኛው መጸሐፌ "የተስፋ በር" ከአንድ የኮሚኒቲ ራዲዮ ፕሮግራም ጋራ አብሬ ሥሰራም ሥያሜውን ከባቢሎን ሥሙ ወደ ተስፋ እንዲሆን ሃሳብ ያቀረብኩት በተስፋ ላይ ተስፈኛ ስለሆንኩ ነው። በጸጋዬ ራዲዮም ለልጆች የተስፋ ብርሃን የሚል የ15 ደቂቃ ፕሮግራም ነበረኝ። 
 
ለተስፋ እሳሳለታለሁኝ። የአንባሳደር ባጫ ደበሌ ንግግር "#እንጨራረሳለን" ተስፋን ነቃይ ስለሆነ ነው የፃፍኩት። በሌላ በኩል የፖለቲካ ድርጅት ሸቀጥ አይደለም። በሰው ይደራጃል። ስለ ሰው ይጨነቃል። የሰውን ልጅ ያደራጃል - ይመራል። መደበኛ ሥራዬ ማደራጀት ነው የነበረው። እና ሰውን አደራጅቶ የሚንቀሳቀስ ድርጅትን ሰማዕትነቱን በገንዘብ እንዋዋለው የሚል አመክንዮ ከባድ ዕሳቤ ነው። 
 
ገንዘብ የሚፈልጉ ከሆነ ከመንግሥት ጋር ተነጋግረው ገንዘብ ይስጣቸው። ብልፄውን ማን ብቸኛ የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ አዛዥ አደረገው። የኢትዮጵያ ሁለመና የሁሉም ነውና። አንዱ ገዢ የመንፈስ፤ የጥንካሬ፤ የብርታት፤ ሌላው ደግሞ በገንዘብ ምርኮ ተሻጭ???
በተጨማሪም የግንቦቱ ምርጫ ሞቶ "ብልጽግና መምረጥ ማለት ነገን መምረጥ ማለት ነው።" የሚል ፓርቲ " #እንጨራረሳለን " መንግሥታችን ማስቀጠል ከተሳነን ፬ኪሎን አትሰቡት ዓይነት ተጫኝ፤ ጨቋኝ የስጋት ቧንቧ ውሃ የሆነ ንግግር ለምን አስፈለገ?
"ህዝብ መርጦናል" ያለ ፓርቲ ምን ---- አሰጋው? ኢትዮጵያ የከበደችን ለሁላችን ነው የምለው ለዚህ ነው። ማንነቷን፤ ኦርጋኒክ ተፈጥሯዋን በፍጹም አናውቀውም ወይንም ////??? አልገባችንም።
 
ዝም ብሎ የሚናድ፤ እንደ አንፖል ስብርብር የሚል ማንነት የላትም --- እናታችን። የፈጠራት አምላክ አኑሯታል። ወደፊትም ያኖራታል።
የማከብራችሁ የአገሬ ልጆች እንዴት ናችሁ። እኔ ደህና ነኝ አምላኬ ክብሩ ይስፋ።
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
09/08/026.
 
ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር ነው።
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።